በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቅር በጠፋበት ዓለም ውስጥ ወዳጅነትን ጠብቆ መኖር

ፍቅር በጠፋበት ዓለም ውስጥ ወዳጅነትን ጠብቆ መኖር

ፍቅር በጠፋበት ዓለም ውስጥ ወዳጅነትን ጠብቆ መኖር

“እነዚህን ነገሮች የማዛችሁ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው።”—ዮሐንስ 15:17

1. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በመካከላቸው ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት ጠብቀው ማቆየት ያስፈለጋቸው ለምን ነበር?

ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ እርስ በርስ ያላቸውን ወዳጅነት ጠብቀው እንዲኖሩ አበረታቷቸው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ አንዳቸው ለሌላው የሚያሳዩት ፍቅር የእሱ ተከታዮች መሆናቸውን እንደሚያሳውቅ ኢየሱስ በዚያው ምሽት ቀደም ብሎ ተናግሮ ነበር። (ዮሐ. 13:35) ሐዋርያቱ ከፊታቸው የሚጠብቋቸውን ፈተናዎች በጽናት ለመወጣት እንዲሁም ኢየሱስ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የሚሰጣቸውን ተልእኮ ለመፈጸም እንዲችሉ በመካከላቸው ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት ጠብቀው ማቆየት ያስፈልጋቸዋል። በእርግጥም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ለአምላክ እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው ባላቸው ጠንካራ ፍቅር የታወቁ ነበሩ።

2. (ሀ) ምን ለማድረግ ቆርጠናል? ለምንስ? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 በዛሬው ጊዜ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች ምሳሌ የሚከተሉ አባላት ያሉት ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ክፍል መሆን እንዴት የሚያስደስት ነው! ኢየሱስ አንዳችን ለሌላው እውነተኛ ፍቅር እንዲኖረን የሰጠንን ትእዛዝ ለመፈጸም ቆርጠናል። ይሁን እንጂ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት አብዛኞቹ ሰዎች ታማኝነት የጎደላቸው ከመሆናቸውም ሌላ ተፈጥሯዊ ፍቅር የላቸውም። (2 ጢሞ. 3:1-3) አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ወዳጅነት ሲመሠርቱ የሚያስቡት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ሲሆን ወዳጅነታቸውም የይስሙላ ነው። እኛም እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን የሚያሳውቀው ምልክት እንዳይጠፋ ከፈለግን እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ ተጽዕኖ እንዳያደርግብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመርምር፦ የእውነተኛ ወዳጅነት መሠረቱ ምንድን ነው? እውነተኛ ወዳጆች ማፍራት የምንችለው እንዴት ነው? ወዳጅነታችንን ማቋረጥ የሚኖርብን መቼ ነው? የመሠረትነውን ጥሩ ወዳጅነት ጠብቀን ማቆየት የምንችለው እንዴት ነው?

የእውነተኛ ወዳጅነት መሠረቱ ምንድን ነው?

3, 4. አንድ ወዳጅነት ከሁሉ ይበልጥ ጠንካራ የሚሆነው በምን ላይ ሲመሠረት ነው? እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

3 አንድ ወዳጅነት ከሁሉ ይበልጥ ጠንካራ የሚሆነው ይሖዋን በመውደድ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ነው። ንጉሥ ሰለሞን “አንድ ሰው ብቸኛውን ቢያጠቃውም፣ ሁለት ከሆኑ ይመክቱታል፤ በሦስት የተገመደ ገመድም ቶሎ አይበጠስም” በማለት ጽፏል። (መክ. 4:12) በሦስት የተገመደ ገመድ በቀላሉ እንደማይበጠስ ሁሉ በወዳጅነት መካከል ይሖዋ መኖሩ ወዳጅነቱ ዘላቂ እንዲሆን ያደርገዋል።

4 እርግጥ ነው፣ ይሖዋን የማይወዱ ሰዎችም ጥሩ ወዳጅነት ሊመሠርቱ ይችላሉ። ይሁንና ግለሰቦቹ እንዲቀራረቡ ያደረጋቸው ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ከሆነ ወዳጅነታቸው በቀላሉ የማይፈርስ ይሆናል። በእውነተኛ ወዳጆች መካከል አለመግባባቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ አንዱ ሌላውን የሚይዘው ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ ነው። የአምላክ ተቃዋሚዎች በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል መከፋፈል ለመፍጠር ይሞክሩ ይሆናል፤ ሆኖም እነዚህ የአምላክ ጠላቶች በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ወዳጅነት ጠንካራ እንደሆነ ይገነዘባሉ። በታሪክ ዘመናት ሁሉ የይሖዋ አገልጋዮች አንዳቸው ሌላውን አሳልፈው ከመስጠት ይልቅ ሞትን እንደሚመርጡ አሳይተዋል።—1 ዮሐንስ 3:16ን አንብብ።

5. የሩትና የኑኃሚን ወዳጅነት ጠንካራና ዘላቂ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው?

5 ከሁሉ ይበልጥ አስደሳች የሆነ ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ስንወዳጅ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። የሩትንና የኑኃሚንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት እጅግ አስደናቂ ወዳጅነቶች አንዱ በእነዚህ ሴቶች መካከል የነበረው ጓደኝነት ነው። ወዳጅነታቸው ጠንካራና ዘላቂ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? ሩት ለኑኃሚን እንደሚከተለው ብላ በተናገረች ጊዜ ምክንያቱን ግልጽ አድርጋለች፦ “ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል። . . . ከእንግዲህ ሞት ከሚለየን በቀር ብለይሽ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህም የከፋ ያድርግብኝ።” (ሩት 1:16, 17) በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ሩትና ኑኃሚን ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ይህ ፍቅር እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር አድርገዋል። በዚህም የተነሳ ሁለቱንም ሴቶች ይሖዋ ባርኳቸዋል።

እውነተኛ ወዳጆች ማፍራት የምንችለው እንዴት ነው?

6-8. (ሀ) አንድ ወዳጅነት ዘላቂ እንዲሆን ምን ያስፈልጋል? (ለ) ወዳጆች በማፍራት ረገድ ቀዳሚ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

6 የሩትና የኑኃሚን ምሳሌ እንደሚያሳየው እውነተኛ ወዳጅነት በአጋጣሚ የሚገኝ ነገር አይደለም። እውነተኛ ወዳጅነት ሁለቱም ወገኖች ለይሖዋ ባላቸው ጥልቅ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው። እርግጥ ነው፣ አንድ ወዳጅነት ዘላቂ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረትና የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ያስፈልጋል። በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ሆነው ይሖዋን የሚያመልኩ የሥጋ ወንድማማቾችና እህትማማቾች እንኳ የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት ማድረግ አለባቸው። ታዲያ እውነተኛ ወዳጆች ማፍራት የምንችለው እንዴት ነው?

7 ቀዳሚ ሁን። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሮም በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ ያሉት ወዳጆቹ “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል” እንዲያዳብሩ አበረታቷቸዋል። (ሮም 12:13) አንድን ነገር የማድረግ ባሕል ወይም ልማድ የምናዳብረው ያንን ነገር አዘውትረን ስናደርገው ነው። በተመሳሳይም የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል ማዳበር፣ ቀላል የሚመስሉ ነገሮችን አዘውትሮ ማድረግን ይጨምራል። እንግዳ ተቀባይ ለመሆን ከፈለግህ ይህን ልማድ ማዳበር ያለብህ አንተው ራስህ ነህ። (ምሳሌ 3:27ን አንብብ።) እንግዳ ተቀባይ መሆን የምትችልበት አንዱ መንገድ ቀለል ያሉ ምግቦችን አዘጋጅተህ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሰዎችን መጋበዝ ነው። የጉባኤህን አባላት መጋበዝ በሕይወትህ ውስጥ አዘውትረህ ከምታደርጋቸው ልማዶች አንዱ እንዲሆን በማድረግ የእንግዳ ተቀባይነትን መንፈስ ማሳየት ትችላለህ?

8 ወዳጆች ለማፍራት ቀዳሚ መሆን የምትችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ከተለያዩ የጉባኤህ አባላት ጋር በስብከቱ ሥራ መካፈል ነው። ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል የአገልግሎት ጓደኛህ ለይሖዋ ፍቅር እንዳለው በሚያሳይ መንገድ ለቤቱ ባለቤት ከልቡ ሲናገር በምትመለከትበት ጊዜ ይህንን ወንድም ይበልጥ ለመቅረብ እንደምትነሳሳ ምንም ጥርጥር የለውም።

9, 10. ጳውሎስ ምን ምሳሌ ትቶልናል? እኛስ የእሱን አርዓያ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

9 ፍቅር በማሳየት ረገድ ልብህን ወለል አድርገህ ክፈት። (2 ቆሮንቶስ 6:12, 13ን አንብብ።) በጉባኤህ ውስጥ ጓደኛ ልታደርገው የምትችል አንድም ሰው እንደሌለ ተሰምቶህ ያውቃል? እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ጓደኛህ ሊሆኑ እንደሚችሉ የምታስባቸውን ሰዎች በተመለከተ አመለካከትህን ማስፋት ያስፈልግህ ይሆን? ሐዋርያው ጳውሎስ ፍቅር በማሳየት ረገድ ልቡን ወለል አድርጎ በመክፈት ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። በአንድ ወቅት አይሁዳውያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ፈጽሞ የማያስበው ነገር ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ “የአሕዛብ ሐዋርያ” ለመሆን በቅቷል።—ሮም 11:13

10 ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ ጓደኝነት የሚመሠርተው ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር ብቻ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል፣ እሱና ጢሞቴዎስ በመካከላቸው የዕድሜና የአስተዳደግ ልዩነት የነበራቸው ቢሆንም የጠበቀ ወዳጅነት መሥርተዋል። በዛሬው ጊዜም በርካታ ወጣቶች በዕድሜ ከሚበልጧቸው የጉባኤው አባላት ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ቨኔሳ እንዲህ ብላለች፦ “በ50ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ በጣም የምወዳት ጓደኛ አለችኝ። ከእኩዮቼ ጋር የማወራውን ማንኛውንም ነገር ከእሷ ጋር ማውራት እችላለሁ። እሷም ለእኔ በጣም ታስብልኛለች።” እንዲህ ዓይነት ወዳጅነት መመሥረት የሚቻለው እንዴት ነው? ቨኔሳ እንዲህ ብላለች፦ “ከእሷ ጋር ያለን ጓደኝነት በራሱ የመጣ ነገር አይደለም፤ ጥረት ማድረግ ጠይቆብኛል።” አንተስ የዕድሜ እኩዮችህ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ፈቃደኛ ነህ? ከሆነ ይሖዋ ጥረትህን እንደሚባርከው ምንም ጥርጥር የለውም።

11. ከዳዊትና ከዮናታን ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

11 ታማኝ ሁን። ሰለሞን “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 17:17) ሰለሞን ይህን ሐሳብ ሲጽፍ አባቱ ዳዊት ከዮናታን ጋር የነበረውን ወዳጅነት በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። (1 ሳሙ. 18:1) ንጉሥ ሳኦል ልጁ ዮናታን የእስራኤልን ዙፋን እንዲወርስ ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለዚህ መብት የመረጠው ዳዊትን እንደሆነ ዮናታን ተገንዝቦ ነበር። ዮናታን እንደ ሳኦል በዳዊት አልቀናም። ዳዊት ክብር በማግኘቱ አልተበሳጨም ወይም ሳኦል ስለ ዳዊት የነገረውን የሐሰት ወሬ አላመነም። (1 ሳሙ. 20:24-34) እኛስ እንደ ዮናታን ነን? ወዳጆቻችን በጉባኤ ውስጥ መብት ሲያገኙ እንደሰታለን? መከራ ሲያጋጥማቸው እናጽናናቸዋለን እንዲሁም እንደግፋቸዋለን? ስለ ወዳጃችን መጥፎ ነገር ብንሰማ ነገሩን ሳናጣራ የሰማነውን እናምናለን? ወይስ እንደ ዮናታን በታማኝነት ከወዳጃችን ጎን እንቆማለን?

ወዳጅነታችንን ማቋረጥ የሚኖርብን መቼ ነው?

12-14. መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ አንዳንድ ሰዎች ምን ዓይነት ፈተና ያጋጥማቸዋል? እኛስ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?

12 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በአኗኗሩ ላይ ለውጥ ማድረግ ሲጀምር ከጓደኛ ጋር በተያያዘ ከባድ ፈተና ሊያጋጥመው ይችላል። ይህ ተማሪ ጓደኞች ይኖሩትና ከእነሱ ጋር መሆኑ ያስደስተው ይሆናል፤ ሆኖም እነዚህ ጓደኞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አይመሩም። ቀደም ሲል ከእነዚህ ጓደኞቹ ጋር አዘውትሮ ጊዜ ያሳልፍ ይሆናል። አሁን ግን ጓደኞቹ የሚያደርጓቸው ነገሮች በእሱ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ስለተገነዘበ ከእነሱ ጋር የሚያሳልፈውን ጊዜ መቀነስ እንዳለበት ይሰማዋል። (1 ቆሮ. 15:33) ያም ቢሆን ግን ከእነዚህ ጓደኞቹ ጋር ያለውን ወዳጅነት ማቋረጥ ለእነሱ ያለውን ታማኝነት ማጉደል እንደሆነ ይሰማው ይሆናል።

13 እንዲህ ዓይነት ፈተና ያጋጠመህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከሆንክ እውነተኛ ወዳጅ ሕይወትህን ለማሻሻል በምታደርገው ጥረት እንደሚደሰት ማስታወስ ያስፈልግሃል። እንዲያውም ወዳጅህ ልክ እንደ አንተ ስለ ይሖዋ ለመማር ሊፈልግ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሐሰተኛ ጓደኞች ‘ባዘቀጠ ወራዳ ሕይወት’ ከእነሱ ጋር ስለማትሮጥ ‘ይሰድቡሃል።’ (1 ጴጥ. 4:3, 4) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ታማኝነታቸውን ያጎደሉት እነዚህ ወዳጆችህ እንጂ አንተ አይደለህም።

14 መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጠኑ አንዳንድ ሰዎችን፣ ለአምላክ ፍቅር የሌላቸው የቀድሞ ጓደኞቻቸው ሲተዉአቸው የጉባኤው አባላት ከእነሱ ጋር ወዳጅነት በመመሥረት ብቸኝነት እንዳይሰማቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። (ገላ. 6:10) በስብሰባዎች ላይ የሚገኙ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመሩ ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ ታውቃቸዋለህ? ከእነሱ ጋር አልፎ አልፎ ጊዜ በማሳለፍ የሚያንጽ ጭውውት ማድረግ ትችላለህ?

15, 16. (ሀ) አንድ ወዳጃችን ይሖዋን ማገልገሉን ቢያቆም ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ለአምላክ ያለንን ፍቅር እንዴት ማሳየት እንችላለን?

15 በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ወዳጃችን ይሖዋን ቢተውስ? ምናልባትም ከጉባኤው መወገድ ቢኖርበትስ? እንዲህ ያለው ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ሊሆን ይችላል። አንዲት እህት የቅርብ ጓደኛዋ ይሖዋን ማገልገል ባቆመችበት ወቅት የተሰማትን ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ሰው የሞተብኝ ያህል በጣም አዘንኩ። ጓደኛዬ በእውነት ውስጥ ጠንካራ አቋም ያላት ይመስለኝ ነበር፤ ሆኖም እንደጠበቅኳት አልነበረችም። ‘ይሖዋን ታገለግል የነበረው ቤተሰቧን ለማስደሰት ስትል ብቻ ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። እኔም ራሴን መመርመር ጀመርኩ። ‘ይሖዋን አገለግል የነበረው በትክክለኛ ዝንባሌ ተነሳስቼ ነው?’ በማለት ራሴን ጠየቅኩ።” ይህች እህት ይህን አሳዛኝ ሁኔታ የተቋቋመችው እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ሸክሜን በይሖዋ ላይ ጣልኩት። ይሖዋን የምወደው በማንነቱ ተስቤ እንጂ በድርጅቱ ውስጥ ጓደኞችን ስለሰጠኝ ብቻ አይደለም፤ ለይሖዋ ይህንን ላሳየው ቆርጫለሁ።”

16 የዓለም ወዳጆች ለመሆን ከመረጡ ሰዎች ጎን ከቆምን የአምላክ ወዳጅ ሆነን መቀጠል አንችልም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ከዓለም ጋር መወዳጀት ከአምላክ ጋር ጠላትነት መፍጠር እንደሆነ አታውቁም? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ራሱን የአምላክ ጠላት ያደርጋል።” (ያዕ. 4:4) ለአምላክ ታማኝ እስከሆንን ድረስ ጓደኛችንን ማጣታችን ያስከተለብንን ሐዘን መቋቋም እንድንችል እሱ ይረዳናል፤ ይህን እንደሚያደርግልን በአምላክ መተማመናችን ለእሱ ፍቅር እንዳለን ያሳያል። (መዝሙር 18:25ን አንብብ።) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው እህት ጉዳዩን ጠቅለል አድርጋ ስትገልጸው እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ሰው ይሖዋንም ሆነ እኛን እንዲወደን ማድረግ እንደማንችል ተምሬያለሁ። ይህ የግለሰቡ ምርጫ ነው።” ይሁንና ከሌሎች የጉባኤ አባላት ጋር የመሠረትነውን ጥሩ ወዳጅነት ጠብቀን ለማቆየት ምን ማድረግ እንችላለን?

የመሠረትነውን ጥሩ ወዳጅነት ጠብቀን ማቆየት

17. ጥሩ ወዳጅነት ያላቸው ሰዎች እርስ በርስ እንዴት ሊነጋገሩ ይገባል?

17 ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ፣ ወዳጅነት ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ስለ ሩትና ኑኃሚን፣ ዳዊትና ዮናታን እንዲሁም ጳውሎስና ጢሞቴዎስ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ስታነብ ጥሩ ወዳጅነት ያላቸው ሰዎች በግልጽ ሆኖም አክብሮት በተሞላበት መንገድ ሐሳባቸውን እንደሚለዋወጡ አስተውለህ ይሆናል። ጳውሎስ፣ ከሌሎች ጋር ስንነጋገር ምን ልናደርግ እንደሚገባ ሲገልጽ “ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለውና በጨው የተቀመመ ይሁን” በማለት ጽፏል። ጳውሎስ ይህንን ሲል በተለይ ‘በውጭ ካሉት’ ማለትም ክርስቲያን ወንድሞቻችን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ስንነጋገር ምን ማድረግ እንዳለብን መግለጹ ነበር። (ቆላ. 4:5, 6) ከማያምኑ ሰዎች ጋር ስንነጋገር አክብሮት ልናሳያቸው የሚገባ ከሆነ በጉባኤ ውስጥ ላሉት ወዳጆቻችን የበለጠ አክብሮት ልናሳያቸው እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም!

18, 19. አንድ ክርስቲያን ወዳጃችን የሚሰጠንን ማንኛውንም ምክር እንዴት ልንመለከተው ይገባል? በኤፌሶን የሚገኙት ሽማግሌዎች ምን ምሳሌ ትተውልናል?

18 ጥሩ ወዳጅነት ያላቸው ሰዎች አንዳቸው የሌላውን ሐሳብ ከፍ አድርገው ይመለከታሉ፤ እርስ በርስ በሚጨዋወቱበት ጊዜ ንግግራቸው ለዛ ያለውና ቀጥተኛ መሆን አለበት። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ የወዳጅ ማስደሰትም ከቅን ምክሩ ይመነጫል” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 27:9) ከወዳጅህ የምታገኘውን ማንኛውንም ምክር የምትመለከተው በዚህ መንገድ ነው? (መዝሙር 141:5ን አንብብ።) አንድ ወዳጅህ አካሄድህ እንዳላማረው ቢገልጽልህ ምን ታደርጋለህ? ወዳጅህ የሚሰጥህን ሐሳብ የፍቅራዊ ደግነት መግለጫ እንደሆነ አድርገህ ትመለከተዋለህ? ወይስ ወዳጅህ በሰጠህ ሐሳብ ቅር ትሰኛለህ?

19 ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ጉባኤ ከሚገኙት ሽማግሌዎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበረው። ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹን ወደ እውነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ሳያውቃቸው አይቀርም። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሽማግሌዎች ጋር ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኘበት ወቅት ቀጥተኛ የሆነ ምክር ሰጥቷቸው ነበር። ሽማግሌዎቹ ምን ተሰማቸው? እነዚህ የጳውሎስ ወዳጆች ምክር ስለሰጣቸው ቅር አልተሰኙም። ከዚህ በተቃራኒ ለእነሱ አስቦ ይህን ማድረጉን ያደነቁ ከመሆኑም ሌላ በድጋሚ እንደማያዩት ሲያስቡ እጅግ አልቅሰዋል።—ሥራ 20:17, 29, 30, 36-38

20. አፍቃሪ የሆነ ወዳጅ ምን ያደርጋል?

20 ጥሩ ወዳጅነት ያላቸው ሰዎች፣ ጓደኛቸው የሚሰጣቸውን ጥበብ ያዘለ ምክር በመቀበል ብቻ ሳይወሰኑ እነሱም ለወዳጃቸው ምክር ይሰጣሉ። በእርግጥ “በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት” መጠንቀቅ ያስፈልገናል። (1 ተሰ. 4:11) በተጨማሪም እያንዳንዳችን “ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ [እንደምንሰጥ]” መገንዘብ ይኖርብናል። (ሮም 14:12) ይሁንና አፍቃሪ የሆነ ወዳጅ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ለጓደኛው የይሖዋን መሥፈርቶች በደግነት ያስታውሰዋል። (1 ቆሮ. 7:39) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ያላገባ ጓደኛህ ከማታምን ሴት ጋር መቀራረብ እንደጀመረ ብትመለከት ምን ታደርጋለህ? ጓደኝነታችሁ እንዳይቋረጥ በመፍራት ጉዳዩ እንዳሳሰበህ ከመናገር ወደኋላ ትላለህ? ወይም ደግሞ ጓደኛህ የሰጠኸውን ምክር ሳይቀበል ቢቀር ምን ታደርጋለህ? ጥሩ ወዳጅ፣ የተሳሳተ እርምጃ የወሰደውን ጓደኛውን አፍቃሪ የሆኑት እረኞች እንዲረዱት ለማድረግ ይሞክራል። እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰድ ድፍረት ይጠይቃል። ሆኖም ወዳጅነቱ ግለሰቦቹ ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ላይ የተመሠረተ ከሆነ ቢቋረጥ እንኳ ለጊዜው ብቻ ነው።

21. ሁላችንም አንዳንድ ጊዜ ምን እናደርጋለን? ያም ቢሆን በጉባኤ ውስጥ ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

21 ቆላስይስ 3:13, 14ን አንብብ። አንዳንድ ጊዜ ወዳጆቻችንን ‘ቅር የሚያሰኝ ነገር’ እናደርጋለን፤ እነሱም እንዲሁ የሚያበሳጨን ነገር ሊናገሩ ወይም ሊያደርጉ ይችላሉ። ያዕቆብ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን” ሲል ጽፏል። (ያዕ. 3:2) ይሁንና ወዳጅነት ጥንካሬው የሚለካው አንዳችን ሌላውን ምን ያህል ጊዜ በድለናል ወይም አልበደልንም በሚለው ሳይሆን የተፈጠረውን ቅሬታ ሙሉ በሙሉ ይቅር በማለታችን ነው። ግልጽ የሆነ ውይይት በማድረግና በነፃ ይቅር በመባባል ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! እንዲህ ዓይነት ፍቅር የምናሳይ ከሆነ ፍቅር “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” ይሆንልናል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• እውነተኛ ወዳጆች ማፍራት የምንችለው እንዴት ነው?

• ወዳጅነታችንን ማቋረጥ የሚኖርብን መቼ ነው?

• የመሠረትነውን ጥሩ ወዳጅነት ጠብቀን ለማቆየት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሩትና በኑኃሚን መካከል የነበረው ጠንካራና ዘላቂ ወዳጅነት በምን ላይ የተመሠረተ ነበር?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዘውትረህ እንግዶችን ትጋብዛለህ?