በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መሆንህን አስመሥክር

እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መሆንህን አስመሥክር

እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መሆንህን አስመሥክር

“ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን የማይጠቅም ፍሬ ያፈራል።”—ማቴ. 7:17

1, 2. እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች በተለይ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ከሐሰተኞቹ ተለይተው የሚታወቁት እንዴት ነው?

ኢየሱስ የእሱ አገልጋዮች እንደሆኑ አድርገው በሐሰት የሚናገሩ ሰዎች ከእውነተኛ ተከታዮቹ ተለይተው የሚታወቁት በፍሬያቸው ይኸውም በትምህርታቸውና በባሕርያቸው እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴ. 7:15-17, 20) ሰዎች ወደ አእምሯቸውና ወደ ልባቸው የሚያስገቡት ነገር በጎ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርባቸው አሌ የማይባል ሐቅ ነው። (ማቴ. 15:18, 19) የሐሰት ትምህርቶችን የሚማሩ ሰዎች “የማይጠቅም ፍሬ” ሲያፈሩ እውነተኛ መንፈሳዊ ምግብ የሚመገቡ ደግሞ “መልካም ፍሬ” ያፈራሉ።

2 በዚህ የፍጻሜ ዘመን እነዚህ ሁለት የፍሬ ዓይነቶች በግልጽ እየታዩ ነው። (ዳንኤል 12:3, 10ን አንብብ።) ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ስለ አምላክ የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው ከመሆኑም በላይ አብዛኛውን ጊዜ ለአምላክ ያደሩ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ መንፈሳዊ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ያመልኩታል። (ዮሐ. 4:24፤ 2 ጢሞ. 3:1-5) እንዲሁም የክርስቶስ ዓይነት ባሕርያትን ለማንጸባረቅ ጥረት ያደርጋሉ። እኛስ በግለሰብ ደረጃ እንዴት ነን? እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁበትን የሚከተሉትን አምስት ነጥቦች ስትመረምር ራስህን እንደሚከተለው በማለት ጠይቅ፦ ‘ምግባሬም ሆነ የማስተምረው ትምህርት ከአምላክ ቃል ጋር ይስማማል? እውነትን ለተጠሙ ሰዎች እውነት ማራኪ ሆኖ እንዲታያቸው ለማድረግ እጥራለሁ?’

የአምላክን ቃል መመሪያህ አድርገው

3. ይሖዋን የሚያስደስተው ምንድን ነው? ይህ ደግሞ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች አኗኗር ጋር በተያያዘ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

3 ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ነው።” (ማቴ. 7:21) አዎን፣ ይሖዋን የሚያስደስተው አንድ ሰው ክርስቲያን ነኝ ብሎ መናገሩ ሳይሆን ከክርስቲያኖች የሚፈለገውን ተግባራዊ ማድረጉ ነው። ይህ ደግሞ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮችን መላ ሕይወት የሚነካ ነው፤ ይህም ስለ ገንዘብ፣ ስለ ሥራ፣ ስለ መዝናኛ፣ ስለ ዓለማዊ ልማዶችና በዓሎች፣ ስለ ጋብቻ እንዲሁም ከሰዎች ጋር ስላላቸው ማኅበራዊ ግንኙነት ያላቸውን አመለካከት ይጨምራል። ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ግን የዓለምን አስተሳሰብና አካሄድ ይከተላሉ፤ እንዲህ ያለው አስተሳሰብና አካሄድ በተለይ በዚህ የመጨረሻ ዘመን እየተበላሸ መጥቷል።—መዝ. 92:7

4, 5. ይሖዋ በሚልክያስ 3:18 ላይ የተናገረውን ቃል በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

4 ነቢዩ ሚልክያስ ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በዚያን ጊዜም እንደ ገና በጻድቁና በኀጢአተኛው መካከል፣ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት ታያላችሁ።” (ሚል. 3:18) በዚህ ጥቅስ ላይ ስታሰላስል ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ከዓለም ጋር ተመሳስያለሁ ወይስ የተለየሁ ነኝ? ከሥራ ባልደረቦቼ ወይም አብረውኝ ከሚማሩ ልጆች የተለየ አቋም ላለመያዝ ጥረት አደርጋለሁ? ወይስ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመከተል ረገድ የጸና አቋም አለኝ? አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜስ አቋሜን በግልጽ እናገራለሁ?’ (1 ጴጥሮስ 3:16ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ ራሳችንን ማመጻደቅ አንፈልግም፤ ሆኖም ለይሖዋ ፍቅር ከሌላቸውና እሱን ማገልገል ከማይፈልጉ ሰዎች የተለየን መሆናችን በግልጽ መታየት ይኖርበታል።

5 ራስህን ስትመረምር ማሻሻያ ልታደርግበት የሚገባ ነገር እንዳለ ከተሰማህ ለምን በጉዳዩ ላይ አትጸልይም? ከዚህም በተጨማሪ አዘውትረህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ፣ በመጸለይ እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ በመካፈል መንፈሳዊ ጥንካሬ ማዳበር ትችላለህ። የአምላክን ቃል በሕይወትህ ተግባራዊ ባደረግህ መጠን የዚያኑ ያህል “መልካም ፍሬ” ታፈራለህ፤ ይህም ‘የአምላክን ስም በይፋ የምታውጅበትን የከንፈር ፍሬ’ ይጨምራል።—ዕብ. 13:15

የአምላክን መንግሥት ስበክ

6, 7. ከመንግሥቱ መልእክት ጋር በተያያዘ በእውነተኛና በሐሰተኛ ክርስቲያኖች መካከል ምን ልዩነት ይታያል?

6 ኢየሱስ “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” ብሏል። (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት የአገልግሎቱ ዋነኛ ጭብጥ ያደረገው ለምን ነበር? በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው መከራና ሥቃይ ዋነኛ መንስኤ የሆኑት ኃጢአትና ዲያብሎስ የሚወገዱት እሱ ንጉሥ ሆኖ በሚያስተዳድረውና ትንሣኤ ያገኙት በመንፈስ የተወለዱ ወንድሞቹ ተባባሪ ገዥዎች በሚሆኑበት በዚህ መንግሥት አማካኝነት እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው። (ሮም 5:12፤ ራእይ 20:10) በመሆኑም ተከታዮቹ ይህ ሥርዓት እስከሚጠፋበት ጊዜ ድረስ ይህን መንግሥት እንዲያውጁ አዟቸዋል። (ማቴ. 24:14) ለአፋቸው ያህል የክርስቶስ ተከታዮች እንደሆኑ የሚናገሩ ሰዎች በዚህ ሥራ አይካፈሉም፤ ደግሞም ይህን ሥራ መሥራት አይችሉም። ለምን? ቢያንስ ሦስት ምክንያቶችን መጥቀስ እንችላለን፤ አንደኛ፣ የማይረዱትን ነገር መስበክ አይችሉም። ሁለተኛ፣ ብዙዎቹ የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎች መስበክ የሚያስከትለውን ፌዝና ተቃውሞ ለመቋቋም የሚያስችል ትሕትና እና ድፍረት የላቸውም። (ማቴ. 24:9፤ 1 ጴጥ. 2:23) ሦስተኛ፣ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች የአምላክ መንፈስ የላቸውም።—ዮሐ. 14:16, 17

7 በሌላ በኩል ግን የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነና ምን ነገሮችን እንደሚያከናውን ጠንቅቀው ያውቃሉ። በተጨማሪም በይሖዋ መንፈስ ታግዘው የአምላክን መንግሥት በዓለም ዙሪያ በመስበክ በሕይወታቸው ውስጥ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጣሉ። (ዘካ. 4:6) አንተስ በዚህ ሥራ አዘውትረህ እየተካፈልክ ነው? ምናልባትም በአገልግሎት ላይ ሰፋ ያለ ጊዜ በማሳለፍ ወይም ይበልጥ ውጤታማ በመሆን የአምላክን መንግሥት በመስበክ ረገድ ያለህን ችሎታ ለማሻሻል ጥረት ታደርጋለህ? አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም የአገልግሎት ጥራታቸውን ለማሻሻል ጥረት አድርገዋል። ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ የማስረዳት ልማድ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው” በማለት ጽፏል።—ዕብ. 4:12፤ ሥራ 17:2, 3

8, 9. (ሀ) በአገልግሎታችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም ጠቃሚ እንደሆነ የሚያጎሉ ምን ተሞክሮዎች አሉ? (ለ) የአምላክን ቃል የመጠቀም ችሎታችንን ለማሻሻል ምን ማድረግ እንችላለን?

8 አንድ ወንድም ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል ለአንድ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ዳንኤል 2:44⁠ን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ካነበበለት በኋላ የአምላክ መንግሥት እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት እንዴት እንደሚያመጣ አብራራለት። በዚህ ጊዜ ሰውየው “እንዲሁ ከመናገር ይልቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቅስ አውጥተህ ስላነበብክልኝ አመሰግንሃለሁ” አለው። አንድ ወንድም ደግሞ የግሪክ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ለሆነች አንዲት ሴት መጽሐፍ ቅዱስ አውጥቶ ሲያነብላት ሴትየዋ ፍላጎት እንዳላት የሚያሳዩ የተለያዩ ግሩም ጥያቄዎችን ጠየቀችው። በዚህ ጊዜም ቢሆን ወንድም ከባለቤቱ ጋር በመሆን ጥያቄዎቿን ከመጽሐፍ ቅዱስ መለሰላት። ከጊዜ በኋላ ሴትየዋ እንዲህ ብላለች፦ “ከእናንተ ጋር ለመነጋገር ለምን ፈቃደኛ እንደሆንኩ ታውቃለህ? መጽሐፍ ቅዱስን ይዛችሁ ወደ ቤቴ ስለመጣችሁና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስላነበባችሁልኝ ነው።”

9 ጽሑፎቻችን ጠቃሚ እንደሆኑና ለሰዎች መበርከት እንዳለባቸው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ዋነኛው ጽሑፋችን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በአገልግሎት ላይ አዘውትሮ የመጠቀም ልማድ ከሌለህ እንዲህ ለማድረግ ለምን ግብ አታወጣም? የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነና በአካባቢህ ያሉ ሰዎች ለሚያስጨንቋቸው አንዳንድ ችግሮች እንዴት መፍትሔ እንደሚያመጣ የሚናገሩ ጥቂት ጥቅሶችን መምረጥ ትችላለህ። ከዚያም ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል እነዚህን ጥቅሶች ለማንበብ ዝግጅት አድርግ።

የአምላክን ስም በመሸከምህ ኩራት ይሰማህ

10, 11. የአምላክን ስም በመጠቀም ረገድ በኢየሱስና ተከታዮቹ እንደሆኑ በሐሰት በሚናገሩ ሰዎች መካከል ምን ልዩነት ይታያል?

10 “‘እኔ አምላክ እንደ ሆንሁ፣ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ’ ይላል እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW]።” (ኢሳ. 43:12) የይሖዋ ዋነኛ ምሥክር የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክን ስም ለመሸከምና ይህን ስሙን ለሰዎች ለማሳወቅ ያገኘውን መብት እንደ ክብር ይቆጥረው ነበር። (ዘፀአት 3:15ን፣ ዮሐንስ 17:6ን እና ዕብራውያን 2:12ን አንብብ።) እንዲያውም ኢየሱስ የአባቱን ስም ያውጅ ስለነበር “የታመነ ምሥክር” ተብሎ ተጠርቷል።—ራእይ 1:5፤ ማቴ. 6:9

11 ከዚህ በተቃራኒ አምላክና ልጁን እንደሚወክሉ በሐሰት የሚናገሩ በርካታ ሰዎች ለመለኮታዊው ስም ተገቢውን አክብሮት ሳያሳዩ ቀርተዋል፤ እንዲያውም የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውስጥ አውጥተውታል። በቅርቡ ለካቶሊክ ጳጳሳት በአምልኮ ሥነ ሥርዓቶች ላይ “በአራት የዕብራይስጥ ፊደላት የሚወከለውን የሐወሐ የሚለውን የአምላክን ስም መጠቀምም ሆነ መጥራት አይገባም” የሚል መመሪያ መተላለፉ አሁንም ተመሳሳይ መንፈስ እንዳለ ያሳያል። * እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ምንኛ አሳፋሪ ነው!

12. የይሖዋ አገልጋዮች ከ1931 ወዲህ ይሖዋ በሚለው ስም ይበልጥ መታወቅ የጀመሩት እንዴት ነው?

12 እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ክርስቶስም ሆነ ከእሱ በፊት የነበሩት ‘እንደ ደመና ያሉ ታላቅ ምሥክሮች’ የተዉትን አርዓያ በመከተል የአምላክን ስም በመጠቀማቸው ኩራት ይሰማቸዋል። (ዕብ. 12:1) እንዲያውም የአምላክ አገልጋዮች በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም መቀበላቸው ይበልጥ በስሙ እንዲታወቁ አድርጓቸዋል። (ኢሳይያስ 43:10-12ን አንብብ።) በመሆኑም የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ለየት ባለ መንገድ ‘በአምላክ ስም የተጠሩ’ ሕዝቦች ሆነዋል።—ሥራ 15:14, 17

13. ስማችን የሚጠይቅብንን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

13 በግለሰብ ደረጃ በአምላክ ስም ከሚጠሩ ሰዎች የሚጠበቀውን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ስለ አምላክ በታማኝነት መመሥከር አለብን። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። ይሁንና ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እሱ ሳይሰሙስ እንዴት ያምኑበታል? ደግሞስ የሚሰብክላቸው ሳይኖር እንዴት ይሰማሉ? ካልተላኩስ እንዴት ይሰብካሉ?” (ሮም 10:13-15) በተጨማሪም ሲኦል ማቃጠያ ነው እንደሚሉት ያሉ ፈጣሪያችንን የሚያሰድቡ የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችን በዘዴ ማጋለጥ ይኖርብናል፤ በእርግጥም ጨካኝ የሆነውን የዲያብሎስ ባሕርይ የፍቅር አምላክ ለሆነው ለፈጣሪያችን መስጠት እሱን ከመስደብ ተለይቶ አይታይም።—ኤር. 7:31፤ 1 ዮሐ. 4:8፤ ከማርቆስ 9:17-27 ጋር አወዳድር።

14. አንዳንዶች የአምላክን የግል ስም ሲያውቁ ምን አድርገዋል?

14 የሰማዩ አባትህን ስም የመሸከም መብት በማግኘትህ ኩራት ይሰማሃል? ሌሎች ይህን ቅዱስ ስም እንዲያውቁ ትረዳቸዋለህ? በፓሪስ፣ ፈረንሳይ የምትኖር አንዲት ሴት የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ስም እንደሚያውቁ ሰማች፤ ከዚያም ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱሷ ላይ እንድታሳያት ጠየቀቻት። ይህች ሴት መዝሙር 83:18⁠ን ማንበቧ ትልቅ እርምጃ እንድትወስድ አነሳስቷታል። ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በታማኝነት በሌላ አገር በማገልገል ላይ ትገኛለች። በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት የካቶሊክ እምነት ተከታይ የአምላክን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስትመለከት በጣም ከመደሰቷ የተነሳ አልቅሳለች። ይህች ሴት የዘወትር አቅኚ ሆና በማገልገል ረጅም ዓመት አሳልፋለች። በቅርቡ ደግሞ ጃማይካ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ለአንዲት ሴት ከራሷ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የአምላክን ስም ሲያሳዩአት እሷም የደስታ እንባ አንብታለች። በመሆኑም የአምላክን ስም የመሸከም እንዲሁም ልክ እንደ ኢየሱስ ይህን ውድ ስም ለሌሎች የማሳወቅ መብት በማግኘትህ ኩራት ይሰማህ።

“ዓለምን . . . አትውደዱ”

15, 16. እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ ዓለም ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል?

15 “ዓለምንም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች አትውደዱ። ማንም ዓለምን የሚወድ ከሆነ የአብ ፍቅር በውስጡ የለም።” (1 ዮሐ. 2:15) ዓለምና ዓለም የሚያንጸባርቀው ሥጋዊ አስተሳሰብ ይሖዋንም ሆነ ቅዱስ የሆነውን መንፈሱን ይቃወማሉ። በመሆኑም የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች የዓለም ክፍል ባለመሆናቸው ብቻ ረክተው አይኖሩም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ከዓለም ጋር መወዳጀት ከአምላክ ጋር ጠላትነት መፍጠር [ነው]” በማለት የጻፈውን ሐሳብ ስለሚያውቁ ዓለምን በጣም ይጠላሉ።—ያዕ. 4:4

16 ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፈተናዎች ባሉበት በዚህ ዓለም ውስጥ እየኖሩ የያዕቆብን ምክር መከተል ከባድ ሊሆን ይችላል። (2 ጢሞ. 4:10) በመሆኑም ኢየሱስ ተከታዮቹን አስመልክቶ እንዲህ በማለት ጸልዮአል፦ “የምለምንህ ከዓለም እንድታወጣቸው ሳይሆን ከክፉው የተነሳ እንድትጠብቃቸው ነው። እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።” (ዮሐ. 17:15, 16) እንግዲያው ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የዓለም ክፍል ላለመሆን ብርቱ ጥረት አደርጋለሁ? ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌላቸውን በዓላትና ልማዶች እንዲሁም ከአረማዊ አምልኮ የመጡ ባይሆኑም እንኳ የዓለም መንፈስ በግልጽ የሚንጸባረቅባቸውን ድርጊቶች በተመለከተ ያለኝን አቋም ሌሎች ያውቃሉ?’—2 ቆሮ. 6:17፤ 1 ጴጥ. 4:3, 4

17. ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከይሖዋ ጎን እንዲቆሙ የሚያነሳሳቸው ምን ሊሆን ይችላል?

17 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው አቋማችን በዓለም ዘንድ ተቀባይነት እንደማያስገኝልን የታወቀ ነው፤ ይሁንና ይህ አቋማችን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የማወቅ ጉጉት እንዲያድርባቸው ሊያደርግ ይችላል። በእርግጥም እንዲህ ያሉ ሰዎች እምነታችን በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በጥብቅ የተመሠረተ እንዲሁም መላው አኗኗራችንን የሚነካ እንደሆነ ሲመለከቱ ተገቢውን እርምጃ ይወስዱ ይሆናል፤ ይህ እርምጃቸው ለቅቡዓኑ “[አምላክ] ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ” ብለው የተናገሩ ያህል ነው።—ዘካ. 8:23

እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር አሳዩ

18. ለይሖዋና ለሰዎች ፍቅር ማሳየት ምን ነገሮችን ይጨምራል?

18 ኢየሱስ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” ብሏል። እንዲሁም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 22:37, 39) ይህ ዓይነቱ ፍቅር (በግሪክኛ አጋፔ ይባላል) በመሠረታዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ሲሆን የሞራል ግዴታ እንዳለብንና ተገቢ እንደሆነ ተሰምቶን የምናሳየው ፍቅር ነው፤ ይህ ሲባል ግን ስሜት አልባ ነው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከልብ የመነጨ ጥልቅ ፍቅር ነው። (1 ጴጥ. 1:22) እንዲህ ያለው ፍቅር ከራስ ወዳድነት ፍጹም ተቃራኒ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ፍቅር የሚያንጸባርቅ ሰው በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ያደርጋል።—1 ቆሮንቶስ 13:4-7ን አንብብ።

19, 20. ክርስቲያናዊ ፍቅር ኃይል እንዳለው የሚያሳዩ ተሞክሮዎችን ተናገር።

19 ፍቅር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ በመሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎች ሊያደርጓቸው የማይችሏቸውን ነገሮች እንዲያከናውኑ ለምሳሌ በዘር፣ በባሕልና በፖለቲካ እንዳይከፋፈሉ አድርጓቸዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35ን አንብብ፤ ገላ. 5:22) በግ መሰል ሰዎች እንዲህ ያለውን ፍቅር ሲመለከቱ ልባቸው ይነካል። ለምሳሌ ያህል፣ በእስራኤል የሚኖር አንድ አይሁዳዊ ወጣት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘበት ወቅት አይሁዳውያንና ዓረቦች በአንድነት ይሖዋን ሲያመልኩ ሲመለከት በጣም ተገርሞ ነበር። በዚህም ምክንያት በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት የጀመረ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና የቀረበለትን ግብዣም ተቀብሏል። አንተስ ለወንድሞችህ እንዲህ ያለ ከልብ የመነጨ ፍቅር ታሳያለህ? አዳዲስ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መንግሥት አዳራሽ ሲመጡ ዜግነታቸው፣ የቆዳ ቀለማቸው ወይም የኑሮ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን ሞቅ ባለ መንፈስ ለመቀበል ጥረት ታደርጋለህ?

20 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለሁሉም ሰዎች ፍቅር ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። በኤል ሳልቫዶር የምትኖር አንዲት ወጣት አስፋፊ፣ አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑ አንዲት የ87 ዓመት አረጋዊ መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠና ነበር። አንድ ቀን እኚህ ሴት በጠና ታመው ሆስፒታል ገቡ። ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ እህቶች ለአንድ ወር ያህል ቤታቸው ሄደው በመጠየቅ ምግብ እንዲበሉ ይከታተሏቸው ነበር። ከቤተ ክርስቲያናቸው ግን አንድም ሰው ጠይቋቸው አያውቅም። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? እኚህ አረጋዊ ምስሎቻቸውን ያስወገዱ ከመሆኑም በላይ ቤተ ክርስቲያናቸውን መልቀቃቸውን አሳወቁ፤ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናታቸውን ቀጠሉ። አዎን፣ ክርስቲያናዊ ፍቅር ኃይል አለው! ከስብከት ይበልጥ የሰዎችን ልብ ይነካል።

21. የወደፊት ሕይወታችንን አስተማማኝ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

21 ኢየሱስ በቅርቡ የእሱ ተከታዮች እንደሆኑ በሐሰት የሚናገሩ ሰዎችን በሙሉ “ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ” ይላቸዋል። (ማቴ. 7:23) በመሆኑም አብንም ሆነ ወልድን የሚያስከብር የመንፈስ ፍሬ እናፍራ። ኢየሱስ “ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል ሁሉ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራን አስተዋይ ሰው ይመስላል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ 7:24) አዎን እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን በተግባር ካስመሠከርን የአምላክን ሞገስ እናገኛለን፤ እንዲሁም የወደፊት ሕይወታችን በዓለት ላይ የተመሠረተ ያህል አስተማማኝ ይሆናል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጨምሮ በእንግሊዝኛ የተዘጋጁ አንዳንድ ዘመናዊ የካቶሊክ ጽሑፎች በአራት የዕብራይስጥ ፊደላት የሚወከለውን የአምላክን ስም “ያህዌህ” በማለት አስቀምጠውታል።

ታስታውሳለህ?

• የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ከሐሰተኞቹ ተለይተው የሚታወቁት እንዴት ነው?

• እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው እንዲታወቁ የሚያደርጓቸውን አንዳንድ “ፍሬዎች” ጥቀስ።

• ክርስቲያናዊ ፍሬዎችን በማፍራት ረገድ ምን ግቦችን ማውጣት ትችላለህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአገልግሎት ላይ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን የመጠቀም ልማድ አለህ?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ በዓሎችን በተመለከተ ያለህን አቋም ያውቃሉ?