በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቶስን መከተል ያለብን ለምንድን ነው?

ክርስቶስን መከተል ያለብን ለምንድን ነው?

ክርስቶስን መከተል ያለብን ለምንድን ነው?

“ሊከተለኝ የሚፈልግ ካለ ራሱን ይካድ፣ . . . ያለማቋረጥም ይከተለኝ።”—ሉቃስ 9:23

1, 2. ክርስቶስን መከተል ያለብን ለምን እንደሆነ መመርመራችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

ይሖዋ በምድር ዙሪያ እሱን ለማምለክ ከተሰበሰቡት በርካታ አገልጋዮቹ መካከል አዲሶችንና ልጆችን ሲመለከት በጣም እንደሚደሰት ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችሁንና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትራችሁ መገኘታችሁን ስትቀጥሉ እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ ስለሚገኘው ሕይወት ሰጪ እውነት ያላችሁ እውቀት እያደገ ሲሄድ ኢየሱስ ያቀረበውን የሚከተለውን ግብዣ በቁም ነገር ልታስቡበት ይገባል፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ካለ ራሱን ይካድ፣ የራሱን የመከራ እንጨት በየዕለቱ ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።” (ሉቃስ 9:23) እዚህ ላይ ኢየሱስ ራስን መካድና የእሱ ተከታይ መሆን፣ በራሳችሁ ፍላጎት ተነሳስታችሁ ልታደርጉት የሚገባ ነገር እንደሆነ ገልጿል። በመሆኑም ‘መሲሑን’ ማለትም ክርስቶስን መከተል ያለብን ለምን እንደሆነ መመርመራችን ጠቃሚ ነው።—ማቴ. 16:13-16

2 የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በመከተል ላይ የምንገኘውን ሰዎች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እኛም ብንሆን ‘ይህንኑ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማድረጋችንን እንድንቀጥል’ ምክር ተሰጥቶናል። (1 ተሰ. 4:1, 2) በእውነት መንገድ መጓዝ የጀመርነው በቅርቡም ይሁን ከአሥርተ ዓመታት በፊት ክርስቶስን ለመከተል የመረጥንባቸውን ምክንያቶች መለስ ብለን ማሰባችን፣ ከጳውሎስ ምክር ጋር በመስማማት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ክርስቶስን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንድንከተል ይረዳናል። ክርስቶስን ለመከተል የሚያነሳሱንን አምስት ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።

ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር ያስችለናል

3. ስለ ይሖዋ ማወቅ የምንችለው በየትኞቹ ሁለት መንገዶች ነው?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ “በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ” ለአቴና ሰዎች ንግግር ባቀረበበት ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “[አምላክ] የተወሰኑትን ዘመናትና የሰው ልጆች የሚኖሩበትንም ድንበር ደነገገ፤ ይህንም ያደረገው ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና አጥብቀው በመሻት እንዲያገኙት ብሎ ነው፤ እንዲህ ሲባል ግን እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ነው ማለት አይደለም።” (ሥራ 17:22, 26, 27) አምላክን መፈለግና ስለ እሱ በሚገባ ማወቅ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች በማየትና በፈጠራቸው ነገሮች ላይ በአድናቆት በማሰላሰል ስለ ባሕርያቱም ሆነ ስለ ችሎታዎቹ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (ሮም 1:20) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ራሱ ብዙ ነገር ገልጾልናል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ‘በሠራቸው ነገሮች’ ላይ ይበልጥ ‘ባሰላሰልን’ መጠን ይሖዋን የዚያኑ ያህል እያወቅነው እንሄዳለን።—መዝ. 77:12

4. ክርስቶስን መከተላችን ከይሖዋ ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ የሚረዳን እንዴት ነው?

4 ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የሚያስችለው የተሻለው መንገድ ክርስቶስን መከተል ነው። ኢየሱስ “ዓለም ከመመሥረቱ በፊት” በአባቱ ዘንድ ስለነበረው ክብር እስቲ አስብ! (ዮሐ. 17:5) ኢየሱስ “ከአምላክ ፍጥረት የመጀመሪያ” ነው። (ራእይ 3:14) “የፍጥረት ሁሉ በኩር” እንደመሆኑ መጠን ከአባቱ ከይሖዋ ጋር ሕልቆ መሳፍርት ለሌለው ዘመን በሰማይ ኖሯል። ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከአባቱ ጋር ረጅም ዘመን ያሳለፈ ከመሆኑም በላይ የአምላክ የቅርብ ወዳጅ ነበር። ሁሉን ቻይ ከሆነው ፈጣሪ ጋር በደስታ ይሠራ የነበረ ሲሆን ይህ ደግሞ በመካከላቸው ከሁሉ የላቀ የተቀራረበ ዝምድና እንዲኖር አድርጓል። ኢየሱስ፣ አባቱ የተለያዩ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ በመመልከት ይሖዋ ምን ዓይነት ስሜቶችና ባሕርያት እንዳሉት በማስተዋል ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ ስለ አባቱ ያወቃቸው ነገሮች በሙሉ ከራሱ ጋር እንዲዋሃዱና የሕይወቱ ክፍል እንዲሆኑ አድርጓል። ታዛዥ የሆነው ይህ የአምላክ ልጅ አባቱን በጣም ከመምሰሉ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ “የማይታየው አምላክ አምሳል” በማለት ይጠራዋል። (ቆላ. 1:15) ክርስቶስን በቅርብ በመከተል ከይሖዋ ጋር የበለጠ መቀራረብ እንችላለን።

ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንድንመስል ይረዳናል

5. ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንድንመስል ምን ሊረዳን ይችላል? እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

5 የተፈጠርነው በአምላክ ‘መልክና አምሳል’ ስለሆነ አምላካዊ ባሕርያትን የማንጸባረቅ ችሎታ አለን። (ዘፍ 1:26) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “የተወደዳችሁ ልጆች በመሆን አምላክን የምትኮርጁ ሁኑ” በማለት መክሯቸዋል። (ኤፌ. 5:1) ክርስቶስን መከተላችን በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን መምሰል እንድንችል ይረዳናል። ምክንያቱም ኢየሱስ ከማንም በተሻለ ሁኔታ የአምላክን አስተሳሰብ፣ ስሜትና ባሕርይ ያንጸባረቀ ከመሆኑም ባሻገር ስለ አባቱ የተሟላ መግለጫ ሰጥቷል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የይሖዋን ስም በማሳወቅ ብቻ ሳይወሰን ስሙ የሚወክለው አካል ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ገልጿል። (ማቴዎስ 11:27ን አንብብ።) ይህንንም ያደረገው በንግግሩ፣ በድርጊቱ፣ በትምህርቶቹና በመላ ሕይወቱ ነው።

6. ኢየሱስ ካስተማራቸው ትምህርቶች ስለ ይሖዋ ምን እንረዳለን?

6 የኢየሱስ ትምህርቶች አምላክ ከእኛ ምን እንደሚፈልግና ስለ አገልጋዮቹ ምን እንደሚሰማው ያስገነዝቡናል። (ማቴ. 22:36-40፤ ሉቃስ 12:6, 7፤ 15:4-7) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል አንዱ የሆነውን “አታመንዝር” የሚለውን ሕግ ከጠቀሰ በኋላ አንድ ሰው ይህን ድርጊት ከመፈጸሙ ከረጅም ጊዜ በፊት በልቡ ውስጥ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚኖርና አምላክ ይህን እንዴት እንደሚመለከተው ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።” (ዘፀ. 20:14፤ ማቴ. 5:27, 28) ፈሪሳውያን ለአንድ ሕግ የሰጡትን “ባልንጀራህን ውደድ፣ ጠላትህን ጥላ” የሚለውን ትርጓሜ ከጠቀሰ በኋላ ይሖዋ በዚህ ረገድ ምን አስተሳሰብ እንዳለው ሲገልጽ “ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ” ብሏል። (ማቴ. 5:43, 44፤ ዘፀ. 23:4፤ ዘሌ. 19:18) የአምላክን አስተሳሰብና ስሜት ማወቃችን እንዲሁም ከእኛ ምን እንደሚፈልግ በሚገባ መረዳታችን እሱን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንድንመስለው ይረዳናል።

7, 8. ከኢየሱስ ሕይወት ስለ ይሖዋ ምን እንማራለን?

7 በተጨማሪም የኢየሱስ መላ ሕይወት ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ለመገንዘብ ያስችለናል። በወንጌሎች ላይ ኢየሱስ ለተቸገሩ ሰዎች እንደራራ፣ የሰዎችን ሥቃይ እንደተረዳ፣ ደቀ መዛሙርቱ ልጆች ወደ እሱ እንዳይቀርቡ ለማድረግ ሲሞክሩ እንደተበሳጨ የሚገልጹ ዘገባዎችን ስናነብ አባቱ ተመሳሳይ ስሜት እንዳለው መረዳት አዳጋች አይሆንብንም። (ማር. 1:40-42፤ 10:13, 14፤ ዮሐ. 11:32-35) ኢየሱስ ያደረጋቸው ነገሮች የአምላክን ዋና ዋና ባሕርያት ለማወቅ የሚያስችሉን እንዴት እንደሆነ አስብ። ክርስቶስ የፈጸማቸው ተአምራት ከፍተኛ ኃይል እንዳለው የሚያሳዩ አይደሉም? ሆኖም ይህን ኃይል የግል ጥቅሙን ለማራመድ ወይም ሌሎችን ለመጉዳት ፈጽሞ አልተጠቀመበትም። (ሉቃስ 4:1-4) ስግብግብ የሆኑትን ነጋዴዎች ከቤተ መቅደሱ ማባረሩ ለፍትሕ እንደሚቆረቆር የሚያሳይ አይደለም? (ማር. 11:15-17፤ ዮሐ. 2:13-16) ትምህርቶቹም ሆኑ የሰዎችን ልብ ለመንካት የተጠቀመባቸው የሚማርኩ ቃላት “ከሰለሞን የሚበልጥ” ጥበብ እንዳለው የሚያረጋግጡ ናቸው። (ማቴ. 12:42) ኢየሱስ ነፍሱን ለሌሎች አሳልፎ በመስጠት ስላሳየው ፍቅር ስናስብ ከዚህ “የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም” ከማለት በቀር ምን ማለት እንችላለን?—ዮሐ. 15:13

8 የአምላክ ልጅ በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ይሖዋን በሚገባ በመወከሉ “እኔን ያየ አብንም አይቷል” ብሎ ለመናገር ችሏል። (ዮሐንስ 14:9-11ን አንብብ።) በእርግጥም ኢየሱስን መምሰል ይሖዋን ከመምሰል ተለይቶ አይታይም።

ኢየሱስ በይሖዋ የተቀባ ነው

9. ኢየሱስ በአምላክ የተቀባው መቼና እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ በ29 ዓ.ም. የመከር ወራት 30 ዓመት ሲሆነው ወደ አጥማቂው ዮሐንስ በመጣ ጊዜ የተፈጸመውን ሁኔታ ተመልከት። “ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃው ወጣ፤ እነሆ፣ ሰማያት ተከፈቱ፤ የአምላክም መንፈስ በእሱ ላይ እንደ ርግብ ሲወርድ አየ።” በዚህ ወቅት ክርስቶስ ወይም መሲሕ ሆነ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ኢየሱስ በእሱ የተቀባ መሆኑን አሳወቀ። (ማቴ. 3:13-17) በእርግጥም ክርስቶስን እንድንከተል የሚያነሳሳን ጥሩ ምክንያት አለን!

10, 11. (ሀ) “ክርስቶስ” የሚለው የማዕረግ ስም ኢየሱስን ለማመልከት የተሠራበት እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ክርስቶስን ከመከተል ወደኋላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው?

10 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ክርስቶስ” የሚለው የማዕረግ ስም ኢየሱስን ለማመልከት የተሠራባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፤ እነሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ክርስቶስ ኢየሱስና ክርስቶስ ናቸው። “ኢየሱስ ክርስቶስ” የሚለውን መጠሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ኢየሱስ ራሱ ነው፤ በዚህ መጠሪያ ላይ፣ ማዕረጉ ስሙን ተከትሎ ገብቷል። ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።” (ዮሐ. 17:3) እዚህ ላይ ማዕረጉ ከስሙ በኋላ መምጣቱ፣ አምላክ በላከውና እሱ በቀባው አካል ላይ ትኩረት እንዲደረግ እንደተፈለገ በግልጽ የሚያሳይ ነው። ማዕረጉ ከስሙ ቀድሞ በሚመጣበት ጊዜ ማለትም “ክርስቶስ ኢየሱስ” ሲባል በዋነኝነት ትኩረቱ የሚያርፈው በኢየሱስ በራሱ ላይ ሳይሆን እሱ በያዘው ቦታ ወይም ሥልጣን ላይ ነው። (2 ቆሮ. 4:5) “ክርስቶስ” የሚለው የማዕረግ ስም ደግሞ ኢየሱስ መሲሕ በመሆን ያለውን ሥልጣን ለማጉላት የሚሠራበት ሌላው መንገድ ነው።—ሥራ 5:42

11 “ክርስቶስ” የሚለው የማዕረግ ስም ኢየሱስን ለማመልከት የተሠራበት መንገድ ምንም ይሁን ምን አንድ የሚያጎላው ሐቅ አለ፦ የአምላክ ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር የመጣና የአባቱን ፈቃድ ያሳወቀ ቢሆንም እንኳ ተራ ሰው ወይም ተራ ነቢይ ነበር ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ የተቀባ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ የቀባውን ኢየሱስን ከመከተል ወደኋላ ማለት የለብንም።

ወደ መዳን የሚያደርሰን ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ ነው

12. ኢየሱስ ለሐዋርያው ቶማስ በሰጠው መልስ ላይ ለእኛ ትልቅ ትርጉም ያለው ምን ሐሳብ ተናግሯል?

12 መሲሑን መከተላችንን እንድንቀጥል የሚያነሳሳን ሌላው አስፈላጊ ምክንያት ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ለታማኝ ሐዋርያቱ በተናገረው ሐሳብ ላይ ተገልጿል። ኢየሱስ ተለይቷቸው እንደሚሄድና ቦታ እንደሚያዘጋጅላቸው ሲነግራቸው ቶማስ አንድ ጥያቄ አነሳ፤ ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” አለ። (ዮሐ. 14:1-6) ኢየሱስ በዚያን ጊዜ እየተናገረ የነበረው ለ11ዱ ታማኝ ሐዋርያት ስለነበር በሰማይ ቦታ እንደሚያዘጋጅላቸው የተናገረውም ለእነሱ ነው፤ ይሁንና ለቶማስ የሰጠው መልስ በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ለሚያደርጉ ሰዎችም ትልቅ ትርጉም አለው። (ራእይ 7:9, 10፤ 21:1-4) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

13. ኢየሱስ “መንገድ” ነው ሲባል ምን ማለት ነው?

13 ኢየሱስ ክርስቶስ “መንገድ” ነው። ይህም ሲባል ወደ አምላክ መቅረብ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ እሱ ነው ማለት ነው። ከጸሎት ጋር በተያያዘ ይህን እውነት ሆኖ እናገኘዋለን፤ ምክንያቱም አምላክ እንደ ፈቃዱ የምናቀርበውን ልመና እንደሚሰማልን እርግጠኛ መሆን የምንችለው በኢየሱስ በኩል ከጸለይን ብቻ ነው። (ዮሐ. 15:16) ይሁንና ኢየሱስ “መንገድ” የሆነበት ሌላም አቅጣጫ አለ። የሰው ዘር በኃጢአት ምክንያት ከአምላክ ተለይቷል። (ኢሳ. 59:2) ኢየሱስ ደግሞ “በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ [ሰጥቷል]።” (ማቴ. 20:28) በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ “የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐ. 1:7) የአምላክ ልጅ እንዲህ በማድረግ ሰዎች ከአምላክ ጋር የሚታረቁበትን መንገድ ከፍቷል። (ሮም 5:8-10) ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት የምንችለው በአምላክ ልጅ በማመንና እሱን በመታዘዝ ነው።—ዮሐ. 3:36

14. ኢየሱስ “እውነት” የሆነው እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ “እውነት” ነው የተባለው ሁልጊዜ እውነትን ይናገርና በእውነት ይመላለስ ስለነበር ብቻ ሳይሆን ስለ መሲሑ የሚናገሩት ትንቢቶች ሁሉ በእሱ ሕይወት ስለተፈጸሙ ጭምር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች የቱንም ያህል ብዙ ቢሆኑም በእሱ አማካኝነት አዎ ሆነዋል” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮ. 1:20) በሙሴ ሕግ ውስጥ “ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ” እንደሆኑ የተገለጹት ነገሮች ሳይቀሩ በክርስቶስ ኢየሱስ እውን ሆነዋል። (ዕብ. 10:1፤ ቆላ. 2:17) ትንቢቶች ሁሉ የሚያተኩሩት በኢየሱስ ላይ ሲሆን በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና እንድንረዳም ያስችሉናል። (ራእይ 19:10) አምላክ የሰጠው ተስፋ ሲፈጸም ለማየት መሲሑን መከተል ያስፈልገናል።

15. ኢየሱስ “ሕይወት” የሆነው እንዴት ነው?

15 ኢየሱስ “ሕይወት” ነው የተባለው የሰውን ዘር በደሙ በመግዛቱና አምላክ የዘላለም ሕይወት ስጦታን የሚሰጠው “በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ” በኩል በመሆኑ ነው። (ሮም 6:23) በተጨማሪም ኢየሱስ ለሙታን “ሕይወት” ነው። (ዮሐ. 5:28, 29) ከዚህም በላይ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ሊቀ ካህን ሆኖ ሲያገለግል ምን ሊያከናውን እንደሚችል አስብ። በምድር ያሉ ተገዥዎቹን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ለዘላለም ነፃ ያወጣቸዋል!—ዕብ. 9:11, 12, 28

16. ኢየሱስን ለመከተል የሚያነሳሳን ምን ምክንያት አለ?

16 ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ለቶማስ የሰጠው መልስ ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው። ኢየሱስ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነው። ዓለም በእሱ አማካኝነት እንዲድን አምላክ ወደ ዓለም የላከው እሱን ነው። (ዮሐ. 3:17) በእሱ በኩል ካልሆነ በስተቀር ማንም ወደ አብ መቅረብ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ “መዳን በሌላ በማንም አይገኝም፤ ምክንያቱም ልንድንበት የሚገባ ከሰማይ በታች ለሰዎች የተሰጠ ሌላ ስም የለም” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ሥራ 4:12) ቀደም ሲል የነበረን እምነት ምንም ይሁን ምን በኢየሱስ ማመናችንና እሱን መከተላችን እንዲሁም በእሱ እየተመራን ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ መጓዛችን የጥበብ እርምጃ ነው።—ዮሐ. 20:31

ክርስቶስን እንድንሰማ ታዘናል

17. የአምላክን ልጅ መስማታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

17 ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ኢየሱስ በተአምር ሲለወጥ በተመለከቱበት ጊዜ “የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ከሰማይ ሰምተው ነበር። (ሉቃስ 9:28, 29, 35) መሲሑን እንድንሰማ የተሰጠንን ትእዛዝ ማክበራችን በጣም አስፈላጊ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 3:22, 23ን አንብብ።

18. ኢየሱስ ክርስቶስን መስማት የምንችለው እንዴት ነው?

18 ኢየሱስን መስማት ‘እሱን በትኩረት መመልከትንና ምሳሌውን በጥሞና ማሰብን’ ይጨምራል። (ዕብ. 12:2, 3) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይም ሆነ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች ላይ ስለ ኢየሱስ ለምናነባቸው ነገሮች እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስለ እሱ “[ለምንሰማቸው] ነገሮች ከወትሮው የተለየ ትኩረት መስጠታችን” ተገቢ ነው። (ዕብ. 2:1፤ ማቴ. 24:45) በጎቹ እንደመሆናችን መጠን ኢየሱስን ለመስማትና እሱን ለመከተል ዝግጁ እንሁን።—ዮሐ. 10:27

19. ክርስቶስን ያለማቋረጥ እንድንከተለው ምን ሊረዳን ይችላል?

19 በሕይወታችን ውስጥ ማንኛውም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥመን ክርስቶስን መከተላችንን በመቀጠል ረገድ ሊሳካልን ይችላል? ‘የጤናማውን ቃላት ንድፍ አጥብቀን እስከያዝንና’ ‘ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ዝምድና ስላለው እምነትና ፍቅር’ የምንማራቸውን ነገሮች ተግባራዊ እስካደረግን ድረስ ይሳካልናል።—2 ጢሞ. 1:13

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• ክርስቶስን መከተላችን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር የሚረዳን እንዴት ነው?

• ኢየሱስን መምሰል ይሖዋን ከመምሰል ተለይቶ አይታይም የምንለው ለምንድን ነው?

• ኢየሱስ “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” ነው ሲባል ምን ማለት ነው?

• ይሖዋ የቀባውን መስማት ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ትምህርቶች የይሖዋን የላቀ አስተሳሰብ ያንጸባርቃሉ

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ የቀባውን በታማኝነት መከተል አለብን

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ “ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት” በማለት ተናግሯል