በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዘጠና ዓመት በፊት ‘ፈጣሪዬን ማሰብ’ ጀመርኩ

ከዘጠና ዓመት በፊት ‘ፈጣሪዬን ማሰብ’ ጀመርኩ

ከዘጠና ዓመት በፊት ‘ፈጣሪዬን ማሰብ’ ጀመርኩ

ኤድዊን ሪጅዌል እንደተናገረው

ኅዳር 11, 1918 ጦርነት ለማቆም ስምምነት በተደረገበት ቀን፣ የታላቁን ጦርነት (በኋላ አንደኛው የዓለም ጦርነት ተብሏል) ማብቃት ምክንያት በማድረግ ደስታቸውን ለመግለጽ በትምህርት ቤታችን ያሉት ልጆች ሳይታሰብ እንዲሰባሰቡ ተደረገ። በወቅቱ የአምስት ዓመት ልጅ ስለነበርኩ ምን እየተከናወነ እንዳለ ሙሉ በሙሉ አልገባኝም። ያም ሆኖ ወላጆቼ ስለ አምላክ ካስተማሩኝ ነገር አንጻር በዚህ ሥነ ሥርዓት መካፈል እንደሌለብኝ ተሰምቶኝ ነበር። ስለዚህ ወደ አምላክ ጸለይኩ፤ ይሁንና ስሜቴን መቆጣጠር ስላልቻልኩ ማልቀስ ጀመርኩ። በሥነ ሥርዓቱ ግን አልተካፈልኩም። ‘ፈጣሪዬን ማሰብ’ የጀመርኩት በዚያ ጊዜ ነበር።—መክ. 12:1

በትምህርት ቤታችን እንዲህ ያለው ሁኔታ ከመከሰቱ ከጥቂት ወራት በፊት ቤተሰባችን ስኮትላንድ በምትገኘው በግላስጎው ከተማ አቅራቢያ መኖር ጀምሮ ነበር። በዚህ ጊዜ አካባቢ አባቴ “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” በሚል ርዕስ የቀረበ አንድ የሕዝብ ንግግር አዳምጦ ነበር። ያዳመጠው ነገር በሕይወቱ ላይ ትልቅ ለውጥ አመጣ። አባቴና እናቴ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመሩ ሲሆን ስለ አምላክ መንግሥት እንዲሁም ወደፊት ስለሚመጡት በረከቶች አዘውትረው ይወያዩ ነበር። ወላጆቼ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለአምላክ ፍቅር እንዲኖረኝና በእሱ ላይ እንድታመን ስላሠለጠኑኝ አምላክን አመሰግነዋለሁ።—ምሳሌ 22:6

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ

አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል የሚያበቃ ውጤት የነበረኝ ቢሆንም እኔ ግን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል በጣም እፈልግ ነበር። አባቴ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ዕድሜዬ ገና እንደሆነ ስለተሰማው ለተወሰነ ጊዜ ያህል በቢሮ ውስጥ እሠራ ጀመር። ይሁንና ይሖዋን በሙሉ ጊዜ የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ በወቅቱ የስብከቱን ሥራ በበላይነት ይከታተል ለነበረው ለወንድም ራዘርፎርድ ደብዳቤ በመጻፍ ስላወጣሁት ዕቅድ ምን እንደሚሰማው ጠየቅሁት። ወንድም ራዘርፎርድ እንዲህ በማለት ጻፈልኝ፦ “ዕድሜህ ለሥራ ከደረሰ በጌታ አገልግሎት ለመካፈልም ብቁ ነህ። . . . ጌታን በታማኝነት ለማገልገል ጥረት ካደረግህ እንደሚባርክህ አምናለሁ።” መጋቢት 10, 1928 የተጻፈው ይህ ደብዳቤ በቤተሰባችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳደረ። ብዙም ሳይቆይ እኔን ጨምሮ አባቴ፣ እናቴና ታላቅ እህቴ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርን።

በ1931 በለንደን በተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ወንድም ራዘርፎርድ ወደ ሌላ አገር ሄደው ምሥራቹን ለመስበክ ፈቃደኛ የሆኑ ወንድሞች እንደሚያስፈልጉ የሚገልጽ ጥሪ አቀረበ። እኔም ፈቃደኛ መሆኔን ስገልጽ አንድሪው ጃክ ከተባለ ወንድም ጋር የሊትዌኒያ ዋና ከተማ በነበረችው በካውናስ እንድናገለግል ተመደብን። በወቅቱ 18 ዓመቴ ነበር።

የመንግሥቱን መልእክት በሌላ አገር መስበክ

በዚያ ወቅት በሊትዌኒያ አብዛኛው ሕዝብ የሚተዳደረው በግብርና ሲሆን አገሪቷም ድህነት የተንሰራፋባት ነበረች፤ በገጠራማው አካባቢ ማገልገል ተፈታታኝ ነበር። መኖሪያ ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ ሲሆን ያረፍንባቸውን አንዳንዶቹን ቦታዎች መቼም ቢሆን አንረሳቸውም። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሌሊት እኔና አንድሪው ለመተኛት ስለተቸገርን ተነስተን ኩራዛችንን ስናበራ አልጋውን ተባይ እንደወረሰው ተመለከትን። ከእግር እስከ ራሳችን መላ ሰውነታችን በተባይ ተበልቶ ነበር! ከዚያ በኋላ ሳምንቱን ሙሉ ጠዋት ጠዋት በአቅራቢያችን ወደሚገኝ ወንዝ በመሄድ ሥቃዩን ለማስታገስ ቀዝቃዛው ውኃ ውስጥ እስከ አንገቴ ድረስ እነከር ነበር። ያም ሆኖ በአገልግሎታችን ለመቀጠል ቆርጠን ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ወጣቶች የሆኑ አንድ ባልና ሚስት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲቀበሉ የመኖሪያ ቤት ችግራችን ተቀረፈ። እነዚህ ባልና ሚስት ጠባብ ብትሆንም ንጹሕ በሆነችው ቤታቸው ውስጥ እንድንኖር ፈቀዱልን። ከተባዮቹ በመገላገላችን በጣም ስለተደሰትን ምንም ቅር ሳይለን መሬት ላይ አንጥፈን እንተኛ ነበር!

በዚያን ጊዜ በሊትዌኒያ የሮም ካቶሊክና የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቀሳውስት ከፍተኛ ተደማጭነት ነበራቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የመግዛት አቅም ያላቸው ሀብታሞች ብቻ ነበሩ። እኛም ዋናው ዓላማችን በተቻለን መጠን ብዙ ክልሎችን መሸፈንና ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ በርካታ ጽሑፎችን ማበርከት ነበር። ወደ አንድ ከተማ ስንገባ መጀመሪያ ማረፊያ እንፈልጋለን። ከዚያም ከከተማዋ ወጣ ብለው የሚገኙ አካባቢዎችን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ከሸፈንን በኋላ በከተማዋ ውስጥ ያሉትን ቤቶች በፍጥነት እናዳርሳለን። በዚህ መንገድ አብዛኛውን ጊዜ የአካባቢው ቀሳውስት ችግር ከመፍጠራቸው በፊት ሥራችንን እናጠናቅቃለን።

ችግር በመፈጠሩ ሕዝቡ ስለ ሥራችን አወቀ

በ1934 አንድሪው በካውናስ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንዲያገለግል ሲመደብ ጆን ሴምፔ የአገልግሎት ጓደኛዬ ሆነ። ከጆን ጋር ያሳለፍናቸው የማይረሱ ትዝታዎች አሉን። አንድ ቀን በአንዲት ትንሽ ከተማ ውስጥ የሚኖር የሕግ ባለሞያ አነጋገርኩ። ሰውየው በቁጣ ገንፍሎ ከመሳቢያው ውስጥ ሽጉጡን በማውጣት ከቢሮው እንድወጣ አዘዘኝ። በዚህ ወቅት በልቤ የጸለይኩ ሲሆን “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አስታወስኩ። (ምሳሌ 15:1) ከዚያም ሰውየውን “የመጣሁት ወዳጃዊ በሆነ መንገድ አንድ ምሥራች ልነግርህ ነው፤ አንተም ስሜትህን ስለተቆጣጠርክ አመሰግንሃለሁ” አልኩት። በዚህ ጊዜ ሰውየው ጣቱን ከቃታው ላይ ቀስ ብሎ አነሳው፤ እኔም ወደኋላዬ እየተራመድኩ ቢሮውን ለቅቄ ወጣሁ።

ከጆን ጋር ስንገናኝ እሱም የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሞት እንደነበር ነገረኝ። ጆን ካነጋገራት ሴት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሰርቀሃል በሚል በሐሰት ተወንጅሎ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ ነበር። እዚያም ልብሱን አስወልቀው ፈተሹት። እርግጥ ገንዘቡን እሱ እንዳልወሰደው ግልጽ ነው። በኋላ ላይ ፖሊሶች የሴትየዋን ገንዘብ የሰረቀውን ሰው ያዙት።

ብዙም እንቅስቃሴ በማይታይባት በዚያች ከተማ ውስጥ የተከሰቱት እነዚህ ሁለት አጋጣሚዎች ግርግር እንዲፈጠር ያደረጉ ሲሆን ይህም ሰዎች ስለ ሥራችን እንዲያውቁ አጋጣሚ ከፍቷል!

በሚስጥር የምናከናውነው ሥራ

እኔና ጆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን የስብከቱ ሥራችን ወደታገደባት ወደ ላትቪያ እናስገባ የነበረ ሲሆን ይህም አደገኛ ሥራ ነበር። በወር አንድ ጊዜ፣ ጎረቤት አገር ወደሆነችው ወደ ላትቪያ ምሽት ላይ በሚጓዘው ባቡር ተሳፍረን እንሄድ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ጽሑፎቹን ላትቪያ ካደረስን በኋላ ወደ ኢስቶኒያ ጉዟችንን በመቀጠል ተጨማሪ ጽሑፎች ይዘን ወደ ላትቪያ እንመለሳለን፤ እዚያም ጽሑፎቹን ለወንድሞች ሰጥተን ወደ ሊትዌኒያ ጉዟችንን እንቀጥላለን።

በአንድ ወቅት አንድ የጉምሩክ ፖሊስ ስለምናከናውነው ሥራ ጥቆማ ደርሶት ስለነበር ከባቡሩ ወርደን ጽሑፎቻችንን አለቃው ቢሮ እንድንወስድ አዘዘን። እኔና ጆን ይሖዋ እንዲረዳን ጸለይን። የሚገርመው ፖሊሱ ለአለቃው ምን እንደያዝን ሳይነግረው “እነዚህ ሰዎች የሚያስመዘግቡት ዕቃ ይዘዋል” አለው። እኔም በትምህርት ቤቶችም ሆነ በኮሌጅ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በችግር በተሞላው ዓለማችን እየተከናወኑ ያሉት ነገሮች ምን ትርጉም እንዳላቸው እንዲገነዘቡ የሚረዳ ጽሑፍ እንደያዝኩ በመግለጽ ዕቃውን “አስመዘገብኩ።” የጉምሩክ ባለሥልጣኑ እንድናልፍ ስለፈቀደልን ጽሑፎቻችንን በሰላም ማድረስ ቻልን።

በባልካን አገሮች የፖለቲካው ሁኔታ እየተባባሰ ሲሄድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ይበልጥ ይቃወሙ ጀመር፤ በሊትዌኒያም የስብከቱ ሥራችን ታገደ። አንድሪውና ጆን ከአገር ተባረሩ፤ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሆነ የሚጠቁሙ ሁኔታዎች ስለነበሩ የብሪታንያ ዜጎች በሙሉ ከሊትዌኒያ እንዲወጡ ተነገራቸው። እኔም እያዘንኩ አገሪቷን ለቅቄ ወጣሁ።

በሰሜን አየርላንድ ያገኘኋቸው መብቶችና በረከቶች

በዚህ ወቅት ወላጆቼ ወደ ሰሜን አየርላንድ ተዛውረው ስለነበር እኔም በ1937 ወደዚያ ሄድኩ። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሰፈነው አለመረጋጋት የተነሳ በሰሜን አየርላንድም ጽሑፎቻችን ታግደው ነበር፤ ቢሆንም ጦርነቱ በተካሄደባቸው ዓመታት በሙሉ መስበካችንን አላቋረጥንም። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እገዳው ስለተነሳ የስብከቱን ሥራችንን እንደገና በነፃነት ማከናወን ቻልን። ሃሮልድ ኪንግ የተባለ ተሞክሮ ያካበተ አቅኚ ከቤት ውጪ የሕዝብ ንግግር መስጠትን ያበረታታና ያደራጅ ነበር፤ ይህ ወንድም ከጊዜ በኋላ በቻይና ሚስዮናዊ ሆኖ አገልግሏል። ወንድም ሃሮልድ “የፊታችን ቅዳሜ ከቤት ውጪ የሚደረገውን የመጀመሪያውን የሕዝብ ንግግር እኔ አቀርባለሁ” ካለ በኋላ ወደ እኔ እየተመለከተ “አንተ ደግሞ በሚቀጥለው ቅዳሜ ታቀርባለህ” አለኝ። ይህን ስሰማ በጣም ደነገጥሁ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረብኩትን ንግግር በደንብ አስታውሰዋለሁ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ንግግሩን ለማዳመጥ መጥተው ነበር። ንግግሩን ያቀረብኩት አንድ ሣጥን ላይ ቆሜ ሲሆን የድምፅ መሣሪያም አልነበረም። ንግግሩ ሲያበቃ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ ከጨበጠኝ በኋላ ቢል ስሚዝ እንደሚባል ነገረኝ። በርካታ ሰዎች ተሰብስበው ሲመለከት ምን እየተከናወነ እንደሆነ ለማወቅ እንደመጣ ገለጸልኝ። ከዚያ ቀደም አባቴ አነጋግሮት የነበረ ቢሆንም አባቴና እንጀራ እናቴ አቅኚዎች ሆነው ወደ ደብሊን ሲሄዱ ከቢል ጋር ያላቸው ግንኙነት ተቋረጠ። ቢልን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመርኩ። ከጊዜ በኋላ ከቤተሰቡ አባላት መካከል ዘጠኙ የይሖዋ አገልጋዮች ሆነዋል።

በቤልፋስት ዙሪያ በሚገኙት ትላልቅ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ሳገለግል በሊትዌኒያ ትኖር የነበረች ሩሲያዊት ሴት አገኘሁ። ለዚህች ሴት አንዳንድ ጽሑፎችን ሳሳያት ወደ አንዱ መጽሐፍ በመጠቆም “ይህ መጽሐፍ አለኝ። መጽሐፉን የሰጠኝ በካውናስ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ፕሮፌሰር የሆነው አጎቴ ነው” አለችኝ። ከዚያም በፖላንድ ቋንቋ የተዘጋጀውን ክርኤሽን የተባለውን መጽሐፍ አሳየችኝ። በመጽሐፉ ኅዳግ ላይ ብዙ ማስታወሻ ተጽፎበት ነበር። ሴትየዋ፣ በካውናስ እያለሁ ይህንን መጽሐፍ ለአጎቷ የሰጠሁት እኔ እንደነበርኩ ስታውቅ በጣም ተገረመች!—መክ. 11:1

ጆን ሴምፔ፣ ወደ ሰሜን አየርላንድ እንደምሄድ ሲሰማ ኔሊ የተባለችው ታናሽ እህቱ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ስላላት እንዳነጋግራት ጠይቆኝ ነበር። ከእህቴ ከኮኒ ጋር ሆነን መጽሐፍ ቅዱስን አስጠናናት። ኔሊ ፈጣን እድገት በማድረግ ራሷን ለይሖዋ ወሰነች። ከጊዜ በኋላ ከኔሊ ጋር መጠናናት ጀመርን፤ ከዚያም ተጋባን።

እኔና ኔሊ ለ56 ዓመታት አብረን ይሖዋን ያገለገልን ሲሆን ከመቶ የሚበልጡ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቁ የመርዳት መብት አግኝተናል። አርማጌዶንን አብረን በማለፍ ይሖዋ በሚያዘጋጀው አዲስ ሥርዓት ውስጥ ለመኖር ተስፋ አድርገን ነበር፤ ሆኖም ጨካኙ ጠላታችን ሞት በ1998 ኔሊን ነጠቀኝ። በሕይወቴ ውስጥ ካጋጠሙኝ መከራዎች ሁሉ ከባዱ ይህ ነበር፤ ሐዘኑ በጣም ጎድቶኛል።

ወደ ባልቲክ አገሮች ተመለስኩ

ኔሊ ከሞተች ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ አስደናቂ የሆነ በረከት አገኘሁ። በታሊን፣ ኢስቶኒያ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ እንድጎበኝ ግብዣ ቀረበልኝ። በኢስቶኒያ የሚገኙት ወንድሞች የጻፉልኝ ደብዳቤ እንዲህ ይላል፦ “በ1920ዎቹ መጨረሻና በ1930ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በባልቲክ አገሮች እንዲያገለግሉ ተመድበው ከነበሩት አሥር ወንድሞች መካከል በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያለኸው አንተ ብቻ ነህ።” ደብዳቤው ቅርንጫፍ ቢሮው በሊትዌኒያ፣ በላትቪያና በኢስቶኒያ ስለተከናወነው ሥራ የሚገልጽ ታሪካዊ ዘገባ ለማዘጋጀት ማቀዱን ከገለጸ በኋላ “መምጣት ትችላለህ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

እኔና የአገልግሎት ጓደኞቼ በእነዚያ ዓመታት ያጋጠሙንን ተሞክሮዎች መናገር እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! በላትቪያ ለቅርንጫፍ ቢሮ እንጠቀምበት የነበረውን የመጀመሪያውን ቤት እንዲሁም ጽሑፎቻችንን እንደብቅበት የነበረውን ከጣሪያው በታች ያለውን ቦታ ለወንድሞች አሳየኋቸው፤ ጽሑፎቻችንን የምንደብቅበትን ቦታ ፖሊሶች ጨርሶ አላገኙትም። በሊትዌኒያ አቅኚ ሆኜ ወዳገለገልኩባት ሻዉላ የተባለች ትንሽ ከተማ ወንድሞች ወሰዱኝ። በዚያም ከወንድሞች ጋር ተሰባስበን እያለ አንድ ወንድም እንዲህ አለኝ፦ “ከዓመታት በፊት እኔና እናቴ ከተማ ውስጥ ቤት ገዛን። ከጣሪያው በታች ያለውን ቦታ ስናጸዳ መለኮታዊው የዘመናት እቅድ እና የአምላክ በገና የተባሉትን መጻሕፍት አገኘሁ። እነዚህን መጻሕፍት ሳነባቸው እውነትን እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ። ከበርካታ ዓመታት በፊት መጻሕፍቱን እዚያ የተውካቸው አንተ ሳትሆን አትቀርም!”

አቅኚ ሆኜ ባገለገልኩባት አንዲት ከተማ ውስጥ በተካሄደ የወረዳ ስብሰባ ላይም መገኘት ችያለሁ። ከ65 ዓመት በፊት በዚህች ከተማ ውስጥ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ በተገኘሁበት ወቅት የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር 35 ነበር። አሁን ከ1,500 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች እንደተገኙ ስመለከት በጣም ተደሰትኩ! በእርግጥም ይሖዋ ሥራውን ባርኮታል!

‘ይሖዋ አልተወኝም’

በቅርቡ ደግሞ ጨርሶ ያልተጠበቀ ሌላ በረከት አገኘሁ። ቢ የተባለች አንዲት ደስ የምትል እህት ለጋብቻ ያቀረብኩላትን ጥያቄ ስለተቀበለችኝ ኅዳር 2006 ተጋባን።

በሕይወቱ ውስጥ ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያስብ ማንኛውም ወጣት፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ምክር በተግባር ማዋሉ የጥበብ አካሄድ እንደሆነ ላረጋግጥለት እወዳለሁ። አሁን እኔም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰው መዝሙራዊ በደስታ እንደሚከተለው ማለት እችላለሁ፦ “አምላክ ሆይ፤ አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እኔም እስከ ዛሬ ድረስ ድንቅ ሥራህን ዐውጃለሁ። አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ፤ ክንድህን ለመጭው ትውልድ፣ ኀይልህን ኋላ ለሚነሣ ሕዝብ ሁሉ፣ እስከምገልጽ ድረስ።”—መዝ. 71:17, 18

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ወደ ላትቪያ ጽሑፎች መውሰድ አደገኛ ሥራ ነበር

ኢስቶኒያ

ታሊን

የሪጋ ባሕረ ሰላጤ

ላትቪያ

ሪጋ

ሊትዌኒያ

ቪልኒየስ

ካውናስ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ15 ዓመቴ በስኮትላንድ ኮልፖርተር (አቅኚ) ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1942 ከኔሊ ጋር በሠርጋችን ቀን