በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አረጋውያንን ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?

አረጋውያንን ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?

አረጋውያንን ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?

በዓለማችን ብዙ ጊዜ ፎቶግራፍ በመነሳት ከሚታወቁት ዛፎች አንዱ በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ዳርቻ ላይ ይገኛል። ሎን ሳይፕረስ በመባል የሚታወቀው ይህ ዛፍ ከ250 ዓመት በላይ ዕድሜ እንዳለው ይነገርለታል። ለዘመናት በጽናት በመቆየቱ የሰዎችን ትኩረት የሚስበው ይህ ውብ ዛፍ በብዙ መንገዶች እንክብካቤ ይደረግለታል። ለምሳሌ ያህል፣ እንዳያዘምም ለማድረግ በገመድ ተወጥሮ የታሰረ ከመሆኑም በላይ በዙሪያው የድንጋይ ካብ ተሠርቶለታል።

ሎን ሳይፕረስ በመካከላችን የሚገኙ ጽናት በማሳየት ረገድ ተጠቃሽ የሆኑ አረጋውያን ክርስቲያኖችን ያስታውሰናል። ይህን ጽናት የሚያሳዩበት አንዱና የላቀው መንገድ ምሥራቹን በማወጅ ነው። ነቢዩ ኢዩኤል ‘ሽማግሌዎች’ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እንደሚያውጁ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ኢዩ. 2:28-32፤ ሥራ 2:16-21) እነዚህ አረጋውያን ሌሎች ስለ “መንግሥቱ ምሥራች” እንዲማሩ ከልባቸው ለመርዳት ሲሉ ምን ያህል ሰዓታትን እንደሚያሳልፉ እስቲ አስብ! (ማቴ. 24:14) የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ከሆኑት ከእነዚህ አረጋውያን መካከል አንዳንዶቹ ለብዙ ዓመታት የደረሰባቸውን ስደት ወይም አስቸጋሪ ሁኔታ በጽናት አሳልፈዋል። አንድ ዛፍ እንኳ በጽናቱ የሰዎችን ትኩረት ከሳበ እንዲሁም ድጋፍ እንዲሆነው የድንጋይ ካብና መወጠሪያ ገመድ ከተደረገለት በመካከላችን የሚገኙት አረጋውያን የበለጠ ትኩረት ሊሰጣቸውና በአክብሮት ሊያዙ አይገባቸውም?

ይሖዋ አምላክ የጥንት ሕዝቦቹን “ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር” በማለት አዟቸው ነበር። (ዘሌ. 19:32) በዛሬው ጊዜ ካሉት የይሖዋ አገልጋዮች መካከል ለብዙ አሥርተ ዓመታት ‘ከአምላክ ጋር የሄዱ’ እንዲሁም ታማኝነት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ክርስቲያኖች እናገኛለን። (ሚክ. 6:8 የ1954 ትርጉም) እነዚህ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋላቸውን በቀጠሉ መጠን በእርግጥም ሽበታቸው “የክብር ዘውድ” ይሆንላቸዋል።—ምሳሌ 16:31

ሐዋርያው ጳውሎስ “ሽማግሌ የሆነውን በኃይለ ቃል አትናገረው” በማለት ለወጣቱ ጢሞቴዎስ መመሪያ ሰጥቶት ነበር። ከዚህ ይልቅ “እንደ አባት በአክብሮት” ሊመክረው ይገባ ነበር። እንዲሁም “አሮጊቶችን እንደ እናቶች” አድርጎ መያዝ ነበረበት። (1 ጢሞ. 5:1, 2) ጢሞቴዎስ በዕድሜ የገፉትን በዚህ መልኩ መያዙ በሽበታሙ ፊት ‘የተነሳ’ ያህል ሊቆጠር ይችላል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ በአነጋገራችን እንዲህ ያለውን አክብሮት እንድናሳይ ይጠብቅብናል።

ሮም 12:10 “አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ” በማለት ይናገራል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ የበላይ ተመልካቾች ለአረጋውያን ክርስቲያኖች ክብር እንደሚያሳዩ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ሁላችንም አንዳችን ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ መሆን አለብን።

እርግጥ ነው፣ የቤተሰብ አባላት ወላጆቻቸውንና አያቶቻቸውን በመንከባከብ ረገድ ተቀዳሚ ኃላፊነት አለባቸው። ሰዎች ሎን ሳይፕረስ የተባለውን ዛፍ ሕይወት ለማቆየት የተለያዩ መንገዶችን ያፈላለጉ ሲሆን ወደፊትም ይህን ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ። እኛም በተመሳሳይ በዕድሜ የገፉ ወላጆቻችንንና አያቶቻችንን ክብር ለመጠበቅ የሚያስችሉንን መንገዶች ሁሉ መፈለግ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ጥሩ አዳማጭ መሆናችን የእነሱን ስሜት ግምት ውስጥ ሳናስገባ ነገሮች እኛ በምንፈልገው መንገድ እንዲደረጉ ከመጫን እንድንቆጠብ ያደርገናል።—ምሳሌ 23:22፤ 1 ጢሞ. 5:4

በመካከላችን የሚገኙት አረጋውያን ለይሖዋ በጣም ውድ ናቸው። ይሖዋ ፈጽሞ አይተዋቸውም። (መዝ. 71:18) እንዲያውም እውነተኛው አምላክ እሱን በታማኝነት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ያጠናክራቸዋል። እኛም አረጋውያንን መደገፋችንንና ማክበራችንን እንቀጥል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሎን ሳይፕረስ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ሁሉ አረጋውያንም የእኛ ድጋፍና አክብሮት ያስፈልጋቸዋል

[ምንጭ]

American Spirit Images/age fotostock