በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የመንፈስን ሰይፍ” ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቀሙበት

“የመንፈስን ሰይፍ” ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቀሙበት

“የመንፈስን ሰይፍ” ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቀሙበት

“የመንፈስን ሰይፍ ይኸውም የአምላክን ቃል ተቀበሉ።”—ኤፌ. 6:17

1, 2. ተጨማሪ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ማስፈለጋቸው ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

ኢየሱስ የሕዝቡን መንፈሳዊ ፍላጎት በተመለከተ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ “አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ጌታ ወደ መከር ሥራው ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።” ኢየሱስ እንዲህ በማለት ብቻ አልተወሰነም። ከላይ ያለውን ሐሳብ ከተናገረ በኋላ “አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ጠርቶ” በስብከቱ ወይም ‘በመከሩ ሥራ’ እንዲካፈሉ ላካቸው። (ማቴ. 9:35-38፤ 10:1, 5) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ተመሳሳይ ሥራ እንዲሠሩ “ሌሎች ሰባ ሰዎች [ከሾመ በኋላ] . . . ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው።”—ሉቃስ 10:1, 2

2 ዛሬም ተጨማሪ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በጣም ያስፈልጋሉ። በ2009 የአገልግሎት ዓመት በመላው ዓለም በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ሰዎች ቁጥር 18,168,323 ነበር። ይህ ቁጥር ከአጠቃላዩ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ነው። በእርግጥም አዝመራው ለአጨዳ ደርሷል። (ዮሐ. 4:34, 35) በመሆኑም ተጨማሪ ሠራተኞች ለማግኘት መጸለይ ይኖርብናል። ይሁንና በዚህ ብቻ ሳንወሰን ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ የምንችለው እንዴት ነው? ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት በምንካፈልበት ጊዜ የበለጠ ውጤታማ አገልጋዮች ለመሆን ጥረት በማድረግ ነው።—ማቴ. 28:19, 20፤ ማር. 13:10

3. የአምላክ መንፈስ ይበልጥ ውጤታማ አገልጋዮች እንድንሆን በመርዳት ረገድ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው እንዴት ነው?

3 በመጀመሪያው የጥናት ርዕስ ላይ በአምላክ መንፈስ መመራት “የአምላክን ቃል በድፍረት መናገር” እንድንችል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተመልክተናል። (ሥራ 4:31) ይህ መንፈስ ውጤታማ አገልጋዮች እንድንሆንም ሊረዳን ይችላል። በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን የሚረዳን አንዱ ዘዴ ይሖዋ አምላክ የሰጠንን ግሩም መሣሪያ ማለትም በጽሑፍ የሰፈረውን ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ መጠቀም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የመንፈስ ቅዱስ ውጤት ነው። (2 ጢሞ. 3:16) መልእክቱ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው። በመሆኑም በአገልግሎት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ውጤታማ በሆነ መንገድ ስንጠቀም በመንፈስ ቅዱስ እየተመራን ነው። ይህንን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ከማየታችን በፊት የአምላክ ቃል ምን ያህል ኃይል እንዳለው እስቲ እንመልከት።

‘የአምላክ ቃል ኃይለኛ ነው’

4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መልእክት አንድ ሰው ምን ዓይነት ለውጥ እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይችላል?

4 የአምላክ ቃል ወይም መልእክት ታላቅ ኃይል አለው! (ዕብ. 4:12) የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በምሳሌያዊ አነጋገር አጥንትንና መቅኒን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ስለሚገባ ከየትኛውም ሰው ሠራሽ ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው ሊባል ይችላል። የቅዱሳን መጻሕፍት እውነት ወደ አንድ ሰው ልብ ዘልቆ በመግባት እንዲሁም ሐሳቡንና ስሜቱን በመንካት ውስጣዊ ማንነቱ በግልጽ እንዲታይ ያደርጋል። ይህ እውነት ኃይል ስላለው አንድ ሰው እውነተኛ ለውጥ እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይችላል። (ቆላስይስ 3:10ን አንብብ።) አዎ፣ የአምላክ ቃል የሰዎችን ሕይወት ሊለውጥ ይችላል!

5. መጽሐፍ ቅዱስ የሚመራን በየትኞቹ መንገዶች ነው? ይህስ ምን ጥቅም ያስገኛል?

5 ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ተወዳዳሪ የሌለው ጥበብ ይዟል። በዚህ አስቸጋሪና ውጥንቅጡ የወጣ ዓለም ውስጥ ሰዎች ሕይወታቸውን በተሳካ መንገድ መምራት የሚችሉበትን አቅጣጫ የሚጠቁም ጠቃሚ ሐሳብ ይዟል። የአምላክ ቃል በቅርባችን ያለው ብቻ ሳይሆን ከርቀት ያለው መንገድም እንዲታየን ብርሃን ይሆነናል። (መዝ. 119:105) ችግሮች ሲያጋጥሙን ወይም ከጓደኛና ከመዝናኛ ምርጫ እንዲሁም ከሥራ፣ ከአለባበስ እና ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር የተያያዙ ውሳኔዎች ስናደርግ የአምላክ ቃል ይህ ነው የማይባል እርዳታ ያበረክትልናል። (መዝ. 37:25፤ ምሳሌ 13:20፤ ዮሐ. 15:14፤ 1 ጢሞ. 2:9) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን ከሌሎች ጋር ተስማምተን ለመኖር ያስችለናል። (ማቴ. 7:12፤ ፊልጵ. 2:3, 4) የአምላክ ቃል በምሳሌያዊ ሁኔታ ከፊታችን ላለው መንገድ ብርሃን እንዲሆንልን ከፈቀድን የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የወደፊቱን ሕይወታችንን እንዴት እንደሚነኩት ማስተዋል እንችላለን። (1 ጢሞ. 6:9) ከዚህም በተጨማሪ ቅዱሳን መጻሕፍት አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለው ዓላማ ምን እንደሆነ ይነግሩናል፤ ይህም ከዚህ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወታችንን እንድንመራ ይረዳናል። (ማቴ. 6:33፤ 1 ዮሐ. 2:17, 18) አንድ ሰው በአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ ከሆነ ሕይወቱ ትርጉም ያለው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም!

6. በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል ኃይል ያለው መሣሪያ ነው?

6 በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ኃይለኛ መሣሪያ በመሆን እንደሚያገለግለንም አስቡ። ጳውሎስ የአምላክን ቃል ‘የመንፈስ ሰይፍ’ ሲል ጠርቶታል። (ኤፌሶን 6:12, 17ን አንብብ።) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መልእክት ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ከዋለ ሰዎችን ከሰይጣን ቁጥጥር ነፃ ሊያወጣቸው ይችላል። መልእክቱ የሰዎችን ሕይወት የሚያጠፋ ሳይሆን የሚያድን ሰይፍ ነው። ታዲያ ይህን መሣሪያ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ጥረት ማድረግ አይገባንም?

በአግባቡ ተጠቀሙበት

7. “የመንፈስን ሰይፍ” በሚገባ መጠቀምን መማር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

7 አንድ ወታደር በጦርነት ላይ መሣሪያዎቹን ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊጠቀምባቸው የሚችለው ጥሩ ልምምድ ካደረገና አጠቃቀማቸውን በሚገባ ከተማረ ብቻ ነው። “የመንፈስን ሰይፍ” በመንፈሳዊ ውጊያ ላይ ከመጠቀም ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ጳውሎስ “የእውነትን ቃል በአግባቡ በመጠቀም ራስህን ተቀባይነት እንዳለውና ምንም የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ አድርገህ በአምላክ ፊት ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ” ሲል ጽፏል።—2 ጢሞ. 2:15

8, 9. የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በትክክል ለመረዳት ምን ሊጠቅመን ይችላል? ምሳሌ ስጥ።

8 በአገልግሎታችን ላይ ‘የእውነትን ቃል በአግባቡ ለመጠቀም’ ምን ሊረዳን ይችላል? መልእክቱን ለሌሎች በግልጽ ለማስተላለፍ መጀመሪያ እኛ ራሳችን መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ መረዳት ይኖርብናል። ለዚህም የአንድን ጥቅስ ዐውድ በደንብ ማስተዋል ያስፈልገናል። አንድ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው “የአንድ ቃል ወይም ዓረፍተ ነገር አሊያም ጽሑፍ ዐውድ የሚባለው ከፊትና ከኋላ ያለው ሐሳብ ሲሆን ይህም የቃሉን፣ የዓረፍተ ነገሩን ወይም የጽሑፉን ትርጉም ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል።”

9 አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በትክክል ለመረዳት በዙሪያው ያለውን ሐሳብ ከግምት ማስገባት ያስፈልገናል። በገላትያ 5:13 ላይ የሚገኘው ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እርግጥ ነው ወንድሞች፣ የተጠራችሁት ነፃ እንድትወጡ ነው፤ ብቻ ይህን ነፃነት የሥጋችሁን ፍላጎት ለማነሳሳት አትጠቀሙበት፤ ይልቁንም አንዳችሁ ሌላውን በፍቅር አገልግሉ።” ጳውሎስ እዚህ ላይ የተናገረው ስለ ምን ዓይነት ነፃነት ነው? ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ስለ መውጣት ነው? ወይስ ከሐሰት እምነቶች ወይም ከሌላ ነገር ነፃ ስለ መሆን? ከጥቅሱ ዐውድ መረዳት እንደምንችለው ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ‘ከሕጉ እርግማን ነፃ ስለ መውጣት’ ነው። (ገላ. 3:13, 19-24፤ 4:1-5) ክርስቲያኖች ስለሚያገኙት ነፃነት እየተናገረ ነበር። ይህንን ነፃነት ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አንዳቸው ሌላውን በፍቅር ያገለግላሉ። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የሌላቸው ግን እርስ በርስ ይቦጫጨቃሉ እንዲሁም ይጣላሉ።—ገላ. 5:15

10. የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም በትክክል ለመረዳት ምን ዓይነት መረጃዎችን ማግኘት ያስፈልገናል? እነዚህን መረጃዎች ልናገኝ የምንችለውስ እንዴት ነው?

10 “ዐውድ” የሚለው ቃል ሌላም ትርጉም አለው። ይህ ቃል “የኋላ ታሪክ፣ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ፣ . . . ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች” ከሚሉት ሐሳቦች ጋር የሚመሳሰል ትርጉም አለው። የአንድን ጥቅስ ትርጉም በትክክል ለመረዳት ከጥቅሱ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች ይኸውም መጽሐፉን ማን እንደጻፈው እንዲሁም መቼና በምን ዓይነት ሁኔታ ሥር እንደተጻፈ ማወቅ ይኖርብናል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፉ የተጻፈበትን ዓላማ ከተቻለ ደግሞ በወቅቱ የነበረውን ማኅበራዊ ሕይወት፣ ሥነ ምግባራዊ ሁኔታና ሃይማኖታዊ ልማድ ማወቁ ጠቃሚ ነው። *

11. ቅዱሳን መጻሕፍትን በምናብራራበት ጊዜ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል?

11 ‘የእውነትን ቃል በአግባቡ መጠቀም’ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን በትክክል ከማብራራት የበለጠ ነገርን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስን ሰዎችን ለማስፈራራት እንዳንጠቀም መጠንቀቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ በዲያብሎስ በተፈተነበት ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ለእውነት ጥብቅና በምንቆምበት ጊዜ በቅዱሳን መጻሕፍት መጠቀም ብንችልም መጽሐፍ ቅዱስ አድማጮቻችንን ለመምታት የምንጠቀምበት በትር አይደለም። (ዘዳ. 6:16፤ 8:3፤ 10:20፤ ማቴ. 4:4, 7, 10) ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል፦ “እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁዎች በመሆን ክርስቶስን እንደ ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት፤ ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን።”—1 ጴጥ. 3:15

12, 13. በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነት እንደ “ምሽግ” ያሉትን የትኞቹን ነገሮች መደርመስ ይችላል? ምሳሌ ስጥ።

12 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በአግባቡ ከተጠቀምንበት ምን ሊያከናውን ይችላል? (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5ን አንብብ።) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው እውነት እንደ “ምሽግ” ያሉ ትምህርቶችን ለመደርመስ ይኸውም የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችን፣ ጎጂ ልማዶችንና ሰብዓዊ ጥበብን የሚያንጸባርቁ ፍልስፍናዎችን ለማጋለጥ ሊያገለግል ይችላል። “የአምላክን እውቀት የሚጻረሩ” ሐሳቦችን በሙሉ ለማስወገድ በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም እንችላለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በመጠቀም ሰዎች አስተሳሰባቸውን ከተማሩት እውነት ጋር እንዲያስማሙ መርዳት እንችላለን።

13 በሕንድ የሚኖሩ አንዲት የ93 ዓመት አረጋዊትን እንደ ምሳሌ እንመልከት። እኚህ ሴት፣ ሰው ሲሞት ነፍሱ ሌላ አካል ለብሳ ዳግም እንደምትወለድ በሚያስተምረው በሪኢንካርኔሽን ጽንሰ ሐሳብ ያምኑ ነበር። በሌላ አገር ከሚኖረው ልጃቸው ጋር በደብዳቤ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምሩ ስለ ይሖዋና ስለ ሰጣቸው ተስፋዎች የተማሩትን ነገር በደስታ ተቀበሉ። ይሁንና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የተማሩት የሪኢንካርኔሽን ጽንሰ ሐሳብ በልባቸው ውስጥ ሥር ሰድዶ ስለነበር ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ልጃቸው የጻፈላቸውን ትምህርት መቀበል ከበዳቸው። ለልጃቸው እንዲህ ብለውት ነበር፦ “የአንተ ቅዱሳን መጻሕፍት የሚያስተምሩትን እውነት መረዳት አልችልም። ሁሉም ሃይማኖቶች በውስጣችን አንድ የማትሞት ነገር እንዳለች ያስተምራሉ። እኔ የማምነው አንድ ሰው ሲሞት ከሥጋው ተለይታ የምትወጣው የማትታይ ነገር በተደጋጋሚ ጊዜ የተለያየ አካል ለብሳ እንደምትወለድና ይህ ሂደት ለ8,400,000 ያህል ጊዜ እንደሚቀጥል ነው።” አክለውም “ታዲያ ይህ እንዴት ስህተት ሊሆን ይችላል? አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ተሳስተዋል ማለት ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተው ነበር። ‘የመንፈስ ሰይፍ’ እንዲህ ያለውን እንደ ምሽግ ጠንካራ የሆነ እምነት መደርመስ ይችላል? እኚህ ሴት ከልጃቸው ጋር በዚህ ርዕስ ዙሪያ ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ካደረጉ ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “አሁን ስለ ሞት እውነቱን እየተረዳሁ ነው። የሞቱ ዘመዶቻችንን በትንሣኤ ማግኘት እንደምንችል ማወቄ በጣም አስደስቶኛል። የአምላክ መንግሥት በቅርቡ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ።”

ቃሉን ማስረጃ እያቀረባችሁ ለማሳመን ተጠቀሙበት

14. አድማጮቻችንን ማሳመን ሲባል ምን ማለት ነው?

14 መጽሐፍ ቅዱስን በአገልግሎታችን ላይ ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ሲባል ጥቅሶችን መጥቀስ ማለት ብቻ አይደለም። ጳውሎስ “አሳማኝ ማስረጃዎች በማቅረብ” ይሰብክ ነበር፤ እኛም እንዲህ ልናደርግ ይገባል። (የሐዋርያት ሥራ 19:8, 9⁠ን እና 28:23ን አንብብ።) “ማሳመን” ሲባል “እንዲቀበል ማድረግ” ማለት ነው። እንዲያምን የተደረገው ሰው በቀረበለት ሐሳብ ትክክለኛነት “በጣም እርግጠኛ ከመሆኑ የተነሳ [በዚያ ነገር] ላይ ሙሉ እምነት ይኖረዋል።” አንድን ሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማስረጃ እያቀረብን ስናሳምነው በዚያ ትምህርት ላይ እምነት በማሳደር እንዲቀበለው እያደረግነው ነው። ይህን ለማድረግ አድማጫችን ስለምንናገረው ነገር እውነተኝነት እርግጠኛ እንዲሆን መርዳት ይኖርብናል። ከዚህ በታች የቀረቡት ነጥቦች እንዲህ ለማድረግ ይረዱናል።

15. ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዲያድርባቸው በሚያደርግ መንገድ ጥቅሶችን መጥቀስ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ሰዎች ለአምላክ ቃል አክብሮት እንዲያድርባቸው በሚያደርግ መንገድ ጥቅሶችን ጥቀሱ። ጥቅሶችን ለሰዎች በምትጠቅሱበት ጊዜ አምላክ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ማወቁ በጣም አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘቡ አድርጉ። አንድ ጥያቄ አንስታችሁ ግለሰቡ መልስ ከሰጣችሁ በኋላ እንዲህ ማለት ትችላላችሁ፦ ‘አምላክ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት ማወቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።’ ወይም ደግሞ ‘አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ምን የሚል ይመስልዎታል?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ትችላላችሁ። ጥቅሱን ከመጥቀሳችን በፊት እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ማቅረባችን መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ ለመሆኑ አጽንዖት የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ አድማጩ ይህንን መጽሐፍ ከፍ አድርጎ እንዲመለከተው ይረዳዋል። በተለይ የምንመሠክርለት ግለሰብ በአምላክ የሚያምን ቢሆንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ግንዛቤ የሌለው ከሆነ ይህን ማድረጋችን ይበልጥ አስፈላጊ ነው።—መዝ. 19:7-10

16. ጥቅሶችን በተገቢው መንገድ ለማብራራት ምን ማድረግ ይቻላል?

16 ጥቅሶችን ማንበብ ብቻ በቂ አይደለም፤ ማብራራት ያስፈልጋችኋል። ጳውሎስ በሚያስተምርበት ጊዜ ‘ማስረጃ እየጠቀሰ የማብራራትና የማስረዳት’ ልማድ ነበረው። (ሥራ 17:3) አብዛኛውን ጊዜ አንድ ጥቅስ ብዙ ነጥቦችን ስለሚይዝ ከምትወያዩበት ርዕስ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ቁልፍ ቃላት ከጥቅሱ ውስጥ ነጥላችሁ በማውጣት ማብራራት ትችላላችሁ። ይህንን ለማድረግ ዋናውን ነጥብ የሚያስተላልፉትን ቃላት መድገም ወይም በሌላ መልክ መግለጽ አሊያም ደግሞ ግለሰቡ ነጥቡን እንዲያስተውል የሚረዱትን ጥያቄዎች መጠየቅ ይቻላል። ከዚያም የተፈለገውን የጥቅሱን ክፍል አብራሩለት። ቀጥላችሁ ደግሞ ግለሰቡ ጥቅሶቹን እንዴት ሊሠራባቸው እንደሚችል እንዲያስተውል እርዱት።

17. ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሳችሁ አሳማኝ በሆነ መንገድ ማስረዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

17 ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሳችሁ አሳማኝ በሆነ መንገድ አስረዱ። ጳውሎስ የታሰበበት ጥያቄና አጥጋቢ ምክንያት በማቅረብ አሳማኝ በሆነ መንገድ ‘ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከሰዎች ጋር ይወያይ’ ነበር። (ሥራ 17:2, 4) እንደ ጳውሎስ የሰዎችን ልብ ለመንካት ጥረት አድርጉ። ለግለሰቡ እንደምታስቡለት የሚያሳዩ በደግነት የቀረቡ ጥያቄዎች በልቡ ውስጥ ያለውን ‘ቀድታችሁ ለማውጣት’ ያስችሏችኋል። (ምሳሌ 20:5) አክብሮት የጎደለው ጥያቄ ከማቅረብ ተቆጠቡ። ግለሰቡን ለማሳመን የምትጠቀሙባቸውን ነጥቦች ግልጽና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ አቅርቡ። እነዚህ ነጥቦች አሳማኝ በሆነ ማስረጃ የተደገፉ ሊሆኑ ይገባል። የምትናገሯቸው ነገሮች ሙሉ በሙሉ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ መሆን ይኖርባቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት ጥቅሶችን በአንዴ ከመደርደር ይልቅ አንድን ጥቅስ በደንብ ማብራራትና ነጥቡን በምሳሌ ማስረዳት የተሻለ ነው። ተጨማሪ ማስረጃዎችን መጥቀስም ‘ለከንፈራችሁ የማሳመን ችሎታ ይጨምርለታል።’ (ምሳሌ 16:23 NW) አንዳንድ ጊዜ ምርምር ማድረግና ሌሎች ማስረጃዎችን ማቅረብ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት የ93 ዓመት አረጋዊት፣ ነፍስ (ወይም መንፈስ) አትሞትም የሚለው ትምህርት ይህን ያህል የተስፋፋው ለምን እንደሆነ ማወቅ አስፈልጓቸው ነበር። እኚህ ሴት በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርት አምነው እንዲቀበሉ ለማድረግ ይህ መሠረተ ትምህርት የመነጨው ከየት እንደሆነና በዓለም ላይ ባሉት በአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው እንዴት እንደሆነ መጀመሪያ መረዳታቸው አስፈላጊ ነበር። *

ቃሉን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀማችሁን ቀጥሉ

18, 19. “የመንፈስን ሰይፍ” ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀማችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

18 መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ ነው” ይላል። ክፉ ሰዎች በክፋት ላይ ክፋትን እየጨመሩ በመሄድ ላይ ናቸው። (1 ቆሮ. 7:31፤ 2 ጢሞ. 3:13) በመሆኑም “የመንፈስን ሰይፍ ይኸውም የአምላክን ቃል” በመጠቀም እንደ “ምሽግ” ያሉ ነገሮችን መደርመሳችንን መቀጠላችን በጣም አስፈላጊ ነው።

19 የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘታችን እንዲሁም በውስጡ ባለው ኃይለኛ መልእክት ተጠቅመን የሐሰት ትምህርቶችን ከሥራቸው ነቅለን ለማስወገድና ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ልብ ለመንካት በመቻላችን ምንኛ ደስተኞች ነን! ይህ መልእክት ማንኛውንም እንደ ምሽግ ያለ ነገር ማሸነፍ ይችላል። እንግዲያው አምላክ በሰጠን መንግሥቱን የማወጅ ሥራ ስንካፈል “የመንፈስን ሰይፍ” ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት እናድርግ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው በሚል ርዕስ በተከታታይ የወጡት ብሮሹሮች፣ ‘ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው’ (እንግሊዝኛ) እና ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባሉት መጻሕፍት እንዲሁም “የይሖዋ ቃል ሕያው ነው” እንደሚለው ያሉ መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጡ ርዕሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መረጃዎች ለማግኘት የሚያስችሉ ግሩም መሣሪያዎች ናቸው።

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• የአምላክ ቃል ምን ያህል ኃይል አለው?

• ‘የእውነትን ቃል በአግባቡ መጠቀም’ የምንችለው እንዴት ነው?

• በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መልእክት እንደ “ምሽግ” ያሉ ነገሮችን ምን ሊያደርጋቸው ይችላል?

• በአገልግሎት ላይ አሳማኝ ማስረጃዎችን በማቅረብ የማሳመን ችሎታህን ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የአምላክን ቃል ማስረጃ እያቀረብን ለማሳመን ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?

▪ ሰዎች ለአምላክ ቃል አክብሮት እንዲያድርባቸው ማድረግ

▪ ጥቅሶችን ማብራራት

▪ የሰዎችን ልብ ለመንካት አሳማኝ በሆነ መንገድ ማስረዳት

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የመንፈስን ሰይፍ” ውጤታማ በሆነ መንገድ የመጠቀም ችሎታ ማዳበር ይኖርብሃል