በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ሥር ሰዳችሁ በመሠረቱ ላይ ታንጻችኋል?’

‘ሥር ሰዳችሁ በመሠረቱ ላይ ታንጻችኋል?’

‘ሥር ሰዳችሁ በመሠረቱ ላይ ታንጻችኋል?’

ኃይለኛ ነፋስ አንድን ትልቅ ዛፍ ወዲያና ወዲህ ሲያወዛውዘው ተመልክተህ ታውቃለህ? ነፋሱ በኃይል ቢገፋውም ዛፉ አይወድቅም። ለምን? ዛፉ አፈሩን ጥብቅ አድርጎ የያዘ ጠንካራ ሥር ስላለው ነው። እኛም እንደዚህ ዛፍ መሆን እንችላለን። ምንጊዜም ‘ሥር ሰድደንና በመሠረቱ ላይ ታንጸን’ የምንመላለስ ከሆነ በሕይወታችን ውስጥ እንደ ኃይለኛ ነፋስ የሆኑ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን መጽናት እንችላለን። (ኤፌ. 3:14-17) እዚህ ላይ የተጠቀሰው መሠረት ምንድን ነው?

የክርስቲያን ጉባኤ “የማዕዘኑ የመሠረት ድንጋይ . . . ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው” በማለት የአምላክ ቃል ይናገራል። (ኤፌ. 2:20፤ 1 ቆሮ. 3:11) ክርስቲያኖች “ከእሱ ጋር በአንድነት መመላለሳችሁን ቀጥሉ፤ . . . በእሱ ላይ ተተክላችሁና ታንጻችሁ ኑሩ፤ እንዲሁም በእምነት ጸንታችሁ መኖራችሁን ቀጥሉ” የሚል ማበረታቻ ተሰጥቶናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በሰዎች “ከንቱ ማታለያ” ላይ የተመሠረቱ ‘ማግባቢያዎችን’ ጨምሮ በእምነታችን ላይ የሚሰነዘሩትን ጥቃቶች በሙሉ መቋቋም እንችላለን።—ቆላ. 2:4-8

“ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ”

ይሁንና ‘ሥር መስደድ’ እንዲሁም ‘በእምነት ጸንተን መኖር’ የምንችለው እንዴት ነው? በምሳሌያዊ አነጋገር ሥራችን አፈሩ ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ ማድረግ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል በትጋት ማጥናት ነው። ይሖዋ፣ የእውነት “ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር [በአእምሯችን] በሚገባ መረዳት” እንድንችል ይፈልጋል። (ኤፌ. 3:18) እንግዲያው ማንኛውም ክርስቲያን ጥልቀት የሌለው እውቀት በመቅሰም ማለትም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን “መሠረታዊ ነገሮች” በማወቅ ብቻ ረክቶ መቀመጥ የለበትም። (ዕብ. 5:12፤ 6:1) ከዚህ ይልቅ ሁላችንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት እውነቶች ጥልቀት ያለው እውቀት እንዲኖረን መጓጓት ይኖርብናል።—ምሳሌ 2:1-5

ይህ ሲባል ግን በእውነት ውስጥ ‘ሥር ለመስደድና በመሠረቱ ላይ ለመታነጽ’ የሚያስፈልገን ሰፊ እውቀት ማካበት ብቻ ነው ማለት እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ሰይጣንም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መልእክት ያውቀዋል። ስለዚህ ከእውቀት የበለጠ ነገር ያስፈልገናል። “ከእውቀት የሚልቀውን የክርስቶስ ፍቅር” ማወቅ ይኖርብናል። (ኤፌ. 3:19) መጽሐፍ ቅዱስን እንድናጠና የሚያነሳሳን ለይሖዋና ለእውነት ያለን ፍቅር ከሆነ ስለ አምላክ ቃል ያለን እውቀት እያደገ ይሄዳል፤ ይህም እምነታችን እንዲጠናከር ያደርጋል።—ቆላ. 2:2

እውቀታችሁን ፈትሹ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት በጣም አስፈላጊ የሆኑ እውነቶች መካከል አንዳንዶቹን ምን ያህል እንደምትረዳቸው ለማየት ለምን አሁኑኑ እውቀትህን አትፈትሽም? እንዲህ ማድረግህ የግል ጥናትህን ይበልጥ በትጋት እንድታከናውን ያበረታታህ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን ደብዳቤ የመጀመሪያ ቁጥሮች እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ጥቅሱን አንብበው። ( “ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ከዚያም ‘በሣጥኑ ውስጥ በተቀመጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ጋደል ተደርገው የተጻፉት ሐረጎች ምን ትርጉም እንዳላቸው ገብቶኛል?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። እስቲ እነዚህን ሐሳቦች ተራ በተራ እንመርምር።

“ዓለም ከመመሥረቱ በፊት” አስቀድሞ መርጦናል

ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “[አምላክ] በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የራሱ ልጆች እንድንሆን አስቀድሞ መርጦናል” በማለት ተናግሯል። ይሖዋ ከሰው ልጆች መካከል የተወሰኑትን እንደ ልጆቹ አድርጎ በመቁጠር በሰማይ የሚገኘው ፍጹም ቤተሰቡ አባላት እንዲሆኑ የማድረግ ዓላማ አለው። እንደ አምላክ ልጆች የመቆጠርን መብት ያገኙት እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሆነው ይገዛሉ። (ሮም 8:19-23፤ ራእይ 5:9, 10) ሰይጣን የይሖዋን ሉዓላዊነት መጀመሪያ በተገዳደረበት ወቅት የአምላክ ሰብዓዊ ፍጥረታት እንከን እንዳለባቸው የሚጠቁም ነገር ተናግሮ ነበር። ከዚህ አንጻር ይሖዋ፣ ከእነዚህ ሰብዓዊ ፍጥረታት መካከል አንዳንዶቹን በመምረጥ የክፋት ምንጭ የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን ማጥፋትን ጨምሮ አጽናፈ ዓለምን ከማንኛውም ክፋት በማጽዳት ረገድ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረጉ ምንኛ የተገባ ነው! ይሁንና በግለሰብ ደረጃ እንደ ልጆች የመቆጠርን መብት የሚያገኙት የትኞቹ ሰዎች እንደሚሆኑ ይሖዋ አስቀድሞ አልወሰነም። ከዚህ ይልቅ አምላክ፣ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዛ የተወሰኑ ሰዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን እንደሚኖር አስቀድሞ ወስኗል።—ራእይ 14:3, 4

ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ “ዓለም ከመመሥረቱ በፊት” በቡድን ደረጃ እንደተመረጡ ሲጽፍላቸው ስለ የትኛው “ዓለም” መናገሩ ነበር? አምላክ ምድርንም ሆነ የሰውን ዘር ከመፍጠሩ በፊት ስለነበረው ጊዜ መናገሩ አልነበረም። ጳውሎስ የተናገረው ስለዚህ ጊዜ ቢሆን ኖሮ የፍትሕ መሠረታዊ ሥርዓት ይጣሳል። አዳምና ሔዋን ከመፈጠራቸው አስቀድሞ አምላክ በኃጢአት እንደሚወድቁ ወስኖ ከነበረ እነዚህ ሰዎች ለወሰዱት እርምጃ እንዴት ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ? ታዲያ አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ጋር በመተባበር በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ ባመፁበት ወቅት ይሖዋ የተፈጠረውን ሁኔታ እንዴት እንደሚያስተካክለው የወሰነው መቼ ነበር? ይሖዋ ይህን ውሳኔ ያደረገው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ካመፁ በኋላ ሆኖም ፍጽምና ቢጎድለውም ከኃጢአት ሊቤዥ የሚችለው የሰው ዘር ዓለም ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት ነበር።

“በአምላክ የተትረፈረፈ ጸጋ መሠረት”

በኤፌሶን መጽሐፍ የመጀመሪያ ቁጥሮች ላይ የተጠቀሰው ዝግጅት “በአምላክ የተትረፈረፈ ጸጋ መሠረት” የተደረገ እንደሆነ ጳውሎስ የገለጸው ለምንድን ነው? ይህን ያለው ይሖዋ በኃጢአት የወደቀውን የሰው ዘር የመዋጀት ግዴታ እንደሌለበት ለማጉላት ፈልጎ ነው።

ማንኛችንም ብንሆን በራሳችን ከኃጢአት መቤዠት የሚገባን እንድንሆን የሚያደርገን ነገር የለንም። ሆኖም ይሖዋ ለሰው ዘር ቤተሰብ ባለው ጥልቅ ፍቅር ተነሳስቶ እኛን ለመቤዠት ልዩ ዝግጅት አድርጓል። ፍጽምና የጎደለንና ኃጢአተኞች ከመሆናችን አንጻር የተደረገልን የመዳን ዝግጅት ጳውሎስ እንዳለው በእርግጥም የአምላክ ጸጋ መግለጫ ነው።

የአምላክ ዓላማ ቅዱስ ሚስጥር

አምላክ ሰይጣን ያስከተለውን ጉዳት እንዴት እንደሚያስተካክለው መጀመሪያ ላይ አልገለጸም ነበር። ይህ “ቅዱስ ሚስጥር” ነበር። (ኤፌ. 3:4, 5) ከጊዜ በኋላ የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም ይሖዋ ለሰው ዘርም ሆነ ለምድር ያለውን የመጀመሪያ ዓላማ እንዴት እንደሚፈጽመው በዝርዝር ገለጸ። “በተወሰኑት ዘመናት ማብቂያ ላይ” አምላክ “አስተዳደር” እንዳቋቋመ ማለትም የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራኑን በሙሉ አንድ ለማድረግ ነገሮችን የሚያስተዳድርበትን መንገድ እንዳዘጋጀ ጳውሎስ ገልጿል።

የማሰብ ችሎታ ያላቸውን የአምላክ ፍጥረታት በሙሉ አንድ ለማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ የተወሰደው በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት ይሖዋ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙትን መሰብሰብ በጀመረበት ጊዜ ነበር። (ሥራ 1:13-15፤ 2:1-4) ሁለተኛው እርምጃ ደግሞ በክርስቶስ መሲሐዊ መንግሥት ሥር ገነት በሆነችው ምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች መሰብሰባቸው ይሆናል። (ራእይ 7:14-17፤ 21:1-5) “አስተዳደር” የሚለው ቃል መሲሐዊውን መንግሥት የሚያመለክት አይደለም፤ ምክንያቱም ይህ መንግሥት እስከ 1914 ድረስ አልተቋቋመም። ከዚህ ይልቅ ቃሉ፣ አምላክ ፍጥረታቱ በሙሉ እንደገና አንድ እንዲሆኑ የማድረግ ዓላማውን ለማስፈጸም ነገሮችን የሚያከናውንበትን ወይም የሚያስተዳድርበትን መንገድ ያመለክታል።

“በማስተዋል ችሎታችሁ የጎለመሳችሁ ሁኑ”

ጥሩ የግል ጥናት ልማድ የእውነት “ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ” ሙሉ በሙሉ ለመረዳት እንደሚያስችልህ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጆች ሕይወት በጥድፊያ የተሞላ መሆኑ ሰይጣን ይህንን ልማድ ለማጥፋት ባይችል እንኳ እንዲዳከም ለማድረግ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥርለታል። ሰይጣን የግል ጥናት ልማድህን እንዳያዳክምብህ ተጠንቀቅ። አምላክ በሰጠህ “የማስተዋል ችሎታ” በመጠቀም በመረዳት ችሎታህ ረገድ ‘የጎለመስክ ሁን።’ (1 ዮሐ. 5:20፤ 1 ቆሮ. 14:20) የምታምንበትን ነገር ለምን እንደምታምንበት መረዳት እንዲሁም ‘ስላለህ ተስፋ ምንጊዜም ምክንያት’ ለመስጠት ዝግጁ መሆን ይኖርብሃል።—1 ጴጥ. 3:15

የጳውሎስ ደብዳቤ መጀመሪያ በተነበበበት ወቅት በኤፌሶን እንደነበርክ አድርገህ አስብ። ሐዋርያው የጻፈው ሐሳብ “ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም” ረገድ እድገት እንድታደርግ አያነሳሳህም ነበር? (ኤፌ. 4:13, 14) እንዲህ ለማድረግ እንደሚያነሳሳህ ምንም ጥርጥር የለውም! እንግዲያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የጻፈው ሐሳብ በዛሬው ጊዜም እድገት ለማድረግ እንዲያንቀሳቅስህ ምኞታችን ነው። ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ማዳበርህና ስለ ቃሉ ትክክለኛ እውቀት መቅሰምህ በማይነቃነቅ ሁኔታ ‘ሥር እንድትሰድና በክርስቶስ መሠረት ላይ እንድትታነጽ’ ይረዳሃል። እንዲህ ካደረግህ ይህ ክፉ ዓለም ሙሉ በሙሉ የሚጠፋበት ጊዜ ከመድረሱ በፊት ሰይጣን የሚያመጣብህን ማንኛውንም ዓይነት እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ፈተና በጽናት ለመቋቋም ትችላለህ።—መዝ. 1:1-3፤ ኤር. 17:7, 8

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 “ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ”

“ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ስለባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ በፊቱ ቅዱሳንና እንከን የለሽ ሆነን በፍቅር እንድንገኝ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት ከክርስቶስ ጋር አንድ እንድንሆን መርጦናል። ደግሞም እንደወደደውና እንደ በጎ ፈቃዱ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የራሱ ልጆች እንድንሆን አስቀድሞ መርጦናል፤ ይኸውም በተወደደው ልጁ አማካኝነት በደግነት ለእኛ በሰጠው ክቡር ጸጋ የተነሳ እንዲመሰገን ነው። በአምላክ የተትረፈረፈ ጸጋ መሠረት ልጁ ቤዛውን በመክፈል በደሙ አማካኝነት ነፃ እንድንወጣ ማለትም ለበደላችን ይቅርታ እንድናገኝ አድርጎናል። ጸጋውንም ከጥበብና ከማስተዋል ሁሉ ጋር አትረፍርፎ ሰጥቶናል፤ በዚህም የፈቃዱን ቅዱስ ሚስጥር አሳውቆናል። ይህ ሚስጥር ደግሞ በልቡ ካሰበው በጎ ሐሳቡ ጋር የሚስማማ ነው፤ ሐሳቡም በተወሰኑት ዘመናት ማብቂያ ላይ ለማቋቋም ባሰበው አስተዳደር አማካኝነት ሁሉንም ነገሮች ይኸውም በሰማያት ያሉትን ነገሮችና በምድር ያሉትን ነገሮች እንደገና በክርስቶስ አንድ ላይ ለመጠቅለል ነው። አዎ፣ በእሱ አማካኝነት ሁሉም ነገሮች አንድ ላይ ይጠቃለላሉ።”—ኤፌ. 1:3-10