በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ አንተን ለማዳን ያደረገውን ዝግጅት ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ?

ይሖዋ አንተን ለማዳን ያደረገውን ዝግጅት ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ?

ይሖዋ አንተን ለማዳን ያደረገውን ዝግጅት ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ?

“የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ፊቱን ወደ ሕዝቡ በመመለስ ለሕዝቡ የማዳን ተግባር ስለፈጸመ የተባረከ ይሁን።”—ሉቃስ 1:68

1, 2. ሁላችንም ያለንበት ሁኔታ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ የሚገልጽ ምሳሌ ተናገር። የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ተኝተሃል እንበል። በተኛህበት ክፍል ውስጥ ያሉት ሰዎች በሙሉ እንደ አንተ ዓይነት በሽታ የያዛቸው ሲሆን ይህ ሕመም መድኃኒት ያልተገኘለትና ገዳይ ነው። አንድ ሐኪም ለበሽታው መድኃኒት ለማግኘት ምርምር እያደረገ እንደሆነ ስትሰማ ተስፋህ ይለመልማል። ሐኪሙ የሚያደርገው ምርምር ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ በጉጉት ትከታተል ይሆናል። አንድ ቀን፣ ለበሽታው መድኃኒት እንደተገኘለት ሰማህ! ሐኪሙ ይህንን መድኃኒት ለማግኘት ከፍተኛ መሥዋዕትነት ከፍሏል። ይህን ስታውቅ ምን ይሰማሃል? አንተንም ሆነ ሌሎች ብዙ ሰዎችን ከሞት ለመታደግ መንገድ ለከፈተው ለዚህ ሰው ጥልቅ አክብሮትና አድናቆት እንደሚኖርህ ምንም ጥርጥር የለውም።

2 ይህ ሁኔታ የተጋነነ ይመስል ይሆናል፤ ሆኖም ሁላችንም ያለንበትን ሁኔታ በትክክል የሚገልጽ ነው። ሁላችንም በምሳሌው ላይ ከተገለጸው ሰው እጅግ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። ከዚህ ሁኔታ ለመውጣት እንድንችል አዳኝ ማግኘታችን በጣም አንገብጋቢ ነገር ነው። (ሮም 7:24ን አንብብ።) ይሖዋ እኛን ለማዳን ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ልጁም ቢሆን ትልቅ መሥዋዕትነት ከፍሏል። እስቲ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አራት መሠረታዊ ጥያቄዎች እንመርምር፦ መዳን ያስፈለገን ለምንድን ነው? መዳን እንድናገኝ ኢየሱስ የከፈለው ዋጋ ምንድን ነው? ይሖዋስ ምን ዋጋ መክፈል ጠይቆበታል? ይሖዋ እኛን ለማዳን ያደረገውን ዝግጅት ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

መዳን ያስፈለገን ለምንድን ነው?

3. ኃጢአት ከወረርሽኝ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

3 በቅርቡ በወጣ አንድ ግምታዊ መረጃ መሠረት፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት ወረርሽኞች ሁሉ አስከፊው በ1918 የተከሰተውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የጨረሰው ስፓንሽ ፍሉ ወይም የኅዳር በሽታ ነው። እርግጥ ነው፣ ከኅዳር በሽታ የበለጠ ገዳይ የሆኑ ሌሎች በሽታዎች አሉ። በእነዚህ በሽታዎች የሚጠቁት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ሊሆን ቢችልም በበሽታው ከተያዙት ሰዎች አብዛኞቹ ይሞታሉ። * ኃጢአትን እንዲህ ካሉ ወረርሽኞች ጋር ብናመሳስለውስ? ሮም 5:12 እንዲህ ይላል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ዘሮች በሙሉ ኃጢአት የሚሠሩ መሆኑ ሁሉም ሰው በኃጢአት የመያዝ አጋጣሚው መቶ በመቶ እንደሆነ ያሳያል። (ሮም 3:23ን አንብብ።) በኃጢአት ወረርሽኝ ከተያዙ ሰዎች መካከል ምን ያህሉ ይሞታሉ? ጳውሎስ በኃጢአት ምክንያት ሞት “ለሰው ሁሉ” እንደተዳረሰ ጽፏል።

4. ይሖዋ ስለ ሕይወታችን ዘመን ምን ይሰማዋል? ይህስ ብዙ ሰዎች ካላቸው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው?

4 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ስለ ኃጢአት የማያስቡ ከመሆኑም ሌላ ሞት የተለመደ ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። አለዕድሜ መቀጨት የሚባለው ነገር ቢያሳስባቸውም አርጅቶ መሞትን ግን “ተፈጥሯዊ” እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። የሰው ልጆች በዚህ ረገድ ፈጣሪ ያለውን አመለካከት ይዘነጉታል። ፈጣሪ መጀመሪያ ካሰበው አንጻር ሕይወታችን በጣም አጭር ነው። እንዲያውም በይሖዋ አመለካከት ማንም ሰው “አንድ ቀን” እንኳ አልኖረም። (2 ጴጥ. 3:8) በዚህም ምክንያት የአምላክ ቃል ሕይወታችን፣ በተወሰነ ጊዜ አድጎ እንደሚጠፋ ሣር ወይም እንደ ተን ጊዜያዊ እንደሆነ ይገልጻል። (መዝ. 39:5፤ 1 ጴጥ. 1:24) ይህንን በአእምሯችን መያዝ አስፈላጊ ነው። ለምን? የያዘን “በሽታ” ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ መረዳታችን “መድኃኒቱ” ማለትም እኛን ለማዳን የተደረገው ዝግጅት ያለውን ዋጋ ይበልጥ እንድናደንቅ ያስችለናል።

5. በኃጢአት ምክንያት ፈጽሞ ልናገኘው ያልቻልነው ነገር ምንድን ነው?

5 ኃጢአት እና ያስከተላቸው ውጤቶች ምን ያህል አስከፊ እንደሆኑ ለመገንዘብ እንድንችል በኃጢአት ምክንያት ያጣነውን ነገር ለመረዳት መጣር ይኖርብናል። ይህን መረዳት መጀመሪያ ላይ አዳጋች ሊሆንብን ይችላል፤ ምክንያቱም በኃጢአት ምክንያት ያጣነውን ነገር ከዚህ በፊት ፈጽሞ አግኝተነው አናውቅም። አዳምና ሔዋን መጀመሪያ ላይ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ነበራቸው። አእምሯቸውም ሆነ አካላቸው ፍጹም ስለነበረ አስተሳሰባቸውን፣ ስሜታቸውንና ድርጊታቸውን መቆጣጠር ይችሉ ነበር። በዚህም የተነሳ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች በመሆን ግሩም የሆኑ ባሕርያትን እያዳበሩ መኖር ይችሉ ነበር። እነሱ ግን ይህንን ውድ ስጦታ አሽቀንጥረው ጣሉት። አዳምና ሔዋን ሆን ብለው በይሖዋ ላይ ኃጢአት በመሥራታቸው አምላክ መጀመሪያ ላይ ለእነሱ ያሰበውን ዓይነት ሕይወት አጡ፤ ዘሮቻቸውም እንዲህ ያለውን ሕይወት እንዲያጡ ምክንያት ሆኑ። (ዘፍ. 3:16-19) ከዚህም በተጨማሪ ቀደም ብለን የጠቀስነውን አስከፊ “በሽታ” በራሳቸውም ሆነ በልጆቻቸው ላይ አምጥተዋል። ይሖዋ በእነሱ ላይ መፍረዱ ተገቢ ነበር። ለእኛ ግን መዳን የምናገኝበት ተስፋ ሰጥቶናል።—መዝ. 103:10

መዳን እንድናገኝ ኢየሱስ የከፈለው ዋጋ

6, 7. (ሀ) እኛን ማዳን ከፍተኛ ዋጋ እንደሚጠይቅ ይሖዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የጠቆመው እንዴት ነበር? (ለ) አቤል እንዲሁም የሙሴ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት የኖሩ የጥንት የአምላክ አገልጋዮች ካቀረቡት መሥዋዕት ምን እንማራለን?

6 ይሖዋ የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ማዳን ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል ያውቅ ነበር። በዘፍጥረት 3:15 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢት እኛን ማዳን ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል ለማወቅ ያስችለናል። ይህ ጥቅስ ይሖዋ አንድ ቀን ሰይጣንን በመቀጥቀጥ ከሕልውና ውጪ የሚያደርገው ‘ዘር’ ማለትም አዳኝ እንደሚያዘጋጅ ይገልጻል። ይሁንና ይህ አዳኝ መከራ ይደርስበታል፤ ምክንያቱም ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተረከዙ ላይ ጉዳት እንደሚያገኘው ትንቢቱ ይገልጻል። ይህ ጉዳት በአዳኙ ላይ ሥቃይ ያስከትልበታል፤ ሆኖም እንዲህ ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋ የመረጠው ይህ አዳኝ በምን ዓይነት መከራ ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል?

7 የሰው ልጆችን ከኃጢአት ለመታደግ አዳኙ ማስተሰረያ ማቅረብ ነበረበት፤ ይህ ማስተሰረያ ኃጢአት ያስከተላቸውን ውጤቶች በመሻር ሰዎችን ከአምላክ ጋር ለማስታረቅ ያስችላል። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? መሥዋዕት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ጥንት የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ተገንዝበው ነበር። የመጀመሪያው ታማኝ ሰው ማለትም አቤል ለይሖዋ የእንስሳት መሥዋዕት ባቀረበበት ጊዜ መሥዋዕቱ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። ከጊዜ በኋላም እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ያዕቆብና ኢዮብ ያሉት በጥንት ዘመን የኖሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው የይሖዋ አገልጋዮች ተመሳሳይ መሥዋዕቶች ያቀረቡ ሲሆን አምላክም በመሥዋዕታቸው ተደስቷል። (ዘፍ. 4:4፤ 8:20, 21፤ 22:13፤ 31:54፤ ኢዮብ 1:5) ከብዙ ዘመናት በኋላ ደግሞ የሙሴ ሕግ መሥዋዕት ማቅረብ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ አድርጓል።

8. ሊቀ ካህናቱ በዓመታዊው የስርየት ቀን ምን ያደርግ ነበር?

8 በሙሴ ሕግ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው መሥዋዕቶች መካከል በዓመታዊው የስርየት ቀን የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ይገኙበታል። በዚያን ቀን ሊቀ ካህናቱ ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ነገሮች ያከናውን ነበር። መጀመሪያ ከካህናት ወገን ለሆኑት ኃጢአት ከዚያም ካህናት ላልሆኑት ነገዶች ኃጢአት ማስተሰረያ የሚሆን መሥዋዕት ለይሖዋ ያቀርብ ነበር። ሊቀ ካህናቱ በመገናኛው ድንኳን ወይም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ወደሚገኘው ቅድስተ ቅዱሳን በዓመት አንድ ጊዜ በስርየት ቀን ብቻ ይገባል፤ ወደዚህ ክፍል ከእሱ ሌላ ማንም ሰው መግባት አይችልም። በዚያም የመሥዋዕቶቹን ደም በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ይረጫል። በዚህ ቅዱስ ሣጥን ላይ አንዳንድ ጊዜ ደማቅና አንጸባራቂ ደመና ይታያል፤ ይህም የይሖዋ አምላክን መገኘት ያመለክታል።—ዘፀ. 25:22፤ ዘሌ. 16:1-30

9. (ሀ) በስርየት ቀን ከሚከናወነው ነገር ጋር በተያያዘ ሊቀ ካህናቱ ማንን ይወክል ነበር? የሚያቀርባቸው መሥዋዕቶችስ? (ለ) ሊቀ ካህናቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መግባቱ ምን ያመለክታል?

9 ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ክንውኖች ምን እንደሚያመለክቱ በመንፈስ ተመርቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጿል። ሊቀ ካህናቱ የሚወክለው መሲሑን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሆነና የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ደግሞ የክርስቶስን መሥዋዕታዊ ሞት እንደሚያመለክቱ ጳውሎስ ገልጿል። (ዕብ. 9:11-14) ፍጹም የሆነው የክርስቶስ መሥዋዕት፣ በመንፈስ ለተቀቡትና ካህናት ሆነው ለሚያገለግሉት 144,000 የክርስቶስ ወንድሞችም ሆነ ‘ለሌሎች በጎች’ እውነተኛ የኃጢአት ስርየት ያስገኛል። (ዮሐ. 10:16) ሊቀ ካህናቱ፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መግባቱ ኢየሱስ የቤዛዊ መሥዋዕቱን ዋጋ ለይሖዋ አምላክ ለማቅረብ ወደ ሰማይ መግባቱን የሚያመለክት ነበር።—ዕብ. 9:24, 25

10. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መሲሑ ምን እንደሚደርስበት ጠቁመዋል?

10 ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው የአዳምና የሔዋን ዘሮችን ማዳን ከፍተኛ ዋጋ ይጠይቃል። መሲሑ ሕይወቱን መሥዋዕት ማድረግ ይኖርበታል! በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱት ነቢያት ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ዝርዝር ሐሳብ አስፍረዋል። ለምሳሌ ነቢዩ ዳንኤል፣ ‘ገዥው መሲሕ በደልን ለማስተሰረይ’ ሲል ‘እንደሚገደል’ በግልጽ ተናግሮ ነበር። (ዳን. 9:24-26) ኢሳይያስም መሲሑ፣ ፍጽምና የጎደላቸውን የሰው ልጆች ኃጢአት ለመሸከም ሲል እንደሚጠላ፣ ስደት እንደሚደርስበትና እንደሚገደል ወይም እንደሚወጋ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር።—ኢሳ. 53:4, 5, 7

11. የይሖዋ ልጅ እኛን ለማዳን ሲል ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ መሆኑን ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

11 የአምላክ አንድያ ልጅ እኛን ለማዳን ምን መሥዋዕት መክፈል እንደሚኖርበት ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ያውቅ ነበር። ከባድ ሥቃይ ከደረሰበት በኋላ መሞት ነበረበት። አባቱ ይህንን ሐቅ ሲነግረው የአምላክን ፈቃድ ከማድረግ ወደኋላ ለማለት ወይም ለማመፅ ሞክሮ ይሆን? በፍጹም፤ ከዚህ በተቃራኒ የአባቱን መመሪያ ለመቀበል ራሱን በፈቃደኝነት አቅርቧል። (ኢሳ. 50:4-6) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅትም የአባቱን ፈቃድ በታዛዥነት ፈጽሟል። እንዲህ ያደረገው ለምን ነበር? አንዱ ምክንያት ‘አብን ስለሚወድ’ እንደሆነ ተናግሯል። “ነፍሱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም” ብሎ በተናገረ ጊዜ ደግሞ ሌላውን ምክንያት ጠቁሟል። (ዮሐ. 14:31፤ 15:13) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው መዳን የምናገኝበት ዝግጅት እንዲኖር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው የይሖዋ ልጅ ፍቅር ያለው መሆኑ ነው። ይህ ዝግጅት እንዲኖር ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት ማድረግ ቢያስፈልገውም እኛን ለማዳን ሲል ይህንን በደስታ አድርጎታል።

መዳን እንድናገኝ ይሖዋ የከፈለው ዋጋ

12. ቤዛው የማን ፈቃድ መግለጫ ነው? እሱስ ቤዛውን ያዘጋጀው ለምንድን ነው?

12 ቤዛዊ መሥዋዕት የማቅረቡን ሐሳብ ያመነጨው ኢየሱስ አልነበረም። ከዚህ በተለየ መልኩ ይህ የመዳን ዝግጅት የይሖዋ ፈቃድ ዋና ገጽታ ነው። በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚገኘውና መሥዋዕቶች የሚቀርቡበት መሠዊያ የይሖዋን ፈቃድ እንደሚያመለክት ሐዋርያው ጳውሎስ ተናግሯል። (ዕብ. 10:10) በመሆኑም በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት ለምናገኘው መዳን በዋነኝነት ልናመሰግን የሚገባን ይሖዋን ነው። (ሉቃስ 1:68) ይህ ዝግጅት ይሖዋ ፍጹም የሆነውን ፈቃዱን ከገለጸባቸው መንገዶች አንዱ ከመሆኑም ሌላ ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ፍቅር በዚህ መንገድ አሳይቷል።—ዮሐንስ 3:16ን አንብብ።

13, 14. የአብርሃም ታሪክ ይሖዋ ለእኛ ሲል ያደረገውን ነገር እንድንገነዘብና ከፍ አድርገን እንድንመለከት የሚረዳን እንዴት ነው?

13 ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር በዚህ መንገድ ለመግለጽ ምን ዋጋ ከፍሏል? ይሖዋ የከፈለውን ዋጋ መረዳት ለእኛ አዳጋች ነው። ሆኖም ይህንን ጉዳይ በተሻለ መልኩ ለመረዳት የሚያስችለን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አለ። ይሖዋ፣ ታማኝ ሰው የነበረውን አብርሃምን በጣም ከባድ ነገር እንዲያደርግ ይኸውም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ጠየቀው። አብርሃም አፍቃሪ አባት ነበር። ይሖዋ ይስሐቅን በተመለከተ አብርሃምን ሲያናግረው “የምትወደውን አንዱን ልጅህን” ማለቱ አብርሃም ለልጁ የነበረውን ፍቅር ያሳያል። (ዘፍ. 22:2) ያም ቢሆን አብርሃም፣ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ለልጁ ለይስሐቅ ካለው ፍቅርም እንኳ መብለጥ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። አብርሃም ይሖዋ ያዘዘውን ለማድረግ ተዘጋጀ። ይሁንና ይሖዋ እሱ ራሱ ወደፊት የሚያደርገውን ነገር አብርሃም እንዲያደርገው አልፈቀደም። አምላክ አንድ መልአክ በመላክ አብርሃም ልጁን መሥዋዕት ከማድረጉ በፊት እንዲያስቆመው አደረገ። አብርሃም እንዲህ ያለ አስቸጋሪ ፈተና በቀረበለት ወቅትም አምላክን ለመታዘዝ ቆርጦ ስለነበር ልጁን እንደገና በሕይወት ማግኘት የሚችልበት ብቸኛው ተስፋ ትንሣኤ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። አብርሃም፣ አምላክ ልጁን ከሞት እንደሚያስነሳው ሙሉ እምነት ነበረው። በእርግጥም ጳውሎስ እንደተናገረው “እንደ ምሳሌ ሆኖ በሚያገለግል ሁኔታ” አብርሃም ይስሐቅን መልሶ አግኝቶታል።—ዕብ. 11:19

14 ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ሲያዘጋጀው አብርሃም የተሰማውን ሥቃይ መገመት ትችላለህ? አብርሃም በዚያ ወቅት የተሰማው ስሜት ይሖዋ “የምወደው ልጄ” በማለት የጠራውን ኢየሱስን መሥዋዕት ሲያደርገው የነበረውን ስሜት በተወሰነ መጠን ለመረዳት ያስችለናል። (ማቴ. 3:17) ሆኖም ይሖዋ በወቅቱ የተሰማው ሥቃይ ከአብርሃም የበለጠ ሊሆን እንደሚችል አስታውስ። እሱና ልጁ በሚሊዮኖች ምናልባትም በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዓመታት አብረው ኖረዋል። ልጁ በአባቱ ዘንድ ተወዳጅ የሆነ “ዋና ባለሙያ” እንዲሁም “ቃል” ማለትም ቃል አቀባይ በመሆን በደስታ አብሮት ሲሠራ ቆይቷል። (ምሳሌ 8:22, 30, 31፤ ዮሐ. 1:1) ይሖዋ ልጁ ሲሠቃይ፣ መሣለቂያ ሲሆንና እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ሲገደል ምን ተሰምቶት እንደሚሆን መገመት አንችልም። በእርግጥም ይሖዋ እኛን ለማዳን ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል! ታዲያ ይህንን የመዳን ዝግጅት ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው እንዴት ማሳየት እንችላለን?

ይሖዋ ያደረገውን የመዳን ዝግጅት ከፍ አድርገህ እንደምትመለከተው እንዴት ማሳየት ትችላለህ?

15. ኢየሱስ ስርየት ለማስገኘት የተደረገውን ታላቅ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ የፈጸመው እንዴት ነው? ይህስ ምን እንዲገኝ መንገድ ከፍቷል?

15 ኢየሱስ ስርየት ለማስገኘት የተደረገውን ታላቅ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ የፈጸመው ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ነው። ከሚወደው አባቱ ጋር እንደገና በተገናኘበት ወቅት የመሥዋዕቱን ዋጋ አቀረበለት። ከዚያ በኋላ ታላላቅ በረከቶች ተገኙ። መጀመሪያ ለተቀቡት የክርስቶስ ወንድሞች ኃጢአት ከዚያም “ለዓለም ሁሉ ኃጢአት” የተሟላ ይቅርታ ማግኘት ተቻለ። ለፈጸሙት ኃጢአት ከልብ ንስሐ የሚገቡና የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች የሚሆኑ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ክርስቶስ ይህንን መሥዋዕት በማቅረቡ በይሖዋ አምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ማግኘት ችለዋል። (1 ዮሐ. 2:2) ይህ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

16. ይሖዋ ላደረገልን የመዳን ዝግጅት አመስጋኝ መሆን የሚገባን ለምን እንደሆነ በምሳሌ ማስረዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

16 እስቲ በመግቢያው ላይ የጠቀስነውን ምሳሌ መለስ ብለን እንመልከት። ለበሽታው መድኃኒት ያገኘው ሐኪም አንተ በተኛህበት ክፍል ውስጥ ላሉት ሕመምተኞች ‘ሕክምናውን የሚቀበልና የተሰጠውን መመሪያ የሚከተል ማንኛውም ሕመምተኛ ያለ ምንም ጥርጥር ከበሽታው ይድናል’ የሚል ሐሳብ አቀረበላቸው እንበል። አብዛኞቹ ሕመምተኞች መድኃኒቱን መውሰድ ወይም የተሰጣቸውን መመሪያ መከተል በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ በመግለጽ ሐኪሙ ያቀረበውን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆኑስ? መድኃኒቱ ሊያድንህ እንደሚችል የሚጠቁም አሳማኝ ማስረጃ ቢኖርም የሌሎቹን ሕመምተኞች ሐሳብ በመስማት ሕክምናውን ላለመቀበል ትመርጣለህ? እንደዚህ እንደማታደርግ የተረጋገጠ ነው! ሐኪሙ መድኃኒቱን ስላገኘ እንደምታመሰግነውና የሚሰጥህን መመሪያ በጥንቃቄ እንደምትከተል ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምናልባትም ያደረግኸውን ውሳኔ ለሌሎች ትናገር ይሆናል። ከዚህ በላቀ መልኩ እያንዳንዳችን ይሖዋ በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ላደረገልን የመዳን ዝግጅት ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆንን ለማሳየት ከልብ ልንነሳሳ ይገባል።—ሮም 6:17, 18ን አንብብ።

17. ይሖዋ አንተን ለማዳን ላደረገው ዝግጅት ያለህን አድናቆት በየትኞቹ መንገዶች ማሳየት ትችላለህ?

17 ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ እኛን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ሲሉ ያደረጉትን ዝግጅት የምናደንቅ ከሆነ ይህንን በተግባር እናሳያለን። (1 ዮሐ. 5:3) ኃጢአት እንድንሠራ የሚገፋፋንን ዝንባሌ እንታገለዋለን። በምንም ዓይነት ሆን ብለን በኃጢአት ጎዳና አንመላለስም፤ እንዲሁም ሁለት ዓይነት ሕይወት በመምራት ግብዞች አንሆንም። እንዲህ ዓይነት አካሄድ መከተል የቤዛውን ዝግጅት ከፍ አድርገን እንደማንመለከተው ወይም እንደማናደንቀው ከመግለጽ አይተናነስም። ከዚህ በተቃራኒ በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ይዘን ለመገኘት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ለቤዛው አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። (2 ጴጥ. 3:14) ግሩም የሆነውን የመዳን ተስፋችንን ለሌሎች በመናገርም አድናቆታችንን እንገልጻለን፤ እንዲህ ማድረጋችን እነሱም በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም እንዲኖራቸውና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲያገኙ ያስችላል። (1 ጢሞ. 4:16) ጊዜያችንንና ጉልበታችንን በሙሉ ይሖዋንና ልጁን ለማወደስ ማዋላችን ተገቢ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም! (ማር. 12:28-30) እስቲ አስበው! ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ የምንድንበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ እንችላለን። አምላክ መጀመሪያ አስቦት እንደነበረው ፍጹም ሆነን ለዘላለም መኖር እንችላለን፤ ይህ ሁሉ የሆነው ይሖዋ እኛን ለማዳን ዝግጅት በማድረጉ ነው!—ሮም 8:21

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 የኅዳር በሽታ በወቅቱ ከነበረው የዓለም ሕዝብ መካከል ከ20 እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን እንዳጠቃ ይነገራል። ቫይረሱ ከያዛቸው ሰዎች መካከል የሞቱት ከ1 እስከ 10 በመቶ ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ በተቃራኒ ኢቦላ ብዙ ጊዜ የማይከሰት ወረርሽኝ ቢሆንም ይህ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው አንዳንድ ወቅቶች በበሽታው ከተጠቁት ሰዎች መካከል ወደ 90 በመቶ የሚጠጉት ሞተዋል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• መዳን ማግኘትህ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ኢየሱስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ማድረጉ አንተን የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

• የይሖዋ ስጦታ ስለሆነው ስለቤዛው ዝግጅት ምን ይሰማሃል?

• ይሖዋ አንተን ለማዳን ያደረገው ዝግጅት ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስርየት ቀን ከሚከናወነው ነገር ጋር በተያያዘ በእስራኤል የነበረው ሊቀ ካህናት መሲሑን ይወክል ነበር

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም ልጁን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑ ይሖዋ ስለከፈለው ከዚያ የላቀ መሥዋዕት ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለ