በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንድሞች፣ ለመንፈስ ብላችሁ በመዝራት ለኃላፊነት ለመብቃት ተጣጣሩ!

ወንድሞች፣ ለመንፈስ ብላችሁ በመዝራት ለኃላፊነት ለመብቃት ተጣጣሩ!

ወንድሞች፣ ለመንፈስ ብላችሁ በመዝራት ለኃላፊነት ለመብቃት ተጣጣሩ!

“ለመንፈስ ብሎ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለም ሕይወት ያጭዳል።”—ገላ. 6:8

1, 2. ማቴዎስ 9:37, 38 ፍጻሜውን በማግኘት ላይ ያለው እንዴት ነው? ይህስ በጉባኤዎች ውስጥ ምን እንዲያስፈልግ አድርጓል?

ታሪካዊ የሆነ ነገር ሲከናወን እየተመለከታችሁ ነው! ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ የተናገረለት ሥራ በአሁኑ ወቅት በስፋትና አስገራሚ በሆነ ፍጥነት እየተከናወነ ነው። ኢየሱስ “አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ጌታ ወደ መከር ሥራው ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” ብሎ ነበር። (ማቴ. 9:37, 38) ይሖዋ አምላክ እንደነዚህ ላሉት ጸሎቶች አስደናቂ በሆነ መንገድ ምላሽ እየሰጠ ነው። በ2009 የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ቁጥር በ2,031 የጨመረ ሲሆን ይህም ጠቅላላውን የጉባኤዎች ቁጥር 105,298 አድርሶታል። በየቀኑ በአማካይ 757 ሰዎች ተጠምቀዋል!

2 እንዲህ ያለ ጭማሪ እየተገኘ በመሆኑ በጉባኤዎች ውስጥ በማስተማሩና በእረኝነቱ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ ብቃት ያላቸው ወንድሞች ያስፈልጋሉ። (ኤፌ. 4:11) ባለፉት አሥርተ ዓመታት ይሖዋ በጎቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ሲል ብቃት ያላቸው ወንዶች አስነስቷል፤ ዛሬም ይህን ማድረጉን እንደሚቀጥል እንተማመናለን። በሚክያስ 5:5 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢት በመጨረሻው ዘመን የይሖዋ ሕዝቦች “ሰባት እረኞች” እንዲሁም “ስምንት አለቆች” እንደሚኖሯቸው ይናገራል፤ ይህም በመካከላቸው ግንባር ቀደም ሆነው አመራር የሚሰጡ በርካታ ወንዶች እንደሚኖሩ ማረጋገጫ ይሰጠናል።

3. ‘ለመንፈስ ብሎ መዝራት’ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ አብራራ።

3 የተጠመቅህ የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ በጉባኤ ውስጥ መብቶችን ለማግኘት የመጣጣር ፍላጎት እንዲያድርብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ቁልፉ ‘ለመንፈስ ብለህ መዝራት’ ነው። (ገላ. 6:8) ‘ለመንፈስ ብሎ መዝራት’ መንፈስ ቅዱስ በነፃነት በውስጥህ እንዲሠራ በሚያደርግ መንገድ መኖርን ይጨምራል። ‘ለሥጋ ብለህ ላለመዝራት’ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብሃል። የተደላደለ ሕይወት የመምራት ምኞት፣ መዝናኛና የመሳሰሉት ነገሮች በአምላክ አገልግሎት ራስህን የማቅረብ ፍላጎትህን እንዲያቀዘቅዙብህ አትፍቀድ። ሁሉም ክርስቲያኖች ‘ለመንፈስ ብለው መዝራት’ ይኖርባቸዋል፤ እንዲህ የሚያደርጉ ወንዶች ውሎ አድሮ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለማግኘት የሚያስችላቸውን ብቃት ሊያሟሉ ይችላሉ። በዛሬው ጊዜ የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች በጣም ስለሚያስፈልጉ ይህ ርዕስ በዋነኝነት የተዘጋጀው ለክርስቲያን ወንዶች ነው። በመሆኑም ወንድሞች፣ ይህንን የጥናት ርዕስ በጸሎት እንድታስቡበት አደራ እንላችኋለን።

ለመልካም ሥራ ብቁ ለመሆን ተጣጣሩ

4, 5. (ሀ) የተጠመቁ ወንዶች በጉባኤ ውስጥ የትኞቹን መብቶች ለማግኘት እንዲጣጣሩ ተበረታትተዋል? (ለ) አንድ ወንድም ለመልካም ሥራ ብቁ ለመሆን ጥረት ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?

4 አንድ ወንድም ምንም ጥረት ሳያደርግ የበላይ ተመልካች ሆኖ ሊሾም አይችልም። ለዚህ “መልካም ሥራ” ብቁ ለመሆን መጣጣር አለበት። (1 ጢሞ. 3:1) ይህም የእምነት ባልንጀሮቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ከልብ ጥረት በማድረግ እነሱን ማገልገልን ይጨምራል። (ኢሳይያስ 32:1, 2ን አንብብ።) አንድ ወንድም ለመልካም ሥራ ብቁ ለመሆን የሚጣጣረው በትክክለኛ ዝንባሌ ተነሳስቶ እስከሆነ ድረስ ለራሱ ክብር እንደሚፈልግ ተደርጎ አይታይም። ከዚህ ይልቅ ይህን ማድረጉ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ሌሎችን የሚጠቅም ነገር ለማከናወን እንደሚፈልግ የሚጠቁም ነው።

5 አንድ ወንድም፣ የጉባኤ አገልጋይ እንዲሁም የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣረው በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተዘረዘሩትን ብቃቶች ለማሟላት ተግቶ በመሥራት ነው። (1 ጢሞ. 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9) የተጠመቅህ ወንድ ከሆንክ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በስብከቱ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ አደርጋለሁ? ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ እረዳቸዋለሁ? ስለ እምነት ባልንጀሮቼ ደኅንነት ከልብ በማሰብ አበረታታቸዋለሁ? የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናት ረገድ ጥሩ ስም አትርፌያለሁ? በስብሰባዎች ላይ የምሰጠውን ሐሳብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻልኩ ነው? ሽማግሌዎች የሚሰጡኝን ኃላፊነቶች በትጋት እየተወጣሁ ነው?’ (2 ጢሞ. 4:5) ወንድሞች እንደነዚህ ያሉትን ጥያቄዎች በቁም ነገር ሊያስቡባቸው ይገባል።

6. በጉባኤ ውስጥ ላሉት ኃላፊነቶች ብቁ ለመሆን የሚያስፈልገው አንዱ ቁልፍ ምንድን ነው?

6 ወንድሞች፣ በጉባኤ ውስጥ ላሉ ኃላፊነቶች ብቁ ለመሆን የሚረዳችሁ ሌላው ነገር ደግሞ ‘ውስጣዊ ሰውነታችሁን የሚያጠነክረውን የአምላክ መንፈስ’ ማግኘት ነው። (ኤፌ. 3:16) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ መሆን በድምፅ ምርጫ የሚገኝ ሥልጣን አይደለም። ይህን መብት ማግኘት የሚቻለው በመንፈሳዊ እድገት በማድረግ ብቻ ነው። በመንፈሳዊ ማደግ የሚቻለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ‘በመንፈስ መመላለሳችሁን መቀጠል’ እንዲሁም የዚህን መንፈስ ፍሬ ማፍራት ነው። (ገላ. 5:16, 22, 23) በጉባኤ ውስጥ ለሚሰጡት ተጨማሪ ኃላፊነቶች የሚያስፈልጉትን መንፈሳዊ ባሕርያት ስታሟሉና ማሻሻያ እንድታደርጉ የሚሰጧችሁን ምክሮች ተግባራዊ ስታደርጉ ‘እድገታችሁ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ ይታያል።’—1 ጢሞ. 4:15

የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ያስፈልጋል

7. ሌሎችን ማገልገል ምን ይጠይቃል?

7 ሌሎችን ማገልገል ብዙ ሥራ ስለሚያስከትል የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማዳበር ያስፈልጋል። ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች መንፈሳዊ እረኞች በመሆናቸው መንጋው የሚያጋጥሙት ችግሮች በጥልቅ ያሳስቧቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከእረኝነቱ ሥራ ጋር የተያያዙ ኃላፊነቶችን መወጣት ምን እንደጠየቀበት እንመልከት። በቆሮንቶስ ለነበሩት የእምነት ባልንጀሮቹ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በብዙ መከራና በልብ ጭንቀት እንዲሁም በብዙ እንባ የጻፍኩላችሁ እንድታዝኑ ሳይሆን ለእናንተ ያለኝን የላቀ ፍቅር እንድታውቁ ነው።” (2 ቆሮ. 2:4) ጳውሎስ ሥራውን የሚያከናውነው በሙሉ ልቡ እንደነበር በግልጽ መመልከት ይቻላል።

8, 9. አንዳንድ ወንዶች ሌሎችን እንዴት እንደተንከባከቡ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ጥቀስ።

8 የይሖዋ አገልጋዮችን ለመርዳት የሚደክሙ ወንዶች ምንጊዜም የሚታወቁት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በማሳየት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኖኅ የቤተሰቡን አባላት ‘መርከቡን ሠርታችሁ ስትጨርሱ ንገሩኝና አብሬያችሁ እገባለሁ’ ብሏቸዋል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው። ሙሴ በግብፅ ለነበሩት እስራኤላውያን ‘ቀይ ባሕር ላይ እንገናኝ። እዚያ ለመድረስ የተሻለ ያላችሁትን መንገድ መከተል ትችላላችሁ’ አላላቸውም። ኢያሱ ‘የኢያሪኮ ግንብ ሲፈርስ ንገሩኝ’ አላለም። ኢሳይያስም ቢሆን ‘ያውልህ፣ እሱን ላከው’ በማለት ወደ ሌላ ሰው አልጠቆመም።—ኢሳ. 6:8

9 የአምላክ መንፈስ እንዲመራው በመፍቀድ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የሚሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለሰው ልጆች ቤዛ እንዲሆን የተሰጠውን ተልእኮ በፈቃደኝነት ተቀብሏል። (ዮሐ. 3:16) ኢየሱስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ያሳየው ፍቅር እኛም በተመሳሳይ ይህን ባሕርይ እንድናንጸባርቅ ሊያነሳሳን አይገባም? ለረጅም ዓመታት የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለ አንድ ወንድም ለመንጋው ያለውን ስሜት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ኢየሱስ ‘ግልገሎቼን ጠብቅ’ በማለት ለጴጥሮስ የተናገረው ሐሳብ በጥልቅ ይነካኛል። ፍቅር የሚንጸባረቅባቸው ጥቂት ቃላት መናገር ወይም በደግነት ተነሳስቶ ትንሽ ነገር ማድረግ የሌላውን ሰው መንፈስ ምን ያህል ሊያድስ እንደሚችል ባለፉት ዓመታት ተመልክቻለሁ። እረኝነት በጣም የምወደው ሥራ ነው።”—ዮሐ. 21:16

10. ክርስቲያን ወንዶች ሌሎችን በማገልገል ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉ ምን ሊያነሳሳቸው ይችላል?

10 የአምላክን መንጋ በመንከባከብ ረገድ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ራሳቸውን የወሰኑ ወንዶች “እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ” በማለት የተናገረውን የኢየሱስን ዓይነት አመለካከት ለማንጸባረቅ እንደሚፈልጉ የተረጋገጠ ነው። (ማቴ. 11:28) ክርስቲያን ወንዶች በአምላክ ላይ ያላቸው እምነትና ለጉባኤው ያላቸው ፍቅር እንደዚህ ያለው መልካም ሥራ ላይ ለመድረስ እንዲጣጣሩ ያነሳሳቸዋል፤ ይህ ሥራ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ወይም ብዙ ልፋት እንደሚጠይቅ በማሰብ ራሳቸውን ከማቅረብ ወደኋላ አይሉም። ይሁን እንጂ አንድ ወንድም ለዚህ ሥራ ብቁ ለመሆን የመጣጣር ፍላጎት ባይኖረውስ? ጉባኤውን የማገልገል ፍላጎት ለማዳበር ምን ማድረግ ይችላል?

ሌሎችን የማገልገል ፍላጎት አዳብሩ

11. አንድ ወንድም ሌሎችን የማገልገል ፍላጎት ለማዳበር ምን ማድረግ ይችላል?

11 ወንድሞች፣ ብቃት የለኝም የሚለው ስሜት ኃላፊነት ለመቀበል እንዳትጣጣሩ እንቅፋት ከሆነባችሁ አምላክ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጣችሁ መጸለያችሁ ተገቢ ነው። (ሉቃስ 11:13) የይሖዋ መንፈስ በዚህ ረገድ ያለባችሁን ማንኛውንም ጭንቀት ማሸነፍ እንድትችሉ ይረዳችኋል። አንድ ወንድም ለኃላፊነት ለመብቃት እንዲጣጣር የሚገፋፋውና ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችለውን ኃይል የሚሰጠው የይሖዋ መንፈስ ስለሆነ ሌሎችን የማገልገል ፍላጎት በውስጣችን እንዲያድር የሚያደርገው አምላክ ነው። (ፊልጵ. 2:13፤ 4:13) እንግዲያው የአገልግሎት መብቶችን የመቀበል ፍላጎት ያድርባችሁ ዘንድ ይሖዋ እንዲረዳችሁ መጸለያችሁ ተገቢ ነው።—መዝሙር 25:4, 5ን አንብብ።

12. አንድ ወንድም የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችለውን ጥበብ እንዴት ማግኘት ይችላል?

12 አንድ ክርስቲያን፣ መንጋው የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት ልፋትና ብዙ ውጣ ውረድ እንደሚጠይቅ የሚያስብ ከሆነ እዚህ መብት ላይ ለመድረስ ጥረት ከማድረግ ወደኋላ ሊል ይችላል። ወይም ደግሞ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ እንደሚጎድለው ይሰማው ይሆናል። ከሆነ የአምላክን ቃልና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በትጋት በማጥናት ጥበብ ማግኘት ይችላል። ‘የአምላክን ቃል ለማጥናት ጊዜ እመድባለሁ? ጥበብ ለማግኘትስ እጸልያለሁ?’ በማለት ራሱን መጠየቁ ጥሩ ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ ምክንያቱም አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣል፤ ለእሱም ይሰጠዋል።” (ያዕ. 1:5) በመንፈስ መሪነት በተጻፈው በዚህ ሐሳብ ላይ እምነት አላችሁ? አምላክ ለሰለሞን “ጥበብና አስተዋይ ልቡና” በመስጠት ጸሎቱን መልሶለታል፤ ይህም ሰለሞን ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ መልካምና ክፉን ለመለየት አስችሎታል። (1 ነገ. 3:7-14) እውነት ነው፣ ሰለሞን የነበረበት ሁኔታ ለየት ያለ ነበር። ያም ቢሆን አምላክ የጉባኤ ኃላፊነቶች የተሰጧቸው ወንዶች የእሱን በጎች በአግባቡ መንከባከብ እንዲችሉ ጥበብ እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ምሳሌ 2:6

13, 14. (ሀ) “ክርስቶስ ያለው ፍቅር” በጳውሎስ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት እንደሆነ አብራራ። (ለ) “ክርስቶስ ያለው ፍቅር” ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

13 ሌሎችን የማገልገል ፍላጎት ለማዳበር የሚረዳን ሌላው ነገር ይሖዋና ልጁ ባደረጉልን በርካታ ነገሮች ላይ በጥልቅ ማሰላሰል ነው። ሁለተኛ2 ቆሮንቶስ 5:14, 15⁠ን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። (ጥቅሱን አንብብ።) “ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ” የሚለን እንዴት ነው? ክርስቶስ ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለእኛ ሲል ሕይወቱን መሥዋዕት በማድረግ ያሳየው ፍቅር እጅግ ታላቅ በመሆኑ ለዚህ ዝግጅት ያለን አድናቆት እየጨመረ ሲሄድ ልባችንም በጥልቅ ይነካል። የክርስቶስ ፍቅር በጳውሎስ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር። የራሱን ፍላጎት ከማሳደድ እንዲቆጠብ ያደረገው ከመሆኑም ሌላ አምላክንና በጉባኤም ሆነ ከዚያ ውጪ ያሉ ሰዎችን ማገልገልን ዋነኛ ዓላማው እንዲያደርግ ረድቶታል።

14 ክርስቶስ ለሰው ልጆች ባለው ፍቅር ላይ ማሰላሰላችን አመስጋኞች እንድንሆን ያነሳሳናል። ይህ ደግሞ ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸውን ግቦች በማሳደድ እንዲሁም የራሳችንን ፍላጎት በማርካት ላይ ያተኮረ ሕይወት በመምራት ‘ለሥጋችን ብለን መዝራት’ ፈጽሞ ተገቢ አለመሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንድናከናውን ለሰጠን ሥራ ቅድሚያ ለመስጠት በሕይወታችን ላይ ማስተካከያ እናደርጋለን። በተጨማሪም ወንድሞቻችንን በፍቅር ‘ለማገልገል’ እንነሳሳለን። (ገላትያ 5:13ን አንብብ።) የይሖዋን ሕዝቦች በትሕትና የምናገለግል ባሪያዎች እንደሆንን አድርገን ራሳችንን የምንመለከት ከሆነ ወንድሞቻችንን በአክብሮት እንይዛቸዋለን። እንደ ሰይጣን የወንድሞቻችንን ድክመት የምንለቃቅምና በሌሎች ላይ የምንፈርድ መሆን እንደማንፈልግ ጥርጥር የለውም።—ራእይ 12:10

በቤተሰብ ደረጃ ጥረት አድርጉ

15, 16. አንድ ወንድም የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆኖ ለመሾም ብቁ እንዲሆን የቤተሰቡ አባላት ምን ሚና ይጫወታሉ?

15 አንድ ወንድም ትዳር የመሠረተና ልጆች ያሉት ከሆነ የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ለመሆን ብቃቱን ያሟላ እንደሆነ በሚገመገምበት ጊዜ በቤተሰቡ ውስጥ ያለው ሁኔታ ግምት ውስጥ ይገባል። የቤተሰቡ አባላት ያላቸው መንፈሳዊነትና ያተረፉት ስም ወንድም በኃላፊነት በመሾሙ ላይ የሚያሳድረው ቀጥተኛ ተጽዕኖ ይኖራል። ይህም አንድ የቤተሰብ ራስ የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ በመሆን ጉባኤውን ለማገልገል በሚያደርገው ጥረት ሚስቱና ልጆቹ ድጋፍ ማድረጋቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያጎላል።—1 ጢሞቴዎስ 3:4, 5, 12ን አንብብ።

16 የአንድ ክርስቲያን ቤተሰብ አባላት እርስ በርስ ለመደጋገፍ የሚያደርጉት ጥረት ይሖዋን ያስደስተዋል። (ኤፌ. 3:14, 15) አንድ የቤተሰብ ራስ የጉባኤ ኃላፊነቶቹን ለመወጣትና ቤተሰቡን “በተገቢው ሁኔታ” ለማስተዳደር ሚዛናዊ መሆን ይጠበቅበታል። በመሆኑም አንድ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ አስፈላጊ ነው፤ ይህም ሁሉም በየሳምንቱ ከሚደረገው ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። የቤተሰቡ ራስ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር አዘውትሮ በመስክ አገልግሎት መካፈል ይኖርበታል። በሌላ በኩል ደግሞ ሚስትና ልጆችም የቤተሰቡ ራስ የሚያደርገውን ጥረት መደገፋቸው አስፈላጊ ነው።

ያጣኸውን መብት መልሰህ ማግኘት ትችላለህ?

17, 18. (ሀ) አንድ ወንድም በኃላፊነት ቦታ ላይ የማገልገል መብቱን ቢያጣ ምን ማድረግ ያስፈልገዋል? (ለ) ቀደም ሲል ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ የነበረ አንድ ወንድም ምን ዓይነት አመለካከት ማዳበሩ ጠቃሚ ይሆናል?

17 በአንድ ወቅት ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ የነበርክ ቢሆንም አሁን ይህን መብት አጥተህ ይሆናል። ይሖዋን እንደምትወደው ምንም ጥርጥር የለውም፤ እሱም አሁንም እንደሚያስብልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (1 ጴጥ. 5:6, 7) አንዳንድ ማስተካከያዎችን እንድታደርግ ተነግሮህ ነበር? ስህተትህን አምነህ ለመቀበል ፈቃደኛ ሁን፤ እንዲሁም በአምላክ እርዳታ ማሻሻያ ለማድረግ ጥረት አድርግ። በሁኔታው ቅር ተሰኝተህ ከነበረ ይህ ስሜት እንዲቆጣጠርህ አትፍቀድ። ጠቢብ በመሆን አዎንታዊ አመለካከት አዳብር። ለበርካታ ዓመታት በሽምግልና ያገለገለና በአንድ ወቅት መብቱን አጥቶ የነበረ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በስብሰባ ላይ በመገኘት፣ በመስክ አገልግሎት በመካፈል እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ረገድ ሽማግሌ በነበርኩበት ወቅት የነበረኝን ልማድ ጠብቄ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ያደረግሁ ሲሆን ይህን ግቤንም ማሳካት ችዬ ነበር። ያጣሁትን መብት በአንድ ወይም በሁለት ዓመት ውስጥ መልሼ እንደማገኝ አስቤ የነበረ ቢሆንም እንደገና ሽማግሌ የሆንኩት ከሰባት ዓመታት በኋላ ነበር፤ ይህም ትዕግሥትን አስተምሮኛል። በዚያ ወቅት ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረጌን እንድቀጥል የተሰጠኝ ማበረታቻ በጣም ጠቅሞኛል።”

18 ከላይ የተገለጸው ዓይነት ሁኔታ ያጋጠመህ ወንድም ከሆንክ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋ፣ አገልግሎትህንና ቤተሰብህን ምን ያህል እየባረከው እንዳለ አስብ። ቤተሰብህን በመንፈሳዊ ለመገንባት ጥረት አድርግ፤ የታመሙትን ጠይቅ እንዲሁም የደከሙትን አጽናና። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ሆነህ አምላክን የማወደስና የመንግሥቱን ምሥራች የማወጅ መብትህን ከፍ አድርገህ ተመልከተው። *መዝ. 145:1, 2፤ ኢሳ. 43:10-12

ጉዳዩን በድጋሚ አስቡበት

19, 20. (ሀ) የተጠመቁ ወንዶች በሙሉ ምን እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኛውን ነጥብ እንመለከታለን?

19 ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች በጣም ያስፈልጋሉ። በመሆኑም የተጠመቃችሁ ወንዶች ሁሉ ሁኔታችሁን እንደገና እንድታስቡበት አጥብቀን እናሳስባችኋለን፤ እንዲሁም ‘የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ካልሆንኩ እዚህ መብት ላይ ያልደረስኩት ለምን እንደሆነ ቆም ብዬ መመርመር ይኖርብኝ ይሆን?’ በማለት ራሳችሁን እንድትጠይቁ እንመክራችኋለን። ትልቅ ቦታ ለሚሰጠው ለዚህ ጉዳይ ተገቢውን አመለካከት እንድታዳብሩ የአምላክ መንፈስ እንዲረዳችሁ ምኞታችን ነው።

20 የእምነት አጋሮቻችን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ለማንጸባረቅ ጥረት ማድረጋቸው ሁሉንም የጉባኤ አባላት ይጠቅማል። ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ድርጊቶች ስንፈጽም ሌሎችን ማገልገልና ለመንፈስ ብሎ መዝራት የሚያስገኘውን ደስታ እናጭዳለን። በሌላ በኩል ደግሞ የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ላለማሳዘን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

[ግርጌ ማስታወሻ]

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

በሚክያስ 5:5 ላይ የሚገኘው ትንቢት ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

• የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ምን ነገሮችን እንደሚጨምር አብራራ።

• አንድ ወንድም ሌሎችን የማገልገል ፍላጎት ለማዳበር ምን ማድረግ ይችላል?

• አንድ ወንድም የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ብቁ እንዲሆን ቤተሰቡ የሚያደርጉለት ድጋፍ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለኃላፊነት ለመጣጣር ምን ማድረግ ትችላለህ?