በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከልብ ተነሳስቶ በደስታ መስጠት

ከልብ ተነሳስቶ በደስታ መስጠት

ከልብ ተነሳስቶ በደስታ መስጠት

ሐዋርያው ጳውሎስ መስጠትን በተመለከተ “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮ. 9:7) ይሖዋ ማንም ሰው ንጹሑን አምልኮ እንዲደግፍ አያስገድድም። አገልጋዮቹ ለእሱ ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ በፈቃዳቸውና በደስታ እንዲሰጡ ይፈልጋል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንደታየው ሕዝቦቹ መዋጮ እንዲያደርጉ የቀረበላቸውን ግብዣ በመቀበል በደስታ ሰጥተዋል። ሦስት ምሳሌዎችን እንመልከት።

ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን ከግብፅ ካወጣቸው በኋላ የማደሪያውን ድንኳን እንዲሠሩ አዘዛቸው። ሥራውን ለማከናወን አንዳንድ ቁሳቁሶች ያስፈልጉ ስለነበር እስራኤላውያን መዋጮ እንዲያደርጉ ግብዣ ቀረበላቸው። በምላሹም ‘ልቡ ያነሣሣው ሁሉ’ ወርቅና ብር፣ ጌጣጌጥ እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶችን አመጣ። ሕዝቡ በልግስና ያመጡት ስጦታ በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ስጦታ ማምጣታቸውን እንዲያቆሙ ማስነገር አስፈልጎ ነበር።—ዘፀ. 35:5, 21፤ 36:6, 7

ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ቤተ መቅደሱ በተገነባበት ጊዜም የአምላክ ሕዝቦች ንጹሑን አምልኮ ለመደገፍ የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ንጉሥ ዳዊት ለግንባታው የሚሆን ከፍተኛ መጠን ያለው መዋጮ በግሉ ያደረገ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም መዋጮ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። ሕዝቡም በፈቃደኝነትና በደስታ ይህንን አድርገዋል። በስጦታ የመጣው ወርቅና ብር ብቻ እንኳ አሁን ባለው ዋጋ ቢተመን ከ100 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይበልጥ ነበር! ሕዝቡ በገዛ ፈቃዳቸው ለይሖዋ መስጠታቸው አስደስቷቸው ነበር።—1 ዜና 29:3-9፤ 2 ዜና 5:1

የጥንቶቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮችም በደስታ የመስጠት መንፈስ እንዳላቸው አሳይተዋል። በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የተጠመቁ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች አልነበሩም። ከእነዚህ ደቀ መዛሙርት መካከል ብዙም ገንዘብ ያልነበራቸው በከተማው ቆይተው ስለ አዲሱ እምነታቸው የበለጠ የማወቅ አጋጣሚ እንዲያገኙ ለመርዳት ሲባል ለተወሰነ ጊዜ ወንድሞች ገንዘብ አሰባስበው ነበር። ወንድሞች ንብረታቸውን በመሸጥ ገንዘቡን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እንዲውል ለሐዋርያት ሰጧቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች እምነታቸውንና ፍቅራቸውን በዚህ መንገድ መግለጻቸው ይሖዋን ምንኛ አስደስቶት ይሆን!—ሥራ 2:41-47

በዛሬው ጊዜም ክርስቲያኖች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን በልግስና እንዲሁም በደስታ በመስጠት ንጹሑን አምልኮ መደገፋቸውን ቀጥለዋል። ከታች የሚገኘው ሣጥን አንተም ይህን ማድረግ የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ይጠቁማል።

[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አንዳንዶች መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች

ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረጉ መዋጮዎች

ብዙዎች “ለዓለም አቀፉ ሥራ” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩት የተወሰነ ገንዘብ ያስቀምጣሉ ወይም ይመድባሉ።

ጉባኤዎች የተዋጣውን ገንዘብ በአገራቸው ሥራውን ለሚቆጣጠረው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ በየወሩ ይልካሉ። ከዚህ በተጨማሪ በፈቃደኝነት የሚደረጉ የገንዘብ መዋጮዎችን በቀጥታ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፖ.ሣ.ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ በሚለው አድራሻ ወይም ባላችሁበት አገር ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። (ከታች በተዘረዘሩት መንገዶች በፈቃደኝነት የሚደረጉ ስጦታዎችንም ባላችሁበት አገር ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል።) ቼኮች ለ“የይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት። ከውድ ማዕድናት የተሠሩ ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም መስጠት ይቻላል። የተላከው ዕቃ ሙሉ በሙሉ ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ ተያይዞ መላክ ይኖርበታል።

ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ የሚሰጥበት ዝግጅት

አንድ ሰው ገንዘቡን የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት ዓለም አቀፉን ሥራ ለማካሄድ እንዲጠቀምበት በአደራ መልክ ሊሰጥና ሲያስፈልገው ድርጅቱን በመጠየቅ መልሶ ማግኘት ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ በመጻፍ ወይም በስልክ ቁጥር 011-6603611 በመደወል የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮ መጠየቅ ይቻላል።

በእቅድ የሚደረግ ስጦታ

ገንዘብ በስጦታ ከመለገስ በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ መደገፍ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። እነዚህም የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ:-

ኢንሹራንስ:- የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት የሕይወት ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል።

የባንክ ሒሳብ:- የአገሩ ባንክ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት ሊሰጥ ይችላል።

አክሲዮኖችና ቦንዶች:- አክሲዮኖችንና ቦንዶችን በስጦታ መልክ ለይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት መስጠት ይቻላል፤ ወይም ደግሞ በሞት ጊዜ ለይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዲሰጥ ስም ሊዛወርለት ይችላል።

የማይንቀሳቀስ ንብረት:- ሊሸጥ ሊለወጥ የሚችል ቋሚ ንብረት በስጦታ መስጠት ወይም መኖሪያ ቤት በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ባለ ንብረቱ በሕይወት እስካለ ድረስ ተጠቅሞበት ከዚያ በኋላ ማውረስ ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ከማዛወሩ በፊት በአገሩ ከሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር መነጋገር ይኖርበታል።

የስጦታ አበል:- የስጦታ አበል አንድ ሰው ገንዘቡን ወይም የባለቤትነት መብትን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን የይሖዋ ምሥክሮችን ወክሎ ለሚሠራው ድርጅት ለማዛወር የሚያደርገውን ዝግጅት ያመለክታል። በምላሹም ለጋሹ ወይም እሱ የወከለው ግለሰብ በሕይወት እስካለበት ጊዜ ድረስ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በየዓመቱ በአበል መልክ ይከፈለዋል።

ኑዛዜዎችና አደራዎች:- ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተቀባይነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት በውርስ ሊሰጥ ወይም የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዛወር ይችላል።

“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው አገላለጽ፣ እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች የሚያደርገው ግለሰብ እቅድ ማውጣት እንደሚያስፈልገው ይጠቁማል። የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ ሥራ በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደገፍ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ዓለም አቀፉን የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ለመደገፍ በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር በእንግሊዝኛና በስፓንኛ ቋንቋ ተዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ሰዎች ስጦታ ለመስጠት ወይም በሚሞቱበት ጊዜ በኑዛዜ ውርስ ለመተው የሚችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች አስመልክቶ መረጃ ለመስጠት ነው። ብዙዎች ይህን ብሮሹር ካነበቡ በኋላ ከሕግ ወይም ከቀረጥ አማካሪዎቻቸው ጋር በመማከር በዓለም ዙሪያ የምናከናውነውን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴና ሰብዓዊ እርዳታ ለመደገፍ ከመቻላቸውም በላይ ከቀረጥ ጋር በተያያዘ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ችለዋል። ይህን ብሮሹር ለማግኘት በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ የሚከታተለውን ቢሮ በቀጥታ መጠየቅ ይቻላል።

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከታች ያለውን አድራሻ ወይም ስልክ ቁጥር ተጠቅመህ ቅርንጫፍ ቢሮውን መጠየቅ ትችላለህ። አሊያም ባለህበት አገር ለሥራው አመራር የሚሰጠውን ቅርንጫፍ ቢሮ ማነጋገር ትችላለህ።

የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት

ፖ.ሣ.ቁ. 5522

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ

ስልክ:- 011-6603611