በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥንት ክርስቲያኖች እና የሮም አማልክት

የጥንት ክርስቲያኖች እና የሮም አማልክት

የጥንት ክርስቲያኖች እና የሮም አማልክት

የቢቲኒያ አገረ ገዥ የነበረው ታናሹ ፕሊኒ፣ የሮም ንጉሠ ነገሥት ለነበረው ለትራጃን በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ክርስቲያን በመሆናቸው ተከሰው በፊቴ በቀረቡት ሰዎች ላይ የወሰድኩት እርምጃ ይህ ነው። ክርስቲያን መሆን አለመሆናቸውን እጠይቃቸዋለሁ፤ ክርስቲያን እንደሆኑ ከተናገሩ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በማስፈራራት ለሁለተኛና ለሦስተኛ ጊዜ ደግሜ እጠይቃቸዋለሁ። አሁንም አቋማቸውን ካልለወጡ እንዲገደሉ ትእዛዝ አስተላልፋለሁ።” ክርስቶስን በመርገም እንዲሁም የንጉሠ ነገሥቱን ምስልና ፕሊኒ ወደ ሸንጎው ያመጣቸውን የአማልክት ምስሎች በማምለክ የክርስትናን እምነት የካዱትን በተመለከተ ግን ፕሊኒ “እነሱን በነፃ መልቀቁን ተገቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ሲል ጽፏል።

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ንጉሠ ነገሥቱንና የአማልክትን ምስሎች ለማምለክ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ስደት ይደርስባቸው ነበር። በመላው የሮም ግዛት ውስጥ ስለነበሩት ሌሎች ሃይማኖቶችስ ምን ማለት ይቻላል? ተከታዮቻቸው የሚያመልኳቸው አማልክት የትኞቹ ነበሩ? የሮም መንግሥት ለእነዚህ አማልክት ምን አመለካከት ነበረው? ክርስቲያኖች ለሮም አማልክት መሥዋዕት ለማቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ስደት ይደርስባቸው የነበረው ለምንድን ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን በዛሬው ጊዜ ለይሖዋ ካለን ታማኝነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ሲነሱ ምን ማድረግ እንዳለብን ለማወቅ ይረዳናል።

በሮም ግዛቶች ውስጥ የነበሩ ሃይማኖቶች

በሮም ግዛቶች ውስጥ የነበሩት ሰዎች ያላቸው ቋንቋና ባሕል የተለያየ እንደሆነ ሁሉ የሚመለኩት አማልክትም የዚያኑ ያህል የተለያዩ ነበሩ። ሮማውያን፣ አይሁዳውያን የሚከተሉትን እምነት እንደ እንግዳ ነገር ቢያዩትም እውቅና እንዳገኘ ሃይማኖት (ሬሊግዮ ሊኪታ) አድርገው ይቆጥሩት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሕጋዊ ከለላ ያደርጉለት ነበር። ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ በቀን ሁለት ጊዜ ለቄሳርና ለሮም ሕዝብ ሁለት በግና አንድ በሬ መሥዋዕት ሆኖ በየዕለቱ ይቀርብ ነበር። እነዚህ መሥዋዕቶች የቀረቡት ለአንድ አምላክ ይሁን ለብዙ አማልክት ሮማውያን ግድ አልነበራቸውም፤ እነሱን የሚያሳስባቸው አይሁዳውያን ለሮም ታማኝ መሆን አለመሆናቸው ነበር። ይህን ለማሳየት አይሁዳውያን የሚያቀርቡት መሥዋዕት በቂ ነበር።

በሮም ግዛቶች ውስጥ የነበሩ ሕዝቦች በሚከተሏቸው ሃይማኖቶች ውስጥ ባዕድ አምልኮ ተስፋፍቶ ነበር። የግሪካውያን እምነቶች ሰፊ ተቀባይነት የነበራቸው ሲሆን ጥንቆላ የተለመደ ነገር ነበር። ከምሥራቅ የመጡ ሚስጥራዊ የሚባሉ ሃይማኖቶች ደግሞ ለአማኞቻቸው ያለመሞትን ባሕርይ እንደሚያላብሷቸው፣ ራእይ እንደሚገልጡላቸው እንዲሁም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በማካሄድ ወደ አማልክት እንዲቀርቡ እንደሚረዷቸው ይናገሩ ነበር። በመላው የሮም ግዛት ውስጥ እንደነዚህ ያሉት ሃይማኖቶች ተስፋፍተው ነበር። ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት በስፋት ይመለኩ ከነበሩት አማልክት መካከል ሰሬፒስና አይስስ የተባሉት የግብፃውያን ወንድና ሴት አማልክት፣ አታርጋቲስ የተባለችው የሶርያውያን እንስት የዓሣ አምላክ እንዲሁም ሚትራ የተባለው የፋርሳውያን የፀሐይ አምላክ ይገኙበታል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በባዕድ አምልኮ ተከበው እንደነበር በግልጽ ያሳያል። ለአብነት ያህል፣ ሮማዊው የቆጵሮስ አገረ ገዥ ከአንድ አይሁዳዊ ጠንቋይ ጋር ግንኙነት ነበረው። (ሥራ 13:6, 7) የልስጥራ ሰዎች ጳውሎስንና በርናባስን ሄርሜስና ዙስ ተብለው የሚጠሩት የግሪክ አማልክት እንደሆኑ ቆጥረዋቸው ነበር። (ሥራ 14:11-13) ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ሳለ የጥንቆላ ጋኔን ያደረባት አንዲት አገልጋይ አግኝቶ ነበር። (ሥራ 16:16-18) በአቴና ደግሞ ነዋሪዎቹ ‘ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ አማልክትን እንደሚፈሩ’ ማስተዋሉን ጳውሎስ ተናግሯል። በዚያው ከተማ ውስጥ “ለማይታወቅ አምላክ” የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት አንድ መሠዊያ ተመልክቶ ነበር። (ሥራ 17:22, 23) የኤፌሶን ነዋሪዎች አርጤምስ የተባለችውን እንስት አምላክ ያመልኩ ነበር። (ሥራ 19:1, 23, 24, 34) በማልታ ደሴት ላይ የሚኖሩ ሰዎች ጳውሎስ በእባብ ተነድፎ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበት ሲመለከቱ አምላክ ነው ብለውት ነበር። (ሥራ 28:3-6) እንደነዚህ ባሉት ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ንጹሑን አምልኳቸውን ሊበክሉ ከሚችሉ ተጽዕኖዎች ራሳቸውን መጠበቅ ነበረባቸው።

የሮማውያን ሃይማኖት

ሮማውያን ግዛታቸውን እያስፋፉ በሚሄዱበት ጊዜ በወረራ የያዟቸውን አገሮች አማልክት በሌላ መልክ እንደተገለጡ የራሳቸው አማልክት አድርገው ይቀበሏቸው ነበር። ሮማውያን እነዚህን ባዕድ አማልክት ከማስወገድ ይልቅ ከራሳቸው አማልክት ጋር ያመልኳቸው ነበር። በዚህም የተነሳ የሮማውያን ሃይማኖት በግዛቶቻቸው ውስጥ እንደሚኖሩት ሰዎች ባሕል ስፍር ቁጥር አልነበረውም ማለት ይቻላል። የሮም ሃይማኖቶች ሌሎች አማልክትን ማምለክን አይከለክሉም ነበር። ሕዝቡ ከራሳቸው አማልክት በተጨማሪ ሌሎች በርካታ አማልክትን ማምለክ ይችሉ ነበር።

ሮማውያን ከነበሯቸው የራሳቸው የሆኑ አማልክት መካከል ከሁሉ የላቀው ጁፒተር ሲሆን ኦፕቲመስ ማክሲመስ (ከሁሉ የበለጠውና ታላቁ ማለት ነው) ተብሎ ይጠራ ነበር። ይህ አምላክ በነፋስ፣ በዝናብ፣ በመብረቅና በነጎድጓድ ራሱን እንደሚገልጥ ይታሰብ ነበር። የጁፒተር እህትና ሚስት የሆነችው እንዲሁም ራሷን በጨረቃ እንደምትገልጥ የምትታሰበው ጁኖ ከሴቶች ሕይወት ጋር የተያያዙ ነገሮችን በሙሉ እንደምትከታተል ይነገር ነበር። የጁፒተር ልጅ የሆነችው ሚነርቫ የዕደ ጥበባት፣ የተለያዩ ሙያዎች፣ የሥነ ጥበብና የጦርነት አምላክ ነበረች።

የሮማውያን አማልክት ማለቂያ ያላቸው አይመስልም። ላርዝና ፐኔቲዝ የቤተሰብ አማልክት ነበሩ። ቨስታ ጎጆ የምታሞቅ እንስት አምላክ ነበረች። ሁለት ፊት ያለው ጄነስ የነገሮች መጀመሪያ አምላክ እንደሆነ ይታመን ነበር። እያንዳንዱ ሙያ የራሱ የሆነ አምላክ አለው። ሮማውያን ሌላው ቀርቶ የጽንሰ ሐሳብ አማልክት እንዳሉ ያምኑ ነበር። ፓክስ የሰላም፣ ሳሉስ የጤንነት፣ ፑዲኪትያ የትሕትናና የሥነ ምግባር ንጽሕና፣ ፊዴስ የታማኝነት፣ ቪርቱስ የድፍረት እንዲሁም ቮሉፕታስ የደስታ አማልክት ነበሩ። ሮማውያን ማኅበራዊም ሆነ የግል ሕይወታቸው በሙሉ በአማልክቱ ፈቃድ ላይ የተመካ እንደሆነ ያስቡ ነበር። በመሆኑም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጥሩ ውጤት እንዲኖረው ሲሉ በመጸለይ፣ መሥዋዕቶችን በማቅረብና ግብዣ በማዘጋጀት ጉዳዩ የሚመለከተውን አምላክ ይለማመኑ ነበር።

ሕዝቡ የአማልክቱን ፈቃድ ለመረዳት ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ ዕጣ ፈንታቸውን ለማወቅ የሚያስችላቸውን ምልክት መፈለግ ነበር። ይህን ከሚያደርጉባቸው መንገዶች ዋነኛው፣ መሥዋዕት ሆነው የቀረቡትን እንስሳት ሆድ ዕቃ መመርመር ነው። የእንስሳቱ ሆድ ዕቃ መልክና ያለበት ሁኔታ ግለሰቡ ሊያደርግ ያሰበውን ነገር አማልክቱ እንደተቀበሉት ወይም እንዳልተቀበሉት ይጠቁማል ተብሎ ይታሰብ ነበር።

በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መገባደጃ አካባቢ ሮማውያን ከዋነኞቹ አማልክቶቻቸው አንዳንዶቹ ከግሪካውያን አማልክት ለምሳሌ ጁፒተር ከዙስ፣ ጁኖ ደግሞ ከሂራ ጋር አንድ እንደሆኑ ማመን ጀምረው ነበር። በተጨማሪም ሮማውያን ከግሪካውያን አማልክት ጋር በተያያዘ የሚነገሩትን አፈ ታሪኮች ተቀብለዋቸው ነበር። እነዚህ አፈ ታሪኮች፣ ልክ እንደ ሰዎች ድክመትና ጉድለት ያላቸውን አማልክት የሚያዋርዱ እንጂ የሚያሞግሱ አልነበሩም። ለአብነት ያህል፣ ሟች ከሆኑና ያለመሞት ባሕርይ እንደተላበሱ ከሚታሰቡ ግለሰቦች ጋር የፆታ ግንኙነት እንደሚፈጽም የሚነገርለት ዙስ፣ ሴቶችን አስገድዶ የሚደፍርና ልጆችን የሚያስነውር አምላክ እንደሆነ ተደርጎ ይገለጽ ነበር። በጥንት ዘመን በቲያትር መልክ ይታይ የነበረው አማልክቱ የሚፈጽሙት እፍረት የለሽ ድርጊት በአብዛኛው በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበረው ሲሆን ይህም ሕዝቡን ወራዳ የሆኑ ድርጊቶች ወደ መፈጸም መርቶታል።

አብዛኞቹ የተማሩ ሰዎች እነዚህን አፈ ታሪኮች ቃል በቃል የተቀበሏቸው አይመስልም። አንዳንዶቹ እነዚህ አፈ ታሪኮች ምሳሌያዊ ትርጉም እንዳላቸው ይናገሩ ነበር። ጳንጥዮስ ጲላጦስ “እውነት ምንድን ነው?” የሚለውን በብዙዎች ዘንድ የታወቀ ጥያቄ ያነሳው በዘመኑ እንዲህ ያለው የጥርጣሬ አመለካከት ሰፍኖ ስለነበር ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐ. 18:38) የጲላጦስ ጥያቄ “በተማሩ ሰዎች ዘንድ ተስፋፍቶ የነበረውን ‘ስለ ማንኛውም ነገር እውነቱን በእርግጠኝነት ለማወቅ የሚደረግ ጥረት ከንቱ ነው’ የሚል አመለካከት የሚያንጸባርቅ” እንደሆነ ይነገራል።

የንጉሠ ነገሥት አምልኮ

የንጉሠ ነገሥት አምልኮ የተጀመረው በአውግስጦስ (ከ27 ዓ.ዓ. እስከ 14 ዓ.ም.) የግዛት ዘመን ነበር። በተለይ በስተ ምሥራቅ በነበሩት ግሪክኛ ተናጋሪ ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ለረጅም ጊዜ ከዘለቀ ጦርነት በኋላ ብልጽግናና ሰላም እንዲሰፍን ላደረገው አውግስጦስ ከልብ የመነጨ ምስጋናቸውን ይገልጹ ነበር። ሕዝቡ ሁልጊዜም ጥበቃ ሊያደርግላቸው የሚችል የሚያዩት አካል እንዲኖር ይፈልጉ ነበር። ሃይማኖታዊ ልዩነቶችን የሚያስወግድ፣ ሕዝቡ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲያድርበት የሚያደርግና “በአዳኙ” አማካኝነት ዓለም አንድነት እንዲኖረው የሚያደርግ አገዛዝ ለማግኘት ይመኙ ነበር። በዚህም የተነሳ ንጉሠ ነገሥቱ እንደ አምላክ ይታይ ጀመር።

አውግስጦስ በሕይወት እያለ ሌሎች አምላክ ብለው እንዲጠሩት ባይፈቅድም ሮምን የምትወክለው ሮማ ዲኣ የተባለችው እንስት አምላክ እንድትመለክ ያስገድድ ነበር። አውግስጦስ ከሞተ በኋላ ግን አምላክ ተባለ። በየግዛቶቹ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ለአምልኮ ያላቸው አመለካከትና የአገር ፍቅር ስሜት የመላው ግዛት እምብርት የሆነችውን ሮምንና ገዥዎቿን ለማምለክ እንዲነሳሱ አደረጋቸው። ይህ አዲስ የተጀመረ የንጉሠ ነገሥት አምልኮ ብዙም ሳይቆይ በሁሉም ግዛቶች የተስፋፋ ሲሆን ሕዝቡ ለአገራቸው ያላቸውን አክብሮትና ታማኝነት የሚገልጹበት መንገድ ሆነ።

እንደ አምላክ እንዲመለክ ያዘዘው የመጀመሪያው የሮም ገዥ ከ81 እስከ 96 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥት የነበረው ደሚሸን ነው። በደሚሸን የግዛት ዘመን ሮማውያን፣ ክርስቲያኖች ከአይሁዳውያን የተለዩ እንደሆኑ ተገንዝበው ስለነበር አዲስ ሃይማኖት እንደሆነ አድርገው የቆጠሩትን ክርስትናን ይቃወሙት ጀመር። ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ስለ ኢየሱስ በመመሥከሩ’ በግዞት ወደ ጳጥሞስ ደሴት የተወሰደው በደሚሸን የግዛት ዘመን ሳይሆን አይቀርም።—ራእይ 1:9

ዮሐንስ የራእይ መጽሐፍን የጻፈው በግዞት በነበረበት ወቅት ነው። ዮሐንስ፣ በጴርጋሞን ስለተገደለ አንቲጳስ የተባለ ክርስቲያን በራእይ መጽሐፍ ላይ ጠቅሷል፤ ጴርጋሞን የንጉሠ ነገሥት አምልኮ ማዕከል ነበረች። (ራእይ 2:12, 13) በዚያ ወቅት ዘውዳዊው አገዛዝ፣ ክርስቲያኖች የመንግሥት ሃይማኖት የሚያከናውናቸውን የአምልኮ ሥርዓቶች እንዲከተሉ ማስገደድ ጀምሮ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ በሰፈረው ለትራጃን የተላከ ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው በ112 ዓ.ም. ፕሊኒ በቢቲኒያ የሚገኙ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን የአምልኮ ሥርዓት እንዲፈጽሙ ያስገድድ ነበር።

ፕሊኒ የቀረቡለትን ጉዳዮች የያዘበት መንገድ ትራጃንን ያስደሰተው ሲሆን የሮምን አማልክት ለማምለክ ፈቃደኛ ያልሆኑ ክርስቲያኖች እንዲገደሉም ትእዛዝ አስተላልፏል። ትራጃን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይሁንና ግለሰቡ ክርስቲያን መሆኑን ከካደና ለአማልክቶቻችን ጸሎት በማቅረብ ክርስቲያን አለመሆኑን በግልጽ ካሳየ (ከዚህ በፊት የፈጸመው ነገር ምንም ይሁን ምን) ንስሐ ገብቷልና ምሕረት ይደረግለት።”

ሮማውያን፣ ተከታዮቹ ሌሎች አማልክትን እንዳያመልኩ የሚያዝዝ ሃይማኖት ይኖራል የሚለው ሐሳብ ፈጽሞ ሊዋጥላቸው አልቻለም። የሮም አማልክት ከተከታዮቻቸው እንዲህ ዓይነት አምልኮ አይጠብቁም፤ ታዲያ የክርስቲያኖች አምላክ እንዲህ ዓይነት ትእዛዝ የሚሰጥበት ምን ምክንያት አለ? የአገሪቷን አማልክት ማምለክ የፖለቲካውን ሥርዓት ከመደገፍ የዘለለ ትርጉም እንደሌለው ይታሰብ ነበር። በመሆኑም እነዚህን አማልክት ለማምለክ እምቢተኛ መሆን አገርን እንደ መካድ ይቆጠር ነበር። ይሁንና ፕሊኒ ከጊዜ በኋላ እንደተገነዘበው አብዛኞቹን ክርስቲያኖች አማልክቱን እንዲያመልኩ ማስገደድ ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነበር። ክርስቲያኖች እንዲህ ማድረግን ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት እንደማጉደል ይቆጥሩት ነበር፤ በዚህም የተነሳ በርካታ የጥንት ክርስቲያኖች ንጉሠ ነገሥቱን በማምለክ በጣዖት አምልኮ ከመካፈል ይልቅ ሞትን መርጠዋል።

ይህ በዛሬው ጊዜ የምንኖረውን ክርስቲያኖች ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው? አንዳንድ አገሮች፣ ለብሔራዊ አርማዎች አምልኮ አከል ክብር እንዲሰጡ ዜጎቻቸውን ይጠብቁባቸዋል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የሰብዓዊ መንግሥታትን ሥልጣን እንደምናከብር ምንም ጥርጥር የለውም። (ሮም 13:1) ከብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማዎች ጋር የተያያዙ ሥርዓቶችን በተመለከተ ግን ይሖዋ አምላክ እሱን ብቻ እንድናመልከው የሰጠንን ትእዛዝ እንከተላለን፤ በተጨማሪም “ከጣዖት አምልኮ ሽሹ” እንዲሁም “ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” የሚሉትን በቃሉ ውስጥ የሰፈሩ ምክሮች ተግባራዊ እናደርጋለን። (1 ቆሮ. 10:14፤ 1 ዮሐ. 5:21፤ ናሆም 1:2 NW) ኢየሱስ “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 4:8) እንግዲያው እኛም ለምናመልከው አምላክ ያለንን ታማኝነት ጠብቀን እንመላለስ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያመልኩት ይሖዋን ብቻ ነው

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ንጉሠ ነገሥቱንም ሆነ የአማልክትን ምስሎች ለማምለክ ፈቃደኞች አልነበሩም

ንጉሠ ነገሥት ደሚሸን

ዙስ

[ምንጭ]

ንጉሠ ነገሥት ደሚሸን፦ Todd Bolen/Bible Places.com; ዙስ፦ Photograph by Todd Bolen/Bible Places.com, taken at Archaeological Museum of Istanbul

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኤፌሶን የነበሩት ክርስቲያኖች አርጤምስ የተባለችውን ታዋቂ እንስት አምላክ ለማምለክ ፈቃደኞች አልነበሩም።—ሥራ 19:23-41