በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሃይማኖቴን መምረጥ ያለብኝ እኔ ነኝ ወይስ ወላጆቼ?

ሃይማኖቴን መምረጥ ያለብኝ እኔ ነኝ ወይስ ወላጆቼ?

ሃይማኖቴን መምረጥ ያለብኝ እኔ ነኝ ወይስ ወላጆቼ?

በፖላንድ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሲያነጋግሯቸው “የተወለድኩት በዚህ ሃይማኖት ውስጥ ነው፤ እስክሞት ድረስ ሃይማኖቴን መለወጥ አልፈልግም” ይላሉ። ይህ አባባል ሃይማኖትን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደሚተላለፍ ነገር አድርገው እንደሚመለከቱት ያሳያል። አንተ በምትኖርበት አካባቢም ሰዎች ስለ ሃይማኖት እንደዚህ ዓይነት አመለካከት አላቸው? እንደዚህ ዓይነቱ አመለካከት አብዛኛውን ጊዜ ምን ያስከትላል? ሃይማኖት ለይስሙላ የሚደረግ ነገር ሆኗል፤ እንዲሁም ሰዎች ሃይማኖታቸውን የሚከተሉት ሲወርድ ሲዋረድ ስለመጣ ብቻ ነው። ከወላጆቻቸው ወይም ከአያቶቻቸው ግሩም መንፈሳዊ ውርሻ ያገኙ የይሖዋ ምሥክሮችስ ሃይማኖታቸውን በተመለከተ እንደዚህ ዓይነት ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል?

ጢሞቴዎስ ስለ ሃይማኖቱ እንደዚህ ዓይነት አመለካከት አልነበረውም፤ ጢሞቴዎስ በእውነተኛው አምላክ እንዲያምንና ለእሱ ፍቅር እንዲያዳብር የረዱት ቀናተኛ የአምላክ አገልጋዮች የነበሩት እናቱና አያቱ ናቸው። ይህ ወጣት ‘ከጨቅላነቱ ጀምሮ’ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያውቅ ነበር። ከጊዜ በኋላ ጢሞቴዎስ እንዲሁም እናቱና አያቱ፣ ክርስትና እውነተኛው ሃይማኖት እንደሆነ አምነው ተቀበሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ አስመልክቶ ከቅዱሳን መጻሕፍት የሰማውን ነገር ‘የተቀበለው አምኖበት’ ነው። (2 ጢሞ. 1:5፤ 3:14, 15) ከዚህ ለማየት እንደምንችለው በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸው የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ ለመርዳት የተቻላቸውን ጥረት ቢያደርጉም ልጆቹ ራሳቸው ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት ማዳበራቸው አስፈላጊ ነው።—ማር. 8:34

እያንዳንዱ ሰው ይሖዋን በፍቅር ተነሳስቶ ማገልገል እንዲሁም ምንም ይምጣ ምን ንጹሕ አቋሙን መጠበቅ እንዲችል የተማረው ነገር አሳማኝ በሆነ ማስረጃ ላይ የተደገፈ መሆኑን ሊያምንበት ይገባል። እንዲህ ካደረገ እምነቱ ጠንካራና ሥር የሰደደ ይሆናል።—ኤፌ. 3:17፤ ቆላ. 2:6, 7

ልጆች የሚኖራቸው ሚና

በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ያደገው አልበርት * እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት እውነት መሆኑን አንድም ቀን ተጠራጥሬ ባላውቅም አኗኗሬን በተመለከተ የሚሰጡኝን ትምህርት ግን መቀበል ይከብደኝ ነበር።” አንተም ወጣት ከሆንክ እንደ አልበርት ይሰማህ ይሆናል። አምላክ በሚፈልገው መንገድ ሕይወታችንን መምራት ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ለማወቅ ለምን ጥረት አታደርግም? እንዲህ ካደረግህ የእሱን ፈቃድ በመፈጸም ደስታ ማግኘት ትችላለህ። (መዝ. 40:8) አልበርት እንዲህ ብሏል፦ “ወደ አምላክ መጸለይ ጀመርኩ። መጀመሪያ ላይ እንዲህ ማድረግ ይከብደኝ ስለነበር ራሴን ማስገደድ ነበረብኝ። ብዙም ሳይቆይ ግን ትክክል የሆነውን ለማድረግ የምጥር ከሆነ አምላክ በእሱ ዘንድ ውድ እንደሆንኩ አድርጎ ሊመለከተኝ እንደሚችል ይሰማኝ ጀመር። ይህ ደግሞ በሕይወቴ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን ለውጦችን እንዳደርግ ጥንካሬ ሰጥቶኛል።” በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት ከመሠረትክ እሱ የሚጠብቅብህን ነገር የማድረግ ፍላጎት ይኖርሃል።—መዝ. 25:14፤ ያዕ. 4:8

ከዚህ ቀደም ስለተጫወትከው አንድ የስፖርት ዓይነት ወይም እንደ ዳማ እና ቼዝ ስላሉት ጨዋታዎች ለማሰብ ሞክር። የጨዋታውን ሕጎች የማታውቅ ወይም በደንብ መጫወት የማትችል ከሆነ እነዚህ ጨዋታዎች አሰልቺ ሊሆኑብህ ይችላሉ። ሆኖም የጨዋታውን ሕጎች የምታውቅና በደንብ መጫወት የምትችል ከሆነ በእነዚህ ጨዋታዎች ለመካፈል አትጓጓም? እንዲያውም ይህን ለማድረግ አጋጣሚዎችን ታመቻች ይሆናል። ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እንግዲያው በራስህ ተነሳስተህ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ዝግጅት አድርግ። በሁሉም ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳትፎ አድርግ። በዕድሜ ትንሽ ብትሆንም ምሳሌነትህ ሌሎችን ሊያበረታታ ይችላል!—ዕብ. 10:24, 25

ስለ እምነትህ ለሌሎች በመናገር ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይህንንም በግዴታ ሳይሆን በፍቅር ተነሳስተህ ማድረግ ይኖርብሃል። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ስለ ይሖዋ ለሌሎች መናገር የምፈልገው ለምንድን ነው? እሱን እንድወደው የሚያደርጉኝ ምን ምክንያቶች አሉ?’ ይሖዋ አፍቃሪ አባት መሆኑን ማወቅ ያስፈልግሃል። ይሖዋ “እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፣ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ” በማለት በኤርምያስ በኩል ተናግሯል። (ኤር. 29:13, 14) ይሖዋን ለማግኘት እንድትችል ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ያኩፕ እንዲህ ብሏል፦ “አመለካከቴን ማስተካከል አስፈልጎኝ ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ በስብሰባዎች ላይ እገኝ እንዲሁም በአገልግሎት እካፈል ነበር፤ ሆኖም እነዚህን እንቅስቃሴዎች የማከናውነው በዘልማድ ነበር። እውነትን የራሴ ማድረግ የቻልኩት ይሖዋን በደንብ ሳውቀውና ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ስመሠርት ነው።”

አገልግሎትህ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆንልህ ሊያንጹህ የሚችሉ ጥሩ ወዳጆች ማፍራትህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። በመንፈስ መሪነት የተጻፈ አንድ ምሳሌ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) እንግዲያው መንፈሳዊ ግቦች ካሏቸውና ይሖዋን በማገልገል ከሚደሰቱ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መሥርት። ዮላ እንዲህ ብላለች፦ “መንፈሳዊ አመለካከት ካላቸው በርካታ ወጣቶች ጋር ጓደኝነት መመሥረቴ አበረታቶኛል። ከዚያ ወዲህ አዘውትሮ በአገልግሎት መካፈል አስደሳች ሆኖልኛል።”

ወላጆች የሚኖራቸው ሚና

ዮላ “ወላጆቼ ስለ ይሖዋ ስላስተማሩኝ በጣም አመሰግናቸዋለሁ” ብላለች። በእርግጥም ወላጆች፣ ልጆቻቸው በሚያደርጉት ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን . . . በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ አሳድጓቸው” ሲል ጽፏል። (ኤፌ. 6:4) በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ምክር በግልጽ እንደሚያሳየው ወላጆች ልጆቻቸውን ሊያስተምሯቸው የሚገባው የራሳቸውን ሳይሆን የይሖዋን መንገድ ነው። ልጆቻችሁ እንዲደርሱባቸው የምትፈልጓቸውን ግቦች በአእምሯቸው ከመቅረጽ ይልቅ ሕይወታቸውን ከይሖዋ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲመሩ ልታሠለጥኗቸው ብትችሉ ምንኛ ግሩም ይሆናል!

የይሖዋን መመሪያዎች ለልጆችህ ማስጠናት እንዲሁም “በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ” መናገር ትችላለህ። (ዘዳ. 6:6, 7) ሦስት ወንዶች ልጆች ያሏቸው ሪሻርድና ኢቫ “ስለ ተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች አዘውትረን እናወራ ነበር” ብለዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ምን ውጤት አስገኘ? “ልጆቻችን በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት መካፈል የጀመሩት ገና ትንንሾች እያሉ ነበር። ከዚያም አስፋፊ ሆነው ማገልገል የጀመሩ ሲሆን በራሳቸው ተነሳሽነት ለመጠመቅ ወሰኑ። ከጊዜ በኋላ ቤቴላዊና አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀመሩ።”

ወላጆች ጥሩ ምሳሌ መሆናቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ሪሻርድ “በቤት ውስጥ ስንሆንና ጉባኤ ስንሄድ የተለያየ ባሕርይ በማሳየት ሁለት ዓይነት ሕይወት ላለመምራት ወስነን ነበር” ብሏል። እናንተ ወላጆች ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ልጆቼ በእኔ ሕይወት የሚመለከቱት ነገር ምንድን ነው? ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር እንዳለኝ ማስተዋል ይችላሉ? ለይሖዋ ከማቀርበው ጸሎትና አዘውትሬ ከማደርገው የግል ጥናት እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዳለኝ መመልከት ይችላሉ? ለመስክ አገልግሎት፣ ለመዝናኛና ለቁሳዊ ነገሮች ያለኝ አመለካከት እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ስላሉ ወንድሞች የምናገረው ነገር ለይሖዋ ፍቅር እንዳለኝ የሚያሳይ ነው?’ (ሉቃስ 6:40) ልጆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችሁን የሚመለከቱ ከመሆኑም በላይ የምትናገሩትና የምታደርጉት ነገር የሚለያይ ከሆነ ይህን ማስተዋላቸው አይቀርም።

በልጆች አስተዳደግ ረገድ ተግሣጽ ትልቅ ድርሻ አለው። ያም ቢሆን በመንፈስ የተጻፈው የአምላክ ቃል “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው” ይላል። (ምሳሌ 22:6) ሪሻርድና ኢቫ “እያንዳንዱን ልጅ ለብቻው መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ጊዜ መድበን ነበር” ብለዋል። እርግጥ ነው፣ እያንዳንዱን ልጅ ለብቻው ማስጠናት ያስፈልጋቸው እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ያለባቸው ወላጆች ናቸው። በዚያም ሆነ በዚህ፣ እያንዳንዱ ልጅ በግሉ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ምክንያታዊነትና ግትር አለመሆን አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሙዚቃዎች መጥፎ እንደሆኑ ብቻ ለልጆቻችሁ ከመናገር አልፋችሁ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለምን አታሳዩአቸውም?

ልጆቻችሁ ከእነሱ ምን እንደምትጠብቁ ስለሚያውቁ እናንተ የምትፈልጉትን እንደሚያደርጉ ሊያስመስሉ ይችላሉ። በመሆኑም ልባቸውን ለመንካት መጣር ይኖርባችኋል። “የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ አስታውሱ። (ምሳሌ 20:5) አስተዋይ ሁኑ፤ ልጆቻችሁ የተደበቀ ችግር እንዳለባቸው የሚጠቁሙ ምልክቶችን በንቃት ተከታተሉ። ጊዜ ሳታጠፉም እርምጃ ውሰዱ። ልጆቻችሁን ሳትወቅሷቸው ጉዳዩ እንዳሳሰባችሁ ግለጹላቸው፤ እንዲሁም ተገቢ ጥያቄዎችን ጠይቋቸው። ሆኖም የጥያቄ መዓት አታዥጎድጉዱባቸው። ለእነሱ በማሰብ የምታደርጉት ጥረት ልባቸውን ለመንካት ይረዳችኋል፤ ይህም እንዴት እንደምትረዷቸው ለማስተዋል ያስችላችኋል።

ጉባኤው የሚኖረው ሚና

የአምላክ አገልጋይ እንደመሆናችሁ መጠን በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ያገኙትን መንፈሳዊ ውርሻ እንዲያደንቁ መርዳት ትችላላችሁ? ልጆችን የማሠልጠኑ ኃላፊነት የወላጆች ቢሆንም ሌሎች የጉባኤ አባላት በተለይ ደግሞ ሽማግሌዎች ወላጆች የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ ይችላሉ። በተለይም በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ልጆችን ለመርዳት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ወጣቶች፣ ይሖዋን እንዲወዱ እንዲሁም እንደሚፈለጉና ውድ እንደሆኑ ተደርገው እንደሚታዩ እንዲሰማቸው ለመርዳት ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ይችላሉ? ፖላንድ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው ማርዩሽ እንዲህ ብሏል፦ “ሽማግሌዎች ወጣቶችን አዘውትረው ሊያነጋግሯቸው ይገባል። ይህን ማድረግ ያለባቸው ችግሮች ሲነሱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አጋጣሚዎችም መሆን አለበት፤ ለምሳሌ አብረው በሚያገለግሉበት ጊዜ፣ ከስብሰባዎች በኋላ ወይም አብረዋቸው ሻይ እየጠጡ ሊያጫውቷቸው ይችላሉ።” ወጣቶች ስለ ጉባኤው ምን እንደሚሰማቸው ለምን አትጠይቋቸውም? በዚህ መንገድ በግልጽ መወያየታችሁ ወጣቶች ከጉባኤው ጋር እንዲቀራረቡ እንዲሁም የጉባኤው አባል እንደሆኑ እንዲሰማቸው ይረዳቸዋል።

ሽማግሌ ከሆንክ በጉባኤው ውስጥ የሚገኙትን ወጣቶች ለማወቅ ጥረት እያደረግህ ነው? ቀደም ሲል የተጠቀሰው አልበርት በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግል ቢሆንም በጉርምስና ዕድሜ ላይ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ችግሮች አጋጥመውት ነበር። “ወጣት በነበርኩበት ወቅት በግለሰብ ደረጃ እረኝነት ሊደረግልኝ ያስፈልግ ነበር” ብሏል። ሽማግሌዎች በጉባኤያቸው ውስጥ ስለሚገኙት ወጣቶች መንፈሳዊ ደኅንነት በመጸለይም በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስቡላቸው ሊያሳዩ ይችላሉ።—2 ጢሞ. 1:3

ወጣቶች በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸው ጠቃሚ ነው። አለዚያ ዓለማዊ ግቦችን ወደ ማሳደድ ዘወር ሊሉ ይችላሉ። አዋቂ የሆናቸሁ የጉባኤው አባላት ከእነሱ ጋር አብራችሁ ልታገለግሉና ጓደኛ ልታደርጓቸው ትችላላችሁ? ከወጣቶች ጋር አብራችሁ በመዝናናት እምነት እንዲጥሉባችሁና እንዲቀርቧችሁ አድርጉ። ዮላ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “አቅኚ የሆነች አንዲት እህት ትኩረት ሰጠችኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ደስ ብሎኝ አገልግሎት የወጣሁት ከእሷ ጋር ነው።”

የግልህ ምርጫህ

ወጣቶች፣ ‘ግቤ ምንድን ነው?’ ያልተጠመቃችሁ ከሆናችሁ ደግሞ ‘የመጠመቅ ግብ አለኝ?’ በማለት ራሳችሁን ጠይቁ። ለመጠመቅ የምትወስኑት ይሖዋን ከልባችሁ ስለምትወዱት እንጂ ቤተሰቦቻችሁን ለማስደሰት ብላችሁ መሆን የለበትም።

ይሖዋ እውነተኛ ወዳጃችሁ እንዲሆንና እውነትን እንደ ውድ ሀብት አድርጋችሁ እንድትመለከቱት ምኞታችን ነው። ይሖዋ “አምላክህ ነኝና አትደንግጥ” በማለት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ተናግሯል። እናንተ የይሖዋ ወዳጅ እስከሆናችሁ ድረስ እሱ ከእናንተ ጋር ይሆናል። ይሖዋ እንደሚያበረታችሁና ‘በጽድቁ ቀኝ እጅ ደግፎ እንደሚይዛችሁ’ እርግጠኞች ሁኑ።—ኢሳ. 41:10

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በልጃችሁ ልብ ውስጥ ምን እንዳለ ለማስተዋል ሞክሩ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመጠመቅ የምትወስኑት ይሖዋን ከልባችሁ ስለምትወዱት መሆን አለበት