ባሎች፣ ፍቅር በማሳየት ረገድ ክርስቶስን ምሰሉ!
ባሎች፣ ፍቅር በማሳየት ረገድ ክርስቶስን ምሰሉ!
ኢየሱስ በምድር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ለታማኝ ሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እየሰጠኋችሁ ነው፤ ልክ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐ. 13:34, 35) በእርግጥም እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርስ መዋደድ አለባቸው።
ሐዋርያው ጳውሎስ ከክርስቶስ ተከታዮች መካከል ባሎችን ለይቶ በመጥቀስ የሚከተለውን ምክር ጽፏል፦ “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ለእሱ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌ. 5:25) አንድ ክርስቲያን ባል በተለይ ሚስቱ ራሷን የወሰነች የይሖዋ አገልጋይ ከሆነች ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በትዳሩ ውስጥ ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው?
ክርስቶስ ለጉባኤው ፍቅር ነበረው
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ምክንያቱም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም ሰው የለም፤ ከዚህ ይልቅ ይመግበዋል እንዲሁም ይሳሳለታል፤ ክርስቶስም ለጉባኤው ያደረገው እንደዚሁ ነው።” (ኤፌ. 5:28, 29) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ፍቅር የነበረው ከመሆኑም ሌላ ከፍ አድርጎ ይመለከታቸው ነበር። በእርግጥም ኢየሱስ ተከታዮቹን በጣም ይወዳቸው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ኢየሱስ በገርነትና በደግነት ይዟቸዋል። ኢየሱስ “[ጉባኤው] ውበቱን እንደጠበቀ ለራሱ ለማቅረብ” ፍላጎት ስለነበረው በደቀ መዛሙርቱ መልካም ባሕርያት ላይ ያተኩር ነበር።—ኤፌ. 5:27
ክርስቶስ ለጉባኤው ያለውን ፍቅር እንደገለጸ ሁሉ አንድ ባልም በቃልም ሆነ በድርጊት የትዳር ጓደኛውን እንደሚወድ ማሳየት ይኖርበታል። አንዲት ሚስት ባሏ እንደሚወዳት ሁልጊዜ የሚገልጽላት ከሆነ እንደምትፈቀር የሚሰማት ከመሆኑም ሌላ ደስተኛ ትሆናለች። በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት ሴት በቁሳዊ ረገድ ሁሉ ነገር የተሟላላት ብትሆንም የትዳር ጓደኛዋ ችላ የሚላት ወይም ትኩረት የማይሰጣት ከሆነ ደስታ የራቃት ልትሆን ትችላለች።
ታዲያ አንድ ባል ሚስቱን እንደሚወዳት እንዴት ማሳየት ይችላል? ከሌሎች ጋር በሚሆንበት ጊዜ አክብሮት በተሞላበት መንገድ ከሰዎች ጋር ያስተዋውቃታል፤ እንዲሁም ለምትሰጠው ድጋፍ በግልጽ ያመሰግናታል። ቤተሰቡ ባገኘው ስኬት ሚስቱ የተጫወተችው ሚና ካለ ይህን ለሌሎች ከመግለጽ ወደኋላ አይልም። ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜም እንደሚወዳት እንዲሰማት ያደርጋል። በእጅ መዳበስ፣ ፈገግታ ማሳየት፣ ማቀፍና አድናቆትን መግለጽ ትንንሽ ነገሮች ሊመስሉ ቢችሉም እንደዚህ ያሉ ነገሮች ለአንዲት ሴት ትልቅ ትርጉም አላቸው።
“‘ወንድሞች’ ብሎ ለመጥራት አያፍርም”
ኢየሱስ ክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮቹን ‘“ወንድሞች” ብሎ ለመጥራት አላፈረም።’ (ዕብ. 2:11, 12, 17) አንተም ክርስቲያን ባል ከሆንክ የትዳር ጓደኛህ፣ ሚስትህ ብቻ ሳትሆን ክርስቲያን እህትህም እንደሆነች አስታውስ። የተጠመቀችው አንተን ከማግባቷ በፊትም ሆነ በኋላ ለይሖዋ የገባችው ቃል ከጋብቻ ቃል ኪዳኗ የበለጠ ቦታ አለው። ባለቤትህ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ሐሳብ ለመስጠት እጇን ስታወጣ ስብሰባውን የሚመራው ወንድም “እህት እገሊት” ብሎ ይጠራታል። በመንግሥት አዳራሹ ብቻ ሳይሆን ቤት በምትሆኑበት ጊዜም እህትህ እንደሆነች ማስታወስ ይገባሃል። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በደግነትና በአክብሮት ልትይዛት እንደሚገባህ ሁሉ ቤታችሁ ስትሆኑም እንደዚሁ ማድረግህ አስፈላጊ ነው።
በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት ካለህ አንዳንድ ጊዜ የጉባኤና የቤተሰብ ኃላፊነትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል። በሽማግሌዎችና በጉባኤ አገልጋዮች በኩል ጥሩ የትብብር መንፈስ መኖሩና ሌሎች
ወንድሞች አንዳንድ የጉባኤ ሥራዎችን እንዲሸፍኑ ሥልጠና ማግኘታቸው ከሁሉ በላይ የአንተ እገዛ ከሚያስፈልጋት እህት ማለትም ከሚስትህ ጋር የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ እንድትችል ይረዳሃል። በጉባኤ ውስጥ አንተ እንድታከናውን የተሰጠህን ሥራ ማከናወን የሚችሉ በርካታ ወንድሞች እንዳሉ አስታውስ፤ ሆኖም ከሚስትህ ጋር በትዳር የተቆራኘኸው ወንድም አንተ ብቻ ነህ።ከዚህም በተጨማሪ የሚስትህ ራስ ነህ። መጽሐፍ ቅዱስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ” እንደሆነ ይናገራል። (1 ቆሮ. 11:3) ታዲያ ይህን ሥልጣንህን ልትጠቀምበት የሚገባው እንዴት ነው? ከላይ ያለውን ጥቅስ ነጋ ጠባ በመጥቀስና መከበር እንደምትፈልግ በመናገር ሳይሆን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። የራስነት ሥልጣንህን በተገቢው መንገድ እንድትጠቀምበት የሚረዳህ ቁልፍ ነገር ሚስትህን የምትይዝበትን መንገድ በተመለከተ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ መከተልህ ነው።—1 ጴጥ. 2:21
“ወዳጆቼ ናችሁ”
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወዳጆቼ በማለት ጠርቷቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ከእንግዲህ ባሪያዎች ብዬ አልጠራችሁም፤ ምክንያቱም ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን ነገር አያውቅም። እኔ ግን ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ።” (ዮሐ. 15:14, 15) ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በነፃነት ይነጋገሩ ነበር፤ እንዲሁም አንድ ላይ ሆነው የተለያዩ ነገሮችን ይሠሩ ነበር። “ኢየሱስ እና ደቀ መዛሙርቱ” በቃና በተዘጋጀው የሠርግ ድግስ ላይ አብረው እንዲገኙ ተጋብዘው ነበር። (ዮሐ. 2:2) እንደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ያሉ አዘውትረው የሚሄዱባቸው ቦታዎች ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚያ ይገናኝ” እንደነበር ይናገራል።—ዮሐ. 18:2
አንዲት ሚስት የባሏ የቅርብ ጓደኛ እሷ እንደሆነች ሊሰማት ይገባል። ባልና ሚስት አስደሳች የሆኑ እንቅስቃሴዎችን አንድ ላይ ማድረጋቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! አምላክን አብራችሁ አገልግሉ። መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ አጥኑ። በእግር በመንሸራሸር፣ በማውራት እንዲሁም አብራችሁ በመመገብ አንድ ላይ ጊዜ አሳልፉ። ባልና ሚስት ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጓደኛሞችም ሁኑ።
“እስከ መጨረሻው ወደዳቸው”
ኢየሱስ ‘ደቀ መዛሙርቱን እስከ መጨረሻው ወዷቸዋል።’ (ዮሐ. 13:1) አንዳንድ ባሎች በዚህ ረገድ ክርስቶስን ሳይመስሉ ቀርተዋል። እነዚህ ባሎች ከሚስታቸው በዕድሜ ያነሰች ሴት ለማግባት ስለፈለጉ ሳይሆን አይቀርም ‘የወጣትነት ሚስታቸውን’ እስከ መተው ደርሰዋል።—ሚል. 2:14, 15
እንደ ወንድም ቪሊ ያሉ ሌሎች ደግሞ የክርስቶስን ምሳሌ ተከትለዋል። የወንድም ቪሊ ባለቤት ጤንነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በመሄዱ ለበርካታ ዓመታት ያልተቋረጠ እንክብካቤ አስፈልጓቸዋል። ወንድም ቪሊ ስለ ሁኔታው ምን እንደሚሰማቸው ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ሁልጊዜም ባለቤቴ ከአምላክ የተሰጠችኝ ስጦታ እንደሆነች ስለሚሰማኝ ውድ እንደሆነች አድርጌ እመለከታታለሁ። ደግሞም ከ60 ዓመታት በፊት፣ በጥሩም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜያት ልንከባከባት ቃል ገብቻለሁ። ያን ጊዜ የገባሁትን ቃል ፈጽሞ አልረሳም።”
ክርስቲያን ባል ከሆንክ ፍቅር በማሳየት ረገድ ክርስቶስን ምሰል። አምላክን የምትፈራዋን ሚስትህን እንዲሁም እህትህንና ጓደኛህን ውደድ።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሚስትህ የቅርብ ጓደኛህ ነች?
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ሚስትህን መውደድህን ቀጥል’