በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቤተሰብ አምልኮ ከጥፋት ለመዳን ወሳኝ ነው!

የቤተሰብ አምልኮ ከጥፋት ለመዳን ወሳኝ ነው!

የቤተሰብ አምልኮ ከጥፋት ለመዳን ወሳኝ ነው!

‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ምን ያህል አስፈሪ እንደሚሆን አስቡት! (ራእይ 16:14) ነቢዩ ሚክያስ በዚያ ቀን የሚኖረውን ሁኔታ በአእምሯችን መሳል እንድንችል በሚያደርግ መንገድ ሲገልጸው እንዲህ ብሏል፦ “ተራሮች . . . ይቀልጣሉ፤ ሸለቆዎችም ይሰነጠቃሉ፤ በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፣ በገደል ላይ እንደሚወርድ ፈሳሽ ይሆናሉ።” (ሚክ. 1:4) ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎች በዚህ ወቅት ምን ይደርስባቸዋል? የአምላክ ቃል “በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር በሁሉ ስፍራ ተረፍርፈው ይታያሉ” ይላል።—ኤር. 25:33

እንደነዚህ ያሉትን ማስጠንቀቂያዎች ግምት ውስጥ በማስገባት የቤተሰብ ራሶች (ነጠላ ወላጆችም ጭምር) ውሳኔ ለማድረግ የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆቻቸውን በተመለከተ ‘ከአርማጌዶን ይተርፉ ይሆን?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቃቸው ተገቢ ነው። ይህ ጥፋት በሚመጣበት ወቅት ልጆቹ ዕድሜያቸው በሚፈቅድላቸው መጠን በመንፈሳዊ ሕያውና ጠንካራ ከሆኑ መዳን እንደሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ይሰጣል።—ማቴ. 24:21

ለቤተሰብ አምልኮ ጊዜ መመደብ አስፈላጊ ነው

ወላጆች፣ ልጆቻችሁን “በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ [ለማሳደግ]” የምትችሉትን ሁሉ ማድረግ ይኖርባችኋል። (ኤፌ. 6:4) ከልጆቻችሁ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጣም አስፈላጊ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ልጆቻችን፣ ይሖዋን በፈቃደኝነት በመታዘዛቸው ጳውሎስ እንዳመሰገናቸው በፊልጵስዩስ እንደነበሩት ክርስቲያኖች እንዲሆኑ እንፈልጋለን። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እኔ አብሬያችሁ ስሆን ብቻ ሳይሆን ይልቁንም አሁን አብሬያችሁ በሌለሁበት ወቅት ሁልጊዜ ታዛዥ እንደሆናችሁ ሁሉ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ለመፈጸም ተግታችሁ ሥሩ።”—ፊልጵ. 2:12

እናንተ አብራችኋቸው በማትሆኑበት ወቅትም ልጆቻችሁ የይሖዋን ሕጎች ይታዘዛሉ? ትምህርት ቤት በሚሆኑበት ጊዜ ምን ያደርጋሉ? ልጆቻችሁ የይሖዋን ሕጎች መታዘዝ የጥበብ አካሄድ መሆኑን እንዲያምኑበት ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችሁ አብራችኋቸው በማትሆኑበት ጊዜም እንኳ በእነዚህ ሕጎች እንዲመሩ ይረዳቸዋል።

ልጆቻችሁ ይህን ለማድረግ የሚያስችላቸው እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት የቤተሰብ አምልኮ ትልቅ ሚና ይጫወታል። የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ የሚረዱ ሦስት ቁልፍ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት።

ፕሮግራማችሁ እንዳይቋረጥ አድርጉ

የአምላክ ቃል፣ የይሖዋ ልጆች የሆኑት መላእክት “አንድ ቀን” እሱ ፊት እንደቀረቡ ይገልጻል፤ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ እዚህ ላይ “አንድ ቀን” ተብሎ የተተረጎመው ሐሳብ አስቀድሞ የተቀጠረ ቀንን ያመለክታል። (ኢዮብ 1:6) እናንተም ከልጆቻችሁ ጋር እንደዚህ አድርጉ። የቤተሰብ አምልኮ የምታደርጉበት የተወሰነ ቀንና ሰዓት መድቡ፤ ከዚያም ፕሮግራማችሁን አክብሩ። በተጨማሪም የቤተሰብ አምልኮ በምታደርጉበት ምሽት ያልታሰበ ነገር ቢያጋጥማችሁ ጥናታችሁን የምታደርጉበት አማራጭ ጊዜ መድቡ።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁን ያዝ ለቀቅ የማድረግ ልማድ እንዳታዳብሩ ተጠንቀቁ። ልትዘነጉት የማይገባው ነገር ከማንም ይበልጥ ትኩረት ልትሰጧቸው የሚገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁ ልጆቻችሁ መሆናቸውን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሰይጣን ሊያጠምዳቸው ይፈልጋል። (1 ጴጥ. 5:8) ቴሌቪዥን ለመመልከት ወይም እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ሌሎች ነገሮችን ለማከናወን ስትሉ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባውን የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁን ከሰረዛችሁ ሰይጣን ድል አደረገ ማለት ነው።—ኤፌ. 5:15, 16፤ 6:12፤ ፊልጵ. 1:10

ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን አካትቱ

የቤተሰብ አምልኮ በምታደርጉበት ምሽት የአእምሮ እውቀት ከማካበት የበለጠ ነገር ልታከናውኑ ይገባል። ፕሮግራሙ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን የሚያካትት እንዲሆን ጥረት አድርጉ። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? አንዳንድ ጊዜ፣ ልጃችሁ በዕለታዊ ሕይወቱ የሚያጋጥሙትን ነገሮች የሚዳስሱ ርዕሰ ጉዳዮችን ምረጡ። ለምሳሌ ያህል፣ ለአገልግሎት ልምምድ ማድረግን በፕሮግራማችሁ ውስጥ ለምን አታካትቱትም? ልጆች በደንብ የሚችሉትን ነገር ማድረግ ያስደስታቸዋል። ለአገልግሎት የሚጠቀሙባቸውን መግቢያዎች እንዲሁም ተቃውሞ ሲያጋጥማቸው መልስ መስጠት የሚችሉባቸውን መንገዶች መለማመዳችሁ ልጆቻችሁ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች በሚካፈሉበት ጊዜ ይበልጥ ደፋሮች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።—2 ጢሞ. 2:15

ከዚህም በተጨማሪ ልጆቻችሁ የእኩዮቻቸውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚረዷቸውን ነጥቦች የምትወያዩበት የልምምድ ፕሮግራም በቤተሰብ አምልኳችሁ ውስጥ ማካተት ትችላላችሁ። በዚህ ወቅት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 በተባለው መጽሐፍ በመጠቀም በቤተሰብ መወያየት ትችላላችሁ። በዚህ መጽሐፍ ገጽ 132 እና 133 ላይ የሚገኘው ሠንጠረዥ ልጃችሁ እንዴት መልስ መስጠት እንደሚችል የሚጠቁሙ ሐሳቦችን የያዘ ከመሆኑም በላይ ልጁ ተስማሚ መስሎ የተሰማውን መልስ ማስፈር የሚችልበት ክፍት ቦታ አለው። በገጽ 133 መጨረሻ ላይ ያለው ዓረፍተ ነገር “በሠንጠረዡ ውስጥ ያሰፈርካቸውን መልሶች ከወላጆችህ ወይም ከአንድ የጎለመሰ ጓደኛህ ጋር ተለማመዳቸው” በማለት ወጣቶችን ያበረታታል። የቤተሰብ አምልኮ በምታደርጉባቸው ምሽቶች አልፎ አልፎ ለምን እንዲህ ዓይነት ልምምድ አታደርጉም?

ወላጆች መንፈሳዊ ግቦች ማውጣት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ለማጉላት እንዲችሉ የቤተሰብ አምልኮ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። በዚህ ረገድ የወጣቶች ጥያቄ፣ ጥራዝ 2 የተባለው መጽሐፍ በምዕራፍ 38 ላይ “ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?” በሚል ርዕስ ግሩም ሐሳብ ይዟል። ወጣቶች—በሕይወታችሁ ምን ለማድረግ አስባችኋል? በሚለው ትራክት ላይም ተመሳሳይ ሐሳብ ማግኘት ይቻላል። በእነዚህ ጽሑፎች ላይ በምትወያዩበት ጊዜ ልጃችሁ፣ ሕይወቱ ይሖዋን በማገልገል ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረጉ ከሁሉ የላቀ አካሄድ መሆኑን እንዲገነዘብ እርዱት። ልጃችሁ አቅኚ የመሆን፣ በቤቴል የማገልገል፣ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የመካፈል አሊያም በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ የመሳተፍ ፍላጎት እንዲያድርበት እርዱት።

ጥንቃቄ ልታደርጉበት የሚገባ ነጥብ፦ አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው በማሰብ ልጁ እንዲሆን በሚፈልጉት ነገር ላይ ከመጠን በላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ ልጁ በአሁኑ ወቅት እያከናወነ ያለውን ነገር አንስተው አያመሰግኑትም። ልጆቻችሁ ቤቴላዊና ሚስዮናዊ እንደመሆን ያሉ ግሩም ግቦችን እንዲያወጡ ማበረታታቱ ጥሩ እንደሆነ አይካድም። ይሁን እንጂ እንዲህ በምታደርጉበት ወቅት ልጃችሁ እናንተ የምትፈልጉት ግብ ላይ እንዲደርስ በመጫን እንዳታበሳጩትና ቅስሙን እንዳትሰብሩት መጠንቀቅ ይኖርባችኋል። (ቆላ. 3:21) ልጃችሁ ይሖዋን ሊወድ የሚገባው ራሱ ስለፈለገ እንጂ እናንተ ስለፈለጋችሁ መሆን እንደሌለበት ምንጊዜም አስታውሱ። (ማቴ. 22:37) ስለዚህ ልጃችሁ ላከናወነው መልካም ነገር ለማመስገን ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም ሳያደርግ በቀረው ነገር ላይ የማተኮርን ዝንባሌ አስወግዱ። ልጃችሁ ይሖዋ ላደረጋቸው በርካታ ነገሮች አድናቆት እንዲያድርበት እርዱት። እንዲህ ማድረጋችሁ ልጁ በራሱ ፍላጎት አንድ ዓይነት እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል።

አስደሳች እንዲሆን አድርጉ

የቤተሰብ አምልኮ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ የሚያደርገው ሦስተኛው ቁልፍ ነጥብ ፕሮግራሙ አስደሳች እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? አንዳንድ ጊዜ፣ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ በድምፅ ብቻ የተቀረጹ ድራማዎችን ማዳመጥ ወይም የቪዲዮ ፊልሞችን መመልከትና በእነዚያ ላይ መወያየት ትችላላችሁ። አሊያም ደግሞ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን አብሮ ማንበብ ይቻላል፤ በዚህ ጊዜ የቤተሰባችሁ አባላት የባለታሪኮቹን ንግግር ተከፋፍለው እንዲያነቡ ማድረግ ትችላላችሁ።

በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! ላይ ለቤተሰብ ውይይት የሚረዱ ግሩም ርዕሰ ጉዳዮች ይወጣሉ። ለምሳሌ በእያንዳንዱ ንቁ! መጽሔት ገጽ 31 ላይ የሚወጣውን “መልስህ ምንድን ነው?” የተባለውን ዓምድ ልትወያዩበት ትችላላችሁ። በሚበረከተው የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ በሁለት ወር አንዴ “ለወጣት አንባቢያን” የሚል ወጣቶች ምርምር እንዲያደርጉ የሚያበረታታ ዓምድ ይወጣል። ይህ ዓምድ በማይወጣባቸው ወራት ደግሞ “ልጆቻችሁን አስተምሩ” የተባለ ለትንንሽ ልጆች የሚሆን ዓምድ ይኖራል።

በንቁ! መጽሔት ላይ “የወጣቶች ጥያቄ” በሚለው ዓምድ ሥር የሚወጡት ርዕሶች እንዲሁም የወጣቶች ጥያቄ፣ ጥራዝ 2 የተባለው መጽሐፍ በተለይ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ያሏቸውን ወላጆች ትኩረት የሚስቡ ናቸው። በዚህ መጽሐፍ ላይ በምትወያዩበት ጊዜ “ምን ይመስልሃል?” የሚለውን በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ ያለውን ሣጥን አትለፉት። ይህ ሣጥን ለክለሳ ብቻ ተብሎ የተዘጋጀ አይደለም። በሣጥኑ ውስጥ ባሉት ጥያቄዎች በመጠቀም በቤተሰብ ውይይት ማድረግ ይቻላል።

ሆኖም የቤተሰብ ጥናት ፕሮግራማችሁ ልጆቻችሁን በጥያቄ የምታፋጥጡበት ጊዜ እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ለምሳሌ፣ የወጣቶች ጥያቄ በተባለው መጽሐፍ ላይ ስትወያዩ “የግል ማስታወሻ” በሚሉት ገጾች ወይም ደግሞ ልጁ ስሜቱን በጽሑፍ እንዲገልጽ በሚያበረታቱት ሌሎች የመጽሐፉ ክፍሎች ላይ ልጃችሁ ያሰፈረውን ሐሳብ ጮክ ብሎ እንዲያነብ ለማስገደድ አትሞክሩ። በዚህ መጽሐፍ ገጽ 3 ላይ የሚገኘው “ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ” የሚለው ርዕስ እንዲህ ይላል፦ “በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ በመጽሐፋቸው ላይ ሐሳባቸውን በሐቀኝነት እንዲያሰፍሩ ለማበረታታት በተወሰነ መጠን ነፃነት ስጧቸው። ከጊዜ በኋላ መጽሐፋቸው ላይ ስላሰፈሯቸው ነገሮች በግልጽ ይነግሯችሁ ይሆናል።”

የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ እንዳይቋረጥና አስደሳች እንዲሆን ጥረት የምታደርጉ እንዲሁም ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን በጥናቱ ላይ የምታካትቱ ከሆነ ይሖዋ ጥረታችሁን አብዝቶ ይባርከዋል። በቤተሰብ ሆናችሁ የምታከናውኑት ይህ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ፕሮግራም ቤተሰባችሁ በመንፈሳዊ ሕያውና ጠንካራ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አዳዲስ መንገዶችን ተጠቀሙ

“እኔና ባሌ ከትንንሽ ሴቶች ልጆቻችን ጋር በምናጠናበት ጊዜ በጉባኤ ስብሰባ ላይ በሚቀርቡት ክፍሎች ላይ ከተወያየን በኋላ ልጆቻችን ትምህርቱን ጠቅለል አድርገው በሥዕል መልክ እንዲያስቀምጡት እናደርጋለን። አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በድራማ መልክ እንሠራቸዋለን፤ ወይም ለመስክ አገልግሎት የሚሆኑ መግቢያዎችን እንለማመዳለን። ጥናቱ ከዕድሜያቸው ጋር የሚመጣጠን፣ አስደሳች፣ አበረታችና ዘና የሚያደርግ እንዲሆን ጥረት እናደርጋለን።”—ጄ. ኤም.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ልጅ፣ በጥንት ዘመን ሰዎች በጥቅልል የሚጠቀሙት እንዴት እንደነበር መገንዘብ እንዲችል ለመርዳት የኢሳይያስን መጽሐፍ ምዕራፎቹንና ቁጥሮቹን ካጠፋን በኋላ በወረቀት ላይ አተምነው። ከዚያም ወረቀቶቹን እርስ በርስ ካያያዝን በኋላ ጫፍና ጫፉን ዘንግ በሚመስሉ ነገሮች ላይ አጣበቅነው። ኢየሱስ በናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ ውስጥ እንዳደረገው የጥናቴ ልጅ ይህንን ጥቅልል ይዞ ለማንበብ ሞከረ። በ⁠ሉቃስ 4:16-21 ላይ የሚገኘው ዘገባ ኢየሱስ የኢሳይያስን ‘ጥቅልል ተርትሮ’ የሚፈልገውን ክፍል እንዳገኘ ይገልጻል። (ኢሳ. 61:1, 2) ይሁን እንጂ ልጁ እንደ ኢየሱስ ለማድረግ ሲሞክር ምዕራፍም ሆነ ቁጥር ካልተጻፈበት ረጅም ጥቅልል ውስጥ ኢሳይያስ ምዕራፍ 61⁠ን ማግኘት አስቸገረው። ልጁ፣ ኢየሱስ ከጥቅልሉ ላይ ጥቅሱን ያገኘበት መንገድ ስላስገረመው ‘ኢየሱስ ጎበዝ ነበር!’ በማለት ተናገረ።”—ዋይ. ቲ.፣ ጃፓን

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤተሰብ ጥናታችሁ ወቅት የልምምድ ፕሮግራም እንዲኖራችሁ ማድረጋችሁ ልጆቻችሁ የእኩዮቻቸውን ተጽዕኖ እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው ይችላል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ አስደሳች እንዲሆን ጥረት አድርጉ