በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መልካም ምግባር እናሳይ

የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መልካም ምግባር እናሳይ

የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መልካም ምግባር እናሳይ

“አምላክን የምትኮርጁ ሁኑ።”—ኤፌ. 5:1

1, 2. (ሀ) መልካም ምግባር ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነጥቦች እንመለከታለን?

ጥሩ ምግባርን በተመለከተ ሱ ፎክስ የተባሉ አንዲት ደራሲ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “መልካም ምግባር ከማሳየት እረፍት መውጣት የሚባል ነገር የለም። በየትኛውም ቦታና በማንኛውም ጊዜ ትሕትና ማሳየት አስፈላጊ ነው።” ሰዎች ትሕትና የማሳየት ልማድ ካዳበሩ ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚፈጠሩት ችግሮች ይቀንሳሉ፤ ብዙውን ጊዜም እስከ ጭራሹ ይወገዳሉ። ሰዎች ትሕትና የማያሳዩ ከሆነ ደግሞ ውጤቱ የተገላቢጦሽ ይሆናል። ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት አክብሮት የጎደለው ከሆነ ግጭት፣ ቅሬታና ሐዘን ይከተላል።

2 በጥቅሉ ሲታይ በእውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉት ሰዎች መልካም ምግባር ያሳያሉ። ያም ቢሆን በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘው መጥፎ ምግባር እንዳይጋባብን ልንጠነቀቅ ይገባል። መልካም ምግባር በማሳየት ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን በዓለም ላይ የሚታየው መጥፎ ምግባር እንዳይጋባብን ሊረዳን እንዲሁም ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲሳቡ ሊያደርግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። መልካም ምግባር ማሳየት የትኞቹን ነገሮች እንደሚጨምር ለመገንዘብ እንድንችል የይሖዋ አምላክንና የልጁን ምሳሌ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋና ልጁ—የመልካም ምግባር ምሳሌ

3. ጥሩ ምግባር በማሳየት ረገድ ይሖዋ አምላክ ምን ምሳሌ ትቷል?

3 ጥሩ ምግባር በማሳየት ረገድ ይሖዋ አምላክ ፍጹም ምሳሌ ይሆነናል። ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ በመሆኑ ከፍተኛ ሥልጣን ቢኖረውም ሰዎችን በታላቅ ደግነትና በአክብሮት ይይዛቸዋል። ይሖዋ አብርሃምንም ሆነ ሙሴን ሲያነጋግራቸው በአንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ “እባክህ” ተብሎ የተተረጎመውን የዕብራይስጥ ቃል ተጠቅሟል። (ዘፍ. 13:14፤ ዘፀ. 4:6) አገልጋዮቹ በሚሳሳቱበት ጊዜ ይሖዋ ‘መሓሪና ርኀሩኀ፣ ለቍጣ የዘገየ እንዲሁም ምሕረቱና ታማኝነቱ የበዛ አምላክ’ መሆኑን አሳይቷል። (መዝ. 86:15) አንዳንዶች፣ ሌሎች እነሱ እንደሚፈልጉት ሳይሆኑላቸው ሲቀሩ በቁጣ ይገነፍላሉ፤ ይሖዋ ግን እንዲህ ካሉ ሰዎች ፈጽሞ የተለየ አምላክ ነው።

4. ሌሎች በሚያነጋግሩን ጊዜ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

4 አምላክ ሰዎችን ካዳመጠበት መንገድም ጥሩ ምግባር ማሳየትን በተመለከተ ከእሱ መማር እንችላለን። አብርሃም የሰዶምን ሰዎች አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲያነሳ ይሖዋ እያንዳንዱን ጥያቄ በትዕግሥት መልሶለታል። (ዘፍ. 18:23-32) ይሖዋ፣ አብርሃም ለሰዶም ሰዎች በማሰብ ላነሳቸው ጥያቄዎች መልስ መስጠት ጊዜውን እንደሚያባክንበት ሆኖ አልተሰማውም። ይሖዋ የአገልጋዮቹን ጸሎት እንዲሁም ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች የሚያሰሙትን ጩኸት ይሰማል። (መዝሙር 51:11, 17ን አንብብ።) እኛም ሌሎች ሲያነጋግሩን በማዳመጥ ይሖዋን መምሰል አይገባንም?

5. ጥሩ ምግባር በማሳየት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያሻሽለው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባቱ ከተማራቸው በርካታ ነገሮች መካከል አንዱ ጥሩ ምግባር ማሳየት ነው። አንዳንዴ አገልግሎቱ ብዙ ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅበት ቢሆንም ኢየሱስ ምንጊዜም ትዕግሥተኛና ደግ ነበር። ኢየሱስ የሥጋ ደዌ ሕመምተኞችን፣ በልመና ለመተዳደር የተገደዱ ዓይነ ስውራንን እንዲሁም እርዳታ የሚሹ ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁና ፈቃደኛ ነበር። እነዚህ ሰዎች ወደ እሱ የሚመጡት በቀጠሮ ባይሆንም ኢየሱስ በቸልታ አላለፋቸውም። አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራውን ነገር ትቶ የተቸገሩ ሰዎችን ይረዳ ነበር። ኢየሱስ በእሱ ላይ እምነት ለነበራቸው ሰዎች ጥልቅ አሳቢነት አሳይቷል። (ማር. 5:30-34፤ ሉቃስ 18:35-41) እኛም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ደግነት በማሳየትና ሌሎችን በመርዳት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። እንዲህ ያለውን ምግባር የምናሳይ ከሆነ ዘመዶቻችን፣ ጎረቤቶቻችንና ሌሎች ሰዎች ይህንን ማስተዋላቸው አይቀርም። ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ ምግባር ይሖዋን ያስከብራል፤ ለእኛም ደስታ ያመጣልናል።

6. ኢየሱስ ሰዎችን ሞቅ ባለና ወዳጃዊ በሆነ መንገድ በመያዝ ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?

6 ኢየሱስ ሰዎችን በስማቸው በመጥራት ለእነሱ አክብሮት እንዳለው አሳይቷል። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችስ በዚህ መንገድ ሌሎችን ያከብሩ ነበር? በፍጹም። ሕጉን የማያውቀውን ኅብረተሰብ ‘የተረገመ ሕዝብ’ በማለት ይጠሩት ነበር፤ የሃይማኖት መሪዎቹ ሕዝቡን የሚይዙበት መንገድም እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ያሳይ ነበር። (ዮሐ. 7:49) የአምላክ ልጅ ግን እንዲህ አላደረገም። ማርታን፣ ማርያምን፣ ዘኬዎስን እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሰዎችን በስማቸው ጠርቷቸዋል። (ሉቃስ 10:41, 42፤ 19:5) በዛሬው ጊዜ ሰዎችን የምንጠራበት መንገድ የሚወሰነው እንደየባሕሉና እንደየሁኔታው ሊሆን ቢችልም የይሖዋ አገልጋዮች ሌሎችን ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ለመጥራት ጥረት ያደርጋሉ። * የመደብ ልዩነት ለእምነት ባልንጀሮቻቸውም ሆነ ለሌሎች ተገቢውን አክብሮት እንዳያሳዩ አያግዳቸውም።—ያዕቆብ 2:1-4ን አንብብ።

7. በየትኛውም ቦታ ለሚኖሩ ሰዎች አክብሮት በማሳየት ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚረዱን እንዴት ነው?

7 አምላክና ልጁ ከሁሉም ብሔራትና ዘሮች የተውጣጡ ሰዎችን ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ መያዛቸው ሰዎቹን እንደሚያከብሯቸው የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ወደ እውነት እንዲመጡ ያደርጋቸዋል። በእርግጥ ጥሩ ምግባር እንደሆነ ተደርጎ የሚታየው ነገር ከቦታ ወደ ቦታ ይለያያል። በመሆኑም መልካም ምግባር በማሳየት ረገድ ግትር የሆነ አቋም አንይዝም። ከዚህ ይልቅ በየትኛውም ቦታ ለሚኖሩ ሰዎች አክብሮት በማሳየት ረገድ ሚዛኑን የጠበቀ አመለካከት እንድንይዝ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት አለብን። ሰዎችን በአክብሮት መያዝ በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ሰዎችን ሰላም ማለት እንዲሁም ማነጋገር

8, 9. (ሀ) የትኛው ልማድ አክብሮት እንደጎደለው ምግባር ሊታይ ይችላል? (ለ) በ⁠ማቴዎስ 5:47 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ለውጥ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል የምንለው ለምንድን ነው?

8 በዛሬው ጊዜ በብዙ ቦታዎች የሰዎች ሕይወት ሩጫ የሞላበት በመሆኑ ሰዎች መንገድ ላይ ሲገናኙ “ጤና ይስጥልኝ” ወይም “እንደምን ነህ?” ሳይባባሉ መተላለፋቸው እየተለመደ መጥቷል። እርግጥ ነው፣ ማንም ሰው ሕዝብ በበዛበት መንገድ ላይ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ እንዲያነጋግር አይጠበቅበትም። ይሁንና በሌሎች በርካታ አጋጣሚዎች ሰዎችን ሰላም ማለት ተገቢ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ልማድ ነው። ሰዎችን ሰላም የማለት ልማድ አለህ? ወይስ አብዛኛውን ጊዜ መንገድ ላይ የምታገኛቸውን ሰዎች ፈገግ አሊያም ጎንበስ በማለት ወዳጃዊ ስሜት ሳታሳያቸው ወይም ሰላምታ ሳትሰጣቸው ዝም ብለህ ታልፋለህ? አንድ ሰው ሳይታወቀው አክብሮት የጎደለው ልማድ ሊያዳብር ይችላል።

9 ኢየሱስ “ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም ብትሉ ምን የተለየ ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም?” ብሏል። (ማቴ. 5:47) ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ዶናልድ ዌስ የተባሉት አማካሪ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሰዎች፣ ሌሎች ትኩረት ሳይሰጧቸው ሲቀሩ ወይም በቸልታ ሲያልፏቸው ቅር ይሰኛሉ። በመሠረቱ አንድን ሰው በቸልታ ለማለፍ ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም። መፍትሔው ቀላል ነው:- ሰዎችን ሰላም በሉ። እንዲሁም አነጋግሯቸው።” በተፈጥሯችን ከሰው ጋር መቀላቀል ወይም መቀራረብ የሚከብደን ሰዎች እንሆን ይሆናል፤ ይህ ባሕርይ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት እንዳያበላሽብን ጥረት ካደረግን ጥሩ ውጤት ማግኘት እንችላለን።

10. ጥሩ ምግባር ማሳየታችን በአገልግሎት ውጤታማ እንድንሆን ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? ( “ሞቅ ያለ ፈገግታ በማሳየት ውይይቱን ጀምር” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

10 በሰሜን አሜሪካ በሚገኝ አንድ ትልቅ ከተማ ውስጥ የሚኖሩት ቶም እና ካሮል የተባሉ ክርስቲያን ባልና ሚስት ምን እንደሚያደርጉ እንመልከት። ከጎረቤቶቻቸው ጋር አስደሳች ውይይት ማድረግ የአገልግሎታቸው ክፍል እንዲሆን አድርገዋል። ይህን ያደረጉት እንዴት ነው? ቶም ያዕቆብ 3:18⁠ን በመጥቀስ እንዲህ ይላል:- “ከሰዎች ጋር ወዳጃዊና ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ለማድረግ እንጥራለን። ከቤታቸው ውጭ ያሉ ወይም ለሥራ ወደ አካባቢያችን የመጡ ሰዎችን ስናይ ቀረብ ብለን በፈገግታ ሰላም እንላቸዋለን። ስለ ልጆቻቸው፣ ስለ ውሾቻቸው፣ ስለ ቤታቸው፣ ስለ ሥራቸውና ስለመሳሰሉት ትኩረታቸውን የሚስቡ ጉዳዮች አንስተን እናዋራቸዋለን። ውሎ አድሮ እኛን እንደ ጓደኞቻቸው ማየት ይጀምራሉ።” ካሮልም አክላ እንዲህ ብላለች:- “በሌላ ጊዜ ስናገኛቸው ደግሞ ስማችንን ካስተዋወቅን በኋላ የእነሱንም እንጠይቃቸዋለን። በአካባቢው ምን እያከናወንን እንዳለ እንነግራቸዋለን፤ ሆኖም ውይይቱ አጭር እንዲሆን እናደርጋለን። ከጊዜ በኋላ እንመሠክርላቸዋለን።” ቶምና ካሮል የአብዛኞቹን ጎረቤቶቻቸውን አመኔታ አትርፈዋል። በርካታ ጎረቤቶቻቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የወሰዱ ሲሆን ጥቂቶቹም እውነትን ለማወቅ ያላቸው ፍላጎት እያደገ መጥቷል።

አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ አክብሮት ማሳየት

11, 12. ምሥራቹን በምንሰብክበት ወቅት ሰዎች ጥሩ ያልሆነ ምላሽ ሊሰጡን እንደሚችሉ መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው? እኛስ ምን ልናደርግ ይገባል?

11 አንዳንድ ጊዜ ምሥራቹን ስንሰብክ ሰዎች መጥፎ ምላሽ ይሰጡናል። ይህም የምንጠብቀው ነገር ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ኢየሱስ “እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስቀድሞ አስጠንቅቋል። (ዮሐ. 15:20) ይሁን እንጂ ሰዎች የሚያንቋሽሽ ነገር ሲናገሩ ተመሳሳይ ምላሽ መስጠታችን ጥሩ ውጤት አያስገኝም። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁዎች በመሆን ክርስቶስን እንደ ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት፤ ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን።” (1 ጴጥ. 3:15) በገርነትና በአክብሮት ምላሽ በመስጠት መልካም ምግባር ማሳየታችን የሚሰድቡን ሰዎች ለመልእክታችን ጥሩ ምላሽ እንዲሰጡ ሊያደርጋቸው ይችላል።—ቲቶ 2:7, 8

12 ሰዎች ትችት በሚሰነዝሩብን ጊዜ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ምላሽ መስጠት እንድንችል አስቀድመን መዘጋጀት እንችላለን? አዎን። ጳውሎስ “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለውና በጨው የተቀመመ ይሁን” የሚል ምክር ሰጥቶናል። (ቆላ. 4:6) ለቤተሰቦቻችን አባላት እንዲሁም በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በጉባኤ ውስጥና በአካባቢያችን ለምናገኛቸው ሰዎች አክብሮት የማሳየት ልማድ ካዳበርን ፌዝና ስድብ ሲሰነዘርብን ከክርስቲያኖች በሚጠበቀው መንገድ ምላሽ መስጠት እንችላለን።—ሮም 12:17-21ን አንብብ።

13. ለተቃዋሚዎች አክብሮት ማሳየታችን ለመልእክታችን ጥሩ ምላሽ እንዲሰጡ ሊያደርጋቸው እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።

13 አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ መልካም ምግባር ማሳየት ጥሩ ውጤት ያስገኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ጃፓን ውስጥ አንድ የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል የቤቱ ባለቤትም ሆነ በእንግድነት የመጣው ሰው ተሳለቁበት። ወንድም ግን አክብሮት በተሞላበት መንገድ ተሰናብቷቸው ሄደ። በኋላ ላይ ወንድም በክልሉ ውስጥ እያገለገለ እያለ እንግዳው ሰው በቅርብ ርቀት እየተከተለው መሆኑን አስተዋለ። ወንድም ሰውየውን ለማነጋገር ሲቀርበው ሰውየው እንዲህ አለው:- “ስለተፈጠረው ነገር ይቅርታ። ደግነት የጎደለው ነገር ብንናገርህም አንተ ግን ፈገግታ አልተለየህም። እንደ አንተ ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ይህ ሰው ሥራውን ያጣ ከመሆኑም ሌላ በቅርቡ እናቱ ስለሞተችበት ፈጽሞ ደስተኛ መሆን እንደማይችል ተሰምቶት ነበር። ወንድም፣ ሰውየው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ግብዣ ያቀረበለት ሲሆን እሱም ለማጥናት ተስማማ። ብዙም ሳይቆይ በሳምንት ሁለት ጊዜ ማጥናት ጀመረ።

ትሕትና ለማዳበር የሚረዳው ከሁሉ የተሻለ መንገድ

14, 15. በጥንት ዘመናት የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮች ልጆቻቸውን ምን እንዲያደርጉ አሠልጥነዋቸው ነበር?

14 በጥንት ዘመናት የኖሩ አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው ወላጆች፣ አክብሮት ከማሳየት ጋር በተያያዘ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ለልጆቻቸው በቤት ውስጥ ያስተምሯቸው ነበር። በዘፍጥረት 22:7 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው አብርሃምና ልጁ ይስሐቅ እርስ በርስ የተነጋገሩት አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንደሆነ ልብ በል። ዮሴፍም ከወላጆቹ ጥሩ ሥልጠና እንዳገኘ በግልጽ መመልከት ይቻላል። እስር ቤት በነበረበት ወቅት አብረውት የታሰሩትን ሰዎችም እንኳ ያነጋገራቸው በትሕትና ነበር። (ዘፍ. 40:8, 14) ፈርዖንን ያነጋገረበት መንገድም ሥልጣን ያለውን ሰው እንዴት ማነጋገር እንደሚገባው እንደተማረ ያሳያል።—ዘፍ. 41:16, 33, 34

15 ለእስራኤላውያን ከተሰጡት አሥር ትእዛዛት አንዱ “አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም” ይላል። (ዘፀ. 20:12) ልጆች፣ ወላጆቻቸውን እንደሚያከብሩ ከሚያሳዩባቸው መንገዶች አንዱ በቤት ውስጥ ጥሩ ምግባር ማንጸባረቅ ነበር። የዮፍታሔ ሴት ልጅ፣ አባቷ የገባውን ቃል እንዲፈጽም በመተባበር እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥም ለአባቷ ልዩ አክብሮት እንዳላት አሳይታለች።—መሳ. 11:35-40

16-18. (ሀ) ልጆች መልካም ምግባር እንዲኖራቸው ለማስተማር ምን ማድረግ ይቻላል? (ለ) ልጆች መልካም ምግባር እንዲኖራቸው ማስተማር ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

16 ልጆቻችን ጥሩ ምግባር እንዲኖራቸው ማሠልጠን በጣም አስፈላጊ ነው። ልጆቻችን፣ አዋቂ ሲሆኑ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው ከፈለግን እንግዶችን ሰላም ሲሉ፣ ስልክ ሲያናግሩና ከሌሎች ጋር ሲመገቡ ሊኖራቸው የሚገባውን ሥርዓት ልናስተምራቸው ይገባል። ለሌሎች ሰዎች በር ከፍቶ ማሳለፍ፣ ለትልቅ ሰው ወንበራቸውን መልቀቅ፣ ለአረጋውያንና ለታመሙ ሰዎች ደግነት ማሳየት እንዲሁም ከባድ ዕቃ የተሸከሙ ሰዎችን ማገዝ ያለባቸው ለምን እንደሆነ እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ከልብ በመነጨ መንገድ “እባክዎ፣” “አመሰግናለሁ፣” “ይቅርታ፣” “ላግዝዎት?” ወይም “የምረዳዎት ነገር አለ?” ማለት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ሊረዱ ይገባል።

17 ልጆች ትሕትናን እንዲያዳብሩ መርዳት ከባድ ሊሆን አይገባም። ይህን ማድረግ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን ነው። የሃያ አምስት ዓመቱ ከርት እሱና ሦስት ወንድሞቹ ትሕትና ማሳየትን እንዴት እንደተማሩ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እማማና አባባ እርስ በርስ በደግነት ሲያወሩ እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን ትዕግሥትና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ሲያነጋግሩ እንመለከትና እንሰማ ነበር። በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ አባባ ከስብሰባው በፊትና በኋላ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶችን ለማነጋገር ሲሄድ አብሬው እንድሆን ያደርግ ነበር። እንዴት ሰላም እንደሚላቸው አዳምጥ እንዲሁም ለእነሱ ያለውን አክብሮት እመለከት ነበር።” ከርት አክሎም እንዲህ ብሏል:- “እያደር የእሱ ዓይነት ምግባር አዳበርኩ። ሰዎችን በደግነት መያዝ ቀላል ሆነልኝ። ይህንን የማደርገው ስለሚጠበቅብኝ ሳይሆን ስለምፈልገው ነው።”

18 ወላጆች መልካም ምግባር እንዲኖራቸው ልጆቻቸውን ማስተማራቸው ምን ውጤት ያስገኛል? ልጆቹ፣ ወዳጆች ማፍራት እንዲሁም ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር ይችላሉ። ከአሠሪዎቻቸውም ሆነ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ተግባብተው መሥራት የሚችሉ ይሆናሉ። ከዚህም በላይ ትሑት፣ ሥርዓታማና ጨዋ የሆኑ ልጆች ለወላጆቻቸው ደስታና እርካታ ያመጣሉ።—ምሳሌ 23:24, 25ን አንብብ።

መልካም ምግባር ከዓለም የተለየን ያደርገናል

19, 20. ለሰዎች አክብሮት የሚያሳየውን የአምላካችንንና የልጁን ምሳሌ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

19 ጳውሎስ “የተወደዳችሁ ልጆች በመሆን አምላክን የምትኮርጁ ሁኑ” በማለት ጽፏል። (ኤፌ. 5:1) ይሖዋ አምላክንና ልጁን መምሰል በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደተመለከትናቸው ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግን ይጨምራል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ከፍተኛ ቦታ ባላቸው ሰዎች ዘንድ ለመወደድ አሊያም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ስንል ከልብ ያልሆነ አክብሮት ከማሳየት እንቆጠባለን።—ይሁዳ 16

20 ሰይጣን ክፉ የሆነው አገዛዙ ሊያበቃ በተቃረበበት በዚህ የመጨረሻ ዘመን፣ ይሖዋ የሰጠንን የመልካም ምግባር መሥፈርቶች ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል። ሆኖም ዲያብሎስ የእውነተኛ ክርስቲያኖችን መልካም ምግባር ጨርሶ ለማጥፋት የሚያደርገው ሙከራ አይሳካም። ሁላችንም ለሰዎች አክብሮት የሚያሳየውን የአምላካችንንና የልጁን ምሳሌ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ንግግራችንም ሆነ ምግባራችን መልካም ምግባር ከሌላቸው ሰዎች ምንጊዜም የተለየ ይሆናል። መልካም ምግባር በማሳየት ረገድ ፍጹም ምሳሌ ለሆነው ለአምላካችን ለይሖዋ ስም ውዳሴ እናመጣለን፤ እንዲሁም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲሳቡ እናደርጋለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 በአንዳንድ ባሕሎች፣ በዕድሜ የሚበልጠንን ግለሰብ በምናነጋግርበት ወቅት ከስሙ በፊት የአክብሮት መጠሪያ ሳናስገባ ስሙን መጥራት (በስሙ ብቻ እንድንጠራው እሱ ራሱ ካልነገረን በቀር) አክብሮት የጎደለው ድርጊት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ክርስቲያኖች እንደነዚህ ያሉ ባሕሎችን ማክበራቸው ተገቢ ነው።

ታስታውሳለህ?

• መልካም ምግባር ማሳየትን በተመለከተ ከይሖዋና ከልጁ ምን እንማራለን?

• ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለሰዎች ሞቅ ያለ ሰላምታ መስጠታችን ስለ እኛ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያደርገው እንዴት ነው?

• ጥሩ ምግባር ማሳየታችን በአገልግሎት ውጤታማ እንድንሆን ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

• ወላጆች፣ ልጆቻቸው መልካም ምግባር እንዲኖራቸው በማሠልጠን ረገድ ምን ድርሻ አላቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 ሞቅ ያለ ፈገግታ በማሳየት ውይይቱን ጀምር

ብዙ ሰዎች ከማያውቁት ሰው ጋር ውይይት መጀመር ይከብዳቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ግን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ለማካፈል ሲሉ ከሰዎች ጋር እንዴት ውይይት መጀመር እንደሚችሉ ለመማር ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር ስላላቸው ነው። አንተስ በዚህ ረገድ ችሎታህን ለማሻሻል ምን ሊረዳህ ይችላል?

በ⁠ፊልጵስዩስ 2:4 ላይ “ስለ ራሳችሁ ጉዳይ ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ጉዳይም ትኩረት ስጡ” የሚል ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓት እናገኛለን። እስቲ ይህንን ጥቅስ በዚህ መልክ ለማሰብ ሞክር:- አንድ ሰው ከአሁን ቀደም አይቶህ የማያውቅ ከሆነ እንግዳ ትሆንበታለህ። ታዲያ እንዲረጋጋ ልታደርገው የምትችለው እንዴት ነው? ሞቅ ያለ ፈገግታ በማሳየት ወዳጃዊ ስሜት በሚንጸባረቅበት መንገድ ሰላም ብትለው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሌላም ልታደርገው የሚገባ ነገር አለ።

ከአንድ ሰው ጋር ውይይት ለመጀመር ስትሞክር የሚያስበውን ነገር አቋርጠህበት ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ በአእምሮው እያውጠነጠነ ያለውን ነገር ግምት ውስጥ ሳታስገባ አንተ ስላሰብከው ነገር ልታወያየው ብትሞክር ጥሩ ምላሽ ላይሰጥህ ይችላል። ስለዚህ ሰውየው ስለምን ነገር እያሰበ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ጥረት አድርግ፤ ከዚያም ያንን መሠረት በማድረግ ውይይቱን መጀመር ትችላለህ። ኢየሱስ በሰማርያ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ካገኛት ሴት ጋር ውይይት የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር። (ዮሐ. 4:7-26) ሴትየዋ ውኃ ስለመቅዳት እያሰበች ነበር። ኢየሱስ ይህንን መሠረት በማድረግ ከእሷ ጋር መነጋገር ጀመረ፤ ብዙም ሳይቆይ የውይይቱን አቅጣጫ በመቀየር አስደሳች መንፈሳዊ ጭውውት ማድረግ ችሏል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሰዎች ወዳጃዊ መንፈስ ማሳየታችን ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ሊረዳን ይችላል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መልካም ምግባር ማሳየት ምንጊዜም አስፈላጊ ነው