በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘መንፈሱና ሙሽራይቱ “ና!” እያሉ ነው’

‘መንፈሱና ሙሽራይቱ “ና!” እያሉ ነው’

‘መንፈሱና ሙሽራይቱ “ና!” እያሉ ነው’

“መንፈሱና ሙሽራይቱም ‘ና!’ እያሉ ነው። . . . የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ።”—ራእይ 22:17

1, 2. ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች በሕይወታችን ውስጥ ምን ቦታ ልንሰጣቸው ይገባል? ለምንስ?

በሕይወታችን ውስጥ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ምን ቦታ ልንሰጣቸው ይገባል? ኢየሱስ ተከታዮቹን ‘ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋቸውን እንዲቀጥሉ’ አሳስቧቸዋል፤ እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ አምላክ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ እንደሚያሟላላቸው ኢየሱስ አረጋግጦላቸዋል። (ማቴ. 6:25-33) ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ከፍተኛ ዋጋ ባለው ዕንቁ የመሰለው ሲሆን አንድ ተጓዥ ነጋዴ ይህን ዕንቁ ሲያገኝ ‘ያለውን ሁሉ በመሸጥ እንደገዛው’ በምሳሌው ላይ ተናግሯል። (ማቴ. 13:45, 46) እኛስ የመንግሥቱን ስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ከምንም ነገር በላይ ትልቅ ቦታ ልንሰጠው አይገባም?

2 ቀደም ባሉት ሁለት የጥናት ርዕሶች ላይ እንደተመለከትነው የአምላክን ቃል በድፍረት መናገራችን እንዲሁም በአገልግሎት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀማችን በአምላክ መንፈስ እንደምንመራ ያሳያል። ይህ መንፈስ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ አዘውትረን እንድንካፈል በመርዳት ረገድም ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ይህን የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ለሁሉም ሰው የቀረበ ግብዣ!

3. ሁሉም ሰዎች ‘መጥተው’ እንዲወስዱ የተጋበዙት ምን ዓይነት ውኃ ነው?

3 የሰው ልጆች በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት አንድ ግብዣ ቀርቦላቸዋል። (ራእይ 22:17ን አንብብ።) ግብዣው ሰዎች ሁሉ ‘መጥተው’ በዓይነቱ ልዩ የሆነውን ውኃ በመውሰድ ጥማቸውን እንዲያረኩ የቀረበ ጥሪ ነው። ይህ ውኃ፣ ሁለት እጅ ሃይድሮጅን እና አንድ እጅ ኦክስጅን ሲቀላቀሉ ከሚገኘው በየቤታችን ካለው ውኃ የተለየ ነው። በምድር ላይ በሕይወት ለመኖር ውኃ አስፈላጊ ቢሆንም ኢየሱስ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሳምራዊት ሴት የተናገረው ግን ስለ ሌላ ዓይነት ውኃ ነበር፤ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ፈጽሞ አይጠማም፤ ከዚህ ይልቅ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ ይሆናል።” (ዮሐ. 4:14) የሰው ልጆች እንዲወስዱት የተጋበዙት ይህ በዓይነቱ ለየት ያለ ውኃ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል።

4. የሰው ልጆች የሕይወትን ውኃ ማግኘታቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ ውኃ ምንን ያመለክታል?

4 የሰው ልጆች እንዲህ ዓይነት ውኃ ማግኘታቸው አስፈላጊ የሆነው የመጀመሪያው ሰው አዳም ከሚስቱ ከሔዋን ጋር በመተባበር ፈጣሪው በሆነው በይሖዋ አምላክ ላይ ባመፀ ጊዜ ነው። (ዘፍ. 2:16, 17፤ 3:1-6) አዳም “እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም እንዳይኖር” ሲባል የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት መኖሪያቸው ከሆነችው ገነት ተባረሩ። (ዘፍ. 3:22) የሰው ዘር የተገኘው ከአዳም በመሆኑ አዳም ኃጢአት ሲሠራ ለሰዎች በሙሉ ሞትን አወረሰ። (ሮም 5:12) የሕይወት ውኃ፣ አምላክ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ብሎም ገነት በሆነች ምድር ላይ ፍጹም ሕይወት አግኝተው ለዘላለም እንዲኖሩ ለማስቻል ያደረጋቸውን ዝግጅቶች በሙሉ ያመለክታል። እነዚህ ዝግጅቶች እውን ሊሆኑ የቻሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ነው።—ማቴ. 20:28፤ ዮሐ. 3:16፤ 1 ዮሐ. 4:9, 10

5. የሰው ልጆች መጥተው “የሕይወትን ውኃ በነፃ [እንዲወስዱ]” የቀረበው ግብዣ ምንጭ ማን ነው? አብራራ።

5 የሰው ልጆች መጥተው “የሕይወትን ውኃ በነፃ [እንዲወስዱ]” የቀረበው ግብዣ ምንጭ ማን ነው? የሰው ልጆች ሕይወት እንዲያገኙ ሲባል በኢየሱስ አማካኝነት የተደረጉት ዝግጅቶች በሙሉ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን በዚያን ጊዜ እነዚህ ዝግጅቶች ‘እንደ ክሪስታል በጠራ የሕይወት ውኃ ወንዝ’ ተመስለዋል። በራእዩ ላይ ይህ ወንዝ “ከአምላክና ከበጉ ዙፋን ወጥቶ [ሲፈስ]” ታይቷል። (ራእይ 22:1) በመሆኑም ሕይወት ሰጪ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዘው ይህ ውኃ የተገኘው የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ ነው። (መዝ. 36:9) “የአምላክ በግ” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይህንን ውኃ ለሰው ልጆች ያዘጋጀው ይሖዋ ነው። (ዮሐ. 1:29) ይህ ምሳሌያዊ ወንዝ ይሖዋ፣ የአዳም አለመታዘዝ በሰው ልጆች ላይ ያመጣውን መዘዝ በሙሉ ለማስወገድ የሚጠቀምበት መንገድ ነው። አዎ፣ “ና!” የሚለው ግብዣ ምንጭ ይሖዋ አምላክ ነው።

6. “የሕይወት ውኃ ወንዝ” መፍሰስ የጀመረው መቼ ነው?

6 “የሕይወት ውኃ ወንዝ” በተሟላ መንገድ የሚፈሰው በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ቢሆንም በ1914 “በጉ” በሰማይ ዙፋን ላይ በተቀመጠበት ወቅት ከጀመረው ‘የጌታ ቀን’ አንስቶ ይህ ወንዝ መፍሰስ ጀምሯል። (ራእይ 1:10) በመሆኑም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሕይወት የሚያስገኙ አንዳንድ ዝግጅቶች ቀርበዋል። እነዚህ ዝግጅቶች የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መልእክት ያካትታሉ፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ‘በውኃ’ ተመስሏል። (ኤፌ. 5:26) የመንግሥቱን ምሥራች ሰምተው እርምጃ በመውሰድ “የሕይወትን ውኃ” እንዲቀበሉ ግብዣ የቀረበው ለሁሉም ሰዎች ነው። ይሁንና በጌታ ቀን ውስጥ ይህን ግብዣ እያቀረቡ ያሉት እነማን ናቸው?

‘ሙሽራይቱ “ና!” ትላለች’

7. ‘በጌታ ቀን’ ውስጥ “ና” የሚለውን ግብዣ መጀመሪያ ያስተጋቡት እነማን ናቸው? ግብዣውን ያቀረቡትስ ለማን ነው?

7 “ና!” የሚለውን ጥሪ መጀመሪያ ያስተጋቡት የሙሽራይቱ ክፍል አባላት የሆኑት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ናቸው። ይህን ግብዣ ያቀረቡት ለማን ነው? መቼም ሙሽራይቱ “ና!” የሚለውን ግብዣ ለራሷ እንደማታቀርብ የታወቀ ነው። ይህን ግብዣ ያቀረበችው ‘ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ በኋላ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ለሚኖራቸው ሰዎች ነው።—ራእይ 16:14, 16ን አንብብ።

8. በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ከ1918 ጀምሮ የይሖዋን ግብዣ እያስተጋቡ እንዳሉ የሚያሳየው ምንድን ነው?

8 የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች ከ1918 አንስቶ ይህንን ግብዣ እያቀረቡ ነው። “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን ላያዩ ይችላሉ” በሚለው በዚያ ዓመት በቀረበው የሕዝብ ንግግር ላይ ከአርማጌዶን ጦርነት በኋላ ብዙዎች በምድር ላይ በገነት የመኖር ተስፋ እንዳላቸው ተገልጾ ነበር። በ1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ ዩ ኤስ ኤ በተካሄደው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከቀረቡት ንግግሮች አንዱ አድማጮች ‘ንጉሡንና መንግሥቱን እንዲያስታውቁ’ የሚያበረታታ ነበር። ይህ ንግግር በምድር ላይ የቀሩት የሙሽራይቱ ክፍል አባላት ለብዙ ሰዎች ግብዣውን ለማቅረብ እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል። በ1929 የታተመው የመጋቢት 15 መጠበቂያ ግንብ በራእይ 22:17 ላይ የተመሠረተ “ደግነት የተንጸባረቀበት ግብዣ” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ርዕሰ ትምህርቱ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ታማኝ የሆኑት ቅቡዓን ቀሪዎች ከልዑሉ ጋር በመሆን ‘ና’ እያሉ ደግነት የተንጸባረቀበት ግብዣ ያቀርባሉ። ይህ መልእክት የእውነትና የጽድቅ ጥማት ላላቸው ሁሉ መታወጅ ይኖርበታል። ይህ አሁኑኑ መከናወን የሚገባው ሥራ ነው።” የሙሽራይቱ ክፍል አባላት ዛሬም ቢሆን ይህንን ግብዣ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።

“የሚሰማም ሁሉ ‘ና!’ ይበል”

9, 10. “ና!” የሚለውን ግብዣ የተቀበሉ ሰዎች እነሱም በምላሹ ይህንን ጥሪ ለሌሎች እንዲያቀርቡ የተጋበዙት እንዴት ነው?

9 “ና!” የሚለውን ጥሪ የሚሰሙ ሰዎችስ ምን እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል? እነሱም “ና!” የሚለውን ጥሪ እንዲያሰሙ ተጋብዘዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የነሐሴ 1, 1932 መጠበቂያ ግንብ በገጽ 232 ላይ እንደሚከተለው ብሎ ነበር፦ “ቅቡዓኑ የመንግሥቱን ምሥራች በመናገር ሥራ ሊካፈሉ የሚፈልጉ ሰዎችን ሁሉ ያበረታቷቸው። እነዚህ ሰዎች የጌታን መልእክት ለማወጅ ለጌታ የታጩ ቅቡዓን መሆን አያስፈልጋቸውም። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች፣ አርማጌዶንን አልፈው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው የሰው ልጆች የሕይወትን ውኃ ለማድረስ እንደተፈቀደላቸው ማወቃቸው በጣም አስደስቷቸዋል።”

10 የነሐሴ 15, 1934 መጠበቂያ ግንብ “ና!” የሚለውን ጥሪ የተቀበሉ ሁሉ ይህን ግብዣ ለሌሎች የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሲያጎላ በገጽ 249 ላይ እንዲህ ብሏል፦ “የኢዮናዳብ ክፍል የሆኑት ክርስቲያኖች፣ የተቀቡ የይሖዋ ምሥክሮች ባይሆኑም እንኳ ኢዩ ጥላ ከሆነለት የቅቡዓን ቡድን ጋር አብረው መሄድና የመንግሥቱን መልእክት ማወጅ ይኖርባቸዋል።” በራእይ 7:9-17 ላይ የተጠቀሱት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ማን እንደሆኑ በ1935 በግልጽ ታወቀ። ይህም የአምላክን ግብዣ ለሌሎች የማስተጋባቱ ሥራ ትልቅ እመርታ እንዲያሳይ ምክንያት ሆኗል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ቁጥራቸው እያደገ የመጣው እጅግ ብዙ ሕዝቦች ይህን ግብዣ የተቀበሉ ሲሆን እነዚህ እውነተኛ አምላኪዎች በአሁኑ ጊዜ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሆነዋል። እነዚህ ሰዎች መልእክቱን በአድናቆት ከተቀበሉ በኋላ ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው በውኃ የተጠመቁ ሲሆን ከሙሽራይቱ ክፍል ጋር በመሆን ሌሎችም ‘መጥተው የሕይወትን ውኃ በነፃ እንዲጠጡ’ በቅንዓት እየጋበዙ ነው።

‘መንፈሱ “ና!” ይላል’

11. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ መንፈስ ቅዱስ ምን ሚና ተጫውቷል?

11 ኢየሱስ ናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ ውስጥ እየሰበከ ሳለ የነቢዩ የኢሳይያስን ጥቅልል ተርትሮ የሚከተለውን አነበበ፦ “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ምሥራች እንዳውጅ ቀብቶኛል፤ ለተማረኩት ነፃነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንድሰብክ፣ የተጨቆኑትን ነፃ እንዳወጣ እንዲሁም በይሖዋ ዘንድ የተወደደውን ዓመት እንድሰብክ ልኮኛል።” በመቀጠልም ኢየሱስ “ይህ አሁን የሰማችሁት የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል ዛሬ ተፈጸመ” በማለት ትንቢቱ በራሱ ላይ እንደሚሠራ ገለጸ። (ሉቃስ 4:17-21) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ . . . እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ሥራ 1:8) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ መንፈስ ቅዱስ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

12. የአምላክ መንፈስ በዛሬው ጊዜ ለሰዎች ግብዣውን በማቅረብ ረገድ ምን ድርሻ አለው?

12 የአምላክ መንፈስ በዛሬው ጊዜ ለሰዎች ግብዣውን በማቅረብ ረገድ ምን ድርሻ አለው? የመንፈስ ቅዱስ ምንጭ ይሖዋ ነው። ይሖዋ የሙሽራይቱ ክፍል አባላት ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲረዱ በመንፈሱ ተጠቅሞ ልባቸውን እና አእምሯቸውን ይከፍትላቸዋል። ቅቡዓን በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው ሰዎች ግብዣውን እንዲያስተጋቡና ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን እንዲያብራሩ መንፈሱ ያነሳሳቸዋል። ግብዣውን ተቀብለው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ይህን ግብዣ ለሌሎች ስለሚያስተጋቡት ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? መንፈሱ ከእነሱም ጋር በተያያዘ የሚጫወተው ሚና አለ። እነዚህ ሰዎች “በመንፈስ ቅዱስ ስም” የተጠመቁ እንደመሆናቸው መጠን ከመንፈሱ ጋር የሚተባበሩ ከመሆኑም ሌላ መንፈሱ እንደሚረዳቸው ይተማመናሉ። (ማቴ. 28:19) ቅቡዓኑም ሆኑ ቁጥራቸው እየጨመረ ያለው እጅግ ብዙ ሕዝቦች የሚሰብኩትን መልእክትም እንውሰድ። መልእክቱ የሚገኘው በአምላክ መንፈስ መሪነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። በመሆኑም ግብዣው የሚቀርበው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው ሊባል ይችላል። በእርግጥም የሚመራን ይህ መንፈስ ነው። ታዲያ ይህን ማወቃችን ግብዣውን ለሌሎች በማቅረቡ ሥራ ያለንን ተሳትፎ እንዴት ሊነካው ይገባል?

“‘ና!’ እያሉ ነው”

13. “መንፈሱና ሙሽራይቱም ‘ና!’ እያሉ ነው” የሚለው ዓረፍተ ነገር ምን ይጠቁማል?

13 “መንፈሱና ሙሽራይቱ” አንድ ጊዜ “ና!” ብለው ብቻ አላቆሙም። እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ግስ ቀጣይነት ያለውን ድርጊት ያመለክታል። አዲስ ዓለም ትርጉም ይህንን ከግምት በማስገባት ጥቅሱን እንዲህ ሲል አስቀምጦታል፦ “መንፈሱና ሙሽራይቱም ‘ና!’ እያሉ ነው።” ይህ የአምላክን ግብዣ ዘወትር እንደሚያቀርቡ ያሳያል። ግብዣውን ሰምተው እርምጃ ስለሚወስዱት ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነሱም “ና!” ይላሉ። እውነተኛ አምላኪ የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ ‘በይሖዋ መቅደስ ውስጥ ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት እንደሚያቀርቡ’ ተገልጿል። (ራእይ 7:9, 15) ‘ቀንና ሌሊት አገልግሎት ያቀርባሉ’ ሲባል ምን ማለት ነው? (ሉቃስ 2:36, 37⁠ን፤ የሐዋርያት ሥራ 20:31ን እና 2 ተሰሎንቄ 3:8ን አንብብ።) ከአረጋዊቷ ነቢይት ከሐና እንዲሁም ከሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ መመልከት እንደምንችለው ‘ቀንና ሌሊት አገልግሎት ማቅረብ’ ሲባል በአገልግሎት በትጋት እንዲሁም ሁልጊዜ መካፈልን ያመለክታል።

14, 15. ዳንኤል አምልኮን አዘውትሮ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

14 ነቢዩ ዳንኤልም አምልኮን አዘውትሮ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን በሕይወቱ አሳይቷል። (ዳንኤል 6:4-10, 16ን አንብብ።) ለአምላክ የሚያቀርበው አምልኮ ክፍል የሆነውን የጸሎት ልማዱን ለአንድ ወር እንኳ ለማቋረጥ ፈቃደኛ አልነበረም፤ እንዲህ ማድረጉ በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ እንደሚያስጥለው ቢያውቅም “ቀድሞ ያደርግ እንደ ነበረው በቀን ሦስት ጊዜ ተንበርክኮ” መጸለዩን ቀጥሏል። ዳንኤል የወሰደው ይህ እርምጃ ለይሖዋ ዘወትር ከሚያቀርበው አምልኮ የሚበልጥበት ምንም ነገር እንደሌለ ለሚመለከቱት ሁሉ ግልጽ እንዲሆን አድርጓል።—ማቴ. 5:16

15 ዳንኤል በአንበሶቹ ጉድጓድ ውስጥ በተጣለ ማግስት ንጉሡ ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ በመሄድ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፤ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሎአልን?” ብሎ ተጣራ። ዳንኤልም ወዲያውኑ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጠ፦ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ ንጉሥ ሆይ፤ በፊቱ ቅን ሆኜ ስለ ተገኘሁ፣ በአንተም ፊት በደል ስላልተገኘብኝ፣ አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፤ እነርሱም አልጐዱኝም።” ዳንኤል “ሁልጊዜ” ያገለግለው ስለነበር ይሖዋ ባርኮታል።—ዳን. 6:19-22

16. ዳንኤል የተወው ምሳሌ በአገልግሎት ያለንን ተሳትፎ በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች እንድንጠይቅ ሊያነሳሳን ይገባል?

16 ዳንኤል መንፈሳዊ ልማዱን ከማቋረጥ ይልቅ ሞትን መርጦ ነበር። እኛስ? የአምላክን መንግሥት ምሥራች አዘውትረን ለማወጅ ስንል ምን መሥዋዕቶችን እየከፈልን ነው? አሊያም መሥዋዕትነት ለመክፈል ምን ያህል ፈቃደኞች ነን? ስለ ይሖዋ ለሌሎች ሳንናገር አንድም ወር ሊያልፍብን አይገባም! እንዲያውም በተቻለ መጠን በየሳምንቱ በአገልግሎት ለመካፈል ጥረት ማድረግ አይኖርብንም? አቅማችን በጣም ውስን ቢሆንም እንኳ በወሩ ውስጥ 15 ደቂቃ ማገልገል ከቻልን ያንን ሪፖርት ማድረግ ይገባናል። ለምን? ምክንያቱም ከመንፈሱና ከሙሽራይቱ ጋር በመሆን “ና!” ማለታችንን መቀጠል እንፈልጋለን። አዎ፣ አዘውታሪ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ሆነን ለመቀጠል የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን።

17. የይሖዋን ግብዣ ለማቅረብ የሚያስችሉንን የትኞቹን አጋጣሚዎች ልናሳልፋቸው አይገባም?

17 የይሖዋን ግብዣ ለሰዎች የምናቀርበው ለአገልግሎት በመደብነው ጊዜ ብቻ ሳይሆን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ሊሆን ይገባል። በሌሎች ጊዜያት ለምሳሌ ገበያ ስንወጣ፣ በጉዞ ላይ ስንሆን፣ በምንዝናናበት ጊዜ፣ በሥራ ቦታ ወይም ወደ ትምህርት ቤት ስንሄድ የምናገኛቸውን የተጠሙ ሰዎች ‘መጥተው የሕይወትን ውኃ በነፃ እንዲወስዱ’ መጋበዝ መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! የመንግሥት ባለሥልጣናት በስብከቱ ሥራችን ላይ እገዳ ቢጥሉ እንኳ በዘዴ መስበካችንን እንቀጥላለን፤ ለምሳሌ ከቤት ወደ ቤት ስንሠራ በአንድ አካባቢ ጥቂት ቤቶችን ብቻ ማንኳኳት ወይም መደበኛ ባልሆነ መንገድ የምናከናውነውን ምሥክርነት ከፍ ማድረግ እንችላለን።

“ና!” የሚለውን ግብዣ ማቅረባችሁን ቀጥሉ

18, 19. ከአምላክ ጋር አብረህ የመሥራት መብትህን ከፍ አድርገህ እንደምትመለከተው እንዴት ማሳየት ትችላለህ?

18 መንፈሱና ሙሽራይቱ፣ የሕይወትን ውኃ ለተጠማ ሁሉ “ና!” የሚለውን ግብዣ ከዘጠና ለሚበልጡ ዓመታት ሲያቀርቡ ቆይተዋል። አንተስ ይህንን አስደሳች ግብዣ ሰምተሃል? ከሆነ ይህንን ግብዣ ለሌሎች እንድታቀርብ እናበረታታሃለን።

19 የይሖዋ ፍቅራዊ ግብዣ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቀጥል የምናውቀው ነገር የለም፤ ሆኖም እኛም ለግብዣው ምላሽ በመስጠት “ና!” ማለታችን ከአምላክ ጋር አብረን ለመሥራት ያስችለናል። (1 ቆሮ. 3:6, 9) ይህ እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው! ይህን መብት ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው እናሳይ፤ እንዲሁም በስብከቱ ሥራ ሳናቋርጥ በመካፈል “የምስጋና መሥዋዕት ዘወትር ለአምላክ እናቅርብ።” (ዕብ. 13:15) በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያለን ሰዎች ከሙሽራይቱ ክፍል ጋር በመሆን “ና!” ማለታችንን እንቀጥል። ብዙዎች ‘የሕይወትን ውኃ በነፃ እንዲወስዱ’ ምኞታችን ነው!

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• “ና!” የሚለው ግብዣ የቀረበው ለእነማን ነው?

• “ና!” የሚለው ግብዣ ምንጭ ይሖዋ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

• “ና!” የሚለውን ግብዣ በማቅረብ ረገድ መንፈስ ቅዱስ ምን ሚና ይጫወታል?

• በአገልግሎታችን አዘውትረን ለመካፈል ጥረት ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/​ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

“ና!” እያሉ ነው

1914

5,100 አስፋፊዎች

1918

ብዙዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ

1922

“ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ”

1929

ታማኞቹ ቀሪዎች “ና!” ይላሉ

1932

“ና!” የሚለው ግብዣ ከቅቡዓኑ በተጨማሪ ለሌሎችም ቀረበ

1934

የኢዮናዳብ ክፍል በስብከቱ ሥራ እንዲካፈል ተጋበዘ

1935

“እጅግ ብዙ ሕዝብ” ማን እንደሆነ ታወቀ

2009

7,313,173 አስፋፊዎች