በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሌሎች ኃላፊነት የምንሰጠው ለምንድን ነው? እንዴትስ?

ለሌሎች ኃላፊነት የምንሰጠው ለምንድን ነው? እንዴትስ?

ለሌሎች ኃላፊነት የምንሰጠው ለምንድን ነው? እንዴትስ?

ኃላፊነት መስጠት የተጀመረው ፕላኔቷ ምድራችን ከመፈጠሯ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። ይሖዋ አንድያ ልጁን ከፈጠረ በኋላ ጽንፈ ዓለሙን ሲፈጥር ልጁን “ዋና ሠራተኛ” [የ1954 ትርጉም] አድርጎ ተጠቅሞበታል። (ምሳሌ 8:22, 23, 30፤ ዮሐ. 1:3) አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ከፈጠረ በኋላም ቢሆን “ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” በማለት ነግሯቸዋል። (ዘፍ. 1:28) ፈጣሪ፣ ለሰዎች ኤደንን በማስፋፋት መላዋን ምድር ወደ ገነትነት የመለወጥ ሥራ ሰጥቷቸው ነበር። በእርግጥም፣ ከጥንት ጀምሮ ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት የይሖዋ ድርጅት ዓይነተኛ መለያ ነው።

ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት ምን ነገሮችን ያካትታል? ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሥራዎችን ለሌሎች የመስጠት ልማድ ማዳበር ያለባቸው ለምንድን ነው? ይህንን ማድረግ የሚችሉትስ እንዴት ነው?

ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት ሲባል ምን ማለት ነው?

ኃላፊነት መስጠት ተብሎ የተተረጎመው “ዴሊጌት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ለሌሎች ማካፈል፣ ሌሎችን ወኪል አድርጎ መሾም፣ ኃላፊነትን ወይም ሥልጣንን መስጠት” የሚል ፍቺ አለው። በመሆኑም ኃላፊነት መስጠት ሌሎች ሰዎች የተለያዩ ተግባሮችን እንዲያከናውኑ ማሳተፍን ይጨምራል። ይህም ሥልጣንን ለሌሎች ወደ ማካፈል ያመራል።

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አንድን ሥራ እንዲያከናውኑ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንድሞች ሥራውን ማከናወን፣ ስለ ሥራው ሪፖርት ማቅረብ እንዲሁም ብዙውን ጊዜ ኃላፊነት የሰጣቸውን ግለሰብ ማማከር ይጠበቅባቸዋል። ይሁን እንጂ ለሥራው በዋነኝነት የሚጠየቀው ኃላፊነቱን የሰጠው ወንድም ነው። ይህ ወንድም ሥራው የሚገኝበትን ሁኔታ መከታተልና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ምክር መስጠት ይኖርበታል። ይሁንና አንዳንዶች ‘አንተው ራስህ ሥራውን መሥራት ከቻልክ ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት ለምን ያስፈልግሃል?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል።

ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት ለምን አስፈለገ?

ይሖዋ፣ አንድያ ልጁን ከፈጠረ በኋላ ልጁ በሌሎች የፍጥረት ሥራዎቹ እንዲካፈል ኃላፊነት ስለመስጠቱ እስቲ አስብ። በእርግጥም “በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ፣ የሚታዩትና የማይታዩት ነገሮች . . . የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት ነው።” (ቆላ. 1:16) ፈጣሪ ሁሉንም ነገር ብቻውን መሥራት ይችል የነበረ ቢሆንም ውጤታማ ሥራ በመሥራት የሚገኘውን ደስታ ለልጁ ለማካፈል ፈለገ። (ምሳሌ 8:31) ይህም ልጁ ስለ አምላክ ባሕርያት ይበልጥ እንዲያውቅ ረድቶታል። በሌላ አነጋገር፣ አባቱ ይህን አጋጣሚ አንድያ ልጁን ለማሠልጠን ተጠቅሞበታል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ለሌሎች ኃላፊነት በመስጠት ረገድ የአባቱን ምሳሌ ተከትሏል። ደቀ መዛሙርቱን ደረጃ በደረጃ አሠልጥኗቸዋል። ኢየሱስ፣ በመጀመሪያ 12ቱን ሐዋርያት ከዚያም 70 ደቀ መዛሙርቱን እሱ ሊሄድበት ወዳሰበበት ቦታዎች ሄደው የስብከቱን ሥራ እንዲያከናውኑ ላካቸው። (ሉቃስ 9:1-6፤ 10:1-7) ደቀ መዛሙርቱ በእነዚህ ቦታዎች ያከናወኑት ሥራ በዚያ ላይ ለመገንባት የሚያስችል ጥሩ መሠረት ሆኖለታል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ፣ ቀደም ሲል ላሠለጠናቸው ደቀ መዛሙርቱ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ ጨምሮ ሌሎች ከባድ ኃላፊነቶችን ሰጥቷቸዋል።—ማቴ. 24:45-47፤ ሥራ 1:8

ከጥንት ጀምሮ ኃላፊነትን ለሌሎች መስጠት እንዲሁም ሌሎችን ማሠልጠን የክርስቲያን ጉባኤ መለያ ሆኖ ቆይቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ከእሱ የሰማውን ነገር “ታማኝ ለሆኑና እነሱም በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር በሚገባ ብቁ ለሚሆኑ ሰዎች አደራ [እንዲሰጥ]” ነግሮታል። (2 ጢሞ. 2:2) ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች ሌሎችን ያሠለጥናሉ፤ ሥልጠናውን የወሰዱትም በበኩላቸው ሌሎችን ያሠለጥናሉ።

አንድ ሽማግሌ ለእሱ የተሰጡትን የተለያዩ ሥራዎች ለሌሎች በማካፈል፣ የማስተማሩና እረኝነት የማድረጉ ሥራ የሚስገኘውን ደስታ ሌሎችም እንዲቀምሱት ማድረግ ይችላል። ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነት ለሌሎች እንዲያካፍሉ የሚያነሳሳቸው ሌላው ምክንያት ደግሞ ሰው የአቅም ገደብ ያለው መሆኑን መረዳታቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በትሑታን ዘንድ ጥበብ ትገኛለች’ ይላል። (ምሳሌ 11:2) ትሕትና አንድ ሰው ያለውን የአቅም ገደብ እንዲገነዘብ ያደርገዋል። አንድ ግለሰብ ሁሉንም ነገር ራሱ ለማከናወን የሚሞክር ከሆነ ሊደክም ይችላል፤ እንዲሁም ከቤተሰቡ ጋር ማሳለፍ የሚገባውን ጊዜ እንዲያጣ ያደርገዋል። በመሆኑም ኃላፊነትን ለሌሎች ማካፈል የጥበብ እርምጃ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ሆኖ የሚያገለግልን ወንድም እንመልከት። ይህ ወንድም ሌሎች ሽማግሌዎች የጉባኤውን ሒሳብ ኦዲት እንዲያደርጉ ሊጠይቅ ይችላል። እነዚህ ሽማግሌዎች ኦዲት ማድረጋቸው ደግሞ ጉባኤው ያለውን ሒሳብ እንዲያውቁ ይረዳቸዋል።

ኃላፊነትን ለሌሎች ማካፈል ወንድሞች አስፈላጊ የሆነ ችሎታና ተሞክሮ እንዲያዳብሩ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል፤ እንዲሁም ኃላፊነት የሰጠው ወንድም ሥራው የተሰጣቸው ግለሰቦች ያላቸውን ችሎታ እንዲያስተውል ይረዳዋል። በመሆኑም ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ላሉ ወንድሞች አንዳንድ ሥራዎችን በመስጠት ወደ ፊት የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስችል ‘ብቃት’ እንዳላቸው ሊፈትኗቸው ይችላሉ።—1 ጢሞ. 3:10

በተጨማሪም፣ ሽማግሌዎች ለሌሎች ኃላፊነት በማካፈል በወንድሞች ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ። ጳውሎስ፣ ከጢሞቴዎስ ጋር አብሮ በመሥራት ለሚስዮናዊ አገልግሎት አሠልጥኖታል። ይህም እነዚህ ሁለት ሰዎች የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ አስችሏቸዋል። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን “በእምነት እውነተኛ ልጄ” በማለት ጠርቶታል። (1 ጢሞ. 1:2) በተመሳሳይም ሌሎች ነገሮች በተፈጠሩበት ጊዜ ይሖዋና ኢየሱስ አብረው መሥራታቸው በመካከላቸው የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖር አስችሏል። በመሆኑም ሽማግሌዎች አንዳንድ ሥራዎችን ለሌሎች በኃላፊነት በመስጠት ከወንድሞች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ይችላሉ።

አንዳንዶች ለሌሎች ኃላፊነት ከመስጠት የሚቆጠቡት ለምንድን ነው?

አንዳንድ ሽማግሌዎች ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት ያለውን ጥቅም ቢገነዘቡም ይህን ከማድረግ ወደኋላ የሚሉት ምናልባትም ያላቸው ሥልጣን የሚቀንስ ስለሚመስላቸው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሽማግሌዎች ሁሉንም ነገር መቆጣጠር እንዳለባቸው ይሰማቸው ይሆናል። ይሁንና ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ደቀ መዛሙርቱ ከእሱ የበለጠ ሥራ እንደሚያከናውኑ በመገንዘብ ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷቸው እንደነበር አስታውስ!—ማቴ. 28:19, 20፤ ዮሐ. 14:12

አንዳንድ ሽማግሌዎች ደግሞ ከዚህ በፊት ኃላፊነትን ቢሰጡም አጥጋቢ ውጤት ሳይገኙ ቀርተው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሽማግሌዎች ሥራውን ራሳቸው ቢያከናውኑት ኖሮ በጥራትና በፍጥነት ይሠሩት እንደነበር ይሰማቸው ይሆናል። ይሁንና ጳውሎስ ምን እንዳደረገ ተመልከት። ጳውሎስ ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት ያለውን ጥቅም ያውቃል፤ እንዲሁም ሥልጠና የሚሰጣቸው ግለሰቦች ሁልጊዜ እሱ እንደሚፈልገው ሊሠሩ እንደማይችሉ ይገነዘባል። ጳውሎስ በመጀመሪያው የሚስዮናዊ ጉዞ ወቅት የአገልግሎት ጓደኛው የነበረውን ወጣቱን ማርቆስን አሠልጥኗል። ማርቆስ የተሰጠውን ሥራ ትቶ ወደ ቤቱ መመለሱ ጳውሎስን በጣም አሳዝኖት ነበር። (ሥራ 13:13፤ 15:37, 38) ይህ መሆኑ ጳውሎስ ሌሎችን እንዳያሠለጥን ሰበብ አልሆነውም። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ወጣቱ ጢሞቴዎስን የጉዞ ጓደኛው አድርጎ መርጦታል። ጢሞቴዎስ ከባድ ኃላፊነቶችን መሸከም የሚችልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን የመሾም ሥልጣን በመስጠት በኤፌሶን እንዲቆይ አበረታቶታል።—1 ጢሞ. 1:3፤ 3:1-10, 12, 13፤ 5:22

በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች አንድ ሰው ጥሩ ምላሽ ስላልሰጠ ብቻ ሌሎችን ከማሠልጠን ወደኋላ ማለት አይገባቸውም። በሌሎች ላይ እምነት መጣልና እነሱን ማሠልጠን የጥበብ አካሄድ ከመሆኑም በላይ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች ለሌሎች ኃላፊነት ሲሰጡ ምን ነገሮችን ማስታወስ ይኖርባቸዋል?

ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት የሚቻለው እንዴት ነው?

ለሌሎች ኃላፊነት ለመስጠት ስታስብ በአእምሮህ የያዝካቸው ወንድሞች ያላቸውን ችሎታ ግምት ውስጥ አስገባ። በኢየሩሳሌም በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ በየዕለቱ ምግብ የሚያከፋፍሉ ግለሰቦች ባስፈለጉ ጊዜ ሐዋርያት ‘በመንፈስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ወንዶችን መርጠው’ ነበር። (ሥራ 6:3) እምነት የማይጣልበትን ሰው፣ አንድን ሥራ እንዲያከናውን ብትጠይቀው ላይሳካለት ይችላል። በመሆኑም በመጀመሪያ ላይ ቀለል ያሉ ሥራዎችን እንዲሠራ አድርግ። ይህ ሰው የተሰጠውን ሥራ በታማኝነት ካከናወነ ተጨማሪ ኃላፊነት ሊሰጠው ይችላል።

እርግጥ ነው፣ ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ሌላም ነገር አለ። የእያንዳንዱ ሰው ባሕርይና ችሎታ ይለያያል። በተጨማሪም አንድ ሰው ያለው ተሞክሮ ከሌላው የተለየ ነው። ተግባቢና በቀላሉ የሚቀረብ ወንድም አስተናጋጅ ሆኖ እንዲያገለግል ሊመደብ ይችላል፤ አንድን ሥራ፣ ሥርዓት ባለውና በዘዴ የማከናወን ችሎታ ያለው ወንድም ደግሞ የጉባኤ ፀሐፊ ረዳት ሆኖ እንዲያገለግል ቢመደብ ይበልጥ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ነገሮችን አሳምሮ የመሥራት ችሎታ ያላት አንዲት እህት የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ዕለት አበባ እንድታዘጋጅ ኃላፊነት ሊሰጣት ይችላል።

ኃላፊነት ለሌሎች ሲሰጥ መከናወን ያለበት ሥራ በግልጽ መነገር ይኖርበታል። መጥምቁ ዮሐንስ፣ መልእክተኞችን ወደ ኢየሱስ ከመላኩ በፊት ማወቅ የፈለገውን ነገር ብቻ ሳይሆን ምን ብለው መጠየቅ እንዳለባቸው ጭምር ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 7:18-20) በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሕዝቡን ከመገበ በኋላ የተረፈውን ምግብ እንዲሰበስቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሲነግራቸው ዝርዝር መመሪያ አልሰጣቸውም። (ዮሐ. 6:12, 13) የምንሰጠው መመሪያ በአብዛኛው የተመካው በሥራው ዓይነትና በሠልጣኞቹ ችሎታ ላይ ነው። ኃላፊነቱን የሰጠውም ሆነ ሥራውን የተቀበለው ግለሰብ ሥራውን በተመለከተ አንድ ዓይነት ግብ ሊኖራቸውና መረጃ ለመለዋወጥ በየስንት ጊዜው ተገናኝተው መነጋገር እንዳለባቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል። ኃላፊነት የተሰጠው ሰው ሥራውን እስከ ምን ድረስ በራሱ መንገድ መሥራት እንደሚችል ሁለቱም ግለሰቦች ማወቅ አለባቸው። ሥራው ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ የሚፈለግበት አንድ የተወሰነ ቀን ካለ ኃላፊነት የተሰጠውን ወንድም በዚያ ቀን ጨርስ ብሎ ጫና ከማድረግ ይልቅ ሁለቱም ግለሰቦች በቀኑ ላይ መወያየታቸውና ስምምነት ላይ መድረሳቸው የበለጠ ለሥራ የሚያነሳሳ ሊሆን ይችላል።

አንድን ሥራ እንዲያከናውን የተመደበ ሰው እንደ አስፈላጊነቱ ገንዘብ ሊሰጠውና የሰው ኃይል ሊመደብለት እንዲሁም ለሥራው የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ሊኖሩት ይገባል። ይህን ዝግጅትም ሌሎች እንዲያውቁ ማድረግ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ለጴጥሮስ “የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች” የሰጠው ሌሎች ደቀ መዛሙርት በተገኙበት ነበር። (ማቴ. 16:13-19) በተመሳሳይም፣ አንዳንድ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ የተመደቡት እነማን እንደሆኑ ጉባኤው እንዲያውቅ ቢደረግ ጥሩ ሊሆን ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ ልንጠነቀቅበት የሚገባ ነገር አለ። አንድን ሥራ በኃላፊነት ከሰጠህ በኋላ እያንዳንዱን ነገር ለመቆጣጠር የምትሞክር ከሆነ “በአንተ አልተማመንም” በማለት ለግለሰቡ የተናገርክ ያክል ነው። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ውጤቱ እንደጠበቅከው ላይሆን ይችላል። ሆኖም አንድን ሥራ እንዲያከናውን የተመደበው ወንድም የተወሰነ ነፃነት ከተሰጠው በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲሁም ተሞክሮ ሊያዳብር ይችላል። ይህ ማለት ግን ሥራውን ሙሉ በሙሉ ለእሱ እንተዋለን ማለት አይደለም። ይሖዋ ከፍጥረት ሥራ ጋር በተያያዘ ለልጁ ኃላፊነት ቢሰጠውም እሱም በሥራው ይካፈል ነበር። ዋና ሠራተኛ ለነበረው ለኢየሱስ ‘ሰውን በመልካችን እንሥራ’ ብሎታል። (ዘፍ. 1:26) በመሆኑም በቃልም ይሁን በድርጊት ለሥራው ድጋፍ ስጥ፤ እንዲሁም ኃላፊነት የተሰጠውን ሰው ለሚያደርገው ጥረት አመስግነው። በተጨማሪም፣ ስለተገኘው ውጤት አጭር ውይይት ማድረጋችሁ ግለሰቡን ሊረዳው ይችላል። ሥራው በተገቢው ሁኔታ እየተሠራ እንዳልሆነ ከተሰማህ ተጨማሪ ምክርም ሆነ እርዳታ ከመስጠት ወደኋላ አትበል። ሥራውን የሰጠኸው አንተ እንደመሆንህ መጠን በኃላፊነት የምትጠየቀው አንተ እንደሆንክ መዘንጋት የለብህም።—ሉቃስ 12:48

ሽማግሌዎች ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው በጉባኤው ውስጥ አንዳንድ ሥራዎችን የማከናወን ኃላፊነት የሰጧቸው ብዙ ወንድሞች ከፍተኛ ጥቅም አግኝተዋል። በእርግጥም፣ ሁሉም ሽማግሌዎች የይሖዋን ምሳሌ በመከተል ለሌሎች ኃላፊነት የሚሰጡት ለምንና እንዴት እንደሆነ መገንዘብ አለባቸው።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት

• አንድን ሥራ በማከናወን ሌሎች ደስታ እንዲያገኙ መንገድ ይከፍታል

• ብዙ ሥራ ማከናወን ያስችላል

• ጥበበኞችና ትሑቶች መሆናችንን ያሳያል

• ሌሎችን ለማሠልጠን ይረዳል

• በሌሎች እንደምንተማመን ያሳያል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኃላፊነት መስጠት የሚቻልበት መንገድ

• ለሥራ የሚሆኑ ሰዎችን ምረጥ

• ስለ ሥራው ግልጽ ማብራሪያ ስጥ/ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ይኑርህ

• ምን ነገር መከናወን እንዳለበት በግልጽ ተናገር

• ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን አቅርብ

• ሥራው መሠራቱን ተከታተል፤ እንዲሁም ኃላፊነት በሰጠኸው ሰው እንደምትተማመን ግለጽ

• መጨረሻ ላይ በኃላፊነት የምትጠየቀው አንተ እንደሆንክ አትዘንጋ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት፣ ሥራ መመደብን ብሎም ሥራው ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ መከታተልን ይጨምራል