በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጉባኤ ውስጥ ያላችሁን ድርሻ ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ

በጉባኤ ውስጥ ያላችሁን ድርሻ ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ

በጉባኤ ውስጥ ያላችሁን ድርሻ ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ

“አምላክ ለእያንዳንዱ የአካል ክፍል እሱ በፈለገው መንገድ በአካል ውስጥ ቦታ መድቦለታል።”—1 ቆሮ. 12:18

1, 2. (ሀ) ሁሉም የጉባኤው አባላት ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ)  በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

ይሖዋ ከጥንት እስራኤላውያን ዘመን ጀምሮ ሕዝቡን በመንፈሳዊ የሚመግበውና መመሪያ የሚሰጠው በጉባኤ አማካኝነት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን የጋይን ከተማ ካጠፉ በኋላ ኢያሱ ‘በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት የሕጉን ቃላት በሙሉ ማለትም በረከቱንና መርገሙን ሁሉ፣ ልክ በሕጉ መጽሐፍ እንደተጻፈው አንብቧል።’—ኢያሱ 8:34, 35

2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የክርስቲያን ጉባኤ ‘የአምላክ ቤተሰብ’ እንዲሁም “የእውነት ዓምድና ድጋፍ” እንደሆነ የጉባኤ ሽማግሌ ለሆነው ለጢሞቴዎስ ነግሮት ነበር። (1 ጢሞ. 3:15) በዛሬው ጊዜ የሚገኘው ‘የአምላክ ቤተሰብ’ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ኅብረት ነው። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ምዕራፍ 12 ላይ ጉባኤውን ከሰው አካል ጋር አመሳስሎታል። እያንዳንዱ የአካል ክፍል የተለያየ ተግባር ቢያከናውንም ሁሉም የአካል ክፍሎች አስፈላጊ እንደሆኑ ገልጿል። ጳውሎስ “አምላክ ለእያንዳንዱ የአካል ክፍል እሱ በፈለገው መንገድ በአካል ውስጥ ቦታ መድቦለታል” ሲል ጽፏል። እንዲያውም “ብዙም ክብር የላቸውም ብለን የምናስባቸውን የአካል ክፍሎች የበለጠ ክብር እንሰጣቸዋለን” በማለት ሐዋርያው ተናግሯል። (1 ቆሮ. 12:18, 23) በመሆኑም አንድ ጻድቅ ሰው በአምላክ ቤት ውስጥ የሚኖረው ድርሻ ሌላው ታማኝ ክርስቲያን ከሚኖረው ድርሻ የተሻለ ወይም ያነሰ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሁሉም ሰው ድርሻ የተለያየ ነው። ታዲያ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ የሚኖረንን ድርሻ ማወቅ እንዲሁም ይህንን ድርሻችንን ከፍ አድርገን መመልከት የምንችለው እንዴት ነው? በጉባኤ ውስጥ ያለን ድርሻ የተለያየ እንዲሆን የሚያደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዲሁም ‘እድገታችን በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ’ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?—1 ጢሞ. 4:15

ድርሻችንን ከፍ አድርገን መመልከት የምንችለው እንዴት ነው?

3. በጉባኤ ውስጥ ያለንን ድርሻ ማወቅና ድርሻችንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

3 በጉባኤ ውስጥ ያለንን ድርሻ ማወቅና ድርሻችንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ‘ከታማኝና ልባም ባሪያ’ እንዲሁም ባሪያውን ከሚወክለው የበላይ አካል ጋር ሙሉ በሙሉ መተባበር ነው። (ማቴዎስ 24:45-47ን አንብብ።) ታማኝና ልባም ባሪያ ለሚሰጠን መመሪያ ምን ያህል ታዛዦች እንደሆንን ራሳችንን መመርመር ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል፣ ባለፉት ዓመታት አለባበስንና አጋጌጥን፣ መዝናኛን እንዲሁም ተገቢ ያልሆነ የኢንተርኔት አጠቃቀምን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መመሪያ ሲሰጠን ቆይቷል። መንፈሳዊነታችንን ከአደጋ ለመጠበቅ የሚረዱትን እነዚህን ጠቃሚ ምክሮች አጥብቀን እንከተላቸዋለን? ቋሚ የሆነ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም እንዲኖረን የተሰጠንን ማሳሰቢያ በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ይህንን ምክር በመቀበል ለዚህ ዓላማ የሚሆን አንድ ምሽት መድበናል? ያላገባን ክርስቲያኖች ከሆንን ደግሞ ቅዱሳን መጻሕፍትን በግላችን ለማጥናት የሚያስችል ጊዜ ዋጅተናል? ታማኝና ልባም ባሪያ የሚሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ በግለሰብም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ይባርከናል።

4. ከግል ጉዳዮቻችን ጋር በተያያዘ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ የትኞቹን ነገሮች ከግምት ማስገባት ይኖርብናል?

4 አንዳንዶች እንደ መዝናኛ እንዲሁም አለባበስና አጋጌጥ ባሉት ጉዳዮች ረገድ እያንዳንዱ ክርስቲያን የራሱን ውሳኔ ሊያደርግ ይገባል የሚል አመለካከት ይኖራቸው ይሆናል። በጉባኤ ውስጥ ያለውን ድርሻ ከፍ አድርጎ የሚመለከት ራሱን የወሰነ ክርስቲያን ግን ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜ ከግምት የሚያስገባው የግል ምርጫውን ብቻ መሆን የለበትም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘውን የይሖዋ አመለካከት ለማወቅ ልዩ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። የአምላክ ቃል ‘ለእግራችን መብራት፣ ለመንገዳችንም ብርሃን’ ሊሆንልን ይገባል። (መዝ. 119:105) ከዚህም በተጨማሪ ከግል ጉዳዮቻችን ጋር በተያያዘ የምናደርገው ምርጫ አገልግሎታችንን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤው ውጪ ያሉትን ሰዎች የሚነካው እንዴት እንደሆነ ከግምት ማስገባታችን የጥበብ አካሄድ ነው።—2 ቆሮንቶስ 6:3, 4ን አንብብ።

5. በራስ የመመራት መንፈስ እንዳናዳብር መጠንቀቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

5 “በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን እየሠራ ያለ መንፈስ” ልክ እንደምንተነፍሰው አየር የትም ቦታ የሚገኝ ሆኗል። (ኤፌ. 2:2) ይህ መንፈስ የይሖዋ ድርጅት መመሪያ አያስፈልገንም የሚል አመለካከት እንዲኖረን ሊያደርግ ይችላል። ‘ከሐዋርያው ዮሐንስ ምንም ነገር በአክብሮት እንዳልተቀበለው’ እንደ ዲዮጥራጢስ መሆን እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። (3 ዮሐ. 9, 10) በራስ የመመራት መንፈስ እንዳናዳብር መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ለሚጠቀምበት ድርጅቱ አክብሮት እንደጎደለን የሚያሳይ ነገር በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን እንዳናንጸባርቅ ልንጠነቀቅ ይገባል። (ዘኍ. 16:1-3) ከዚህ ይልቅ ከባሪያው ጋር ተባብሮ የመሥራት መብታችንን ከፍ አድርገን መመልከት ይኖርብናል። በጉባኤያችን ውስጥ አመራር የሚሰጡንን ወንዶች ለመታዘዝ እንዲሁም ለእነሱ ለመገዛት መጣር ይኖርብናል።—ዕብራውያን 13:7, 17ን አንብብ።

6. የግል ሁኔታችንን መመርመር የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

6 በጉባኤ ውስጥ ያለንን ድርሻ ከፍ አድርገን እንደምንመለከት የምናሳይበት ሌላው መንገድ ደግሞ ሁኔታችንን በጥንቃቄ መመርመርና ‘አገልግሎታችንን ለማክበር’ እንዲሁም ለይሖዋ ክብር ለማምጣት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ነው። (ሮም 11:13) አንዳንዶች የዘወትር አቅኚ ሆነው ማገልገል ችለዋል። ሌሎች ደግሞ ሚስዮናዊ፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ አባላት በመሆን በአንድ ዓይነት የልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ተሰማርተዋል። በርካታ ወንድሞችና እህቶች በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ይካፈላሉ። አብዛኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች የቤተሰባቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት እንዲሁም በየሳምንቱ በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ የተቻላቸውን ያህል ይጥራሉ። (ቆላስይስ 3:23, 24ን አንብብ።) እኛም አምላክን ለማገልገል ራሳችንን በፈቃደኝነት ስናቀርብ እንዲሁም እሱን በሙሉ ነፍስ ለማገልገል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ምንጊዜም በድርጅቱ ውስጥ ድርሻ እንደሚኖረን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ድርሻችን የተለያየ እንዲሆን የሚያደርጉት ነገሮች

7. ሁኔታዎቻችን በጉባኤ ውስጥ በሚኖረን ድርሻ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አብራራ።

7 በተወሰነ መጠንም ቢሆን በጉባኤ ውስጥ የሚኖረን ድርሻ የተመካው በሁኔታችን ላይ በመሆኑ ያለንበትን ሁኔታ መመርመራችን በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በጉባኤ ውስጥ ወንድሞች የሚኖራቸው ድርሻ በአንዳንድ መንገዶች ከእህቶች የተለየ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ዕድሜ፣ ጤንነት እንዲሁም ሌሎች ነገሮች በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን በምንችለው ነገር ላይ ተጽዕኖ ያደርጋሉ። ምሳሌ 20:29 “የጎልማሶች ክብር ብርታታቸው፣ የሽማግሌዎችም ሞገስ ሽበታቸው ነው” ይላል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ባላቸው ኃይል ተጠቅመው ይበልጥ ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎችን ማከናወን ይችሉ ይሆናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በዕድሜ የገፉት የጉባኤው አባላት ባካበቱት ጥበብና ተሞክሮ ጉባኤውን በእጅጉ ይጠቅማሉ። ሌላው ልናስታውሰው የሚገባ ነጥብ ደግሞ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ማንኛውንም ነገር ማከናወን የቻልነው በአምላክ ጸጋ መሆኑን ነው።—ሥራ 14:26፤ ሮም 12:6-8

8. በጉባኤ ውስጥ በምናከናውነው ነገር ላይ ፍላጎት ምን ያህል ተጽዕኖ ያሳድራል?

8 የሁለት ወጣት እህትማማቾችን ሁኔታ እንደ ምሳሌ መመልከታችን በጉባኤ ውስጥ የሚኖረን ድርሻ የተለያየ እንዲሆን የሚያደርገውን ሌላ ምክንያት ለመረዳት ያስችለናል። እህትማማቾቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል። ያሉበት ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። እነዚህ ልጆች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የዘወትር አቅኚ እንዲሆኑ ለማበረታታት ወላጆቻቸው የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። እህትማማቾቹ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ አንደኛዋ የዘወትር አቅኚ ስትሆን ሌላዋ የሙሉ ቀን ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ጀመረች። የተለያየ ምርጫ ያደረጉት ለምንድን ነው? ፍላጎታቸው የተለያየ በመሆኑ ነው። ሁለቱም በፍላጎታቸው መሠረት የየራሳቸውን ምርጫ አድርገዋል። የአብዛኞቻችን ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ አይደለም? በአምላክ አገልግሎት ምን ማከናወን እንደምንፈልግ በቁም ነገር ልናስብ ይገባል። ሁኔታዎቻችንን ማስተካከል የሚጠይቅብን ቢሆንም እንኳ በአምላክ አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ መጨመር እንችል ይሆን?—2 ቆሮ. 9:7

9, 10. በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ተሳትፎ የማድረግ ፍላጎት ባይኖረን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

9 በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ተሳትፎ የማድረግ ፍላጎት ባይኖረንና በጉባኤ ውስጥ የተወሰነ እንቅስቃሴ በማድረግ ብቻ ረክተን የምንኖር ብንሆንስ? ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ሲል ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በውስጣችሁ የሚሠራው አምላክ ነው።” አዎ፣ ፍላጎት እንዲያድርብን ይሖዋ በውስጣችን ሊሠራ ይችላል።—ፊልጵ. 2:13፤ 4:13

10 እንግዲያው ይሖዋ፣ ፈቃዱን እንድናደርግ ያነሳሳን ዘንድ ልንጠይቀው አይገባም? የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት እንዲህ አድርጓል። “እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ። አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣ በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ” በማለት ጸልዮአል። (መዝ. 25:4, 5) እኛም ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር የማከናወን ፍላጎት እንዲኖረን ይረዳን ዘንድ በመጸለይ የዳዊትን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ይሖዋ አምላክና ልጁ፣ የሚፈልጉትን ነገር ስናደርግ ምን እንደሚሰማቸው ማሰባችን ልባችን ለእነሱ ባለን አድናቆት እንዲሞላ ያደርጋል። (ማቴ. 26:6-10፤ ሉቃስ 21:1-4) እንዲህ ያለው የአድናቆት ስሜት ደግሞ መንፈሳዊ እድገት የማድረግ ፍላጎት ይኖረን ዘንድ እንዲረዳን ይሖዋን እንድንጠይቀው ሊያነሳሳን ይችላል። ነቢዩ ኢሳይያስ ልናዳብረው የሚገባንን ዝንባሌ በተመለከተ አርዓያ ትቶልናል። የይሖዋ ድምፅ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” በማለት ሲጠይቅ ነቢዩ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።—ኢሳ. 6:8

እድገት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

11. (ሀ) በድርጅቱ ውስጥ ኃላፊነት ወስደው የሚያገለግሉ ወንድሞች በጣም ያስፈልጋሉ የምንለው ለምንድን ነው? (ለ)  አንድ ወንድም ጉባኤውን ለማገልገል የሚያስችል መብት ላይ መድረስ የሚችለው እንዴት ነው?

11 በ2008 የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ 289,678 ሰዎች የተጠመቁ ሲሆን ይህም ጉባኤውን የሚመሩ በርካታ ወንድሞች እንደሚያስፈልጉ በግልጽ ያሳያል። አንድ ወንድም ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ምን ማድረግ ይኖርበታል? በአጭር አነጋገር፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች የሚጠበቁባቸውን ብቃቶች ለማሟላት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። (1 ጢሞ. 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9) አንድ ወንድም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ብቃቶች ለማሟላት ጥረት ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? በአገልግሎት በንቃት በመሳተፍ፣ የጉባኤ ኃላፊነቶቹን በትጋት በመወጣት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጠውን ሐሳብ ለማሻሻል ጠንክሮ በመሥራት እንዲሁም ለእምነት ባልንጀሮቹ በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት በማሳየት ነው። እንዲህ ማድረጉ በጉባኤ ውስጥ ያለውን ድርሻ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ያሳያል።

12. ወጣቶች ለእውነት ቅንዓት እንዳላቸው ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

12 ወጣት የሆኑ ወንድሞች በተለይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙት በጉባኤ ውስጥ እድገት ለማድረግ ምን ማድረግ ይችላሉ? የቅዱሳን መጻሕፍትን እውቀት በመቅሰም ‘በጥበብና በመንፈሳዊ ግንዛቤ’ እድገት ለማድረግ መጣር ይችላሉ። (ቆላ. 1:9) የአምላክን ቃል በትጋት ማጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ጥርጥር የለውም። ወጣት ወንዶች፣ በተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መብቶች ለመካፈል በሚያስችላቸው “ትልቅ የሥራ በር” ለመግባት የሚያስፈልጋቸውን ብቃት ለሟሟላት በመጣጣርም እድገት ማድረግ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 16:9) በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ተሰማርተን ይሖዋን ማገልገል በሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ እርካታ እንድናገኝ የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ የተትረፈረፈ በረከት ለማጨድ ያስችለናል።—መክብብ 12:1ን አንብብ።

13, 14. እህቶች በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ ማሳየት የሚችሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

13 እህቶች ደግሞ መዝሙር 68:11 (የ1980 ትርጉም) ፍጻሜውን እንዲያገኝ በግለሰብ ደረጃ አስተዋጽኦ በማበርከት በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ ማሳየት ይችላሉ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጠ፤ ብዙ ሴቶችም ዜናውን አሰራጩ።” እህቶች በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ እንደሚያደንቁ ማሳየት ከሚችሉባቸው መንገዶች መካከል ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈል ነው። (ማቴ. 28:19, 20) በመሆኑም እህቶች በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ በማድረግና ለዚህ ሥራ ሲሉ በፈቃዳቸው መሥዋዕትነት በመክፈል በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ያሳያሉ።

14 ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል:- “አረጋውያን ሴቶች ለቅዱሳን ሰዎች የሚገባ ባሕርይ ያላቸው፣ . . . እንዲሁም ጥሩ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ፤ ይህም ወጣት ሴቶችን ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ በመርዳት ባሎቻቸውን የሚወዱ፣ ልጆቻቸውን የሚወዱ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ንጹሖች፣ በቤት ውስጥ የሚሠሩ፣ ጥሩዎችና ለባሎቻቸው የሚገዙ እንዲሆኑ ለማድረግ ያስችላቸዋል፤ ይህም የአምላክ ቃል እንዳይሰደብ ያደርጋል።” (ቲቶ 2:3-5) በእርግጥም የጎለመሱ እህቶች በጉባኤ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ። እህቶች በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡትን ወንድሞች በማክበር እንዲሁም እንደ አለባበስ፣ አጋጌጥና መዝናኛ ባሉት ጉዳዮች ረገድ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ በማድረግ ለሌሎች ግሩም ምሳሌ የሚተዉ ከመሆኑም ሌላ በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ ያሳያሉ።

15. አንዲት ያላገባች እህት የብቸኝነትን ስሜት ለማሸነፍ ምን ማድረግ ትችላለች?

15 አንዳንድ ጊዜ፣ ያላገቡ እህቶች በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ማስተዋል ያስቸግራቸው ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ችግር ያጋጠማት አንዲት እህት “የነጠላነት ሕይወት አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነት እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል” ብላለች። ይህች እህት ይህንን ሁኔታ እንዴት እንደተቋቋመችው ስትጠየቅ እንዲህ ብላለች:- “ጸሎትና የግል ጥናት በጉባኤ ውስጥ ያለኝን ድርሻ እንደገና እንዳስተውል ረድተውኛል። በግል ጥናቴ ላይ ይሖዋ ለእኔ ስላለው አመለካከት ለማወቅ ምርምር አደርጋለሁ። እንዲሁም የጉባኤውን አባላት ለመርዳት ጥረት አደርጋለሁ። እንዲህ ማድረጌ ስለ ራሴ ብቻ እንዳላስብ ረድቶኛል።” በመዝሙር 32:8 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ ዳዊትን “እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” ብሎታል። በእርግጥም፣ ይሖዋ ያላገቡ እህቶችን ጨምሮ ለእያንዳንዱ አገልጋዩ በግለሰብ ደረጃ ያስባል፤ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።

ድርሻችሁን ላለማጣት ተጠንቀቁ!

16, 17. (ሀ) የይሖዋን ግብዣ ተቀብለን የድርጅቱ ክፍል መሆናችን በሕይወታችን ውስጥ ካደረግናቸው ውሳኔዎች ሁሉ የላቀ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ)  በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያለንን ውድ ቦታ እንዳናጣ መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

16 ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ አገልጋዮቹ ከእሱ ጋር ዝምድና እንዲመሠርቱ በግለሰብ ደረጃ ስቧቸዋል። ኢየሱስ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም” ብሏል። (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ በምድር ላይ ካሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሃል እኛን መርጦ በዛሬው ጊዜ ያለው ጉባኤው ክፍል እንድንሆን በግለሰብ ደረጃ ግብዣ አቅርቦልናል። እኛም ይህን ግብዣ ተቀብለን የጉባኤው ክፍል መሆናችን በሕይወታችን ውስጥ ካደረግናቸው ውሳኔዎች ሁሉ የላቀ ነው። ይህ ሕይወታችን ዓላማና ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርጎታል። በጉባኤ ውስጥ ድርሻ ያለን መሆኑ ታላቅ ደስታና እርካታ አስገኝቶልናል!

17 መዝሙራዊው ‘ይሖዋ ሆይ፤ የምትኖርበትን ቤት ወደድሁ’ በማለት ተናግሯል። አክሎም “እግሮቼ በደልዳላ ስፍራ ቆመዋል፤ በታላቅ ጉባኤ መካከልም እግዚአብሔርን እባርከዋለሁ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 26:8, 12) እውነተኛው አምላክ በድርጅቱ ውስጥ ሁላችንም ድርሻ እንዲኖረን አድርጓል። ቲኦክራሲያዊውን አመራር መከተላችንን በመቀጠል እንዲሁም በአምላክ አገልግሎት ሥራ የበዛልን በመሆን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያለንን ውድ ቦታ እንዳናጣ መጠንቀቅ እንችላለን።

ታስታውሳለህ?

• ሁሉም ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ድርሻ አላቸው ብለን መደምደማችን ምክንያታዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

• በአምላክ ድርጅት ውስጥ ያለንን ድርሻ ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• በጉባኤ ውስጥ ያለን ድርሻ የተለያየ እንዲሆን የሚያደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

• ክርስቲያን ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች በድርጅቱ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድሞች ጉባኤውን ለማገልገል የሚያስችል መብት ላይ መድረስ የሚችሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እህቶች በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?