በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የጸሎትህን ይዘት አሻሽል

መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የጸሎትህን ይዘት አሻሽል

መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የጸሎትህን ይዘት አሻሽል

“[ይሖዋ] ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎት፣ . . . ጆሮህ ታድምጥ።”—ነህ. 1:11

1, 2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ አንዳንድ ጸሎቶችን መመርመራችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

ጸሎትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የእውነተኛው አምልኮ ዓቢይ ክፍል ናቸው። (1 ተሰ. 5:17፤ 2 ጢሞ. 3:16, 17) እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የጸሎት መጽሐፍ አይደለም። ያም ሆኖ በርካታ ጸሎቶችን ይዟል፤ ከእነዚህም አብዛኞቹ የሚገኙት በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ነው።

2 መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ እንዲሁም ስታጠና አንተ ካጋጠሙህ ሁኔታዎች ጋር የሚስማሙ ጸሎቶችን ታገኝ ይሆናል። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን የጸሎት ይዘት ያላቸው ሐሳቦች በጸሎትህ ውስጥ ማካተትህ የጸሎትህን ይዘት ለማሻሻል ይረዳሃል። እርዳታ ለማግኘት ወደ አምላክ ያቀረቡት ልመና ከተሰማላቸው ሰዎች እንዲሁም ከጸሎታቸው ይዘት ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

የአምላክን መመሪያ ፈልግ፤ ተከተለውም

3, 4. የአብርሃም አገልጋይ የተሰጠው ተልእኮ ምን ነበር? ይሖዋ ከሰጠው ምላሽ ምን ትምህርት ማግኘት ይቻላል?

3 መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና የአምላክን መመሪያ ለማግኘት ሁልጊዜ መጸለይ እንዳለብህ ትገነዘባለህ። የእስራኤላውያን አባት የሆነው አብርሃም፣ ለይስሐቅ ፈሪሃ አምላክ ያላት ሚስት እንዲያመጣ በዕድሜ አንጋፋ የነበረውን አገልጋዩን (ኤሊዔዘር ሳይሆን አይቀርም) ወደ መስጴጦምያ በላከው ጊዜ የተከናወነውን ሁኔታ እንመልከት። ሴቶች ውኃ ለመቅዳት ወደ አንድ ጉድጓድ ሲመጡ የአብርሃም አገልጋይ እንዲህ በማለት ጸለየ:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ . . . እንግዲህ፣ ‘እንስራሽን አውርጂና ውሃ አጠጪኝ’ ስላት፣ ‘እንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም ላጠጣልህ’ የምትለኝ ቈንጆ እርሷ ለባሪያህ ለይስሐቅ የመረጥካት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ቸርነትህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።”—ዘፍ. 24:12-14

4 ርብቃ ግመሎቹን ውኃ ማጠጣት ስትጀምር የአብርሃም አገልጋይ ያቀረበው ጸሎት እንደተሰማለት ተገነዘበ። ብዙም ሳይቆይ ርብቃ ከአገልጋዩ ጋር ወደ ከነዓን ምድር በመሄድ የይስሐቅ ሚስት ሆነች፤ ይስሐቅም ሚስቱን ወደዳት። እርግጥ ነው፣ አምላክ የተለየ ምልክት እንዲሰጥህ መጠበቅ የለብህም። ይሁንና የምትጸልይና በእሱ መንፈስ ለመመራት ቁርጥ ውሳኔ የምታደርግ ከሆነ በሕይወትህ ውስጥ መመሪያ ይሰጥሃል።—ገላ. 5:18

ጸሎት ጭንቀትን ለማቅለል ይረዳል

5, 6. ያዕቆብ ከዔሳው ጋር ሊገናኝ ሲል ያቀረበው ጸሎት ትኩረት የሚስብ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ጸሎት ጭንቀትን ለማቅለል ሊረዳ ይችላል። ያዕቆብ፣ መንትያ ወንድሙ የሆነው ዔሳው ጉዳት እንዳያደርስበት ስለፈራ እንዲህ በማለት ጸልዮ ነበር:- “አምላክ ሆይ፤ . . . እኔ ባሪያህ እስካሁን ላደረግህልኝ ቸርነትና ታማኝነት ብቁ አይደለሁም፤ . . . ከወንድሜ ከዔሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ መጥቶ እኔንም ሆነ እነዚህን እናቶች ከነልጆቻቸው ያጠፋናል ብዬ ፈርቻለሁና፤ ነገር ግን፣ አንተ ራስህ፣ ‘አበለጽግሃለሁ፤ ዘርህንም ሊቈጠር እንደማይቻል እንደ ባሕር አሸዋ አበዛዋለሁ’ ብለኸኛል።”—ዘፍ. 32:9-12

6 በእርግጥ ያዕቆብ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ሲል አንዳንድ እርምጃዎችን ወስዷል፤ ያም ቢሆን በእሱና በዔሳው መካከል እርቅ መውረዱ ለጸሎቱ ምላሽ እንዳገኘ ያሳያል። (ዘፍ. 33:1-4) ያዕቆብ ያቀረበውን ልመና ትኩረት ሰጥተህ ስታነበው እርዳታ ለማግኘት ልመና በማቅረብ ብቻ እንዳልተወሰነ ትገነዘባለህ። ያዕቆብ ተስፋ በተሰጠበት ዘር ላይ ያለውን እምነት እንዲሁም አምላክ ላሳየው ቸርነት ወይም ፍቅራዊ ደግነት ያለውን አድናቆት ገልጿል። አንተስ ‘በውስጥህ ፍርሃት’ አለብህ? (2 ቆሮ. 7:5) ከሆነ ያዕቆብ ያቀረበው ልመና፣ ጸሎት ጭንቀትን ለማቅለል እንደሚረዳ እንድታስታውስ ሊረዳህ ይችላል። ይሁን እንጂ የምታቀርበው ጸሎት ልመና ብቻ የያዘ መሆን የለበትም፤ እምነትህን የሚገልጽም ሊሆን ይገባል።

ጥበብ ለማግኘት ጸልይ

7. ሙሴ መንገዱን እንዲያስተምረው ወደ ይሖዋ የጸለየው ለምን ነበር?

7 ይሖዋን ለማስደሰት ያለህ ፍላጎት ጥበብ ለማግኘት እንድትጸልይ ሊያነሳሳህ ይገባል። ሙሴ አምላክ መንገዱን እንዲያስተምረው ጸልዮ ነበር፤ “‘እነዚህን ሕዝብ [ከግብፅ] ምራ’ ብለህ ነግረኸኝ ነበር፤ . . . በእኔ ደስ ተሰኝተህ ከሆነ፣ . . . ያለማቋረጥ በፊትህ ሞገስ አገኝ ዘንድ መንገድህን አስተምረኝ” በማለት ወደ ይሖዋ ልመና አቅርቧል። (ዘፀ. 33:12, 13) አምላክም ሙሴ ስለ መንገዱ ብዙ እንዲያውቅ በመርዳት ለጸሎቱ ምላሽ ሰጥቶታል፤ ሙሴ የይሖዋን ሕዝቦች ለመምራት እንዲችል እንዲህ ያለ እውቀት ማግኘቱ በጣም አስፈላጊ ነበር።

8. በ⁠1 ነገሥት 3:7-14 ላይ ማሰላሰልህ እንዴት ሊጠቅምህ ይችላል?

8 ዳዊትም “እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ” በማለት ጸልዮአል። (መዝ. 25:4) የዳዊት ልጅ የሆነው ሰለሞን እስራኤልን ንጉሥ ሆኖ የማስተዳደር ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስፈልገውን ጥበብ እንዲሰጠው አምላክን ጠይቋል። ይሖዋ ሰለሞን ባቀረበው ጸሎት ስለተደሰተ የጠየቀውን ነገር ብቻ ሳይሆን ብልጽግናና ክብርም ሰጠው። (1 ነገሥት 3:7-14ን አንብብ።) በጉባኤ ውስጥ የተሰጠህ የአገልግሎት መብት ልትወጣው የማትችል እንደሆነ ከተሰማህ ጥበብ ለማግኘት ጸልይ፤ እንዲሁም የትሕትና መንፈስ ይኑርህ። እንዲህ ካደረግህ የተሰጡህን ኃላፊነቶች በአግባቡና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ለመወጣት የሚያስፈልግህን እውቀት እንድታገኝ እንዲሁም ነገሮችን በጥበብ ማከናወን እንድትችል አምላክ ይረዳሃል።

ከልብህ ጸልይ

9, 10. ሰለሞን ቤተ መቅደሱ በተመረቀበት ወቅት ባቀረበው ጸሎት ላይ ልብን መጥቀሱ ምን ጠቃሚ ትምህርት ይሰጠናል?

9 ጸሎት፣ ተሰሚነት እንዲያገኝ ከልብ የመነጨ መሆን አለበት። በ1 ነገሥት ምዕራፍ 8 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው በ1026 ዓ.ዓ. የይሖዋ ቤተ መቅደስ ሲመረቅ በኢየሩሳሌም ተሰብስቦ በነበረው ሕዝብ ፊት ሰለሞን ልባዊ ጸሎት አቅርቧል። የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ሲገባና የይሖዋ ደመና ቤተ መቅደሱን ሲሞላው ሰለሞን አምላክን አወድሷል።

10 ሰለሞን ያቀረበውን ጸሎት በጥሞና ስታነብ ስለ ልብ በተደጋጋሚ ጊዜ እንደጠቀሰ መመልከት ትችላለህ። ሰለሞን የሰውን ልብ የሚያውቀው ይሖዋ ብቻ መሆኑን ገልጿል። (1 ነገ. 8:38, 39) በዚሁ ጸሎት ላይ አንድ ኃጢአት የሠራ ሰው ‘በፍጹም ልቡ ወደ አምላክ ቢመለስ’ ይሖዋ ሊቀበለው እንደሚችል ተገልጿል። እንዲሁም ጠላት የአምላክን ሕዝቦች ማርኮ ቢወስዳቸው ሕዝቡ ልባቸው ከይሖዋ ጋር ፍጹም እስከሆነ ድረስ ልመናቸው ተሰሚነት ያገኛል። (1 ነገ. 8:48, 58, 61) ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው የምታቀርባቸው ጸሎቶች ከልብ የመነጩ መሆን አለባቸው።

የመዝሙር መጽሐፍ የጸሎትህን ይዘት ለማሻሻል የሚረዳህ እንዴት ነው?

11, 12. ለተወሰነ ጊዜ ያህል ወደ ይሖዋ መቅደስ መሄድ ያልቻለ አንድ ሌዋዊ ከተናገረው የጸሎት ይዘት ያለው ሐሳብ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

11 የመዝሙር መጽሐፍን ማጥናትህ የጸሎትህን ይዘት እንድታሻሽል እንዲሁም ተስፋህን በአምላክ ላይ በማድረግ መልስ እስኪሰጥህ በትዕግሥት እንድትጠብቅ ሊረዳህ ይችላል። በግዞት ተወስዶ የነበረ አንድ ሌዋዊ ያሳየውን ትዕግሥት እንመልከት። ይህ ሌዋዊ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ወደ ይሖዋ መቅደስ መሄድ ባይችልም እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ? ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ? ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፤ አዳኜና አምላኬን፣ ገና አመሰግነዋለሁና።”—መዝ. 42:5, 11፤ 43:5

12 ከዚህ ሌዋዊ ምን ልትማር ትችላለህ? ለጽድቅ ስትል በመታሰርህ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ለአምልኮ መሰብሰብ ባትችል ተስፋህን በአምላክ ላይ በማድረግ አንተን ለመርዳት የሚያከናውነውን ነገር በትዕግሥት ተጠባበቅ። (መዝ. 37:5) እንደ ቀድሞው ከሕዝቦቹ ጋር በአንድነት መሰብሰብ እንድትችል እንዲረዳህ ‘ተስፋህን በአምላክ ላይ አድርገህ’ በምትጠባበቅበት ወቅት ከዚህ ቀደም በአምላክ አገልግሎት ባሳለፍካቸው አስደሳች ሁኔታዎች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ለመጽናት እንድትችል ጸልይ።

በእምነት ጸልይ

13. በ⁠ያዕቆብ 1:5-8 መሠረት በእምነት መጸለይ ያለብህ ለምንድን ነው?

13 ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ምንጊዜም በእምነት ጸልይ። ንጹሕ አቋምህን ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ፈተና ቢያጋጥምህ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ አድርግ። ይሖዋ ያጋጠመህን ፈተና ለመቋቋም የሚያስፈልግህን ጥበብ እንደሚሰጥህ ሳትጠራጠር ወደ እሱ ጸልይ። (ያዕቆብ 1:5-8ን አንብብ።) አምላክ የሚረብሽህን ማንኛውንም ሐሳብ ያውቃል፤ በመንፈሱ አማካኝነት መመሪያ ሊሰጥህና ሊያጽናናህ ይችላል። ‘ምንም ሳትጠራጠር’ በእምነት የልብህን አውጥተህ ጸልይ፤ እንዲሁም በመንፈሱ የሚሰጥህን መመሪያና በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተቀበል።

14, 15. ሐና ወደ አምላክ በምትጸልይበት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ እምነት እንዳላት አሳይታለች እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው?

14 ሌዋዊው ሕልቃና ከነበሩት ሁለት ሚስቶች አንዷ የሆነችው ሐና ወደ አምላክ በምትጸልይበት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ እምነት እንዳላት አሳይታለች። ሐና ልጅ ስላልነበራት ብዙ ልጆች ያሏት ጣውንቷ ፍናና ታበሳጫት ነበር። ሐና፣ ወንድ ልጅ ከወለደች ለይሖዋ እንደምትሰጠው ወደ ማደሪያው ድንኳን በመሄድ ተሳለች። ሐና ጸሎቷን በምታቀርብበት ወቅት ድምፅዋ ሳይሰማ ከንፈሯ ይንቀሳቀስ ስለነበር ሊቀ ካህናቱ ዔሊ እንደሰከረች አድርጎ ቈጠራት። ዔሊ እንዳልሰከረች ሲያውቅ “የእስራኤል አምላክ የለመንሺውን ይስጥሽ” አላት። ሐና ጸሎቷ ምላሽ የሚያገኘው እንዴት እንደሆነ ባታውቅም ለጸሎቷ መልስ እንደምታገኝ እምነት ነበራት። በመሆኑም ከዚያ በኋላ “በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።”—1 ሳሙ. 1:9-18

15 ሐና ሳሙኤልን ከወለደችና ጡት ካስጣለችው በኋላ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርብ ለይሖዋ ሰጠችው። (1 ሳሙ. 1:19-28) ሐና በዚያ ወቅት ባቀረበችው ጸሎት ላይ ጊዜ ወስደህ ማሰላሰልህ የጸሎትህን ይዘት ያዳብረዋል፤ ከዚህም በላይ የሚያስጨንቅ ነገር በሚያጋጥምህ ጊዜ ይሖዋ ጸሎትህን እንደሚመልስልህ በማመን መጸለይህ ሐዘንህን ለመቋቋም እንደሚያስችልህ እንድትገነዘብ ይረዳሃል።—1 ሳሙ. 2:1-10

16, 17. ነህምያ በሚጸልይበት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ እምነት እንዳለው በማሳየቱ ምን ተከናውኗል?

16 በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ይኖር የነበረው ነህምያ የተባለ ጻድቅ ሰውም በሚጸልይበት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ እምነት እንዳለው አሳይቷል። እንዲህ የሚል ልመና አቅርቦ ነበር:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎት፣ ስምህን በመፍራት ደስ የሚሰኙትን የባሪያዎችህንም ጸሎት ጆሮህ ታድምጥ። በዚህ ሰው ፊት ሞገስን አድርገህለት ዛሬ ለባሪያህ መከናወንን ስጠው።” ነህምያ “በዚህ ሰው” ያለው ማንን ነበር? እንዲህ ያለው ፋርሳዊውን ንጉሥ አርጤክስስን ሲሆን ነህምያ የእሱ ጠጅ አሳላፊ ሆኖ ያገለግል ነበር።—ነህ. 1:11

17 ነህምያ ከባቢሎን ግዞት ነፃ የወጡት አይሁዳውያን ‘በታላቅ መከራና ውርደት ላይ እንደሚገኙና የኢየሩሳሌም ቅጥር እንደፈራረሰ’ ሲሰማ ለብዙ ቀናት በእምነት ጸለየ። (ነህ. 1:3, 4) ንጉሥ አርጤክስስ፣ ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ቅጥሯን እንደገና እንዲገነባ ሲፈቅድለት ጸሎቱ እሱ ከጠበቀው በላቀ መንገድ ተመልሶለታል። (ነህ. 2:1-8) ብዙም ሳይቆይ የከተማዋ ቅጥር ታደሰ። የነህምያ ጸሎት መልስ ያገኘው ጸሎቱ በእውነተኛው አምልኮ ላይ ያተኮረ ስለሆነና በእምነት ስለቀረበ ነው። አንተ የምታቀርበው ጸሎት እንደዚህ ዓይነት ነው?

ውዳሴና ምስጋና ማቅረብን አትርሳ

18, 19. አንድ የይሖዋ አገልጋይ አምላክን እንዲያወድስና እንዲያመሰግን የሚያነሳሱት ምን ምክንያቶች አሉ?

18 በጸሎትህ ላይ ይሖዋን ማወደስና ማመስገንን አትርሳ። እንዲህ ለማድረግ የሚያነሳሱ በጣም ብዙ ምክንያቶች አሉ! ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊት ይሖዋን ስለ መንግሥቱ አወድሶታል። (መዝሙር 145:10-13ን አንብብ።) የይሖዋን መንግሥት የማስታወቅ መብትህን እንደምታደንቅ በጸሎትህ ላይ ታሳያለህ? ከዚህም በተጨማሪ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይኸውም ለጉባኤ፣ ለወረዳና ለልዩ እንዲሁም ለአውራጃ ስብሰባዎች ያለህን አድናቆት ከልብ በመነጨ ጸሎት ለአምላክ ለመግለጽ ሊረዱህ ይችላሉ።—መዝ. 27:4፤ 122:1

19 ከአምላክ ጋር ለመሠረትከው ውድ ዝምድና ያለህ አድናቆት ከልብ የመነጨ ጸሎት እንድታቀርብ ያነሳሳህ ይሆናል፤ ጸሎትህ እንደሚከተለው ያለ ሐሳብ የያዘ ሊሆን ይችላል:- “ጌታ ሆይ፤ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤ በሰዎችም መካከል እዘምርልሃለሁ፤ ምሕረትህ እስከ ሰማይ ከፍ ብላለችና፤ ታማኝነትህም እስከ ደመናት ትደርሳለች። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትስፈን።” (መዝ. 57:9-11) እንዴት ያለ ልብ የሚነካ ሐሳብ ነው! በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት እንዲህ ያሉ ልብ የሚነኩ ሐሳቦች በጸሎትህ ይዘት ላይ ለውጥ ሊያመጡና ጸሎትህን እንድታሻሽል ሊረዱህ ይገባል ቢባል አትስማማም?

ጥልቅ አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ጸልይ

20. ማርያም ለአምላክ ያላትን ጥልቅ አክብሮት የገለጸችው እንዴት ነበር?

20 የምታቀርባቸው ጸሎቶች ለአምላክ ጥልቅ አክብሮት እንዳለህ የሚያሳዩ መሆን አለባቸው። ማርያም የመሲሑ እናት እንደምትሆን ካወቀች በኋላ የተናገረችው ጥልቅ አክብሮት የተንጸባረቀበት ሐሳብ፣ ሐና በማደሪያው ድንኳን ውስጥ እንዲያገለግል ትንሹን ሳሙኤልን በሰጠችበት ወቅት ካቀረበችው ጸሎት ጋር ይመሳሰላል። ማርያም “ነፍሴ ይሖዋን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም አዳኜ በሆነው አምላክ እጅግ ደስ ይሰኛል” በማለት መናገሯ ለአምላክ ጥልቅ አክብሮት እንዳላት በግልጽ ያሳያል። (ሉቃስ 1:46, 47) አንተስ እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን በማካተት የጸሎትህን ይዘት ማሻሻል ትችላለህ? በእርግጥም ፈሪሃ አምላክ የነበራት ማርያም የመሲሑ የኢየሱስ እናት እንድትሆን መመረጧ ምንም አያስገርምም!

21. ኢየሱስ ያቀረባቸው ጸሎቶች ጥልቅ አክብሮትና እምነት እንዳለው የሚያሳዩት እንዴት ነው?

21 ኢየሱስ ሙሉ እምነት እንዳለው በሚያሳይ መንገድ በአክብሮት ጸልዮአል። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ አልዓዛርን ከማስነሳቱ በፊት “ወደ ሰማይ ከተመለከተ በኋላ እንዲህ አለ:- ‘አባት ሆይ፣ ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። እውነት ነው፣ ሁልጊዜ እንደምትሰማኝ አውቃለሁ።’ ” (ዮሐ. 11:41, 42) አንተስ የምታቀርበው ጸሎት እንዲህ ያለ ጥልቅ አክብሮትና እምነት እንዳለህ ያሳያል? ጥልቅ አክብሮት የሚንጸባረቅበትን ኢየሱስ የሰጠውን የናሙና ጸሎት በትኩረት አንብበው፤ በዚህ ጸሎት ላይ ጎላ ብለው የሚታዩት ነጥቦች የይሖዋ ስም መቀደስ፣ የመንግሥቱ መምጣትና የፈቃዱ መፈጸም እንደሆኑ መመልከት ትችላለህ። (ማቴ. 6:9, 10) እስቲ አንተ ስለምታቀርባቸው ጸሎቶች አስብ። ጸሎቶችህ ስለ ይሖዋ መንግሥት፣ ስለ ፈቃዱ መፈጸም እንዲሁም ስለ ስሙ መቀደስ በጥልቅ እንደምታስብ የሚያሳዩ ሊሆኑ ይገባል።

22. ይሖዋ ምሥራቹን ለማወጅ ድፍረት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

22 የአምላክ አገልጋዮች ስደት ወይም ሌሎች መከራዎች ስለሚደርሱባቸው አብዛኛውን ጊዜ ጸሎታቸው፣ ይሖዋን በድፍረት ለማገልገል እርዳታ እንዲያገኙ የሚያቀርቡትን ምልጃም ያካትታል። የሳንሄድሪን ሸንጎ፣ ጴጥሮስና ዮሐንስን ‘በኢየሱስ ስም ማስተማራቸውን’ እንዲያቆሙ ባዘዛቸው ጊዜ ሐዋርያቱ ይህን እንደማያደርጉ በድፍረት ተናገሩ። (ሥራ 4:18-20) ሐዋርያቱ ከተለቀቁ በኋላ ያጋጠማቸውን ነገር ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ነገሯቸው። በዚያ የነበሩት ሁሉ አምላክ ቃሉን በድፍረት እንዲናገሩ እንዲረዳቸው ልመና አቀረቡ። “በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው የአምላክን ቃል በድፍረት መናገር [መጀመራቸው]” የጸሎታቸው መልስ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ምን ያህል ተደስተው ይሆን! (የሐዋርያት ሥራ 4:24-31ን አንብብ።) እነዚህ ክርስቲያኖች በድፍረት መናገር በመቻላቸውም ብዙዎች የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ ረድተዋል። ጸሎት፣ አንተም ምሥራቹን በድፍረት እንድታውጅ ብርታት ሊሰጥህ ይችላል።

የጸሎትህን ይዘት ማሻሻልህን ቀጥል

23, 24. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጸሎትህን ይዘት እንደሚያሻሽል የሚያሳዩ ሌሎች ምሳሌዎችን ጥቀስ። (ለ)  የጸሎትህን ይዘት ለማሻሻል ምን ለማድረግ አስበሃል?

23 መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማጥናት የጸሎትህን ይዘት ሊያዳብር እንደሚችል የሚጠቁሙ ሌሎች በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ፣ አንተም እንደ ዮናስ ‘ድነት ከይሖዋ መሆኑን’ እንደምትቀበል በጸሎትህ ላይ መጥቀስ ትችላለህ። (ዮናስ 2:1-10) ከባድ ኃጢአት በመሥራትህ ትረበሽ ይሆናል፤ እንዲሁም የሽማግሌዎችን እርዳታ ጠይቀህ ይሆናል። በዚህ ወቅት፣ መጸጸትህን ለመግለጽ በግልህ ጸሎት ስታቀርብ የዳዊት መዝሙር ሊረዳህ ይችላል። (መዝ. 51:1-12) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ልክ እንደ ኤርምያስ ይሖዋን በጸሎት ልታወድሰው ትችላለህ። (ኤር. 32:16-19) የትዳር ጓደኛ የምትፈልግ ከሆነ በዕዝራ ምዕራፍ 9 ላይ የሚገኘውን ጸሎት ማጥናትህና በግልህ ልመና ማቅረብህ “በጌታ ብቻ” በማግባት አምላክን ለመታዘዝ ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ሊያጠናክርልህ ይችላል።—1 ቆሮ. 7:39፤ ዕዝራ 9:6, 10-15

24 መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብህንና ማጥናትህን እንዲሁም መመርመርህን ቀጥል። በጸሎትህ ውስጥ ልታካትታቸው የምትችላቸውን ነጥቦች ፈልግ። ልመና እንዲሁም የውዳሴና የምስጋና ጸሎቶች በምታቀርብበት ጊዜ እነዚህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ልትጠቀምባቸው ትችል ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የጸሎትህን ይዘት የምታሻሽል ከሆነ ከመቼው ጊዜ በበለጠ ወደ ይሖዋ አምላክ እየቀረብክ እንደምትሄድ እርግጠኛ ሁን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የአምላክን መመሪያ መፈለግና መከተል ያለብን ለምንድን ነው?

• ጥበብ ለማግኘት እንድንጸልይ ሊያነሳሳን የሚገባው ምንድን ነው?

• በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ሐሳቦች የጸሎታችንን ይዘት ለማሻሻል ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው?

• በእምነትና ጥልቅ አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ መጸለይ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአብርሃም አገልጋይ የአምላክን መመሪያ ለማግኘት ጸልዮአል። አንተስ እንዲህ ታደርጋለህ?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤተሰብ አምልኮ የጸሎታችሁን ይዘት ለማሻሻል ሊረዳችሁ ይችላል