በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁ የሚያጋጥሟቸውን ተደራራቢ ፈተናዎች እንዲቋቋሙ እርዷቸው

ልጆቻችሁ የሚያጋጥሟቸውን ተደራራቢ ፈተናዎች እንዲቋቋሙ እርዷቸው

ልጆቻችሁ የሚያጋጥሟቸውን ተደራራቢ ፈተናዎች እንዲቋቋሙ እርዷቸው

ወጣቶቻችን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያጋጥማቸዋል። ወጣቶች ክፉ ለሆነው የሰይጣን ዓለም መንፈስ የተጋለጡ ከመሆናቸውም በላይ “ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ምኞቶች” ጋር መታገል ግድ ሆኖባቸዋል። (2 ጢሞ. 2:22፤ 1 ዮሐ. 5:19) ከዚህም በላይ ‘ታላቁን ፈጣሪያቸውን’ ለማሰብ ጥረት ስለሚያደርጉ እምነታቸውን ከሚቃወሙ ሰዎች የሚደርስባቸውን ፌዝ አልፎ ተርፎም ጥቃት መቋቋም ይኖርባቸዋል። (መክ. 12:1) ቪንሰንት የሚባል አንድ ወንድም፣ ወጣት ሳለ ያጋጥመው የነበረውን ሁኔታ አስታውሶ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ምክንያት ነገር የሚፈልገኝ፣ የሚያስፈራራኝ ወይም እኔን ለመደብደብ የሚጋበዝ ሰው አይጠፋም ነበር። ብዙ ጊዜ የሚደርስብኝ ነገር ከአቅሜ በላይ ስለሚሆንብኝ ትምህርት ቤት መሄድ ያስጠላኝ ነበር።” *

ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ዓለም ከሚያደርስባቸው ተጽዕኖ ጋር ብቻ ሳይሆን እንደ እኩዮቻቸው ለመሆን ከሚሰማቸው ውስጣዊ ግፊት ጋርም መታገል ያስፈልጋቸዋል። በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የምትገኘው ካትሊን የተባለች እህት “ከሌሎች የተለዩ ሆኖ መታየት ቀላል አይደለም” በማለት ተናግራለች። አለን የሚባል አንድ ወጣት ወንድም ደግሞ “አብረውኝ የሚማሩ ልጆች ብዙ ጊዜ ቅዳሜና እሁድ አብረን እንድንዝናና ይጠይቁኝ ነበር፤ እኔም ከእነሱ ጋር መዝናናት እፈልግ ነበር” በማለት ስሜቱን ሳይደብቅ ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶች በትምህርት ቤት በሚካሄዱ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የመካፈል ከፍተኛ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፤ ይህ ደግሞ በቀላሉ ለመጥፎ ጓደኝነት ያጋልጣቸዋል። ታንያ የምትባል አንዲት ወጣት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ስፖርት እወዳለሁ። በትምህርት ቤታችን ያሉ አሠልጣኞች በቡድን ውስጥ ታቅፌ እንድጫወት ሁልጊዜ ይጎተጉቱኝ ነበር። እምቢ ማለት ለእኔ በጣም ከባድ ነበር።”

ታዲያ ልጆቻችሁ ያሉባቸውን ተደራራቢ ፈተናዎች እንዲቋቋሙ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው አመራር እንዲሰጡ ኃላፊነት ጥሎባቸዋል። (ምሳሌ 22:6፤ ኤፌ. 6:4) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ዋነኛ ዓላማቸው ልጆቻቸው ይሖዋን የመታዘዝ ልባዊ ፍላጎት እንዲያድርባቸው መርዳት ነው። (ምሳሌ 6:20-23) እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ ልጆች ወላጆቻቸው በማያዩአቸው ጊዜም እንኳ የዓለምን ግፊት ለመቋቋም ይነሳሳሉ።

ወላጆች ሰብዓዊ ሥራቸውን፣ የቤተሰብ ኃላፊነታቸውንና የጉባኤ እንቅስቃሴዎቻቸውን በሙሉ በአንድ ጊዜ መወጣት ተፈታታኝ እንደሚሆንባቸው እሙን ነው። አንዳንዶች እነዚህን ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚጣጣሩት ብቻቸውን ልጆቻቸውን እያሳደጉ አሊያም ከማያምን የትዳር ጓደኛ ተቃውሞ እየደረሰባቸው ነው። ያም ሆኖ ይሖዋ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ሥልጠናና ድጋፍ መስጠት የሚያስችላቸውን ጊዜ እንዲመድቡ ይጠብቅባቸዋል። ታዲያ ልጆቻችሁ የእኩዮቻቸውን ተጽዕኖ፣ የልባቸውን ግፊትና በየዕለቱ የሚደርስባቸውን ጥቃት እንዲቋቋሙ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ወጣቶቻችን ይሖዋ እውን ሊሆንላቸው ይገባል። “የማይታየው” እውን ሆኖ ‘እንዲታያቸው’ እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። (ዕብ. 11:27) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቪንሰንት ወላጆቹ ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና እንዲመሠርት እንዴት እንደረዱት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የጸሎትን አስፈላጊነት አስተምረውኝ ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ ሁልጊዜ ማታ ማታ ከመተኛቴ በፊት ወደ ይሖዋ እጸልይ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ይሖዋ ለእኔ እውን ነበር።” እናንተስ ከልጆቻችሁ ጋር ትጸልያላችሁ? በግል በሚያቀርቡት ጸሎት ላይ ይሖዋን ምን እንደሚሉት ለምን አታዳምጧቸውም? ሁልጊዜ ተመሳሳይ ቃላት ተጠቅመው አንድ ዓይነት ጸሎት ይጸልያሉ? ወይስ በጸሎታቸው ላይ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚሰማቸው ይገልጻሉ? ልጆቻችሁ ሲጸልዩ በማዳመጥ ምን ያህል መንፈሳዊ እድገት እንዳደረጉ ማወቅ ትችላላችሁ።

ወጣቶች ይበልጥ ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚችሉበት ሌላው ወሳኝ መንገድ ደግሞ በግላቸው የአምላክን ቃል ማንበብ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካትሊን እንደሚከተለው በማለት ትናገራለች፦ “ልጅ እያለሁ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ማንበቤ ረድቶኛል። ሰዎች ቢቃወሙኝ እንኳ ይሖዋ እንደሚደግፈኝ እርግጠኛ እንድሆን አድርጎኛል።” ታዲያ የእናንተስ ልጆች የራሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም አላቸው?—መዝ. 1:1-3፤ 77:12

እውነት ነው፣ ልጆች ለወላጆች አመራር ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ ይለያያል። በተጨማሪም መንፈሳዊ እድገታቸው በዕድሜያቸው ላይ የተመካ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ወጣቶች አመራር ሳያገኙ ይሖዋን እንደ አንድ እውን አካል አድርገው መመልከት ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ወላጆች ልጆቻቸው የትም ይሁኑ የት ሁልጊዜ የይሖዋን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ እንዲችሉ የአምላክን ቃል በልባቸው ውስጥ መቅረጽ ይኖርባቸዋል። (ዘዳ. 6:6-9) ልጆቻችሁ ይሖዋ ለእነሱ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላቸው ማመን ይኖርባቸዋል።

ትርጉም ያለው የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ

ልጆቻችሁን መርዳት የምትችሉበት ሌላው አስፈላጊ መንገድ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ነው። እርግጥ ነው፣ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ሲባል ከልጆቻችሁ ጋር ማውራት ማለት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጥያቄ መጠየቅን ብሎም የሚሰጡት መልስ እናንተ ከምትጠብቁት የተለየ ቢሆንም እንኳ መልስ ሲሰጡ በትዕግሥት ማዳመጥን ያጠቃልላል። የሁለት ወንዶች ልጆች እናት የሆነችው አን “ልጆቼ ምን እንደሚያስቡ እንዲሁም በሕይወታቸው ውስጥ ምን ነገሮች እንደሚያጋጥሟቸው እንደተረዳሁ እስኪሰማኝ ድረስ ጥያቄ እጠይቃቸዋለሁ” በማለት ተናግራለች። ልጆቻችሁ እንደምታዳምጧቸው ይሰማቸዋል? ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ታንያ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ከልብ ያዳምጡኝ የነበረ ሲሆን የተነጋገርንባቸውን ነገሮች በደንብ ያስታውሳሉ። የክፍል ጓደኞቼን ስም ያውቃሉ። ስለ እነሱና ከዚያ በፊት ተነጋግረንባቸው ስለነበሩ ሌሎች ነገሮች አስታውሰው ይጠይቁኛል።” ማዳመጥና ማስታወስ ስኬታማ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ በጣም ወሳኝ ነገሮች ናቸው።

በርካታ ቤተሰቦች፣ የምግብ ሰዓት ትርጉም ያለው የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተገንዝበዋል። ቪንሰንት እንዲህ ብሏል፦ “በቤተሰባችን ውስጥ አብሮ መመገብ ትልቅ ቦታ ይሰጠው ነበር። በተቻለ መጠን ከቤተሰባችን ጋር በማዕድ እንድንቀርብ ይጠበቅብናል። በምግብ ሰዓት ቴሌቪዥን መመልከት፣ ሬዲዮ ማዳመጥ ወይም ማንበብ አይፈቀድም ነበር። አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ወቅት ዘና ያለ ጭውውት እናደርጋለን፤ ይህ ደግሞ በትምህርት ቤት ያለውን ትርምስና የሚያጋጥመኝን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል የተረጋጋ መንፈስ ይፈጥርልኛል።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በምግብ ሰዓት ከወላጆቼ ጋር የመነጋገር ልማድ የነበረኝ መሆኑ አሳሳቢ ጉዳይ አጋጥሞኝ እነሱን በማማክርበት ጊዜም ሐሳቤን መግለጽ እንዳይቸግረኝ ረድቶኛል።”

‘በሳምንት ውስጥ አብረን የምንመገበው ምን ያህል ጊዜ ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። በዚህ ረገድ ማስተካከያ ማድረጋችሁ ከልጆቻችሁ ጋር የተሻለ የሐሳብ ልውውጥ እንድታደርጉ እንዲሁም እርስ በርስ ለመጨዋወት የሚያስችል ተጨማሪ ጊዜ እንድታገኙ ይረዳችኋል።

የልምምድ ፕሮግራሞች ጠቃሚ የሆኑበት ምክንያት

ምሽት ላይ የሚደረገው ሳምንታዊው የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም፣ ትርጉም ያለው ጭውውት ለማድረግ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ይረዳቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው አለን እንደሚከተለው በማለት ይናገራል፦ “ወላጆቼ በቤተሰብ ጥናት ወቅት የልባችንን አውጥተን እንድንናገር ለማድረግ ይጥሩ ነበር። ካጋጠመን ችግር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ርዕሶች መርጠው እንድንወያይ ያደርጉ ነበር።” የአለን እናት እንዲህ ብላለች፦ “በቤተሰብ ጥናት ወቅት የተወሰነውን ሰዓት ለልምምድ እንጠቀምበት ነበር። እነዚህ የልምምድ ፕሮግራሞች ልጆቻችን የተቃውሞ ሐሳብ ሲነሳ ስለሚያምኑበት ነገር መልስ መስጠትም ሆነ የሚያምኑት ነገር እውነት መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲማሩ ረድተዋቸዋል። ይህ ደግሞ ልጆቻችን የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለማሸነፍ የሚያስችል በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲኖራቸው አድርጓል።”

በእርግጥም ልጆች እኩዮቻቸው አንድ ነገር እንዲያደርጉ ግፊት ሲያደርጉባቸው ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ገልጸው ከመሄድ ያለፈ ነገር ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ለምን እና ምን ችግር አለው እንደሚሉት ላሉት ጥያቄዎች መልስ መስጠት መቻል አለባቸው። እንዲሁም ሌሎች በእምነታቸው ምክንያት ሲያሾፉባቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው በእርግጠኝነት ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ስለሚያምኑበት ነገር እንዴት መልስ መስጠት እንደሚችሉ ካላወቁ ለእውነተኛው አምልኮ የጸና አቋም መያዝ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። የልምምድ ፕሮግራሞች አቋማቸውን በግልጽ የማሳወቅ ድፍረት እንዲኖራቸው ያስችሏቸዋል።

 በገጽ 18 ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ ልምምድ ልታደርጉ የምትችሉባቸው አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ተዘርዝረዋል። ለልጆቻችሁ ከበድ ያሉ ጥያቄዎችን በማንሳት የልምምድ ፕሮግራማችሁ ሕያው እንዲሆን ለማድረግ ጣሩ። እንዲህ ያለ የልምምድ ፕሮግራም ከማድረግ በተጨማሪ ተያያዥነት ያላቸውን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን ተመልከቱ። በቤት ውስጥ የምትሰጡት ይህ ሥልጠና ልጆቻችሁ በትምህርት ቤትም ሆነ በሌላ ቦታ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ችግሮች ለመቋቋም እንደሚያስታጥቃቸው ምንም ጥርጥር የለውም።

ቤታችሁ እፎይታ የሚገኝበት ቦታ ነው?

ቤታችሁ፣ ልጆቻችሁ ትምህርት ቤት ከዋሉ በኋላ ሊመለሱበት የሚናፍቁት ዓይነት ቦታ ነው? ቤታችሁ እፎይታ የሚገኝበት ቦታ ከሆነ ልጆቻችሁ በየዕለቱ የሚደርሱባቸውን ፈተናዎች እንዲጋፈጡ ይረዳቸዋል። በአሁኑ ጊዜ የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነች አንዲት እህት እንደሚከተለው በማለት ተናግራለች፦ “ልጅ እያለሁ ከፍተኛ ጥቅም ካስገኙልኝ ነገሮች መካከል አንዱ ቤታችን እፎይታ የሚገኝበት ቦታ መሆኑ ነበር። በትምህርት ቤት ውስጥ ምንም ያህል የከፋ ችግር ቢያጋጥመኝ ቤት ስመለስ ሁሉንም ነገር እንደምረሳ አውቅ ነበር።” በእናንተ ቤት ያለው ሁኔታስ ምን ይመስላል? ቤታችሁ “በቁጣ መገንፈል፣ የከረረ ጭቅጭቅ፣ [እና] መከፋፈል” የሰፈነበት ነው? ወይስ የሚታወቀው “ፍቅር፣ ደስታ፣ [እና] ሰላም” ያለበት በመሆኑ ነው? (ገላ. 5:19-23) ብዙ ጊዜ በቤታችሁ ውስጥ ሰላም የማይኖር ከሆነ ቤታችሁ ልጆቻችሁ እፎይታ የሚያገኙበት አስተማማኝ ቦታ እንዲሆንላቸው ምን ለውጥ ማድረግ እንዳለባችሁ ለመረዳት ትጥራላችሁ?

ልጆቻችሁ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲወጡ መርዳት የምትችሉበት ሌላው መንገድ ደግሞ ጥሩ ጓደኝነት እንዲመሠርቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ቤተሰባችሁ ለሽርሽር ወጣ ሲል በጉባኤያችሁ የሚገኙ አንዳንድ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች አብረዋችሁ እንዲሄዱ ማድረግ ትችሉ ይሆን? ወይም ደግሞ ተጓዥ የበላይ ተመልካቹን ወይም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሠማሩ ወንድሞችንና እህቶችን ቤታችሁ መጋበዝ ትችላላችሁ? የምታውቋቸው ሚስዮናውያን ወይም ቤቴላውያን ካሉ ልጆቻችሁ ከእነሱ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ትችሉ ይሆን? ምናልባትም ደብዳቤ በመጻጻፍ፣ ኢሜይል በመላላክ ወይም አልፎ አልፎ ስልክ በመደዋወል ይህን ማድረግ ይቻላል። ልጆቻችሁ እንዲህ ያለ ወዳጅነት መመሥረታቸው ለእግራቸው ቀና መንገድ እንዲያበጁ ብሎም መንፈሳዊ ግብ እንዲኖራቸው ሊረዳቸው ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በወጣቱ ጢሞቴዎስ ላይ ያሳደረውን በጎ ተጽዕኖ አስቡ። (2 ጢሞ. 1:13፤ 3:10) ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር የቅርብ ወዳጅነት መመሥረቱ መንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዲያተኩር ረድቶታል።—1 ቆሮ. 4:17

ልጆቻችሁን አመስግኗቸው

ይሖዋ፣ ወጣቶች ከሰይጣን ዓለም የሚደርሱባቸውን ተጽዕኖዎች ተቋቁመው ትክክል ለሆነው ነገር አቋም መውሰዳቸውን ሲመለከት ይደሰታል። (መዝ. 147:11፤ ምሳሌ 27:11) እናንተም ብትሆኑ ወጣቶቻችን ትክክለኛውን ጎዳና ሲመርጡ መመልከታችሁ እንደሚያስደስታችሁ ጥርጥር የለውም። (ምሳሌ 10:1) ልጆቻችሁ ስለ እነሱ ምን እንደሚሰማችሁ እንዲያውቁ አድርጉ፤ እንዲሁም ከልብ የመነጨ ምስጋና በማቅረብ ረገድም ንፉጎች አትሁኑ። ይሖዋ ለወላጆች ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ይሖዋ “አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” ብሎት ነበር። (ማር. 1:11) ኢየሱስ ከአባቱ ያገኘው ይህ ማበረታቻ ከፊቱ የሚጠብቁትን በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ አስገኝቶለት መሆን አለበት! እናንተም በተመሳሳይ ልጆቻችሁን እንደምትወዷቸው ግለጹላቸው፤ እንዲሁም እያከናወኑ ላሉት ነገር እውቅና ስጧቸው።

ልጆቻችሁን ሙሉ በሙሉ ከተጽዕኖ፣ ከጥቃትና ከፌዝ ልታድኗቸው እንደማትችሉ የታወቀ ነው። ያም ሆኖ እነሱን ለመርዳት ልታደርጉት የምትችሉት ብዙ ነገር አለ። በምን መንገድ ልትረዷቸው ትችላላችሁ? ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና እንዲመሠርቱ እርዷቸው። በቤታችሁ ውስጥ ትርጉም ያለው ጭውውት ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ እንዲሰፍን አድርጉ። የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ተግባራዊ ጠቀሜታ ያለው እንዲሁም ቤታችሁ እፎይታ የሚገኝበት ቦታ እንዲሆን ለማድረግ ጣሩ። እንዲህ ማድረጋችሁ ልጆቻችሁ ያሉባቸውን ተደራራቢ ፈተናዎች እንዲቋቋሙ እንደሚያስታጥቃቸው ምንም ጥርጥር የለውም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገን ሣጥን/​ሥዕል]

 የልምምድ ፕሮግራሞች ሊረዱ ይችላሉ

ወጣቶቻችን ሊያጋጥሟቸው ከሚችሉ ሁኔታዎች መካከል አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል። አንዳንዶቹን በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ ለምን አትለማመዱባቸውም?

▸ አንድ የስፖርት አስተማሪ ልጃችሁ በትምህርት ቤቱ ቡድን ውስጥ እንድትታቀፍ ይጠይቃታል።

▸ ልጃችሁ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ሲመለስ ሲጋራ እንዲያጨስ ግብዣ ይቀርብለታል።

▸ አንዳንድ ልጆች ልጃችሁን ዳግመኛ ሲሰብክ ካዩት እንደሚመቱት ይዝቱበታል።

▸ ልጃችሁ ከቤት ወደ ቤት እያገለገለች ሳለ አንደኛውን ቤት ስታንኳኳ አብራት የምትማር አንዲት ልጅ አገኘች።

▸ ልጃችሁ ተማሪዎች ፊት ወጥቶ ብሔራዊ መዝሙር የማይዘምረው ለምን እንደሆነ እንዲያስረዳ ተጠይቋል።

▸ ልጃችሁ የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ አንድ ልጅ ሁልጊዜ ያበሽቀዋል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆቻችሁ የራሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም አላቸው?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሽርሽር ወጣ ስትሉ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች አብረዋችሁ እንዲሄዱ ታደርጋላችሁ?