በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጠመቅ ያለብን በማንና በምን ስም ነው?

መጠመቅ ያለብን በማንና በምን ስም ነው?

መጠመቅ ያለብን በማንና በምን ስም ነው?

“ሂዱና . . . ሰዎችን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴ. 28:19

1, 2. (ሀ) በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ምን ተከናወነ? (ለ) ብዙዎቹን እንዲጠመቁ ያነሳሳቸው ምን ነበር?

ኢየሩሳሌም ከተለያዩ አገሮች በመጡ ሰዎች ተጨናንቃለች። በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አንድ በዓል እየተከበረ ሲሆን በርካታ እንግዶችም በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል። በዚያን ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ አስደናቂ ውጤት ያስገኘ ስሜት ቀስቃሽ ንግግር ካቀረበ በኋላ አንድ እንግዳ የሆነ ነገር ተከሰተ። አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ 3,000 የሚሆኑ ሰዎች በንግግሩ ልባቸው ተነክቶ ንስሐ በመግባት በውኃ ተጠመቁ። በዚህ መንገድ እነዚህ ሰዎች አዲስ የተቋቋመውን የክርስቲያን ጉባኤ ተቀላቀሉ። (ሥራ 2:41) በዚያ ወቅት ይህን ያህል ሰው ሲጠመቅ በኢየሩሳሌም አካባቢ ባሉ ገንዳዎችና የውኃ ማጠራቀሚያዎች አካባቢ ግርግር ተፈጥሮ መሆን አለበት!

2 ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዲጠመቁ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? ያን ዕለት ጠዋት “እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ።” አንድ ፎቅ ላይ ባለ ክፍል ውስጥ የነበሩት 120 የሚሆኑ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ። ከዚያ በኋላ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ተሰብስበው እያለ እነዚህ ደቀ መዛሙርት “በተለያዩ ልሳኖች” ሲናገሩ ሲሰሙ ተገረሙ። ሰዎቹ፣ ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ሞት የተናገረውን ሐሳብ ጨምሮ እሱ ያቀረበውን ንግግር ሲሰሙ “ልባቸው እጅግ [ተነካ]።” ታዲያ ምን ማድረግ ነበረባቸው? ጴጥሮስ “ንስሐ ግቡ፤ እያንዳንዳችሁም . . . በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ነፃ ስጦታ ትቀበላላችሁ” አላቸው።—ሥራ 2:1-4, 36-38

3. በጴንጤቆስጤ ዕለት ንስሐ የገቡ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ምን ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር?

3 ጴጥሮስን ያዳምጡ የነበሩ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ይከተሉት ስለነበረው ሃይማኖት አስብ። እነዚህ ሰዎች ቀድሞውኑም ቢሆን ይሖዋን እንደ አምላካቸው አድርገው ተቀብለውት ነበር። እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ፣ አምላክ በፍጥረት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ የተጠቀመበት ኃይሉ እንደሆነ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ተረድተው ነበር። (ዘፍ. 1:2፤ መሳ. 14:5, 6፤ 1 ሳሙ. 10:6፤ መዝ. 33:6) ይሁንና ከዚያ የበለጠ ነገር ያስፈልጋቸው ነበር። አምላክ ሰዎችን ለማዳን ስለሚጠቀምበት መንገድ ይኸውም ስለ መሲሑ ስለ ኢየሱስ ማወቅና እሱን መቀበል ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም ጴጥሮስ ‘በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቃቸው’ አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገለጸላቸው። ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ከጥቂት ቀናት በፊት “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንዲያጠምቁ ጴጥሮስንና ሌሎች ሰዎችን አዟቸው ነበር። (ማቴ. 28:19, 20) ይህ ትእዛዝ በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በዛሬው ጊዜ ትልቅ ትርጉም አለው። ታዲያ ትርጉሙ ምንድን ነው?

በአብ ስም

4. ከይሖዋ ጋር ዝምድና መሥርተው ከነበሩ ሰዎች ጋር በተያያዘ ምን ለውጥ ተከናወነ?

4 ቀደም ሲል እንደተገለጸው የጴጥሮስን ንግግር ሰምተው የተጠመቁ ሰዎች ይሖዋን ያመልኩ የነበረ ሲሆን ከእሱ ጋር ዝምድና መሥርተው ነበር። እነዚህ ሰዎች ሕጉን ለመከተል ጥረት ያደርጉ ነበር፤ ከሌላ አገር ወደ ኢየሩሳሌም መምጣታቸውም ይህን ያሳያል። (ሥራ 2:5-11) ይሁን እንጂ አምላክ በወቅቱ ከሰዎች ጋር ግንኙነት በሚያደርግበት መንገድ ላይ ትልቅ ለውጥ አድርጎ ነበር። አይሁዳውያንን የተለዩ ሕዝቦቹ አድርጎ መመልከቱን አቁሟል፤ እንዲሁም የእሱን ሞገስ ለማግኘት ሕጉን መጠበቅ እንደ መሥፈርት መታየቱ አብቅቷል። (ማቴ. 21:43፤ ቆላ. 2:14) ያዳምጡ የነበሩት ሰዎች ከይሖዋ ጋር ቀጣይነት ያለው ዝምድና መመሥረት ከፈለጉ ሌላ ነገር ያስፈልጋቸው ነበር።

5, 6. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ በርካታ ሰዎች ከአምላክ ጋር ዝምድና ለመመሥረት ምን አደረጉ?

5 ይህ ለውጥ ሕይወት ለሰጣቸው ለይሖዋ ጀርባቸውን እንዲሰጡ የሚያደርግ አልነበረም። (ሥራ 4:24) እንዲያውም የጴጥሮስን ንግግር ሰምተው እርምጃ የወሰዱ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይሖዋ ደግ አምላክ መሆኑን መመልከት ይችላሉ። እነሱን ለማዳን መሲሑን የላከ ከመሆኑም በላይ ጴጥሮስ “ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን አምላክ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ቤት ሁሉ በእርግጥ ይወቅ” ያላቸውን ሰዎች እንኳ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ የጴጥሮስን ንግግር ሰምተው ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች አብ ከእሱ ጋር ዝምድና መመሥረት ለሚፈልጉ ሁሉ ያደረገውን ዝግጅት ይበልጥ እንዲያደንቁ ይገፋፋቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 2:30-36ን አንብብ።

6 በእርግጥም እነዚህ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ዝምድና ለመመሥረት፣ በኢየሱስ አማካኝነት መዳን የሚቻልበትን መንገድ ያዘጋጀው ይሖዋ መሆኑን አምኖ መቀበል እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ችለዋል። ይህ ደግሞ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ከኢየሱስ መገደል ጋር በተያያዘ የፈጸሙትን በደል ጨምሮ ከሠሩት ኃጢአት ሁሉ ንስሐ የገቡት ለምን እንደሆነ እንድትገነዘብ ያደርግሃል። ከዚህም በተጨማሪ በቀጣዩቹ ቀናት “የሐዋርያቱንም ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን [የቀጠሉት]” ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። (ሥራ 2:42) በመሆኑም ‘የመናገር ነፃነት ኖሯቸው ወደ ጸጋው ዙፋን መቅረብ’ ይችላሉ፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ እንደሚፈልጉ ጥርጥር የለውም።—ዕብ. 4:16

7. በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ስለ አምላክ የነበራቸው አመለካከት ተለውጦ በአብ ስም የተጠመቁት እንዴት ነው?

7 በዛሬው ጊዜ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ ይሖዋ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እውነቱን ተምረዋል። (ኢሳ. 2:2, 3) ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በአምላክ መኖር የማያምኑ ወይም አምላክ ቢኖርም ስለ ፍጡሮቹ ደንታ የለውም የሚል አመለካከት ያላቸው ነበሩ፤ ሆኖም እነዚህ ሰዎች ፈጣሪ መኖሩንና ከእሱ ጋር ትርጉም ያለው ዝምድና መመሥረት የሚቻል መሆኑን አምነዋል። ሌሎች ደግሞ ሥላሴን ወይም የተለያዩ ጣዖታትን ያመልኩ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ከይሖዋ በቀር ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሌለ የተማሩ ሲሆን እሱን በግል ስሙ መጥራት ጀምረዋል። ይህ ደግሞ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በአብ ስም መጠመቅ እንዳለባቸው ከተናገረው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው።

8. ስለ አዳም ኃጢአት ምንም እውቀት ያልነበራቸው ሰዎች ስለ አብ ምን መገንዘብ ይኖርባቸዋል?

8 ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ሰዎች ከአዳም ኃጢአት እንደወረሱ ተረድተዋል። (ሮም 5:12) ይህ በእርግጥ አምነው ሊቀበሉት የሚገባ አዲስ ነገር ነው። እንዲህ ያሉ ሰዎች የበሽታውን ምንነት በውል ካላወቀ አንድ የታመመ ሰው ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ይህ ሰው አንዳንድ ምልክቶች ይታዩበት ይኸውም አልፎ አልፎ ሕመም ይሰማው ይሆናል። ይሁንና ተመርምሮ ችግሩ ስላልታወቀለት በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ይሰማው ይሆናል። ሐቁ የሚያሳየው ግን ተቃራኒውን ነው። (ከ1 ቆሮንቶስ 4:4 ጋር አወዳድር።) የጤና ምርመራ አድርጎ ችግሩ በትክክል ቢታወቅለትስ? ግለሰቡ ፈውስ ለማግኘት የታወቀ፣ የተረጋገጠና ውጤታማ የሆነ መድኃኒት ለማግኘት ጥረት ማድረጉ ብሎም የታዘዘለትን መድኃኒት መውሰዱ ጥበብ አይሆንም? በተመሳሳይም ብዙ ሰዎች ከአዳም ኃጢአት መውረሳቸውን በማመን የመጽሐፍ ቅዱስን “የምርመራ ውጤት” የተቀበሉ ሲሆን አምላክ ፈውስ የሚያገኙበትን “መድኃኒት” እንዳዘጋጀላቸው ተገንዝበዋል። አዎን፣ ከአብ የራቁ ሁሉ ፈውስ ሊያስገኝላቸው የሚችለውን “መድኃኒት” መቀበል ያስፈልጋቸዋል።—ኤፌ. 4:17-19

9. ይሖዋ ከእሱ ጋር ዝምድና መመሥረት እንድንችል ምን ዝግጅት አድርጓል?

9 ሕይወትህን ለይሖዋ አምላክ ወስነህ የተጠመቅክ ክርስቲያን ከሆንክ ከእሱ ጋር ዝምድና መመሥረት ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ ታውቃለህ። አባትህ ይሖዋ ምን ያህል አፍቃሪ እንደሆነ ተረድተሃል። (ሮም 5:8ን አንብብ።) አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ኃጢአት ቢሠሩም እኛን ጨምሮ ዘሮቻቸው በሙሉ ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት እንዲችሉ ዝግጅት አድርጓል። አምላክ ይህን ዝግጅት ማድረጉ ውድ ልጁ ሲሠቃይና ሲሞት መመልከት ግድ እንዲሆንበት አድርጓል። ታዲያ ይህን ማወቃችን የአምላክን ሥልጣን እንድንቀበልና በፍቅር ተገፋፍተን ትእዛዛቱን እንድንፈጽም አያነሳሳንም? እስካሁን ካልተጠመቅክ ለአምላክ ራስህን ወስነህ እንድትጠመቅ የሚገፋፋህ በቂ ምክንያት አለህ።

በወልድ ስም

10, 11. (ሀ) ምን ያህል የኢየሱስ ውለታ አለብህ? (ለ) ኢየሱስ ቤዛ ሆኖ ስለሞተልህ ምን ይሰማሃል?

10 አሁን ደግሞ ጴጥሮስ በዚያ ተሰብስበው ለነበሩ ሰዎች ስለተናገረው ነገር እንደገና አስብ። ኢየሱስን መቀበል ወሳኝ ነገር መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል፤ ይህ እርምጃ “በወልድ . . . ስም” ከመጠመቅ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት አለው። በወልድ ስም መጠመቅ በዚያን ጊዜም ሆነ በዛሬው ጊዜ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስን መቀበልና በስሙ መጠመቅ ሲባል ከፈጣሪያችን ጋር ለምንመሠርተው ዝምድና እሱ ትልቅ ሚና እንዳለው መገንዘብ ማለት ነው። ኢየሱስ አይሁዳውያንን ከሕጉ እርግማን ነፃ ለማድረግ በመከራ እንጨት ላይ መሰቀል ነበረበት፤ ይሁንና የእሱ ሞት ከዚያም የበለጠ ጥቅም አለው። (ገላ. 3:13) ለሰው ዘር በሙሉ የሚያስፈልገውን ቤዛዊ መሥዋዕት ከፍሏል። (ኤፌ. 2:15, 16፤ ቆላ. 1:20፤ 1 ዮሐ. 2:1, 2) ኢየሱስ ይህን ለማድረግ የፍትሕ መዛባትን፣ ስድብን፣ ሥቃይን መቋቋም በመጨረሻም መሞት ግድ ሆኖበታል። ለከፈለው መሥዋዕት ምን ያህል አድናቆት አለህ? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ በ1912 ከበረዶ ዓለት ጋር ተጋጭታ በሰመጠችው ታይታኒክ የተባለች መርከብ ላይ የተሳፈርክ የ12 ዓመት ልጅ ነህ እንበል። ከአደጋው ለመትረፍ ስትል በሕይወት አድን ጀልባ ላይ ለመሳፈር ስትሞክር ጀልባው ሙሉ ሆነብህ። ሆኖም በሕይወት አድን ጀልባው ላይ ተሳፍሮ የነበረ አንድ ሰው ሚስቱን በመሳም ከተሰናበተ በኋላ ወደ መርከቡ በመመለስ በምትኩ አንተን አሳፈረህ። በዚህ ጊዜ ምን ይሰማሃል? በጣም እንደምታመሰግነው ምንም ጥርጥር የለውም! እንዲህ ያለው ሁኔታ አጋጥሞት የነበረ አንድ ልጅ ምን ተሰምቶት እንደነበር መገመት አያዳግትህም። * ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለአንተ ያደረገው ከዚህ እጅግ የላቀ ነው። እሱ የሞተልህ ለዘላለም እንድትኖር ነው።

11 የአምላክ ልጅ ለአንተ ያደረገልህን ነገር ስታውቅ ምን ተሰምቶህ ነበር? (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15ን አንብብ።) ጥልቅ የአድናቆት ስሜት ተሰምቶህ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ደግሞ ሕይወትህን ለአምላክ እንድትወስንና ‘ለራስህ ከመኖር ይልቅ ለአንተ ሲል ለሞተው እንድትኖር’ ገፋፍቶሃል። በወልድ ስም መጠመቅ ሲባል ኢየሱስ ለአንተ ያደረገውን መረዳት እንዲሁም ‘የሕይወት ዋና ወኪል’ እንዲሆን የተሰጠውን ሥልጣን መቀበል ማለት ነው። (ሥራ 3:15፤ 5:31) ከመጠመቅህ በፊት ከፈጣሪ ጋር ገና ዝምድና ስላልመሠረትክ የተጨበጠ ተስፋ አልነበረህም። አሁን ግን በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ላይ እምነት በማሳደርና በመጠመቅ ከአብ ጋር ዝምድና መመሥረት ችለሃል። (ኤፌ. 2:12, 13) ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “እናንተ በአንድ ወቅት አእምሯችሁ በክፉ ሥራዎች የተጠመደ ስለነበር ከአምላክ የራቃችሁና ጠላቶች ነበራችሁ፤ አሁን ግን [አምላክ] ቅዱሳንና እንከን የሌለባችሁ . . . አድርጎ በፊቱ ሊያቀርባችሁ ስለፈለገ ራሱን ለሞት አሳልፎ በሰጠው [በኢየሱስ] ሥጋዊ አካል አማካኝነት እንደገና ከራሱ ጋር አስታርቋችኋል።”—ቆላ. 1:21, 22

12, 13. (ሀ) በወልድ ስም መጠመቅህ አንድ ሰው ሲያስቀይምህ ምን እንድታደርግ ሊያነሳሳህ ይገባል? (ለ) በኢየሱስ ስም የተጠመቅክ ክርስቲያን መሆንህ ምን ኃላፊነት ያስከትልብሃል?

12 በወልድ ስም የተጠመቅክ ቢሆንም እንኳ የኃጢአት ዝንባሌ ያለህ መሆኑን በሚገባ ታውቃለህ። ይህን ማወቅህ ደግሞ በየዕለቱ እንደሚጠቅምህ እሙን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ሲያስቀይምህ ሁለታችሁም ኃጢአተኞች መሆናችሁን ግምት ውስጥ ታስገባለህ? ሁለታችሁም አምላክ ይቅር እንዲላችሁ ትፈልጋላችሁ፤ እንዲሁም ሁለታችሁም ይቅር ባዮች መሆን ይኖርባችኋል። (ማር. 11:25) ኢየሱስ የዚህን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ለመግለጽ አንድ ምሳሌ ተናገረ፤ አንድ ጌታ ለባሪያው የነበረበትን አሥር ሺህ ታላንት (60 ሚሊዮን ዲናር) ዕዳ ሰረዘለት። ብዙም ሳይቆይ ይህ ባሪያ ለሌላ ባሪያ አበድሮት የነበረውን አንድ መቶ ዲናር ለመሰረዝ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ኢየሱስ ነጥቡን ግልጽ ለማድረግ ሲል ‘ይሖዋ ወንድሙን ይቅር የማይለውን ሰው ይቅር አይለውም’ በማለት ተናገረ። (ማቴ. 18:23-35) በእርግጥም በወልድ ስም መጠመቅ ሲባል የኢየሱስን ሥልጣን መቀበል እንዲሁም እሱ የተወውን ምሳሌና ያስተማረውን ትምህርት ለመከተል ጥረት ማድረግ ማለት ነው፤ ከትምህርቶቹ መካከል ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ስለመሆን የሰጠው ትምህርት ይገኝበታል።—1 ጴጥ. 2:21፤ 1 ዮሐ. 2:6

13 ፍጽምና ስለሚጎድልህ የኢየሱስን ምሳሌ ሙሉ በሙሉ መከተል አትችልም። ያም ሆኖ በሙሉ ልብህ ራስህን ለአምላክ ስለወሰንክ አቅምህ የፈቀደውን ያህል የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ትፈልጋለህ። ይህ ደግሞ አሮጌውን ስብዕና ጥሎ አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። (ኤፌሶን 4:20-24ን አንብብ።) አንድ የምታከብረው ጓደኛ ካለህ ምሳሌውን ለመከተልና ያሉትን ግሩም ባሕርያት ለመምሰል ጥረት እንደምታደርግ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ከክርስቶስ ለመማርና የእሱን ምሳሌ ለመከተል እንደምትፈልግ አይካድም።

14. ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ እንዲገዛ የተሰጠውን ሥልጣን እንደምትቀበል ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

14 በወልድ ስም መጠመቅ የሚጨምራቸውን ነገሮች እንደተገነዘብክ ማሳየት የምትችልበት ሌላም መንገድ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ሁሉንም ነገር [ከኢየሱስ እግር] በታች አስገዛለት፤ ከጉባኤው ጋር በተያያዘም በሁሉ ነገር ላይ ራስ አደረገው” ይላል። (ኤፌ. 1:22) ስለሆነም ኢየሱስ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሰዎችን ለመምራት የሚጠቀምበትን መንገድ ማክበር ይኖርብሃል። ክርስቶስ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን በተለይም በመንፈሳዊ የሸመገሉ ይኸውም የተሾሙ ሽማግሌዎችን ይጠቀማል። እነዚህ ሰዎች የሚሾሙት ‘ቅዱሳንን እንዲያስተካክሉና የክርስቶስን አካል እንዲገነቡ ነው።’ (ኤፌ. 4:11, 12) ፍጹም ያልሆነ አንድ ሰው ስህተት ቢሠራ እንኳ በሰማይ የሚገኘው መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ነገሩን በራሱ ጊዜና መንገድ ይፈታዋል። ይህን ታምናለህ?

15. በአሁኑ ጊዜ ያልተጠመቅክ ከሆንክ ስትጠመቅ ምን በረከቶችን እንደምታገኝ ትጠብቃለህ?

15 በሌላ በኩል ግን ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ያልተጠመቁ አንዳንድ ሰዎች አሉ። እስካሁን ካልተጠመቅክ ከላይ የተመለከትናቸው ሐሳቦች የወልድን ሥልጣን መቀበሉ ምክንያታዊ እንደሆነ እንዲሰማህ አላደረገህም? ደግሞስ አመስጋኝ መሆንህን እንድታሳይ አልገፋፋህም? በወልድ ስም መጠመቅህ ታላላቅ በረከቶችን ለማግኘት ብቁ እንድትሆን ያስችልሃል።—ዮሐንስ 10:9-11ን አንብብ።

በመንፈስ ቅዱስ ስም

16, 17. በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

16 በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው? ከላይ እንደተገለጸው በጴንጤቆስጤ ዕለት ጴጥሮስን ያዳምጡ የነበሩ ሰዎች ስለ መንፈስ ቅዱስ ያውቁ ነበር። እንዲያውም አምላክ ቅዱስ መንፈሱን መጠቀሙን እንደቀጠለ የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎችን ተመልክተው ሊሆን ይችላል። ጴጥሮስ ‘በመንፈስ ቅዱስ ከተሞሉትና በተለያዩ ልሳኖች መናገር ከጀመሩት’ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። (ሥራ 2:4, 8) “በ . . . ስም” የሚለው አገላለጽ ስብዕና ያለውን አካል ስም ያመለክታል ማለት አይደለም። በዛሬው ጊዜ “በመንግሥት ስም” በርካታ ነገሮች ይደረጋሉ፤ መንግሥት ደግሞ ስብዕና ያለው አካል አይደለም። እነዚህ ነገሮች የሚደረጉት በመንግሥት ሥልጣን ነው። በተመሳሳይም በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚጠመቅ ሰው መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ አካል ሳይሆን የይሖዋ ኃይል መሆኑን ይቀበላል። አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቋል ሲባል መንፈስ ቅዱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና አምኖ ተቀብሏል ማለት ነው።

17 መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ስለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ነገሮችን እንደተገነዘብክ ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን የጻፉት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው መሆኑን ተረድተሃል። (2 ጢሞ. 3:16) መንፈሳዊ እድገት እያደረግህ ስትመጣ “በሰማይ ያለው አባት” አንተን ጨምሮ ‘ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ’ ስለመሆኑ ጥልቅ ግንዛቤ እንዳገኘህ ምንም ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 11:13) በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ በአንተም ሕይወት ውስጥ እንደሚሠራ ተመልክተህ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ እስከ አሁን በመንፈስ ቅዱስ ስም ካልተጠመቅክ ኢየሱስ ‘አብ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥ’ ማረጋገጫ መስጠቱ አንተም ወደፊት ይህን መንፈስ ስትቀበል አስደሳች በረከቶችን እንደምታገኝ እንድትተማመን ያደርግሃል።

18. በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚጠመቁ ሰዎች ምን በረከቶች ያገኛሉ?

18 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ክርስቲያን ጉባኤን በመንፈሱ አማካኝነት በመምራት ላይ እንደሆነ ግልጽ ነው። በተጨማሪም ይህ መንፈስ በየዕለቱ በምናደርገው እንቅስቃሴ በግለሰብ ደረጃ ይረዳናል። በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ ይህ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ የሚጫወተውን ሚና መረዳትንና ከዚህ መንፈስ ጋር በደስታ መተባበርን ይጨምራል። ይሁንና አንዳንዶች ‘ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን መኖር የምንችለው እንዴት ነው? መንፈስ ቅዱስስ በዚህ ረገድ የሚረዳን እንዴት ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ይህን በሚቀጥለው ጥናት ላይ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 የጥቅምት 22, 1981 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 3-8 ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• በአብ ስም መጠመቅ ምን ነገሮችን እንድታደርግ ይጠይቅብሃል?

• በወልድ ስም መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው?

• በአብና በወልድ ስም መጠመቅ ያለውን ትርጉም እንደተገነዘብክ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

• በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል በኋላ ደቀ መዛሙርት የሆኑ ሰዎች ከአብ ጋር ምን ዓይነት ዝምድና መሥርተዋል?

[የሥዕል ምንጭ]

By permission of the Israel Museum, Jerusalem