በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የታመመ የቤተሰብ አባልን ስትንከባከብ መንፈሳዊነትህን ጠብቅ

የታመመ የቤተሰብ አባልን ስትንከባከብ መንፈሳዊነትህን ጠብቅ

የታመመ የቤተሰብ አባልን ስትንከባከብ መንፈሳዊነትህን ጠብቅ

የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ኪም በአከርካሪዋ አካባቢ ዕጢ በተገኘበት ወቅት ካንሰር እንዳለባት ታወቀ። * ባለቤቷ ስቲቭ እንዲህ ብሏል፦ “ዕጢው በቀዶ ሕክምና ከወጣላት በኋላ ራዲዮቴራፒ እና ኬሞቴራፒ የተባሉትን ሕክምናዎች መከታተል ጀመረች። ሕክምናው ያስከተለባት የጎንዮሽ ጉዳት አቅም እንድታጣ አደረጋት። እንደ ልብ መንቀሳቀስ በጣም ያስቸግራት ነበር።”

ስቲቭ የሚወዳት አጋሩ አቅም ከሚያሳጣው ከዚህ በሽታ ጋር ስትታገል ሲመለከት ምን ያህል እንደሚሠቃይ መገመት አያዳግትም። ምናልባት አንተም እየተባባሰ በሚሄድ በሽታ ወይም የዕድሜ መግፋት በሚያስከትላቸው ችግሮች የሚሠቃይ የቅርብ የቤተሰብ አባል ይኖርህ ይሆናል። (መክ. 12:1-7) ከሆነ የምትወደውን የቤተሰብህን አባል ጥሩ አድርገህ ለመንከባከብ እንድትችል ራስህን በደንብ መንከባከብ እንዳለብህ ታውቃለህ። መንፈሳዊነትህ ከተዳከመ ስሜታዊም ሆነ አካላዊ ጤንነትህ እየተጎዳ የሚሄድ ሲሆን ይህ ደግሞ ለቤተሰብህ አባል የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እንድታጣ ያደርግሃል። የታመመ ወይም በዕድሜ የገፋ የቤተሰብህን አባል ከመንከባከብ ጎን ለጎን መንፈሳዊ ሚዛንህን ጠብቀህ መመላለስ የምትችለው እንዴት ነው? ሌሎች የጉባኤው አባላት እንደነዚህ ላሉ የታመሙ ሰዎች አሳቢነት ለማሳየት ምን ማድረግ ይችላሉ?

ሚዛንህን ጠብቅ—እንዴት?

የታመመ የቤተሰብህን አባል እየተንከባከብክ መንፈሳዊ ሚዛንህንና አካላዊ ጤንነትህን ጠብቀህ መመላለስ እንድትችል ራስህን ከሁኔታዎች ጋር ማስማማት እንዲሁም ጊዜህንና ጉልበትህን በጥበብ መጠቀም ያስፈልግሃል። ምሳሌ 11:2 “በትሑት ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል። እዚህ ላይ “ትሑት” የሚለው ቃል አቅምን ማወቅን ሊያመለክት ይችላል። ከአቅምህ በላይ እንዳትወጣጠር ፕሮግራምህንና ያሉብህን ኃላፊነቶች ቆም ብለህ መመርመር ያስፈልግህ ይሆናል።

ስቲቭ ያለበትን የሥራ ኃላፊነት መለስ ብሎ በመገምገም ጥበበኛና ልኩን የሚያውቅ መሆኑን አሳይቷል። ከሰብዓዊ ሥራው በተጨማሪ አየርላንድ ውስጥ በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪና የአገልግሎት የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግል ነበር። በተጨማሪም በአካባቢው ባለ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ውስጥ ይሠራ ነበር። ስቲቭ እንዲህ ብሏል፦ “ኪም ለእነዚህ ኃላፊነቶቼ ከመጠን ያለፈ ትኩረት በመስጠት እሷን ችላ እንዳልኳት ተናግራ አታውቅም። ያም ቢሆን ከአቅሜ በላይ እየሠራሁ እንደሆነ ታውቆኝ ነበር።” ስቲቭ ሁኔታውን ለማስተካከል ምን አደረገ? “ጉዳዩን በጸሎት ካሰብኩበት በኋላ አስተባባሪ ሆኜ ማገልገሌን ለማቆም ወሰንኩ። ሽማግሌ ሆኜ ማገልገሌን ብቀጥልም በጉባኤ ውስጥ ያሉኝን አንዳንድ ኃላፊነቶች ለሌሎች በማስተላለፌ ለኪም የሚያስፈልጋትን ጊዜና ትኩረት መስጠት ችያለሁ” ብሏል።

ከጊዜ በኋላ የኪም ጤንነት በመጠኑም ቢሆን መሻሻል አሳየ። ስቲቭና ኪም ሁኔታቸውን እንደገና የገመገሙ ሲሆን ስቲቭ ባለቤቱ ድጋፍ ስለምታደርግለት ቀድሞ በጉባኤ ውስጥ የነበሩትን ኃላፊነቶች መልሶ ማግኘት ችሏል። ስቲቭ “ሁለታችንም ምንም ነገር ስንሠራ በሽታው የፈጠረውን የአቅም ውስንነት ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለብን ተምረናል” ብሏል። “ይሖዋ ለሚያደርግልኝ እርዳታም ሆነ ባለቤቴ ታማሚ ብትሆንም እንኳ ምንም ሳታጉረመርም ለምትሰጠኝ ድጋፍ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”

ጄሪ የተባለውን ተጓዥ የበላይ ተመልካችና የባለቤቱን የመሪያን ሁኔታም እንመልከት። እነዚህ ባልና ሚስት በዕድሜ የገፉትን ወላጆቻቸውን ለመንከባከብ ሲሉ በግባቸው ላይ ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር። መሪያ “እኔና ባለቤቴ በሌላ አገር ሚስዮናውያን ሆነን የማገልገል ግብ ነበረን” ብላለች። “ይሁንና ጄሪ ለወላጆቹ አንድ ልጅ ሲሆን ወላጆቹ ደግሞ እንክብካቤ ያስፈልጋቸው ነበር። በመሆኑም እነሱን ለመንከባከብ ስንል በአየርላንድ ለመቆየት ወሰንን። ይህን በማድረጋችን የጄሪ አባት ሆስፒታል በቆየባቸው ጊዜያት ሁሉ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ከጎኑ መሆን ችለናል። በአሁኑ ጊዜ ከጄሪ እናት ጋር በየዕለቱ የምንገናኝ ሲሆን የምናገለግለው እሷ ከምትኖርበት አካባቢ ብዙም ሳንርቅ በመሆኑ እርዳታ በሚያስፈልጋት ጊዜ ልንደርስላት እንችላለን። የጄሪ እናት ያለችበት ጉባኤ ብዙ እርዳታና ድጋፍ ስለሚያደርግላት በወረዳ ሥራ መቀጠል ችለናል።”

ሌሎች መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ በዕድሜ የገፉ መበለቶች ምን ዓይነት ቁሳዊ ድጋፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት በተለይ ደግሞ ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ ከመሆኑም በላይ እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው።” ጳውሎስ፣ የእምነት ባልንጀሮቹ የሚያደርጉት ነገር “በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት” እንዲኖረው ከፈለጉ በዕድሜ ለገፉ ወላጆቻቸውና አያቶቻቸው አስፈላጊውን ቁሳዊ እርዳታ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስቧቸዋል። (1 ጢሞ. 5:4, 8) ሌሎች የጉባኤው አባላትም በዚህ ረገድ የሚያስፈልገውን እርዳታ መስጠት የሚችሉ ሲሆን እንዲህ እንዲያደርጉም ይጠበቅባቸዋል።

በስዊድን የሚኖሩትን ሆከን እና ኢንገር የሚባሉ በዕድሜ የገፉ ባልና ሚስት ሁኔታ እንመልከት። ሆከን እንዲህ ብለዋል፦ “ባለቤቴ ካንሰር እንዳለባት ሲታወቅ ነገሩ ዱብ ዕዳ ሆኖብን ነበር። ኢንገር ምንጊዜም ጤናማና ጠንካራ ነበረች። አሁን ግን ለሕክምና በየዕለቱ ወደ ሆስፒታል መሄድ አስፈለገን፤ በዚያ ላይ ደግሞ የምትወስዳቸው መድኃኒቶች ያስከተሉት የጎንዮሽ ጉዳት አቅም አሳጣት። በዚህ ጊዜ ኢንገር ቤት ለመዋል የተገደደች ሲሆን እኔም አጠገቧ ሆኜ እሷን መንከባከብ ነበረብኝ።” ታዲያ በዚህ ጊዜ ጉባኤያቸው ሆከንን እና ኢንገርን የረዳቸው እንዴት ነበር?

የጉባኤው ሽማግሌዎች ለእነዚህ ባልና ሚስት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በስልክ እንዲተላለፉላቸው ዝግጅት አደረጉ። ከዚህም በተጨማሪ ወንድሞችና እህቶች በአካል እየሄዱና ስልክ እየደወሉ ይጠይቋቸው ነበር። እንዲሁም ደብዳቤና ካርድ ይልኩላቸው ነበር። ሆከን እንዲህ ብለዋል፦ “ይሖዋም ሆነ ሁሉም ወንድሞቻችን እንደሚደግፉን ተሰምቶናል። እንዲህ ዓይነት ትኩረት ማግኘታችን በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነን እንድንቀጥል ረድቶናል። ደስ የሚለው ነገር ኢንገር ከበሽታዋ ስላገገመች በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንደገና መገኘት ችለናል።” የጉባኤ አባላት በመካከላቸው ያሉትን የታመሙና በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች የሚችሉትን ያህል የሚረዱ ከሆነ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ እንደሠሩበት ያስመሠክራሉ።—ምሳሌ 17:17

ይሖዋ ጥረታችሁን ያደንቃል

ለታመመ የቤተሰብ አባል እንክብካቤ ማድረግ አድካሚ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ሆኖም ንጉሥ ዳዊት “ለተቸገረ ሰው አሳቢነት የሚያሳይ ደስተኛ ነው፤ በመከራ ቀን ይሖዋ ያድነዋል” ሲል ጽፏል።—መዝ. 41:1 NW

የታመሙ ወይም የተቸገሩ ሰዎችን የሚንከባከቡ ደስተኞች ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? ምሳሌ 19:17 “ለድኻ [“ለችግረኛው ሰው፣” NW] የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ ስላደረገውም ተግባር ዋጋ ይከፍለዋል” ይላል። እውነተኛው አምላክ በሕመም ለሚሠቃዩ ታማኝ አገልጋዮቹ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን ለእነሱ ለሚራራ ሰውም በረከት ያፈስለታል። መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ላለው ሰው ይሖዋ ምን እንደሚያደርግለት ሲገልጽ “ታሞ ባለበት ዐልጋ ላይ እግዚአብሔር ይንከባከበዋል፤ በበሽታውም ጊዜ መኝታውን ያነጥፍለታል” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 41:3) በፍቅር ተነሳስቶ ሌሎችን የሚንከባከበው ሰው አንድ ቀን ችግር ወይም መከራ ቢደርስበት ይሖዋ እንደሚረዳው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ይሖዋ አምላክ፣ የታመመ የቤተሰባችንን አባል ለመንከባከብ የምናደርገውን ጥረት እንደሚያስተውልና ጥረታችንን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ማወቃችን እንዴት የሚያስደስት ነው! እንዲህ ያለ እርዳታ ማድረግ ጥረት የሚጠይቅብን ቢሆንም ቅዱሳን መጻሕፍት “አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጡናል።—ዕብ. 13:16

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሚዛናችሁን ጠብቁ እንዲሁም ሌሎች የሚያደርጉላችሁን እርዳታ ተቀበሉ