በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ”

“በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ”

“በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ”

“በሥራችሁ አትለግሙ። በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ። ይሖዋን እንደ ባሪያ አገልግሉ።”—ሮም 12:11

1. እስራኤላውያን የእንስሳትና ሌሎች መሥዋዕቶች የሚያቀርቡት ለምን ነበር?

የይሖዋ አገልጋዮች ለእሱ ፍቅር እንዳላቸውና ለፈቃዱ እንደሚገዙ ለማሳየት በፈቃደኝነት የሚያቀርቧቸውን መሥዋዕቶች አምላክ ያደንቃል። በጥንት ጊዜያት ይሖዋ የተለያዩ የእንስሳት መሥዋዕቶችንና ሌሎች መሥዋዕቶችን ተቀብሏል። እስራኤላውያን የሙሴ ሕግ በሚያዘው መሠረት እነዚህን መሥዋዕቶች የሚያቀርቡት የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘትና አመስጋኝነታቸውን ለመግለጽ ነበር። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ይሖዋ አንድን ዓይነት ሥርዓት በተከተለ መልኩ የእንስሳት ወይም የሌሎች ነገሮች መሥዋዕት እንድናቀርብ አይጠብቅብንም። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ምዕራፍ 12 ላይ እንደገለጸው በአሁኑ ጊዜም ቢሆን መሥዋዕት ማቅረብ ይጠበቅብናል። ይህንን የምናደርገው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ሕያው መሥዋዕት

2. ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ምን ዓይነት ሕይወት መምራት ይኖርብናል? ይህስ ምን ማድረግን ይጨምራል?

2 ሮም 12:1, 2ን አንብብ። ጳውሎስ በደብዳቤው መጀመሪያ ላይ አይሁዳውያንም ሆኑ አሕዛብ የሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአምላክ ፊት ጻድቃን ተብለው ሊጠሩ የሚችሉት በሥራ ሳይሆን በእምነት መሆኑን በግልጽ አብራርቶ ነበር። (ሮም 1:16፤ 3:20-24) ጳውሎስ በምዕራፍ 12 ላይ ክርስቲያኖች የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ሕይወት በመምራት አመስጋኝነታችንን ማሳየት እንዳለብን ገልጿል። ይህንንም ለማድረግ አእምሯችንን ማደስ ያስፈልገናል። በወረስነው አለፍጽምና የተነሳ ‘በኃጢአትና በሞት ሕግ’ ሥር ነን። (ሮም 8:2) በመሆኑም መለወጥ ይኸውም ዝንባሌያችንን ሙሉ በሙሉ በመቀየር ‘አእምሯችንን በሚያሠራው ኃይል መታደስ’ ይኖርብናል። (ኤፌ. 4:23) እንዲህ ያለ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ የምንችለው የአምላክንና የመንፈሱን እርዳታ ካገኘን ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ‘በማሰብ ችሎታችን’ መጠቀምና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ይህም ሲባል ብልሹ ሥነ ምግባርና ወራዳ የሆኑ መዝናኛዎች የሞሉበትን እንዲሁም የተዛባ አስተሳሰብ የሚንጸባረቅበትን ‘የዚህን ሥርዓት የአኗኗር ዘይቤ ላለመኮረጅ’ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል ማለት ነው።—ኤፌ. 2:1-3

3. በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች የምንካፈለው ለምንድን ነው?

3 በተጨማሪም ጳውሎስ ‘የማሰብ ችሎታችንን’ ተጠቅመን “ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ” ራሳችን መርምረን እንድናረጋግጥ ጋብዞናል። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የምናነበው፣ ባነበብነው ነገር ላይ የምናሰላስለው፣ የምንጸልየው፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምንገኘው እንዲሁም የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ የምንካፈለው ለምንድን ነው? የጉባኤ ሽማግሌዎች እነዚህን ነገሮች እንድናደርግ ስለሚያሳስቡን ነው? እውነት ነው፣ ሽማግሌዎች ለሚሰጡን ጠቃሚ ማሳሰቢያዎች አመስጋኞች ነን። ሆኖም በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች የምንካፈለው ለይሖዋ ያለንን ልባዊ ፍቅር በተግባር እንድናሳይ የአምላክ መንፈስ ስለሚያነሳሳን ነው። ከዚህም በተጨማሪ እንደነዚህ ባሉት እንቅስቃሴዎች መካፈል የአምላክን ፈቃድ ማድረግ መሆኑን ስላመንበት ነው። (ዘካ. 4:6፤ ኤፌ. 5:10) በእውነተኛ የክርስትና ሕይወት በመመላለስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እንደምንችል መገንዘባችን ታላቅ ደስታና እርካታ ያስገኝልናል።

የተለያዩ ስጦታዎች

4, 5. ክርስቲያን ሽማግሌዎች ስጦታቸውን እንዴት ሊጠቀሙበት ይገባል?

4 ሮም 12:6-8, 11ን አንብብ። ጳውሎስ “በተሰጠን ጸጋ መሠረት የተለያዩ ስጦታዎች” እንዳሉን ገልጿል። ሐዋርያው ከጠቀሳቸው ስጦታዎች አንዳንዶቹ መምከርና ማስተዳደር ሲሆኑ እነዚህ በተለይ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን የሚመለከቱ ናቸው፤ ሽማግሌዎች “በትጋት” እንዲያስተዳድሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።

5 ጳውሎስ፣ የበላይ ተመልካቾች በሚያስተምሩበት እንዲሁም ‘በሚያገለግሉበት’ ጊዜም እንዲህ ያለውን ትጋት ማሳየት እንዳለባቸው ገልጿል። በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው ጳውሎስ “ማገልገል” ሲል “አንድ አካል” በማለት በጠቀሰው ጉባኤ ውስጥ የሚከናወነውን አገልግሎት ማመልከቱ ይመስላል። (ሮም 12:4, 5) ይህ አገልግሎት በ⁠ሐዋርያት ሥራ 6:4 (አ.መ.ት.) ላይ ከተጠቀሰው ጋር ተመሳሳይ ነው፤ በዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያት “እኛ ግን በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት እንተጋለን” ብለው ነበር። እንዲህ ዓይነቱ አገልግሎት ምን ነገሮችን ይጨምራል? ክርስቲያን ሽማግሌዎች የተቀበሉትን ስጦታ የጉባኤውን አባላት ለማነጽ ይጠቀሙበታል። ሽማግሌዎች ለጉባኤው ከአምላክ ቃል በትጋት መመሪያና ትምህርት መስጠት አለባቸው፤ ይህንን ሥራ በአግባቡ የሚያከናውኑት ጸሎት የታከለበት ጥናትና ምርምር በማድረግ፣ በማስተማር እንዲሁም እረኝነት በማድረግ ነው። ሽማግሌዎች ይህንን ሁሉ የሚያከናውኑ ከሆነ በትጋት ‘ማገልገላቸውን እንደቀጠሉ’ ያሳያሉ። የበላይ ተመልካቾች በጎቹን “በደስታ” ለመንከባከብና ስጦታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።—ሮም 12:7, 8፤ 1 ጴጥ. 5:1-3

6. ይህ የጥናት ርዕስ የተመሠረተበትን በ⁠ሮም 12:11 ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

6 በተጨማሪም ጳውሎስ “በሥራችሁ አትለግሙ። በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ። ይሖዋን እንደ ባሪያ አገልግሉ” ብሏል። ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት እንደቀዘቀዘ ከተሰማን የጥናት ልማዳችንን መመርመር እንዲሁም የይሖዋን መንፈስ ለማግኘት አጥብቀንና አዘውትረን መጸለይ ይኖርብን ይሆናል፤ የይሖዋ መንፈስ ለብ ያልን እንዳንሆንና ቅንዓታችን እንደገና እንዲቀጣጠል ሊረዳን ይችላል። (ሉቃስ 11:9, 13፤ ራእይ 2:4፤ 3:14, 15, 19) መንፈስ ቅዱስ በጥንት ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” እንዲናገሩ ኃይል ሰጥቷቸዋል። (ሥራ 2:4, 11) እኛም በአገልግሎት ቀናተኛ እንዲሁም ‘በመንፈስ የጋልን እንድንሆን’ መንፈስ ቅዱስ ሊያነሳሳን ይችላል።

ትሕትና እና ልክን ማወቅ

7. አገልግሎታችንን በምናከናውንበት ጊዜ ትሑቶችና ልካችንን የምናውቅ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

7 ሮም 12:3, 16ን አንብብ። ያሉንን ስጦታዎች ያገኘነው በይሖዋ “ጸጋ” ነው። ጳውሎስ በሌላ ጥቅስ ላይ “ብቃታችንን ያገኘነው ከአምላክ ነው” ሲል ገልጿል። (2 ቆሮ. 3:5) ስለዚህ ራሳችንን ከፍ ከፍ ማድረግ የለብንም። በአገልግሎታችን ፍሬያማ መሆን የቻልነው በራሳችን ብቃት ሳይሆን አምላክ ስለባረከን እንደሆነ በትሕትና አምነን መቀበል ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 3:6, 7) ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት” የሚል ምክር ሰጥቷል። ለራሳችን ጥሩ ግምት መያዛችን እንዲሁም ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት ደስታና እርካታ ማግኘታችን ተገቢ ነው። ሆኖም ልካችንን ማወቃችን ወይም አቅማችን ውስን መሆኑን መገንዘባችን ግትር ከመሆን ይጠብቀናል። እንዲሁም ‘ጤናማ አእምሮ እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማሰብ’ እንፈልጋለን።

8. ‘ራሳችንን ልባሞች አድርገን ከመቁጠር’ እንድንቆጠብ የሚረዳን ምንድን ነው?

8 ባከናወንናቸው ነገሮች መኩራራት ሞኝነት ነው። “የሚያሳድገው አምላክ” መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 3:7) አምላክ ለእያንዳንዱ የጉባኤው አባል የተወሰነ መጠን ያለው “እምነት” እንደሰጠው ጳውሎስ ገልጿል። ከሌሎች እንደምንበልጥ አድርገን ከማሰብ ይልቅ ሌሎች በተሰጣቸው እምነት መጠን የሚያከናውኑትን ነገር ከፍ አድርገን መመልከት ይኖርብናል። ጳውሎስ አክሎም “ለራሳችሁ ያላችሁ ዓይነት አመለካከት ለሌሎችም ይኑራችሁ” ብሏል። ሐዋርያው በሌላ ደብዳቤው ላይ ደግሞ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ አድርጋችሁ በትሕትና አስቡ እንጂ በምቀኝነት ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ” ሲል መክሮናል። (ፊል. 2:3) ሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሆነ መልኩ ከእኛ እንደሚበልጡ አድርገን ለማሰብ እውነተኛ ትሕትና ሊኖረንና ልባዊ ጥረት ልናደርግ ይገባል። ትሕትና ‘ራሳችንን ልባሞች አድርገን ከመቁጠር’ እንድንቆጠብ ሊረዳን ይችላል። አንዳንዶች ልዩ የሆኑ የአገልግሎት መብቶች ያሏቸው መሆኑ ትኩረት እንዲሰጣቸው ሊያደርግ ቢችልም ሁላችንም ‘ትሕትና የሚንጸባረቅባቸውን’ ሥራዎች ማለትም ብዙውን ጊዜ ሰዎች ትኩረት የማይሰጧቸውን ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ተግባሮች በማከናወን ከፍተኛ ደስታ ማግኘት እንችላለን።—1 ጴጥ. 5:5

ክርስቲያናዊ አንድነታችን

9. ጳውሎስ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ከአካል ክፍሎች ጋር ያመሳሰላቸው ለምንድን ነው?

9 ሮም 12:4, 5, 9, 10ን አንብብ። ጳውሎስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ከአካል ክፍሎች ጋር ያመሳሰላቸው ሲሆን ራሳቸው በሆነው በክርስቶስ ሥር በአንድነት እንደሚያገለግሉ ገልጿል። (ቆላ. 1:18) ጳውሎስ፣ በአንድ አካል ላይ የተለያዩ ሥራዎች ያሏቸው ብዙ የአካል ክፍሎች እንዳሉና እነዚህ የአካል ክፍሎች ‘ብዙ ቢሆኑም እንኳ ከክርስቶስ ጋር ባላቸው አንድነት አንድ አካል እንደሆኑ’ በመንፈስ ለተቀቡት ክርስቲያኖች አስታውሷቸዋል። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ጳውሎስ በኤፌሶን የሚገኙትን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል፦ “በሁሉም ነገር ወደ እሱ ይኸውም ራስ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ በፍቅር እንደግ። እሱን መሠረት በማድረግ፣ የአካል ክፍሎች ሁሉ አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሚያሟላው በእያንዳንዱ መገጣጠሚያ አማካኝነት እርስ በርስ ተስማምተው እየተገጣጠሙና እያንዳንዱ የአካል ክፍል እንደ አቅሙ በሚያከናውነው የሥራ ድርሻ መሠረት እርስ በርስ ተደጋግፈው እየሠሩ፣ አካሉ እንዲያድግና በፍቅር ራሱን እንዲያንጽ ያደርጉታል።”—ኤፌ. 4:15, 16

10. “ሌሎች በጎች” የእነማንን ሥልጣን መቀበል ይኖርባቸዋል?

10 “ሌሎች በጎች” የክርስቶስ አካል ክፍል ባይሆኑም ከዚህ ምሳሌ ብዙ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። (ዮሐ. 10:16) ይሖዋ “ሁሉንም ነገር [ለክርስቶስ] ከእግሩ በታች አስገዛለት፤ ከጉባኤው ጋር በተያያዘም በሁሉ ነገር ላይ ራስ አደረገው” በማለት ጳውሎስ ተናግሯል። (ኤፌ. 1:22) አምላክ በልጁ የራስነት ሥልጣን ሥር እንዲሆኑ ያደረጋቸው ‘ሁሉም ነገሮች’ በዛሬው ጊዜ ሌሎች በጎችንም ይጨምራሉ። ሌሎች በጎች፣ ክርስቶስ ‘ለታማኝና ልባም ባሪያው’ በአደራ ከሰጣቸው ‘ንብረቶች’ መካከልም ይገኙበታል። (ማቴ. 24:45-47) በመሆኑም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች፣ ክርስቶስ ራሳቸው መሆኑን መቀበል የሚገባቸው ከመሆኑም ሌላ ለታማኝና ልባም ባሪያ እንዲሁም ለበላይ አካሉ አልፎ ተርፎም በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆነው ለተሾሙት ወንዶች መገዛት ይኖርባቸዋል። (ዕብ. 13:7, 17) እንዲህ ማድረጋቸው ክርስቲያናዊ አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል።

11. አንድነታችን በምን ላይ የተመሠረተ ነው? ጳውሎስ ምን ተጨማሪ ምክር ሰጥቷል?

11 እንዲህ ያለው አንድነት “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” በሆነው በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው። (ቆላ. 3:14) ጳውሎስ በ⁠ሮም ምዕራፍ 12 ላይ ይህን ሲያጎላ ፍቅራችን “ግብዝነት የሌለበት” መሆን እንደሚገባውና “በወንድማማች ፍቅር” ‘እርስ በርሳችን ከልብ መዋደድ’ እንዳለብን ተናግሯል። እንዲህ ያለው ፍቅር እርስ በርስ እንድንከባበር ያደርገናል። ሐዋርያው “አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ” በማለት ተናግሯል። እርግጥ ነው፣ ፍቅራችንን ስንገልጽ ተገቢ ያልሆነ ታማኝነት እናሳያለን ማለት አይደለም። የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ጳውሎስ ስለ ፍቅር በሰጠው ምክር ላይ አክሎ “ክፉ የሆነውን ነገር ተጸየፉ፤ ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቃችሁ ያዙ” በማለት ተናግሯል።

የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል

12. የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየት ረገድ በጥንቷ መቄዶንያ ከነበሩት ክርስቲያኖች ምን መማር እንችላለን?

12 ሮም 12:13ን አንብብ። ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር አቅማችን በፈቀደ መጠን ‘ለቅዱሳን እንደየችግራቸው ያለንን እንድናካፍል’ ያነሳሳናል። ኑሯችን ዝቅተኛ ቢሆንም ያለንን ነገር ለሌሎች ማካፈል እንችላለን። ጳውሎስ በመቄዶንያ የሚገኙ ክርስቲያኖችን አስመልክቶ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ከባድ ፈተና ደርሶባቸው በመከራ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ታላቅ ደስታ የነበራቸው ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ልግስና አሳይተዋል፤ ይህንም ያደረጉት ከባድ ድህነት ውስጥ እያሉ ነው። እንደ አቅማቸው እንዲያውም ከአቅማቸው በላይ እንደሰጡ እመሠክርላቸዋለሁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ወንድሞች [በይሁዳ ላሉት ቅዱሳን] የልግስና ስጦታ ለመስጠትና በዚህ መንገድ እነሱን ከሌሎች ጋር ለማገልገል የሚያስችል መብት እንዲሰጣቸው በራሳቸው ፍላጎት ተነሳስተው ይለምኑን እንዲያውም ይማጸኑን ነበር።” (2 ቆሮ. 8:2-4) በመቄዶንያ የነበሩት ክርስቲያኖች ድሆች ቢሆኑም በጣም ለጋሶች ነበሩ። በይሁዳ ለሚገኙት ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞቻቸው ያላቸውን ማካፈልን እንደ መብት ቆጥረውት ነበር።

13. ‘የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል ማዳበር’ ሲባል ምን ማለት ነው?

13 “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል አዳብሩ” የሚለው ሐረግ በራስ ተነሳሽነት አንድ ነገር ማድረግን ከሚያመለክት የግሪክኛ አገላለጽ የተተረጎመ ነው። ዘ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል ይህንን አገላለጽ “እንግዳ ተቀባይ ለመሆን አጋጣሚዎችን ፈልጉ” በማለት ተርጉሞታል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ምግብ በመጋበዝ የእንግዳ ተቀባይነትን መንፈስ ማሳየት ይቻላል፤ ይህንን የምናደርገው በፍቅር ተነሳስተን ከሆነ የሚያስመሰግን ተግባር ነው። በዚህ ረገድ ተነሳሽነቱ ካለን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስን ማሳየት የምንችልባቸው ሌሎች በርካታ መንገዶችም አሉ። ምግብ ሠርተን ሌሎችን ለመጋበዝ ኢኮኖሚያችን ወይም ጤንነታችን የማይፈቅድ ከሆነ ሻይ ቡና ወይም ሌሎች ቀለል ያሉ ነገሮችን መጋበዝም እንግዳ ተቀባይ መሆናችንን ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ነው።

14. (ሀ) “እንግዳ ተቀባይነት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል የየትኞቹ ቃላት ጥምረት ነው? (ለ) በአገልግሎት ላይ ለሌላ አገር ዜጎች ያለንን አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 እንግዳ ተቀባይ መሆን ከአመለካከታችን ጋር የተያያዘ ነገር ነው። “እንግዳ ተቀባይነት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ፍቅር” እና “እንግዳ” የሚል ትርጉም ያላቸው ሁለት ቃላት ጥምረት ነው። ስለ እንግዶች ወይም ስለ ሌላ አገር ዜጎች ምን አመለካከት አለን? ወደ ጉባኤያቸው ክልል ለመጡ የሌላ አገር ዜጎች ምሥራቹን ለመስበክ ሲሉ ሌላ ቋንቋ ለመማር ጥረት የሚያደርጉ ክርስቲያኖች በእውነትም የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል እያዳበሩ ነው። እርግጥ ነው፣ አብዛኞቻችን ሌላ ቋንቋ ለመማር ሁኔታችን አይፈቅድ ይሆናል። ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በበርካታ ቋንቋዎች የያዘውን ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች የተባለውን ቡክሌት ጥሩ አድርገን በመጠቀም ሁላችንም የሌላ አገር ዜጎችን መርዳት እንችላለን። ይህንን ቡክሌት በአገልግሎት ላይ በመጠቀም ጥሩ ውጤት አግኝተሃል?

የሌሎችን ስሜት መጋራት

15. ኢየሱስ በ⁠ሮም 12:15 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ያደረገው እንዴት ነው?

15 ሮም 12:15ን አንብብ። ጳውሎስ በዚህ ጥቅስ ላይ የሰጠውን ምክር ‘የሌሎችን ስሜት መጋራት’ በሚለው ሐረግ ጠቅለል አድርገን መግለጽ እንችላለን። ደስታም ይሁን ሐዘን የሌላውን ሰው ስሜት መረዳትንና አልፎ ተርፎም ስሜቱን መጋራትን መማር አለብን። በመንፈስ የጋልን ከሆንን የሌሎች ደስታ እንደሚያስደስተን ወይም ሐዘናቸው እንደሚያሳዝነን በግልጽ ይታያል። ሰባዎቹ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከስብከት ዘመቻቸው ደስ ብሏቸው ሲመለሱና ያገኙትን ጥሩ ውጤት ለኢየሱስ ሲነግሩት ኢየሱስ “በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት አድርጎ” ነበር። (ሉቃስ 10:17-21) ኢየሱስ ደስታቸውን ተጋርቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ወዳጁ አልዓዛር በሞተ ጊዜ ‘ከሚያለቅሱ ሰዎች ጋር አልቅሷል።’—ዮሐ. 11:32-35

16. የሌሎችን ስሜት እንደምንጋራ እንዴት ማሳየት እንችላለን? በተለይ እነማን ይህን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?

16 እኛም የሌሎችን ስሜት በመጋራት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንፈልጋለን። አንድ የእምነት ባልንጀራችን ሲደሰት እኛም የደስታው ተካፋይ መሆናችንን በግልጽ ማሳየት እንፈልጋለን። በሌላ በኩል ደግሞ የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን መከራና ሐዘን ሊሰማን ይገባል። የስሜት ሥቃይ እየደረሰባቸው ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ጊዜ ሰጥተን ስሜታቸውን እንደምንረዳላቸው በሚያሳይ መንገድ ማዳመጣችን አብዛኛውን ጊዜ እፎይታ ሊያመጣላቸው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ባጋጠማቸው ሁኔታ ልባችን በጥልቅ በመነካቱ እናለቅስ ይሆናል። (1 ጴጥ. 1:22) በተለይ ሽማግሌዎች የሌሎችን ስሜት በመጋራት ረገድ ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

17. በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ከሮም ምዕራፍ 12 ምን ትምህርት አግኝተናል? በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?

17 በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ ከ⁠ሮም ምዕራፍ 12 ላይ የመረመርናቸው ጥቅሶች በክርስትና ሕይወታችን እንዲሁም ከወንድሞቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ተግባራዊ ልናደርገው የምንችል ጥሩ ምክር ሰጥተውናል። በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ደግሞ ተቃዋሚዎችንና አሳዳጆችን ጨምሮ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ላሉት ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ እንዲሁም ከእነሱ ጋር ያለን ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት የሚያወሱትን ከዚህ ምዕራፍ የቀሩትን ቁጥሮች እንመረምራለን።

ለክለሳ ያህል

• ‘በመንፈስ የጋልን’ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• አገልግሎታችንን በምናከናውንበት ጊዜ ትሑቶችና ልካችንን የምናውቅ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

• የእምነት ባልንጀሮቻችንን ስሜት እንደምንጋራና እንደምናዝንላቸው ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእነዚህ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች የምንካፈለው ለምንድን ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁላችንም የሌላ አገር ዜጎች ስለ መንግሥቱ ምሥራች እንዲማሩ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?