በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለይሖዋ ምን ልከፍለው እችላለሁ?

ለይሖዋ ምን ልከፍለው እችላለሁ?

ለይሖዋ ምን ልከፍለው እችላለሁ?

ሩት ዳኔ እንደተናገረችው

እናቴ 1933 መጥፎ ነገሮች የተከሰቱበት ዓመት እንደሆነ በቀልድ መልክ ስትናገር “ሂትለር ሥልጣን ላይ ወጣ፤ ጳጳሱ ቅዱስ ዓመት ብለው ሰየሙት፤ እንዲሁም አንቺ ተወለድሽ” ትል ነበር።

ወላጆቼ ሎሬን በተባለው የፈረንሳይ ግዛት ውስጥ ትገኝ በነበረችው በዩትስ ከተማ ይኖሩ ነበር፤ ሎሬን ለጀርመን ድንበር ቅርብ የሆነ የፈረንሳይ ታሪካዊ አካባቢ ነው። ቀናተኛ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነችው እናቴና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነው አባቴ በ1921 ተጋቡ። በ1922 ታላቅ እህቴ ሄለን የተወለደች ሲሆን ወላጆቼም በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሕፃንነቷ አስጠመቋት።

በ1925 አባቴ በጀርመንኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን የአምላክ በገና የተባለ መጽሐፍ አገኘ። በመጽሐፉ ላይ ያነበበው ነገር እውነትን እንዳገኘ እንዲሰማው አደረገው። ከዚያም ለመጽሐፉ አዘጋጆች ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን እነሱም በዚያን ጊዜ በጀርመን ውስጥ ቢቤልፎርሸር በሚል ስም ይጠሩ ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር አገናኙት። አባቴ ወዲያውኑ ስለተማረው ነገር ለሌሎች መመሥከር ጀመረ። እናቴ ግን ይህን ማድረጉ አላስደሰታትም። በሚጥም ጀርመንኛ “ያሻህን መሆን ትችላለህ፤ ብቻ ከእነዛ ቢቤልፎርሸር ከሚባሉት ሰዎች ጋር እንዳትገናኝ!” ትለው ነበር። ይሁን እንጂ አባቴ በጀመረው መንገድ ለመግፋት ቆርጦ ስለነበር በ1927 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።

በዚህም ምክንያት አያቴ፣ ትዳሯን እንድታፈርስ እናቴን ትገፋፋት ጀመር። አንድ ቀን አንድ የካቶሊክ ቄስ፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲያስተምር ምዕመናኑን “ሐሰተኛ ነቢይ ከሆነው ከዳኔ ራቁ” ሲል አስጠነቀቃቸው። የዚያን ቀን አያቴ ከቤተ ክርስቲያን ስትመለስ ከቤታችን ፎቅ ላይ ሆና የአበባ መትከያ ዕቃ አባቴ ላይ ወረወረችበት። የተወረወረበት ከባድ ዕቃ ጭንቅላቱን ለትንሽ ስቶት ትከሻውን መታው። ይህ ሁኔታ እናቴ ‘ሰዎች ነፍሰ ገዳይ እንዲሆኑ የሚያበረታታ ሃይማኖት ጥሩ ሊሆን አይችልም’ ብላ እንድታስብ አደረጋት። ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች ማንበብ ጀመረች። እናቴ ያነበበችው ነገር እውነት እንደሆነ ለማመን ብዙ ጊዜ አልወሰደባትም፤ በመሆኑም በ1929 ተጠመቀች።

ወላጆቼ፣ ይሖዋ ለእኔና ለእህቴ እውን ሆኖ እንዲታየን ለማድረግ ይጥሩ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ካነበቡልን በኋላ በታሪኮቹ ውስጥ የተገለጹት ሰዎች ለምን እንደዚያ ዓይነት እርምጃ እንደወሰዱ ይጠይቁን ነበር። በዚያን ጊዜ አባቴ፣ ብዙ ገንዘብ የሚያስቀርብን ቢሆንም እንኳ አምሽቶ ላለመሥራት ወይም የሌሊት ፈረቃ ላለመግባት ወሰነ። ይህን ያደረገው ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ ለአገልግሎትና ከልጆቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚያስችለውን ጊዜ ለማግኘት ስለፈለገ ነበር።

አስጨናቂ ጊዜ እየተቃረበ ነበር

ወላጆቼ፣ ከስዊዘርላንድና ከፈረንሳይ የሚመጡ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና ቤቴላውያንን ተቀብለው የማስተናገድ ልማድ ነበራቸው። እነዚህ ወንድሞች ከእኛ አካባቢ ጥቂት ርቀው የሚገኙት የጀርመን ወንድሞች ምን ዓይነት ችግር እየደረሰባቸው እንዳለ ይነግሩን ነበር። የናዚ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን ወደ ማጎሪያ ካምፖች ይልክ እንዲሁም ልጆቻቸውን ከወላጆቻቸው ነጥሎ ይወስድ ነበር።

እኔና ሄለን ከፊታችን ለሚጠብቀን ከባድ ፈተና ተዘጋጅተን ነበር። ወላጆቻችን መመሪያ የሚሆኑንን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በአእምሯችን እንድንይዝ ረድተውናል። እንዲህ ይሉን ነበር፦ “ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ካላወቃችሁ ምሳሌ 3:5, 6⁠ን አስቡ። በትምህርት ቤት የሚያጋጥማችሁ ፈተና ካስፈራችሁ አንደኛ ቆሮንቶስ 10:13⁠ን አስታውሱ። ከእኛ ከተለያችሁ ምሳሌ 18:10 ትዝ ይበላችሁ።” መዝሙር 23⁠ንና 91⁠ን በቃሌ መያዝ ችዬ የነበረ ሲሆን ይህም ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚጠብቀኝ እምነት እንዲኖረኝ አድርጓል።

በ1940 የናዚ መንግሥት አልሳስ-ሎሬን የጀርመን ክፍል እንዲሆን አደረገ፤ በዚህም የተነሳ አዲሱ አገዛዝ ሁሉም አዋቂዎች የናዚ ፓርቲ አባል እንዲሆኑ ማስገደድ ጀመረ። አባቴ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ጌስታፖ የሚባሉት የጀርመን ፖሊሶች እንደሚያስሩት ያስፈራሩት ጀመር። እናቴም የወታደሮች የደንብ ልብስ ለመስፋት ፈቃደኛ ባለመሆኗ ጌስታፖዎች እሷንም ማስፈራራት ጀመሩ።

ለእኔም ቢሆን ትምህርት ቤት የሚያጋጥመኝ ሁኔታ ቀላል አልነበረም። በየቀኑ ትምህርት ከመጀመራችን በፊት ለሂትለር መጸለይ፣ “ሃይል ሂትለር” (ሂትለር አዳኝ ነው የሚል ትርጉም አለው) የሚለውን ሰላምታ መስጠትና ቀኝ እጅ ዘርግቶ ብሔራዊ መዝሙር መዘመር ግዴታ ነበር። ወላጆቼ “ሃይል ሂትለር” የሚለውን ሰላምታ እንዳልሰጥ ከመንገር ይልቅ ሕሊናዬን እንዳሠለጥን ረድተውኛል። በመሆኑም ይህን ሰላምታ ላለመስጠት በራሴ ወሰንኩ። በዚህም ምክንያት አስተማሪዎች በጥፊ መተውኛል፤ እንዲሁም ከትምህርት ቤት እንደምባረር በመንገር ያስፈራሩኝ ነበር። አንድ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ 12ቱም የትምህርት ቤታችን አስተማሪዎች ፊታቸው አቁመውኝ “ሃይል ሂትለር” የሚለውን ሰላምታ እንድሰጥ ሊያስገድዱኝ ሞከሩ። ያም ሆኖ በይሖዋ እርዳታ መጽናት ችያለሁ።

አንዲት አስተማሪ ደግሞ በዘዴ ልታግባባኝ ሞከረች። ጥሩ ተማሪ እንደሆንኩ፣ በጣም እንደምትወደኝና ከትምህርት ቤት ብባረር እንደምታዝን ገለጸችልኝ። ከዚያም እንዲህ አለች፦ “እጅሽን ሙሉ በሙሉ መዘርጋት አያስፈልግሽም። በትንሹ ብቻ ካወጣሽ ይበቃል። ‘ሃይል ሂትለር!’ የሚለውን ሰላምታ መስጠትም ቢሆን አያስፈልግሽም። ከንፈርሽን በማንቀሳቀስ የምትናገሪ ማስመሰል ትችያለሽ።”

ስለ አስተማሪዬ ለእናቴ ስነግራት፣ የባቢሎን ንጉሥ ባቆመው ምስል ፊት እንዲሰግዱ ስለተጠየቁት ሦስት ወጣት ዕብራውያን የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አስታወሰችኝ። “እነዚህ ወጣቶች እንዲያደርጉ የተጠየቁት ነገር ምን ነበር?” ስትል ጠየቀችኝ። “ለምስሉ እንዲሰግዱ ነበር” ብዬ መለስኩላት። “ለምስሉ መስገድ በነበረባቸው ሰዓት ጫማቸውን ለማሰር በማጎንበስ ለማስመሰል ቢሞክሩ ትክክል ይሆኑ ነበር? አንቺ ራስሽ ወስነሽ ትክክል መስሎ የታየሽን አድርጊ” አለችኝ። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ እንዳደረጉት እኔም ለይሖዋ ብቻ ታማኝ ለመሆን ወሰንኩ።—ዳን. 3:1, 13-18

አስተማሪዎቹ በተደጋጋሚ ከትምህርት ቤት አስወጥተውኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከወላጆቼ ነጥለው እንደሚወስዱኝ በመንገር ያስፈራሩኝ ነበር። በወቅቱ በጣም ብጨነቅም እንኳ የወላጆቼ ማበረታቻ አልተለየኝም። ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ እናቴ አብራኝ ትጸልይ የነበረ ሲሆን በዚህ ጊዜም ይሖዋን እንዲጠብቀኝ ትጠይቀዋለች። ይሖዋ ለእውነት መቆም እንድችል ጥንካሬ እንደሚሰጠኝ እርግጠኛ ነበርኩ። (2 ቆሮ. 4:7) አባቴ በትምህርት ቤት የሚያጋጥመኝ ተጽዕኖ በጣም ከከበደብኝ ወደ ቤት ለመምጣት ማመንታት እንደሌለብኝ ይነግረኝ ነበር። “እንወድሻለን፤ ሁልጊዜም ቢሆን ለእኛ ልጃችን ነሽ። ደግሞም ይህ በአንቺና በይሖዋ መካከል ያለ ጉዳይ ነው” ይለኝ ነበር። ይህ ማበረታቻ ንጹሕ አቋሜን ለመጠበቅ ያለኝን ፍላጎት አጠናክሮልኛል።—ኢዮብ 27:5 NW

ጌስታፖዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች ለማግኘትና ወላጆቼን ለመመርመር በተደጋጋሚ ወደ ቤታችን ይመጡ ነበር። በተጨማሪም እናቴን ወስደው ለሰዓታት ያቆዩዋት የነበረ ከመሆኑም ሌላ አባቴንና እህቴንም ከሥራ ቦታቸው ይወስዷቸው ነበር። በመሆኑም ከትምህርት ቤት ስመለስ እናቴን ቤት እንደማገኛት እርግጠኛ አልሆንም። አንዳንድ ጊዜም አንዲት ጎረቤታችን “እናትሽን ወስደዋታል” ብላ ትነግረኛለች። ከዚያም ቤት ገብቼ እደበቅና ‘እናቴን እያሠቃዩዋት ይሆን? እንደገና አገኛት ይሆን?’ እያልኩ አስባለሁ።

ወደ ካምፕ ተላክን

ጥር 28, 1943 ጌስታፖዎች ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ከእንቅልፋችን ቀሰቀሱን። ወላጆቼም ሆኑ እኔና እህቴ የናዚ ፓርቲ አባል ለመሆን ከተስማማን ወደ ካምፕ እንደማንላክ ነገሩን። ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች ባለመሆናችንም ጓዛችንን እንድናዘጋጅ ሦስት ሰዓት ሰጡን። እማማ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊመጣ እንደሚችል ትጠብቅ ስለነበር የሚያስፈልጉንን ቅያሪ ልብሶችና መጽሐፍ ቅዱስ የያዙ ቦርሳዎች አዘጋጅታ ነበር፤ በመሆኑም ይህን ጊዜ ለመጸለይና እርስ በርስ ለመበረታታት ተጠቀምንበት። አባባም ‘ምንም ነገር ቢሆን ከአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል’ አሳሰበን።—ሮም 8:35-39

ጌስታፖዎቹ ተመልሰው መጡ። አንግላድ የተባሉ አንዲት እህት ዓይናቸው እንባ አቅርሮ እጃቸውን እያውለበለቡ ሲሰናበቱን እስካሁን ድረስ ትዝ ይሉኛል። ጌስታፖዎቹ ሜትስ እስከሚገኘው ባቡር ጣቢያ ድረስ በመኪና ወሰዱን። ከዚያም ለሦስት ቀናት በባቡር ከተጓዝን በኋላ ፖላንድ ወደሚገኘው በኦውሽቪትስ ካምፕ ወደሚተዳደረው ኮክዎቪትሰ ካምፕ ደረስን። ከሁለት ወር በኋላ ደግሞ፣ ቀደም ሲል የሴቶች ገዳም ወደነበረውና የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ወደ ግሊቪትሰ ካምፕ ተዛወርን። በዚያም ናዚዎች እምነታችንን እንደካድን በሚናገር ወረቀት ላይ ከፈረምን እንደምንለቀቅና ንብረታችን እንደሚመለስልን ነገሩን። አባቴና እናቴ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም፤ በዚህም ምክንያት ወታደሮቹ “ወደ ቤታችሁ መቼም አትመለሱም” አሉን።

ሰኔ ወር ላይ ወደ ሽፋየንቶክዎቪትሰ ያዘዋወሩን ሲሆን እዚያም እስካሁን ድረስ የሚያሠቃየኝ የራስ ምታት ሕመም ጀመረኝ። ጣቶቼ ላይ የሚያመረቅዝ ቁስል ስለወጣብኝ አንድ ዶክተር ያለ ማደንዘዣ አብዛኞቹን ጥፍሮቼን ነቀላቸው። ይህ ሁሉ ቢደርስብኝም የምጽናናበት ነገር ነበረኝ። ሥራዬ ለጥበቃ ሠራተኞቹ መላላክ ስለነበር ብዙ ጊዜ ዳቦ ቤት እሄድ ነበር፤ እዚያ የምትሠራው ሴት ደግሞ የምበላው ነገር ትሰጠኝ ነበር።

እስከዚህ ጊዜ ድረስ ቤተሰባችን ሳይለያይ ከሌሎች እስረኞች ተነጥለን ቆይተናል። ጥቅምት 1943 ዞምፕኮቪትሰ ወደሚገኘው ካምፕ ተላክን። እዚያም ወደ 60 ከሚጠጉ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ጋር ጣሪያ ሥር ባለ ክፍል ውስጥ ተደራራቢ አልጋ ላይ እንተኛ ነበር። የናዚ ወታደሮች የሚሰጡን ምግብ የተበላሸ ከመሆኑ የተነሳ ለመብላት በጣም ይቀፍ ነበር።

እነዚህ ሁሉ መከራዎች ቢፈራረቁብንም ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጥንም። በመጠበቂያ ግንብ ላይ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ስለሚከናወነው ታላቅ የስብከት ሥራ አንብበናል። በመሆኑም ሥቃይ የሚደርስብን ለምን እንደሆነ እንዲሁም ይህ መከራ በቅርቡ እንደሚያበቃ እናውቅ ነበር።

የሕብረ ብሔሩ ጦር እየተቃረበ እንደሆነ ስንሰማ ናዚዎች በጦርነቱ እየተሸነፉ መሆኑን ተረዳን። በ1945 መጀመሪያ አካባቢ የናዚ ወታደሮች ካምፑን ጥለው ለመሄድ ወሰኑ። በመሆኑም የካቲት 19 ቀን 240 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የእግር ጉዞ እንድንጀምር ተደረገ። ከአራት ሳምንት ጉዞ በኋላ ሽታይንፌልስ፣ ጀርመን የደረስን ሲሆን ጠባቂዎቹ ማዕድን ለማውጣት በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ከተቱን። ብዙዎች እዚያ እንደምንገደል አስበው ነበር። ሆኖም በዚያኑ ቀን የሕብረ ብሔሩ ጦር በመድረሱ የናዚ ወታደሮች ሸሽተው ያመለጡ ሲሆን የእኛም መከራ አበቃ።

ግቦቼ ላይ ለመድረስ ያደረግኩት ጥረት

ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ ግንቦት 5, 1945 ዩትስ የሚገኘው ቤታችን ስንደርስ በጣም ቆሽሸንና ቅማል ወርሶን ነበር። ከየካቲት ጀምሮ ልብስ አልቀየርንም፤ በመሆኑም የለበስናቸውን አሮጌ ልብሶች ለማቃጠል ወሰንን። እናቴ እንዲህ ስትል የተናገረችውን አልረሳውም፦ “የዛሬው ቀን በሕይወታችሁ ውስጥ በጣም የተደሰታችሁበት ዕለት ይሁን። ምንም ነገር የለንም። የለበስነው ልብስ እንኳ ሰዎች የሰጡን ነው። ያም ሆኖ አራታችንም ታማኝነታችንን እንደጠበቅን ወደ ቤታችን ተመልሰናል። እምነታችንን አልካድንም።”

ጤንነቴ እስኪሻሻል ድረስ ለሦስት ወራት ያህል በስዊዘርላንድ ከቆየሁ በኋላ ትምህርት ቤት ገባሁ፤ በዚህ ጊዜ ግን እባረራለሁ የሚል ስጋት አልነበረብኝም። አሁን ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችን ጋር በነፃነት መሰብሰብና በግልጽ መስበክ እንችላለን። ከዓመታት በፊት ለይሖዋ የገባሁትን ቃል በሕዝብ ፊት ለማሳየት ነሐሴ 28, 1947 በ13 ዓመቴ ተጠመቅኩ። በሞዜል ወንዝ ውስጥ ያጠመቀኝ አባቴ ነበር። እንደተጠመቅኩ አቅኚ ለመሆን ፈልጌ ነበር፤ ሆኖም አባቴ መጀመሪያ አንድ ሙያ እንድማር አበረታታኝ። በመሆኑም የልብስ ስፌት ሙያ ተማርኩ። በ1951 ማለትም በ17 ዓመቴ አቅኚ ሆኜ በአቅራቢያችን በምትገኘው ትዮንቪል የተባለች ከተማ እንዳገለግል ተመደብኩ።

በዚያው ዓመት በፓሪስ በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ የተገኘሁ ሲሆን በሚስዮናዊነት አገልግሎት ለመካፈል አመለከትኩ። ለሚስዮናዊነት አገልግሎት ለማመልከት ዕድሜዬ ያልደረሰ ቢሆንም ወንድም ናታን ኖር ማመልከቻዬ “ሌላ ጊዜ” ሊታይ እንደሚችል ነገረኝ። ሰኔ 1952 በሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የሚስዮናውያን ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በ21ኛው ክፍል እንድማር ተጠራሁ።

ጊልያድና ከዚያ በኋላ ያሳለፍኩት ሕይወት

በጣም አስደሳች ጊዜ ነበር! ብዙውን ጊዜ በራሴ ቋንቋ እንኳ በሕዝብ ፊት መናገር ይከብደኝ ነበር። በጊልያድ ትምህርት ቤት ግን እንግሊዝኛ መናገር ነበረብኝ። ይሁንና አስተማሪዎቹ በፍቅር ረድተውኛል። እንዲያውም አንድ ወንድም ሳፍር ፈገግ እል ስለነበር ቅጽል ስም አወጣልኝ።

የምረቃው ሥነ ሥርዓት የተካሄደው ሐምሌ 19, 1953 ኒው ዮርክ በሚገኘው በያንኪ ስታዲየም ሲሆን እኔም ከአይዳ ካንዱሶ (በኋላ አይዳ ሳኒዮቦስ ሆናለች) ጋር በፓሪስ እንዳገለግል ተመደብኩ። ሃብታም ለሆኑት የፓሪስ ነዋሪዎች መስበክ የሚያስፈራ ቢሆንም ትሑት የሆኑ በርካታ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ችያለሁ። በ1956 አይዳ አግብታ ወደ አፍሪካ የሄደች ሲሆን እኔ ግን እዛው ፓሪስ ቆየሁ።

በ1960 በቤቴል ያገለግል የነበረ ወንድም ካገባሁ በኋላ አብረን ሾመን እና ቪሺ በተባሉት ከተሞች በልዩ አቅኚነት ማገልገል ጀመርን። ከአምስት ዓመት በኋላ የሳንባ ነቀርሳ ስለያዘኝ አቅኚነቴን ማቆም ግድ ሆነብኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል እንዲሁም እስከ መጨረሻው በዚህ አገልግሎት የመቀጠል ግብ ስለነበረኝ በጣም አዘንኩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ባለቤቴ ሌላ ሴት ወድዶ ጥሎኝ ሄደ። በእነዚያ አስጨናቂ ዓመታት የመንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ድጋፍና እርዳታ አልተለየኝም። ይሖዋም ሸክሜን ሁሉ ተሸክሞልኛል።—መዝ. 68:19

በአሁኑ ጊዜ የምኖረው በሉቭዬ፣ ኖርመንዲ ሲሆን ከፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ ብዙም አይርቅም። የጤና ችግር ቢኖርብኝም የይሖዋን እጅ በሕይወቴ በማየቴ ደስተኛ ነኝ። በልጅነቴ ያገኘሁት ሥልጠና አሁንም እንኳ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ወላጆቼ፣ ይሖዋ እውን ሆኖ እንዲታየኝ ረድተውኛል፤ ልወደውና ላነጋግረው የምችል እንዲሁም ለጸሎቴ መልስ የሚሰጠኝ አምላክ እንደሆነ እንድተማመን አድርገውኛል። በእርግጥም ‘ስለ ዋለልኝ ውለታ ሁሉ፣ ለይሖዋ ምን እከፍለዋለሁ?’—መዝ. 116:12

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የይሖዋን እጅ በሕይወቴ በማየቴ ደስተኛ ነኝ”

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስድስት ዓመቴ የጋዝ መከላከያ ይዤ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ16 ዓመቴ ከሚስዮናውያንና ከአቅኚዎች ጋር በልዩ የስብከት ዘመቻ ላይ ለመካፈል ሉክሰምበርግ በሄድኩበት ጊዜ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1953 ከእናቴና ከአባቴ ጋር በአውራጃ ስብሰባ ላይ