በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በነጠላነት ሕይወት ደስተኛ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

በነጠላነት ሕይወት ደስተኛ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

በነጠላነት ሕይወት ደስተኛ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

“ከዚያም ተጋቡና በደስታ ኖሩ።” የልጆች የተረት መጻሕፍት አብዛኛውን ጊዜ የሚደመደሙት በዚህ መንገድ ነው። የፍቅር ፊልሞችና ልቦለድ መጻሕፍትም ብዙውን ጊዜ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል መልእክት ያስተላልፋሉ፤ አንድ ሰው እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ትዳር መመሥረት አለበት የሚል አንድምታ አላቸው! ከዚህም በላይ በብዙ ባሕሎች ውስጥ ለማግባት የደረሱ ሰዎች ትዳር እንዲመሠርቱ ጫና ይደረግባቸዋል። ዴቢ በ20ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ እያለች እንዲህ ስትል ተናግራ ነበር፦ “ሰዎች፣ አንዲት ሴት በሕይወቷ ውስጥ ዋነኛ ግቧ ትዳር መመሥረት እንደሆነ እንዲሰማችሁ ያደርጓችኋል። አንድ ሰው መኖር የሚጀምረው ካገባ በኋላ ነው የሚል አመለካከት ያንጸባርቃሉ።”

መንፈሳዊ የሆነ ሰው ለነገሮች ያለው አመለካከት ከላይ ከተገለጸው የተለየ ነው። አብዛኞቹ እስራኤላውያን ትዳር ይመሠርቱ የነበረ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያረካ ሕይወት ስላሳለፉ ያላገቡ ወንዶችና ሴቶች ይናገራል። በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሳያገቡ ለመኖር የመረጡ ሲሆን ሌሎች በርካታ ክርስቲያኖች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ሳያገቡ ቀርተዋል። አንድ ሰው ነጠላ ሆኖ እንዲኖር ያደረገው ምክንያት ምንም ይሁን ምን አንድ ወሳኝ ጥያቄ ይነሳል፦ አንድ ክርስቲያን ነጠላነት ያለውን ጥሩ ጎን በተሻለ መንገድ ሊጠቀምበት የሚችለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ አላገባም ነበር፤ ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር ይህን ያደረገበትን ምክንያት ለመረዳት አያዳግትም። አንዳንድ ተከተዮቹም ነጠላነትን ‘ተቀብለው’ መኖር እንደሚችሉ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 19:10-12) ኢየሱስ፣ ነጠላነት ያለውን ጥሩ ጎን በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ከፈለግን አእምሯችንም ሆነ ልባችን እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት ሊቀበለው እንደሚገባ ገልጿል።

ኢየሱስ የሰጠው ምክር የሚሠራው በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ በሙሉ ለማተኮር ሲሉ በዓላማ የነጠላነትን ሕይወት ለመረጡ ሰዎች ብቻ ነው? (1 ቆሮ. 7:34, 35) እንደዚያ ማለት አይደለም። ለማግባት ቢፈልጉም እስካሁን ድረስ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ማግኘት ያልቻሉ ክርስቲያኖችን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው አና የተባለች ያላገባች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በቅርብ ጊዜ፣ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ሳላስበው የጋብቻ ጥያቄ አቀረበልኝ። በዚያ ወቅት በተወሰነ መጠን ብደሰትም ወዲያውኑ ስሜቴን ተቆጣጠርኩት፤ ማግባት የምፈልገው ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድቀርብ የሚረዳኝን ሰው ብቻ ነው።”

እንደ አና ሁሉ በርካታ እህቶችም “በጌታ” ለማግባት ስለሚፈልጉ የማያምን ሰው ከማግባት ይቆጠባሉ። * (1 ቆሮ. 7:39፤ 2 ቆሮ. 6:14) አምላክ ለሰጠው ምክር አክብሮት ስላላቸው ተስማሚ የትዳር ጓደኛ እስኪያገኙ ድረስ ሳያገቡ ለመኖር ወስነዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ነጠላነት ያለውን ጥሩ ጎን በተሻለ መንገድ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው?

ነጠላነት ባለው ጥሩ ጎን ላይ አተኩሩ

ሁኔታዎች እንደምንፈልገው ባይሆኑም አመለካከታችንን ማስተካከላችን ያለንበትን ሁኔታ ተቀብለን ለመኖር በእጅጉ ይረዳናል። በ40ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ካርመን የተባለች ያላገባች እህት “ባለኝ ነገር እደሰታለሁ፤ የሌለኝን ነገር ለማግኘት አልጓጓም” ብላለች። አንዳንድ ጊዜ በብቸኝነት ስሜት ልንዋጥ አሊያም ልናዝን እንደምንችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚያጋጥማቸው ማወቃችን በልበ ሙሉነት ወደፊት እንድንገፋ ያበረታታናል። በርካታ ክርስቲያኖች ነጠላነት ያለውን ጥሩ ጎን በተሻለ መንገድ እንዲጠቀሙበትና የሚያጋጥሟቸውን ሌሎች ችግሮች መቋቋም እንዲችሉ ይሖዋ ረድቷቸዋል።—1 ጴጥ. 5:9, 10

ብዙ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ሳያገቡ መኖር ጠቃሚ ጎን እንዳለው ተገንዝበዋል። በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ ኤስተር የተባለች ያላገባች እህት እንደሚከተለው ብላለች፦ “ያላችሁበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ደስተኛ ለመሆን ቁልፉ የሁኔታውን ጥሩ ጎን መመልከት መቻላችሁ እንደሆነ ይሰማኛል። ትዳር ኖረኝም አልኖረኝ በሕይወቴ ውስጥ ከአምላክ መንግሥት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ እስከሰጠሁ ድረስ ይሖዋ መልካም ነገር እንደማይነፍገኝ አምናለሁ።” (መዝ. 84:11) አክላም “በሕይወቴ ውስጥ የምመኘውን ነገር ማግኘት አልቻልኩ ይሆናል። ያም ቢሆን ደስተኛ ነኝ፤ ወደፊትም ደስተኛ ሆኜ እኖራለሁ” ብላለች።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሳያገቡ የኖሩ ሰዎች

የዮፍታሔ ልጅ ሳታገባ የመኖር ሐሳብ አልነበራትም። ይሁንና አባቷ የተሳለውን ስዕለት ለመፈጸም ስትል ከወጣትነቷ ጀምሮ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ስታገለግል ኖራለች። እንዲህ ያለው ያልተጠበቀ ሁኔታ፣ በሕይወቷ ለማከናወን ያሰበቻቸውን ነገሮች እንድትለውጥ እንዳደረጋትና ከተፈጥሯዊ ፍላጎቷ ጋር የሚጋጭ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። አግብታ ቤተሰብ መመሥረት እንደማትችል ስታውቅ ለሁለት ወራት ያህል አልቅሳለች። ያም ቢሆን አዲሱን ሁኔታዋን በመቀበል በቀሪው ሕይወቷ አምላክን በፈቃደኝነት አገልግላለች። እንዲህ ያለ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በማሳየቷ ሌሎች እስራኤላውያን ሴቶች በየዓመቱ “ያመሰግኗት” (NW) ነበር።—መሳ. 11:36-40

በኢሳይያስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ጃንደረባ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች በደረሰባቸው ሁኔታ ሳያዝኑ አልቀሩም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እነዚህ ሰዎች ጃንደረባ የሆኑት በምን ምክንያት እንደሆነ አይናገርም። እነዚህ ሰዎች ወደ ይሖዋ ጉባኤ መግባትም ሆነ አግብተው ልጅ መውለድ አይችሉም ነበር። (ዘዳ. 23:1) ያም ቢሆን ይሖዋ ስሜታቸውን የሚረዳላቸው ከመሆኑም በላይ ለቃል ኪዳኑ በሙሉ ነፍስ በመታዘዛቸው አመስግኗቸዋል። ይሖዋ በቤቱ “መታሰቢያና . . . ለዘላለም፣ የማይጠፋ ስም” እንደሚሰጣቸው ነግሯቸዋል። በሌላ አባባል እነዚህ ታማኝ ጃንደረቦች በኢየሱስ መሲሐዊ አገዛዝ ሥር የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ የተረጋገጠ ተስፋ አላቸው። ይሖዋ ፈጽሞ አይረሳቸውም።—ኢሳ. 56:3-5

የኤርምያስ ሁኔታ ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነበር። አምላክ ለኤርምያስ የነቢይነት ተልዕኮ ከሰጠው በኋላ ሳያገባ እንዲኖር አዘዘው፤ ይሖዋ ይህን ትእዛዝ የሰጠው ኤርምያስ የኖረበት ዘመን በጣም አስጨናቂ ስለሆነና የተሰጠው ተልዕኮ ከባድ ስለነበር ነው። ይሖዋ ኤርምያስን “በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይኑሩህ” ብሎት ነበር። (ኤር. 16:1-4) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኤርምያስ እንዲህ ያለ መመሪያ ሲሰጠው ምን እንደተሰማው የሚናገረው ነገር የለም፤ ይሁንና ነቢዩ በይሖዋ ቃል የሚደሰት ሰው እንደነበረ ይገልጻል። (ኤር. 15:16) ከጊዜ በኋላ ኤርምያስ ኢየሩሳሌም ለ18 ወራት በተከበበችበት ወቅት የነበረውን አሰቃቂ ሁኔታ ሲመለከት ሳያገባ እንዲኖር ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ መታዘዙ የጥበብ አካሄድ መሆኑን እንደተገነዘበ ምንም ጥርጥር የለውም።—ሰቆ. 4:4, 10

ሕይወታችሁ ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ማድረግ የምትችሉባቸው መንገዶች

ከላይ የተመለከትናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ትዳር ባይመሠርቱም የይሖዋ ድጋፍ አልተለያቸውም፤ እነሱም አምላክን በማገልገል ራሳቸውን አስጠምደው ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ ሕይወታችን ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ለማድረግ ጠቃሚ በሆኑ እንቅስቃሴዎች መጠመድ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ምሥራቹን የሚያውጅ ታላቅ የሴቶች ሠራዊት እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል። (መዝ. 68:11 የ1980 ትርጉም) ይህ ሠራዊት በሺዎች የሚቆጠሩ ያላገቡ እህቶችንም ይጨምራል። ብዙ ነጠላ እህቶች አገልግሎታቸው ፍሬ በማፍራቱ በመንፈሳዊ ሁኔታ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በማግኘት ተባርከዋል።—ማር. 10:29, 30፤ 1 ተሰ. 2:7, 8

ለ14 ዓመታት በአቅኚነት ስታገለግል የቆየችው ሎሊ እንዲህ ብላለች፦ “አቅኚነት ሕይወቴ አቅጣጫ እንዲይዝ ረድቶኛል። ያላገባሁ ክርስቲያን ብሆንም ራሴን በሥራ ማስጠመዴ ብቸኝነት እንዳይሰማኝ አስችሎኛል። በአገልግሎቴ ለሰዎች ከፍተኛ እርዳታ እንደማበረክት ማወቄ በየዕለቱ ውስጣዊ እርካታና ጥልቅ ደስታ እንዳገኝ ያደርገኛል።”

በርካታ እህቶች አዲስ ቋንቋ ተምረው የሌላ አገር ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች በመስበክ አገልግሎታቸውን ማስፋት ችለዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አና “በምኖርበት ከተማ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የሌላ አገር ዜጎች ይገኛሉ” ብላለች። አና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች ምሥራቹን መስበክ ያስደስታታል። እንዲህ ብላለች፦ “ከአብዛኞቹ ሰዎች ጋር ለመግባባት የሚያስችለኝን ቋንቋ መማሬ አዲስ የአገልግሎት መስክ የከፈተልኝ በመሆኑ የስብከቱ ሥራ በጣም አስደሳች እንዲሆንልኝ አድርጓል።”

አብዛኛውን ጊዜ ያላገቡ ሰዎች ብዙ የቤተሰብ ኃላፊነት ስለሌለባቸው አንዳንዶቹ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ማገልገል ችለዋል። በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ ሊዲያና የምትባል ያላገባች እህት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው አገሮች ስታገለግል ቆይታለች። ይህች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ በተካፈላችሁ መጠን የቅርብ ወዳጆች ማፍራትና የሚወዷችሁ ሰዎች ማግኘት ቀላል እንደሚሆን አምናለሁ። የተለያየ አስተዳደግና ዜግነት ያላቸው በርካታ የቅርብ ጓደኞች አፍርቻለሁ፤ እንዲህ ያለው ወዳጅነት ደግሞ ሕይወቴ ይበልጥ ትርጉም እንዲኖረው አስችሎኛል።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ትንቢት የሚናገሩ አራት ያላገቡ ሴቶች ልጆች ስለነበሩት ፊልጶስ የሚባል ወንጌላዊ ይናገራል። (ሥራ 21:8, 9) የፊልጶስ ልጆች እንደ አባታቸው ለአገልግሎታቸው ቅንዓት የነበራቸው ክርስቲያኖች ሳይሆኑ አይቀሩም። ትንቢት የመናገር ስጦታቸውን በመጠቀም በቂሳርያ የሚገኙትን የእምነት ባልጀሮቻቸውን አበረታትተው ይሆን? (1 ቆሮ. 14:1, 3) በዛሬው ጊዜም በርካታ ያላገቡ እህቶች አዘውትረው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና ተሳትፎ በማድረግ ሌሎችን ያበረታታሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ በጥንቷ ፊልጵስዩስ ትኖር የነበረችው ሊዲያ የተባለች ክርስቲያን፣ እንግዳ ተቀባይ በመሆኗ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመስግናለች። (ሥራ 16:14, 15, 40) ሊዲያ ያላገባች ወይም ባሏ የሞተባት ሴት ሳትሆን አትቀርም፤ ይህች ክርስቲያን በጣም ለጋስ ስለነበረች እንደ ጳውሎስ፣ ሲላስና ሉቃስ ያሉ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን በማስተናገዷ ተጠቅማለች። ዛሬም እንዲህ ያለ መንፈስ ማንጸባረቅ ተመሳሳይ በረከት ያስገኛል።

የመወደድ ፍላጎታችንን ማርካት

ሁላችንም ብንሆን በሕይወታችን ውስጥ ትርጉም ያለው ሥራ ከማከናወን በተጨማሪ ሌሎች እንዲወዱን እንፈልጋለን። ያላገቡ ሰዎች ይህን ፍላጎታቸውን እንዴት ማርካት ይችላሉ? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ ሁልጊዜም እንደሚወደን፣ እንደሚያበረታታንና ሊያዳምጠን ዝግጁ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ንጉሥ ዳዊት አንዳንድ ጊዜ ‘የብቸኝነትና የጭንቀት’ ስሜት ይሰማው የነበረ ቢሆንም ምንጊዜም ከይሖዋ እርዳታ ማግኘት እንደሚችል ያውቅ ነበር። (መዝ. 25:16፤ 55:22) ‘አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ ይሖዋ ይቀበለኛል’ በማለት ጽፏል። (መዝ. 27:10) አምላክ ሁሉም አገልጋዮቹ ወደ እሱ እንዲቀርቡና ወዳጆቹ እንዲሆኑ ግብዣ አቅርቧል።—መዝ. 25:14፤ ያዕ. 2:23፤ 4:8

ከዚህም በተጨማሪ በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ የሚወዱንና ሕይወታችን ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርጉ መንፈሳዊ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች ማግኘት እንችላለን። (ማቴ. 19:29፤ 1 ጴጥ. 2:17) በርካታ ያላገቡ ክርስቲያኖች “መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት [ትታወቅ]” የነበረችውን የዶርቃን ምሳሌ በመከተላቸው ከፍተኛ እርካታ አግኝተዋል። (ሥራ 9:36, 39) ሎሊ እንዲህ ብላለች፦ “የትም አካባቢ ብሄድ፣ የሚወዱኝና በሚከፋኝ ወቅት የሚደግፉኝ እውነተኛ ጓደኞች በጉባኤ ውስጥ ለማግኘት እጥራለሁ። እንዲህ ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር ለሌሎች ፍቅርና አሳቢነት ለማሳየት ጥረት አደርጋለሁ። በተለያዩ ጊዜያት በስምንት ጉባኤዎች ውስጥ ያገለገልኩ ሲሆን በሁሉም ቦታዎች እውነተኛ ወዳጆች ማፍራት ችያለሁ። ብዙውን ጊዜ ወዳጅነት የመሠረትኩት እኩዮቼ ከሆኑ እህቶች ጋር አይደለም፤ አንዳንዶቹ አያቶች ሌሎቹ ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው።” በሁሉም ጉባኤዎች ውስጥ ፍቅር ማግኘትና ወዳጅነት መመሥረት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። እንደነዚህ ላሉ ሰዎች ልባዊ አሳቢነት በማሳየት ልንረዳቸው የምንችል ከመሆኑም ሌላ እኛም የመውደድም ሆነ የመወደድ ፍላጎታችንን ማርካት እንችላለን።—ሉቃስ 6:38

አምላክ አይረሳም

የምንኖረው አስጨናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ በመሆኑ ሁሉም ክርስቲያኖች የተለያዩ መሥዋዕቶችን መክፈል እንደሚኖርባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ቆሮ. 7:29-31) ክርስቲያኖች በጌታ ብቻ እንዲያገቡ የሚያዘውን መለኮታዊ መመሪያ ለማክበር ሲሉ ሳያገቡ ለሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች፣ ለየት ያለ አክብሮት ልንሰጣቸው ብሎም አሳቢነት ልናሳያቸው እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም። (ማቴ. 19:12) እነዚህ ክርስቲያኖች ለሚከፍሉት መሥዋዕትነት መደነቅ አለባቸው ሲባል ግን በሕይወታቸው ውስጥ እውነተኛ ደስታ ማግኘት አይችሉም ማለት አይደለም።

ሊዲያና እንዲህ ብላለች፦ “ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት በመመሥረቴና እሱን በማገልገሌ የሚያረካ ሕይወት መምራት ችያለሁ። አንዳንድ ያገቡ ሰዎች በትዳራቸው ደስተኛ ሲሆኑ ሌሎች ግን በትዳራቸው እንደማይደሰቱ ተመልክቻለሁ። ይህን ሐቅ ማወቄ፣ ደስተኛ መሆኔ የተመካው ወደፊት ትዳር በመመሥረቴ ላይ እንዳልሆነ እንዳምን አድርጎኛል።” ኢየሱስ እንደተናገረው ደስታ ማግኘታችን በዋነኝነት የተመካው በመስጠትና ሌሎችን በማገልገል ላይ ነው፤ ይህን ደግሞ ሁሉም ክርስቲያኖች ሊያደርጉት ይችላሉ።—ዮሐ. 13:14-17፤ ሥራ 20:35

ይሖዋ የእሱን ፈቃድ ለማድረግ ስንል ማንኛውንም መሥዋዕት ብንከፍል እንደሚባርከን ማወቃችን ከምንም በላይ እንደሚያስደስተን ጥርጥር የለውም። አምላክ “የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዕብ. 6:10

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 እዚህ ላይ የተጠቀሱት ክርስቲያን እህቶች ቢሆኑም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለወንድሞችም ይሠራል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ባለኝ ነገር እደሰታለሁ፤ የሌለኝን ነገር ለማግኘት አልጓጓም።”—ካርመን

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሎሊ እና ሊዲያና የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች በማገልገላቸው ደስተኞች ናቸው

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ሁሉም አገልጋዮቹ ወደ እሱ እንዲቀርቡ ግብዣ አቅርቧል