በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጊዜ መድበሃል?

ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጊዜ መድበሃል?

ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጊዜ መድበሃል?

ባለፈው ዓመት የበላይ አካሉ በጉባኤ ስብሰባ ፕሮግራሞች ላይ ማስተካከያ እንደሚደረግ ያሳወቀ ሲሆን ይህ ማስተካከያ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና በቤተሰብ ደረጃ ለመወያየት የሚያስችል ሰፋ ያለ ጊዜ እንዲኖረን የሚረዳ ነው። የቤተሰብ ራስ ከሆንክ ከባለቤትህና ከልጆችህ ጋር ጠቃሚ የሆነ ብሎም የማያቋርጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም እንዲኖርህ አድርግ። ልጆች የሌሏቸው ባልና ሚስት ይህንን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን አብረው ለማጥናት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የቤተሰብ ኃላፊነት የሌለባቸው ነጠላ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ደግሞ ጊዜውን በግላቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ሊያውሉት ይችላሉ።

ብዙዎች የቤተሰብ አምልኮ የሚያደርጉበት ምሽት እንዲኖራቸው ለተደረገው ዝግጅት ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ለምሳሌ፣ ኬቨን የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የጉባኤው አባላት የተሰማንን ስሜት ‘እናመሰግናለን’ የሚለው ቃል አይገልጸውም። የጉባኤው ሽማግሌዎች አሁን ያገኘነውን ነፃ ጊዜ የበላይ አካሉ በሚፈልገው መሠረት ማለትም ከቤተሰባችን ጋር ለማጥናት ልንጠቀምበት ተነጋግረናል።”

ባለቤቷ ሽማግሌ የሆነው ጆዲ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ዕድሜያቸው 15፣ 11 እና 2 ዓመት የሆኑ ሦስት ሴቶች ልጆች አሉን። በምልክት ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ በቅርቡ ተዛውረናል። ለሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች መዘጋጀት ብዙ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ይህ ማስተካከያ ከተደረገ በኋላ ለቤተሰብ አምልኮ ትኩረት መስጠት የምንችልበት አንድ ተጨማሪ ምሽት አግኝተናል!”

ጆንና ጆአን የተባሉ አቅኚ የሆኑ ባልና ሚስት እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “በተለያዩ የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ስለምንወጠር የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምናደርገው አልፎ አልፎ ነበር። አዲስ የተደረገው ማስተካከያ ከይሖዋ ያገኘነው በመንፈሳዊ የሚያድስ ስጦታ ሆኖልናል፤ በእርግጥ ይህ የሚሆነው ያገኘነውን ጊዜ ለታሰበበት ዓላማ ከተጠቀምንበት ነው።”

ቶኒ የተባለው በ20ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኝ ነጠላ ወንድም የግል ጥናት ለማድረግ የመደበው ጊዜ ማክሰኞ ምሽት ነው። በሳምንቱ ውስጥ ሌላውን ጊዜ ለጉባኤ ስብሰባዎች ለመዘጋጀት ይጠቀምበታል። ይሁንና ቶኒ “ማክሰኞ እስኪደርስ እጓጓለሁ” ብሏል። እንዲህ ያለው ለምንድን ነው? “ይህ ጊዜ ከይሖዋ ጋር የማሳልፈው ልዩ ምሽት ነው። ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድና እንዲጠናከር በሚረዱኝ ርዕሶች ላይ ለሁለት ሰዓት ያህል ጥናት አደርጋለሁ። ለጥናት ሰፋ ያለ ጊዜ ማግኘቴ በማነባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ለማሰላሰል አስችሎኛል” ብሏል። እንዲህ በማድረጉ ምን ውጤት አግኝቷል? “ይሖዋ የሚሰጠኝ ምክር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ወደ ልቤ ጠልቆ እየገባ ነው” በማለት ተናግሯል። ለዚህም ምሳሌ ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል፦ “ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው መጽሐፍ ላይ በዳዊትና በዮናታን መካከል ስለነበረው ወዳጅነት አነበብኩ። ዮናታን ከነበረው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ባሕርይ ብዙ ተምሬያለሁ። እሱ የተወው ምሳሌ እውነተኛ ወዳጅ መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ይበልጥ እንድገነዘብ ረድቶኛል። ማክሰኞ ምሽት በማደርገው ጥናት እንደነዚህ ያሉ ተጨማሪ ዕንቁዎችን ለማግኘት እጓጓለሁ!”

ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ትርጉም ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ የሚያስችላቸው ተጨማሪ ጊዜ እንዲያገኙ በተደረገው ዝግጅት በሚገባ ከተጠቀሙ የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያገኙ ምንም ጥርጥር የለውም።