በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ’

‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ’

‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ’

“ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።”—ሮም 12:18

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? (ለ) ተቃውሞ በሚያጋጥመን ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚጠቁም ምክር ከየት ማግኘት እንችላለን?

ኢየሱስ ተከታዮቹን በዓለም ያሉ ሰዎች ስደት እንደሚያደርሱባቸው አስጠንቅቋቸው ነበር፤ ተቃውሞ የሚደርስባቸው ለምን እንደሆነ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ሲገልጽ ለሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የዓለም ክፍል ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ የሆነውን በወደደ ነበር። አሁን ግን እኔ ከዓለም መረጥኳችሁ እንጂ የዓለም ክፍል ስላልሆናችሁ ከዚህ የተነሳ ዓለም ይጠላችኋል።”—ዮሐ. 15:19

2 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን በሕይወቱ ተመልክቷል። ጳውሎስ የአገልግሎት ባልደረባው ለነበረው ለወጣቱ ጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “አንተ ግን ትምህርቴን፣ አኗኗሬን፣ ዓላማዬን፣ እምነቴን፣ ትዕግሥቴን፣ ፍቅሬንና ጽናቴን በጥብቅ ተከትለሃል፤ በተጨማሪም የደረሰብኝን ስደትና መከራ . . . ታውቃለህ።” ከዚያም ጳውሎስ “በእርግጥም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል” ብሏል። (2 ጢሞ. 3:10-12) ጳውሎስ ወደ ሮም በጻፈው ደብዳቤ ምዕራፍ 12 ላይ ክርስቲያኖች ተቃውሞ ሲደርስባቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚጠቁም ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷል። እሱ የሰጠው ምክር በመጨረሻው ዘመን ለምንኖረው ክርስቲያኖችም መመሪያ ሊሆን ይችላል።

“መልካም የሆነውን አድርጉ”

3, 4. በ⁠ሮም 12:17 ላይ የሚገኘውን ምክር (ሀ) በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ (ለ) ከጎረቤቶቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

3 ሮም 12:17ን አንብብ። ጳውሎስ ሰዎች በሚጠሉን ጊዜ አጸፋውን መመለስ እንደሌለብን ገልጿል። በተለይም በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። አንድ ክርስቲያን የማታምን የትዳር ጓደኛው ደግነት የጎደለው ነገር ስትናገረው ወይም ስታደርግበት እሱም በዚያው መንገድ ምላሽ መስጠት አይኖርበትም። ‘በክፉ ፋንታ ክፉ መመለስ’ ምንም ጥቅም አያስገኝም። እንዲህ ማድረግ ሁኔታውን ከማባባስ በቀር የሚፈይደው ነገር የለም።

4 ከዚህ በተቃራኒ ምን ማድረግ እንደሚሻል ጳውሎስ ሲገልጽ “በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አድርጉ” ብሏል። በቤተሰብ ውስጥ አንዲት ሚስት ባለቤቷ እምነቷን በተመለከተ ደስ የማይል ሐሳብ በሚሰነዝርበት ጊዜ ከልቧ ደግነት ማሳየቷ ሊፈጠር የሚችለውን ጭቅጭቅ ያስቀር ይሆናል። (ምሳሌ 31:12) አሁን በቤቴል የሚያገለግለው ካርሎስ፣ እናቱ ምንጊዜም ደግነት በማሳየትና ቤቷን በደንብ በመያዝ ባለቤቷ የሚያደርስባትን ከፍተኛ ተቃውሞ እንዴት መቋቋም እንደቻለች ያስታውሳል። ካርሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ምንጊዜም አባታችንን እንድናከብረው ታበረታታን ነበር። ቡል የተሰኘውን የፈረንሳይ ጨዋታ እኔ ባልወደውም ከአባቴ ጋር እንድጫወት ትገፋፋኝ ነበር። አብረን መጫወታችን አባቴን ያስደስተው ነበር።” የካርሎስ አባት ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንቶ ለመጠመቅ በቅቷል። በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋ ወቅት ጎረቤቶቻቸውን በመርዳት “በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን” በማድረጋቸው ሰዎች ስለ እነሱ ያላቸውን መሠረተ ቢስ ጥላቻ ብዙውን ጊዜ ማስወገድ ችለዋል።

‘ፍም በመከመር’ ተቃውሞ እንዲቀልጥ ማድረግ

5, 6. (ሀ) በጠላት ራስ ላይ “ፍም” መከመር ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) በ⁠ሮም 12:20 ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ መልካም ውጤት ሊያስገኝ የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ በአካባቢህ የተገኘ ተሞክሮ ተናገር።

5 ሮም 12:20ን አንብብ። ጳውሎስ በዚህ ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ሲጽፍ ምሳሌ 25:21, 22⁠ን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም ውሃ አጠጣው። ይህን በማድረግህም፣ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ፤ እግዚአብሔርም ዋጋህን ይከፍልሃል።” ጳውሎስ በ⁠ሮም ምዕራፍ 12 ላይ ከሰጠው ምክር አንጻር እዚህ ላይ ፍምን የጠቀሰው ተቃዋሚውን መቅጣትን ወይም ማሳፈርን ለማመልከት እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ ይልቅ በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰውም ሆነ ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች የጻፈው ሐሳብ፣ በጥንት ጊዜ ሰዎች ብረት ለማቅለጥ የሚጠቀሙበትን ዘዴ የሚያመለክት ይመስላል። በ19ኛው መቶ ዘመን የኖሩት ቻርልስ ብሪጅስ የተባሉ የእንግሊዝ ምሑር እንዲህ ብለዋል፦ “በቀላሉ የማይቀልጠውን ብረት እሳት ላይ ያስቀምጡና በላዩ ላይ ፍም በመከመር ብረቱ ከታች ብቻ ሳይሆን ከላይም እሳት እንዲያገኘው ያደርጉ ነበር። ትዕግሥት፣ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ እና የሞቀ ፍቅር የሚያሳድሩት ተጽዕኖ የማያቀልጡት ልብ የለም ማለት ይቻላል።”

6 “ፍም” ብረትን እንደሚያቀልጠው ሁሉ የደግነት ተግባርም የተቃዋሚው ልብ እንዲለወጥ ምናልባትም ጥላቻው ቀልጦ እንዲወገድ ሊያደርግ ይችላል። የይሖዋ ሕዝቦች የሚያከናውኑት የደግነት ተግባር ሰዎች ለእነሱም ሆነ ለሚሰብኩት የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ምንም እንኳ ክፉ አድራጊዎች እንደሆናችሁ አድርገው ቢናገሩም አምላክ ለመመርመር በሚመጣበት ቀን እነሱ ራሳቸው በዓይናቸው ባዩት መልካም ሥራችሁ የተነሳ አምላክን እንዲያከብሩ በአሕዛብ መካከል መልካም ምግባር ይዛችሁ ኑሩ።”—1 ጴጥ. 2:12

‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ’

7. ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የሚተውላቸው ሰላም ምን ያመለክታል? እንዲህ ያለው ሰላምስ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

7 ሮም 12:18ን አንብብ። ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 14:27) ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የሚተውላቸው ሰላም፣ ይሖዋ አምላክና ውድ ልጁ እንደሚወዷቸውና በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኙ ሲሰማቸው የሚኖራቸውን ውስጣዊ መረጋጋት ያመለክታል። ይህ ውስጣዊ ሰላም ከሌሎች ጋር በሰላም እንድንኖር ሊያነሳሳን ይገባል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ሰላም ወዳዶች እንዲሁም ሰላም ፈጣሪዎች ናቸው።—ማቴ. 5:9

8. በቤተሰባችንም ሆነ በጉባኤያችን ውስጥ ሰላም ፈጣሪ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

8 በቤተሰብ ውስጥ ሰላም ፈጣሪ መሆን የሚቻልበት አንዱ መንገድ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ሁኔታው እየተባባሰ እንዲሄድ ከመፍቀድ ይልቅ ችግሩን በተቻለ መጠን በአፋጣኝ መፍታት ነው። (ምሳሌ 15:18፤ ኤፌ. 4:26) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ይሠራል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሰላምን መከታተልን ምላስን ከክፉ ነገር ከመከልከል ጋር አያይዞታል። (1 ጴጥ. 3:10, 11) ያዕቆብም ምላስን በተገቢው መንገድ ስለመጠቀም እንዲሁም ቅናትንና ምቀኝነትን ስለማስወገድ ጠንከር ያለ ምክር ከሰጠ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ከላይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም በአድልዎ ሰዎችን የማይለያይና ግብዝነት የሌለበት ነው። ከዚህም በላይ ሰላም ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች የጽድቅን ዘር ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ይዘሩና የጽድቅ ፍሬ ያጭዳሉ።”—ያዕ. 3:17, 18

9. “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር” ጥረት ስናደርግ የትኛውን ነጥብ መዘንጋት አይኖርብንም?

9 ጳውሎስ በ⁠ሮም 12:18 ላይ ሰላማዊ ስለመሆን የሰጠው ምክር ከቤተሰብና ከጉባኤ ውጭም እንደሚሠራ ጠቁሟል። ሐዋርያው “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር” ጥረት ማድረግ እንዳለብን ተናግሯል። ይህ ደግሞ ጎረቤቶቻችንን፣ የሥራ ባልደረቦቻችንን አብረውን የሚማሩትን ልጆች እንዲሁም በአገልግሎት የምናገኛቸውን ሰዎች ይጨምራል። ሆኖም ሐዋርያው ምክሩን ይበልጥ ግልጽ ሲያደርገው “በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” ብሏል። እንዲህ ሲባል “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር” የምንችለውን ሁሉ ብናደርግም የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች እስከመጣስ ድረስ እንሄዳለን ማለት ግን አይደለም።

በቀል የይሖዋ ነው

10, 11. “ለአምላክ ቁጣ ዕድል” መስጠት ሲባል ምን ማለት ነው? እንዲህ ማድረጋችን ተገቢ የሚሆነውስ ለምንድን ነው?

10 ሮም 12:19ን አንብብ። በቀጥታ የሚቃወሙንን ጨምሮ ለሥራችንና ለመልእክታችን ‘ቀና አመለካከት ከሌላቸው’ ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት እንኳ ‘ክፉ ነገር ሲደርስብን በትዕግሥት ልናሳልፍ’ እንዲሁም ነገሮችን “በገርነት” ልንይዝ ይገባል። (2 ጢሞ. 2:23-25) ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ራሳቸው እንዳይበቀሉ ከዚህ ይልቅ “ለአምላክ ቁጣ ዕድል” እንዲሰጡ መክሯቸዋል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን በቀል የእኛ እንዳልሆነ እናውቃለን። መዝሙራዊው “ከንዴት ተቈጠብ፤ ቍጣንም ተወው፤ ወደ እኵይ ተግባር እንዳይመራህ አትከፋ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 37:8) ሰለሞንም “‘ለደረሰብኝ በደል ብድሬን ባልመልስ!’ አትበል፤ እግዚአብሔርን ጠብቅ፤ እርሱ ይታደግሃል” የሚል ምክር ሰጥቷል።—ምሳሌ 20:22

11 ተቃዋሚዎች የሚጎዳን ነገር ቢያደርጉብን ይሖዋ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው እሱ ባሰበው ጊዜ እንዲቀጣቸው ነገሩን ለእሱ መተዉ የጥበብ አካሄድ ነው። ጳውሎስ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ይላል ይሖዋ” ተብሎ እንደተጻፈ ገልጿል። (ከ⁠ዘዳግም 32:35 ጋር አወዳድር።) ራሳችን ለመበቀል መሞከር ይሖዋ ሊወስደው የሚገባውን እርምጃ እኛ መውሰድ ይሆንብናል፤ ይህም ቦታችንን አለማወቅ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ “እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” በማለት በገባው ቃል ላይ እምነት እንደጎደለን የሚያሳይ ይሆናል።

12. የይሖዋ ቁጣ የሚገለጠው መቼና እንዴት ነው?

12 ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ መግቢያ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እውነትን ለማፈን የተንኮል ዘዴ የሚጠቀሙ ሰዎች በሚፈጽሙት አምላክን የሚጻረር ድርጊትና ክፋት ሁሉ ላይ የአምላክ ቁጣ ከሰማይ ይገለጣል።” (ሮም 1:18) ይሖዋ “ታላቁን መከራ” በሚያመጣበት ወቅት በልጁ አማካኝነት ከሰማይ ቁጣውን ይገልጣል። (ራእይ 7:14) ይህም “አምላክ ትክክለኛ ፍርድ እንደፈረደ የሚያሳይ ማስረጃ” እንደሚሆን ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት በጻፈው ሌላ ደብዳቤ ላይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከዚህ አንጻር አምላክ መከራን ለሚያመጡባችሁ በአጸፋው መከራን መክፈሉ የጽድቅ እርምጃ ነው፤ መከራን ለምትቀበሉት ለእናንተ ግን ጌታ ኢየሱስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ከእኛ ጋር እረፍትን ይሰጣችኋል፤ ከሰማይ የሚገለጠውም በሚንበለበል እሳት ነው፤ በዚያን ጊዜ አምላክን በማያውቁትና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች በማይታዘዙት ላይ የበቀል እርምጃ ይወስዳል።”—2 ተሰ. 1:5-8

ክፉውን በመልካም ማሸነፍ

13, 14. (ሀ) ተቃውሞ ሲያጋጥመን ግራ የማንጋባው ለምንድን ነው? (ለ) የሚያሳድዱንን ሰዎች መባረክ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ሮም 12:14, 21ን አንብብ። ይሖዋ ዓላማዎቹን እንደሚፈጽም ሙሉ በሙሉ በመተማመን እሱ እንድናከናውነው በሰጠን ተልእኮ ማለትም “በመላው ምድር” ላይ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በመስበኩ ሥራ በተሟላ መንገድ ለመካፈል ጥረት ማድረግ እንችላለን። (ማቴ. 24:14) ኢየሱስ “በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት ስላስጠነቀቀን የምናከናውነው ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ጠላቶቻችንን እንደሚያስቆጣቸው እናውቃለን። (ማቴ. 24:9) በመሆኑም ተቃውሞ ሲያጋጥመን ግራ አንጋባም ወይም ተስፋ አንቆርጥም። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እንደ እሳት በሚያቃጥሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ስትፈተኑ እንግዳ የሆነ ነገር እንደደረሰባችሁ አድርጋችሁ በማሰብ ግራ አትጋቡ። ከዚህ ይልቅ ክርስቶስ . . . የተቀበለው መከራ ተካፋዮች በሆናችሁበት በዚያው መጠን ምንጊዜም ደስ ይበላችሁ።”—1 ጴጥ. 4:12, 13

14 የሚያሳድዱንን ሰዎች ከመጥላት ይልቅ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ይህን የሚያደርጉት ባለማወቅ ሊሆን እንደሚችል በመገንዘብ እነሱን ለማስተማር ጥረት እናደርጋለን። (2 ቆሮ. 4:4) “ስደት የሚያደርሱባችሁን መባረካችሁን ቀጥሉ፤ ባርኩ እንጂ አትርገሙ” የሚለውን የጳውሎስ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እንጥራለን። (ሮም 12:14) ተቃዋሚዎቻችንን መባረክ የምንችልበት አንዱ መንገድ ለእነሱ መጸለይ ነው። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን፣ ለሚጠሏችሁ መልካም ማድረጋችሁን፣ የሚረግሟችሁን መመረቃችሁን እንዲሁም ለሚሰድቧችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 6:27, 28) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አሳዳጅ የሆነ ሰው ተለውጦ ታማኝ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሁም ቀናተኛ የይሖዋ አገልጋይ ሊሆን እንደሚችል ከራሱ ተሞክሮ ያውቅ ነበር። (ገላ. 1:13-16, 23) ጳውሎስ በሌላ ደብዳቤው ላይ “ሲሰድቡን እንባርካለን፤ ስደት ሲያደርሱብን ችለን እንኖራለን፤ ስማችንን ሲያጠፉት በለሰለሰ አንደበት እንማጸናለን” ብሏል።—1 ቆሮ. 4:12, 13

15. ክፉውን በመልካም ለማሸነፍ ከሁሉ የተሻለው መንገድ የትኛው ነው?

15 ከላይ ከተመለከትነው አንጻር አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በ⁠ሮም ምዕራፍ 12 የመጨረሻ ቁጥር ላይ የሚገኘውን “በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ያደርጋል። የክፋት ሁሉ ምንጭ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (ዮሐ. 8:44፤ 1 ዮሐ. 5:19) ለሐዋርያው ዮሐንስ በተሰጠው ራእይ ላይ ኢየሱስ፣ ቅቡዓን ወንድሞቹ ‘ከበጉ ደም የተነሳና ከምሥክርነታቸው ቃል የተነሳ ሰይጣንን ድል እንደነሱት’ ገልጧል። (ራእይ 12:11) ይህም ሰይጣንንም ሆነ በዚህ ሥርዓት ላይ የሚያሳድረውን መጥፎ ተጽዕኖ ድል መንሳት የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ በምሥክርነቱ ሥራ መልካም ማድረግ ማለትም የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ እንደሆነ ያሳያል።

በተስፋው ደስ ይበላችሁ

16, 17. ሮም ምዕራፍ 12 (ሀ) ሕይወታችንን እንዴት ልንጠቀምበት እንደሚገባ (ለ) በጉባኤ ውስጥ እንዴት ልንመላለስ እንደሚገባ (ሐ) እምነታችንን የሚቃወሙ ሰዎችን እንዴት ልንይዛቸው እንደሚገባ ምን አስተምሮናል?

16 ጳውሎስ በሮም ለሚገኙት ክርስቲያኖች የጻፈውን ደብዳቤ 12ኛ ምዕራፍ አጠር ባለ መልኩ መመርመራችን ብዙ ነገሮችን አስታውሶናል። ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንን አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች መሆን እንዳለብን ተምረናል። የአምላክ መንፈስ በፈቃደኝነት መሥዋዕትነት እንድንከፍል ያነሳሳናል፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረግ የአምላክ ፈቃድ መሆኑን በማሰብ ችሎታችን ተጠቅመን አረጋግጠናል። በመንፈስ የጋልን ከመሆናችንም በላይ ያሉንን የተለያዩ ስጦታዎች በቅንዓት እንጠቀምባቸዋለን። በትሕትና እንዲሁም ልካችንን በማወቅ አምላክን እናገለግላለን፤ ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ለመጠበቅ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል እናዳብራለን፤ እንዲሁም የሌሎችን ስሜት እንደምንጋራ እናሳያለን።

17 ሮም ምዕራፍ 12 ተቃውሞ ሲያጋጥመን ምን ማድረግ እንዳለብንም ሰፋ ያለ ምክር ይሰጠናል። አጸፋ መመለስ የለብንም። ከዚህ በተቃራኒ ተቃውሞ ሲያጋጥመን ደግነት የተንጸባረቀበት እርምጃ ለመውሰድ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ሳንጥስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ከቤተሰባችንና ከጉባኤው አባላት እንዲሁም ከጎረቤቶቻችን፣ ከሥራ ባልደረቦቻችን፣ አብረውን ከሚማሩት ልጆችና በአገልግሎት ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ሰዎች እንደሚጠሉን በግልጽ ቢያሳዩንም በቀል የይሖዋ እንደሆነ በማስታወስ ክፉውን በመልካም ለማሸነፍ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።

18. በ⁠ሮም 12:12 ላይ ምን ሦስት ምክሮች ተሰጥተዋል?

18 ሮም 12:12ን አንብብ። ጳውሎስ ከእነዚህ ሁሉ ጥበብ ያዘሉና ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦች በተጨማሪ ሦስት ምክሮችን ሰጥቷል። የይሖዋን እርዳታ ካላገኘን እነዚህን ሁሉ ነገሮች በፍጹም ማከናወን ስለማንችል ሐዋርያው “በጽናት ጸልዩ” በማለት መክሮናል። እንዲህ ማድረጋችን “መከራን በጽናት ተቋቋሙ” በማለት ቀጥሎ የሰጠውን ምክር ለመከተል ይረዳናል። በመጨረሻም ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በገባው ቃል ላይ በማተኮር በሰማይ አሊያም በምድር የዘላለም ሕይወት በማግኘት ‘ተስፋችን መደሰት’ ይኖርብናል።

ለክለሳ ያህል

• ተቃውሞ ሲደርስብን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

• በየትኞቹ መስኮች ሰላም ፈጣሪ ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል? ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

• ራሳችን ለመበቀል መሞከር የሌለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጎረቤቶቻችንን መርዳታችን ሰዎች ስለ እኛ ያላቸውን መሠረተ ቢስ ጥላቻ ለማስወገድ ሊረዳን ይችላል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጉባኤ ውስጥ ሰላም ፈጣሪ ለመሆን ጥረት ታደርጋለህ?