በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ወዳጆቼ ናችሁ”

“ወዳጆቼ ናችሁ”

“ወዳጆቼ ናችሁ”

“እያዘዝኳችሁ ያለውን ነገር የምትፈጽሙ ከሆነ ወዳጆቼ ናችሁ።”—ዮሐንስ 15:14

1, 2. (ሀ) የኢየሱስ ወዳጆች ምን ዓይነት አስተዳደግና የኑሮ ሁኔታ ነበራቸው? (ለ) የኢየሱስ ወዳጅ መሆናችን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው የምንለው ለምንድን ነው?

በሰገነት ላይ ባለው ክፍል ውስጥ ከኢየሱስ ጋር የነበሩት ሰዎች የተለያየ አስተዳደግና የኑሮ ሁኔታ ነበራቸው። ጴጥሮስና እንድርያስ የተባሉት ወንድማማቾች ዓሣ አጥማጆች ነበሩ። ማቴዎስ ቀደም ሲል ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረ ሲሆን ይህ ሞያ በአይሁዳውያን ዘንድ የተጠላ ነበር። እንደ ያዕቆብና ዮሐንስ ያሉት ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን ከልጅነቱ ጀምሮ ሳያውቁት አይቀሩም። እንደ ናትናኤል ያሉት ደግሞ ኢየሱስን ካወቁት ብዙም አልቆዩ ይሆናል። (ዮሐ. 1:43-50) ያም ሆኖ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ያንን የፋሲካ በዓል ለማክበር በኢየሩሳሌም የተሰበሰቡት ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ፣ የሕያው አምላክ ልጅ እንደሆነ እርግጠኞች ነበሩ። (ዮሐ. 6:68, 69) እነዚህ ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ “ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ” ብሎ ሲናገር መስማታቸው ልባቸው በደስታ እንዲሞላ እንዳደረገ ምንም ጥርጥር የለውም።—ዮሐ. 15:15

2 ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ የተናገረው ይህ ሐሳብ በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ በዛሬው ጊዜ የሚገኙትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ አልፎ ተርፎም “ሌሎች በጎች” የተባሉትን አጋሮቻቸውን ይመለከታል። (ዮሐ. 10:16) እኛም የኋላ ታሪካችን ምንም ይሁን ምን የኢየሱስ ወዳጅ የመሆን መብት ማግኘት እንችላለን። ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት መመሥረታችን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው፤ ምክንያቱም የእሱ ወዳጅ መሆናችን የይሖዋ ወዳጆችም ለመሆን ያስችለናል። እንዲያውም ወደ ኢየሱስ ሳንቀርብ ወደ ይሖዋ መቅረብ ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው። (ዮሐንስ 14:6, 21ን አንብብ።) ታዲያ ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረትና ይህን ወዳጅነት ጠብቀን ለማቆየት ምን ማድረግ አለብን? ይህን አስፈላጊ ጉዳይ ከመመልከታችን በፊት ጥሩ ወዳጅ በመሆን ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንመርምር፤ እንዲሁም ደቀ መዛሙርቱ ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረታቸው ካሳደረባቸው በጎ ተጽዕኖ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እንመልከት።

ኢየሱስ ጥሩ ወዳጅ በመሆን ረገድ የተወው ምሳሌ

3. ኢየሱስ የሚታወቀው በምን ነበር?

3 ንጉሥ ሰለሞን “ባለጠጎች . . . ብዙ ወዳጆች አሏቸው” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 14:20) ይህ አባባል ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ያላቸውን ዝንባሌ ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል፤ ብዙዎች ወዳጅነት የሚመሠረቱት ለሌሎች የሚሰጡትን ሳይሆን ከእነሱ የሚያገኙትን ነገር በማሰብ ነው። ኢየሱስ ግን እንዲህ ዓይነት ድክመት አልነበረበትም። የሰዎች የኑሮ ደረጃ ወይም በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው ቦታ በጓደኛ ምርጫው ረገድ ተጽዕኖ አላደረገበትም። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ከአይሁድ አለቆች አንዱ የሆነውን ሀብታም ወጣት ስለወደደው ተከታዩ እንዲሆን ግብዣ አቅርቦለት ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ወጣቱ ያለውን ሸጦ ለድሆች እንዲሰጥ ነግሮታል። (ማር. 10:17-22፤ ሉቃስ 18:18, 23) ኢየሱስ የሚታወቀው ሀብታምና ዝነኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመወዳጀት ሳይሆን በኅብረተሰቡ ዘንድ ዝቅ ተደርገው ከሚታዩና ከተናቁ ግለሰቦች ጋር ወዳጅነት በመመሥረቱ ነው።—ማቴ. 11:19

4. የኢየሱስ ወዳጆች ጉድለቶች ያሏቸው ሰዎች ነበሩ የምንለው ለምንድን ነው?

4 እርግጥ ነው፣ የኢየሱስ ወዳጆች ጉድለቶች ያሏቸው ሰዎች ነበሩ። ጴጥሮስ ነገሮችን በመንፈሳዊ ዓይን ለመመልከት የተቸገረበት ወቅት ነበር። (ማቴ. 16:21-23) ያዕቆብና ዮሐንስ ደግሞ በመንግሥቱ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው ኢየሱስን መጠየቃቸው ትልቅ ቦታ የማግኘት ምኞት እንደነበራቸው ያሳያል። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ያደረጉት ነገር ሌሎቹን ሐዋርያት አስቆጥቷቸዋል፤ ሐዋርያቱ ትልቅ ቦታ የማግኘት ምኞት ስለነበራቸው በመካከላቸው ሁልጊዜ አለመግባባት ይፈጠር ነበር። ሆኖም ኢየሱስ በትዕግሥት የወዳጆቹን አስተሳሰብ ለማስተካከል ከመሞከሩም ሌላ በእነሱ ቶሎ አይበሳጭም ነበር።—ማቴ. 20:20-28

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ ከአብዛኞቹ ሐዋርያቱ ጋር ወዳጅነቱን የቀጠለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ከይሁዳ ጋር የነበረው ወዳጅነት እንዲቋረጥ ያደረገው ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ፍጽምና ከጎደላቸው ከእነዚህ ሰዎች ጋር ወዳጅነቱን የቀጠለው ምንም ቢያደርጉ ግድ ስለማይሰጠው ወይም ጉድለታቸው ስለማይታየው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ትኩረት ያደረገው ባሏቸው መልካም ባሕርያት እንዲሁም ውስጣዊ ዝንባሌያቸው ጥሩ በመሆኑ ላይ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞት በነበረበት ወቅት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ እሱን ከመደገፍ ይልቅ እንቅልፍ ጥሏቸው ነበር። በዚህ ወቅት ኢየሱስ እንዳዘነባቸው ግልጽ ነው። ያም ቢሆን ውስጣዊ ዝንባሌያቸው ጥሩ እንደሆነ ስላስተዋለ “መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው” ብሏቸዋል።—ማቴ. 26:41

6 ከዚህ በተቃራኒ ግን ኢየሱስ ከአስቆሮቱ ይሁዳ ጋር የነበረው ወዳጅነት እንዲቋረጥ አድርጓል። ይሁዳ ጥሩ ወዳጅ እንደሆነ ለማስመሰል ቢሞክርም ኢየሱስ፣ የቅርብ ወዳጁ የነበረው የዚህ ሰው የልብ ዝንባሌ መጥፎ መሆን እንደጀመረ አስተውሎ ነበር። ይሁዳ የዓለም ወዳጅ በመሆኑ ራሱን የአምላክ ጠላት አድርጓል። (ያዕ. 4:4) በዚህም የተነሳ ኢየሱስ ለ11ዱ ታማኝ ሐዋርያት ወዳጆቹ እንደሆኑ ከመናገሩ በፊት ይሁዳን አስወጥቶታል።—ዮሐ. 13:21-35

7, 8. ኢየሱስ ለወዳጆቹ ያለውን ፍቅር የገለጸው እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ ታማኝ ወዳጆቹ በሚሠሯቸው ስህተቶች ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ለእነሱ የሚበጀውን ነገር አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ፈተና በሚያጋጥማቸው ጊዜ አባቱ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:11ን አንብብ።) ኢየሱስ አቅማቸው ውስን መሆኑን ከግምት በማስገባት አሳቢነት አሳይቷቸዋል። (ማር. 6:30-32) ከዚህም ሌላ የራሱን ሐሳብ ብቻ ከመናገር ይልቅ የእነሱን ሐሳብና ስሜት ለመስማትና ለመረዳት ይፈልግ ነበር።—ማቴ. 16:13-16፤ 17:24-26

8 ኢየሱስ በሕይወቱም ሆነ በሞቱ ወዳጆቹን የሚጠቅም ነገር አከናውኗል። እርግጥ ነው፣ በሕጉ መሠረት የአባቱ የፍትሕ መሥፈርት እንዲሟላ ሕይወቱን መሥዋዕት ማድረግ እንደሚኖርበት ያውቅ ነበር። (ማቴ. 26:27, 28፤ ዕብ. 9:22, 28) ሆኖም ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠው ፍቅሩን ለመግለጽ ነው። “ነፍሱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም” ብሏል።—ዮሐ. 15:13

ደቀ መዛሙርቱ ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረታቸው ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል?

9, 10. ኢየሱስ ለጋስ መሆኑ ሰዎች ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል?

9 ኢየሱስ ጊዜውን በመስጠት፣ ፍቅሩን በማሳየትና ያለውን በማካፈል ረገድ ለጋስ ነበር። በዚህም የተነሳ ሰዎች ወደ እሱ ይቀርቡ የነበረ ከመሆኑም በላይ በምላሹ ለእሱ መስጠት ያስደስታቸው ነበር። (ሉቃስ 8:1-3) ኢየሱስ በራሱ ሕይወት ከተመለከተው በመነሳት እንዲህ ማለት ይችል ነበር፦ “ሰጪዎች ሁኑ፤ ሰዎችም ይሰጧችኋል። ተትረፍርፎ እስኪፈስ ድረስ በተጠቀጠቀና በተነቀነቀ ጥሩ መስፈሪያ ሰፍረው በእቅፋችሁ ይሰጧችኋል። ምክንያቱም በምትሰፍሩበት መስፈሪያ መልሰው ይሰፍሩላችኋል።”—ሉቃስ 6:38

10 እርግጥ ነው፣ አንዳንዶች ከኢየሱስ ጋር መቀራረብ የፈለጉት ከእሱ የሚያገኙትን ጥቅም በማሰብ ብቻ ነበር። እነዚህ የሐሰት ወዳጆች በአንድ ወቅት ኢየሱስ የተናገረውን ነገር በተሳሳተ መንገድ ስለተረዱት ጥለውት ሄዱ። ኢየሱስ የተናገረው ነገር ባይገባቸውም እንኳ ጥርጣሬያቸውን እንዲያስወግድላቸው ዕድል ከመስጠት ይልቅ ቸኩለው የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ በመድረስ ትተውት ሄደዋል። ከዚህ በተቃራኒ ሐዋርያቱ ለእሱ ታማኝ ነበሩ። ከኢየሱስ ጋር የነበራቸው ወዳጅነት በተደጋጋሚ ቢፈተንም በመልካምም ሆነ በክፉ ጊዜ ከጎኑ ለመቆም የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። (ዮሐንስ 6:26, 56, 60, 66-68ን አንብብ።) ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ “እናንተ በፈተናዎቼ ከጎኔ ሳትለዩ ቆይታችኋል” በማለት ለእነሱ ያለውን አድናቆት ገልጿል።—ሉቃስ 22:28

11, 12. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ወዳጃቸው መሆኑን በድጋሚ ያረጋገጠላቸው እንዴት ነው? ደቀ መዛሙርቱስ ምን አደረጉ?

11 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ታማኝ በመሆናቸው ካመሰገናቸው ብዙም ሳይቆይ እነዚሁ ሰዎች ትተውት ሸሹ። የሰው ፍርሃት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ለክርስቶስ ያላቸው ፍቅር እንዲደበዝዝ አድርጎ ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን ኢየሱስ ይቅር ብሏቸዋል። ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ለእነሱ በመገለጥ ወዳጃቸው መሆኑን በድጋሚ አረጋግጦላቸዋል። ከዚህም በላይ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን” ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉና “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ምሥክሮቹ እንዲሆኑ በማዘዝ ቅዱስ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:19፤ ሥራ 1:8) ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ ምን አደረጉ?

12 ደቀ መዛሙርቱ የመንግሥቱን መልእክት ለማሰራጨት ሁለንተናቸውን ሰጥተዋል። በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በመታገዝ ብዙም ሳይቆዩ ኢየሩሳሌምን በትምህርታቸው ሞሏት። (ሥራ 5:27-29) የኢየሱስ ተከታዮች፣ እንደሚገደሉ ዛቻ ቢደርስባቸውም እንኳ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ክርስቶስ የሰጣቸውን ትእዛዝ ከመፈጸም ወደኋላ አላሉም። የኢየሱስን ትእዛዝ በተቀበሉ በጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ መካከል” እንደተሰበከ ሐዋርያው ጳውሎስ መጻፍ ችሎ ነበር። (ቆላ. 1:23) በእርግጥም፣ እነዚህ ደቀ መዛሙርት ከኢየሱስ ጋር ለመሠረቱት የጠበቀ ወዳጅነት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡት በተግባር አሳይተዋል!

13. የኢየሱስ ትምህርት ደቀ መዛሙርቱን ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል?

13 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ትምህርቱ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል። ብዙዎቹ በአኗኗራቸውና በባሕርያቸው ረገድ ትልቅ ለውጥ ማድረግ አስፈልጓቸዋል። ደቀ መዛሙርት ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ግብረ ሰዶማውያን፣ አመንዝሮች፣ ሰካራሞች ወይም ሌቦች ነበሩ። (1 ቆሮ. 6:9-11) አንዳንዶቹ ደግሞ ሌላ ዘር ላላቸው ሰዎች የነበራቸውን አመለካከት ማስተካከል አስፈልጓቸዋል። (ሥራ 10:25-28) ያም ቢሆን ኢየሱስን ታዘዋል። አሮጌውን ስብዕናቸውን አውልቀው አዲሱን ስብዕና ለብሰዋል። (ኤፌ. 4:20-24) የኢየሱስን አስተሳሰብና ድርጊት በመማር እንዲሁም ከዚያ ጋር ተስማምተው በመኖር “የክርስቶስ አስተሳሰብ” እንዳላቸው አሳይተዋል።—1 ቆሮ. 2:16

በዛሬው ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ወዳጅነት መመሥረት

14. ኢየሱስ ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ወቅት ምን ለማድረግ ቃል ገብቶ ነበር?

14 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ብዙ ክርስቲያኖች ኢየሱስን በግለሰብ ደረጃ ያውቁት ነበር፤ አሊያም ከሞት ከተነሳ በኋላ አይተውታል። እኛ ግን እንዲህ ዓይነት መብት እንዳላገኘን ግልጽ ነው። ታዲያ የክርስቶስ ወዳጆች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያሉትን በመንፈስ የተቀቡ የኢየሱስ ወንድሞች ያቀፈው ታማኝና ልባም ባሪያ የሚሰጠውን መመሪያ በመታዘዝ ነው። ኢየሱስ ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ወቅት ይህን ባሪያ “በንብረቱ ሁሉ ላይ” እንደሚሾመው ቃል ገብቶ ነበር። (ማቴ. 24:3, 45-47) በዛሬው ጊዜ የክርስቶስ ወዳጅ መሆን የሚፈልጉት አብዛኞቹ ሰዎች የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል አይደሉም። እነዚህ ሰዎች ከታማኝና ልባም ባሪያ ለሚያገኙት መመሪያ የሚሰጡት ምላሽ ከክርስቶስ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት የሚነካው እንዴት ነው?

15. አንድ ሰው ከበግ ወይም ከፍየል ወገን የሚመደበው በምን መሠረት ነው?

15 ማቴዎስ 25:31-40ን አንብብ። ኢየሱስ የታማኙ ባሪያ አባላት የእሱ ወንድሞች እንደሆኑ ተናግሯል። ኢየሱስ፣ በጎቹን ከፍየሎቹ ስለመለየት በሰጠው ምሳሌ ላይ በግልጽ እንደተናገረው ለወንድሞቹ የምናደርገውን ነገር ለእሱ እንዳደረግነው አድርጎ ይቆጥረዋል። እንዲያውም ኢየሱስ በጎቹን ከፍየሎቹ የሚለያቸው ‘ከሁሉ ለሚያንሱት ለእነዚህ ወንድሞቹ’ ያደረጉትን ነገር በማየት እንደሆነ ገልጿል። በመሆኑም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች የክርስቶስ ወዳጅ ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳዩበት ዋነኛው መንገድ ታማኙን ባሪያ በመደገፍ ነው።

16, 17. የክርስቶስ ወንድሞች ወዳጅ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ተስፋህ በአምላክ መንግሥት ሥር በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ከሆነ የክርስቶስ ወንድሞች ወዳጅ መሆንህን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ይህንን ማሳየት የምትችልባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት። በመጀመሪያ፣ በስብከቱ ሥራ በሙሉ ልብ በመካፈል ነው። ክርስቶስ ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ እንዲሰብኩ ለወንድሞቹ ትእዛዝ ሰጥቷል። (ማቴ. 24:14) ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የቀሩት የክርስቶስ ወንድሞች፣ አጋሮቻቸው የሆኑትን የሌሎች በጎችን እገዛ ሳያገኙ ይህን ኃላፊነት መወጣት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ ሰዎች በስብከቱ ሥራ በሚካፈሉበት ጊዜ ሁሉ የክርስቶስ ወንድሞች የተሰጣቸውን ቅዱስ ተልእኮ እንዲወጡ እየረዷቸው ነው ማለት ይቻላል። እንደ ክርስቶስ ሁሉ ታማኝና ልባም ባሪያም የወዳጅነት መግለጫ የሆነውን ይህን ተግባር ያደንቃል።

17 ሌሎች በጎች የክርስቶስ ወንድሞችን መርዳት የሚችሉበት ሁለተኛው መንገድ የስብከቱን ሥራ በገንዘብ በመደገፍ ነው። ኢየሱስ “በዓመፅ ሀብት” ለራሳቸው ወዳጆች እንዲያፈሩ ተከታዮቹን አበረታቷቸው ነበር። (ሉቃስ 16:9) ይህ ሲባል የኢየሱስን ወይም የይሖዋን ወዳጅነት በገንዘብ መግዛት እንችላለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቁሳዊ ሀብታችንን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለመደገፍ በማዋል ወዳጅነታችንንና ፍቅራችንን በቃል ብቻ ሳይሆን “በተግባርና በእውነት” መግለጽ እንችላለን ማለት ነው። (1 ዮሐ. 3:16-18) እንዲህ ዓይነቱን ቁሳዊ ድጋፍ የምናደርገው በስብከቱ ሥራ በመካፈል፣ የአምልኮ ቦታዎቻችንን ለመገንባትና ለመጠገን የሚውል ገንዘብ በማዋጣት እንዲሁም ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ የገንዘብ መዋጮ በማድረግ ነው። የምንሰጠው የገንዘብ መጠን ምንም ያህል ቢሆን ይሖዋና ኢየሱስ በደስታ የምናደርገውን ልግስና እንደሚያደንቁት ምንም ጥርጥር የለውም።—2 ቆሮ. 9:7

18. የጉባኤ ሽማግሌዎች የሚሰጡንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ መታዘዝ ያለብን ለምንድን ነው?

18 ሁላችንም የክርስቶስ ወዳጆች መሆናችንን የምናሳይበት ሦስተኛው መንገድ የጉባኤ ሽማግሌዎች የሚሰጡንን መመሪያ ተቀብለን በመታዘዝ ነው። ክርስቶስ የጉባኤው ራስ ስለሆነና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ጉባኤውን ስለሚመራ እነዚህ ሰዎች የተሾሙት በመንፈስ ቅዱስ ነው። (ኤፌ. 5:23) ሐዋርያው ጳውሎስ “በመካከላችሁ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 13:17) አንዳንድ ጊዜ የጉባኤያችን ሽማግሌዎች የሚሰጡንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ መታዘዝ ይከብደን ይሆናል። እነዚህ ወንድሞች ጉድለት እንዳለባቸው ማስተዋላችን አይቀርም፤ ይህ ደግሞ ለሚሰጡን ምክር የተዛባ አመለካከት እንዲኖረን ሊያደርግ ይችላል። ያም ቢሆን የጉባኤው ራስ የሆነው ክርስቶስ ፍጽምና በጎደላቸው በእነዚህ ሰዎች ለመጠቀም እንደመረጠ ማስታወስ ይኖርብናል። በመሆኑም ለእነሱ ሥልጣን ያለን አመለካከት ከክርስቶስ ጋር ያለንን ወዳጅነት በቀጥታ ይነካዋል። ሽማግሌዎች በሚሠሯቸው ስህተቶች ላይ ሳናተኩር የሚሰጡንን መመሪያ በደስታ የምንታዘዝ ከሆነ ለክርስቶስ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን።

ጥሩ ወዳጆች የት ማግኘት እንችላለን?

19, 20. በጉባኤ ውስጥ ምን ማግኘት እንችላለን? በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ የትኛውን ጥያቄ እንመረምራለን?

19 ኢየሱስ አፍቃሪ የሆኑ እረኞች እንዲመሩን በማድረግ ብቻ ሳይሆን በጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች በመስጠትም እየተንከባከበን ነው። (ማርቆስ 10:29, 30ን አንብብ።) ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መተባበር ስትጀምር ዘመዶችህ ምን ተሰማቸው? ወደ አምላክና ወደ ክርስቶስ ለመቅረብ ጥረት ስታደርግ ደግፈውህ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ እንዳስጠነቀቀው አንዳንድ ጊዜ “የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ።” (ማቴ. 10:36) በዚህ ወቅት ከሥጋ ወንድሞቻችን የበለጠ የሚቀርቡን ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ማግኘት እንደምንችል ማወቃችን በጣም የሚያጽናና ነው!—ምሳሌ 18:24

20 ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ መደምደሚያ ላይ እያንዳንዱን ሰው በስም በመጥራት ካቀረበው ሰላምታ መረዳት እንደምንችለው ብዙ የቅርብ ወዳጆች አፍርቶ ነበር። (ሮም 16:8-16) ሐዋርያው ዮሐንስ ሦስተኛ ደብዳቤውን የደመደመው “ሰላምታዬን ለወዳጆች በየስማቸው አቅርብልኝ” በማለት ነበር። (3 ዮሐ. 14) በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ዮሐንስም ከብዙዎች ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መሥርቶ ነበር። ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ጤናማ ወዳጅነት በመመሥረትና ወዳጅነታችንን ጠብቀን በማቆየት ረገድ የኢየሱስንም ሆነ በጥንት ጊዜ የነበሩትን ደቀ መዛሙርት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ኢየሱስ ጥሩ ወዳጅ በመሆን ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?

• የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረታቸው ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል?

• የክርስቶስ ወዳጆች መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የወዳጆቹን ሐሳብና ስሜት ለማወቅ ይፈልግ ነበር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የክርስቶስ ወዳጅ መሆን እንደምንፈልግ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?