በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’

‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’

‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’

“ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላችሁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረት እየተጠባበቃችሁ ኑሩ።”—ይሁዳ 21

1, 2. ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው? ይሖዋ የፈለግነውን ነገር ለማድረግ ብንመርጥም ከፍቅሩ ሳንወጣ እንድንኖር ይፈቅድልናል ማለት የማንችለው ለምንድን ነው?

ይሖዋ አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር ስፍር ቁጥር በሌላቸው መንገዶች አሳይቷል። ለእኛ ፍቅር እንዳለው የሚያሳየው ከሁሉ የላቀው ማስረጃ ግን የቤዛው ዝግጅት እንደሆነ ምንም አያጠያይቅም። ይሖዋ ለሰው ዘር ያለው ፍቅር እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሚወደውን ልጁን ወደዚህ ምድር በመላክ ለእኛ ሲል እንዲሞት አድርጓል። (ዮሐ. 3:16) ይህን ያደረገው ደግሞ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ብሎም ፍጻሜ ለሌለው ጊዜ የእሱን ፍቅር እያገኘን እንድንኖር ስለሚፈልግ ነው!

2 ታዲያ የፈለግነውን ነገር ለማድረግ ብንመርጥም ይሖዋ ከፍቅሩ ሳንወጣ እንድንኖር ይፈቅድልናል ብለን ማሰብ እንችላለን? በፍጹም። ምክንያቱም ይሁዳ ቁጥር 21 የሚከተለውን ጥብቅ ምክር ይሰጠናል፦ “ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላችሁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረት እየተጠባበቃችሁ ኑሩ።” ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የሚለው አባባል በእኛ በኩል ልናደርገው የሚገባ ነገር እንዳለ ይጠቁመናል። ታዲያ ከአምላክ ፍቅር ላለመውጣት ምን ማድረግ ያስፈልገናል?

ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

3. ኢየሱስ ከአባቱ ፍቅር ሳይወጣ ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገው ተናግሯል?

3 ኢየሱስ በምድር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ የተናገረው ሐሳብ የዚህን ጥያቄ መልስ ይዟል። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እኔ የአብን ትእዛዛት ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር እናንተም ትእዛዛቴን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።” (ዮሐ. 15:10, 10) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ፣ ከይሖዋ ጋር ያለውን ጥሩ ዝምድና ይዞ እንዲኖር የአባቱን ትእዛዛት መጠበቁ አስፈላጊ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ፍጹም የሆነው የአምላክ ልጅ እንዲህ እንዲያደርግ ይጠበቅበት ከነበረ እኛስ ትእዛዛቱን እንድንከተል አይጠበቅብንም?

4, 5. (ሀ) ይሖዋን እንደምንወደው የምናሳይበት ዋነኛው መንገድ ምንድን ነው? (ለ) የይሖዋን ትእዛዛት ከማክበር ወደኋላ የምንልበት ምንም ምክንያት የለም እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው?

4 ለይሖዋ ፍቅር እንዳለን የምናሳይበት ዋነኛው መንገድ እሱን በመታዘዝ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም።” (1 ዮሐ. 5:3) እርግጥ ነው፣ ታዛዥነት የሚለው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ብዙ ሰዎች አይዋጥላቸውም። ይሁንና ጥቅሱ “ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም” እንደሚል ልብ በሉ። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ አይጠይቀንም።

5 እስቲ ይህንን በምሳሌ ለማየት እንሞክር፦ አንድ የቅርብ ጓደኛችሁ ለማንሳት በጣም እንደሚከብደው እያወቃችሁ ከአቅሙ በላይ የሆነ እቃ እንዲሸከምላችሁ ትጠይቁታላችሁ? እንዲህ እንደማታደርጉ የታወቀ ነው! ይሖዋ ደግሞ ከእኛ የበለጠ እጅግ ደግ ነው፤ እንዲሁም ከእኛ በበለጠ ያሉብንን የአቅም ገደቦች ይረዳልናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ‘ትቢያ መሆናችንን ያስባል’ የሚል የሚያጽናና ሐሳብ ይዟል። (መዝ. 103:14) ማድረግ ከምንችለው በላይ እንድናደርግ በፍጹም አይጠይቀንም። ስለሆነም የይሖዋን ትእዛዛት ከማክበር ወደኋላ የምንልበት ምንም ምክንያት የለም። እንዲያውም ታዛዥነት በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን በእርግጥ እንደምንወደውና ከእሱ ፍቅር ሳንወጣ መኖር እንደምንፈልግ የምናሳይበት ግሩም አጋጣሚ እንደሆነ አድርገን እናየዋለን።

ከይሖዋ ያገኘነው ልዩ ስጦታ

6, 7. (ሀ) ሕሊና ምንድን ነው? (ለ) ሕሊና ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ እንድንኖር ሊረዳን የሚችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

6 ውጥንቅጡ በወጣው በዚህ ዓለም ውስጥ ስንኖር ለአምላክ ያለንን ታዛዥነት የሚነኩ ውሳኔዎችን እንድናደርግ የሚጠይቁ በርካታ ጉዳዮች ያጋጥሙናል። ታዲያ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ከአምላክ ፈቃድ ጋር የተስማሙ መሆናቸውን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ይሖዋ ታዛዦች በመሆን ረገድ በጣም ሊረዳን የሚችል አንድ ስጦታ ሰጥቶናል። ይህ ስጦታ ሕሊና ነው። ሕሊና ምንድን ነው? ሕሊና ራሳችንን ማወቅ የምንችልበት ልዩ ስጦታ ነው። ሕሊና በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ምርጫዎች እንድናመዛዝን ወይም የወሰድናቸውን እርምጃዎች መለስ ብለን እንድናጤንና ጥሩ ወይም መጥፎ፣ ትክክል ወይም ስሕተት መሆናቸውን እንድንገመግም የሚያስችለን በውስጣችን ያለ ዳኛ ነው።—ሮም 2:14, 15ን አንብብ።

7 ታዲያ በሕሊናችን ጥሩ አድርገን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ መንገደኛ ጭው ባለ በረሃ ላይ በእግሩ እየተጓዘ ነው። የእግር ዱካም ሆነ መንገድ ወይም አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶች የሉም። ሆኖም ወደ መድረሻው ቀጥ ብሎ ይገሰግሳል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? መንገደኛው፣ ኮምፓስ ይዟል። ኮምፓስ፣ አራቱን ዋና ዋና አቅጣጫዎች የሚጠቁሙ ምልክቶችና ምንጊዜም ወደ ሰሜን አቅጣጫ የሚያመለክት ባለ ማግኔት ቀስት ያለው መሣሪያ ነው። ይህ መንገደኛ ያለ ኮምፓስ ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዞ ይጓዛል ማለት ዘበት ነው። በተመሳሳይም አንድ ሰው ሕሊና ከሌለው በሕይወቱ ውስጥ ትክክለኛ፣ ጥሩና ከጽድቅ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ምርጫ ለማድረግ በጣም ይቸገራል።

8, 9. (ሀ) ሕሊናችን ምን ገደብ እንዳለበት መዘንጋት የለብንም? (ለ) ሕሊናችን ጠቃሚ መመሪያ እንዲሰጠን ምን ማድረግ እንችላለን?

8 እንደ ኮምፓስ ሁሉ ሕሊናም አንዳንድ ገደቦች አሉት። መንገደኛው ኮምፓሱ አጠገብ ማግኔት ቢያስቀምጥ ቀስቱ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ማመልከቱን ያቆማል። በተመሳሳይ እኛም ለልባችን ፍላጎት ትልቅ ቦታ የምንሰጥ ከሆነ ምን ሊደርስብን ይችላል? ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ዝንባሌያችን ሕሊናችንን ሊያዛባው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም” በማለት ያስጠነቅቃል። (ኤር. 17:9፤ ምሳሌ 4:23) በተጨማሪም መንገደኛው ትክክለኛና አስተማማኝ ካርታ ካልያዘ ኮምፓሱ ብቻውን ብዙም የሚፈይድለት ነገር አይኖርም። በተመሳሳይ እኛም በአምላክ ቃል ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው ትክክለኛና የማይለዋወጥ መመሪያ ካልተመራን ሕሊናችን ምንም ላይጠቅመን ይችላል። (መዝ. 119:105) የሚያሳዝነው በዚህ ዓለም የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ለልባቸው ፍላጎት ከሚገባው በላይ ቦታ የሚሰጡ ሲሆን በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኙት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ግን ያን ያህል ትኩረት አይሰጡም። (ኤፌሶን 4:17-19ን አንብብ።) ብዙ ሰዎች ሕሊና ቢኖራቸውም እንኳ በጣም አስከፊ የሆኑ ነገሮችን የሚሠሩት በዚህ ምክንያት ነው።—1 ጢሞ. 4:2

9 እኛ እንደነዚህ ሰዎች ላለመሆን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል! እንዲያውም ሕሊናችን ጠቃሚ መመሪያ እንዲሰጠን ዘወትር ከአምላክ ቃል ትምህርትና ሥልጠና እንዲያገኝ ልናደርግ ይገባል። እንዲሁም ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸው ዝንባሌዎቻችን ሕሊናችንን እንዲቆጣጠሩት ከመፍቀድ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናችን የሚነግረንን መስማት ያስፈልገናል። ከዚህም በተጨማሪ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ከልብ ስለምንወዳቸው ሕሊናቸውን ለማክበር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። የአንድ ወንድማችን ሕሊና ከእኛ ሕሊና ይልቅ በቀላሉ የሚጎዳ ወይም ጥብቅ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ እሱን ላለማሰናከል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።—1 ቆሮ. 8:12፤ 2 ቆሮ. 4:2፤ 1 ጴጥ. 3:16

10. ከዚህ ቀጥሎ የትኞቹን ሦስት የሕይወት ዘርፎች እንመረምራለን?

10 እስቲ አሁን ደግሞ ታዛዥ በመሆን ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸውን ሦስት የሕይወት ዘርፎች እንመልከት። በሦስቱም ዘርፎች ረገድ ሕሊና የሚጫወተው ሚና እንዳለ የታወቀ ነው፤ ያም ሆኖ ሕሊናችን ከምንም ነገር በላይ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ በያዛቸው የሥነ ምግባር መመሪያዎች መሠልጠን አለበት። ታዛዥ በመሆን ይሖዋን እንደምንወደው የምናሳይባቸው ሦስቱ መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፦ (1) ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎች መውደድ፣ (2) ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት እንዲሁም (3) በአምላክ ፊት ንጹሕ ሆነን ለመኖር ጥረት ማድረግ።

ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎች ውደዱ

11. ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎች መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?

11 በመጀመሪያ፣ ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎች መውደድ አለብን። ጓደኝነት የመመሥረት ነገር ከተነሳ፣ ሰዎች እንደ ስፖንጅ ናቸው ማለት ይቻላል። ሰዎች ስንባል በዙሪያችን ያለውን ማንኛውንም ነገር ልክ እንደ ስፖንጅ የመምጠጥ ባሕርይ አለን። ፈጣሪያችን ጓደኝነት ፍጹማን ላልሆኑ ሰዎች ምን ያህል አደገኛ ወይም ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል በሚገባ ያውቃል። በመሆኑም ይህን ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቶናል፦ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።” (ምሳሌ 13:20, 20፤ 1 ቆሮ. 15:33) ማናችንም ብንሆን ‘ጉዳት እንዲያገኘን’ አንፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ ሁላችንም “ጠቢብ” መሆን እንፈልጋለን። ይሖዋ ፍጹም ጥበብ ስላለው የሌሎች ወዳጅነት ጥበብ ሊጨምርለት አይችልም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ማንም በመጥፎ ሊቀርጸው አይችልም። ይሁንና የጓደኛ ምርጫን በተመለከተ ለእኛ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። እስቲ ቆም ብላችሁ አስቡ፣ ይሖዋ ፍጽምና ከሚጎድላቸው ሰዎች መካከል ወዳጆቹ እንዲሆኑ የመረጠው እነማንን ነው?

12. ይሖዋ የሚመርጠው ምን ዓይነት ወዳጆችን ነው?

12 ይሖዋ የእምነት አባት የሆነውን አብርሃምን “ወዳጄ” ሲል ጠርቶታል። (ኢሳ. 41:8) የእምነት ሰው የሆነው አብርሃም በታማኝነትና በታዛዥነት እንዲሁም ጽድቅ ወዳድ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው። (ያዕ. 2:21-23) ይሖዋ ወዳጅ አድርጎ የመረጠው እንዲህ ያለውን ሰው ነው። ዛሬም ቢሆን እንዲህ ያሉ ሰዎችን ወዳጆቹ አድርጎ ይቀበላቸዋል። ይሖዋ ለወዳጅነት የሚመርጠው እንዲህ ያሉ ሰዎችን ከሆነ እኛም ከጠቢባን ጋር በመሄድ ጠቢብ መሆን እንድንችል ጓደኞቻችንን በጥንቃቄ መምረጣችን አስፈላጊ አይደለም?

13. ጓደኛ በመምረጥ ረገድ ጥሩ ውሳኔ እንድናደርግ ምን ሊረዳን ይችላል?

13 በዚህ ረገድ ጥሩ ምርጫ እንድታደርጉ ምን ሊረዳችሁ ይችላል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ምሳሌዎችን ማጥናት ትክክለኛ ምርጫ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይችላል። በሩትና በአማቷ በኑኃሚን፣ በዳዊትና በዮናታን ወይም በጢሞቴዎስና በጳውሎስ መካከል የነበረውን ጓደኝነት አስቡ። (ሩት 1:16, 17፤ 1 ሳሙ. 23:16-18፤ ፊልጵ. 2:19-22) እነዚህ ሰዎች የቅርብ ጓደኞች ሊሆኑ የቻሉበት ከሁሉ የላቀው ምክንያት ለይሖዋ ልባዊ ፍቅር የነበራቸው መሆኑ ነው። ልክ እንደ እናንተ ይሖዋን የሚወዱ ጓደኞች ማግኘት ትችላላችሁ? በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንዲህ ያሉ ጓደኞች የማግኘት አጋጣሚያችሁ ሰፊ እንደሆነ እርግጠኞች ሁኑ። እንዲህ ዓይነት ጓደኞች በመንፈሳዊነታችሁ ላይ ጉዳት አያደርሱም። እንዲያውም ይሖዋን እንድትታዘዙ፣ በመንፈሳዊ እድገት እንድታደርጉና ለመንፈስ ብላችሁ እንድትዘሩ ይረዷችኋል። (ገላትያ 6:7, 8ን አንብብ።) ደግሞም ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ እንድትኖሩ ያግዟችኋል።

ለሥልጣን አክብሮት አሳዩ

14. ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ብዙ ጊዜ ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርጉ ምን ምክንያቶች አሉ?

14 ይሖዋን እንደምንወድ የምናሳይበት ሁለተኛው መንገድ ከሥልጣን ጋር የተያያዘ ነው። ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት አለብን። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የሚከብደን ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ፍጽምና የሚጎድላቸው መሆኑ ነው። በተጨማሪም እኛ ራሳችን ፍጹማን አይደለንም። ከዚህም የተነሳ በውስጣችን ካለው የዓመፀኝነት ዝንባሌ ጋር ትግል አለብን።

15, 16. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቦቹን እንዲንከባከቡ ኃላፊነት የሰጣቸውን ሰዎች ማክበራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ እስራኤላውያን በሙሴ ላይ ባመፁ ጊዜ ከተሰማው ስሜት ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?

15 ታዲያ ‘ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያን ያህል አስቸጋሪ ከሆነ ይህን ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። የዚህ ጥያቄ መልስ የይሖዋን ሉዓላዊነት በተመለከተ ከተነሳው አከራካሪ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው። ሉዓላዊ ገዥያችሁ አድርጋችሁ የምትቀበሉት ማንን ነው? ይሖዋን ሉዓላዊ ገዥያችን አድርገን ከተቀበልን የእሱን ሥልጣን ማክበር ይኖርብናል። ሥልጣኑን የማናከብር ከሆነ ገዥያችን ነው ብንል እውነት ይሆናል? ከዚህ በተጨማሪ ይሖዋ አብዛኛውን ጊዜ አመራር የሚሰጠን ሕዝቦቹን እንዲንከባከቡ ኃላፊነት በሰጣቸው ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች አማካኝነት ነው። በእነዚህ ሰዎች ላይ የምናምፅ ከሆነ ይሖዋ አድራጎታችንን እንዴት ይመለከተዋል?—1 ተሰሎንቄ 5:12, 13ን አንብብ።

16 ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን በሙሴ ላይ ባጉረመረሙና ባመፁ ጊዜ ይሖዋ ይህን አድራጎታቸውን በእሱ ላይ እንደተፈጸመ አድርጎ ቆጥሮታል። (ዘኍ. 14:26, 27) አምላክ ዛሬም አልተለወጠም። እሱ በሥልጣን ላይ ባስቀመጣቸው ሰዎች ላይ የምናምፅ ከሆነ በእሱ ላይ ማመፅ ይሆንብናል!

17. በጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ላላቸው ሰዎች ሊኖረን የሚገባው ተገቢ አመለካከት ምንድን ነው?

17 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ላላቸው ሰዎች ሊኖረን የሚገባውን ተገቢ አመለካከት ገልጿል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ነፍሳችሁን ተግተው ስለሚጠብቁና ይህን በተመለከተ ስሌት ስለሚያቀርቡ በመካከላችሁ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ፤ ይህንም የምታደርጉት ሥራቸውን በደስታ እንዲያከናውኑ ነው፤ አለበለዚያ ሥራቸውን በሐዘን ያከናውናሉ፤ ይህ ደግሞ እናንተን ይጎዳችኋል።” (ዕብ. 13:17) እንዲህ ያለውን የተገዥነትና የታዛዥነት መንፈስ ለማዳበር በእኛ በኩል ልባዊ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅብን እሙን ነው። ይሁንና ጥረታችን ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ታዲያ ይህ ማንኛውንም ዓይነት ጥረት ልናደርግለት የሚገባ ግብ አይደለም?

በአምላክ ፊት ንጹሕ ሆናችሁ ኑሩ

18. ይሖዋ ንጹሕ ሆነን እንድንኖር የሚፈልገው ለምንድን ነው?

18 ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምናሳይበት ሦስተኛው መንገድ በእሱ ፊት ንጹሕ ሆነን ለመኖር ጥረት ማድረግ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች የልጆቻቸውን ንጽሕና ለመጠበቅ ብዙ ይደክማሉ። እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? አንደኛ ነገር፣ ንጽሕና ለልጁ ደህንነትና ጤና በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም፣ ንጹሕ የሆነ ልጅ ቤተሰቡን የሚያስመሰግን ከመሆኑም ሌላ ወላጆቹ ለእሱ ፍቅር እንዳላቸውና እንክብካቤ እንደሚያደርጉለት ያሳያል። ይሖዋም ንጹሕ እንድንሆን የሚፈልግበት ምክንያት ከዚህ የተለየ አይደለም። ንጽሕና ለደህንነታችን ወሳኝ ነገር እንደሆነ ያውቃል። በተጨማሪም ንጹሕ መሆናችን በሰማይ የሚኖረው አባታችንን ያስከብራል። ይህ ትልቅ ትርጉም ያለው ነገር ነው፤ ምክንያቱም ንጽሕናችን በዚህ የረከሰ ዓለም ውስጥ ከብዙኃኑ የተለየን መሆናችንን ሰዎች እንዲያስተውሉና ወደምናገለግለው አምላክ እንዲሳቡ ሊያደርጋቸው ይችላል።

19. አካላዊ ንጽሕና አስፈላጊ እንደሆነ እንዴት እናውቃለን?

19 ንጹሕ መሆን የሚያስፈልገን በየትኞቹ መንገዶች ነው? በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች እንደሆነ የታወቀ ነው። ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን አካላዊ ንጽሕና አስፈላጊ ነገር እንደሆነ አስገንዝቧቸው ነበር። (ዘሌ. 15:31) የሙሴ ሕግ ቆሻሻን ከማስወገድ፣ ዕቃዎችን ከማንጻት፣ እጅና እግርን ከመታጠብ እንዲሁም ልብስን ከማጠብ ጋር የተያያዙ ደንቦችን ያካተተ ነበር። (ዘፀ. 30:17-21፤ ዘሌ. 11:32፤ ዘኍ. 19:17-20፤ ዘዳ. 23:13, 14) እስራኤላውያን አምላካቸው ይሖዋ ቅዱስ ማለትም ንጹሕ፣ የጠራና እንከን የለሽ እንደሆነ ተነግሯቸው ነበር። ቅዱስ የሆነውን አምላክ የሚያገለግሉ ሰዎች እነሱም ቅዱስ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል።—ዘሌዋውያን 11:44, 45ን አንብብ።

20. ንጹሕ ሆነን መኖር ያለብን በየትኞቹ መንገዶች ነው?

20 አካላዊ ንጽሕናን መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ውስጣችንም ንጹሕ መሆን አለበት። የምናስበው ነገር ንጹሕ እንዲሆን ጥረት እናደርጋለን። በዓለም ያሉ ሰዎች ስለ ጾታ ያላቸው አመለካከት ምንም ያህል ያዘቀጠ ቢሆን ይሖዋ ስለ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ያወጣቸውን መሥፈርቶች በጥብቅ እንከተላለን። ከሁሉም በላይ በሐሰት ሃይማኖት ላለመበከል በመጠንቀቅ አምልኮታችን ንጹሕ ሆኖ እንዲቀጥል የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። በ⁠ኢሳይያስ 52:11 ላይ የሚገኘውንና በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ፈጽሞ አንዘነጋም፦ “ተለዩ፤ ተለዩ፤ ከዚያ ውጡ፤ ርኵስ ነገር አትንኩ፤ ከዚያ ውጡ ንጹሓንም ሁኑ።” ዛሬም ይሖዋ ርኩስ አድርጎ ከሚመለከታቸው ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪነት ካላቸው ነገሮች ሙሉ በሙሉ በመራቅ መንፈሳዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን እንኖራለን። ለምሳሌ ያህል፣ በአሁኑ ጊዜ በጣም ተወዳጅ ከሆኑት የሐሰት ሃይማኖት በዓላት የምንርቀው ከዚህ የተነሳ ነው። እርግጥ ነው፣ ንጽሕናን ጠብቆ መኖር ተፈታታኝ ነው። ይሁንና የይሖዋ ሕዝቦች በሁሉም መንገድ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ለመኖር ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋቸው ከአምላክ ፍቅር እንዳይወጡ ይረዳቸዋል።

21. ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ምን ሊረዳን ይችላል?

21 ይሖዋ ለዘላለም ከእሱ ፍቅር ሳንወጣ እንድንኖር ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ሁላችንም በግለሰብ ደረጃ ከአምላክ ፍቅር ላለመውጣት የተቻለንን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህንንም ማድረግ የምንችለው የኢየሱስን ምሳሌ በመከተልና የይሖዋን ሕጎች በመታዘዝ ለእሱ ፍቅር እንዳለን በማሳየት ነው። እንዲህ ካደረግን ምንም ነገር “በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል” እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሮም 8:38, 39

ታስታውሳለህ?

• ሕሊናችን ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ እንድንኖር የሚረዳን እንዴት ነው?

• ይሖዋ የሚወዳቸውን መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?

• ለሥልጣን አክብሮት ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• የአምላክ ሕዝቦች ንጹሕ መሆናቸው ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ጥሩ ባሕርያትን እንድናፈራ የሚያበረታታ መጽሐፍ

በ2008 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለ ባለ 224 ገጽ መጽሐፍ ወጥቶ ነበር። ይህ አዲስ መጽሐፍ የተዘጋጀበት ዓላማ ምንድን ነው? መጽሐፉ በዋነኝነት የሚያተኩረው በክርስቲያናዊ ባሕርያት ላይ ሲሆን ክርስቲያኖች የአምላክን የሥነ ምግባር መስፈርቶች እንዲያውቁና ለእነሱም ፍቅር እንዲኖራቸው ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ በጥልቀት ማጥናታችን ከይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር በአሁኑ ጊዜ ከሁሉ የተሻለ የሕይወት ጎዳና እንደሆነና ወደፊት ደግሞ ለዘላለም ሕይወት እንደሚያበቃ ያለንን ጽኑ እምነት ያጠናክርልናል።

ከዚህም በላይ ይህ መጽሐፍ ይሖዋን መታዘዝ ሸክም እንዳልሆነ እንድንገነዘብ እኛን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። እንዲያውም ታዛዥነት ይሖዋን ምን ያህል እንደምንወደው የምናሳይበት መንገድ ነው። በመሆኑም ይህ መጽሐፍ ‘ይሖዋን የምታዘዘው ለምንድን ነው?’ ብለን እንድንጠይቅ ያነሳሳናል።

አንዳንድ ሰዎች ከይሖዋ ፍቅር በመውጣት አሳዛኝ የሆነ ስሕተት ሲሠሩ በአብዛኛው የችግሩ መንስኤ ከመሠረተ ትምህርት ጋር ሳይሆን ከባሕርይና ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዘ ሆኖ ይገኛል። እንግዲያው ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን መመሪያ ለሚሆኑን የይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለንን ፍቅር እንዲሁም አድናቆት ማሳደጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ይህ አዲስ ጽሑፍ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ በጎች ትክክል ለሆነው ነገር ጥብቅ አቋም እንዲኖራቸው፣ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን እንዲያጋልጡና ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአምላክ ፍቅር ሳይወጡ እንዲኖሩ እንደሚረዳቸው እርግጠኞች ነን!

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“እኔ የአብን ትእዛዛት ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር እናንተም ትእዛዛቴን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ”