በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተደብቀው የቆዩ ውድ ሀብቶች ተገኙ

ተደብቀው የቆዩ ውድ ሀብቶች ተገኙ

ተደብቀው የቆዩ ውድ ሀብቶች ተገኙ

ባልጠበቅከው ቦታ ላይ የተደበቀ ውድ ሀብት አግኝተህ ታውቃለህ? በኢስቶኒያ የሚኖር ኢቮ ሎድ የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር መጋቢት 27, 2005 ላይ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞታል። ይህ ወንድም፣ አልማ ቫርድያ የተባሉ አንዲት አረጋዊት እህት አርጅቶ የነበረውን የዕቃ ማስቀመጫ ቤታቸውን በማፍረስ እየረዳቸው ነበር። ግድግዳውን በውጪ በኩል ሲያፈርሱት አንድ ጎኑ በጣውላ የተሸፈነ ምሰሶ አገኙ። ጣውላውን በሚያነሱበት ወቅት ምሰሶው ተቦርቡሮ ነበር፤ የተቦረቦረው ይህ ቦታ 10 ሴንቲ ሜትር ስፋት፣ 1.2 ሜትር ርዝመትና 10 ሴንቲ ሜትር ጥልቀት ያለው ሲሆን በማያስታውቅ መንገድ በሌላ እንጨት ተሸፍኗል። (1) ይህ ጎድጓዳ ስፍራ የተደበቀ ውድ ሀብት ይዞ ነበር! ይህ ሀብት ምንድን ነው? የደበቀውስ ማን ነው?

በዚህ ስፍራ በወፍራም ወረቀት በጥንቃቄ የተጠቀለሉ በርካታ እሽጎች ተገኝተዋል። (2) እሽጎቹ በይሖዋ ምሥክሮች የሚዘጋጁ ጽሑፎችን የያዙ ሲሆን ከእነዚህም አብዛኞቹ በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጡ የጥናት ርዕሶች ናቸው፤ አንዳንዶቹ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በ1947 የተዘጋጁ ነበሩ። (3) በኢስቶኒያ ቋንቋ የተዘጋጁት እነዚህ ጽሑፎች የተጻፉት ልቅም ባለ የእጅ ጽሑፍ ነበር። አንዳንዶቹ እሽጎች፣ ጽሑፎቹን እዚህ ቦታ ላይ የደበቃቸው ማን እንደሆነ ፍንጭ የሚሰጡ ሰነዶችን ይዘዋል። እነዚህ ሰነዶች የእህት አልማ ባለቤት የሆኑት ቪለም ቫርድያ ፖሊሶች በመረመሯቸው ወቅት ያጋጠሟቸውን ሁኔታዎች በዝርዝር ይዘዋል። እኚህ ወንድም በእስር ቤት ስላሳለፏቸው ዓመታት የሚናገሩ መረጃዎችም ተገኝተዋል። ወንድም እስር ቤት የገቡት ለምን ነበር?

ቪለም ቫርድያ፣ ከቀድሞዋ የሶቪየት ሕብረት አገሮች አንዷ በሆነችው በኢስቶኒያ የሚገኘው ታርቱ በተባለ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ፣ በኋላ ላይ ደግሞ ኦቴፓ በተባለ ጉባኤ በኃላፊነት አገልግለዋል። እኚህ ወንድም እውነትን የሰሙት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ ጥቂት ጊዜያት ቀደም ብሎ ሳይሆን አይቀርም። ከጥቂት ዓመታት በኋላ በወቅቱ የነበረው የኮሚኒስት መንግሥት፣ ወንድም ቫርድያ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው ታኅሣሥ 24, 1948 እንዲታሰሩ አደረገ። እኚህ ወንድም የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ስም ለፖሊስ ለመስጠት ፈቃደኛ ስላልነበሩ ደህንነቶች ከፍተኛ ምርመራ ያካሄዱባቸው ከመሆኑም በላይ እንግልትና ሥቃይ አድርሰውባቸዋል። ወንድም ቫርድያ ፍርድ ቤት ቀርበው የመከላከያ ሐሳብ እንዳያቀርቡ የተከለከሉ ሲሆን በመጨረሻም በሩሲያ በሚገኙ ወኅኒ ቤቶች ለአሥር ዓመት እንዲታሰሩ ተበየነባቸው።

ወንድም ቫርድያ መጋቢት 6, 1990 በሞት ያንቀላፉ ሲሆን እስከዚያች ዕለት ድረስ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ኖረዋል። የወንድም ቫርድያ ባለቤት ጽሑፎቹ እዚያ ቦታ ስለ መደበቃቸው ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ወንድም ቫርድያ ስለ ጽሑፎቹ ለባለቤታቸው ያልነገሯቸው እህት አልማ በፖሊሶች ተይዘው ቢመረመሩ ለችግር ይጋለጣሉ የሚል ስጋት ስላደረባቸው ሊሆን ይችላል። ወንድም ጽሑፎቹን የደበቁት ለምን ነበር? ኬጂቢ ማለትም የሶቪየት ኅብረት የደኅንነት ኮሚቴ፣ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን ለመያዝ ሲል የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች በድንገት የመፈተሽ ልማድ ስለነበረው ነው። ወንድም ቫርድያ እነዚህን ጽሑፎች የደበቁት ኬጂቢ ድንገት ሁሉንም ጽሑፎች ቢወስድ ወንድሞች መንፈሳዊ ምግብ ያጣሉ ብለው በማሰብ ሳይሆን አይቀርም። ከዚህ ቀደም በ1990 አጋማሽ ላይ ጽሑፎች የተደበቁባቸው ሌሎች ቦታዎች ተገኝተው ነበር። ከእነዚህ መካከል አንዱ የተገኘው ደቡብ ኢስቶኒያ ውስጥ ባለችው በታርቱ ነው። በዚህ ቦታ ላይም ጽሑፎችን የደበቁት ወንድም ቪለም ቫርድያ ነበሩ።

ታዲያ እነዚህን ጽሑፎች እንደ ውድ ሀብት የምንመለከታቸው ለምንድን ነው? ልቅም ባለ የእጅ ጽሑፍ የተጻፉትና በጥንቃቄ የተደበቁት እነዚህ ጽሑፎች፣ ወንድሞች በዚያን ወቅት ለሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ምን ያህል አድናቆት እንዳላቸው የሚያሳዩ በመሆናቸው ነው። (ማቴ. 24:45) አንተስ በአሁኑ ጊዜ ለምታገኛቸው መንፈሳዊ ምግቦች አድናቆት አለህ? በዛሬው ጊዜ ከሚቀርቡት መንፈሳዊ ምግቦች መካከል የኢስቶኒያ ቋንቋን ጨምሮ ከ170 በሚበልጡ ሌሎች ቋንቋዎች የሚታተመው መጠበቂያ ግንብ ይገኝበታል።