በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማስተዋል ችሎታችሁን ማሠልጠናችሁን ቀጥሉ

የማስተዋል ችሎታችሁን ማሠልጠናችሁን ቀጥሉ

የማስተዋል ችሎታችሁን ማሠልጠናችሁን ቀጥሉ

በጂምናስቲክ የተካነ አንድ ስፖርተኛ ቅልጥፍና በተሞላበት ሁኔታ አስገራሚ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መመልከት እንዴት ደስ ይላል! አንድ የጂምናስቲክ ስፖርተኛ ልምምድ እንደሚያደርግ ሁሉ ክርስቲያኖችም የማመዛዘን ችሎታቸውን እንዲያሠለጥኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያበረታታቸዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ጠንካራ ምግብ ግን ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን [ቃል በቃል ሲተረጎም “የስሜት ሕዋሶቻቸውን”] በማሠራት [ልክ እንደ አንድ የጂምናስቲክ ስፖርተኛ] ላሠለጠኑ ጎልማሳ ሰዎች ነው” ብሏል። (ዕብ. 5:14) ጳውሎስ የዕብራውያን ክርስቲያኖች በጂምናስቲክ ስፖርት ልምድ ያለው አንድ ሰው ጡንቻዎቹን ከሚያሠራበት መንገድ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የማመዛዘን ችሎታቸውን እንዲያሠለጥኑ በጥብቅ ያሳሰባቸው ለምን ነበር? እኛስ የማስተዋል ችሎታችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው?

“አስተማሪዎች ልትሆኑ ይገባችሁ” ነበር

ጳውሎስ፣ ኢየሱስ “በመልከጼዴቅ ሥርዓት መሠረት . . . ሊቀ ካህናት” በመሆን የሚጫወተውን ሚና ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “[ኢየሱስን] በተመለከተ ብዙ የምንናገረው ነገር አለን፤ ይሁንና ጆሯችሁ ስለደነዘዘ ለማስረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ከጊዜው አንጻር አስተማሪዎች ልትሆኑ ይገባችሁ የነበረ ቢሆንም የአምላክን ቅዱስ መልእክት መሠረታዊ ነገሮች እንደገና ከመጀመሪያ ጀምሮ የሚያስተምራችሁ ሰው ትፈልጋላችሁ፤ ደግሞም ጠንካራ ምግብ ሳይሆን ወተት እንደሚፈልግ ሰው ሆናችኋል።”—ዕብ. 5:10-12

በግልጽ ማየት እንደምንችለው በአንደኛው መቶ ዘመን ከኖሩት አይሁድ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ የማገናዘብ ችሎታቸው እየጨመረ እንዲመጣ ስላላደረጉ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የሙሴን ሕግና ግዝረትን በተመለከተ የተገኘውን አዲስ የእውቀት ብርሃን መቀበል ከብዷቸው ነበር። (ሥራ 15:1, 2, 27-29፤ ገላ. 2:11-14፤ 6:12, 13) አንዳንዶቹ በየሳምንቱ ከሚከበረው ሰንበትና ከዓመታዊው የሥርየት ቀን ጋር የተያያዙ ልማዶችን መተው ከባድ ሆኖባቸው ነበር። (ቆላ. 2:16, 17፤ ዕብ. 9:1-14) ስለዚህ ጳውሎስ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት የሚረዳቸውን የማስተዋል ችሎታቸውን እንዲያሠለጥኑ ያበረታታቸው ከመሆኑም ሌላ ‘ወደ ጉልምስና እንዲገፉ’ ነግሯቸው ነበር። (ዕብ. 6:1, 2) ጳውሎስ የሰጣቸው ምክር የማመዛዘን ችሎታቸውን እንዴት እየተጠቀሙበት እንዳሉ መለስ ብለው እንዲያስቡ አንዳንዶቹን አነሳስቷቸው መሆን አለበት፤ ይህም መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ሳይረዳቸው አልቀረም። እኛስ እንዴት ነን?

የማስተዋል ችሎታችሁን አሠልጥኑ

በመንፈሳዊ ጎልማሶች መሆን እንድንችል የማመዛዘን ችሎታችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችለው “በማሠራት” እንደሆነ ጳውሎስ ተናግሯል። የጂምናስቲክ ስፖርተኞች ለዓይን የሚማርኩና አስገራሚ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ለማሳየት ሲሉ ጡንቻዎቻቸውንና ሰውነታቸውን በልምምድ እንደሚያሠለጥኑ ሁሉ እኛም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት የማመዛዘን ችሎታችንን ማሠልጠን ይኖርብናል።

በሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት የሥነ ልቦና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ሬቲ “ለአንጎላችሁ ልታደርጉለት የምትችሉት ብቸኛውና ከሁሉ የተሻለው ነገር ማሠራት ነው” ብለዋል። በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ስለ እርጅና፣ ስለ ጤናና ስለ ሰው ልጆች ሕይወት የሚያጠና ማዕከል ውስጥ ዳይሬክተር ሆነው የሚሠሩት ጂን ኮኸን እንደተናገሩት ከሆነ “አእምሯችንን የሚያታግል ተግባር ስናከናውን የአንጎላችን ሴሎች አዳዲስ ቅርንጫፎችን ማውጣት ይጀምራሉ፤ ይህ ደግሞ የነርቭ ሴሎችን ጫፍ በማገናኘት መልእክት የሚያስተላልፉት ሲናፕሶች ቁጥር እንዲበዛ ያደርጋል።”

እንግዲያው የማስተዋል ችሎታችንን ማሠልጠናችንና ስለ አምላክ ቃል ያለንን እውቀት መጨመራችን ብልኅነት ነው። እንዲህ ካደረግን “ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ” ለመፈጸም በተሻለ ሁኔታ የታጠቅን እንሆናለን።—ሮም 12:1, 2

“ጠንካራ ምግብ” የመመገብ ፍላጎት አዳብሩ

‘ወደ ጉልምስና ለመግፋት’ የምንጓጓ ከሆነ ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ ያስፈልገናል፦ ‘የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመረዳት ረገድ እድገት እያሳየሁ ነው? ሌሎች እኔን የሚመለከቱኝ በመንፈሳዊ ጎልማሳ እንደሆንኩ አድርገው ነው?’ አንዲት እናት ሕፃን ልጇን ወተትና የሕፃን ምግብ ስትመግበው ደስ ይላታል። ነገር ግን ዓመታት እያለፉ ቢሄዱም ልጁ ጠንካራ ምግብ መመገብ ባይጀምር ምን ያህል እንደምትጨነቅ መገመት ትችላለህ። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው ሰው እድገት በማድረግ ራሱን ወስኖ ሲጠመቅ ማየት ያስደስተናል። ይሁንና ከዚያ በኋላ መንፈሳዊ እድገት ማድረጉን ቢያቆምስ? ሁኔታው አሳዛኝ አይሆንም? (1 ቆሮ. 3:1-4) ምክንያቱም አስተማሪው ተስፋ የሚያደርገው አዲሱ ደቀ መዝሙር በተራው አስተማሪ ይሆናል ብሎ ነው።

የማስተዋል ችሎታችንን ተጠቅመን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለማድረግ ማሰላሰል የሚያስፈልግ ሲሆን ይህ ደግሞ ጥረት ይጠይቃል። (መዝ. 1:1-3) እምብዛም አእምሮን ማሠራት የማይጠይቁ እንደ ቴሌቪዥን ወይም የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ያሉ ነገሮች ትኩረታችንን በመስረቅ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዳናሰላስል እንቅፋት እንዲሆኑብን መፍቀድ አይገባንም። የማመዛዘን ችሎታችን እንዲያድግ ከተፈለገ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች የማጥናት ጉጉት እንዲኖረን ማድረግና ይህን ፍላጎታችንን ማርካት ያስፈልገናል። (ማቴ. 24:45-47) መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን አዘውትረን ከማንበብ በተጨማሪ ለቤተሰብ አምልኮና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ጥናት ለማድረግ ጊዜ መመደባችን አስፈላጊ ነው።

ሜክሲኮ ውስጥ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት የሚያገለግለው ጄሮኒሞ እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብ እትም ገና እንደደረሰው እንደሚያጠናው ተናግሯል። በተጨማሪም ከባለቤቱ ጋር ሆኖ የሚያጠናበት ጊዜ መድቧል። ጄሮኒሞ “ባለትዳሮች እንደመሆናችን መጠን መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ አንድ ላይ የማንበብ ልማድ ያለን ሲሆን በንባባችን ላይ ‘መልካሚቱ ምድር’ እንደሚለው ብሮሹር ያሉ አጋዥ ጽሑፎችን እንጠቀማለን” ብሏል። ሮናልድ የሚባል አንድ ክርስቲያን የጉባኤውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ተከትሎ ለማንበብ ምንጊዜም ጥረት ያደርጋል። በተጨማሪም በረጅም ጊዜ የሚጠናቀቁ አንድ ወይም ሁለት የጥናት ፕሮጀክቶች አሉት። ሮናልድ “እነዚህ ፕሮጀክቶች የሚቀጥለውን የጥናት ክፍለ ጊዜዬን በጉጉት እንድጠብቅ ያደርጉኛል” በማለት ተናግሯል።

እኛስ? መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና በአምላክ ቃል ላይ ለማሰላሰል በቂ ጊዜ እንመድባለን? ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማሙ ውሳኔዎችን በማድረግ ረገድ የማመዛዘን ችሎታችንን እያሠለጠንንና ተሞክሮ እያካበትን ነው? (ምሳሌ 2:1-7) ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት የማስተዋል ችሎታቸውን ያሠለጠኑ ሰዎች ያላቸው ዓይነት እውቀትና ጥበብ ያለን በመንፈሳዊ የጎለመስን ግለሰቦች መሆን ግባችን ይሁን!

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማመዛዘን ችሎታችንን “በማሠራት” እናሠለጥነዋለን