በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን እንደ አባትህ አድርገህ ትመለከተዋለህ?

ይሖዋን እንደ አባትህ አድርገህ ትመለከተዋለህ?

ይሖዋን እንደ አባትህ አድርገህ ትመለከተዋለህ?

‘ጌታ ሆይ፣ እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን።’ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ይህን ጥያቄ ባቀረበለት ጊዜ ኢየሱስ የሚከተለውን መልስ ሰጠ፦ “በምትጸልዩበት ጊዜ ሁሉ እንዲህ በሉ፦ ‘አባት ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።’” (ሉቃስ 11:1, 2) ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር ‘ሁሉን ማድረግ የሚችል፣’ ‘ታላቅ አስተማሪ፣’ “ፈጣሪ፣” “ጥንታዌ ጥንቱ” ወይም ‘የዘላለም ንጉሥ’ እንደሚሉት ባሉ የይሖዋን ታላቅነት የሚያንጸባርቁ መጠሪያዎች መጠቀም ይችል ነበር። (ዘፍ. 49:25፤ ኢሳ. 30:20 NW፤ 40:28፤ ዳን. 7:9፤ 1 ጢሞ. 1:17) ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “አባት” የሚለውን መጠሪያ ተጠቅሟል። ለምን? ይህን ያደረገው በጽንፈ ዓለም ውስጥ የላቀውን አካል፣ አንድ ትሑት ልጅ አፍቃሪ የሆነ አባቱን በሚጠራበት መንገድ እንድንጠራው ፈልጎ ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ ሰዎች ግን አምላክን እንደ አባታቸው አድርገው ማየት ይከብዳቸዋል። አትሱኮ * የተባለች አንዲት ክርስቲያን “ከተጠመቅኩ በኋላ ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን እንደ አባት አድርጌ ለመቅረብም ሆነ እሱን እንደ አባት በማየት ለመጸለይ እቸገር ነበር” ብላለች። እንዲህ ያለችበትን ምክንያት ስትገልጽ “እኔ እስከማስታውሰው ድረስ ወላጅ አባቴ ፍቅር አሳይቶኝ አያውቅም” ብላለች።

በዓይነቱ ልዩ በሆነው በዚህ የመጨረሻ ዘመን ከአባት የሚጠበቀው “ተፈጥሯዊ ፍቅር” በእጅጉ እየጠፋ መጥቷል። (2 ጢሞ. 3:1, 3) በመሆኑም እንደ አትሱኮ የሚሰማቸው ሰዎች መኖራቸው እንግዳ ነገር አይደለም። ይሁንና ይሖዋን እንደ አፍቃሪ አባታችን አድርገን እንድንመለከተው የሚያነሳሱን ጠንካራ ምክንያቶች እንዳሉ ማወቃችን ያጽናናናል።

ይሖዋ—በፍቅር የሚሰጥ አምላክ

ይሖዋን እንደ አባታችን መመልከት እንድንችል እሱን በደንብ ልናውቀው ይገባል። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ከአብ በቀር ወልድን ሙሉ በሙሉ የሚያውቅ የለም፣ ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን ሙሉ በሙሉ የሚያውቅ ማንም የለም።” (ማቴ. 11:27) ይሖዋ ምን ዓይነት አባት እንደሆነ ለማወቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ኢየሱስ ስለ እውነተኛው አምላክ በተናገራቸው ሐሳቦች ላይ ማሰላሰል ነው። ታዲያ ኢየሱስ ስለ አባቱ የገለጣቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

ኢየሱስ ‘ከአብ የተነሳ በሕይወት እኖራለሁ’ በማለት ሲናገር የሕይወቱ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን ገልጿል። (ዮሐ. 6:57) እኛም ሕይወት ያገኘነው ከአብ ነው። (መዝ. 36:9፤ ሥራ 17:28) ይሖዋ ለሌሎች ሕይወት እንዲሰጥ ያነሳሳው ምንድን ነው? ፍቅር አይደለም? በሰማይ የሚኖረው አባታችን እንዲህ ያለ ስጦታ ስለሰጠን ልንወደው እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም።

አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር የገለጸበት ከሁሉ የላቀው መንገድ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። ይህ የፍቅር መግለጫ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ተወዳጅ በሆነው ልጁ አማካኝነት ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንዲመሠርቱ አስችሏል። (ሮም 5:12፤ 1 ዮሐ. 4:9, 10) የሰማዩ አባታችን የገባቸውን ተስፋዎች የሚፈጽም በመሆኑ እሱን የሚወዱና የሚታዘዙ ሰዎች በሙሉ በመጨረሻ “የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት” እንደሚያገኙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሮም 8:21

ከዚህም በተጨማሪ በሰማይ የሚኖረው አባታችን በየዕለቱ ‘ፀሐዩን ያወጣልናል።’ (ማቴ. 5:45) ፀሐይ እንድትወጣ መጸለይ አስፈላጊ እንደሆነ አይሰማንም። ይሁንና ከፀሐይ የምናገኘው ብርሃንና ሙቀት በጣም የሚያስፈልገን ከመሆኑም በላይ ያስደስተናል። ከዚህም በተጨማሪ አባታችን ገና ሳንለምነው የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች የሚያውቅ ተወዳዳሪ የሌለው ሰጪ ነው። በመሆኑም የሰማዩ አባታችን ፍጥረታቱን እንዴት እንደሚንከባከብ ጊዜ ወስደን ማጤንና በአድናቆት ማሰላሰል አይኖርብንም?—ማቴ. 6:8, 26

አባታችን—‘ሩኅሩኅ ጠባቂ’

የጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች በኢሳይያስ ትንቢት ላይ የሚከተለው ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው ነበር፦ “‘ተራሮች ቢናወጡ፣ ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤ የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም’ ይላል [“በርኅራኄ የሚጠብቅሽ ይሖዋ፣” ዘ ባይብል ኢን ሊቪንግ ኢንግሊሽ]።” (ኢሳ. 54:10) ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት ላይ ያቀረበው ጸሎትም ይሖዋ ‘ሩኅሩኅ ጠባቂ’ እንደሆነ የሚገልጸውን ከላይ ያለውን ሐሳብ ያጠናክረዋል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አስመልክቶ ሲጸልይ እንዲህ ብሏል፦ “[እነሱ] በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፣ . . . ስለ ራስህ ስም ስትል ጠብቃቸው።” (ዮሐ. 17:11, 14) ይሖዋም ለኢየሱስ ተከታዮች ጥበቃ አድርጎላቸዋል።

በዛሬው ጊዜ አምላክ ሰይጣን ከሚሰነዝርብን ጥቃት እኛን ለመጠበቅ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት በጊዜው የሚሰጠን መንፈሳዊ ምግብ ነው። (ማቴ. 24:45) ጥንካሬ የሚሰጠንን ይህን ምግብ መመገባችን “ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ [ለመልበስ]” በጣም አስፈላጊ ነው። “የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን” እንድንችል የሚረዳንን “ትልቅ የእምነት ጋሻ” እንደ ምሳሌ እንመልከት። (ኤፌ. 6:11, 16) በአምላካችን ላይ ያለን እምነት ከመንፈሳዊ ጉዳት የሚጠብቀን ከመሆኑም ሌላ አባታችን እኛን ለመጠበቅ ኃይል እንዳለው እርግጠኞች መሆናችንን ያሳያል።

የአምላክ ልጅ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ያደረጋቸውን ነገሮች በጥልቅ መመርመራችን በሰማይ የሚኖረው አባታችን ምን ያህል ሩኅሩኅ እንደሆነ የበለጠ ለማወቅ ያስችለናል። በማርቆስ 10:13-16 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ተመልከት። በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ” ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እንደተናገራቸው ተገልጿል። እነዚያ ልጆች በዙሪያው ሲሰበሰቡ ኢየሱስ በርኅራኄ እንዳቀፋቸውና እንደባረካቸው ዘገባው ይናገራል። ልጆቹ ከደስታ ብዛት ፍንድቅድቅ ብለው ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! ኢየሱስ “እኔን ያየ አብንም አይቷል” ብሎ ስለተናገረ እውነተኛው አምላክ ወደ እሱ እንድንቀርብ እንደሚፈልግ ማወቅ እንችላለን።—ዮሐ. 14:9

የይሖዋ አምላክ ፍቅር ወሰን የለውም። በሰጪነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ከመሆኑም ሌላ ከማንም በላይ ጥበቃ ያደርግልናል፤ እንዲሁም ወደ እሱ እንድንቀርብ ይፈልጋል። (ያዕ. 4:8) በመሆኑም ይሖዋ ልንገምተው ከምንችለው በላይ ጥሩ አባት መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም!

በእጅጉ እንጠቀማለን!

ይሖዋን በሰማይ የሚኖር አፍቃሪና ሩኅሩኅ አባታችን እንደሆነ አድርገን በማየት በእሱ መታመናችን በእጅጉ ይጠቅመናል። (ምሳሌ 3:5, 6) ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ በአባቱ በመታመኑ ተጠቅሟል። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ “ብቻዬን አይደለሁም፤ ከዚህ ይልቅ የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 8:16) ኢየሱስ የይሖዋ ድጋፍ እንደማይለየው ምንጊዜም እርግጠኛ ነበር። ለምሳሌ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ አባቱ “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ፍቅሩን አረጋግጦለታል። (ማቴ. 3:15-17) ኢየሱስም ከመሞቱ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት “አባት ሆይ፣ መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 23:46) ኢየሱስ በዚህ ወቅትም እንደ ሁልጊዜው በአባቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመን አሳይቷል።

እኛም እንዲሁ በይሖዋ መተማመን እንችላለን። ይሖዋ ከእኛ ጋር እስከሆነ ድረስ ምን የሚያስፈራን ነገር አለ? (መዝ. 118:6) በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው አትሱኮ ችግሮች ሲያጋጥሟት በራሷ የመታመን ልማድ ነበራት። ከጊዜ በኋላ ግን በኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት በተለይ ደግሞ ከሰማዩ አባቱ ጋር ባለው የጠበቀ ዝምድና ላይ ትኩረት በማድረግ የግል ጥናት ማድረግ ጀመረች። ውጤቱ ምን ሆነ? አትሱኮ “አባት ምን ማለት እንደሆነና በእሱ መታመን ምን ትርጉም እንዳለው ገባኝ” ብላለች። አክላም “እውነተኛ ሰላምና ደስታ አገኘሁ። በእርግጥም ስለየትኛውም ነገር የምንጨነቅበት ምንም ምክንያት የለም” በማለት ተናግራለች።

ይሖዋን እንደ አባታችን በመመልከታችን ምን ተጨማሪ ጥቅም እናገኛለን? ልጆች ወላጆቻቸውን እንደሚወዱና ሊያስደስቷቸው እንደሚፈልጉ የታወቀ ነው። የአምላክ ልጅ አባቱን ስለሚወደው ‘ሁልጊዜ አባቱን ደስ የሚያሰኘውን ያደርግ ነበር።’ (ዮሐ. 8:29) እኛም በተመሳሳይ በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ያለን ፍቅር እንደ ጥበበኞች እንድንመላለስና ‘በሕዝብ ፊት እንድናወድሰው’ ሊያነሳሳን ይችላል።—ማቴ. 11:25፤ ዮሐ. 5:19

አባታችን ‘ቀኝ እጃችንን ይይዘናል’

የሰማዩ አባታችን “ረዳት” የሆነውን ቅዱስ መንፈሱንም ይሰጠናል። ይህ መንፈስ ‘ወደ እውነት ሁሉ እንደሚመራን’ ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐ. 14:15-17፤ 16:12, 13) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አባታችንን ይበልጥ እንድናውቀው ይረዳናል። ይህ መንፈስ ‘ምሽግን’ ለመደርመስ ይኸውም ቀደም ሲል የነበረንን የተሳሳተ ወይም የተዛባ አመለካከት ለማስወገድ ይረዳናል፤ በዚህ መንገድ “ማንኛውንም አስተሳሰብ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ” እናደርጋለን። (2 ቆሮ. 10:4, 5) እንግዲያው “በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን” እንደሚሰጣቸው በመተማመን ቃል የተገባልንን “ረዳት” እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ እንጸልይ። (ሉቃስ 11:13) መንፈስ ቅዱስ ወደ ይሖዋ የበለጠ እንድንቀርብ እንዲረዳን መጸለያችንም ተገቢ ነው።

አንድ ትንሽ ልጅ የአባቱን እጅ ይዞ በሚሄድበት ጊዜ አንዳች ፍርሃት የማይሰማው ከመሆኑም ሌላ የመረጋጋትና የደኅንነት ስሜት ይኖረዋል። አንተም ይሖዋን እንደ አባትህ አድርገህ የምታየው ከሆነ “እኔ [“ይሖዋ፣” NW] አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ” በሚሉት ቃላት ልትተማመን ትችላለህ። (ኢሳ. 41:13) እንዲሁም ለዘላለም ከአምላክ ጋር ‘የመራመድ’ ግሩም መብት ታገኛለህ። (ሚክ. 6:8) የአምላክን ፈቃድ ማድረግህን ከቀጠልክ ይሖዋን እንደ አባትህ አድርገህ ማየትህ የሚያስገኘውን ፍቅር፣ ደስታና የመረጋጋት ስሜት ታገኛለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ስሟ ተቀይሯል።