ታስታውሳለህ?
ታስታውሳለህ?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
• መሲሑ መሞት የነበረበት ለምንድን ነው?
የኢየሱስ መሞት፣ ፍጹም የሆነ ሰው በጣም ከባድ ፈተና ቢደርስበትም እንኳ ምንጊዜም ለአምላክ ያደረ ሊሆን እንደሚችል አረጋግጧል። በተጨማሪም ኢየሱስ፣ በአዳም ዘሮች ላይ የተጣለውን የኃጢአት ቅጣት በማስቀረት ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መንገድ ከፍቷል።—12/15 ከገጽ 22-23
• አንድ ሰው ለአልኮል ትክክለኛ አመለካከት ለማዳበር ምን ሊረዳው ይችላል?
ጸሎትና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሊረዳው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር፣ በአቋም መጽናትና ጥሩ ጓደኞች መምረጥ ግለሰቡ ለአልኮል ተገቢ አመለካከት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። አንድ ሰው ለመጠጣት ከመረጠ ገደብ ማበጀትና ከዚያ በላይ እንዲጠጣ ግብዣ ሲቀርብለት አልፈልግም ማለትን መማር ይገባዋል።—1/1 ከገጽ 7-9
• ከልጆች ጋር ትርጉም ያለው የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ምን ነገሮችን ይጨምራል?
የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ሲባል ከልጆቻችሁ ጋር ማውራት ማለት ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ጥያቄ መጠየቅን ብሎም የሚሰጡትን መልስ በትዕግሥት ማዳመጥን ያጠቃልላል። በርካታ ቤተሰቦች፣ የምግብ ሰዓት የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተገንዝበዋል።—1/15 ገጽ 18,19
• ይሖዋ ፍጹም ሆኖ ሳለ ሊጸጸት የሚችለው እንዴት ነው?
አምላክ ለሰዎች የነበረውን አመለካከት የሚለውጥበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜያት ይሖዋን በመተው ሌሎች አማልክትን ተከትለዋል። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ለእነሱ ጥበቃ ማድረጉን ትቶ ነበር። ይሁንና ሕዝቡ በሠሩት ስህተት ሲያዝኑና አምላክ እንዲረዳቸው ወደ እሱ ሲጮኹ ለእነሱ የነበረው አመለካከት ተለውጧል ወይም ‘ተጸጽቷል።’ (መሳ. 2:18 NW)—2/1 ገጽ 21
• ድጋሚ መጠመቅ አስፈላጊ ሊሆን የሚችለው መቼ ነው?
ይህ ሊሆን የሚችለው አንድ ሰው በተጠመቀበት ወቅት ይከተለው የነበረው አኗኗር ወይም በድብቅ ይፈጽመው የነበረው ድርጊት፣ ተቀባይነት ባለው ሁኔታ ተጠምቆ ቢሆን ኖሮ ከጉባኤ ሊያስወግደው የሚችል ዓይነት ከሆነ ነው።—2/15 ገጽ 22
• አንዳንዶች ሐቀኝነት የጎደለው ተግባር ሲፈጽሙ ሰበብ አድርገው የሚያቀርቧቸው ሦስት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
ድሆች መሆናቸው ለመስረቅ ሰበብ እንደሚሆናቸው የሚሰማቸው ሰዎች አሉ። ሌሎች ደግሞ “ሁሉም ሰው የሚያደርገው ነው” የሚል ሰበብ ያቀርባሉ። አንዳንዶች በጣም ውድ የሆነ ነገር ወድቆ ሲያገኙ ለራሳቸው ይወስዱታል፤ “የወደቀ አንሱ” የሚለውን አባባል በመጥቀስ ድርጊታቸው ትክክል እንደሆነ ምክንያት ያቀርባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉት ምክንያቶች ትክክል እንደሆኑ አይገልጽም።—3/1 3/1, ከገጽ 12-14
• ኢየሱስ ስለ ስንዴውና እንክርዳዱ በተናገረው ምሳሌ ላይ ጥሩውን ዘር የመዝራቱ ሥራ ምን ያመለክታል?
የሰው ልጅ ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ጊዜያት ውስጥ እርሻውን አለስልሶ ለዘር አዘጋጅቷል። ጥሩው ዘር መዘራት የጀመረው በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ ዕለት አንስቶ ክርስቲያኖች የአምላክ ልጆች ይኸውም የመንግሥቱ ልጆች ሆነው ሲቀቡ ነው።—3/15 ገጽ 20
• ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተገለጸው ምሳሌያዊ ስንዴ ወደ ይሖዋ ጎተራ እየገባ ያለው እንዴት ነው? (ማቴ. 13:30)
ስንዴውን ወደ ጎተራው የማስገባቱ ሥራ በሥርዓቱ መደምደሚያ ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ቀጥሏል። ስንዴው ወደ ይሖዋ ጎተራ ገባ ሊባል የሚችለው በስንዴ የተመሰሉት የተቀቡ የመንግሥቱ ልጆች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሲታቀፉ ወይም በሰማይ ሽልማታቸውን ሲያገኙ ነው።—3/15 ገጽ 22
• የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መሆን ያለባቸው የትኞቹ መጻሕፍት እንደሆኑ የወሰነው ማን ነው?
ይህንን የወሰነው የአንድ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ወይም ሃይማኖታዊ መሪ አይደለም። ከዚህ ይልቅ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከአምላክ ቅዱስ መንፈስ ባገኙት አመራር አማካኝነት በትክክል በመንፈስ መሪነት የተጻፉት መጻሕፍት የትኞቹ እንደሆኑ ለይተው ማወቅ ችለዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ከተሰጡት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አንዱ “በመንፈስ መሪነት የተነገረን ቃል የመረዳት” ችሎታ መሆኑ ከላይ የተገለጸውን ሐቅ የሚደግፍ ነው። (1 ቆሮ. 12:4, 10)—4/1 ገጽ 28