“ከሁሉ የላቀውን” የፍቅርን መንገድ ለመከተል ጥረት ታደርጋለህ?
“ከሁሉ የላቀውን” የፍቅርን መንገድ ለመከተል ጥረት ታደርጋለህ?
“አምላክ ፍቅር ነው።” ሐዋርያው ዮሐንስ የተናገረው ይህ ሐሳብ ከአምላክ ባሕርያት መካከል ዋነኛውን ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (1 ዮሐ. 4:8) ወደ አምላክ ለመቅረብና ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስቻለን፣ አምላክ ለሰው ዘር ያሳየው ፍቅር ነው። የአምላክ ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት ሌላው መንገድስ ምንድን ነው? “ለአንድ ነገር ያለን ፍቅር ማንነታችንን ይቀርጸዋል” የሚል አባባል አለ። ይህ አባባል በሌላ መንገድም እውነት ሆኖ እናገኘዋለን፤ ለሌሎች ያለን ፍቅርና እነሱ ለእኛ ያላቸው ፍቅርም ማንነታችንን ይቀርጸዋል። የተፈጠርነው በአምላክ መልክ በመሆኑ የእሱን ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ የማንጸባረቅ ችሎታ አለን። (ዘፍ. 1:27) በመሆኑም ሐዋርያው ዮሐንስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ አምላክ “አስቀድሞ ስለወደደን” እኛም በበኩላችን እንደምንወደው ገልጿል።—1 ዮሐ. 4:19
ፍቅርን ለመግለጽ የተሠራባቸው አራት ቃላት
ሐዋርያው ጳውሎስ ፍቅርን ‘ከሁሉ የላቀው መንገድ’ በማለት ጠርቶታል። (1 ቆሮ. 12:31) ጳውሎስ ፍቅርን በዚህ መንገድ የገለጸው ለምን ነበር? የተናገረውስ ስለ ምን ዓይነት ፍቅር ነበር? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት “ፍቅር” የሚለውን ቃል ትርጉም በጥልቀት እንመርምር።
የጥንቶቹ ግሪኮች ፍቅርን ለመግለጽ በተለያየ መንገድ የሚሠራባቸውን አራት መሠረታዊ ቃላት ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን እነሱም ስቶርጌ፣ ኤሮስ፣ ፊሊያ እና አጋፔ ናቸው። ከእነዚህ ቃላት መካከል “ፍቅር” የሆነውን አምላክ ለማመልከት የተሠራበት አጋፔ የሚለው ቃል ነው። * ይህንን የፍቅር ዓይነት በተመለከተ ፕሮፌሰር ዊልያም ባርክሌይ፣ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “አጋፔ ከአእምሮ ጋር የተያያዘ ነገር ነው፤ ሳናስበው በልባችን ውስጥ የሚፈጠር ስሜት ሳይሆን አስበንበት በሕይወታችን ውስጥ የምንመራበት መሠረታዊ ሥርዓት ነው። አጋፔ በፈቃዳችን የምናዳብረው ፍቅር ነው።” አጋፔ በዚህ አገባቡ በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ፍቅርን ያመለክታል፤ ያም ቢሆን ብዙውን ጊዜ ጥልቅ ከሆነ ስሜት ጋር የተያያዘ ነው። ይሁንና ሰዎች የሚመሩባቸው መልካምም ሆኑ መጥፎ መሠረታዊ ሥርዓቶች ስላሉ ክርስቲያኖች ይሖዋ አምላክ ራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በገለጻቸው መልካም መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት እንደሚኖርባቸው የታወቀ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አጋፔ የተገለጸበትን መንገድ ፍቅርን ለመግለጽ ከተሠራባቸው ሌሎች ቃላት ጋር ማወዳደራችን ልናንጸባርቀው የሚገባንን ፍቅር ይበልጥ ለመረዳት ያስችለናል።
በቤተሰብ መካከል የሚኖረው ፍቅር
ፍቅርና አንድነት ባለው ቤተሰብ ውስጥ መኖር እንዴት የሚያስደስት ነው! ስቶርጌ አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ቤተሰብ አባላት መካከል ያለውን ተፈጥሯዊ ፍቅር ለማመልከት ይሠራበት የነበረ የግሪክኛ ቃል ነው። ክርስቲያኖች በቤተሰባቸው *—2 ጢሞ. 3:1, 3
መካከል ያለው ፍቅር እንዳይጠፋ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። ጳውሎስ በመጨረሻዎቹ ቀኖች አብዛኞቹ ሰዎች “ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተናግሯል።በቤተሰብ አባላት መካከል ሊኖር የሚገባው ተፈጥሯዊ ፍቅር በዛሬው ጊዜ እየጠፋ መሆኑ ያሳዝናል። በርካታ ነፍሰ ጡር ሴቶች ውርጃ የሚፈጽሙት ለምንድን ነው? ብዙ ቤተሰቦች በዕድሜ ለገፉ ወላጆቻቸው አሳቢነት የማያሳዩት ለምንድን ነው? የፍቺ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ያለውስ ለምንድን ነው? ሰዎች ተፈጥሯዊ ፍቅር በማጣታቸው እንደሆነ ምንም አያጠያይቅም።
ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው” ይላል። (ኤር. 17:9) ለቤተሰባችን ያለን ፍቅር ከልባችን የሚመነጭ ሲሆን ስሜትንም ይጨምራል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ አንድ ባል ለሚስቱ ሊኖረው የሚገባውን ፍቅር ለመግለጽ አጋፔ በሚለው ቃል መጠቀሙ ትኩረት የሚስብ ነው። ጳውሎስ አንድ ባል ለሚስቱ ሊኖረው የሚገባውን ፍቅር ክርስቶስ ለጉባኤው ካሳየው ፍቅር ጋር አመሳስሎታል። (ኤፌሶን 5:28, 29) ይህ ዓይነቱ ፍቅር የቤተሰብ መሥራች የሆነው ይሖዋ ባስቀመጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ነው።
ለቤተሰባችን አባላት እውነተኛ ፍቅር ማዳበራችን በዕድሜ ለገፉ ወላጆቻችን አሳቢነት እንድናሳይ ወይም ልጆቻችንን የማሳደግ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ይገፋፋናል። ከዚህም በተጨማሪ ወላጆች አጋፔን በማዳበር ስቶርጌ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ማድረጋቸው፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በፍቅር ተነሳስተው ለልጆቻቸው ተግሣጽ እንዲሰጡ ያነሳሳቸዋል፤ እንዲሁም ለልጆቻቸው ተገቢ ያልሆነ አዘኔታ በማሳየት ልጆቻቸውን መረን ከመልቀቅ እንዲቆጠቡ ይረዳቸዋል።—ኤፌ. 6:1-4
በተቃራኒ ጾታዎች መካከል ያለው ፍቅርና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች
በተጋቡ ወንድና ሴት መካከል ያለው ፍቅር በእርግጥም ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው። (ምሳሌ 5:15-17) ያም ቢሆን በመንፈስ መሪነት መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች፣ በተቃራኒ ጾታ መካከል ያለውን ፍቅር የሚያመለክተውን ኤሮስ የሚለውን ቃል አልተጠቀሙበትም። ለምን? ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚከተለው ሐሳብ ወጥቶ ነበር፦ “በዛሬው ጊዜ መላው ዓለም የጥንቶቹ ግሪኮች የፈጸሙትን ስሕተት እየደገመው ያለ ይመስላል። የጥንቶቹ ግሪኮች ኤሮስን እንደ አምላክ ያመልኩት፣ በመሠዊያው ፊት ይሰግዱ እንዲሁም መሥዋዕት ያቀርቡለት ነበር። . . . ይሁን እንጂ ታሪክ እንደሚያሳየው ለጾታ የሚሰጠው እንዲህ ያለው አምልኮ፣ ወራዳ ድርጊትና መረን የለቀቀ አኗኗር እንዲስፋፋ እንዲሁም የሥነ ምግባር ደንቦች እንዲፈራርሱ ከማድረግ ውጪ ያስገኘው ነገር የለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ኤሮስ የሚለውን ቃል ያልተጠቀሙበት ለዚህ ሊሆን ይችላል።” እኛም ከተቃራኒ ጾታ ጋር የምንመሠርተው ጓደኝነት በውጫዊ መልክ ላይ ብቻ ያተኮረ እንዳይሆን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተውን ፍቅር በማዳበር ለተቃራኒ ጾታ ያለን የፍቅር ስሜት ሚዛኑን እንዲጠብቅ ማድረግ ይኖርብናል። ስለዚህ ‘ለትዳር ጓደኛዬ ወይም ለጋብቻ ለምጠናናው ሰው ያለኝ የፍቅር ስሜት በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ።
አብዛኛውን ጊዜ የጾታ ስሜት በሚያይልበት ‘በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ’ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሙጥኝ ማለታቸው በሥነ ምግባር ንጹሖች ሆነው እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። (1 ቆሮ. 7:36፤ ቆላ. 3:5) ጋብቻን ከይሖዋ አምላክ የተገኘ ቅዱስ ስጦታ እንደሆነ አድርገን እንመለከተዋለን። ኢየሱስ ባለትዳሮችን አስመልክቶ ሲናገር “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ብሏል። (ማቴ. 19:6) ከትዳር ጓደኛችን ጋር አብረን የምንኖረው በግለሰቡ ላይ የሚማርከን ነገር እስካለ ድረስ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የጋብቻ ቃል ኪዳናችንን በቁም ነገር እንመለከተዋለን። በትዳር ውስጥ ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ በቀላሉ የምንገላገልበት መንገድ ከመፈለግ ይልቅ የቤተሰባችን ሕይወት አስደሳች እንዲሆን አምላካዊ ባሕርያትን ለማሳየት ልባዊ ጥረት እናደርጋለን። እንዲህ ያለ ጥረት ማድረጋችን ዘላቂ የሆነ ደስታ ያስገኝልናል።—ኤፌ. 5:33፤ ዕብ. 13:4
በጓደኛሞች መካከል ያለው ፍቅር
ጓደኞች ባይኖሩን ሕይወት እንዴት አሰልቺ ይሆን ነበር! አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛም አለ” ይላል። (ምሳሌ 18:24) ይሖዋ እውነተኛ ወዳጆች እንዲኖሩን ይፈልጋል። በዳዊትና በዮናታን መካከል የነበረው የጠበቀ ወዳጅነት በብዙዎች ዘንድ የታወቀ ነው። (1 ሳሙ. 18:1) ኢየሱስ፣ ሐዋርያው ዮሐንስን “ይወደው” እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዮሐ. 20:2) በጓደኞች መካከል ያለውን “ፍቅር” ወይም “ወዳጅነት” የሚያመለክተው የግሪክኛ ቃል ፊሊያ ነው። በጉባኤ ውስጥ የቅርብ ጓደኞች ቢኖሩን ምንም ስሕተት የለውም። ይሁንና 2 ጴጥሮስ 1:7 “በወንድማዊ መዋደድ” (ፊላደልፊያ) ላይ ፍቅርን (አጋፔን) እንድንጨምር ያበረታታናል፤ (ፊላደልፊያ የሚለው ቃል ፊሎስ እና አዴልፖስ የሚሉት ቃላት ጥምረት ነው፤ ፊሎስ የሚለው ቃል በግሪክኛ “ወዳጅ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን አዴልፖስ የሚለው ቃል ደግሞ “ወንድም” የሚል ትርጉም አለው።) ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት ለመመሥረት ይህንን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ‘ለጓደኞቼ ያለኝ ፍቅር ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ነው?’ በማለት ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው።
የአምላክ ቃል ከጓደኞቻችን ጋር ባለን ግንኙነት አድሎ እንዳናደርግ ይረዳናል። ለጓደኞቻችን ሲሆን ልል፣ ጓደኞቻችን ባልሆኑት ላይ ደግሞ ጥብቅ በመሆን ሁለት ዓይነት አቋም አንይዝም። ከዚህም በላይ ጓደኞች ለማፍራት ስንል ሰዎችን አንሸነግልም። ከሁሉ በላይ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋላችን፣ ጓደኞችን በምንመርጥበት ጊዜ አስተዋዮች እንድንሆን እንዲሁም ‘መልካሙን አመል ከሚያበላሹ መጥፎ ጓደኞች’ ጋር ከመግጠም እንድንቆጠብ ይረዳናል።—1 ቆሮ. 15:33
ልዩ የሆነ ፍቅር!
ክርስቲያኖች አንድነት እንዲኖራቸው የሚያደርጋቸው ፍቅር በእርግጥም ልዩ ነው! ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅራችሁ ግብዝነት የሌለበት ይሁን። . . . በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ” ሲል ጽፏል። (ሮም 12:9, 10) በእውነትም በክርስቲያኖች መካከል ያለው ‘ፍቅር (አጋፔ) ግብዝነት የሌለበት’ ነው። ይህ ዓይነቱ ፍቅር በስሜት ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ የሚመራ ነው። አክሎም ጳውሎስ ‘ስለ ወንድማማች ፍቅር’ (ፊላደልፊያ) እና ‘ከልብ ስለ መዋደድ’ (ፊሎስቶርጎስ) ተናግሯል፤ (ፊሎስቶርጎስ የሚለው ቃል ፊሎስ እና ስቶርጌ የሚሉት ቃላት ጥምረት ነው።) አንድ ምሑር እንደተናገሩት ‘የወንድማማች ፍቅር’ ሲባል “አሳቢነት የተሞላበት ፍቅርን፣ ደግነትና ርኅራኄ ማሳየትን እንዲሁም እርዳታ ማድረግን” ያመለክታል። እንዲህ ያለው ፍቅር ከአጋፔ ጋር ሲጣመር በይሖዋ አምላኪዎች መካከል የቀረበ ወዳጅነት እንዲኖር ያስችላል። (1 ተሰ. 4:9, 10) “ከልብ ተዋደዱ” ተብሎ የተተረጎመው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን በቤተሰብ ውስጥ ያለውን ዓይነት በጣም የተቀራረበ ግንኙነት ያመለክታል።
እውነተኛ ክርስቲያኖች አንድነት እንዲኖራቸው ያደረገው፣ ቤተሰባዊ ፍቅርና በእውነተኛ ወዳጆች መካከል ያለው ዓይነት ፍቅር በመካከላቸው መኖሩ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚመራው ፍቅር ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው። የክርስቲያን ጉባኤ፣ ሰዎች ከሌሎች ጋር ለመቀራረብ የሚሰባሰቡበት ክበብ ወይም ሰዎች ያቋቋሙት ድርጅት ሳይሆን በይሖዋ አምልኮ አንድ የሆነ በጣም የሚቀራረብ ቤተሰብ ነው። ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር እንደ አንድ ቤተሰብ አባላት የምንተያይ ሲሆን እርስ በርስ ወንድም እና እህት እየተባባልን እንጠራራለን። የእምነት ባልንጀሮቻችን የመንፈሳዊው ቤተሰባችን አባላት ናቸው፤ እንደ ጓደኛ እንወዳቸዋለን እንዲሁም ከእነሱ ጋር ያለን ግንኙነት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ነው። እንግዲያው ሁላችንም እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ አንድነት እንዲኖረውና ከሌሎች ተለይቶ እንዲታወቅ የሚያደርገው ፍቅር እያደገ እንዲሄድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረጋችንን እንቀጥል።—ዮሐ. 13:35
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 አጋፔ ለመጥፎ ነገሮች ፍቅር ማሳደርን ለማመልከትም ተሠርቶበታል።—ዮሐ. 3:19፤ 12:43፤ 2 ጢሞ. 4:10፤ 1 ዮሐ. 2:15-17
^ አን.7 “ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” የሚለው ሐረግ የተገኘው ስቶርጌ ከሚለው ቃል ሲሆን ቃሉ ኤ የሚል አሉታዊ መልእክት የሚያስተላልፍ ቅጥያ ከፊቱ ተጨምሮበታል፤ ኤ የሚለው የግሪክኛ ቅጥያ “የሌለው” የሚል ትርጉም አለው።—ሮም 1:31ንም ተመልከት።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንድነት እንዲኖረን የሚያደርገው ፍቅር እያደገ እንዲሄድ አስተዋጽኦ የምታበረክተው እንዴት ነው?