በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ሴቶች፣ ለራስነት ሥልጣን መገዛት ያለባችሁ ለምንድን ነው?

እናንት ሴቶች፣ ለራስነት ሥልጣን መገዛት ያለባችሁ ለምንድን ነው?

እናንት ሴቶች፣ ለራስነት ሥልጣን መገዛት ያለባችሁ ለምንድን ነው?

“የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ [ነው]።”—1 ቆሮ. 11:3

1, 2. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋ የራስነት ሥልጣንንና ለዚህ ሥልጣን መገዛትን በተመለከተ ስላደረገው ዝግጅት ምን ብሏል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

ሐዋርያው ጳውሎስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ . . . የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ” በመናገር ይሖዋ ያቋቋመውን የሥልጣን ተዋረድ ገልጿል። (1 ቆሮ. 11:3) ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ፣ ራሱ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ሥልጣን መገዛት ያስደስተው የነበረ ከመሆኑም ሌላ እንደ ክብር ይቆጥረው ነበር። ክርስቲያን ወንዶችም ራስ እንዳላቸውና እሱም ክርስቶስ እንደሆነ ተመልክተናል። ክርስቶስ ሰዎችን በደግነት፣ በገርነት፣ በርኅራኄ እንዲሁም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ይይዝ ነበር። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንዶችም ከሌሎች በተለይም ከሚስቶቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት እነዚህን ባሕርያት ማሳየት ይኖርባቸዋል።

2 ስለ ሴቶችስ ምን ማለት ይቻላል? ራሳቸው ማን ነው? ጳውሎስ “የሴት ሁሉ ራስ . . . ወንድ” እንደሆነ ጽፏል። ሴቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈውን ይህን ሐሳብ እንዴት ሊመለከቱት ይገባል? አንዲት ሚስት ባሏ የማያምን ቢሆንም ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ሊሠራ ይችላል? ሚስቶች ለወንድ የራስነት ሥልጣን መገዛት አለባቸው ሲባል በትዳር ውስጥ በሚደረጉት ውሳኔዎች ረገድ ምንም ድርሻ አይኖራቸውም ማለት ነው? አንዲት ሴት ለራሷ ምስጋና ማትረፍ የምትችለው እንዴት ነው?

“ረዳት አበጅለታለሁ”

3, 4. የራስነት ሥርዓት በትዳር ውስጥ ጠቃሚ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

3 የራስነትን ሥርዓት ያዘጋጀው አምላክ ነው። ይሖዋ አምላክ፣ አዳም ከተፈጠረ በኋላ “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” ብሎ ነበር። ሔዋን በተፈጠረች ጊዜ አዳም ጓደኛና ረዳት በማግኘቱ እጅግ ስለተደሰተ “እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት” አለ። (ዘፍ. 2:18-24) አዳምና ሔዋን መላዋን ምድር ገነት በማድረግና ፍጹማን የሆኑ ልጆችን በመውለድ ለዘላለም ከልጆቻቸው ጋር በደስታ የመኖር ግሩም አጋጣሚ ነበራቸው።

4 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በኤደን ገነት በአምላክ ላይ ካመፁ ወዲህ የሰው ልጆች የራስነትን ሥርዓት ፍጹም በሆነ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም። (ሮም 5:12ን አንብብ።) ይሁንና በአምላክ ዘንድ አሁንም ቢሆን የሚስት ራስ ባል ነው። የራስነት ሥርዓት በተገቢው መንገድ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ በትዳር ውስጥ ብዙ ጥቅም እና ደስታ ያስገኛል። ባልና ሚስቱ ይህን ሥርዓት በአግባቡ መከተላቸው ኢየሱስ፣ ራሱ ለሆነው ለይሖዋ በመገዛቱ የተሰማው ዓይነት ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት “ሁልጊዜ [በይሖዋ ፊት] ሐሤት” ያደርግ ነበር። (ምሳሌ 8:30) ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸው ስለሆኑ ወንዶች የራስነት ሥልጣናቸውን ፍጹም በሆነ መንገድ ሊጠቀሙበት አይችሉም፤ ሴቶችም ቢሆኑ ፍጹም ታዛዥነት ማሳየት አይችሉም። ይሁን እንጂ ባሎችም ሆኑ ሚስቶች በዚህ ረገድ አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ ሁልጊዜ የሚጥሩ ከሆነ ይህ ዝግጅት በዛሬው ጊዜም ከትዳር ማግኘት የሚቻለውን የላቀ ደስታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።

5. የትዳር ጓደኛሞች በ⁠ሮም 12:10 ላይ የሚገኘውን ምክር በቁም ነገር ሊመለከቱት የሚገባው ለምንድን ነው?

5 የትዳር ጓደኛሞች ጋብቻቸው የተሳካ እንዲሆን ከፈለጉ ለሁሉም ክርስቲያኖች የተሰጠውን የሚከተለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በተግባር ማዋላቸው አስፈላጊ ነው፦ “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” (ሮም 12:10) በተጨማሪም ባልም ሆነ ሚስት ‘አንዳቸው ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የሚራሩ ለመሆን እንዲሁም እርስ በርሳቸው በነፃ ይቅር ለመባባል’ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።—ኤፌ. 4:32

የትዳር ጓደኛ የማያምን በሚሆንበት ጊዜ

6, 7. አንዲት ክርስቲያን ሚስት ለማያምን ባሏ መገዛቷ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

6 የትዳር ጓደኛችሁ የይሖዋ አገልጋይ ባይሆንስ? አብዛኛውን ጊዜ ከትዳር ጓደኛሞች መካከል አማኝ የማይሆነው ባል ነው። በዚህ ጊዜ ሚስት ለባሏ ምን አመለካከት ሊኖራት ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን መልስ ይሰጣል፦ “እናንተ ሚስቶች፣ ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለገዛ ባሎቻችሁ ተገዙ፤ ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት በዓይናቸው ሲመለከቱ ነው።”—1 ጴጥ. 3:1, 2

7 የአምላክ ቃል ሚስት ለማያምነው ባሏ እንድትገዛ ያዛል። ሚስት መልካም ምግባር ማሳየቷ ባሏ እንዲህ ዓይነት ጥሩ ጠባይ እንዲኖራት ያደረጋት ምን እንደሆነ ለማወቅ እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል። በዚህም ምክንያት ይህ ባል ክርስቲያን ሚስቱ የምትከተለውን እምነት ሊመረምርና ውሎ አድሮ እሱ ራሱ እውነትን ሊቀበል ይችላል።

8, 9. አንዲት ክርስቲያን ሚስት መልካም ምግባር ብታሳይም የማያምን ባሏ ለጥረቷ ጥሩ ምላሽ ባይሰጥ ምን ማድረግ ትችላለች?

8 ይሁንና አንድ የማያምን ባል ሚስቱ ለምታደርገው ጥረት ጥሩ ምላሽ ባይሰጥስ? አማኝ የሆነችው ሚስት ሁልጊዜ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማሳየት አስቸጋሪ ቢሆንባትም እንኳ ይህን ማድረጓን እንድትቀጥል ቅዱሳን መጻሕፍት ያበረታታሉ። ለምሳሌ ያህል 1 ቆሮንቶስ 13:4 “ፍቅር ታጋሽ” እንደሆነ ይናገራል። በመሆኑም ክርስቲያን የሆነችው ሚስት ሁኔታውን በፍቅር በመያዝ ‘ፍጹም ትሕትናና ገርነት እንዲሁም ትዕግሥት’ ለማሳየት ሁልጊዜ ጥረት ማድረጓ የተሻለ ነው። (ኤፌ. 4:2) አንዲት ሚስት አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥርም እንኳ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማንጸባረቅ ትችላለች።

9 ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵ. 4:13) የአምላክ መንፈስ ክርስቲያን የሆነችው የትዳር ጓደኛ፣ በራሷ ኃይል ቢሆን ኖሮ የማትችላቸውን በርካታ ነገሮች እንድታደርግ ያስችላታል። ለምሳሌ ያህል፣ የትዳር ጓደኛዋ መጥፎ ነገር ሲያደርግባት እሷም በዚያው መንገድ ምላሽ ለመስጠት ትፈተን ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ያሳስባል፦ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። . . . ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ይላል ይሖዋ’ ተብሎ [ተጽፏል]።” (ሮም 12:17-19) በተመሳሳይም በ⁠1 ተሰሎንቄ 5:15 ላይ እንዲህ የሚል ምክር እናገኛለን፦ “ማንም ሰው በማንም ላይ በክፉ ፋንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርሳችሁም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁሉ ምንጊዜም መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ተጣጣሩ።” የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ የሚያደርግልን ድጋፍ በራሳችን አቅም ፈጽሞ የማንችለውን ነገር ለማድረግ ያስችለናል። እንግዲያው የሚጎድለንን ነገር ለማሟላት እንዲረዳን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት መጸለያችን ምንኛ ተገቢ ነው!

10. ኢየሱስ ሰዎች መጥፎ ነገር ሲናገሩት ወይም ሲያደርጉበት ጉዳዩን የያዘው በምን መንገድ ነው?

10 ኢየሱስ ሰዎች መጥፎ ነገር ሲናገሩት ወይም ሲያደርጉበት ጉዳዩን የያዘበት መንገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። አንደኛ1 ጴጥሮስ 2:23 እንዲህ ይላል፦ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” እኛም የክርስቶስን ግሩም ምሳሌ እንድንከተል ምክር ተሰጥቶናል። ሌሎች መጥፎ ነገር ሲያደርጉብን አጸፋውን መመለስ አይኖርብንም። ሁሉም ክርስቲያኖች የሚከተለው ምክር ተሰጥቷቸዋል፦ “ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፣ ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ ይኑራችሁ፣ ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ።”—1 ጴጥ. 3:8, 9

ምንም ድርሻ አይኖራትም?

11. አንዳንድ ክርስቲያን ሴቶች የትኛውን ታላቅ መብት ያገኛሉ?

11 ሴቶች ለባላቸው የራስነት ሥልጣን ይገዛሉ ሲባል በትዳራቸው ውስጥ ምንም ድርሻ የላቸውም ማለት ነው? ከቤተሰብም ሆነ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሐሳብ መስጠት አይችሉም ማለት ነው? በፍጹም! ይሖዋ ለሴቶችም ሆነ ለወንዶች በርካታ መብቶችን ሰጥቷል። ክርስቶስ ምድርን በሚገዛበት ጊዜ በሰማይ ከእሱ ጋር ነገሥታትና ካህናት የሚሆኑት 144,000 ሰዎች የተሰጣቸውን ታላቅ መብት እንደ ምሳሌ እንመልከት። ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል ሴቶችም ይገኙበታል! (ገላ. 3:26-29) በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ በዝግጅቱ ውስጥ ለሴቶችም ድርሻ ሰጥቷቸዋል።

12, 13. ሴቶች ትንቢት እንደተናገሩ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

12 ለምሳሌ ያህል፣ በጥንት ዘመን ሴቶች ትንቢት ይናገሩ ነበር። ኢዩኤል 2:28, 29 እንዲህ ይላል፦ “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ . . . በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ እንኳ፣ መንፈሴን አፈሳለሁ።”

13 በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ በዓል ቀን ኢየሩሳሌም በሚገኝ ሰገነት ላይ ባለ አንድ ክፍል ውስጥ ከተሰበሰቡት 120 የሚያህሉ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል ሴቶችም ይገኙበት ነበር። የአምላክ መንፈስ የፈሰሰው በተሰበሰቡት ሁሉ ላይ ነበር። በመሆኑም ጴጥሮስ፣ ኢዩኤል የተናገረውን ትንቢት በመጥቀስ ትንቢቱ በወንዶችም በሴቶችም ላይ ፍጻሜውን እንዳገኘ መናገር ችሏል። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ይህ የሆነው ነቢዩ ኢዩኤል እንዲህ ሲል በተናገረው መሠረት ነው፦ አምላክ እንዲህ ይላል፦ ‘በመጨረሻው ቀን መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ . . . በዚያ ቀን በወንዶች ባሪያዎቼና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ሳይቀር መንፈሴን አፈሳለሁ፤ እነሱም ትንቢት ይናገራሉ።’”—ሥራ 2:16-18

14. በጥንት ጊዜ ክርስትናን በማስፋፋት ረገድ ሴቶች ምን ሚና ተጫውተዋል?

14 በአንደኛው መቶ ዘመን ሴቶች ክርስትናን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ስለ አምላክ መንግሥት ለሰዎች የሰበኩ ከመሆኑም ሌላ ከስብከቱ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አከናውነዋል። (ሉቃስ 8:1-3) ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ፌበን ‘በክንክራኦስ ጉባኤ እንደምታገለግል’ ተናግሯል። እንዲሁም ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ ሰላምታ በላከ ጊዜ በርካታ ታማኝ ሴቶችን የጠቀሰ ሲሆን ከእነሱ መካከል ‘በጌታ ሆነው በትጋት የሚሠሩት ጥራይፊና እና ጥራይፎሳ የተባሉት ሴቶች’ ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ “በጌታ ሥራ ብዙ የደከመችውን የምንወዳትን ጰርሲስን ሰላም በሉልኝ” ብሏል።—ሮም 16:1, 12

15. በዛሬው ጊዜ ክርስትናን በማስፋፋት ረገድ ሴቶች ምን ሚና ይጫወታሉ?

15 በዛሬው ጊዜ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ ከሚያውጁት ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አብዛኞቹ በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች ናቸው። (ማቴ. 24:14) ከእነዚህ ሴቶች መካከል ብዙዎቹ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች፣ ሚስዮናውያን እንዲሁም ቤቴላውያን ናቸው። መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጠ፤ ብዙ ሴቶችም ዜናውን አሰራጩ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 68:11 የ1980 ትርጉም) እነዚህ ቃላት በእርግጥም እውነት መሆናቸው ተረጋግጧል! ይሖዋ ምሥራቹን በመስበክና ዓላማውን ከግብ በማድረስ ረገድ ሴቶች የሚጫወቱትን ሚና ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ ክርስቲያን ሴቶች ለራስነት ሥልጣን እንዲገዙ መመሪያ ሰጥቷል ሲባል ምንም ድርሻ አይኖራቸውም ማለት አይደለም።

ዝም አላሉም

16, 17. ሴቶች በትዳር ውስጥ ሐሳባቸውን መግለጽ እንደሚችሉ የሣራ ምሳሌ የሚያሳየው እንዴት ነው?

16 ይሖዋ ለሴቶች ብዙ መብቶችን ሰጥቷቸዋል፤ ታዲያ ባሎች ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ከማድረጋቸው በፊት ሚስቶቻቸውን ማማከር አይኖርባቸውም? እንዲህ ማድረጋቸው ጥበብ ነው። ሚስቶች፣ ባሎቻቸው ባያማክሯቸውም እንኳ ሐሳባቸውን እንደገለጹ ወይም እርምጃ እንደወሰዱ የሚናገሩ የተለያዩ ዘገባዎችን በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እናገኛለን። እስቲ ከእነዚህ መካከል ሁለቱን እንመልከት።

17 የአብርሃም ሁለተኛ ሚስትና ልጇ አክብሮት የጎደለው ነገር በማድረጋቸው አብርሃም እንዲያባርራቸው ሣራ በተደጋጋሚ ትነግረው ነበር። “ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው።” ይሖዋ ግን የሣራን ሐሳብ ተቀብሎት ነበር። አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ አሳብ አይግባህ፤ . . . ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ።” (ዘፍ. 21:8-12) አብርሃም ይሖዋን በመታዘዝ የሣራን ሐሳብ የተቀበለ ሲሆን ያለችውንም አድርጓል።

18. አቢግያ በራሷ ተነሳስታ ምን እርምጃ ወስዳለች?

18 የናባል ሚስት የነበረችውን የአቢግያንም ሁኔታ እንመልከት። ዳዊት፣ ይቀናበት ከነበረው ከንጉሥ ሳኦል በሸሸ ጊዜ የሚኖረው የናባል መንጋ በሚሰማራበት አካባቢ ነበር። ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ይህ ሀብታም ሰው ካሉት በርካታ ንብረቶች መካከል አንዱንም አልወሰዱም፤ ከዚህ ይልቅ ንብረቱን ጠብቀውለታል። ናባል ግን “ባለጌና ምግባረ ብልሹ ሰው” ስለነበረ ዳዊት በላካቸው ሰዎች ላይ “የስድብ ናዳ አወረደባቸው።” ናባል ‘ጅልነት አብሮት የኖረ ባለጌ’ ሰው ነበር። ዳዊት የላካቸው ሰዎች ናባል ምግብ እንዲሰጣቸው በአክብሮት ሲጠይቁት ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም። አቢግያ የተፈጠረውን ነገር ስትሰማ ምን እርምጃ ወሰደች? ዘገባው እንደሚገልጸው “አቢግያም ጊዜ አላጠፋችም፤ ሁለት መቶ እንጀራ፣ ሁለት አቍማዳ የወይን ጠጅ፣ አምስት የተሰናዱ በጎች፣ አምስት መስፈሪያ የተጠበሰ እሸት፣ መቶ የወይን ዘለላና ዘቢብ፣ ሁለት መቶ ጥፍጥፍ የበለስ ፍሬ ወስዳ” ለዳዊትና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ሰጠቻቸው፤ ለባሏ ለናባል ግን ይህን አልነገረችውም። አቢግያ ያደረገችው ነገር ትክክል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፤ እርሱም ሞተ” ይላል። በኋላ ላይ ደግሞ ዳዊት አቢግያን አግብቷታል።—1 ሳሙ. 25:3, 14-19, 23-25, 38-42

‘የተመሰገነች ሴት’

19, 20. አንዲትን ሴት ምስጋና እንድታተርፍ የሚያስችላት ምንድን ነው?

19 ቅዱሳን መጻሕፍት ነገሮችን በይሖዋ መንገድ ስለሚያከናውኑ ሚስቶች በአድናቆት ይናገራሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ “ጠባየ መልካምን ሚስት” እንዲህ በማለት ያወድሳታል፦ “ከቀይ ዕንቍ እጅግ ትበልጣለች። ባሏ ሙሉ በሙሉ ይተማመንባታል፤ የሚጐድልበትም ነገር የለም። በሕይወት ዘመኗ ሁሉ፣ መልካም ታደርግለታለች እንጂ አትጐዳውም።” አክሎም እንዲህ ስላለችው ሚስት እንደሚከተለው ይላል፦ “በጥበብ ትናገራለች፤ በአንደበቷም ቀና ምክር አለ። የቤተ ሰዎቿን ጕዳይ በትጋት ትከታተላለች፤ የስንፍና እንጀራ አትበላም። ልጆቿ ተነሥተው፤ ቡርክት ይሏታል፤ ባሏም እንዲሁ።”—ምሳሌ 31:10-13, 26-29

20 አንዲትን ሴት ምስጋና እንድታተርፍ የሚያስችላት ምንድን ነው? ምሳሌ 31:30 “ቍንጅና አታላይ ነው፤ ውበትም ይረግፋል፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን የተመሰገነች ናት” ይላል። ይሖዋን መፍራት እሱ ላቋቋመው የራስነት ሥርዓት በፈቃደኝነት መገዛትንም ይጨምራል። “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ” እንዲሁም “የክርስቶስ ራስ . . . አምላክ እንደሆነ” ሁሉ “የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ” ነው።—1 ቆሮ. 11:3

ለአምላክ ስጦታ አመስጋኞች ሁኑ

21, 22. (ሀ) በትዳር የተጣመሩ ክርስቲያኖች ከአምላክ ላገኙት የጋብቻ ስጦታ አመስጋኝ እንዲሆኑ የሚያነሳሷቸው ምን ምክንያቶች አሉ? (ለ) ይሖዋ ከሥልጣንና ከራስነት ሥርዓት ጋር በተያያዘ ላደረጋቸው ዝግጅቶች አክብሮት ማሳየት የሚኖርብን ለምንድን ነው? (በገጽ 17 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

21 በትዳር የተጣመሩ ክርስቲያኖች አምላክን እንዲያመሰግኑ የሚያነሳሷቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ! በትዳራቸው ደስተኛ ሆነው መኖር ይችላሉ። በተለይ ከአምላክ ያገኙት የጋብቻ ስጦታ አንድ ሆነው ከይሖዋ ጋር እንዲሄዱ ስለሚያስችላቸው ለዚህ ስጦታ አመስጋኞች ሊሆኑ ይችላሉ። (ሩት 1:9፤ ሚክ. 6:8) በትዳር ውስጥ ደስተኛ ለመሆን ምን እንደሚያስፈልግ በትክክል የሚያውቀው የጋብቻ መሥራች የሆነው ይሖዋ ነው። ማንኛውንም ነገር ከእሱ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ አድርጉ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜም እንኳ “የእግዚአብሔር ደስታ ብርታታችሁ” ይሆናል።—ነህ. 8:10

22 ሚስቱን እንደራሱ የሚወድ ክርስቲያን ባል የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀምበት ፍቅርና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። ፈሪሃ አምላክ ያላት ሚስቱ ደግሞ እሱን ስለምትደግፈውና በጥልቅ ስለምታከብረው ተወዳጅ ትሆናለች። ከምንም በላይ ደግሞ በትዳራቸው ምሳሌ ስለሚሆኑ ውዳሴ ለሚገባው አምላካችን ለይሖዋ ክብር ያመጣሉ።

ታስታውሳለህ?

• ይሖዋ የራስነት ሥልጣንንና ለዚህ ሥልጣን መገዛትን በተመለከተ ያደረገው ዝግጅት ምንድን ነው?

• የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርስ መከባበር ያለባቸው ለምንድን ነው?

• አንዲት ክርስቲያን ሚስት የማያምን ባሏን እንዴት ልትይዘው ይገባል?

• ባሎች ከባድ ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት ሚስቶቻቸውን ማማከር ያለባቸው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ባላቸው ፍጥረታቱ መካከል የሥልጣን ተዋረድና የራስነት ሥርዓት እንዲኖር ዝግጅት አድርጓል። ይህን ዝግጅት ያደረገው ለመንፈሳዊም ሆነ ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ ጥቅም ሲል ነው። ይህ ዝግጅት፣ እነዚህ ፍጥረታት በነፃ ምርጫቸው ለመጠቀም እንዲሁም አንድነትና ስምምነት በሚንጸባረቅበት መንገድ አምላክን በማገልገል ለእሱ ክብር ለማምጣት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።—መዝ. 133:1

የተቀቡ ክርስቲያኖች ጉባኤ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥልጣንና ራስነት ይቀበላል። (ኤፌ. 1:22, 23) ከጊዜ በኋላ ደግሞ “ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር ላስገዛለት ራሱን ያስገዛል፤ ይህም አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር መሆን ይችል ዘንድ ነው።” በዚህ መንገድ ኢየሱስ የይሖዋን ሥልጣን እንደሚቀበል ያሳያል። (1 ቆሮ. 15:27, 28) እንግዲያው ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች በጉባኤና በቤተሰብ ውስጥ ካለው የራስነት ሥርዓት ጋር ተስማምተው መኖራቸው ምንኛ ተገቢ ነው! (1 ቆሮ. 11:3፤ ዕብ. 13:17) እንዲህ ካደረግን የይሖዋን ሞገስና በረከት እናገኛለን።—ኢሳ. 48:17

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጸሎት አንዲት ክርስቲያን ሚስት አምላካዊ ባሕርያትን እንድታንጸባርቅ ሊረዳት ይችላል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ይሖዋ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማከናወን ረገድ ሴቶች የሚጫወቱትን ሚና ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል