በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታቀርበው ጸሎት ስለ አንተ ምን ይገልጻል?

የምታቀርበው ጸሎት ስለ አንተ ምን ይገልጻል?

የምታቀርበው ጸሎት ስለ አንተ ምን ይገልጻል?

“ጸሎትን የምትሰማ ሆይ፤ የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ።”—መዝ. 65:2

1, 2. የይሖዋ አገልጋዮች አምላክ እንደሚሰማቸው በመተማመን ወደ እሱ መጸለይ የሚችሉት ለምንድን ነው?

ይሖዋ የታማኝ አገልጋዮቹን ጸሎት ምንጊዜም ይሰማል። አምላክ የምናቀርበውን ጸሎት እንደሚሰማ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በተመሳሳይ ጊዜ ወደ አምላክ ቢጸልዩ እንኳ አንዳቸውም ‘መስመሩ ተይዟል’ የሚል ምላሽ አያገኙም።

2 መዝሙራዊው ዳዊት፣ የሚያቀርበውን ልመና አምላክ እንደሚሰማው በመተማመን “ጸሎትን የምትሰማ ሆይ፤ የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 65:2) ዳዊት ታማኝ የይሖዋ አምላኪ በመሆኑ ጸሎቱ ተሰምቶለታል። እኛም እንደሚከተለው በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘የማቀርበው ጸሎት በይሖዋ እንደምተማመንና ለንጹሕ አምልኮ ቅድሚያ እንደምሰጥ ያሳያል? ጸሎቴ ስለ እኔ ምን ይገልጻል?’

ወደ ይሖዋ በትሕትና ጸልይ

3, 4. (ሀ) ወደ አምላክ ስንጸልይ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል? (ለ)  በፈጸምነው ከባድ ኃጢአት የተነሳ አእምሯችን በሚያስጨንቅ ‘ሐሳብ’ ቢወጠር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

3 ጸሎታችን እንዲሰማ ከፈለግን በትሕትና ወደ አምላክ መቅረብ አለብን። (መዝ. 138:6) ዳዊት እንደሚከተለው በማለት ይሖዋን ጠይቆ ነበር:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ፤ የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።” (መዝ. 139:23, 24) እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ እንዲመረምረን በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል። እንዲህ ዓይነት ጸሎት ከማቅረብም በተጨማሪ አምላክ እንዲመረምረን ፈቃደኞች መሆንና በቃሉ አማካኝነት የሚሰጠንን ምክር መቀበል አለብን። ይሖዋ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን ጎዳና እንድንከተል በመርዳት ‘በዘላለም መንገድ’ ሊመራን ይችላል።

4 በፈጸምነው ከባድ ኃጢአት የተነሳ አእምሯችን በሚያስጨንቅ ‘ሐሳብ’ ቢወጠር ምን ማድረግ ይኖርብናል? (መዝሙር 32:1-5ን አንብብ።) በበጋ ወቅት የሚኖረው ኃይለኛ ሙቀት አንድን ዛፍ እንደሚያደርቀው ሁሉ የሕሊናችንን ወቀሳ ለመሸሽ መሞከርም ኃይላችንን ሊያሟጥጠው ይችላል። ዳዊት በሠራው ኃጢአት ምክንያት ደስታውን ያጣ ከመሆኑም ሌላ ጤንነቱ ተቃውሶ ሊሆን ይችላል። ኃጢአቱን ለአምላክ መናዘዙ ግን ትልቅ እፎይታ አስገኝቶለታል! ዳዊት ‘መተላለፉ ይቅር ሲባልለትና’ ይሖዋ ምሕረት ሲያደርግለት ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ኃጢአትን ለአምላክ መናዘዝ እፎይታ ሊያስገኝ ይችላል፤ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሚሰጡት እርዳታም የተሳሳተው ሰው መንፈሳዊ ጤንነቱን መልሶ እንዲያገኝ ይረዳዋል።—ምሳሌ 28:13፤ ያዕ. 5:13-16

ለአምላክ ምልጃና ምስጋና አቅርብ

5. ለይሖዋ ምልጃ ማቅረብ ሲባል ምን ማለት ነው?

5 አንድ በጣም የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥመን የሚከተለውን የጳውሎስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል:- “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።” (ፊልጵ. 4:6) “ምልጃ” ሲባል “በትሕትና ልመና ማቅረብ” ማለት ነው። በተለይም በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ወይም ስደት ሲደርስብን ይሖዋ እንዲረዳንና እንዲመራን ምልጃ ማቅረብ ይኖርብናል።

6, 7. በጸሎታችን ውስጥ ምስጋናን ማካተት ያለብን ለምንድን ነው?

6 ይሁን እንጂ የምንጸልየው አንድ ነገር ስንፈልግ ብቻ ከሆነ ይህ ከይሖዋ ጋር ስላለን ዝምድና ምን ይገልጻል? ጳውሎስ ልመናችንን ‘ከምስጋና ጋር’ ለአምላክ ማቅረብ እንዳለብን ተናግሯል። ዳዊት እንደሚከተለው በማለት አምላክን አመስግኖ ነበር:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ ታላቅነት፣ ኀይል፣ ክብርና ግርማ የአንተ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ መንግሥትም የአንተ ነው፤ አንተም እንደ ራስ ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያልህ ነህ። . . . አምላካችን ሆይ፤ አሁንም እናመሰግንሃለን፤ ለከበረው ስምህም ውዳሴ እናቀርባለን።” (1 ዜና 29:11-13) እኛም እንደ ዳዊት ምስጋናችንን ለመግለጽ የሚያበቃ ምክንያት እንዳለን ምንም ጥርጥር የለውም።

7 ኢየሱስ በምግብ ሰዓት የማመስገን ልማድ የነበረው ከመሆኑም በላይ በጌታ ራት ምሽት ለቀረበው ቂጣና ወይን አምላክን አመስግኖ ነበር። (ማቴ. 15:36፤ ማር. 14:22, 23) እኛም ልክ እንደ ኢየሱስ ላገኘነው ምግብ አመስጋኝነታችንን ከመግለጽ አልፈን ‘ለሰው ልጆች ስላደረገው ድንቅ ሥራ’ ብሎም ‘ስለ ጻድቅ ሥርዓቱ’ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው ቃሉ ወይም መልእክቱ ይሖዋን ‘ማመስገን’ ይኖርብናል።—መዝ. 107:15፤ 119:62,105

ለሌሎች ጸልይ

8, 9. ለክርስቲያን ባልንጀሮቻችን መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

8 ስለራሳችን እንደምንጸልይ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ስለሌሎች ሌላው ቀርቶ በስም ስለማናውቃቸው ክርስቲያኖች ጭምር መጸለይ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ የነበሩትን ክርስቲያኖች በሙሉ ባያውቃቸውም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ስለ እናንተ ስንጸልይ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነውን አምላክ ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ ምክንያቱም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ ያላችሁን እምነትና ለቅዱሳን ሁሉ የምታሳዩትን ፍቅር ሰምተናል።” (ቆላ. 1:3, 4) ጳውሎስ በተሰሎንቄ ስለሚገኙ ክርስቲያኖችም ጸልዮአል። (2 ተሰ. 1:11, 12) እንዲህ ዓይነት ጸሎት ማቅረባችን ስለ መንፈሳዊነታችንም ሆነ ለክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስላለን አመለካከት በሚገባ ይገልጻል።

9 ቅቡዓን ክርስቲያኖችንም ሆነ አጋሮቻቸው የሆኑትን “ሌሎች በጎች” በተመለከተ የምናቀርበው ጸሎት ስለ አምላክ ድርጅት እንደምናስብ ያሳያል። (ዮሐ. 10:16) ጳውሎስ ‘የመናገር ችሎታ ኖሮት የምሥራቹን ቅዱስ ሚስጥር ለሌሎች ማሳወቅ ይችል ዘንድ’ እንዲጸልዩለት የእምነት ባልንጀሮቹን ጠይቋቸዋል። (ኤፌ. 6:17-20) እኛስ ስለ ሌሎች ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ጸሎት እናቀርባለን?

10. ስለ ሌሎች መጸለያችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

10 ስለ ሌሎች መጸለያችን ለእነሱ ያለን አመለካከት እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል። ለመውደድ የሚከብደን አንድ ሰው ይኖር ይሆናል፤ ይሁንና ይህን ሰው በተመለከተ የምንጸልይ ከሆነ ለግለሰቡ ያለን አመለካከት መለወጡ አይቀርም። (1 ዮሐ. 4:20, 21) እንዲህ ዓይነት ጸሎት ማቅረብ የሚያንጽ ከመሆኑም በላይ ከወንድሞቻችን ጋር አንድነት እንዲኖረን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ያለ ጸሎት የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር እንዳለን ያሳያል። (ዮሐ. 13:34, 35) ይህ ባሕርይ ከአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ነው። ታዲያ እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነትና ራስን መግዛት ያሉትን የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ለማንጸባረቅ እንዲረዳን የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት እንጸልያለን? (ሉቃስ 11:13፤ ገላ. 5:22, 23) ከሆነ ንግግራችንም ሆነ ድርጊታችን በመንፈስ እንደምንመላለስና እንደምንኖር የሚያሳይ ይሆናል።—ገላትያ 5:16, 25ን አንብብ።

11. ሌሎች ስለ እኛ እንዲጸልዩልን መጠየቃችን ተገቢ ነው የምትለው ለምንድን ነው?

11 ልጆቻችን በትምህርት ቤት ፈተና ላይ ከመኮረጅ ጋር በተያያዘ እንደሚፈተኑ ካወቅን ስለ እነሱ ልንጸልይ እንዲሁም በሐቀኝነት እንዲመላለሱና ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር እንዳያደርጉ ቅዱስ ጽሑፋዊ እርዳታ ልናደርግላቸው ይገባል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “ምንም መጥፎ ነገር እንዳትሠሩ ወደ አምላክ እንጸልያለን” ብሏቸዋል። (2 ቆሮ. 13:7) በትሕትና እንዲህ ዓይነት ጸሎት ማቅረባችን ይሖዋን የሚያስደስተው ከመሆኑም ሌላ ስለ እኛ መልካምነት ይመሠክራል። (ምሳሌ 15:8ን አንብብ። ) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረገው ሌሎች ስለ እኛ እንዲጸልዩልን መጠየቅ እንችላለን። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለእኛ መጸለያችሁን ቀጥሉ፤ ምክንያቱም በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር ስለምንመኝ ሐቀኛ ሕሊና እንዳለን እርግጠኞች ነን።”—ዕብ. 13:18

ጸሎቶቻችን ስለ እኛ የሚገልጿቸው ሌሎች ነገሮች

12. የጸሎታችን ዓቢይ ክፍል ሊሆኑ የሚገባቸው የትኞቹ ነገሮች ናቸው?

12 ጸሎቶቻችን ደስተኛና ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆንን ይጠቁማሉ? የምናቀርበው ልመና በዋነኝነት የሚያተኩረው ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምቶ በመኖር፣ የመንግሥቱን መልእክት በመስበክ፣ በይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥና በስሙ መቀደስ ላይ ነው? ኢየሱስ የሰጠው የናሙና ጸሎት እንደሚያሳየው እነዚህ ጉዳዮች የጸሎታችን ዓቢይ ክፍል መሆን ይገባቸዋል፤ ኢየሱስ የናሙና ጸሎቱን የጀመረው እንዲህ በማለት ነበር:- “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።”—ማቴ. 6:9, 10

13, 14. የምናቀርባቸው ጸሎቶች ስለ እኛ ምን ያሳያሉ?

13 ለአምላክ የምናቀርባቸው ጸሎቶች ውስጣዊ ዝንባሌያችን፣ ፍላጎታችንና ምኞታችን ምን እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ። ይሖዋ ውስጣዊ ማንነታችንን ያውቃል። ምሳሌ 17:3 እንዲህ ይላል:- “ማቅለጫ ለብር፣ ከውር ለወርቅ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይመረምራል።” አምላክ በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ይመለከታል። (1 ሳሙ. 16:7) ስለ ስብሰባዎቻችን፣ ስለ አገልግሎታችን እንዲሁም ስለ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምን እንደሚሰማን ያውቃል። ይሖዋ ለክርስቶስ ‘ወንድሞች’ ያለንን አመለካከት ጠንቅቆ ያውቃል። (ማቴ. 25:40) ስንጸልይ አንድን ነገር የምንጠይቀው ከልባችን እንደሆነ ወይም የተለመዱ ቃላትን በዘልማድ እየጠቀስን እንደሆነ ማወቅ ይችላል። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ስለ ጸሎት የተሳሳተ አመለካከት ስለነበራቸው እንዲህ ብሏል:- “በምትጸልዩበት ጊዜ አሕዛብ እንደሚያደርጉት አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ፤ እነሱ ቃላት በማብዛት ተሰሚነት የሚያገኙ ይመስላቸዋል።”—ማቴ. 6:7

14 የምናቀርባቸው ጸሎቶች በአምላክ ላይ ምን ያህል እንደምንታመንም ያሳያሉ። ዳዊት እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “አንተ [ይሖዋ] መጠጊያዬ፣ ከጠላትም የምተገንብህ ጽኑ ግንብ ሆነኸኛልና። በድንኳንህ ለዘላለም ልኑር፤ በክንፎችህም ጥላ ልከለል።” (መዝ. 61:3, 4) አምላክ ምሳሌያዊ በሆነ ሁኔታ ‘ድንኳኑን በላያችን ላይ ሲዘረጋ’ ጥበቃ እናገኛለን እንዲሁም የደኅንነት ስሜት ይኖረናል። (ራእይ 7:15) ማንኛውም የእምነት ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ ይሖዋ ‘ከእኛ ጋር’ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ በመተማመን በጸሎት ወደ እሱ መቅረብ እንዴት የሚያጽናና ነው!—መዝሙር 118:5-9ን አንብብ።

15, 16. የአገልግሎት መብቶችን ለማግኘት የምንመኝበት ዓላማ ምን እንደሆነ ለማስተዋል ጸሎት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

15 ውስጣዊ ዝንባሌያችንን አስመልክተን በሐቀኝነት ወደ ይሖዋ መጸለያችን እነዚህን ዝንባሌዎች በተመለከተ እውነታውን እንድናስተውል ሊረዳን ይችላል። ለአብነት ያህል፣ በአምላክ ሕዝቦች መካከል በኃላፊነት ቦታ ላይ ለማገልገል የምንጓጓው ትሑት በመሆን እርዳታ ለማበርከትና ከስብከቱ ሥራም ሆነ ከጉባኤ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ከልብ ስለምንፈልግ ነው? ወይስ “የመሪነት ቦታ” ለመያዝ አሊያም በሌሎች ላይ ‘ሥልጣናችንን ለማሳየት’ ስለምንፈልግ ነው? በይሖዋ ሕዝቦች መካከል እንዲህ ያለ ዝንባሌ መታየት የለበትም። (3 ዮሐንስ 9, 10ን እና ሉቃስ 22:24-27ን አንብብ።) የተሳሳቱ ምኞቶች ካሉን በሐቀኝነት ወደ ይሖዋ አምላክ መጸለያችን እነዚህን ምኞቶች ለማወቅ የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ በውስጣችን ሥር ከመስደዳቸው በፊት ለውጥ ለማድረግ ይረዳናል።

16 ክርስቲያን ሚስቶች፣ ባሎቻቸው የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሆኑ ውሎ አድሮ ደግሞ የበላይ ተመልካቾች ወይም ሽማግሌዎች ሆነው እንዲያገለግሉ ይጓጉ እንዲያውም ይህን ስሜታቸውን በግላቸው በሚያቀርቡት ጸሎት ይገልጹ ይሆናል። እነዚህ እህቶች በአኗኗራቸው ለሌሎች አርዓያ ለመሆን ጥረት በማድረግ ከጸሎታቸው ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ ይችላሉ። ደግሞም እንዲህ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም የአንድ ወንድም ቤተሰብ በንግግራቸውም ሆነ በአኗኗራቸው የሚተዉት ምሳሌ ጉባኤው ለእሱ በሚኖረው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። 

ሌሎችን ወክሎ በሕዝብ ፊት መጸለይ

17. በግላችን በምንጸልይበት ጊዜ ለብቻችን መሆናችን ተመራጭ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

17 ኢየሱስ በግሉ ለአባቱ ለመጸለይ ሲል ከሕዝቡ ተለይቶ ገለል ወዳለ ስፍራ የመሄድ ልማድ ነበረው። (ማቴ. 14:13፤ ሉቃስ 5:16፤ 6:12) እኛም ለብቻችን ሆነን መጸለይ ያስፈልገናል። ሰላማዊ በሆነ አካባቢ በተረጋጋ ሁኔታ የምናቀርበው ጸሎት ይሖዋን የሚያስደስቱና መንፈሳዊነታችን ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል የሚረዱን ውሳኔዎች ለማድረግ ሊረዳን ይችላል። ኢየሱስ በሕዝብ ፊትም የጸለየባቸው ወቅቶች አሉ፤ በመሆኑም ይህንን በተገቢው መንገድ ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ መመርመራችን ጥሩ ነው።

18. ወንድሞች ጉባኤውን ወክለው በሕዝብ ፊት በሚጸልዩበት ወቅት በአእምሯቸው ሊይዟቸው የሚገቡ አንዳንድ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

18 ስብሰባ በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ ታማኝ የሆኑ ወንድሞች ጉባኤውን ወክለው በሕዝብ ፊት ይጸልያሉ። (1 ጢሞ. 2:8) በዚህ ጊዜ የእምነት ባልንጀሮቻቸው በጸሎቱ መጨረሻ ላይ “አሜን” (“ይሁን” የሚል ትርጉም አለው) ማለት መቻል ይኖርባቸዋል። ይህን ለማድረግ ግን በጸሎቱ መስማማት አለባቸው። ኢየሱስ በሰጠው የናሙና ጸሎት ውስጥ መጥፎ ስሜት የሚያሳድር ወይም ቅር የሚያሰኝ ምንም ነገር አልነበረም። (ሉቃስ 11:2-4) ከዚህም በላይ ኢየሱስ በዚያ የነበረው እያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ወይም የገጠመውን ችግር በዝርዝር አልጠቀሰም። ስለ ግል ጉዳዮች መጸለይ ያለብን በግላችን እንጂ በሕዝብ ፊት መሆን የለበትም። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎችን ወክለን ስንጸልይ በሚስጥር መያዝ ያለባቸውን ጉዳዮች ከመጥቀስ መቆጠብ አለብን።

19. በሕዝብ ፊት ጸሎት በሚቀርብበት ወቅት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19 ሌሎች እኛን ወክለው በሚጸልዩበት ጊዜ ‘አምላክን እንደምንፈራ’ ማሳየት ይጠበቅብናል። (1 ጴጥ. 2:17) አንዳንድ ድርጊቶች ተገቢ የሚሆኑበት ጊዜና ቦታ ሊኖር ቢችልም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ግን ተገቢ ላይሆኑ ይችላሉ። (መክ. 3:1) ለምሳሌ ያህል፣ በሕዝብ ፊት ጸሎት በሚቀርብበት ጊዜ አንድ ሰው የተሰበሰቡት በሙሉ እጅ ለእጅ እንዲያያዙ ቢፈልግ እንዲህ ማድረግ እምነታችንን የማይጋሩ እንግዶችን ጨምሮ አንዳንዶችን ቅር ሊያሰኛቸው ወይም ትኩረታቸውን ሊሰርቀው ይችላል። አንዳንድ የትዳር ጓደኛሞች ትኩረት በማይስብ መልኩ እጅ ለእጅ ይያያዙ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በሕዝብ ፊት ጸሎት በሚቀርብበት ወቅት ቢተቃቀፉ እንዲህ ሲያደርጉ የሚያዩአቸው ሰዎች ሊሰናከሉ ይችላሉ። የሚያዩአቸው ሰዎች፣ እነዚህ ባልና ሚስት ለይሖዋ ጥልቅ አክብሮት እንዳላቸው ከማሳየት ይልቅ ትኩረት ያደረጉት የፍቅር ስሜታቸውን በመግለጽ ላይ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። እንግዲያው ለይሖዋ ያለን ጥልቅ አክብሮት “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር” እንድናደርግ እንዲሁም ሌሎች መጥፎ ስሜት እንዲያድርባቸው ወይም እንዲሰናከሉ አሊያም ትኩረታቸው እንዲሰረቅ የሚያደርግ ነገር ከመፈጸም እንድንቆጠብ ሊያነሳሳን ይገባል።—1 ቆሮ. 10:31, 32፤ 2 ቆሮ. 6:3

ስለምን ጉዳይ መጸለይ እንችላለን?

20. ሮም 8:26, 27 ምን ትርጉም እንዳለው አብራራ።

20 በግላችን በምንጸልይበት ወቅት ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን ሊጠፋን ይችላል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ችግሩ መጸለይ በሚያስፈልገን ጊዜ ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን አለማወቃችን ነው፤ ሆኖም በቃላት መግለጽ ተስኖን በምንቃትትበት ጊዜ መንፈስ [ቅዱስ] ራሱ ስለ እኛ ይማልዳል። ይሁንና ልብን የሚመረምረው አምላክ የመንፈስን ትርጉም ያውቃል።” (ሮም 8:26, 27) ይሖዋ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በርካታ ጸሎቶች እንዲካተቱ አድርጓል። በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን እነዚህን ልመናዎች እኛ እንዳቀረብነው ጸሎት አድርጎ በመቀበል ምላሽ ይሰጠናል። አምላክ ምን እንደምንፈልግ ያውቃል፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በመንፈሱ እየተመሩ የጻፉት ሐሳብ ምን ትርጉም እንዳለው ያውቃል። መንፈሱ ስለ እኛ “በሚማልድበት” ወይም እኛን ወክሎ በሚለምንበት ጊዜ ይሖዋ ልመናችንን ይሰማል። ሆኖም የአምላክን ቃል ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ ልንጸልይበት የሚገባው ጉዳይ በቀላሉ ወደ አእምሯችን ሊመጣ ይችላል።

21. በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ምን ነገር እንመረምራለን?

21 እስካሁን እንደተመለከትነው ጸሎቶቻችን ስለ እኛ ብዙ ይገልጻሉ። ለምሳሌ ጸሎታችን ወደ ይሖዋ ምን ያህል እንደቀረብን እንዲሁም ቃሉን ምን ያህል እንደምናውቀው ያሳያል። (ያዕ. 4:8) በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ አንዳንድ ጸሎቶችንና የጸሎት ይዘት ያላቸው ሐሳቦችን እንመረምራለን። በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ እንዲህ ያለ ምርምር ማድረጋችን ለአምላክ በምናቀርበው ጸሎት ረገድ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይችላል?

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል?

• ስለ እምነት ባልንጀሮቻችን መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

• የምናቀርባቸው ጸሎቶች ስለ እኛም ሆነ ስለ ውስጣዊ ዝንባሌዎቻችን ምን ያሳያሉ?

• በሕዝብ ፊት ጸሎት በሚቀርብበት ወቅት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋን አዘውትረህ የማወደስና የማመስገን ልማድ አለህ?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሕዝብ ፊት ጸሎት በሚቀርብበት ወቅት ምግባራችን ምንጊዜም ይሖዋን የሚያስከብር መሆን ይኖርበታል