በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቶስን ሙሉ በሙሉ እየተከተላችሁት ነው?

ክርስቶስን ሙሉ በሙሉ እየተከተላችሁት ነው?

ክርስቶስን ሙሉ በሙሉ እየተከተላችሁት ነው?

‘በዚሁ መንገድ እየተመላለሳችሁ ነው፤ ይህንኑ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማድረጋችሁን ቀጥሉ።’—1 ተሰ. 4:1

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን የኖሩ ብዙ ሰዎች ምን አስደናቂ ነገሮች ሲከናወኑ ተመልክተዋል? (ለ) እኛ የምንኖርበት ዘመንም ታሪካዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት በሕይወት መኖር ምን ያህል አስደሳች ሊሆን እንደሚችል አስበህ ታውቃለህ? ኢየሱስ ከሕመምህ ይፈውስህና በሽታው ካስከተለብህ ጭንቀት ይገላግልህ እንደነበር ታስብ ይሆናል። ወይም ደግሞ ኢየሱስ ሲናገር ለመስማትና የሚያደርጋቸውን ነገሮች ለማየት ትጓጓ ይሆናል፤ ምናልባትም እሱ ሲያስተምር ለማዳመጥ ወይም አንዳንድ ተአምራትን ሲፈጽም ለማየት ትፈልግ ይሆናል። (ማር. 4:1, 2፤ ሉቃስ 5:3-9፤ 9:11) ኢየሱስ እነዚያን ሁሉ አስደናቂ ነገሮች ሲያከናውን በዚያ መገኘት ቢቻል ኖሮ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ይሆን ነበር! (ሉቃስ 19:37) ከዚያ ጊዜ ወዲህ እንዲህ ዓይነት ክንውኖችን የተመለከተ ትውልድ የለም፤ ኢየሱስ “ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ” በምድር ላይ ያከናወነው ነገርም የሚደገም አይደለም።—ዕብ. 9:26፤ ዮሐ. 14:19

2 እኛም የምንኖረው ታሪካዊ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የምንኖረው ቅዱሳን መጻሕፍት ‘የፍጻሜው ዘመን’ እንዲሁም ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ብለው በሚጠሩት ጊዜ ውስጥ ነው። (ዳን. 12:1-4, 9፤ 2 ጢሞ. 3:1) ሰይጣን ዲያብሎስ ከሰማይ የተወረወረው በዚህ ዘመን ነው። በቅርቡ ደግሞ ታስሮ “ወደ ጥልቁ” ይጣላል። (ራእይ 12:7-9, 12፤ 20:1-3) በተጨማሪም በዚህ ዘመን ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በዓለም ዙሪያ በማወጁ ሥራ የመካፈል ታላቅ መብት አግኝተናል፤ ወደፊት በገነት ውስጥ የመኖር ተስፋ እንዳለ ለሰዎች በመናገር የምናከናውነው ይህ ሥራ ፈጽሞ የሚደገም አይደለም።—ማቴ. 24:14

3. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ተከታዮቹ ምን እንዲያደርጉ ነግሯቸው ነበር? ይህስ ምን ይጨምራል?

3 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለተከታዮቹ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8) በምድር ዙሪያ የሚከናወነው ይህ ሥራ ማስተማርንም ይጨምራል። የዚህ ሥራ ዓላማ ምንድን ነው? መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የክርስቶስ ተከታዮች የሚሆኑ ሌሎች ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ታዲያ ክርስቶስ የሰጠንን ተልእኮ ከፍጻሜው ለማድረስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

4. (ሀ) በ⁠2 ጴጥሮስ 3:11, 12 ላይ የሚገኘው ጴጥሮስ የተናገረው ሐሳብ ምን የማድረግን አስፈላጊነት ያጎላል? (ለ) ምን እንዳንሆን መጠንቀቅ ያስፈልገናል?

4 ሐዋርያው ጴጥሮስ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል! . . . የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ ይገባል!” (2 ጴጥ. 3:11, 12) ጴጥሮስ የተናገረው ሐሳብ፣ በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሕይወታችን ምንጊዜም ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮችን በመፈጸም ላይ ያተኮረ እንዲሆን ከፈለግን ነቅተን መኖራችን አስፈላጊ መሆኑን ያጎላል። እነዚህ ተግባሮች ምሥራቹን መስበክን ይጨምራሉ። በመሆኑም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞቻችን ክርስቶስ የሰጠውን የስብከት ተልእኮ በቅንዓት እያከናወኑ መሆናቸውን መመልከት እንዴት የሚያስደስት ነው! በሌላ በኩል ደግሞ በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት ወደ ሥጋዊ ነገሮች የምናዘነብል መሆናችን የሰይጣን ዓለም በየዕለቱ ከሚያሳድርብን ተጽዕኖ ጋር ተዳምሮ ለአምላክ አገልግሎት ያለንን ቅንዓት እንዳያቀዘቅዝብን መጠንቀቅ እንደሚገባን እንገነዘባለን። እንግዲያው ክርስቶስን መከተላችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

አምላክ የሰጠንን ኃላፊነቶች በደስታ ተቀበሉ

5, 6. (ሀ) ጳውሎስ በኢየሩሳሌም የነበሩ የእምነት ባልንጀሮቹን ያመሰገናቸው ለምን ነበር? ምን ማስጠንቀቂያስ ሰጥቷቸዋል? (ለ) አምላክ የሰጠንን ኃላፊነቶች አቅልለን ልንመለከታቸው የማይገባው ለምንድን ነው?

5 ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ለሚገኙት ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እነዚህ የእምነት ባልንጀሮቹ ስደት ቢደርስባቸውም በታማኝነት በመጽናታቸው አመስግኗቸዋል። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ በመከራ ውስጥ በብርቱ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀድሞውን ጊዜ ዘወትር አስታውሱ።” አዎን፣ ይሖዋም ያሳዩትን ታማኝነት አልረሳም። (ዕብ. 6:10፤ 10:32-34) እነዚያ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ጳውሎስ በጻፈላቸው የአድናቆት ቃላት በጣም ተበረታትተው መሆን አለበት። ይሁንና በዚያው ደብዳቤ ላይ ጳውሎስ፣ ካልተቆጣጠሩት ለአምላክ አገልግሎት ያላቸውን ቅንዓት ሊቀንስባቸው ስለሚችል በሰዎች ላይ የሚታይ አንድ ዝንባሌ አስጠንቅቋቸው ነበር። ክርስቲያኖች የአምላክን ትእዛዝ ከመፈጸም ‘ወደኋላ እንዳይሉ’ ወይም ትእዛዙን ላለመፈጸም ሰበብ አስባብ እንዳያቀርቡ አሳስቧቸዋል።—ዕብ. 12:25

6 የዕብራውያን ክርስቲያኖች አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነቶች በደስታ ከመቀበል ‘ወደኋላ የማለት’ አዝማሚያ እንዳይኖራቸው የተሰጣቸው ማሳሰቢያ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖችም ይሠራል። ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻችንን አቅልለን የመመልከት ዝንባሌ እንዳይጠናወተን ወይም ለአምላክ አገልግሎት ያለን ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችን አስፈላጊ መሆኑን እንገነዘባለን። (ዕብ. 10:39) ደግሞም ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው።—1 ጢሞ. 4:16

7, 8. (ሀ) ለአምላክ አገልግሎት ያለንን ቅንዓት ጠብቀን ለመመላለስ ምን ሊረዳን ይችላል? (ለ) የቀድሞ ቅንዓታችን በተወሰነ መጠን እንደቀዘቀዘ ከተሰማን ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

7 አምላክ የሰጠንን ኃላፊነቶች ላለመፈጸም ሰበብ የመፍጠር አዝማሚያ እንዳይኖረን ምን ሊረዳን ይችላል? እንዲህ ያለውን አዝማሚያ ለመዋጋት የሚረዳን አንዱ ጠቃሚ ነገር ራሳችንን ስንወስን የገባነው ቃል ምን ትርጉም እንዳለው አዘውትረን ማሰላሰል ነው። ራሳችንን ወስነናል ሲባል በሕይወታችን ውስጥ አንደኛ ቦታ የምንሰጠው ለአምላክ ፈቃድ እንደሚሆን ለይሖዋ ቃል ገብተናል ማለት ነው፤ ይህንን ቃላችንንም መጠበቅ እንፈልጋለን። (ማቴዎስ 16:24ን አንብብ።) በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ቆም ብለን ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘በተጠመቅሁበት ጊዜ ለአምላክ ከገባሁት ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር የነበረኝ ቁርጥ ውሳኔ አሁንም እንዳለ ነው? ወይስ መጀመሪያ የነበረኝ ቅንዓት ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ቀንሷል?’

8 ራሳችንን በሐቀኝነት ስንመረምር በተወሰነ መጠንም ቢሆን ቅንዓታችን እንደቀዘቀዘ ከተሰማን ነቢዩ ሶፎንያስ የተናገራቸውን የሚያበረታቱ ቃላት ማስታወሳችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እጆችሽም አይዛሉ። አምላክሽ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፤ እርሱ የሚታደግ ኀያል ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል።” (ሶፎ. 3:16, 17) ይህ የሚያበረታታ ሐሳብ በመጀመሪያ የተነገረው ከባቢሎን ምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም ለተመለሱት የጥንት እስራኤላውያን ነበር። ይሁንና ይህ ማበረታቻ በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦችም ይሠራል። የምናከናውነው የይሖዋን ሥራ በመሆኑ አምላክ የሰጠንን ኃላፊነቶች በተሟላ መንገድ እንድንወጣ ይሖዋም ሆነ ልጁ ከጎናችን ሆነው እንደሚደግፉንና እንደሚያጠነክሩን ማስታወስ ይኖርብናል። (ማቴ. 28:20፤ ፊልጵ. 4:13) የአምላክን ሥራ በቅንዓት ማከናወናችንን ለመቀጠል ጥረት ካደረግን ይሖዋ የሚባርከን ከመሆኑም ሌላ በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።

በቅንዓት “አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት” ፈልጉ

9, 10. ኢየሱስ ስለ ታላቁ የራት ግብዣ በተናገረው ምሳሌ ላይ ሊያስተላልፍ የፈለገው ቁም ነገር ምንድን ነው? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

9 ኢየሱስ በአንድ የፈሪሳውያን አለቃ ቤት ምግብ እየበላ ሳለ ስለ አንድ ትልቅ የራት ግብዣ የሚገልጽ ምሳሌ ተናገረ። በምሳሌው ላይ የተለያዩ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ስለቀረበላቸው ግብዣ ገለጸ። እንዲሁም ‘ሰበብ ማቅረብ’ ወይም ወደኋላ ማለት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። (ሉቃስ 14:16-21ን አንብብ።) ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተጋበዙት እንግዶች በድግሱ ላይ ላለመገኘት የተለያዩ ሰበቦች አቅርበዋል። አንደኛው፣ እርሻ ስለገዛ ሄዶ ማየት እንዳለበት ተናገረ። ሌላው ከብቶች እንደገዛና ሊፈትናቸው እንደሚፈልግ ገለጸ። ሌላኛው ደግሞ ‘ገና ማግባቴ ስለሆነ መምጣት አልችልም’ አለ። እነዚህ የማይረቡ ምክንያቶች ነበሩ። አንድ ሰው እርሻ ወይም ከብቶች ከመግዛቱ በፊት አስቀድሞ ማየቱ ስለማይቀር ከገዛ በኋላ እርሻውን ለማየት ወይም ከብቶቹን ለመፈተን ያን ያህል የሚያጣድፈው ነገር የለም። አንድ ሰው በቅርቡ ማግባቱስ ቢሆን እንዲህ ባለ አስፈላጊ ግብዣ ላይ እንዳይገኝ እንዴት ሊያግደው ይችላል? በእርግጥም ጋባዡ በሁኔታው መቆጣቱ ምንም አያስገርምም!

10 ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች ኢየሱስ ከተናገረው ምሳሌ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ምን ዓይነት ትምህርት? በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተገለጹት ያሉት የግል ጉዳዮች በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ በመያዛቸው ለአምላክ ለምናቀርበው አገልግሎት ሁለተኛ ደረጃ እንድንሰጥ እንዲያደርጉን ፈጽሞ መፍቀድ የለብንም። አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ውስጥ ለግል ጉዳዮች ከሚገባው በላይ ቦታ የሚሰጥ ከሆነ ለአገልግሎት ያለው ቅንዓት ቀስ በቀስ ይቀንሳል። (ሉቃስ 8:14ን አንብብ።) ይህ ነገር በእኛ ላይ እንዳይደርስ ከፈለግን ኢየሱስ የሰጠውን “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋችሁን ቀጥሉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን። (ማቴ. 6:33) ወጣት አዋቂ ሳይል ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ይህንን ጠቃሚ ምክር በሥራ ሲያውሉ መመልከት ምንኛ የሚያበረታታ ነው! እንዲያውም ብዙዎች በአገልግሎት ላይ ተጨማሪ ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል ለማድረግ የሚያስችሏቸውን እርምጃዎች ወስደዋል። እነዚህ ወንድሞች በቅንዓት አስቀድሞ የአምላክን መንግሥት መፈለግ እውነተኛ ደስታና ታላቅ እርካታ እንደሚያስገኝ በራሳቸው ሕይወት ተመልክተዋል።

11. አምላክን በቅንዓትና በሙሉ ልብ የማገልገልን አስፈላጊነት የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ተናገር።

11 በአምላክ አገልግሎት ቀናተኛ የመሆንን አስፈላጊነት በምሳሌ ለማስረዳት የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በዮአስ ሕይወት ውስጥ የተከናወነውን ነገር እንመልከት። ዮአስ፣ እስራኤላውያን በሶርያውያን እጅ ይወድቃሉ የሚል ፍርሃት ስላደረበት ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ መጥቶ አለቀሰ። ኤልሳዕም በመስኮት በኩል ወደ ሶርያ አቅጣጫ አንድ ቀስት እንዲያስፈነጥር ለዮአስ ነገረው፤ ይህን ማድረጉ በይሖዋ እርዳታ በዚያ ብሔር ላይ ድል እንደሚቀዳጅ የሚያሳይ ነበር። ይህ ንጉሡን በቅንዓት እንዲነሳሳ ሊያደርገው እንደሚገባ ጥርጥር የለውም። ኤልሳዕ ቀጥሎም ቀስቶቹን በመውሰድ መሬቱን እንዲወጋ ለዮአስ ነገረው። ዮአስ ግን መሬቱን ሦስት ጊዜ ብቻ ወግቶ አቆመ። ኤልሳዕ ይህን ሲያይ ተቆጣ፤ ምክንያቱም መሬቱን አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መውጋት ‘ሶርያን ማሸነፍንና ፈጽሞ መደምሰስን’ ያመለክት ነበር። አሁን ግን ዮአስ የሚያሸንፈው ሦስት ጊዜ ብቻ በመሆኑ ድሉ የተሟላ አይሆንም። ዮአስ መሬቱን የወጋው ቅንዓት በጎደለው መንገድ ስለነበር ያገኘው ድል ውስን ሊሆን ችሏል። (2 ነገ. 13:14-19) ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ አትረፍርፎ የሚባርከን የሰጠንን ሥራ በሙሉ ልብና በቅንዓት ስንፈጽም ብቻ ነው።

12. (ሀ) በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ውጣ ውረዶች እየተቋቋምን አምላክን በቅንዓት ማገልገላችንን እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል? (ለ) በአገልግሎት ሥራ የበዛልህ መሆንህ ምን ጥቅም እንዳስገኘልህ ተናገር።

12 በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙን ውጣ ውረዶች አምላክን በቅንዓትና በፍቅር እንዳናገለግል ፈተና ሊሆኑብን ይችላሉ። በርካታ ወንድሞችና እህቶች የሚያጋጥማቸውን ከባድ የኢኮኖሚ ችግር መቋቋም አስፈልጓቸዋል። ሌሎች ደግሞ ያለባቸው ከባድ የጤና እክል በይሖዋ አገልግሎት የሚያደርጉትን ተሳትፎ ስለሚገድብባቸው ያዝናሉ። ያም ቢሆን እያንዳንዳችን ቅንዓታችንን ጠብቀን ለመኖርና ክርስቶስን ሙሉ በሙሉ መከተላችንን ለመቀጠል አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን። “ክርስቶስን መከተልህን እንድትቀጥል ምን ሊረዳህ ይችላል?” በሚለው ሣጥን ውስጥ የቀረቡትን አንዳንድ ሐሳቦችና ጥቅሶች እንድትመለከት እንጋብዝሃለን። እነዚህን ነጥቦች አቅምህ በፈቀደ መጠን ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ቆም ብለህ አስብ። ምክሮቹን ተግባራዊ ካደረግህ ብዙ በረከቶች ታጭዳለህ። በአገልግሎታችን ሥራ የበዛልን መሆናችን ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል፤ እንዲሁም ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን ብሎም የተትረፈረፈ ሰላምና ደስታ እንዲኖረን ያደርገናል። (1 ቆሮ. 15:58) ከዚህም በላይ አምላክን በሙሉ ነፍሳችን ማገልገላችን ‘የይሖዋን ቀን መምጣት በአእምሯችን አቅርበን እየተመለከትን ለመኖር’ ይረዳናል።—2 ጴጥ. 3:12

ራስህን በሐቀኝነት መርምር

13. እያንዳንዳችን አምላክን በሙሉ ነፍስ እያገለገልን መሆናችንን ለማወቅ ምን ማድረግ እንችላለን?

13 አምላክን በሙሉ ነፍስ ማገልገላችን በአገልግሎት በምናሳልፈው ሰዓት ብዛት ላይ የተመካ እንዳልሆነ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። የእያንዳንዱ ግለሰብ ሁኔታ የተለያየ ነው። አንድ ሰው በወር ውስጥ በመስክ አገልግሎት የሚያሳልፈው አንድ ወይም ሁለት ሰዓት ብቻ ቢሆን እንኳ ጤንነቱ የሚፈቅድለት ይህ እስከሆነ ድረስ አገልግሎቱ ይሖዋን በጣም ያስደስተዋል። (ከ⁠ማርቆስ 12:41-44 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ እያንዳንዳችን አምላክን በሙሉ ነፍስ እያገለገልን መሆናችንን ለማወቅ አቅማችንንና ሁኔታችንን በተመለከተ ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመራችን አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበር እንፈልጋለን። (ሮም 15:5ን አንብብ፤ 1 ቆሮ. 2:16) ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሰጠው ነገር ምንድን ነው? በቅፍርናሆም ለተሰበሰቡት ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው።” (ሉቃስ 4:43፤ ዮሐ. 18:37) ኢየሱስ በአገልግሎቱ ያሳየውን ቅንዓት በአእምሮህ በመያዝ አንተም አገልግሎትህን ማስፋት ትችል እንደሆነ ሁኔታህን ገምግም።—1 ቆሮ. 11:1

14. በየትኞቹ መንገዶች አገልግሎታችንን ማስፋት እንችላለን?

14 ሁኔታችንን በቁም ነገር መመርመራችን በአገልግሎት የምናሳልፈውን ጊዜ መጨመር እንደምንችል እንድንገነዘብ ሊያደርገን ይችላል። (ማቴ. 9:37, 38) ለምሳሌ ያህል፣ በቅርቡ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶቻችን አገልግሎታቸውን ያሰፉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በአቅኚነት በቅንዓት መካፈል የሚያስገኘውን ደስታ እያጣጣሙ ነው። አንተም እንደዚህ ዓይነት ደስታ ማግኘት ትፈልጋለህ? አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ሁኔታቸውን ከመረመሩ በኋላ በአገራቸው ውስጥ ሌላው ቀርቶ በሌላ አገር የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ለመዛወር ወስነዋል። ሌሎች ደግሞ የውጪ አገር ዜጎችን ለመርዳት ሲሉ አዲስ ቋንቋ ተምረዋል። አገልግሎታችንን ማስፋት ተፈታታኝ ሊሆን ቢችልም በረከት ያስገኛል፤ እንዲሁም በርካታ ሰዎች “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ለመርዳት ያስችለናል።—1 ጢሞ. 2:3, 4፤ 2 ቆሮ. 9:6

ልንከተላቸው የሚገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች

15, 16. ቀናተኛ የክርስቶስ ተከታዮች በመሆን ረገድ የእነማንን ምሳሌ መከተል እንችላለን?

15 ሐዋርያት ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹ ክርስቶስ ተከታዮቹ እንዲሆኑ ግብዣ ባቀረበላቸው ጊዜ ምላሽ የሰጡት በምን መንገድ ነበር? ማቴዎስን በተመለከተ ዘገባው “ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ በመተው ተነስቶ ተከተለው” ይላል። (ሉቃስ 5:27, 28) ዓሣ ያጠምዱ የነበሩትን ጴጥሮስንና እንድርያስን በተመለከተ ደግሞ “ወዲያውኑም መረባቸውን ትተው ተከተሉት” ይላል። ቀጥሎም ኢየሱስ ከአባታቸው ጋር ሆነው መረባቸውን ይጠግኑ የነበሩትን ያዕቆብንና ዮሐንስን ተከታዮቹ እንዲሆኑ ጠራቸው። ኢየሱስ ላቀረበላቸው ግብዣ ምን ምላሽ ሰጡ? “ወዲያውኑም ጀልባዋንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።”—ማቴ. 4:18-22

16 ሌላው ግሩም ምሳሌ ደግሞ በኋላ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለው ሳኦል ነው። በጭፍን ጥላቻ ተሞልቶ የክርስቶስን ተከታዮች ያሳድድ የነበረ ቢሆንም አካሄዱን ቀይሮ የክርስቶስን ስም የሚሸከም “የተመረጠ ዕቃ” ለመሆን በቅቷል። “ወዲያውም [ጳውሎስ] ስለ ኢየሱስ እሱ የአምላክ ልጅ እንደሆነ በምኩራቦቹ ውስጥ መስበክ ጀመረ።” (ሥራ 9:3-22) ጳውሎስ ከፍተኛ ፈተናና ስደት ቢደርስበትም ቅንዓቱ ፈጽሞ አልቀዘቀዘም።—2 ቆሮ. 11:23-29፤ 12:15

17. (ሀ) ክርስቶስን በመከተል ረገድ ምኞትህ ምንድን ነው? (ለ) በሙሉ ልባችንና ኃይላችን የይሖዋን ፈቃድ ማድረጋችን ምን በረከቶች ያስገኝልናል?

17 ግሩም አርዓያ የሚሆኑንን የእነዚህን ደቀ መዛሙርት ምሳሌ መከተልና ክርስቶስን እንድንከተል ለቀረበልን ግብዣ ምንም ሳናቅማማ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደምንፈልግ ጥርጥር የለውም። (ዕብ. 6:11, 12) ክርስቶስን በቅንዓትና ሙሉ በሙሉ ለመከተል የማያቋርጥ ጥረት ማድረጋችን ምን በረከት ያስገኝልናል? የአምላክን ፈቃድ በማድረግ እውነተኛ ደስታ እናገኛለን፤ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶችንና ኃላፊነቶችን መቀበል የሚያመጣውን እርካታ እናገኛለን። (መዝ. 40:8፤ 1 ተሰሎንቄ 4:1ን አንብብ።) አዎን፣ ክርስቶስን ለመከተል ብርቱ ጥረት ማድረጋችን የአእምሮ ሰላም፣ እርካታ፣ ደስታ፣ የአምላክን ሞገስ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ተስፋና የመሳሰሉትን ዘላቂ የሆኑ የተትረፈረፉ በረከቶች ያስገኝልናል።—1 ጢሞ. 4:10

ታስታውሳለህ?

• ምን አስፈላጊ ሥራ ተሰጥቶናል? እንዴትስ ልንመለከተው ይገባል?

• የትኛውን ዝንባሌ እንዳናዳብር ልንጠነቀቅ ይገባል? ለምንስ?

• የትኞቹን ጉዳዮች በተመለከተ ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል?

• ክርስቶስን መከተላችንን ለመቀጠል ምን ሊረዳን ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ክርስቶስን መከተልህን እንድትቀጥል ምን ሊረዳህ ይችላል?

▪ የአምላክን ቃል በየቀኑ አንብብ፤ እንዲሁም ባነበብከው ነገር ላይ አሰላስል።—መዝ. 1:1-3፤ 1 ጢሞ. 4:15

▪ የአምላክን መንፈስ ድጋፍና መመሪያ ለማግኘት አዘውትረህ ጸልይ።—ዘካ. 4:6፤ ሉቃስ 11:9, 13

▪ ለአገልግሎቱ ከልብ የመነጨ ቅንዓት ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት መሥርት።—ምሳሌ 13:20፤ ዕብ. 10:24, 25

▪ የምንኖርበትን ጊዜ አጣዳፊነት ተገንዘብ።—ኤፌ. 5:15, 16

▪ ‘ሰበብ ማቅረብ’ የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት አስታውስ።—ሉቃስ 9:59-62

▪ ራስህን ስትወስን በገባኸው ቃል ላይ እንዲሁም ይሖዋን ማገልገልና ክርስቶስን በሙሉ ልብ መከተል በሚያስገኘው የተትረፈረፈ በረከት ላይ ዘወትር አሰላስል።—መዝ. 116:12-14፤ 133:3፤ ምሳሌ 10:22