በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መስማት የተሳናቸውን ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ውድ እንደሆኑ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው!

መስማት የተሳናቸውን ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ውድ እንደሆኑ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው!

መስማት የተሳናቸውን ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ውድ እንደሆኑ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው!

በዛሬው ጊዜ ያሉት የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶችን ያቀፈ ትልቅ ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ ይህ ቤተሰብ የጀመረው በጥንት ዘመን ከኖሩ ወንዶችና ሴቶች ነው። ከእነዚህም መካከል ሳሙኤል፣ ዳዊት፣ ሳምሶን፣ ረዓብ፣ ሙሴ፣ አብርሃም፣ ሣራ፣ ኖኅ እና አቤል ይገኙበታል። ታማኝ ከሆኑት የይሖዋ አገልጋዮች መካከል መስማት የተሳናቸው በርካታ ግለሰቦችም ይገኛሉ። ለአብነት ያህል፣ በሞንጎሊያ የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች መስማት የተሳናቸው ባልና ሚስት ነበሩ። እንዲሁም በሩሲያ የሚኖሩ መስማት የተሳናቸው የእምነት ባልንጀሮቻችን ያሳዩት የአቋም ጽናት የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ሕጋዊ መብታችን እንዲከበር እንዲፈርድልን አድርጓል።

በዘመናችን “ታማኝና ልባም ባሪያ” በምልክት ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ ከማድረጉም በላይ በምልክት ቋንቋ ጽሑፎች እንዲሁም የልዩ፣ የወረዳና የአውራጃ ስብሰባዎች እንዲዘጋጁ አድርጓል። (ማቴ. 24:45) እነዚህ ዝግጅቶች መስማት የተሳናቸውን ሰዎች በእጅጉ ጠቅመዋቸዋል። * እነዚህ ዝግጅቶች ባልነበሩበት ጊዜ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ስለ እውነተኛው አምላክ ለመማርና በእውነት ውስጥ እድገት ለማድረግ ምን ያደርጉ እንደነበር አስበህ ታውቃለህ? በአካባቢህ የሚኖሩ መስማት የተሳናቸው ሰዎችን እንዴት መርዳት እንደምትችልስ አስበህ ታውቃለህ?

በዘመናችን ያሉት ዝግጅቶች ከመደረጋቸው በፊት

በዕድሜ የገፉ መስማት የተሳናቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች ስለ አምላክ ያወቁት እንዴት እንደሆነ ብትጠይቃቸው ምን መልስ የሚሰጡህ ይመስልሃል? አምላክ፣ ስም እንዳለው ለመጀመሪያ ጊዜ ባወቁበት ወቅት ምን እንደተሰማቸው ይነግሩህ ይሆናል፤ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጥልቀት ያላቸው የቅዱሳን መጻሕፍት እውነቶችን እንዲማሩ ለመርዳት ሲባል በምልክት ቋንቋ የቪዲዮ ፕሮግራሞች ወይም ዲቪዲዎች ከመዘጋጀታቸው በፊት እነዚህ ግለሰቦች በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ እንዲያደርጉና ለረጅም ዓመታት በመንፈሳዊ ጸንተው እንዲቀጥሉ ያስቻላቸው የአምላክን ስም ማወቃቸው ብቻ ነበር። በምልክት ቋንቋ የሚመሩ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ባልነበሩበት ወይም ስብሰባው ወደ ምልክት ቋንቋ በማይተረጎምበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ይገልጹልህ ይሆናል። በእነዚያ ወቅቶች መስማት የተሳናቸው ሰዎች የሚተላለፈውን ትምህርት መረዳት እንዲችሉ አንድ ሰው አጠገባቸው ተቀምጦ ሐሳቡን በወረቀት ላይ እየጻፈ ያሳያቸው ነበር። መስማት የተሳነው አንድ ወንድም፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡት ትምህርቶች ወደ ምልክት ቋንቋ መተርጎም እስከጀመሩበት ጊዜ ድረስ ለሰባት ዓመት ያህል በስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የሚማረው በዚህ መንገድ ነበር።

መስማት የተሳናቸው በዕድሜ የገፉ የይሖዋ ምሥክሮች፣ መስማት ለሚችሉ ሰዎች እንዴት ይሰብኩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከቤት ወደ ቤት በሚሄዱበት ጊዜ የሚጠቀሙባቸውን አጠር ያሉ መግቢያዎች የያዘ ካርድ በአንድ እጃቸው ይይዛሉ። በሌላኛው እጃቸው ደግሞ መጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶችን ይይዛሉ። ከዚህም ሌላ እነዚህ ወንድሞች መስማት ለሚችሉ ግለሰቦች በተዘጋጁ ጽሑፎች ተጠቅመው መስማት የተሳናቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ያስቸግራቸው ነበር፤ ምክንያቱም አስጠኚውም ሆነ ጥናቱ ጽሑፉን በደንብ አይረዱትም። መስማት የተሳናቸው አስፋፊዎች ከሌሎች ጋር መግባባት ስለሚቸግራቸው መንፈሳዊ እውነቶችን በደንብ ማስተላለፍ ይከብዳቸው ነበር፤ ይህ ምን ያህል ያበሳጫቸው እንደነበር በዕድሜ የገፉት መስማት የተሳናቸው አስፋፊዎች ያስታውሱ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ቢኖራቸውም አንድን ጉዳይ የተረዱት በትክክለኛው መንገድ መሆኑን እርግጠኞች መሆን ስለማይችሉ በልበ ሙሉነት እርምጃ መውሰድ ይከብዳቸው ነበር፤ ይህን ማድረግ ባለመቻላቸው ምን ይሰማቸው እንደነበረም ያስታውሳሉ።

መስማት የተሳናቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እነዚህ ሁሉ እንቅፋቶች ቢኖሩባቸውም በታማኝነት ይሖዋን ሲያገለግሉ ቆይተዋል። (ኢዮብ 2:3) በትዕግሥት ይሖዋን ሲጠባበቁ ኖረዋል። (መዝ. 37:7) በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ አብዛኞቹ ካሰቡት በላቀ መንገድ መስማት የተሳናቸውን ክርስቲያኖች እየባረካቸው ነው።

ባለትዳርና የልጆች አባት የሆነ አንድ መስማት የተሳነው ወንድም ያደርግ የነበረውን ጥረት እንመልከት። ይህ ወንድም በምልክት ቋንቋ ቪዲዮ ከመዘጋጀቱ በፊትም እንኳ አዘውትሮ የቤተሰብ ጥናት ይመራ ነበር። ከልጆቹ አንዱ እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “አባታችን በወቅቱ እኛን ለማስተማር መጠቀም የሚችለው መስማት ለሚችሉ ሰዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችን ብቻ በመሆኑ የቤተሰብ ጥናቱን መምራት ሁልጊዜ ለእሱ ከባድ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ የጽሑፉን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ አይረዳውም። እኛም ልጆች በነበርንበት ጊዜ ሁኔታው ይበልጥ አስቸጋሪ እንዲሆንበት እናደርግ ነበር። ትምህርቱን በትክክል እንዳላብራራው ስናውቅ መሳሳቱን ለመንገር እንቸኩል ነበር። ያም ቢሆን የቤተሰብ ጥናቱን አለማቋረጥ ይመራ ነበር። እንግሊዝኛ መረዳት ስለሚከብደው አንዳንድ ጊዜ የሚያሸማቅቁት ሁኔታዎች ቢፈጠሩም ይበልጥ የሚያሳስበው እኛ ስለ ይሖዋ መማራችን ነበር።”

በብሩክሊን ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩትንና በ70ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙትን ሪቻርድ የተባሉ መስማትና ማየት የተሳናቸው ወንድም ምሳሌም እንመልከት። ወንድም ሪቻርድ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አዘውትረው በመምጣት የሚታወቁ ወንድም ናቸው። ወደ ስብሰባዎች ለመሄድ ባቡር የሚሳፈሩት ራሳቸው ሲሆኑ የሚወርዱበትን ቦታ ለማወቅ ፌርማታዎቹን ይቆጥራሉ። በቅዝቃዜው ወራት አንድ ቀን ነፋስ የቀላቀለ ኃይለኛ በረዶ ይጥል ስለነበር በዕለቱ ይደረግ የነበረው ስብሰባ ተሰረዘ። ስብሰባው መሰረዙ ለሁሉም የጉባኤው አባላት ቢነገርም እንዳጋጣሚ ሆኖ ለወንድም ሪቻርድ ሳይነገራቸው ቀረ። ወንድሞች ይህን ሲረዱ ወንድም ሪቻርድን መፈለግ ጀመሩ፤ በኋላም ከመንግሥት አዳራሹ ውጭ ቆመው በሩ እስኪከፈት በትዕግሥት ሲጠብቁ አገኟቸው። ኃይለኛ በረዶ እየጣለ ለምን ከቤታቸው እንደወጡ ሲጠየቁ የሰጡት መልስ “ይሖዋን ስለምወድ ነው” የሚል ነበር።

ምን ልታደርግ ትችላለህ?

በአካባቢህ የሚኖሩ መስማት የተሳናቸው ሰዎች አሉ? ከእነሱ ጋር መነጋገር እንድትችል በመጠኑም ቢሆን የምልክት ቋንቋ መማር ትችላለህ? አብዛኛውን ጊዜ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ቋንቋቸውን ለሌሎች የሚያስተምሩት በትዕግሥትና ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። ዕለታዊ እንቅስቃሴዎችህን በምታከናውንበት ጊዜ ወይም አገልግሎት ላይ እያለህ መስማት የተሳነው ሰው ታገኝ ይሆናል። በዚህ ወቅት ምን ማድረግ ትችላለህ? ከግለሰቡ ጋር ለመግባባት ጥረት አድርግ። ምልክት በማሳየት፣ ወረቀት ላይ በመጻፍ፣ በመሳል ወይም ሥዕሎችን በማሳየት ሐሳብህን ለመግለጽ ሞክር። ግለሰቡ እውነትን ለማወቅ እንደማይፈልግ ቢገልጽም እንኳ መስማት ለተሳናቸው ወይም የምልክት ቋንቋ ለሚችሉ ወንድሞች ስለ ግለሰቡ ንገራቸው። መስማት የተሳነው ግለሰብ መልእክቱ በምልክት ቋንቋ ሲነገረው ይበልጥ ሊማርከው ይችላል።

የምልክት ቋንቋ እየተማርክ እንዲሁም በምልክት ቋንቋ በሚመራ የጉባኤ ስብሰባ ላይ እየተገኘህ ይሆናል። በምልክት ቋንቋ የመናገርና ቋንቋውን የመረዳት ችሎታህን እንዴት ማሻሻል ትችላለህ? በጉባኤህ ውስጥ መስማት የሚችሉ ሌሎች አስፋፊዎች ቢኖሩም ከእነሱ ጋር በምትነጋገርበት ወቅት ለምን በምልክት ቋንቋ አትጠቀምም? እንዲህ ማድረግህ በምልክት ቋንቋ ለማሰብ ይረዳሃል። አንዳንድ ጊዜ በምልክት ቋንቋ ከመጠቀም ይልቅ ሐሳብህን በቃላት ለመግለጽ ትፈተን ይሆናል። ይሁን እንጂ ማንኛውንም ቋንቋ አጣርተህ ለመቻል ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል።

በምልክት ቋንቋ ለመናገር ከፍተኛ ጥረት ማድረጋችን መስማት ለተሳናቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍቅርና አክብሮት እንዳለን ያሳያል። መስማት የተሳናቸው ሰዎች በሥራ ወይም በትምህርት ቤት በየዕለቱ ከሚያገኟቸው ግለሰቦች ጋር ለመግባባት አለመቻላቸው ምን ያህል ሊያበሳጫቸው እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። አንድ መስማት የተሳነው ወንድም እንዲህ ብሏል:- “በየዕለቱ የማገኛቸው ሰዎች ሁሉ ሲነጋገሩ እመለከታለሁ። አብዛኛውን ጊዜ የብቸኝነት ስሜት ስለሚያድርብኝና እንደተገለልኩ ስለሚሰማኝ እበሳጫለሁ አልፎ ተርፎም በቁጣ እሞላለሁ። አንዳንድ ጊዜ የሚያድርብኝን ስሜት ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል።” ስብሰባዎቻችን መስማት የተሳናቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መንፈሳዊ ምግብ የሚያገኙበትና አስደሳች ጭውውት የሚያደርጉበት የእረፍት ቦታ ሊሆኑላቸው ይገባል።—ዮሐ. 13:34, 35

መስማት የሚችሉ ሰዎች ባሉባቸው ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መስማት የተሳናቸው ሰዎችን ያቀፉ በርካታ ቡድኖችም ሳይጠቀሱ ሊታለፉ አይገባም። ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ትምህርቱ ለእነዚህ ሰዎች ይተረጎምላቸዋል። መስማት የተሳናቸው የጉባኤው አባላት የሚቀርበውን ትምህርት በደንብ ለመረዳት እንዲችሉ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ከፊት ባሉት ወንበሮች ላይ ይቀመጣሉ። ይህም አስተርጓሚውንም ሆነ ተናጋሪውን ምንም ሳይቸገሩ ፊት ለፊት ለማየት ይረዳቸዋል። ከተሞክሮ እንደታየው ሌሎች የጉባኤው አባላት መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የሚደረገውን እንዲህ ያለውን ዝግጅት ብዙም ሳይቆይ ስለሚለምዱት ትኩረታቸው ሳይሰረቅ የሚቀርበውን ትምህርት መከታተል ይችላሉ። ይህ ዝግጅት በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባ ላይ ትምህርቱ ወደ ምልክት ቋንቋ በሚተረጎምበት ጊዜም ይሠራል። መስማት የተሳነው ሰው ሐሳቡን በሚገልጽበት መንገድ ይኸውም ትርጉም በሚሰጥና የቋንቋውን ለዛ በጠበቀ መንገድ ለመተርጎም ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉት የጉባኤ አባላት ሞቅ ያለ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።

አንተ ባለህበት ጉባኤ ሥር የሚገኝ በምልክት ቋንቋ የሚመራ ቡድን ይኖር ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ስብሰባው የሚተረጎምላቸው አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መስማት የተሳናቸው ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። መስማት ለተሳናቸው ለእነዚህ ወንድሞች በግለሰብ ደረጃ እንደምታስብላቸው ለማሳየት ምን ማድረግ ትችላለህ? ወደ ቤትህ ጋብዛቸው። ሁኔታህ የሚፈቅድልህ ከሆነ የምልክት ቋንቋን በመጠኑም ቢሆን ለመማር ሞክር። መስማት ከተሳናቸው ሰዎች ጋር ለመግባባት ስትሞክር የሚፈጠሩት እንቅፋቶች ከእነሱ ጋር ከመቀራረብ ወደኋላ እንድትል አያድርጉህ። ከእነዚህ የእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ለመግባባት የሚያስችልህ መንገድ ማግኘትህ አይቀርም፤ በዚህ መንገድ ፍቅር ማሳየትህ ደግሞ ከእነሱ ጋር የማይረሳ ጊዜ ለማሳለፍ ያስችልሃል። (1 ዮሐ. 4:8) መስማት ከተሳናቸው የእምነት ባልንጀሮቻችን የምናገኘው ብዙ ነገር አለ። በቀላሉ ከሰዎች ጋር ማውራት ይችላሉ፤ ሌሎችን ለመረዳት ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ እንዲሁም ተጫዋች ናቸው። መስማት የተሳናቸው ወላጆች ያሉት አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “አብዛኛውን ሕይወቴን ያሳለፍኩት መስማት ከተሳናቸው ሰዎች ጋር ሲሆን መቼም ቢሆን መልሼ ልከፍለው የማልችለው በጣም ብዙ ጥቅም አግኝቻለሁ። መስማት ከተሳናቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ልንማረው የምንችለው ብዙ ነገር አለ።”

ይሖዋ፣ መስማት የተሳናቸውን ጨምሮ ታማኝ አምላኪዎቹን በሙሉ ይወዳቸዋል። መስማት የተሳናቸው ክርስቲያኖች በእምነታቸውና በጽናታቸው የተዉት አርዓያ ለይሖዋ ድርጅት በረከት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። እንግዲያው መስማት የተሳናቸውን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ውድ እንደሆኑ አድርገን እንመልከታቸው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በነሐሴ 15, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ይሖዋ ፊቱን አብርቶላቸዋል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ መስማት የተሳነው ግለሰብ የመንግሥቱ መልእክት በምልክት ቋንቋ ሲነገረው ይበልጥ ሊማርከው ይችላል

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስብሰባዎቻችን መስማት የተሳናቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መንፈሳዊ ማበረታቻ የሚያገኙበት የእረፍት ቦታ ሊሆኑላቸው ይገባል