ጊዜው “የምሥራች ቀን” በመሆኑ ትኩረትህን ከሚከፋፍሉ ነገሮች ራቅ
ጊዜው “የምሥራች ቀን” በመሆኑ ትኩረትህን ከሚከፋፍሉ ነገሮች ራቅ
አራቱ የሥጋ ደዌ በሽተኞች ምን አማራጭ እንዳላቸው እያሰቡ ነው። ከከተማዪቱ መግቢያ በር አጠገብ የተቀመጡት እነዚህ ሰዎች ምፅዋት የሚሰጣቸው ሰው አላገኙም። የሶርያ ሠራዊት፣ የሰማርያ ነዋሪዎች በረሃብ እንዲያልቁ በማሰብ ከተማዋን ከቧታል። በሰማርያ የምግብ ዋጋ እጅግ በመናሩ አራቱ የሥጋ ደዌ በሽተኞች ወደ ከተማዪቱ ቢገቡ ምንም የሚያገኙት ነገር አይኖርም። እንዲያውም አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች የሰው ሥጋ እንደበሉ እየተወራ ነው።—2 ነገ. 6:24-29
የሥጋ ደዌ በሽተኞቹ ‘መሞታችን ካልቀረ ለምን ወደ ሶርያውያኑ ሰፈር አንሄድም?’ በማለት አሰቡ። ከዚያም በዚያው ዕለት መሸትሸት ሲል ጨለማን ተገን አድርገው ጉዟቸውን ጀመሩ። ወደ ሰፈሩ ሲደርሱ አካባቢው ጭር ብሏል። የሰፈሩ ጠባቂዎች በአካባቢው የሉም። ፈረሶቹና አህዮቹ እንደታሰሩ ናቸው፤ ይሁንና አንድም ወታደር የለም። አራቱ ሰዎች ወደ አንድ ድንኳን አጮልቀው ሲመለከቱ በድንኳኑ ውስጥ ማንም ሰው አልነበረም፤ የሚበላና የሚጠጣ ነገር ግን በገፍ ነበር። በመሆኑም ወደ ድንኳኑ ገብተው መብላትና መጠጣት ጀመሩ። የሥጋ ደዌ በሽተኞቹ በድንኳኑ ውስጥ ወርቅ፣ ብር፣ ልብስና የተለያዩ ውድ ነገሮች መኖራቸውን አስተዋሉ። ከዚያም የቻሉትን ያህል ወስደው ከደበቁት በኋላ ተጨማሪ ለመውሰድ እንደገና ተመልሰው መጡ። ሶርያውያኑ የጦር ሰፈሩን ሙሉ ለሙሉ ለቀው ሄደው ነበር። ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ በጦር ሰፈሩ የብዙ ሠራዊት ድምፅ እንዲሰማ በማድረጉ ሶርያውያኑ ጥቃት ሊሰነዘርብን ነው በሚል ስጋት እግሬ አውጭኝ ብለው ነበር። ሶርያውያኑ ያላቸውን ነገር ሁሉ ትተው ስለ ሸሹ ማንም ሰው ወደ ጦር ሰፈሩ ገብቶ መዝረፍ ይችል ነበር!
የሥጋ ደዌ በሽተኞቹ ወደ ጦር ሰፈሩ እየተመላለሱ ውድ የሆኑትን ሀብቶች በመውሰድ መደበቃቸውን ቀጠሉ። ይሁን እንጂ በሰማርያ የሚኖሩት ሰዎች ተርበው ሳለ እነሱ ለራሳቸው ጥቅም ብቻ ማሰባቸው ሕሊናቸውን ይረብሸው ጀመር። ከዚያም እርስ በርሳቸው “ያደረግነው ትክክል አይደለም፤ ዕለቱ የምሥራች ቀን ነው” ተባባሉ። ወዲያውኑም ወደ ሰማርያ ተመልሰው የምሥራቹን ለሕዝቡ ተናገሩ።—2 ነገ. 7:1-11
እኛም የምንኖርበት ጊዜ “የምሥራች ቀን” ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ኢየሱስ “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት” ያሉትን ጎላ ያሉ ገጽታዎች አስመልክቶ በተናገረበት ወቅት እንዲህ ብሏል፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴ. 24:3, 14) ይህ አባባል እኛን ሊነካን ይገባል የምንለው ለምንድን ነው?
የግል ጉዳዮቻችን ከባድ ሸክም ሊሆኑብን ይችላሉ
የሥጋ ደዌ በሽተኞቹ ባገኙት ነገር ከመጠን በላይ በመደሰታቸው የሰማርያን ነዋሪዎች ለጊዜውም ቢሆን ረስተዋቸው ነበር። ትኩረት ያደረጉት ማግኘት በሚችሉት ነገር ላይ ብቻ ነበር። እኛስ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል? የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ካሉት ገጽታዎች መካከል አንዱ “የምግብ እጥረት” ነው። (ሉቃስ 21:7, 11) ኢየሱስ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት፣ እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አሳስቧቸዋል። (ሉቃስ 21:34) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚያጋጥሙን ጉዳዮች፣ የምንኖረው ‘በምሥራች ቀን’ ውስጥ መሆኑን እንድንዘነጋ እንዳያደርጉን መጠንቀቅ አለብን።
ብሌሲንግ የተባለች አንዲት ክርስቲያን፣ በግል ጉዳዮቿ በመጠመድ በራሷ ላይ ሸክም ማብዛት አልፈለገችም። ትምህርቷን እየተማረች ሳለ አቅኚ ሆና ታገለግል ነበር። ትምህርቷን ከጨረሰች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አንድ ቤቴላዊ ያገባች ሲሆን አሁን በቤኒን ቅርንጫፍ ቢሮ ቤቴላዊ ሆና እያገለገለች ትገኛለች። ብሌሲንግ እንዲህ ብላለች፦ “በጽዳት ሥራ እንዳገለግል የተመደብኩ ሲሆን ሥራዬንም በጣም እወደዋለሁ።” ብሌሲንግ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስላሳለፈቻቸው 12 ዓመታት መለስ ብላ ስታስብ ምንም የምትቆጭበት ነገር
የለም። ትኩረቷን አሁን በምንኖርበት “የምሥራች ቀን” ላይ በማድረጓ በጣም ደስተኛ ናት።ጊዜህን ከሚሻሙብህ ነገሮች ተጠበቅ
ኢየሱስ 70ዎቹን ደቀ መዛሙርት በላከበት ወቅት እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በእርግጥም አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ ሥራ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።” (ሉቃስ 10:2) አንድ ገበሬ በመከር ወቅት ሰብሉን ቶሎ አለመሰብሰቡ እህሉ ለብክነት እንዲዳረግ እንደሚያደርግ ሁሉ አንድ ክርስቲያንም የስብከቱን ሥራ ችላ ማለቱ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ኢየሱስ “በመንገድ ላይም ቆማችሁ ከማንም ጋር ሰላምታ አትለዋወጡ” ሲል ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 10:4) “ሰላምታ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ጤና ይስጥልን” ወይም “እንዴት ዋልክ” የሚል አጭር ሰላምታ ከመስጠት የበለጠ ነገርን ሊያመለክት ይችላል። በተጨማሪም ቃሉ፣ ሰዎች አንድ ወዳጃቸውን ሲያገኙት እንደሚያደርጉት ተቃቅፎ ሰላም መባባልንና ረጅም ጭውውት ማድረግን ሊያመለክት ይችላል። በመሆኑም ኢየሱስ ትኩረትን የሚከፋፍሉ አላስፈላጊ ነገሮችን ከማድረግ በመቆጠብ ጊዜያቸውን በጥበብ እንዲጠቀሙበት ተከታዮቹን አዝዟቸዋል። የሚሰብኩት መልእክት በጣም አጣዳፊ ነበር።
ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮች ጊዜህን ምን ያህል እንደሚሻሙብህ እስቲ ለማሰብ ሞክር። ባለፉት በርካታ ዓመታት፣ ቁጥር አንድ የጊዜ ሌባ ተደርጎ የሚታየው ቴሌቪዥን ነበር። ይሁንና ስለ ሞባይል ስልኮችና ስለ ግል ኮምፒውተሮችስ ምን ማለት ይቻላል? በብሪታንያ በሚኖሩ 1,000 አዋቂ ሰዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “መካከለኛ ኑሮ ያለው አንድ ብሪታንያዊ፣ በቀን ውስጥ 88 ደቂቃ የመስመር ስልክ በመጠቀም፣ 62 ደቂቃ በሞባይል ስልክ በማውራት፣ 53 ደቂቃ ኢሜይል በመጠቀም እንዲሁም 22 ደቂቃ በሞባይል ስልክ መልእክት በመለዋወጥ ያሳልፋል።” እነዚህ ደቂቃዎች አንድ ላይ ሲደመሩ አንድ ረዳት አቅኚ በቀን ውስጥ በአገልግሎት ከሚያሳልፈው ሰዓት በእጥፍ ይበልጣሉ! አንተስ በእነዚህ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ምን ያህል ሰዓት ታጠፋለህ?
ኧርንስት እና ሂልደጋርት ዜሌገር በጊዜ አጠቃቀም ረገድ ጠንቃቆች ነበሩ። በናዚ የማጎሪያ ካምፖችና በኮሚኒስት እስር ቤቶች ውስጥ ሁለቱም ያሳለፉት ጊዜ በድምሩ ከ40 ዓመታት ይበልጣል። ከእሥር ከተፈቱ በኋላ ምድራዊ ሕይወታቸውን እስካጠናቀቁበት ጊዜ ድረስ በአቅኚነት አገልግለዋል።
በርካታ ሰዎች ከኧርንስት እና ከሂልደጋርት ጋር ደብዳቤ መጻጻፍ ይወዱ ነበር። በመሆኑም እነዚህ ባልና ሚስት የሚላኩላቸውን ፖስታዎች በማንበብና ደብዳቤ በመጻፍ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ማሳለፍ ይችሉ ነበር። ይሁንና በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዙት መንፈሳዊ ነገሮች ነበሩ።
እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ብንሆን ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር በደብዳቤም ሆነ በስልክ መገናኘት ያስደስተናል፤ ደግሞም እንዲህ ማድረጋችን ምንም ስህተት የለውም። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የተለያዩ ሆኖም የተመረጡ እንቅስቃሴዎችን ማድረጋችን ጠቃሚ ነው። ያም ሆኖ በዚህ ዘመን ምሥራቹን ለመስበክ በቂ ጊዜ መዋጀት እንድንችል ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች ጊዜያችንን እንዳይሻሙብን መጠንቀቃችን ብልኅነት ነው።
ምሥራቹን በተሟላ ሁኔታ ስበኩ
‘በምሥራች ቀን’ ውስጥ መኖር እንዴት ያለ በረከት ነው! የሥጋ ደዌ በሽተኞቹ በመጀመሪያ ላይ እንደሆኑት ሁሉ እኛም በሌሎች ነገሮች ትኩረታችን መሰረቅ የለበትም። ሰዎቹ ‘ያደረጉት ነገር ትክክል አለመሆኑን’ አምነው እንደተቀበሉ አስታውስ። እኛም የግል ጉዳዮቻችን ወይም ትኩረትን የሚሰርቁ ነገሮች በስብከቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ እንዳንሳተፍ ጊዜያችንን እየተሻሙብን ከሆነ የምናደርገው ነገር ትክክል አይደለም።
ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ሐዋርያው በአገልግሎት ያሳለፋቸውን የመጀመሪያዎቹን 20 ዓመታት መለስ ብሎ በማሰብ ሲጽፍ “ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ ሰብኬያለሁ” ብሏል። (ሮም 15:19) ጳውሎስ ምንም ነገር ቅንዓቱን እንዲያቀዘቅዝበት አልፈቀደም። እኛም ልክ እንደ እሱ በዚህ “የምሥራች ቀን” የመንግሥቱን መልእክት በቅንዓት እንስበክ።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብሌሲንግ፣ የግል ጉዳዮቿ በሙሉ ጊዜ አገልግሎቷ እንዳትቀጥል እንቅፋት እንዲሆኑባት አልፈቀደችም
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኧርንስት እና ሂልደጋርት በጊዜ አጠቃቀም ረገድ ጠንቃቆች ነበሩ