በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላክ አገልግሎት መጠመድ የሚያስገኘው ደስታ

በአምላክ አገልግሎት መጠመድ የሚያስገኘው ደስታ

በአምላክ አገልግሎት መጠመድ የሚያስገኘው ደስታ

ይሖዋ ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል። (መዝ. 100:2) የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን አንተም ሥራ ይበዛብህ ይሆናል። ሕይወትህን ለአምላክ ወስነህ በተጠመቅክበት ሰሞን የአሁኑን ያህል ሥራ አይበዛብህም ነበር፤ አሁን ግን ሰብዓዊና መንፈሳዊ ኃላፊነቶችህን ለመወጣት የምታደርገው ጥረት ጫና ፈጥሮብህ ይሆናል። እንዲያውም ያቀድካቸውን ነገሮች ሁሉ እንዳሰብከው መፈጸም አለመቻልህ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማህ አድርጎህ ሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ ሚዛንህን በመጠበቅ ምንጊዜም ‘የይሖዋን ደስታ’ እንዳገኘህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?—ነህ. 8:10

በዓይነቱ ልዩ በሆነ አስጨናቂ ዘመን ውስጥ ስለምንኖር ብዙ ጫና እንዳለብህ ግልጽ ነው፤ በመሆኑም በፕሮግራም መመራት ያስፈልግሃል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የጻፈው የሚከተለው ምክር በዚህ ረገድ ሊረዳህ ይችላል፦ “የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሰዎች ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ስለሆኑ ለራሳችሁ አመቺ የሆነውን ጊዜ ግዙ።”—ኤፌ. 5:15, 16

ይህን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ምክንያታዊ የሆነ ግብ ማውጣትና የግል ጥናትህን፣ ለቤተሰብህ የምታደርገውን እንክብካቤ፣ የመስክ አገልግሎትህን፣ ሰብዓዊ ሥራህንና ሌሎች አስፈላጊ እንቅስቃሴዎችህን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማካሄድ የምትችለው እንዴት ነው?

ራስህን ለአምላክ በወሰንክበትና በተጠመቅክበት ጊዜ ምን ያህል ተደስተህ እንደነበር ታስታውሳለህ? እንድትደሰት ያደረገህ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው የቀሰምከው እውቀት ነው። ይህን እውቀትና ደስታ ለማግኘት ለበርካታ ወራት ትጋት የተሞላበት ጥናት ማድረግ ጠይቆብህ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ካገኘኸው ደስታ አንጻር ልፋትህ የሚያስቆጭ አይደለም። ያደረግከው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሕይወትህ እንዲለወጥ አድርጓል።

ደስታህን ጠብቀህ ለመኖር በመንፈሳዊ መመገብህን መቀጠል አለብህ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት የሚያስችል ጊዜ እንዳጣህ ከተሰማህ መለስ ብለህ ፕሮግራምህን ገምግም። በቀን ውስጥ ጥቂት ደቂቃዎችን ወስደህ ማጥናትህና ማሰላሰልህ ብቻ እንኳ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ያደርግሃል፤ ይህ ደግሞ ደስታህን እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም።

አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች በጣም አስፈላጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ የሚያስችላቸውን ጊዜ ለመግዛት እምብዛም አስፈላጊ ባልሆኑ እንቅስቃሴዎች የሚያሳልፉትን ጊዜ ቀንሰዋል። አንተም ‘ዓለማዊ መጽሔቶችን ወይም ጋዜጦችን በማንበብ፣ ቴሌቪዥን በመመልከት፣ ሙዚቃ በመስማት አሊያም በሌላ የጊዜ ማሳለፊያ በመካፈል ምን ያህል ሰዓት አጠፋለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እንዲህ ያሉ ነገሮች ደስታ ሊያስገኙ ይችላሉ፤ ሆኖም ይህ የሚሆነው ሚዛኑን በጠበቀ ሁኔታ ካደረግናቸው ብቻ ነው። (1 ጢሞ. 4:8) በጊዜ አጠቃቀም ረገድ ችግር እንዳለብህ ከተገነዘብክ በፕሮግራምህ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን አድርግ።

የጉባኤ ሽማግሌ፣ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የሆነው አዳም ምን እንደረዳው ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ቀለል ያለ ሕይወት ለመምራት ጥረት አደርጋለሁ። ጊዜዬን ሊያባክኑ በሚችሉ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ እንቅስቃሴዎች ከመካፈል እቆጠባለሁ፤ እንዲሁም ብዙ ትኩረት የሚጠይቁ ዕቃዎችን አስወግዳለሁ። ይህን ስል ግን የባሕታዊ ዓይነት ኑሮ እኖራለሁ ማለቴ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ጊዜና ትኩረት በማይሻሙ ቀለል ባሉ መዝናኛዎች እካፈላለሁ።”

ያደረግከው ውሳኔ ባስገኘልህ ጥሩ ውጤት ላይ ማሰላሰልህ ደስታህን የሚጨምርልህ ከመሆኑም በላይ አዎንታዊ አመለካከት ይዘህ እንድትኖር ይረዳሃል። ለምሳሌ ያህል፣ የጉባኤ ሽማግሌና የሦስት ልጆች አባት የሆነው ማርዩሽ እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ አመለካከት መያዝ ጀመርኩ። በየጊዜው የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሙኛል፤ ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ እኔና ይሖዋ ብቻ የምናውቃቸው ናቸው። ይሖዋ ምስጋና ይግባውና በእሱ እርዳታ የወደፊቱን ጊዜ በደስታ መጠባበቅ ችያለሁ።”

ከማርዩሽ ምሳሌ ማየት እንደሚቻለው አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ከጭንቀት ነፃ ያደርጋል ማለት አይደለም። ሆኖም እንዲህ ያለ አመለካከት መያዝህ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህና በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሻለ መንገድ እንድትወጣ ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ልቡ የሚያዝን ሰው ዘመኑ ሁሉ የከፋች ናት፤ የልብ ደስታ ግን ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው” ይላል። (ምሳሌ 15:15 የ1954 ትርጉም) በተጨማሪም አምላክ ባሳየህ ፍቅር ላይ አሰላስል። እንዲህ ማድረግህ ለእሱ ያለህን ፍቅር የሚጨምርልህ ከመሆኑም ሌላ ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆን ያስችልሃል።—ማቴ. 22:37

አንድ ቤተሰብ ለይሖዋና ለእሱ ፈቃድ ቅድሚያ የሚሰጥ ከሆነ ይበልጥ ደስተኛ ይሆናል። የቤተሰቡ አባላት ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማንጸባረቃቸው በመካከላቸው ሊፈጠር የሚችለውን አለመግባባት ይቀንሰዋል፤ እንዲሁም ይበልጥ እንዲቀራረቡና አስደሳች ግንኙነት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። አንተም እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ቤትህ ሰላምና አንድነት የሰፈነበት ይሆናል።—መዝ. 133:1

በቤተሰብ አንድ ላይ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን ይረዳል። ማርዩሽ እንዲህ ብሏል፦ “በቤተሰብ አንድ ላይ ለምናሳልፈው ጊዜ ትልቅ ግምት እሰጣለሁ። ባለቤቴ በጣም ትረዳኛለች። በማንኛውም ጊዜ ማለትም አገልግሎት ስወጣም ሆነ ከትልልቅ ስብሰባዎች በፊት ስታዲየሙን በማጽዳት ሥራ ስካፈል ከጎኔ አትጠፋም፤ እንዲሁም የሕዝብ ንግግር ለመስጠት ወደ ሌላ ጉባኤ ስሄድ አብራኝ ትሄዳለች። እንዲህ ማድረጓ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል።”

ቅዱሳን መጻሕፍት ክርስቲያኖች ለቤተሰቦቻቸው መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ይሰጣሉ። (1 ጢሞ. 5:8) ይሁንና ሰብዓዊ ሥራህ ብዙ ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅብህ ከሆነ ለአምላክ በምታቀርበው አገልግሎት እንዳትደሰት ሊያደርግህ ይችላል። ይህን ጉዳይ አስመልክተህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። (መዝ. 55:22) እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም ሲሉ ሥራ እስከ መቀየር የሚያደርስ እርምጃ ወስደዋል። ብዙ ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅ አንድ ሥራ ጥሩ ክፍያ ያለው መሆኑ ማንኛውንም ክርስቲያን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን መንፈሳዊ ነገር ችላ እንዲል ሊያደርገው አይገባም።—ምሳሌ 22:3

አሁን ያለህ ሥራ ወይም ወደፊት ልትይዘው ያሰብከው ሥራ ሊኖረው የሚችለውን ጥቅምና ጉዳት በዝርዝር መጻፍህ ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። አንድ ሥራ አርኪ ብሎም ጥሩ ክፍያ የሚያስገኝ መሆን እንዳለበት የታወቀ ነው። ሆኖም አሁን ያለህ ሥራ የቤተሰብህን መንፈሳዊ ደኅንነት እንድትጠብቅ የሚረዳህ ነው? ሁሉንም ነገር በሚገባ ካመዛዘንክ በኋላ ከይሖዋ ጋር ለመሠረትከው ግንኙነት ቅድሚያ እንድትሰጥ የሚያስችልህን ውሳኔ አድርግ።

የሥራህ ጠባይ መንፈሳዊ እድገት እንዳታደርግ እንቅፋት የሚሆንብህ ከሆነ ሁኔታህን ማስተካከል ይኖርብሃል። በርካታ ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊ ነገሮች ጊዜ ለማግኘት ሲሉ ሥር ነቀል ለውጥ አድርገዋል። በፖላንድ የሚገኝ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ጊዜ ለሥራ ጉዳይ ወደተለያዩ ቦታዎች እሄድ ስለነበር እሠራበት የነበረውን ድርጅት ከመልቀቅ ውጪ ምንም ምርጫ አልነበረኝም። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈልም ሆነ ቤተሰቤን በሚገባ ለመንከባከብ የሚያስችል በቂ ጊዜ አልነበረኝም።” በአሁኑ ጊዜ ይህ ወንድም የሚተዳደረው ብዙ ጊዜና ጉልበት የማይጠይቅ ሥራ በመሥራት ነው።

ሌሎችን መርዳት የሚያስገኘው ደስታ

ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 20:35) ክርስቲያኖች ለሌሎች የሚሰጧቸው ብዙ ነገሮች አሏቸው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክርስቲያን ላከናወነው ትጋት የታከለበት ቲኦክራሲያዊ ሥራ ሞቅ ያለ ፈገግታ በማሳየትና በመጨበጥ አድናቆታችንን መግለጻችን ብቻ እንኳ ለእሱም ሆነ ለእኛ ደስታ ሊያስገኝልን ይችላል።

ሐዋርያው ጳውሎስ “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው” በማለት ክርስቲያን ወንድሞቹን አበረታቷል። (1 ተሰ. 5:14) የተጨነቁ ነፍሳት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በራሳቸው ኃይል መቋቋም እንደማይችሉ ሊሰማቸው ይችላል። እንዲህ ያሉ ክርስቲያኖችን ልትረዳቸው ትችላለህ? አንድ ክርስቲያን ወንድምህ ይሖዋን ማገልገል የሚያስገኝለት ደስታ እየቀነሰ እንደመጣ ካስተዋልክ እሱን ለማበረታታት ጥረት አድርግ። እንዲህ ማድረግህ አንተንም ያበረታታል። ከሰው አቅም በላይ የሆኑ ችግሮች አሉ። ይሁንና ለወንድምህ ከልብ የመነጨ ርኅራኄ ማሳየትና ፈጽሞ በማይጥለው በይሖዋ ላይ እንዲታመን መንገር ትችላለህ። በይሖዋ የሚታመኑ ሁሉ ተስፋ ያደረጉትን ነገር አጥተው ለሐዘን አይዳረጉም።—መዝ. 27:10፤ ኢሳ. 59:1

ልትወስደው የምትችለው ሌላም እርምጃ አለ፤ በአገልግሎት ደስታ ካጣው ወንድምህ ጋር ማገልገል ትችላለህ። ኢየሱስ ሰባውን ደቀ መዛሙርት የላካቸው “ሁለት ሁለት” አድርጎ ነበር። (ሉቃስ 10:1) ሁለት ሁለት አድርጎ የመደባቸው እርስ በርስ እንዲበረታቱ አስቦ ነው ቢባል አትስማማም? በዛሬውም ጊዜ አንዳንዶች ደስታቸውን መልሰው እንዲያገኙ ለመርዳት አብረውህ እንዲያገለግሉ ማድረግ ትችል ይሆን?

በሕይወታችን ውስጥ ብዙ የሚያሳስቡን ነገሮች አሉ። እንደዚያም ሆኖ ጳውሎስ “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ!” በማለት ተናግሯል። (ፊልጵ. 4:4) አምላክን ስለምትወደው፣ ስለምትታዘዘውና የሰጠህን ሥራ በቅንዓት ማከናወንህን ስለምትቀጥል ሕይወት ትርጉም ያለው ሆኖልሃል። ይህም ደስታ ያስገኝልሃል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ የሚያጋጥሙህን ተጽዕኖዎችና ችግሮች እንድትወጣ ይረዳሃል።—ሮም 2:6, 7

ይሖዋ ቃል የገባልን አዲስ ዓለም በቅርቡ እንደሚመጣ እምነት አለን። በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ ብዙ በረከቶችንና ለደስታ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን እናገኛለን! (መዝ. 37:34) ይሖዋ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ምን ያህል እየባረከን እንዳለ ባለመዘንጋት ደስ ሊለን ይገባል። በመሆኑም ይህን በማሰብ ‘ይሖዋን በደስታ ልናገለግለው’ እንችላለን።—መዝ. 100:2

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ምንጊዜም ደስተኛ ሆነህ መኖር የምትፈልግ ከሆነ ጊዜህን በምትጠቀምበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ይኖርብሃል

መዝናኛ

ቤትን እና ቤተሰብን መንከባከብ

ሥራ

ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች

የግል ጥናት

አገልግሎት

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሌሎች ደስታቸውን መልሰው እንዲያገኙ መርዳት ትችላለህ?