በምድር ላይ ለዘላለም መኖር—እንደገና የታወቀ ተስፋ
በምድር ላይ ለዘላለም መኖር—እንደገና የታወቀ ተስፋ
“ዳንኤል ሆይ፤ አንተ ግን፣ እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ የመጽሐፉን ቃል ዝጋ፤ . . . ብዙዎች ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ፤ ዕውቀትም ይበዛል።”—ዳን. 12:4
1, 2. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገረው ተስፋ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ እንዳለው በግልጽ ተረድተዋል። (ራእይ 7:9, 17) አምላክ፣ ሰዎች የተፈጠሩት ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ኖረው እንዲሞቱ ሳይሆን ለዘላለም እንዲኖሩ እንደነበር የገለጸው በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ ነበር።—ዘፍ. 1:26-28
2 እስራኤላውያን በተስፋ ሲጠባበቋቸው ከኖሩት ነገሮች መካከል የሰው ዘር አዳም ያጣውን ፍጽምና መልሶ እንደሚያገኝ የሚናገረው ተስፋ ይገኝበታል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ አምላክ የሰው ልጆች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ የሚያደርገው በምን መንገድ እንደሆነ ይገልጻሉ። ታዲያ ይህ የሰው ልጆች ተስፋ እንደገና መታወቅ አስፈልጎታል የምንለው ለምንድን ነው? ይህ ተስፋ ወደ ብርሃን የመጣውና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሊያውቁት የቻሉትስ እንዴት ነው?
ተሰውሮ የነበረ ተስፋ
3. በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገረው የሰው ልጆች ተስፋ መሰወሩ የማያስደንቀን ለምንድን ነው?
3 ኢየሱስ ሐሰተኛ ነቢያት እሱ ያስተማረውን ትምህርት እንደሚበርዙትና ብዙ ሰዎች እንደሚሳሳቱ አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴ. 24:11) ሐዋርያው ጴጥሮስም ክርስቲያኖችን “በእናንተም መካከል ሐሰተኛ አስተማሪዎች ይነሳሉ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (2 ጴጥ. 2:1) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “[ሰዎች] ጤናማውን ትምህርት የማይታገሡበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ከራሳቸው ፍላጎት ጋር በሚስማማ ሁኔታ ጆሯቸውን እንዲኮረኩሩላቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።” (2 ጢሞ. 4:3, 4) ሰዎችን በዋነኝነት የሚያሳስተው ሰይጣን፣ አምላክ ለምድርና ለሰዎች ስላለው ዓላማ የሚናገረውን አስደሳች እውነት ለመሰወር ከሃዲ በሆኑ የክርስትና ሃይማኖቶች ሲጠቀም ኖሯል።—2 ቆሮንቶስ 4:3, 4ን አንብብ።
4. ከሃዲ የሆኑት ሃይማኖታዊ መሪዎች ገሸሽ ያደረጉት የትኛውን የሰው ልጆች ተስፋ ነው?
4 ቅዱሳን መጻሕፍት የአምላክ መንግሥት በሰማይ የተቋቋመ መስተዳድር እንደሆነ እንዲሁም ይህ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ እንደሚያደቅና እስከ መጨረሻውም እንደሚያጠፋቸው ይናገራሉ። (ዳን. 2:44) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ሰይጣን በጥልቁ ውስጥ ይታሰራል፤ ሙታን ይነሳሉ እንዲሁም የሰው ዘር ፍጽምና አግኝቶ በምድር ላይ ይኖራል። (ራእይ 20:1-3, 6, 12፤ 21:1-4) ይሁንና ከሃዲ የሆኑት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ከዚህ የተለዩ ጽንሰ ሐሳቦችን የተቀበሉ ሲሆን እነዚህንም በትምህርቶቻቸው ውስጥ አካትተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረውና የቤተ ክርስቲያን አባት የነበረው የእስክንድሪያው ኦሪጀን፣ በሺው ዓመት ግዛት ወቅት በምድር ላይ ብዙ በረከቶች እንደሚኖሩ የሚያምኑ ሰዎችን አውግዟል። የሮም ካቶሊክ ሃይማኖታዊ ምሑር የሆነው የሂፖው ኦገስቲን (354-430 ዓ.ም.) “ወደፊት የሺህ ዓመት ግዛት አይኖርም የሚለውን አመለካከት ይደግፍ” እንደነበር ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ገልጿል። *
5, 6. ኦሪጀንም ሆነ ኦገስቲን ወደፊት የሺህ ዓመት ግዛት እንደሚመጣ የሚገልጸውን እውነት ያልተቀበሉት ለምንድን ነው?
5 ኦሪጀንም ሆነ ኦገስቲን ወደፊት የሺህ ዓመት ግዛት እንደሚመጣ የሚገልጸውን እውነት ያልተቀበሉት ለምንድን ነው? ኦሪጀን የእስክንድሪያው ክሌመንት ተማሪ የነበረ ሲሆን ክሌመንት የማትሞት ነፍስ አለች የሚለውን የግሪክ ፍልስፍና የሚከተል ሰው ነበር። ፕላቶ ስለ ነፍስ ያለው አመለካከት ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮበት የነበረው ኦሪጀን “ነፍስን በተመለከተ ከፕላቶ የወሰዳቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ትምህርቶች በክርስትና መሠረተ ትምህርት ውስጥ [ማስገባቱን]” የሃይማኖት ምሑር የሆኑት ቨርነር ዬገር ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ኦሪጀን በሺው ዓመት ግዛት ወቅት የሚገኘው በረከት
ቃል በቃል በምድር ላይ የሚፈጸም ሳይሆን በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ የሚፈጸም መሆኑን አስተምሯል።6 ኦገስቲን በ33 ዓመቱ ወደ “ክርስትና” ከመለወጡ በፊት ኒኦፕላቶኒዚም የተባለ ፍልስፍና አራማጅ ሆኖ ነበር፤ ፕላቶ ያመነጨውን የኒኦፕላቶኒዝምን ጽንሰ ሐሳብ ያዳበረው በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረው ፕሎቲነስ ነው። ኦገስቲን ወደ “ክርስትና” ከተቀየረም በኋላ የኒኦፕላቶኒዝምን ፍልስፍና መከተሉን አልተወም ነበር። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደገለጸው “በኦገስቲን አእምሮ ውስጥ የአዲስ ኪዳኑ ሃይማኖትና የግሪክ ፍልስፍና የሆነው የፕላቶ እምነት ፍጹም የሆነ ውሕደት ፈጥረው ነበር።” ኦገስቲን በራእይ ምዕራፍ 20 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የሺህ ዓመት ግዛት “ምሳሌያዊ ፍቺ በመስጠት እንዳብራራው” ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ገልጿል። ኢንሳይክሎፒዲያው በማከል እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ማብራሪያ ከዚያ በኋላ በተነሱት ምዕራባውያን የሃይማኖት ምሑራን ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ የሺው ዓመት ግዛትን በተመለከተ ቀደም ሲል ይታመንበት የነበረው አስተሳሰብ ተሰሚነት አጣ።”
7. በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገረው የሰው ልጆች ተስፋ እየተሸረሸረ እንዲመጣ ያደረገው የትኛው የሐሰት ትምህርት ነው? እንዴትስ?
7 ሰዎች ወደፊት በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ የሚገልጸው ተስፋ፣ በጥንቷ ባቢሎን በሰፊው ይታመንበት በነበረውና በመላው ዓለም በተስፋፋው ‘በሰው አካል ውስጥ የማይሞት ነፍስ ወይም መንፈስ አለ’ በሚለው ጽንሰ ሐሳብ መሸርሸር ጀምሮ ነበር። ሕዝበ ክርስትና ይህን አስተሳሰብ ስትቀበል የሃይማኖት ምሑራን ስለ ሰማያዊ ተስፋ የሚናገሩትን ጥቅሶች ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ የሚያስተምሩ እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጣመም ጀመሩ። እንደ እነሱ አመለካከት ከሆነ አንድ ሰው በምድር ላይ የሚያሳልፈው ሕይወት ጊዜያዊ ነው፤ በሌላ አባባል ግለሰቡ በምድር ላይ እንዲኖር የተደረገው ለሰማያዊ ሕይወት ብቁ መሆን አለመሆኑን ለመፈተን ነው። በምድር ላይ ለዘላለም መኖርን በተመለከተ አይሁዳውያን ከጥንት ጀምሮ በነበራቸው አመለካከት ላይም ተመሳሳይ ለውጥ ተከስቶ ነበር። አይሁዳውያን ነፍስ አትሞትም የሚለውን የግሪካውያንን እምነት ቀስ በቀስ እየተቀበሉ ሲሄዱ ቀደም ሲል ያምኑበት የነበረው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እየደበዘዘ መጣ። ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነት መጽሐፍ ቅዱስ ሰውን በተመለከተ ከሚናገረው ሐሳብ ምንኛ የተለየ ነው! ሰው ሥጋዊ እንጂ መንፈሳዊ ፍጡር አይደለም። ይሖዋ ለመጀመሪያው ሰው “ዐፈር ነህ” ብሎታል። (ዘፍ. 3:19) የሰው ልጅ ዘላለማዊ መኖሪያ ምድር እንጂ ሰማይ አይደለም።—መዝሙር 104:5 እና 115:16ን አንብብ።
በጨለማ ውስጥ የፈነጠቀ የእውነት ብርሃን
8. በ1600ዎቹ ዓመታት የኖሩ አንዳንድ ምሑራን ስለ ሰው ዘር የወደፊት ተስፋ ምን ብለዋል?
8 ክርስቲያን ነን የሚሉ በርካታ ሃይማኖቶች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለ የማያስተምሩ ቢሆንም ሰይጣን እውነትን ለመሰወር ያደረገው ጥረት ሙሉ በሙሉ አልተሳካለትም። በታሪክ ዘመናት ሁሉ የእውነት ብልጭታዎችን መመልከት የቻሉ ጥቂት ሰዎች ነበሩ፤ መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ይመረምሩ የነበሩት እነዚህ ሰዎች አምላክ የሰው ዘር ያጣውን ፍጽምና መልሶ እንዲያገኝ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ በተወሰነ ደረጃ መረዳት ችለው ነበር። (መዝ. 97:11፤ ማቴ. 7:13, 14፤ 13:37-39) በ1600ዎቹ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቋንቋዎች መተርጎሙና መታተሙ ቅዱሳን መጻሕፍት በብዛት እንዲሰራጩ አስችሏል። አንድ ምሑር በ1651 እንደጻፉት፣ ሰዎች በአዳም ምክንያት “ገነትንና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚያቸውን ያጡ” በመሆኑ በክርስቶስ በኩል “ሁሉም ሰው በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖር መደረግ አለበት፤ አለበለዚያ [በሁለቱ መካከል] የቀረበው ንጽጽር ተገቢ አይሆንም።” (1 ቆሮንቶስ 15:21, 22ን አንብብ።) በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ ታዋቂ ከሆኑት ባለቅኔዎች አንዱ የሆነው ጆን ሚልተን (1608-1674) ፓራዳይዝ ሎስት (የጠፋችው ገነት) እና ፓራዳይዝ ሪጌይንድ (ዳግም የተቋቋመችው ገነት) የተባሉትን ተከታታይ መጻሕፍት ለሕትመት አብቅቶ ነበር። ሚልተን በጽሑፎቹ ላይ ታማኝ የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ስለሚያገኙት በረከት ገልጿል። ሚልተን አብዛኛውን ሕይወቱን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ቢያሳልፍም ክርስቶስ እስከሚገኝበት ጊዜ ድረስ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማይቻል ተገንዝቦ ነበር።
9, 10. (ሀ) አይዛክ ኒውተን የሰውን ዘር የወደፊት ተስፋ አስመልክቶ ምን ጽፏል? (ለ) ኒውተን፣ ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ የሚገኘው ከብዙ ዘመናት በኋላ እንደሆነ ያስብ የነበረው ለምንድን ነው?
9 ታዋቂ የሒሳብ ሊቅ የሆነው ሰር አይዛክ ኒውተን (1642-1727) ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ፍቅር ነበረው። ኒውተን፣ ቅዱሳኑ ሰማያዊ ሕይወት ለማግኘት ከሙታን እንደሚነሱና በማይታይ ሁኔታ ከክርስቶስ ጋር እንደሚገዙ ተረድቶ ነበር። (ራእይ 5:9, 10) የመንግሥቱን ተገዢዎች አስመልክቶ ሲጽፍ “ከፍርድ ቀን በኋላ ምድር ለ1000 ዓመት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም የሰዎች መኖሪያ ትሆናለች” ብሏል።
10 ኒውተን ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ የሚገኘው ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ እንደሚሆን ያስብ ነበር። ስቲቨን ስኖቤለን የተባሉት የታሪክ ምሑር እንዲህ ብለዋል፦ “ኒውተን፣ የአምላክ መንግሥት የሚመጣው ከብዙ ዘመናት በኋላ እንደሆነ እንዲያምን ያደረገው አንዱ ምክንያት በወቅቱ የሥላሴ አማኞች በሚያስፋፉት ሥር የሰደደ የክህደት ትምህርት ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ የነበረው መሆኑ ነው።” በዚያን ወቅት ምሥራቹ ገና ያልታወቀ ሲሆን ኒውተንም ምሥራቹን የሚሰብክ የክርስቲያኖች ቡድን እንደሌለ አስተውሎ ነበር። “የዳንኤል ትንቢትና ዮሐንስ የተናገራቸው [በራእይ መጽሐፍ ላይ ተመዝግበው የሚገኙት] ትንቢቶች የመጨረሻው ዘመን እስኪመጣ ድረስ ግልጽ ሊሆኑ እንደማይችሉ” ኒውተን ጽፏል። እሱ ራሱ ይህን ያለበትን ምክንያት ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “ዳንኤል እንደተናገረው ‘በዚያን ዘመን ብዙዎች ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ፤ ዕውቀትም ይበዛል።’ ምክንያቱም ታላቁ መከራና የዓለም መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት ወንጌል ለሁሉም ብሔራት መሰበክ አለበት። ታላቁን መከራ አልፈው የመጡትና የዘንባባ ዝንጣፊ በእጆቻቸው የያዙት በርካታ ሰዎች፣ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡና አንድም ሰው ሊቆጥራቸው እስከማይችል ድረስ ብዙ እንዲሆኑ ከተፈለገ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ወንጌል ሊሰበክላቸው ይገባል።”—ዳን. 12:4፤ ማቴ. 24:14፤ ራእይ 7:9, 10
11. ሚልተን እና ኒውተን በኖሩበት ዘመን የሰው ልጆች ተስፋ ለአብዛኞቹ ሰዎች ተሰውሮባቸው የነበረው ለምንድን ነው?
11 ሚልተንና ኒውተን በኖሩበት ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከምታስተምረው ትምህርት የተለየ ነገር መናገር አደገኛ ነበር። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ካደረጓቸው ምርምሮች ጋር በተያያዘ ያዘጋጇቸው አብዛኞቹ ጽሑፎች እነሱ እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ ለኅትመት አልበቁም። በ16ኛው መቶ ዘመን የተካሄደው ሃይማኖታዊ ተሃድሶ የማትሞት ነፍስ አለች በሚለው ትምህርት ላይ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም፤ ዋና ዋናዎቹ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የሺው ዓመት ግዛት ያለፈ ታሪክ እንጂ ወደፊት የሚመጣ ነገር እንዳልሆነ የሚናገረውን የኦገስቲንን ትምህርት ማስተማራቸውን ቀጥለዋል። ታዲያ በመጨረሻው ዘመን እውቀት ጨምሯል?
ትክክለኛው “ዕውቀትም ይበዛል”
12. ትክክለኛው እውቀት የበዛው መቼ ነው?
12 ዳንኤል ‘በፍጻሜው ዘመን’ መልካም ነገር እንደሚከናወን አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ዳንኤል 12:3, 4, 9, 10ን አንብብ።) ኢየሱስ “በዚያ ጊዜ ጻድቃን . . . እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 13:43) ታዲያ በፍጻሜው ዘመን ትክክለኛው እውቀት የበዛው እንዴት ነው? የፍጻሜው ዘመን ከጀመረበት ከ1914 በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት የታዩትን አንዳንድ ታሪካዊ እድገቶች እስቲ እንመልከት።
13. ቻርልስ ቴዝ ራስል የሰው ልጆች አዳም ያሳጣቸውን ፍጽምና እንደገና ከማግኘታቸው ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ካጠና በኋላ ምን በማለት ጽፏል?
13 በ1800ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ ቅን ልብ ያላቸው ጥቂት ግለሰቦች ‘የጤናማ ቃላትን ንድፍ’ ለመረዳት ምርምር ማድረግ ጀመሩ። (2 ጢሞ. 1:13) ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ቻርልስ ቴዝ ራስል ነበር። በ1870 እሱና ሌሎች እውነትን የተጠሙ ጥቂት ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አቋቋሙ። በ1872 ደግሞ የሰው ልጆች አዳም ያሳጣቸውን ፍጽምና እንደገና ከማግኘታቸው ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማጥናት ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ ራስል እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “አሁን እየተፈተነች ያለችው ቤተ ክርስቲያን [የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ] በምታገኘው ሽልማትና ታማኝ የሆኑት የሰው ልጆች በሚያገኙት ሽልማት መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት እስከዚህ ጊዜ ድረስ በግልጽ መረዳት አልቻልንም ነበር።” ታማኝ የሆኑት የሰው ልጆች የሚያገኙት ሽልማት “የመጀመሪያው ወላጃቸውና ቅድመ አያታቸው የሆነው አዳም በኤደን ገነት ሳለ የነበረው ዓይነት ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት መልሰው ማግኘት ነው።” ራስል መጽሐፍ ቅዱስን በሚያጠናበት ወቅት ሌሎች ሰዎችም እንደረዱት በግልጽ ተናግሯል። እነዚህ ሰዎች እነማን ነበሩ?
14. (ሀ) ሄንሪ ደን፣ የሐዋርያት ሥራ 3:21ን የተረዳው እንዴት ነበር? (ለ) ሄንሪ ደን፣ በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩት እነማን እንደሆኑ ተናግሯል?
ሥራ 3:21) ሄንሪ ደን፣ ይህ መታደስ በክርስቶስ ሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የሰው ልጆች በምድር ላይ የሚያገኙትን ፍጽምና እንደሚያካትት ተገንዝቦ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ‘በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩት እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?’ ለሚለው በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ሲጉላላ ለቆየው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ምርምር አድርጎ ነበር። ሄንሪ ደን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት እንደሚነሱና እውነትን እንደሚማሩ እንዲሁም በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት በተግባር የሚያሳዩበት አጋጣሚ እንደሚያገኙ አብራርቷል።
14 ሄንሪ ደን ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። ሄንሪ ደን ‘አምላክ በጥንቶቹ ቅዱሳን ነቢያቱ አፍ ስለተናገረው ስለ ሁሉም ነገር መታደስ’ ጽፏል። (15. ጆርጅ ስቶርዝ ስለ ትንሣኤ ምን ነገር አስተውሎ ነበር?
15 በተጨማሪም በ1870 ጆርጅ ስቶርዝ ኃጢአተኞች ከሞት ተነስተው የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል ወደሚል መደምደሚያ ደርሶ ነበር። በተጨማሪም ትንሣኤ ያገኘ አንድ ሰው በዚህ አጋጣሚ የማይጠቀም ከሆነ “‘ይህ ኃጢአተኛ አንድ መቶ ዓመት’ ቢሆነውም እንኳ በሞት እንደሚቀሠፍ” ከቅዱሳን መጻሕፍት መረዳት ችሎ ነበር። (ኢሳ. 65:20 የ1954 ትርጉም) በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ይኖር የነበረው ጆርጅ ስቶርዝ ባይብል ኤግዛሚነር የተባለ መጽሔት ያሳትም ነበር።
16. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ከሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች የተለዩ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምን ነበር?
16 ወንድም ራስል፣ ምሥራቹ በሰፊው የሚታወጅበት ጊዜ መድረሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተረድቶ ነበር። በመሆኑም በ1879 በዛሬው ጊዜ የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ ተብሎ የሚታወቀውን የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ የተባለውን መጽሔት ማሳተም ጀመረ። ከዚያ ቀደም፣ ስለ ሰው ልጆች ተስፋ የሚናገረውን እውነት የተረዱት በጣም ጥቂት ሰዎች ነበሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን በበርካታ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ያቀፉ ቡድኖች መጠበቂያ ግንብ የማግኘት አጋጣሚ ስለነበራቸው ይህን መጽሔት ማጥናት ቻሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ወደ ሰማይ የሚሄዱት ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑና የተቀሩት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት አግኝተው በምድር ላይ እንደሚኖሩ በሚገልጸው እውነት ማመናቸው ከአብዛኛዎቹ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች የተለዩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
17. ትክክለኛው እውቀት የተትረፈረፈው በምን መንገድ ነው?
17 በትንቢት ተነግሮ የነበረው ‘የፍጻሜ ዘመን’ የጀመረው በ1914 ነው። ታዲያ ስለ ሰው ልጆች ተስፋ የሚናገረው ትክክለኛ እውቀት ተትረፍርፎ ነበር? (ዳን. 12:4) እስከ 1913 ባለው ጊዜ የራስል ስብከቶች በ2,000 ጋዜጦች ላይ ታትመው የወጡ ሲሆን በአጠቃላይ 15,000,000 ሰዎች መልእክቱን አንብበውታል። በ1914 መገባደጃ ላይ በሦስት አህጉራት የሚገኙ ከ9,000,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች የክርስቶስን የሺህ ዓመት ግዛት የሚያብራራውን “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን በተንቀሳቃሽ ምስሎችና በስላይዶች የታገዘውን ፊልም ተመልክተው ነበር። ከ1918 እስከ 1925 ባሉት ጊዜያት ውስጥ የይሖዋ አገልጋዮች፣ በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገረውን ተስፋ የሚያብራራውንና “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚል ርዕስ ያለውን ንግግር በ30 ቋንቋዎች በምድር ዙሪያ አቅርበዋል። በ1934 የይሖዋ ምሥክሮች፣ በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች መጠመቅ እንዳለባቸው ተገነዘቡ። በምድር ላይ ለዘላለም ከመኖር ጋር በተያያዘ ያገኙት ግንዛቤ የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ያላቸውን ቅንዓት እንዲያቀጣጥሉ አድርጓቸዋል። በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገረውን ተስፋ ማወቃቸው ይሖዋን ከልብ እንዲያመሰግኑ አነሳስቷቸዋል።
“ክብራማ ነፃነት” ከፊታችን ይጠብቀናል!
18, 19. በኢሳይያስ 65:21-25 ላይ በትንቢት እንደተነገረው ሰዎች ወደፊት ምን ዓይነት ሕይወት ይኖራቸዋል?
18 ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ ተመርቶ የአምላክ ሕዝቦች ወደፊት በምድር ላይ የሚያገኙትን ሕይወት በተመለከተ ትንቢት ጽፏል። (ኢሳይያስ 65:21-25ን አንብብ።) ኢሳይያስ ትንቢቱን በጻፈበት ወቅት ማለትም ከዛሬ 2,700 ዓመታት በፊት የነበሩ አንዳንድ ዛፎች ዛሬም ድረስ እንዳሉ ይታመናል። አንተም ጥንካሬና ጥሩ ጤንነት ኖሮህ የዚህን ያህል ዓመት ስትኖር በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ?
19 ሕይወት ጠዋት ታይቶ ወዲያው እንደሚጠፋ ጤዛ ከመሆን ይልቅ ዘላለማዊ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ቤት እንደ መገንባት፣ አትክልት እንደ መትከልና ስለተለያዩ ነገሮች እውቀት እንደ መቅሰም ባሉ ማለቂያ የሌላቸው እንቅስቃሴዎች ለመካፈል የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጥርልናል። ወደፊት ከሌሎች ጋር መመሥረት ስለምትችለው ወዳጅነት አስብ። በፍቅር ላይ የሚመሠረተው እንዲህ ዓይነቱ ወዳጅነት ለዘላለም የሚዘልቅ ከመሆኑም በላይ ዕለት ዕለት እየተጠናከረ ይሄዳል። በዚያን ወቅት በምድር ላይ የሚኖሩት ‘የአምላክ ልጆች’ የሚያገኙት “ክብራማ ነፃነት” ምንኛ ታላቅ ይሆናል!—ሮም 8:21
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 ኦገስቲን በአምላክ መንግሥት ሥር የሚኖረው የሺህ ዓመት ግዛት ወደፊት የሚፈጸም ነገር ሳይሆን [የካቶሊክ] ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ የጀመረ መሆኑን ተናግሯል።
ልታብራራ ትችላለህ?
• የሰው ልጆች በምድር ላይ እንደሚኖሩ የሚናገረው ተስፋ ተሰውሮ የነበረው እንዴት ነው?
• በ1600ዎቹ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ይመረምሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ምን ነገር ተገንዝበው ነበር?
• ከ1914 በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት የሰው ዘር ትክክለኛ ተስፋ ግልጽ እየሆነ የመጣው እንዴት ነው?
• ስለ ምድራዊ ተስፋ የሚናገረው እውቀት የበዛው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባለቅኔው ጆን ሚልተን (በስተ ግራ) እና የሒሳብ ሊቅ የሆነው አይዛክ ኒውተን (በስተ ቀኝ) በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገረውን ተስፋ ያውቁ ነበር
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቀድሞዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የሰው ልጆች ትክክለኛ ተስፋ በመላው ዓለም በሚታወጅበት ጊዜ ላይ እንዳሉ ከቅዱሳን መጻሕፍት ተገንዘበው ነበር