በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዚህ ቀደም ታገለግል ነበር? አሁንስ ማገልገል ትችላለህ?

ከዚህ ቀደም ታገለግል ነበር? አሁንስ ማገልገል ትችላለህ?

ከዚህ ቀደም ታገለግል ነበር? አሁንስ ማገልገል ትችላለህ?

በአንድ ወቅት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ታገለግል ነበር? ምናልባትም የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነህ አገልግለህ ሊሆን ይችላል። አሊያም በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ተካፍለህ ታውቅ ይሆናል። በወቅቱ፣ በተሰጡህ የአገልግሎት መብቶች ደስታና ጥልቅ እርካታ አግኝተህ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይሁንና በአንዳንድ ምክንያቶች የተነሳ እነዚህን መብቶች አጥተሃል።

ቤተሰብህን ለመንከባከብ ስትል በጉባኤ ውስጥ ያለህን የአገልግሎት መብት ለመተው ተገደህ ይሆናል። ወይም ደግሞ መብትህን የተውኸው በዕድሜ መግፋት አሊያም በጤና እክል ምክንያት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ የድክመት ምልክት አይደለም። (1 ጢሞ. 5:8) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ፊልጶስ ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለግል ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ግን መኖሪያውን በቂሳርያ በማድረግ ቤተሰቡን መንከባከብ ጀመረ። (ሥራ 21:8, 9) የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊትም ዕድሜው እየገፋ ሲሄድ ልጁ ሰለሞን እሱን ተክቶ እንዲነግሥ አድርጓል። (1 ነገ. 1:1, 32-35) ፊልጶስም ሆነ ዳዊት የተሰጣቸውን መብት ቢተዉም ይሖዋ ለእነሱ ያለው ፍቅርና አድናቆት አልቀነሰም፤ ከዚህም ሌላ በዛሬው ጊዜም በሰዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ያለህን የአገልግሎት መብት እንድታጣ ተደርገህ ሊሆን ይችላል። ይህ የሆነው ጥበብ የጎደለው ድርጊት በመፈጸምህ ይሆን? ወይስ ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ ችግሮች በመከሰታቸው? (1 ጢሞ. 3:2, 4, 10, 12) በወቅቱ መብትህን እንድታጣ መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነ ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል፤ ምናልባት አሁንም ድረስ ቅሬታህ ከውስጥህ አልወጣ ይሆናል።

ያጣኸውን መብት ለማግኘት ጥረት ማድረግ ትችላለህ

አንድ ሰው በጉባኤ ውስጥ የነበረውን መብት ካጣ በኋላ መልሶ ሊያገኘው አይችልም ማለት ነው? አብዛኛውን ጊዜ እንደዚያ ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ የአገልግሎት መብትህን እንደገና ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። (1 ጢሞ. 3:1) ሆኖም መብትህን መልሰህ ለማግኘት እንድትመኝ የሚያነሳሳህ ምንድን ነው? ይህን ለማድረግ የሚገፋፋህ ምክንያት ሕይወትህን ለአምላክ ለመወሰን እንድትነሳሳ ካደረገህ ምክንያት ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ይኸውም ለይሖዋና እሱን ለሚያገለግሉት ሰዎች ያለህ ፍቅር ነው። መብትህን መልሰህ ለማግኘት ፈቃደኛ በመሆን እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዳለህ የምታሳይ ከሆነ ይሖዋ መብትህን ከማጣትህ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ያካበትከውን ልምድ ተጠቅመህ ይበልጥ እንድታገለግለው የሚያስችልህን አጋጣሚ ያመቻቻል።

ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ባጠፉት ጥፋት የተነሳ መብታቸውን እንዲያጡ ካደረገ በኋላ የሰጣቸውን ማበረታቻ ለማስታወስ ሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አልጠፋችሁም።” (ሚል. 3:6) ይሖዋ እስራኤላውያንን የሚወዳቸው ከመሆኑም ሌላ ይበልጥ ሊጠቀምባቸው ይፈልግ ነበር። አንተንም ወደፊት ሊጠቀምብህ ይፈልጋል። ታዲያ አሁን ባለህበት ሁኔታ ምን ማድረግ ትችላለህ? አንድ ሰው ከቲኦክራሲያዊ ሥራዎች ጋር የተያያዙ መብቶች ላይ ለመድረስ ይበልጥ የሚያስፈልገው ጥሩ መንፈሳዊ አቋም እንጂ ተፈጥሯዊ ችሎታ አይደለም። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ስለሌሉህ አጋጣሚውን መንፈሳዊነትህን ለማጠናከር ተጠቀምበት።

በእምነት ‘ብርቱ’ ለመሆን ‘ይሖዋንና ብርታቱን መፈለግ’ ይኖርብሃል። (1 ቆሮ. 16:13፤ መዝ. 105:4) ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ነው። ያለህበትን ሁኔታ በተመለከተ ወደ ይሖዋ ስትጸልይ የልብህን አውጥተህ ንገረው፤ እንዲሁም መንፈሱን እንዲሰጥህ ለምነው። እንዲህ ስታደርግ ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ የምትችል ሲሆን ይህ ደግሞ ጠንካራ እንድትሆን ይረዳሃል። (መዝ. 62:8፤ ፊልጵ. 4:6, 13) መንፈሳዊነትህን እንድታጠናክር የሚረዳህ ሌላው እርምጃ የአምላክን ቃል የማጥናት ልማድህን ማሻሻል ነው። በአሁኑ ወቅት ብዙ ኃላፊነቶች ስለሌሉብህ የግልና የቤተሰብ ጥናት ልማድህን ማሻሻል ምናልባትም ከዚህ በፊት ቋሚ ማድረግ አስቸግሮህ የነበረውን የጥናት ፕሮግራም በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ትችል ይሆናል።

አሁንም ቢሆን ይሖዋን ከሚወክሉት ምሥክሮቹ አንዱ መሆንህን መዘንጋት አይኖርብህም። (ኢሳ. 43:10-12) ማንኛችንም ልናገኘው ከምንችለው መብት ሁሉ የላቀው “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ” መሆናችን ነው። (1 ቆሮ. 3:9) በመስክ አገልግሎት የምታደርገውን ተሳትፎ ማሳደግህ መንፈሳዊነትን ለማጠናከር የሚያስችል ግሩም መንገድ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል።

መጥፎ ስሜቶችን መቋቋም

በጉባኤ ውስጥ የነበረህን መብት በማጣትህ የኃፍረት ወይም የጸጸት ስሜት ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል። ለፈጸምከው ድርጊት ምክንያት ለማቅረብ ጥረት ታደርግ ይሆናል። ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች፣ ራስህን ለመከላከል ያቀረብከውን ሐሳብ ያዳምጡ ይሆናል፤ ያም ሆኖ መብትህን ልታጣ እንደሚገባ ቢሰማቸውስ? እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በሚፈጠርበት ወቅት ስለ እነዚያ ወንድሞች መጥፎ ስሜት ሊያድርብህ ይችላል፤ ይህ ደግሞ መብትህን መልሰህ ለማግኘት ጥረት እንዳታደርግ አልፎ ተርፎም ከደረሰብህ ሁኔታ ትምህርት እንዳትወስድ እንቅፋት ይሆንብሃል። ኢዮብ፣ ምናሴና ዮሴፍ የተዉትን ምሳሌ መመርመርህ መጥፎ ስሜቶችን እንድትቋቋም የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ኢዮብ ሌሎችን ወክሎ ወደ ይሖዋ ይቀርብ የነበረ ከመሆኑም በላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሽማግሌና ዳኛ ሆኖ ይሠራ ነበር። (ኢዮብ 1:5፤ 29:7-17, 21-25) ሆኖም ኢዮብ ሁሉ ነገር በተሳካለት በዚህ ወቅት ላይ ሀብት ንብረቱን፣ ልጆቹን እንዲሁም ጤንነቱን አጣ። በዚህም የተነሳ በሰዎች ዘንድ የነበረውን ተቀባይነትም አጣ። ኢዮብ “በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ . . . ይሣለቁብኛል” በማለት ተናግሯል።—ኢዮብ 30:1

ኢዮብ ምንም ስህተት እንዳልሠራ ስለተሰማው በአምላክ ፊት ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ፈልጎ ነበር። (ኢዮብ 13:15) ያም ቢሆን ኢዮብ፣ ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነበር፤ ይህ ደግሞ በረከት አስገኝቶለታል። ይህ የአምላክ አገልጋይ በተለይ ፈተና ሲያጋጥመው በሰጠው ምላሽ ረገድ እርማት ማግኘቱ አስፈላጊ እንደነበር ተምሯል። (ኢዮብ 40:6-8፤ 42:3, 6) ኢዮብ ትሕትና በማሳየቱ አምላክ አትረፍርፎ ባርኮታል።—ኢዮብ 42:10-13

መብትህን ያጣኸው በፈጸምከው ስህተት ምክንያት ከሆነ ይሖዋም ሆነ ክርስቲያን ወንድሞችህ ከልባቸው ይቅር ሊሉህና በደልህን ሊረሱት መቻላቸውን ትጠራጠር ይሆናል። የይሁዳ ንጉሥ የነበረውን የምናሴን ታሪክ እስቲ እንመልከት። ምናሴ “እግዚአብሔርን ለቍጣ የሚያነሣሣውን ክፉ ድርጊት በፊቱ [ፈጽሟል]።” (2 ነገ. 21:6) ያም ሆኖ ምናሴ ሲሞት ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የነበረ ከመሆኑም በላይ ንግሥናውንም አላጣም ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

ከጊዜ በኋላ ምናሴ የተሰጠውን ተግሣጽ ተቀበለ። ከዚያ ቀደም ምናሴ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ አልሰማ በማለቱ ይሖዋ አሦራውያንን በማምጣት በሰንሰለት አስረው በግዞት ወደ ባቢሎን እንዲወስዱት አድርጎ ነበር። ምናሴ በባቢሎን ሳለ “የአምላኩን የእግዚአብሔርን በጎነት ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ። ወደ እርሱም [ጸለየ]።” ምናሴ ከልቡ ንስሐ በመግባት ጥፋቱን ለማስተካከል እርምጃ በመውሰዱ ይሖዋ ይቅርታ አደረገለት።—2 ዜና 33:12, 13

በእርግጥ አንድ ሰው ያጣቸውን መብቶች በሙሉ በአንድ ጊዜ ማግኘት የሚችለው ከስንት አንዴ ነው። በሌላ በኩል ግን እያደር አንዳንድ መብቶችን ልታገኝ ትችላለህ። የተሰጡህን መብቶች ተቀብለህ ኃላፊነትህን ለመወጣት የተቻለህን ሁሉ ማድረግህ አብዛኛውን ጊዜ ሌሎች መብቶች እንድታገኝ መንገድ ይከፍታል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ሲባል ሁኔታዎች አንተ እንደምትጠብቀው በፍጥነት ይስተካከላሉ ማለት ላይሆን ይችላል። ሁኔታዎች አንተ ባሰብከው መንገድ እንዳይሄዱ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ያም ቢሆን የፈቃደኝነት ስሜት ማዳበርህና መጽናትህ መልካም ፍሬ ያፈራል።

የያዕቆብ ልጅ የሆነውን ዮሴፍን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዮሴፍ የ17 ዓመት ልጅ እያለ ወንድሞቹ በባርነት በመሸጥ ግፍ ፈጽመውበት ነበር። (ዘፍ. 37:2, 26-28) የገዛ ወንድሞቹ እንዲህ ያለ ግፍ ይፈጽማሉ ብሎ እንደማይጠብቅ ግልጽ ነው። ያም ቢሆን ዮሴፍ ራሱን ከሁኔታዎች ጋር አስማምቶ ለመኖር ፈቃደኛ ነበር፤ ይሖዋ ስለባረከው “ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው።” (ዘፍ. 39:4) ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ወኅኒ ቤት ወረደ። እዚያም ቢሆን ዮሴፍ በታማኝነት የጸና ሲሆን ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበረ፤ በዚህም ምክንያት ውሎ አድሮ በእስር ቤቱ ውስጥ ኃላፊነት ተሰጠው።—ዘፍ. 39:21-23

ዮሴፍ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በእሱ ላይ እንዲደርሱ ይሖዋ የፈቀደው በዓላማ እንደሆነ አልተገነዘበም ነበር። ይሁንና ሳያጉረመርም አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደርግ ነበር። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ቃል የተገባለት ዘር የሚመጣበትን መስመር ጠብቆ ለማቆየት ዮሴፍን ሊጠቀምበት ችሏል። (ዘፍ. 3:15፤ 45:5-8) ማንኛችንም ብንሆን እንደ ዮሴፍ ያለ ቁልፍ ሚና እንጫወታለን ብለን ባንጠብቅም በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ዘገባ አገልጋዮቹ መብት እንዲያገኙ የሚያደርገው ይሖዋ መሆኑን ይጠቁማል። አንተም የዮሴፍን ምሳሌ በመከተል በጉባኤ ውስጥ መብት ማግኘት የምትችልበት አጋጣሚ ክፍት እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ።

አስቸጋሪ ከሆኑ ሁኔታዎች ትምህርት ማግኘት

ኢዮብ፣ ምናሴና ዮሴፍ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው ነበር። ሦስቱም ሰዎች፣ ይሖዋ በእነሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደውን ሁኔታ ተቀብለው በመኖር ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን መቅሰም ችለዋል። አንተስ ካጋጠመህ ሁኔታ ምን መማር ትችላለህ?

ይሖዋ ምን ሊያስተምርህ እንደፈለገ ለመገንዘብ ሞክር። ኢዮብ ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ጋር እየታገለ በነበረበት ወቅት በራሱ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረጉ ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮችን ማስተዋል አቅቶት ነበር። ሆኖም ኢዮብ፣ ይሖዋ በፍቅር የሰጠውን እርማት በመቀበል ሚዛኑን እንደገና መጠበቅ የቻለ ሲሆን “የማላስተውለውን . . . ነገር ተናግሬአለሁ” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ኢዮብ 42:3) የነበሩህን መብቶች በማጣትህ ስሜትህ ተጎድቶ ከሆነ ‘ከሚገባው በላይ ስለ ራስህ በማሰብ ራስህን ከፍ አድርገህ ከመመልከት ይልቅ ጤናማ አእምሮ እንዳለህ በሚያሳይ መንገድ አስብ።’ (ሮም 12:3) አንተ ለጊዜው ሙሉ በሙሉ ባትረዳውም ይሖዋ ሊያስተካክልህ እየሞከረ ሊሆን ይችላል።

ተግሣጽን ተቀበል። መጀመሪያ ላይ ምናሴ የተሰጠው እርማት ከሚገባው በላይ ከባድ እንደሆነ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን የተሰጠውን እርማት ተቀብሎ ንስሐ በመግባት መጥፎ አካሄዱን እርግፍ አድርጎ ትቷል። አንተም የተሰጠህ ተግሣጽ ያሳደረብህ ስሜት ምንም ይሁን ምን ‘በይሖዋ ፊት ራስህን ዝቅ አድርግ፤ እሱም ከፍ ከፍ ያደርግሃል።’—1 ጴጥ. 5:6፤ ያዕ. 4:10

ትዕግሥተኛና ፈቃደኛ ሁን። ዮሴፍ ያጋጠመው ሁኔታ የጥላቻና የበቀል ስሜት እንዲያድርበት ሊያደርገው ይችል ነበር። እሱ ግን አስተዋይነትንና ምሕረትን አዳበረ። (ዘፍ. 50:15-21) አንተም ቅር የሚያሰኝ ነገር አጋጥሞህ ከሆነ ትዕግሥተኛ ሁን። ይሖዋ እንዲያሠለጥንህ ፈቃደኛ ሁን።

በአንድ ወቅት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ታገለግል ነበር? ይሖዋ ወደፊት መብቶች እንዲሰጥህ አጋጣሚውን ክፈትለት። መንፈሳዊነትህን አጠናክር። ትዕግሥትና ትሕትናን በማዳበር የሚታገልህን መጥፎ ስሜት ለማሸነፍ ሞክር። የሚሰጥህን ማንኛውንም ኃላፊነት በፈቃደኝነት ተቀበል። ይሖዋ “በቅንነት የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር [እንደማይነፍጋቸው]” እርግጠኛ ሁን።—መዝ. 84:11

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ልባዊ ጸሎት በማቅረብ በእምነት ብርቱ መሆን ትችላለህ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመስክ አገልግሎት የምታደርገውን ተሳትፎ ማሳደግህ መንፈሳዊነትህን ለማጠናከር የሚያስችል ግሩም መንገድ ነው

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ወደፊት መብቶች እንዲሰጥህ አጋጣሚውን ክፈትለት