በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ትልቋ ቀይ ደሴት ደረሰ

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ትልቋ ቀይ ደሴት ደረሰ

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ትልቋ ቀይ ደሴት ደረሰ

ከአፍሪካ በስተ ደቡብ ምሥራቅ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ማዳጋስካር በምድር ላይ ካሉት ደሴቶች መካከል በትልቅነቷ በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከ170 ዓመት በፊት የተተረጎመው የማለጋሲ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም ስለነበረበት ይህ ስም ለማለጋሲ ሕዝብ አዲስ አይደለም። ይህን የማለጋሲ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማዘጋጀት የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ጽናትና መሥዋዕትነት ጠይቆ ስለነበር ትልቅ ታሪክ ይወጣዋል።

መጽሐፍ ቅዱስን በማለጋሲ ቋንቋ ለመተርጎም ጥረት ማድረግ የተጀመረው በማዳጋስካር አቅራቢያ በምትገኘው በሞሪሽየስ ደሴት ነበር። በ1813 መጀመሪያ አካባቢ የሞሪሽየስ ገዥ የነበረው ብሪታንያዊው ሰር ሮበርት ፋርክወር ወንጌሎችን ወደ ማለጋሲ ቋንቋ የመተርጎም ሥራ አስጀምሮ ነበር። ይህ ገዥ ከጊዜ በኋላ አስተማሪዎችን ከለንደን ሚስዮናውያን ማኅበር ወደ ማዳጋስካር እንዲያስመጣ የማዳጋስካርን ንጉሥ ቀዳማዊ ራደማንን አበረታታው፤ ማዳጋስካር ብዙውን ጊዜ ትልቋ ቀይ ደሴት ተብላ ትጠራለች።

ነሐሴ 18, 1818 ዴቪድ ጆንስ እና ቶማስ ቤቨን የተባሉ ሁለት የዌልስ ሚስዮናውያን ከሞሪሽየስ ተነስተው ቶኦማሲና ወደምትባለው የወደብ ከተማ ደረሱ። እነዚህ ሚስዮናውያን የአካባቢው ሰዎች ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ እንዳላቸው ተረዱ፤ እንዲያውም ሕዝቡ በቀድሞ አባቶች አምልኮና በወግ የታሰረ ነበር። የማለጋሲ ሕዝብ በዋነኝነት የማሊዮ-ፖሊኔዥያ ሥረ መሠረት ያለውና ውብ በሆኑ ቃላት የበለጸገ ገላጭ ቋንቋ ይናገራል።

ጆንስ እና ቤቨን አንድ አነስተኛ ትምህርት ቤት ከከፈቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ከሞሪሽየስ ወደ ቶኦማሲና አመጧቸው። የሚያሳዝነው ግን ሁሉም በወባ በሽታ ስለተያዙ ታኅሣሥ 1818 ጆንስ ባለቤቱንና ልጁን በሞት አጣ። ከሁለት ወር በኋላ ደግሞ መላው የቤቨን ቤተሰብ በበሽታው አለቀ። ከእነሱ መካከል የተረፈው ዴቪድ ጆንስ ብቻ ነበር።

ጆንስ እንዲህ ያለው መከራ አልበገረውም። የማዳጋስካር ሕዝብ የአምላክን ቃል በገዛ ቋንቋው እንዲያገኝ ለማድረግ ቆርጦ ነበር። ከበሽታው እስኪያገግም ድረስ ለተወሰነ ጊዜ በሞሪሽየስ ከቆየ በኋላ ጆንስ የማለጋሲን ቋንቋ መማር ጀመረ፤ ቋንቋውን መማር አስቸጋሪ ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የዮሐንስን ወንጌል ለመተርጎም ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ጀመረ።

ጆንስ ጥቅምት 1820 ወደ ማዳጋስካር ተመለሰ። በዋና ከተማዋ በአንታናናሪቮ ከደረሰ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አዲስ ትምህርት ቤት ከፈተ። እርግጥ ሁኔታዎቹ አስቸጋሪ ነበሩ። መማሪያ መጻሕፍት፣ ጥቁር ሠሌዳ ወይም ተማሪዎቹ የሚቀመጡበት ዴስክ አልነበረም። ይሁንና ሥርዓተ ትምህርቱ በጣም ጥሩ ነበር፤ ልጆቹም ከፍተኛ የመማር ጉጉት ነበራቸው።

ጆንስ ሰባት ወር ለሚያህል ጊዜ ብቻውን ከሠራ በኋላ ቤቨንን የሚተካ ዴቪድ ግሪፈትስ የተባለ ሚስዮናዊ ተላከለት። ደከመኝ ሰለቸኝ የማያውቁት እነዚህ ሁለት ሚስዮናውያን መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ማለጋሲ ለመተርጎሙ ሥራ ሁለመናቸውን ሰጡ።

የትርጉም ሥራው ተጀመረ

በ1820ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የማለጋሲን ቋንቋ በጽሑፍ ለማስፈር ጥቅም ላይ ይውል የነበረው የአረብኛ ፊደል ሲሆን ይህም ሶራቤ ተብሎ ይጠራ ነበር። ይሁንና በዚህ መንገድ የተጻፉ ጽሑፎችን ማንበብ የሚችሉት በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ። በመሆኑም ሚስዮናውያኑ ቀዳማዊ ራደማንን ካማከሩ በኋላ ንጉሡ በሶራቤ ምትክ የላቲን ፊደላትን እንዲጠቀሙ ፈቀደላቸው።

የትርጉም ሥራው መስከረም 10, 1823 ተጀመረ። ጆንስ ዘፍጥረትንና ማቴዎስን ሲተረጉም ግሪፈትስ ደግሞ ዘፀአትንና ሉቃስን ይተረጉማል። የሚገርመው እነዚህ ሁለት ሰዎች ድካም የሚባል ነገር አያውቃቸውም። አብዛኛውን የትርጉም ሥራ እነሱ ራሳቸው ያከናውኑ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጠዋትና ከሰዓት በኋላ ያስተምሩ ነበር። በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያን እንዲያገለግሉ ስለሚጠበቅባቸው በሦስት ቋንቋዎች ተዘጋጅተው ትምህርቱን ያቀርቡ ነበር። ያም ሆኖ ከምንም በላይ ትኩረት የሚሰጡት ለትርጉም ሥራቸው ነበር።

እነዚህ ሁለት ሚስዮናውያን በ12 ተማሪዎች እየታገዙ ሙሉውን የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትንና በርካታ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ከ18 ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተርጉመው ጨረሱ። በቀጣዩ ዓመት ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ የመተርጎሙ የመጀመሪያ ሥራ ተጠናቀቀ። እርግጥ ነው፣ ትርጉሙን የማረምና የማጣራት ሥራ ይቀረው ነበር። በመሆኑም ለዚህ ሥራ እገዛ ለማድረግ ዴቪድ ጆንስ እና ጆሴፍ ፍሪመን የተባሉ ሁለት የቋንቋ ምሑራን ከእንግሊዝ መጡ።

ማቆሚያ የሌላቸው መሰናክሎች

በማለጋሲ ቋንቋ የተዘጋጀው ትርጉም ከተጠናቀቀ በኋላ የለንደን ሚስዮናውያን ማኅበር በማዳጋስካር የመጀመሪያ የሆነውን የማተሚያ ማሽን እንዲተክል ቻርለስ ሃቨንደንን ላከው። ሃቨንደን ኅዳር 21, 1826 ማዳጋስካር ደረሰ። ይሁን እንጂ ሃቨንደን አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በወባ በሽታ ምክንያት ስለሞተ የማተሚያ ማሽኑን የሚያንቀሳቅስ ሰው ጠፋ። በቀጣዩ ዓመት ጄምስ ካምረን የተባለ ከስኮትላንድ የመጣ የተዋጣለት የእጅ ባለሙያ በማሽኑ ውስጥ ባገኘው መመሪያ መጽሐፍ እየታገዘ ማተሚያ ማሽኑን ገጣጠመው። ከብዙ ሙከራ በኋላ ካምረን ታኅሣሥ 4, 1827 የ⁠ዘፍጥረት ምዕራፍ 1⁠ን የተወሰነ ክፍል ማተም ቻለ። *

ቀዳማዊ ራደማ ከሞተ በኋላ ሐምሌ 27, 1828 ሌላ መሰናክል ብቅ አለ። ንጉሥ ራደማ ለትርጉም ሥራው ከፍተኛ ድጋፍ ያደርግ ነበር። በወቅቱ ዴቪድ ጆንስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ንጉሥ ራደማ በጣም ደግና የሚቀረብ ሰው ነው። ለትምህርት መስፋፋት ተግቶ የሚሠራ ሲሆን ወርቅና ብር ከማካበት ይልቅ ሕዝቡ በሥልጣኔ ጎዳና ላይ ለመጓዝ የሚያስችለውን ትምህርት ሲቀስም የማየት ከፍተኛ ጉጉት አለው።” ይሁን እንጂ ንጉሡ ሲሞት ሚስቱ ቀዳማዊት ራናቨሎና ሥልጣን ያዘች፤ ብዙም ሳይቆይ ንግሥቲቱ የትርጉም ሥራውን የባልዋን ያህል እንደማትደግፍ በግልጽ መታየት ጀመረ።

ንግሥቲቱ ሥልጣን ከያዘች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከእንግሊዝ የመጣ አንድ ሰው ከንግሥቲቱ ጋር ስለ ትርጉም ሥራው ለመነጋገር ቀጠሮ እንዲያዝለት ጠየቀ። ይሁንና ጥያቄው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ሚስዮናውያኑ ግሪክኛንና ዕብራይስጥን ጨምሮ ለሕዝቡ ገና ብዙ የሚያስተምሩት ነገር እንዳለ ለንግሥቲቱ ሲነግሯት እንዲህ አለቻቸው፦ “ግሪክኛና ዕብራይስጥ መማር ምን ያደርግልናል? ይልቁንም ለሕዝቤ ሳሙናን እንደ መሥራት ያለ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነ ነገር ማስተማር ትችሉ እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ።” የማለጋሲ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከመጠናቀቁ በፊት ከአገሪቱ ሊባረሩ እንደሚችሉ ስለገባቸው ካምረን ንግሥቲቱ ባቀረበችው ሐሳብ ላይ ለማሰብ የአንድ ሳምንት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠየቀ።

በቀጣዩ ሳምንት ካምረን በአካባቢው ከተገኙ ነገሮች የሠሯቸውን ሁለት ሳሙናዎች ከቤተ መንግሥት ለመጡ የንግሥቲቱ መልእክተኞች አቀረበ። ሚስዮናውያኑ ለሕዝቡ ያከናወኑት ይህና ሌሎች ሥራዎች ንግሥቲቱን እንድትታገስ ስላደረገላቸው ከጥቂቶቹ በስተቀር ሁሉንም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት አትመው ማጠናቀቅ ችለዋል።

ያልተጠበቁ ውሳኔዎች

ንግሥቲቱ መጀመሪያ ላይ ለሚስዮናውያኑ ጥሩ ስሜት ባይኖራትም ግንቦት 1831 አንድ ያልተጠበቀ ድንጋጌ አወጣች፤ ድንጋጌው ዜጎቿ ክርስቲያን ሆነው እንዲጠመቁ የሚፈቅድ ነበር! ይሁንና ውሳኔው ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ማዳጋስካር የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ወግ አጥባቂ የሆኑ አንዳንድ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ብዙ ሰዎች መጠመቃቸው ስላሳሰባቸው ቁርባን ለብሪታንያ መንግሥት ታማኝ ለመሆን የሚፈጸም የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት እንደሆነ አድርገው በመንገር ንግሥቲቱን አሳመኗት።” በመሆኑም ሰዎች ክርስቲያን ሆነው እንዲጠመቁ ወጥቶ የነበረው ድንጋጌ ከስድስት ወር በኋላ ማለትም በ1831 መገባደጃ አካባቢ ተነሳ።

ንግሥቲቱ አንድ አቋም አለመያዟ እንዲሁም በመንግሥቱ ውስጥ የነበሩት ወግ አጥባቂ ኃይሎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እየጨመረ መምጣቱ ሚስዮናውያኑ መጽሐፍ ቅዱስ የማተሙን ሥራቸውን በአፋጣኝ እንዲያጠናቅቁ ገፋፋቸው። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቀድሞውኑም ቢሆን ተጠናቀው ስለነበር በሺህ የሚቆጠሩ ቅጂዎች እየተሠራጩ ነበር። ይሁን እንጂ መጋቢት 1, 1835 ቀዳማዊት ራናቨሎና ክርስትና በሕግ የታገደ መሆኑን የሚገልጽና ሰዎች ያሏቸውን የክርስትና መጻሕፍት በሙሉ ለባለሥልጣናት አሳልፈው እንዲሰጡ የሚያዝ ድንጋጌ ባወጣች ጊዜ ሌላ እንቅፋት አጋጠማቸው።

ንግሥቲቱ ያሳለፈችው ድንጋጌ ሚስዮናውያኑ ያሚያሠለጥኗቸው የማለጋሲ ዜጎች በሕትመት ሥራው ላይ እንዳይካፈሉም የሚያግድ ነበር። በመሆኑም በጣት የሚቆጠሩት ሚስዮናውያን ሥራውን ብቻቸውን መጨረስ ግድ ሆነባቸው፤ ሥራው ሌት ተቀን ከተሠራ በኋላ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ሰኔ 1835 ለስርጭት በቃ። አዎን፣ የማለጋሲ መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ መከራ በኋላ ተጠናቀቀ!

እገዳው ተጥሎ እያለ መጽሐፍ ቅዱስ በፍጥነት የተሰራጨ ሲሆን መጽሐፉን ከጥፋት ለመታደግ ሲባል 70 የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች እንዲቀበሩ ተደረጉ። እንዲህ መደረጉ በእርግጥም ተገቢ ነበር፤ ምክንያቱም ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሁለት ሚስዮናውያን በስተቀር ሌሎቹ አገሪቱን ለቀው ለመውጣት ተገደው ነበር። የአምላክ ቃል ግን በዚህች ትልቅ ቀይ ደሴት ውስጥ መሰራጨቱን ቀጥሏል።

የማለጋሲ ሕዝብ ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለው ፍቅር

የማዳጋስካር ሕዝብ የአምላክን ቃል በገዛ ቋንቋው የማንበብ አጋጣሚ ማግኘቱ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አንዳንድ ስህተቶች ያሉበት ከመሆኑም ሌላ ቋንቋው በብዙዎች ዘንድ ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ የሌለበት ቤት የለም ማለት ይቻላል፤ በመሆኑም በርካታ የማለጋሲ ዜጎች መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው ያነባሉ። ይህን ትርጉም ለየት የሚያደርገው ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም በመላው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሰፊው የሚጠቀምበት መሆኑ ነው። ይህ መለኮታዊ ስም በመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች ላይ በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥም ይገኛል። በመሆኑም አብዛኛው የማለጋሲ ሕዝብ የአምላክን ስም በሚገባ ያውቃል።

የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ለመጀመሪያ ጊዜ እየታተሙ ከማሽኑ ውስጥ ሲወጡ ሕትመቱን ያከናውን የነበረው ሚስተር ቤከር፣ የማለጋሲ ሕዝብ ምን ያህል እንደሚደሰት ታይቶት “ትንቢት መናገሬ እንኳ አይደለም፤ ነገር ግን የአምላክ ቃል ከዚህች አገር ጨርሶ ሊጠፋ ይችላል ብዬ አላምንም!” ሲል በአድናቆት ተናግሯል። የተናገረው ነገር እውነት መሆኑ ታይቷል። የወባ በሽታም ሆነ ለመማር የሚያስቸግረው ቋንቋ ወይም አንዲት ገዥ መጥፎ ድንጋጌ ማውጣቷ የአምላክ ቃል በማዳጋስካር እንዳይተረጎም ሊያግድ አልቻለም።

በአሁኑ ጊዜ ሁኔታዎች ይበልጥ ተሻሽለዋል። እንዴት? በ2008 ሙሉው የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በማለጋሲ ቋንቋ ወጥቷል። ይህ ትርጉም ዘመናዊ በሆነና በቀላሉ ሊገባ በሚችል ቋንቋ ስለተዘጋጀ የአምላክን ቃል ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ረገድ ትልቅ እመርታ አስገኝቷል። በመሆኑም የአምላክ ቃል በዚህች ትልቅ ቀይ ደሴት ላይ ፈጽሞ ሊነቀል የማይችል ሥር ሰዷል።—ኢሳ. 40:8

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 በማለጋሲ ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሥርቱ ትእዛዛትና የጌታ ጸሎት ናቸው፤ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የታተሙት በሞሪሽየስ ሲሆን ጊዜውም ሚያዝያ/ግንቦት 1826 ነበር። ይሁንና የጽሑፉ ቅጂዎች የተሰራጩት ለንጉሥ ራደማ ቤተሰብና ለአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ ነበር።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማለጋሲ ቋንቋ የተዘጋጀው “አዲስ ዓለም ትርጉም” ይሖዋ ለሚለው የአምላክ ስም ክብር ይሰጣል