በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ልጆች መንፈሳዊ ሥልጠና የማግኘት መብት አላቸው”

“ልጆች መንፈሳዊ ሥልጠና የማግኘት መብት አላቸው”

“ልጆች መንፈሳዊ ሥልጠና የማግኘት መብት አላቸው”

ታኅሣሥ 9, 2008 የስዊድን የልጆች መብት አካዳሚ “ልጆች መንፈሳዊ ሥልጠና የማግኘት መብት አላቸው” በሚል ጭብጥ አንድ ልዩ ሴሚናር አካሂዶ ነበር። የስዊድን ቤተ ክርስቲያንን፣ ሌሎች የክርስትና ሃይማኖታዊ ቡድኖችን፣ እስልምናን እንዲሁም በሰብዓዊ ጥበብ መምራትን የሚያበረታታውን ንቅናቄ በመወከል የመጡ ተናጋሪዎች በሴሚናሩ ላይ የተለያዩ ሐሳቦችን አቅርበው ነበር።

ከተናጋሪዎቹ አንዱ የሆኑት ቄስ እንዲህ ብለው ነበር፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በልጆች መንፈሳዊነት ረገድ የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና በሚገባ መግለጽ ያዳግታል።” ቅዱሳን መጻሕፍት የልጆችን መንፈሳዊ ፍላጎት የሚያሟሉት በምን መንገድ ነው?

ቄሱ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት “ጥቅሶችና ታሪኮች ልጆች በግላቸው ለማሰላሰል የሚረዷቸውን ትምህርቶች ይዘዋል” ብለዋል። “እንደ ማታለል፣ ይቅር ባይነት፣ ስርየት፣ ጥላቻ፣ መዋረድ፣ ካሳ መክፈል፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ የወንድማማች ፍቅር ማሳየት ባሉት ወሳኝ ጉዳዮች ረገድ [የልጁን] አስተሳሰብ ለመቅረጽ ከሚረዱ ምሳሌዎች መካከል” አንዳንዶቹን ጠቅሰዋል፤ ከዘረዘሯቸው ውስጥ “ስለ አዳምና ሔዋን፣ ስለ ቃየንና አቤል፣ ስለ ዳዊትና ጎልያድ፣ ስለ ኢየሱስ መወለድ፣ ቀረጥ ሰብሳቢ ስለነበረው ዘኬዎስ፣ ስለ አባካኙ ልጅ፣ ስለ ደጉ ሳምራዊ” የሚገልጹት ታሪኮች ይገኙበታል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ ታሪኮች አንድ ሰው ከሕይወቱ ጋር ሊያያይዛቸው፣ ተግባራዊ ሊያደርጋቸው [እንዲሁም] ጠቃሚ ተሞክሮ ሊሆኑት የሚችሉ መመሪያዎች ይሰጣሉ።”

ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ ማበረታታት ጥሩ ነገር እንደሆነ ምንም አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ ልጆች ከቅዱሳን መጻሕፍት ባነበቡት ነገር ላይ ‘በግላቸው ማሰላሰል’ እንዲሁም ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ መድረስ በእርግጥ ይችላሉ?

አዋቂዎች እንኳ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን እንዲረዱ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል። ለአብነት ያህል፣ ‘በግሉ በማሰላሰል’ መንፈሳዊ ነገሮችን በትክክል መረዳት ስላልቻለ አንድ ግለሰብ የሚናገር ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ይህ ሰው ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን ነበር። ሰውየው የኢሳይያስን ትንቢት ያነብ የነበረ ቢሆንም ትርጉሙን መረዳት አልቻለም። ይህ ባለሥልጣን፣ ነቢዩ የተናገረውን መልእክት ለመረዳት ፈልጎ ስለነበር ደቀ መዝሙሩ ፊልጶስ ያቀረበለትን ማብራሪያ በደስታ ተቀብሎታል። (ሥራ 8:26-40) ቅዱሳን መጻሕፍትን ለመረዳት ማብራሪያ ያስፈለገው ይህ ኢትዮጵያዊ ብቻ አይደለም። ሁላችንም በተለይ ደግሞ ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል” ይላል። (ምሳሌ 22:15) ልጆች መመሪያ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ወላጆች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በክርስቲያን ጉባኤ በሚሰጠው ትምህርት ላይ የተመሠረተ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ትምህርት ለልጆቻቸው የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። ልጆች እንዲህ ዓይነት ሥልጠና የማግኘት መብት አላቸው። ልጆች ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ያሠለጠኑ ጎልማሳ ሰዎች’ እንዲሆኑ ለመንፈሳዊ እድገታቸው የሚረዳ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ሥልጠና ከትንሽነታቸው ጀምሮ ሊሰጣቸው ይገባል።—ዕብ. 5:14