በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በችግር ጊዜ ደስታን ጠብቆ መኖር

በችግር ጊዜ ደስታን ጠብቆ መኖር

በችግር ጊዜ ደስታን ጠብቆ መኖር

‘ይሖዋን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ደስ ይበላቸው፤ ዘላለም በደስታ ይዘምሩ።’—መዝ. 5:11

1, 2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትሉ ምን ነገሮች ያጋጥሙናል? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች በሰዎች ሁሉ ላይ ከሚደርሰው መከራ በተጨማሪ ምን ነገር በጽናት መቋቋም ይኖርባቸዋል?

የይሖዋ ምሥክሮች በሰው ዘር ላይ ከሚደርሰው መከራ ነፃ አይደሉም። በርካታ የአምላክ ሕዝቦች ወንጀልና ፍትሕ የጎደላቸው ድርጊቶች ይፈጸሙባቸዋል፤ እንዲሁም የጦርነት ሰለባ ይሆናሉ። በተጨማሪም የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ድህነት፣ ሕመምና ሞት ከፍተኛ ሥቃይ ሊያስከትሉባቸው ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ በአንድነት ሆኖ በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን” ብሎ መጻፉ የተገባ ነው። (ሮም 8:22) ከዚህም በላይ ፍጹም አለመሆናችን የሚያስከትልብን ችግር አለ። ጥንት እንደኖረው እንደ ንጉሥ ዳዊት ሁሉ እኛም “በደሌ ውጦኛል፤ እንደ ከባድ ሸክምም ተጭኖኛል” እንል ይሆናል።—መዝ. 38:4

2 እውነተኛ ክርስቲያኖች በሰዎች ሁሉ ላይ ከሚደርሰው መከራ በተጨማሪ ምሳሌያዊውን የመከራ እንጨት ተሸክመዋል። (ሉቃስ 14:27) አዎን፣ እንደ ኢየሱስ ሁሉ ደቀ መዛሙርቱም ይጠላሉ እንዲሁም ስደት ይደርስባቸዋል። (ማቴ. 10:22, 23፤ ዮሐ. 15:20፤ 16:2) በመሆኑም በአዲሱ ዓለም የምናገኛቸውን በረከቶች እየተጠባበቅን ባለንበት በዚህ ጊዜ ላይ ክርስቶስን መከተል ከፍተኛ ተጋድሎና ጽናት ይጠይቅብናል።—ማቴ. 7:13, 14፤ ሉቃስ 13:24

3. ክርስቲያኖች አምላክን ለማስደሰት የመከራ ሕይወት መምራት እንደማያስፈልጋቸው እንዴት ማወቅ እንችላለን?

3 ታዲያ ይህ ሲባል እውነተኛ ክርስቲያኖች ደስታና እርካታ የሌለው ሕይወት ይመራሉ ማለት ነው? መጨረሻው እስኪመጣ ድረስ ሕይወታችን በሐዘን የተሞላ ይሆናል ማለት ነው? የተሰጠን ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በምንጠባበቅበት በዚህ ወቅት ላይ ይሖዋ ደስተኞች እንድንሆን የሚፈልግ መሆኑ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እውነተኛ የይሖዋ አገልጋዮችን ደስተኛ ሕዝብ እንደሆኑ አድርጎ በተደጋጋሚ ጊዜያት ይገልጻቸዋል። (ኢሳይያስ 65:13, 14ን አንብብ።) መዝሙር 5:11 “[ይሖዋን] መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ግን ደስ ይበላቸው፤ ዘላለም በደስታ ይዘምሩ” ይላል። አዎን፣ ሥቃይ በበዛበት በዚህ ወቅትም እንኳ ከፍተኛ ደስታ፣ የአእምሮ ሰላምና እርካታ ማግኘት ይቻላል። እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንቋቋም ብሎም ደስታችንን ጠብቀን እንድንኖር የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

‘ደስተኛ አምላክ የሆነው’ ይሖዋ

4. ይሖዋ ፍጥረታቱ ፈቃዱን ችላ ሲሉ ምን ይሰማዋል?

4 እስቲ ይሖዋን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሁሉን ቻይ አምላክ እንደመሆኑ መጠን መላው ጽንፈ ዓለም በእሱ ቁጥጥር ሥር ነው። ይሖዋ ምንም የሚጎድለው ነገር የሌለ ሲሆን የማንም እርዳታ አያስፈልገውም። ተወዳዳሪ የሌለው ኃይል ቢኖረውም እንኳ ከመንፈሳዊ ልጆቹ መካከል አንዱ ዓምፆ ሰይጣን በሆነበት ወቅት ሐዘን ተሰምቶት መሆን አለበት። ሌሎች መላእክትም ከጊዜ በኋላ ከሰይጣን ጎን በተሰለፉ ጊዜ አምላክ አዝኖ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ከዚህም በተጨማሪ ድንቅ የፍጥረት ሥራዎቹ የነበሩት አዳምና ሔዋን ጀርባቸውን ለእሱ በሰጡ ጊዜ ምን ያህል አዝኖ ሊሆን እንደሚችል አስብ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእነሱ ልጆች የሆኑት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋን ሥልጣን ለመቀበል አሻፈረኝ ብለዋል።—ሮም 3:23

5. ይሖዋን በተለይ ያሳዘነው ነገር ምንድን ነው?

5 በዚያን ጊዜ ሰይጣን ያስነሳው ዓመፅ አሁንም አልረገበም። ይሖዋ 6,000 ለሚያህሉ ዓመታት የጣዖት አምልኮ፣ ዓመፅ፣ ግድያና ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ የፆታ ግንኙነት ሲፈጸሙ ተመልክቷል። (ዘፍ. 6:5, 6, 11, 12) ከዚህም በላይ አሳፋሪ ውሸቶችንና ስድቦችን ሰምቷል። እውነተኛ አገልጋዮቹም እንኳ ስሜቱን የሚጎዱበት ጊዜ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ወቅት የተፈጸመውን እንዲህ ያለውን ሁኔታ እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል፦ “በምድረ በዳ ስንት ጊዜ ዐመፁበት! በበረሓስ ምን ያህል አሳዘኑት! ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጡት።” (መዝ. 78:40, 41) ይሖዋ ሕዝቦቹ ለእሱ ጀርባቸውን ሲሰጡ ማየት በጣም እንደሚያሳዝነው ጥርጥር የለውም። (ኤር. 3:1-10) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ መጥፎ ነገሮች ያጋጥሙታል፤ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ደግሞ በጣም ያዝናል።—ኢሳይያስ 63:9, 10ን አንብብ።

6. አምላክ የሚያጋጥሙትን አሳዛኝ ሁኔታዎች የሚወጣው እንዴት ነው?

6 ይሁን እንጂ ይሖዋ የደረሰበት አሳዛኝ ሁኔታ እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ አላደረገውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ችግሮች በተከሰቱበት ጊዜ እነዚህ ነገሮች ሊያስከትሉት የሚችሉትን መጥፎ ውጤት ለመቀነስ ወዲያውኑ እርምጃ ወስዷል። ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ሲል ከረጅም ጊዜ በኋላ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል እርምጃ ወስዷል። ይሖዋ እንዲህ ያሉ እርምጃዎችን ስለወሰደ ሉዓላዊነቱ የሚረጋገጥበትንና ታማኝ አገልጋዮቹ በረከት የሚያገኙበትን ጊዜ በደስታ ይጠባበቃል። (መዝ. 104:31) አዎን፣ ይሖዋ ምንም ያህል ነቀፋ ቢሰነዘርበት ሁልጊዜ ‘ደስተኛ የሆነ አምላክ’ ነው።—1 ጢሞ. 1:11፤ መዝ. 16:11

7, 8. ነገሮች እንዳሰብናቸው ሳይሆኑ ሲቀሩ የይሖዋን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

7 እርግጥ ነው፣ እኛ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የይሖዋ ዓይነት ችሎታ የለንም። ያም ቢሆን ችግሮች ሲያጋጥሙን የይሖዋን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ነገሮች እንዳሰብናቸው ሳይሆኑ ሲቀሩ ማዘናችን ያለ ነገር ቢሆንም በሐዘን ተቆራምደን መቆየት አይኖርብንም። በይሖዋ አምሳል የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን ችግሮቻችንን ለይተን ለማወቅና አመቺ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የማመዛዘን ችሎታና ጥበብ አለን።

8 በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመቋቋም ከሚረዱን አስፈላጊ ነገሮች አንዱ አንዳንድ ነገሮች ከእኛ ቁጥጥር በላይ እንደሆኑ አምኖ መቀበል ነው። ስላጋጠሙን ችግሮች እያሰብን መቆዘማችን ይበልጥ ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርገናል፤ እንዲሁም በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ የምናደርገው እንቅስቃሴ ሊያስገኝልን የሚችለውን ደስታ ያሳጣናል። ችግሩን ለመፍታት ተገቢውን እርምጃ ከወሰድን በኋላ ስለ ሁኔታው ማሰባችንን ትተን ይበልጥ ውጤታማ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት ማድረጋችን የተሻለ ነው። ቀጥሎ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይህን ነጥብ በደንብ እንድንረዳ ያስችለናል።

ምክንያታዊ መሆን አስፈላጊ ነው

9. ሐና ምክንያታዊ መሆኗን ያሳየችው እንዴት ነበር?

9 ከጊዜ በኋላ የነቢዩ ሳሙኤል እናት የሆነችውን የሐናን ምሳሌ እንመልከት። ሐና ልጅ መውለድ ባለመቻሏ በጣም አዝና ነበር። መካን በመሆኗ ምክንያት ይፌዝባት ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሐና በጣም ተስፋ ከመቁረጧ የተነሳ ታለቅስ የነበረ ከመሆኑም ሌላ እህል አትቀምስም ነበር። (1 ሳሙ. 1:2-7) ሐና በአንድ ወቅት ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ሄዳ “በነፍሷ ተመርራ አብዝታ በማልቀስ ወደ [ይሖዋ] ጸለየች።” (1 ሳሙ. 1:10) ሐና ለይሖዋ የልቧን ግልጥልጥ አድርጋ ከነገረችው በኋላ ሊቀ ካህናቱ ዔሊ ወደ እሷ ቀርቦ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሺውን ይስጥሽ” አላት። (1 ሳሙ. 1:17) በዚህ ጊዜ ሐና የምትችለውን ሁሉ ማድረጓን እንደተገነዘበች ምንም ጥርጥር የለውም። መካን መሆኗ ከቁጥጥሯ በላይ ስለሆነ ማድረግ የምትችለው ነገር አልነበረም። በዚህ ረገድ ምክንያታዊ መሆኗን አሳይታለች። ሐናም “መንገዷን ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።”—1 ሳሙ. 1:18

10. ጳውሎስ ሊያስወግደው የማይችለው ችግር ሲያጋጥመው ምክንያታዊ ሰው መሆኑን የታየው እንዴት ነው?

10 ሐዋርያው ጳውሎስም ችግር በገጠመው ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ መንፈስ አሳይቷል። ጳውሎስ ከፍተኛ ሥቃይ ያስከተለበት አንድ ችግር ነበረበት። ይህን ችግር “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” በማለት ጠርቶታል። (2 ቆሮ. 12:7) ችግሩ ምንም ይሁን ምን ጳውሎስ ከሥቃዩ ለመገላገል ማድረግ የሚችለውን አድርጓል፤ ይኸውም ችግሩን እንዲያስወግድለት ወደ ይሖዋ ጸልዩአል። ጳውሎስ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ የጸለየው ምን ያህል ጊዜ ነበር? ሦስት ጊዜ ነበር። ጳውሎስ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ይሖዋ ከጸለየ በኋላ አምላክ ‘ሥጋውን የሚወጋውን እሾህ’ በተአምር እንደማያስወግድለት ገለጸለት። ጳውሎስም ይህን ሐቅ ተቀብሎ በሙሉ ልቡ ይሖዋን በማገልገል ላይ አተኮረ።—2 ቆሮንቶስ 12:8-10ን አንብብ።

11. ችግሮቻችንን በመወጣት ረገድ ጸሎትና ምልጃ ምን ሚና አላቸው?

11 እነዚህ ምሳሌዎች፣ ስለሚያስጨንቁን ነገሮች አንድ ጊዜ ወደ ይሖዋ ከጸለይን በኋላ መጸለያችንን ማቆም እንዳለብን የሚያሳዩ አይደሉም። (መዝ. 86:7) ከዚህ በተቃራኒ የአምላክ ቃል “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ” በማለት ያበረታታናል። ይሖዋ እንዲህ ላለው ልመናና ምልጃ መልስ የሚሰጠው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አክሎ “ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል” ይላል። (ፊልጵ. 4:6, 7) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ችግሮቻችንን አያስወግድልን ይሆናል፤ ሆኖም አእምሯችንን በመጠበቅ ለጸሎቶቻችን መልስ ይሰጣል። አንድን ጉዳይ አስመልክተን መጸለያችን በጭንቀት መዋጥ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ እንድንገነዘብ ሊያደርገን ይችላል።

የአምላክን ፈቃድ ማድረግ የሚያስገኘው ደስታ

12. ለረጅም ጊዜ ማዘን ጉዳት ያስከትላል የምንለው ለምንድን ነው?

12 ምሳሌ 24:10 “በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣ [“ተስፋ ብትቆርጥ፣” NW] ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው!” ይላል። አንድ ሌላ ምሳሌ ደግሞ “የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይሰብራል” ይላል። (ምሳሌ 15:13) አንዳንድ ክርስቲያኖች በጣም ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበባቸውንም ሆነ በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰላቸውን እስከ ማቆም ደርሰዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች በዘልማድ የሚጸልዩ ከመሆኑም ሌላ ራሳቸውን ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ሊያገሉ ይችላሉ። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ሐዘን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።—ምሳሌ 18:1, 14

13. ተስፋ በመቁረጥ ፋንታ ከፍተኛ ደስታ እንድናገኝ የሚረዱን አንዳንድ እንቅስቃሴዎች የትኞቹ ናቸው?

13 በሌላ በኩል ግን ብሩህ አመለካከት መያዝ ደስታ በሚያስገኙልን ነገሮች ላይ ትኩረት እንድናደርግ ይረዳናል። ዳዊት “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል” በማለት ጽፏል። (መዝ. 40:8 NW) በሕይወታችን ውስጥ አሳዛኝ ነገሮች ሲያጋጥሙን ፈጽሞ ልናደርገው የማይገባን ነገር ቢኖር ከአምልኮታችን ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ማቋረጥ ነው። እንዲያውም ሐዘንን ለመቋቋም መፍትሔው ደስታ ሊያስገኙ በሚችሉ እንቅስቃሴዎች መጠመድ ነው። ይሖዋ ትኩረት ሰጥተን ቃሉን በየዕለቱ ካነበብን ደስታና እርካታ እንደምናገኝ ነግሮናል። (መዝ. 1:1, 2፤ ያዕ. 1:25) ከቅዱሳን መጻሕፍትም ሆነ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች “ደስ የሚያሰኝ ቃል” እናገኛለን፤ ይህ ደግሞ የሚያበረታታን ከመሆኑም በላይ ልባችን በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል።—ምሳሌ 12:25፤ 16:24

14. ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ለደስታ ምክንያት የሚሆን ምን ተስፋ ሰጥቶናል?

14 ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉን። አምላክ የሰጠን የመዳን ተስፋ ከፍተኛ የደስታ ምንጭ ይሆንልናል። (መዝ. 13:5) በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብን ችግር ምንም ይሁን ምን አምላክ እሱን አጥብቀው የሚፈልጉ ሰዎችን ወደፊት እንደሚባርካቸው እናውቃለን። (መክብብ 8:12ን አንብብ።) ነቢዩ ዕንባቆም በዚህ ረገድ ያለውን የጸና እምነት እንደሚከተለው በማለት ግሩም በሆነ መንገድ ገልጾታል፦ “ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣ ከወይን ተክልም ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራም ዛፍ ፍሬ ባይሰጥ፣ ዕርሻዎችም ሰብል ባይሰጡ፣ የበጎች ጕረኖ እንኳ ባዶውን ቢቀር፣ ላሞችም በበረት ውስጥ ባይገኙ፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ደስ ይለኛል፤ በድነቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።”—ዕን. 3:17, 18

‘ይሖዋ አምላኩ የሆነ ሕዝብ ደስተኛ ነው’

15, 16. ወደፊት የምናገኘውን አስደሳች ተስፋ በምንጠባበቅበት በዚህ ጊዜ ደስታ ሊያስገኙልን የሚችሉ አንዳንድ የይሖዋ ስጦታዎች ምንድን ናቸው?

15 ወደፊት የምናገኘውን አስደሳች ተስፋ እየተጠባበቅን ባለንበት በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ እሱ በሰጠን መልካም ነገሮች እንድንደሰት ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለሰዎች፣ በሕይወት እያሉ ደስ ከመሰኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ነው።” (መክ. 3:12, 13) ‘መልካም ነገር ማድረግ’ ለሌሎች ጥሩ ነገር ማድረግንም ይጨምራል። ኢየሱስ ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ እንደሚያስገኝ ተናግሯል። ለትዳር ጓደኛችን፣ ለልጆቻችን፣ ለወላጆቻችንና ለዘመዶቻችን የደግነት ተግባር ማድረጋችን እርካታ ያስገኝልናል። (ምሳሌ 3:27) ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ባለን ግንኙነት አሳቢዎች፣ እንግዳ ተቀባዮችና ይቅር ባዮች መሆናችን ደስታ የሚያስገኝልን ከመሆኑም በላይ ይሖዋን ያስደስተዋል። (ገላ. 6:10፤ ቆላ. 3:12-14፤ 1 ጴጥ. 4:8, 9) የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ አገልግሎታችንን ማከናወናችን በእርግጥም መልሶ የሚክስ ነው።

16 ከላይ ባየነው የመክብብ መጽሐፍ ጥቅስ ላይ እንደ መብላትና መጠጣት ያሉ ሕይወታችንን አስደሳች የሚያደርጉ የተለመዱ ነገሮች ተጠቅሰዋል። መከራ በሚደርስብን ጊዜም ቢሆን ከይሖዋ የምናገኘው ማንኛውም ቁሳዊ ነገር የደስታ ምንጭ ሊሆንልን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ፀሐይ ስትጠልቅ የሚፈጠረውን ውበት፣ ግርማ ሞገስ የተላበሰውን መልክዓ ምድር፣ የእንስሳትን ቡረቃና አስገራሚ የሆኑ ሌሎች የፍጥረት ሥራዎችን መመልከት ወጪ አይጠይቅም፤ ያም ሆኖ እነዚህ ነገሮች ልባችን በአድናቆት ስሜት እንዲሞላ የሚያደርጉ ከመሆኑም ሌላ ደስታ ያስገኙልናል። በእነዚህ ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን የመልካም ነገሮች ሁሉ ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ ያለን ፍቅር እንዲጨምር ያደርጋል።

17. ከመከራዎች ሙሉ በሙሉ እንድንገላገል የሚያደርገን ምንድን ነው? እስከዚያው ድረስ ግን የሚያጽናናን ምንድን ነው?

17 ለአምላክ ያለን ፍቅር፣ ለመመሪያዎቹ ታዛዥ መሆናችንና በቤዛዊ መሥዋዕቱ ላይ ያለን እምነት ፍጹም ባለመሆናችን ምክንያት ከሚመጣብን መከራ ሙሉ በሙሉ እንድንገላገል የሚያደርገን ሲሆን ዘላቂ ደስታም ያስገኝልናል። (1 ዮሐ. 5:3) እስከዚያው ድረስ ግን ይሖዋ የሚደርሱብንን ችግሮች ሁሉ እንደሚገነዘብ ማወቃችን ያጽናናናል። ዳዊት “በምሕረትህ ደስ እሰኛለሁ፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤ መከራዬን አይተሃልና፤ የነፍሴንም ጭንቀት ዐውቀሃል” ሲል ጽፏል። (መዝ. 31:7) በእርግጥም ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር ከሚደርሱብን መከራዎች ሁሉ እኛን ለማዳን ያነሳሳዋል።—መዝ. 34:19

18. ደስታ በአምላክ ሕዝቦች ዘንድ ጎልቶ መታየት አለበት እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው?

18 ተስፋችን የሚፈጸምበትን ጊዜ እየተጠባበቅን ደስተኛ አምላክ የሆነውን የይሖዋን ምሳሌ ለመከተል እንጣር። የሚሰማን አሉታዊ ስሜት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ እንዲያግደን አንፍቀድ። ችግሮች ሲያጋጥሙን በማመዛዘን ችሎታና በጥበብ ተመርተን ተገቢውን እርምጃ እንውሰድ። ይሖዋ ስሜታችንን እንድንቆጣጠር እንዲሁም የሚያጋጥሙን ችግሮች የሚያስከትሉብንን መጥፎ ውጤት ለመቀነስ የሚያስችል ተገቢ እርምጃ እንድንወስድ ይረዳናል። ከይሖዋ በምናገኛቸው መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ስጦታዎች እንደሰት። ‘ይሖዋ አምላኩ የሆነ ሕዝብ ደስተኛ’ ስለሆነ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና በመመሥረት ደስተኛ መሆን እንችላለን።—መዝ. 144:15

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• መከራ ሲያጋጥመን የይሖዋን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

• ምክንያታዊ መሆናችን የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?

• አሳዛኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ደስታ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ በምድር ላይ የሚፈጸሙት መጥፎ ነገሮች ያሳዝኑታል

[ምንጭ]

© G.M.B. Akash/Panos Pictures

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ደስታችንን ጠብቀን እንድንኖር በርካታ ነገሮችን ሰጥቶናል