የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ድጋሚ መጠመቅ አስፈላጊ ሊሆን የሚችለው መቼ ነው?
አንድ የተጠመቀ ግለሰብ ጥምቀቱ ተቀባይነት ያለው መሆኑን እንዲጠራጠርና እንደገና መጠመቅ እንደሚያስፈልገው እንዲሰማው የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው በተጠመቀበት ወቅት ይከተለው የነበረው አኗኗር ወይም በድብቅ ይፈጽመው የነበረው ድርጊት፣ ተቀባይነት ባለው ሁኔታ ተጠምቆ ቢሆን ኖሮ ከጉባኤ የሚያስወግደው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለአምላክ ራሱን መወሰን ይችላል? ይህ ግለሰብ ተቀባይነት ባለው መንገድ ለይሖዋ ራሱን መወሰን የሚችለው ከቅዱስ ጽሑፉ ጋር የሚጋጭ ተግባር መፈጸሙን ካቆመ ብቻ ነበር። በመሆኑም እንዲህ ያለ ከባድ ችግር እያለበት የተጠመቀ ሰው እንደገና መጠመቅ እንዳለበት ማሰቡ ተገቢ ነው።
በተጠመቀበት ወቅት የኃጢአት ጎዳና ይከተል የነበረ ባይሆንም ከዚያ በኋላ በፈጸመው ኃጢአት የተነሳ በፍርድ ኮሚቴ ፊት ስለቀረበ ሰውስ ምን ማለት ይቻላል? ይህ ግለሰብ ‘በተጠመቅኩበት ወቅት ጥምቀት ምን ማለት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ስላልገባኝ ጥምቀቴ ተቀባይነት ያለው ነው ሊባል አይችልም’ ቢልስ? ሽማግሌዎች ስህተት የሠራን ሰው ሲያነጋግሩ ጥምቀቱ ተቀባይነት እንዳልነበረው የሚጠቁም ነገር መናገር የለባቸውም፤ እንዲሁም ራሱን መወሰኑና ጥምቀቱ ተቀባይነት እንዳለው ይሰማው እንደሆነ መጠየቅ አይኖርባቸውም። ግለሰቡ ከመጠመቁ በፊት ጥምቀት ትልቅ ትርጉም ያለው እርምጃ መሆኑን የሚገልጽ ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግር ሰምቷል። እንዲሁም ራስን ስለ መወሰንና ስለ መጠመቅ ለቀረቡት ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቷል። ከዚያም ልብሱን ከቀየረ በኋላ ውኃ ውስጥ ገብቶ ተጠምቋል። ስለሆነም የወሰደው እርምጃ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ሙሉ በሙሉ ተገንዝቦ ነበር ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ ነው። ከዚህ አንጻር ሽማግሌዎች ግለሰቡን የሚመለከቱት እንደ አንድ የተጠመቀ ክርስቲያን አድርገው ነው።
አንድ ግለሰብ ጥምቀቱ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ ጥያቄ ካነሳ ሽማግሌዎች በድጋሚ ስለ መጠመቅ ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠበትን የመጋቢት 1, 1960 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 159 እና 160 (እንግሊዝኛ) እንዲሁም የየካቲት 15, 1964 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 123 እስከ 126 (እንግሊዝኛ) እንዲመለከት ሊያደርጉ ይችላሉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ አንድ ሰው (ለምሳሌ፣ ሲጠመቅ በቂ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ካልነበረው) ከጊዜ በኋላ በድጋሚ ለመጠመቅ ሊወስን ይችላል፤ ይህ የግለሰቡ ውሳኔ ነው።
አንድ ላይ መኖርን በተመለከተ ክርስቲያኖች የትኞቹን ነገሮች ከግምት ማስገባት ይኖርባቸዋል?
ሁሉም ሰው የሚኖርበት ቦታ ያስፈልገዋል። ይሁንና በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የራሳቸው ቤት የላቸውም። የሰዎች የኢኮኖሚ አቅም፣ የጤንነት ሁኔታ ወይም ሌሎች ነገሮች በርከት ያሉ ዘመዳሞች አንድ ላይ ለመኖር እንዲገደዱ ያደርጉ ይሆናል። በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ዘመዳሞች በአንድ ክፍል ውስጥ ተጨናንቀው ይኖሩ ይሆናል።
የይሖዋ ድርጅት፣ ተገቢ የመኖሪያ ቦታን በተመለከተ ለመላው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ዝርዝር ሕግጋት የማውጣት ኃላፊነት የለበትም። ክርስቲያኖች የሚኖሩበት ሁኔታ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆን አለመሆኑን ለመወሰን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ከግምት እንዲያስገቡ ይበረታታሉ። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
በዋነኝነት ልናስብበት የሚገባው ነጥብ ከሌሎች ጋር መኖራችን በእኛም ሆነ በመንፈሳዊነታችን ላይ ሊያሳድር 1 ቆሮ. 15:33
የሚችለው ተጽዕኖ ነው። አብረውን የሚኖሩት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? የይሖዋ አምላኪዎች ናቸው? አኗኗራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” በማለት ጽፏል።—ይሖዋ ዝሙትንና ምንዝርን እንደሚያወግዝ ቅዱሳን መጻሕፍት ይገልጻሉ። (ዕብ. 13:4) በመሆኑም ያልተጋቡ ወንድና ሴት እንደ ባልና ሚስት በአንድ ክፍል ውስጥ ማደራቸው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ግልጽ ነው። አንድ ክርስቲያን የሥነ ምግባር ብልግና በሚፈጸምበት ቦታ መኖር እንደማይፈልግ የታወቀ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ሞገስ ማግኘት ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ “ከዝሙት ሽሹ” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል። (1 ቆሮ. 6:18) በመሆኑም ክርስቲያኖች የሥነ ምግባር ብልግና እንዲፈጽሙ የሚፈትናቸው አጋጣሚ እንዲፈጠር ከሚያደርግ ከማንኛውም የመኖሪያ ሁኔታ መራቃቸው የጥበብ እርምጃ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በርካታ ክርስቲያኖች በአንድ ጣሪያ ሥር የሚያድሩበትን ሁኔታ እንመልከት። እንዲህ ያለው ሁኔታ በፈተና ሊወድቁ የሚችሉበት አጋጣሚ እንዲፈጠር ያደርግ ይሆን? ያልተጋቡ ወንድና ሴት፣ አብረዋቸው የሚኖሩት ሌሎች ሰዎች በአጋጣሚ ባለመኖራቸው ምክንያት ብቻቸውን እንዲሆኑ የሚያደርግ ያልታሰበ ሁኔታ ቢፈጠርስ? እንዲሁም ያልተጋቡ ሆኖም የሚዋደዱ ወንድና ሴት በአንድ ቤት ውስጥ አብረው መኖራቸው ከሥነ ምግባር አንጻር አደገኛ ነው። እንዲህ ዓይነት የመኖሪያ ሁኔታዎችን ማስወገዱ የጥበብ እርምጃ ነው።
የተፋቱ ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ አብረው መኖራቸውን መቀጠላቸውም ተገቢ አይሆንም። እነዚህ ሰዎች ባልና ሚስት ስለነበሩና በጣም የተቀራረበ ግንኙነት ስለነበራቸው በአንድ ቤት መኖራቸው በቀላሉ የሥነ ምግባር ብልግና ወደመፈጸም ሊመራቸው ይችላል።—ምሳሌ 22:3
ሌላው ከግምት መግባት የሚኖርበት አስፈላጊ ነጥብ ደግሞ ኅብረተሰቡ የአንድን ሰው ምርጫ እንዴት ይመለከተዋል የሚለው ነው። አንድ ክርስቲያን የሚኖርበት ሁኔታ ተቀባይነት እንዳለው ሆኖ ቢሰማውም ማኅበረሰቡ በመጥፎ እንዲመለከተው የሚያደርግ ከሆነ ጉዳዩ ሊታሰብበት ይገባል። አኗኗራችን የይሖዋን ስም የሚያስነቅፍ እንዲሆን ፈጽሞ አንፈልግም። ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ለአይሁዳውያንም ሆነ ለግሪካውያን እንዲሁም ለአምላክ ጉባኤ እንቅፋት ከመሆን ተቆጠቡ፤ እኔ ብዙዎች እንዲድኑ የእነሱን እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በማደርገው ነገር ሁሉ፣ ሁሉንም ሰው እንደማስደስት እናንተም እንዲሁ አድርጉ።”—1 ቆሮ. 10:32, 33
የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ለመጠበቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ተስማሚ የመኖሪያ ቦታ ወይም ሁኔታ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች “በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም [መርምረው ማረጋገጥ]” ይኖርባቸዋል። በሚኖሩበት ቦታ ተገቢ ያልሆነ ምንም ነገር እንደማይፈጸም ማረጋገጥ ይገባቸዋል። (ኤፌ. 5:5, 10) ክርስቲያኖች ይህን በተግባር ማዋል እንዲችሉ መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት መጸለይ እንዲሁም አንዳቸው የሌላውን አካላዊና ሥነ ምግባራዊ ደኅንነት ለመጠበቅ አልፎ ተርፎም የይሖዋን ስም የሚያስነቅፍ ነገር ላለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ መጣር ይኖርባቸዋል።