ወጣቶች ፈጣሪያቸውን እንዲያስቡ የሚረዳ ጠቃሚ መሣሪያ
ወጣቶች ፈጣሪያቸውን እንዲያስቡ የሚረዳ ጠቃሚ መሣሪያ
ጠቢቡ ሰለሞን የዛሬ 3,000 ዓመት ገደማ “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” በማለት ጽፎ ነበር። (መክ. 12:1) ክርስቲያን ወጣቶች ይህን ለማድረግ የሚረዳቸው ተጨማሪ መሣሪያ አግኝተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ከግንቦት 2008 እስከ ጥር 2009 ባደረጉት “በአምላክ መንፈስ መመራት” የሚል ርዕስ ያለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 * የተባለ መጽሐፍ ወጥቶ ነበር።
በመጽሐፉ ሽፋን ውስጠኛ ገጽ ላይ ከበላይ አካሉ ለወጣቶች የተጻፈ ደብዳቤ ይገኛል። ደብዳቤው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች፣ በዛሬው ጊዜ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ተጽዕኖዎችና ፈተናዎች ለመቋቋም እንዲረዱህ እንዲሁም ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ውሳኔዎችን ማድረግ የምትችልባቸውን መንገዶች እንዲጠቁሙህ ልባዊ ጸሎታችን ነው።”
ወላጆች ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ” ለማሳደግ መፈለጋቸው የተገባ ነው። (ኤፌ. 6:4) ይሁንና በርካታ ወጣቶች የጉርምስና ዕድሜ ላይ ሲደርሱ በራሳቸው መተማመን ስለሚያቅታቸው መመሪያ ለማግኘት አጥብቀው ይሻሉ። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ካሏችሁ ልጆቻችሁ በዚህ መጽሐፍ በሚገባ እንዲጠቀሙ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል።
▪ የዚህ መጽሐፍ የራሳችሁ ቅጂ ይኑራችሁ፤ እንዲሁም መጽሐፉን በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ይህ መጽሐፉን ከማንበብ የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። የመጽሐፉን መንፈስም ለመረዳት ጥረት አድርጉ። ይህ መጽሐፍ ለወጣቶች ትክክልና ስህተት የሆነውን ከመንገር ባለፈ “የማስተዋል ችሎታቸውን” ለማሠልጠን የሚረዱ ሐሳቦች ይዟል። (ዕብ. 5:14) ከዚህም በተጨማሪ ትክክለኛ ለሆነው ነገር እንዴት አቋም መውሰድ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን ይሰጣል። ለምሳሌ፣ ምዕራፍ 15 (“የእኩዮቼን ተጽዕኖ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?”) ወጣቶች ‘እንቢ’ እንዲሉ ከማበረታታት ያለፈ ምክር ይሰጣል። በምዕራፉ ላይ ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉ ዘዴዎችን እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ እንዲሁም በሕይወታቸው ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች እንዴት መልስ መስጠት እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ሐሳቦች ቀርበዋል፤ እነዚህ ነጥቦች ወጣቶች “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት” እንደሚችሉ ያሠለጥኗቸዋል።—ቆላ. 4:6
▪ አንባቢውን ለማሳተፍ ተብለው የተዘጋጁትን የመጽሐፉን ክፍሎች በሚገባ ተጠቀሙባቸው። እነዚህ ክፍሎች የተዘጋጁት ለወጣቶች ቢሆንም እናንተም ስሜታችሁን ብትገልጹ ምክንያታዊ እንደሆነ የሚሰማችሁ ክፍል ካለ በራሳችሁ ቅጂ ላይ ሐሳባችሁን ለምን አታሰፍሩም? * ለምሳሌ ያህል፣ የፍቅር ጓደኝነት መጀመርን አስመልክቶ በገጽ 16 ላይ የቀረቡትን ሐሳባችሁን እንድትገልጹ የሚጋብዙ ሁለት ጥያቄዎች በምታነቡበት ጊዜ በልጃችሁ ዕድሜ ላይ በነበራችሁበት ወቅት ምን ይሰማችሁ እንደነበር ለማስታወስ ሞክሩ። በዚያን ወቅት ልትመልሱ ትችሉት የነበረውን መልስ ክፍት ቦታው ላይ ማስፈር ትፈልጉ ይሆናል። ከዚያም እንዲህ በማለት ራሳችሁን መጠየቅ ትችላላችሁ፦ ‘ዓመታት ሲያልፉ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝ አመለካከት ምን ያህል ተለውጧል? የጉርምስናን ዕድሜ ካለፍኩ በኋላ ምን ማስተዋል አግኝቻለሁ? ይህንንስ ለልጄ ጥሩ አድርጌ መንገር የምችለው እንዴት ነው?’
▪ ለልጃችሁ ነፃነት ስጡት። አንባቢውን የሚያሳትፉት የመጽሐፉ ክፍሎች የተዘጋጁት ልጃችሁ የልቡን አውጥቶ በጽሑፍ እንዲያሰፍር አሊያም ለራሱ መልስ እንዲሰጥ ለማበረታታት ነው። ዓላማችሁ ልጃችሁ በመጽሐፉ ላይ የጻፈውን ሳይሆን በልቡ ውስጥ ያለውን ማግኘት ሊሆን ይገባል። በገጽ 3 ላይ የሚገኘው “ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ” የሚለው ክፍል የሚከተለውን ሐሳብ ይዟል፦ “በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ በመጽሐፋቸው ላይ ሐሳባቸውን በሐቀኝነት እንዲያሰፍሩ ለማበረታታት በተወሰነ መጠን ነፃነት ስጧቸው። መጽሐፋቸው ላይ ስላሰፈሯቸው ነገሮች ከጊዜ በኋላ በግልጽ ይነግሯችሁ ይሆናል።”
ለቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚረዳ መሣሪያ
የወጣቶች ጥያቄ፣ ጥራዝ 2 በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ልትጠቀሙበት የምትችሉት ግሩም መሣሪያ ነው። በእርግጥ መጽሐፉ ለእያንዳንዱ አንቀጽ የተዘጋጁ ጥያቄዎች የሉትም፤ ታዲያ መጽሐፉን ለጥናት ልትጠቀሙበት የምትችሉት እንዴት ነው? ለልጆቻችሁ ከሁሉ የተሻለ የሚሆነውን መንገድ በመጠቀም የራሳችሁን የአጠናን ዘዴ ለምን አትከተሉም?
ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ቤተሰቦች በገጽ 132 እና 133 ላይ በሚገኘው “የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም” በሚለው ሣጥን ላይ ሲወያዩ ልምምድ የሚያደርጉበት ጊዜ ይመድቡ ይሆናል። በሣጥኑ ውስጥ የሚገኘው የመጀመሪያ ጥያቄ ልጃችሁ ይበልጥ ፈታኝ የሆነበትን ጉዳይ ለይቶ እንዲጠቅስ ሊረዳው ይችላል። ሁለተኛው ጥያቄ፣ እንዲህ ያለው ተጽዕኖ ሊያጋጥም የሚችልበትን ሁኔታ እንዲናገር ይጋብዘዋል። ልጃችሁ ለተጽዕኖው ቢሸነፍ ወይም ተጽዕኖውን ቢቋቋም ውጤቱ ምን እንደሚሆን ካሰበበት በኋላ ከታች ባለው “እኩዮችህ ሲያሾፉብህ” በሚለው የሣጥኑ ክፍል ላይ ልጃችሁ የሚደርስበትን ጫና ለመቀበል ወይም አቅጣጫውን ማስቀየስ አሊያም ወደ እኩዮቹ ለማዞር የሚያስችሉትን መልሶች ማስፈር ይችላል። ልጃችሁ አዳዲስ ሐሳቦችን እንዲያፈልቅ እንዲሁም ሳይሸማቀቅና ሳይፈራ በሙሉ እምነት ለእኩዮቹ የሚሰጠው መልስ እንዲያዘጋጅ እርዱት።—መዝ. 119:46
ለውይይት የሚረዳ መሣሪያ
የወጣቶች ጥያቄ፣ ጥራዝ 2 ወጣቶች ከወላጆቻቸው ጋር በግልጽ እንዲወያዩ ያበረታታል። ለምሳሌ ያህል፣ “ከአባባ ወይም ከእማማ ጋር ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ማውራት (ከገጽ 63-64) እንዲሁም የምችለው እንዴት ነው?”“ወላጆችህን አነጋግራቸው!” (ገጽ 189) የሚሉት ሣጥኖች ለመነጋገር አስቸጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ለመጀመር የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን ይዘዋል። አንዲት የ13 ዓመት ልጅ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ይህ መጽሐፍ በአእምሮዬ ስለሚመላለሱ ጉዳዮች ሌላው ቀርቶ ስለፈጸምኳቸው ነገሮች እንኳ ለወላጆቼ ለመናገር ድፍረት እንዳገኝ ረድቶኛል።”
መጽሐፉ ልጆቻችሁ ከእናንተ ጋር በግልጽ እንዲወያዩ የሚያበረታታባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ “ምን ይመስልሃል?” የሚል ርዕስ ያለው ሣጥን ይገኛል። በዚህ ሣጥን ውስጥ ያሉትን ጥያቄዎች ለክለሳ ብቻ ሳይሆን ከቤተሰብ ጋር ውይይት ለማድረግም መጠቀም ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ “ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች” የሚል ርዕስ ያለው ሣጥን ይገኛል። ይህ ሣጥን ወጣቶች በምዕራፉ ላይ የተማሩትን ነገር በተግባር የሚያውሉባቸውን መንገዶች ለይተው ለመጻፍ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። “ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች” በሚለው ሣጥን ውስጥ የመጨረሻው ሐሳብ “ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር . . .” የሚል ዓረፍተ ነገር ይዟል። ይህ ደግሞ ወጣቶች ምክር ለማግኘት ወደ ወላጆቻቸው ዘወር እንዲሉ ያበረታታቸዋል።
ልባቸውን ለመንካት ጣሩ!
ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ግባችሁ የልጆቻችሁን ልብ መንካት ነው። የወጣቶች ጥያቄ፣ ጥራዝ 2 ይህንን ለማድረግ ይረዳችኋል። አንድ አባት በዚህ መጽሐፍ በመጠቀም ከሴት ልጁ ጋር ልብ ለልብ መወያየት የቻለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
“እኔና ሬቤካ በእግራችን፣ በብስክሌት ወይም በመኪና ለመንሸራሸር የምንመርጣቸው አንዳንድ ጥሩ ቦታዎች አሉ። እነዚህ ቦታዎች ልጄ የልቧን አውጥታ ለማውራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩላት ተገንዝቤያለሁ።
“ከዚህ መጽሐፍ ላይ መጀመሪያ የተወያየነው የበላይ አካሉ በጻፈው ደብዳቤና ‘ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ’ በሚለው ክፍል ላይ ነበር። በገጽ 3 ላይ እንደተገለጸው ልጄ ምንም ሳትሸማቀቅ በመጽሐፏ ላይ ሐሳቧን በግልጽ ማስፈር እንደምትችል ገለጽኩላት። ምን እንደጻፈች ለማወቅ መጽሐፏን እንደማላይ አረጋገጥኩላት።
“ሬቤካ እንድንወያይባቸው የምትፈልጋቸውን ምዕራፎች በቅደም ተከተል እንድትመርጥ ጠየቅኳት። መጀመሪያ ከመረጠቻቸው ምዕራፎች አንዱ ‘የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን መጫወት ይኖርብኛል?’ የሚለው ነበር። ይህንን ምዕራፍ ትመርጣለች ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም ነበር! ሆኖም ይህንን የመረጠችበት ምክንያት ነበራት። ከጓደኞቿ መካከል አብዛኞቹ ዘግናኝ የሆነ ጌም ይጫወታሉ! እነዚህ ጨዋታዎች የዓመፅ ድርጊቶችን በግልጽ የሚያሳዩና ጸያፍ የሆነ ንግግር የያዙ እንደሆኑ በጭራሽ አላውቅም ነበር! ይህን ሁሉ ያወቅኩት ‘ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች’ በሚለው ገጽ 251 ላይ በሚገኘው ሣጥን ላይ ስንወያይ ነው። ይህ ሣጥን ሬቤካ እንዲህ ዓይነት ጌም እንድትጫወት ግፊት ቢደረግባት የምትሰጠውን መልስ እንድታዘጋጅም ረድቷታል።
“በአሁኑ ወቅት ሬቤካ መጽሐፏ ላይ የጻፈችውን ምንም ሳትደብቅ ትነግረኛለች። ያለ ምንም ችግር በነፃነት እንወያያለን። የምናነበው ተራ በተራ ሲሆን ካነበብን በኋላ ሥዕሎቹንና ሣጥኖቹን ጨምሮ መጽሐፉ ላይ ስላሉት ነገሮች በሙሉ እንድንነጋገር ትፈልጋለች። ይህም በእሷ ዕድሜ እያለሁ ስላጋጠሙኝ ሁኔታዎች እንድነግራት አጋጣሚ ይፈጥርልኛል፤ እሷም በተራዋ በአሁኑ ጊዜ ስላለው ሁኔታ ትነግረኛለች። ስለማንኛውም ነገር ከመናገር ወደኋላ አትልም!”
ወላጆች፣ ይህ መጽሐፍ ሲወጣ በጣም እንደተደሰታችሁ ምንም ጥርጥር የለውም። አሁን ይህን መጽሐፍ ጥሩ አድርጋችሁ ለመጠቀም የሚያስችል አጋጣሚ ተከፍቶላችኋል። ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 ለቤተሰባችሁ በረከት እንደሚሆን የበላይ አካሉ ተስፋ ያደርጋል። ሁላችሁንም በተለይ ደግሞ ውድ የሆኑት ወጣቶቻችንን ‘በመንፈስ መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ’ እንዲረዳቸው ምኞታችን ነው።—ገላ. 5:16
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 አሁን በአማርኛ አይገኝም።
^ አን.6 በመጽሐፉ ላይ ከቀረቡት አንባቢውን የሚያሳትፉ ሣጥኖች አንዳንዶቹ በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ይሠራሉ። ለምሳሌ “ቁጣህን መቆጣጠር” የሚለው ሣጥን (ገጽ 221) ለልጆቻችሁ ጠቃሚ እንደሆነ ሁሉ ለእናንተም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። “የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም” (ከገጽ 132-133)፣ “ወርኃዊ በጀት”፣ (ገጽ 163) “ግቦቼ” (ገጽ 314) ከሚሉት ሣጥኖች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንድ ወጣቶች ምን ይላሉ?
“የወጣቶች ጥያቄ፣ ጥራዝ 2 እርሳስህን ይዘህ እያሰላሰልክ በእርጋታ ልታነበው የሚገባ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉን የግል ማስታወሻ መጻፊያችን አድርገን እንድንጠቀምበት ተደርጎ መዘጋጀቱ ሕይወታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንዴት መምራት እንደምንችል እያሰላሰልን ለማንበብ አጋጣሚ ይፈጥራል።”—ኒኮላ
“የፍቅር ጓደኛ እንድይዝ ከፍተኛ ጫና ይደረግብኛል፤ እንዲያውም አንዳንዶች ይህን የሚያደርጉት ለእኔ በማሰብ ነው። ይሁንና ሰዎች ምንም አሉኝ ምን፣ የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት እንዳልደረስኩ እንድገነዘብ የዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ክፍል ረድቶኛል።”—ካትሪና
“‘ለመጠመቅ እያሰብክ ነው?’ የሚለው ሣጥን ስጠመቅ ያደረግኩትን ውሳኔ የበለጠ በቁም ነገር እንድመለከተው ረድቶኛል። የጥናትና የጸሎት ልማዴን እንድመረምር አነሳስቶኛል።”—አሽሊ
“ክርስቲያን የሆኑት ወላጆቼ ከሕፃንነቴ ጀምሮ ያስተማሩኝ ቢሆንም ይህ መጽሐፍ በሕይወቴ ውስጥ ልወስዳቸው ስለሚገቡኝ እርምጃዎች ቆም ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል። ከዚህም በተጨማሪ ከወላጆቼ ጋር የበለጠ በግልጽ እንድነጋገር ረድቶኛል።”—ዛሚራ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች፣ ይህንን መጽሐፍ በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርጉ
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዋና ግባችሁ የልጆቻችሁን ልብ መንካት ይሁን