ካራን—ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ የነበራት ጥንታዊት ከተማ
ካራን—ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ የነበራት ጥንታዊት ከተማ
ቅዱሳን መጻሕፍትን የሚያነቡ ሰዎች ካራን የሚለውን ቃል ሲሰሙ ወዲያው የሚመጣላቸው ታማኙ አብርሃም ነው። አብርሃም ከዑር ተነስቶ ወደ ከነዓን ሲጓዝ እሱና ሚስቱ ሣራ እንዲሁም አባቱ ታራ እና የወንድሙ ልጅ ሎጥ በካራን አርፈው ነበር። በዚያም አብርሃም ብዙ ንብረት አፍርቶ ነበር። አብርሃም አባቱ ከሞተ በኋላ እውነተኛው አምላክ ሊሰጠው ቃል ወደገባለት ምድር ጉዞውን ቀጠለ። (ዘፍ. 11:31, 32፤ 12:4, 5፤ ሥራ 7:2-4) ከጊዜ በኋላ አብርሃም ከካራን ወይም በአቅራቢያው ከሚገኝ ቦታ ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት እንዲያመጣለት በዕድሜ አንጋፋ የሆነውን አገልጋዩን ልኮት ነበር። የአብርሃም የልጅ ልጅ የሆነው ያዕቆብም በዚህች ከተማ ለበርካታ ዓመታት ኖሯል።—ዘፍ. 24:1-4, 10፤ 27:42-45፤ 28:1, 2, 10
የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም፣ የይሁዳ ንጉሥ የሆነውን ሕዝቅያስን ሲያስፈራራ የአሦር ነገሥታት ድል እንዳደረጓቸው ከጠቀሳቸው “ሕዝቦች” መካከል የካራን ሰዎች ይገኙበታል። እዚህ ላይ “ካራን” ሲባል ከተማዋን ብቻ ሳይሆን በዙሪያዋ ያሉትን አካባቢዎችም ያመለክታል። (2 ነገ. 19:11, 12) በሕዝቅኤል ትንቢት ላይ ካራን ከጢሮስ ዋነኛ የንግድ ሸሪኮች መካከል መጠቀሷ ይህች ከተማ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣት የንግድ መናኸሪያ እንደነበረች ይጠቁማል።—ሕዝ. 27:1, 2, 23
ካራን በአሁኑ ጊዜ በምሥራቃዊ ቱርክ በሻንሊዩርፋ አቅራቢያ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ናት። ይሁንና ጥንታዊቷ የካራን ከተማ በአንድ ወቅት ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ ይካሄድባት ነበር። አሁንም ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው ስማቸው ከሚጠሩ በጣት የሚቆጠሩ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ ካራን ናት። በአሦር ቋንቋ ካራኑ የሚባለው የዚህች ከተማ ስም “ጎዳና” ወይም “የቅፍለት ጎዳና” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ይህም ካራን በትልልቅ ከተሞች መካከል ባሉ ዋነኛ የንግድ መሥመሮች ላይ የምትገኝ ከተማ እንደነበረች ይጠቁማል። በካራን የተገኙ ጽሑፎች እንደሚጠቁሙት የባቢሎን ንጉሥ የሆነው የናቦኒደስ እናት፣ ሲን በተባለው የካራን የጨረቃ አምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ ዋና ሊቀ ካህን ነበረች። አንዳንዶች ይህንን ቤተ መቅደስ ያደሰው ናቦኒደስ እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚያ በኋላ ካራን በርካታ መንግሥታት ሲነሱና ሲወድቁ ተመልክታለች።
በዛሬው ጊዜ ካራን ያላት ገጽታ በጥንት ጊዜ ከነበራት በእጅጉ የተለየ ነው። የጥንቷ ካራን በተለይ በአንዳንድ ወቅቶች በሥልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰችና ወሳኝ ሚና የምትጫወት ከተማ ነበረች። የዛሬዋ ካራን ግን ሞላላ ቅርጽ ያለው ጣሪያ ያላቸው ቤቶች በብዛት የሚገኙባት አነስተኛ ከተማ ናት። በከተማዋ ዙሪያ የጥንቱን ሥልጣኔ የሚያንጸባርቁ ፍርስራሾች ይታያሉ። አምላክ በሚያዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ አብርሃምን፣ ሣራንና ሎጥን ጨምሮ በአንድ ወቅት በካራን የኖሩ በርካታ ሰዎች ትንሣኤ ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ከተማ ስለነበረችው ስለ ካራን ብዙ የሚነግሩን ነገር እንደሚኖር ምንም ጥርጥር የለውም።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የካራን ፍርስራሽ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሞላላ ቅርጽ ያለው ጣሪያ ያላቸው ቤቶች
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ካራን ከሩቅ ስትታይ