በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዛ ያለው አነጋገር ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ያደርጋል

ለዛ ያለው አነጋገር ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ያደርጋል

ለዛ ያለው አነጋገር ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ያደርጋል

“ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለው . . . ይሁን።”—ቆላ. 4:6

1, 2. አንድ ወንድም ለዛ ባለው ወይም አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ መናገሩ ምን ጥሩ ውጤት አስገኝቷል?

“ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል አንድ ሰው አገኘሁ፤ ሰውየውን ሳነጋግረው በጣም ከመበሳጨቱ የተነሳ ከንፈሩና መላ ሰውነቱ ይንቀጠቀጥ ነበር” በማለት አንድ ወንድም ይናገራል። “ጥቅሶች እያወጣሁ በተረጋጋ መንፈስ ላስረዳው ብሞክርም ይባስ እየተቆጣ ሄደ። ሚስቱና ልጆቹም ከእሱ ጋር በማበር ሰደቡኝ፤ በዚህ ጊዜ ትቻቸው ብሄድ የተሻለ እንደሚሆን ተሰማኝ። የመጣሁት ሰላማቸውን ለማደፍረስ እንዳልሆነና በሰላም ለመለያየት እንደምፈልግ ነገርኳቸው። ከዚያም በ⁠ገላትያ 5:22 እና 23 ላይ የሚገኘውን ፍቅር፣ ገርነት፣ ራስን መግዛትና ሰላም የተጠቀሱበትን ጥቅስ ካሳየኋቸው በኋላ ትቻቸው ሄድኩ።”

2 “በኋላ ላይ፣ ከቤታቸው ማዶ ያሉትን ቤቶች ሳንኳኳ ሰውየውና ቤተሰቡ በረንዳቸው ላይ ቁጭ ብለው አየኋቸው። እነሱም ሲያዩኝ ጠሩኝ። ‘ደግሞ አሁን ምን ፈለጉ?’ ብዬ አሰብኩ። ሰውየው ቀዝቃዛ ውኃ ይዞ ስለነበር መጠጣት እፈልግ እንደሆነ ጠየቀኝ። መጥፎ ነገር ስለተናገረኝ ይቅርታ ከጠየቀኝ በኋላ ጠንካራ እምነት ስላለኝ እንደሚያደንቀኝ ነገረኝ። በዚህ ሁኔታ በሰላም ተለያየን።”

3. ሌሎች የሚያናድድ ነገር ቢያደርጉብንም በቁጣ መገንፈል የሌለብን ለምንድን ነው?

3 በውጥረት በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ በአገልግሎት ላይም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች ከተበሳጩ ሰዎች ጋር መገናኘታችን የማይቀር ነገር ነው። በዚህ ጊዜ ‘የገርነት መንፈስና ጥልቅ አክብሮት’ ማሳየታችን በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ጴጥ. 3:15) ከላይ የተጠቀሰው ወንድም፣ ሰውየው በቁጣና ደግነት በጎደለው መንገድ ሲናገረው እሱም ቢቆጣ ኖሮ የሰውየው አመለካከት ላይለወጥ ይችል ነበር፤ እንዲያውም የባሰ ሊበሳጭ ይችላል። ወንድም ስሜቱን ተቆጣጥሮ ለዛ ባለው መንገድ መልስ በመስጠቱ ጥሩ ውጤት ሊገኝ ችሏል።

አነጋገራችን ለዛ ያለው እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?

4. ለዛ ያለው አነጋገር መጠቀማችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

4 ከጉባኤ ውጪም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ካሉት ሰዎች ሌላው ቀርቶ ከቤተሰባችን አባላት ጋር ባለን ግንኙነት እንኳ “ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለው . . . ይሁን” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር መከተላችን አስፈላጊ ነው። (ቆላ. 4:6) እንዲህ ዓይነቱ አግባብ ያለውና ለዛውን የጠበቀ አነጋገር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግና ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር ወሳኝ ነው።

5. ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ሲባል ምን ማለት አይደለም? አብራራ።

5 ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ሲባል ያሰብከውንና የሚሰማህን ሁሉ በማንኛውም ሰዓት በተለይ ደግሞ ተበሳጭተህ ባለህበት ጊዜ መናገር ማለት አይደለም። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚገልጹት በቁጣ ገንፍሎ መናገር የድክመት እንጂ የጥንካሬ ምልክት አይደለም። (ምሳሌ 25:28ን እና ምሳ 29:11⁠ን አንብብ።) በወቅቱ በምድር ላይ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ “እጅግ ትሑት” የነበረው ሙሴ ዓመፀኛ በሆነው የእስራኤል ብሔር በጣም ተበሳጭቶ በቁጣ የገነፈለበትና ለአምላክ ክብር ሳይሰጥ የቀረበት ጊዜ ነበር። በዚያ ወቅት ሙሴ የተሰማውን ሁሉ አውጥቶ ተናግሮ ነበር፤ ሆኖም እንዲህ በማድረጉ ይሖዋ አልተደሰተም። በዚህ የተነሳ፣ ሙሴ እስራኤላውያንን ለ40 ዓመታት ሲመራቸው የቆየ ቢሆንም ብሔሩን ወደ ተስፋይቱ ምድር ይዞ የመግባት መብቱን አጣ።—ዘኍ. 12:3፤ 20:10, 12፤ መዝ. 106:32

6. በንግግራችን ጠንቃቃ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

6 ቅዱሳን መጻሕፍት አንደበታችንን መግታትንና ጠቢብ ወይም ጠንቃቃ መሆንን ያበረታታሉ። “ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤ አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው።” (ምሳሌ 10:19፤ 17:27) ይሁንና በንግግራችን ጠቢብ ወይም ጠንቃቃ መሆን ሲባል ጨርሶ ሐሳባችንን መግለጽ የለብንም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘ለዛ ባለው’ መንገድ ማለትም ሌሎችን በሚጎዳ ሳይሆን ፈውስ በሚያመጣ መንገድ አንደበታችንን መጠቀም ማለት ነው።—ምሳሌ 12:18 እና ምሳ 18:21⁠ን አንብብ።

“ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው”

7. የትኞቹን ነገሮች ማስወገድ ይኖርብናል? ለምንስ?

7 በሥራ ቦታ ወይም በአገልግሎት ላይ ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ ለዛ ባለው መንገድ ሐሳባችንን መግለጽ እንዲሁም አንደበታችንን መግታት እንደሚያስፈልገን ሁሉ በጉባኤና በቤት ውስጥ ስንሆንም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። የሚያስከትለውን ጣጣ ሳናመዛዝን ቁጣችንን ያለገደብ መልቀቅ በራሳችንም ሆነ በሌሎች መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ ጤንነት ላይ ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። (ምሳሌ 18:6, 7) ያለፍጽምና ውጤት የሆኑትን መጥፎ ስሜቶች ልንቆጣጠራቸው ይገባል። ስድብ፣ ፌዝ፣ ማንጓጠጥና ቁጣ ሊወገዱ የሚገባቸው መጥፎ ነገሮች ናቸው። (ቆላ. 3:8፤ ያዕ. 1:20) እነዚህ ነገሮች ከሰዎችም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያለንን ውድ ዝምድና ሊያበላሹብን ይችላሉ። ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስተምሯል፦ “በወንድሙ ላይ ተቆጥቶ ቁጣው የማይበርድለት ሁሉ በፍርድ ቤት ይጠየቃል፤ ወንድሙንም ጸያፍ በሆነ ቃል የሚያጥላላ ሁሉ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይጠየቃል፤ ‘አንተ የማትረባ ጅል’ የሚለው ደግሞ ለእሳታማ ገሃነም ሊዳረግ ይችላል።”—ማቴ. 5:22

8. ስሜታችንን መግለጽ የሚኖርብን መቼ ነው? ይህንንስ ማድረግ የሚኖርብን በምን መንገድ ነው?

8 አንዳንድ ጉዳዮችን ግን መነጋገሩ የተሻለ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። አንድ ወንድም የተናገረው ወይም ያደረገው ነገር በጣም ከረበሸህና በዝምታ ልታልፈው እንደማትችል ከተሰማህ በልብህ ጥላቻ እንዲያቆጠቁጥ አትፍቀድ። (ምሳሌ 19:11) አንድ ሰው ካበሳጨህ መጀመሪያ ስሜትህን አረጋጋ፤ ከዚያም ጉዳዩን ለመፍታት የሚያስፈልገውን እርምጃ ውሰድ። ጳውሎስ “ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ” ሲል ጽፏል። የተፈጠረው ችግር ከአእምሮህ አልወጣ ብሎ እያስቸገረህ በመሆኑ አመቺ ጊዜ ጠብቀህ በደግነት ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት አድርግ። (ኤፌሶን 4:26, 27, 31, 32ን አንብብ።) ስለ ጉዳዩ ከወንድምህ ጋር በግልጽ ሆኖም ለዛ ባለው መንገድ ተነጋገር፤ ይህን ስታደርግ ዓላማህ እርቅ መፍጠር ሊሆን ይገባል።—ዘሌ. 19:17፤ ማቴ. 18:15

9. ሌሎችን ቀርበን ከማነጋገራችን በፊት ስሜታችንን ማረጋጋታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9 እርግጥ ነው፣ ለመነጋገር አመቺ የሆነውን ጊዜ መምረጥ ይኖርብሃል። “ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው።” (መክ. 3:1, 7) ከዚህም በተጨማሪ “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል” የሚለውን ጥቅስ አስታውስ። (ምሳሌ 15:28) ይህም ችግሩን አንስቶ ከመነጋገር በፊት ጊዜ መስጠትን ይጨምራል። አንደኛው ወገን ተቆጥቶ እያለ ለመነጋገር መሞከር ሁኔታውን ከማባባስ ውጪ የሚፈይደው ነገር አይኖርም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሳይነጋገሩ ረጅም ጊዜ መቆየትም ጥበብ አይደለም።

የደግነት ድርጊት ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ያደርጋል

10. ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ድርጊቶችን መፈጸማችን ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያሻሽለው እንዴት ነው?

10 ለዛ ያለው ወይም ደግነት የሚንጸባረቅበት ንግግርና ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለመመሥረትም ሆነ ይህን ወዳጅነት ጠብቀን ለማቆየት ይረዳል። በመሆኑም ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሻሻል የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችን የተሻለ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ከልብ ተነሳስተን ለሌሎች ደግነት የሚንጸባረቅበት ነገር ማድረጋችን ለምሳሌ እርዳታ ለመስጠት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች መፈለጋችን፣ ስጦታ መስጠታችንና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየታችን ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል። እንዲያውም እንዲህ ያለ ተግባር መፈጸማችን በአንድ ሰው ላይ ‘ፍም በመከመር’ መልካም ባሕርያቱ ጎልተው እንዲወጡ ሊያደርግ ይችላል፤ ይህም ጉዳዩን በግልጽ ተነጋግሮ መፍታት ቀላል እንዲሆን ያደርጋል።—ሮም 12:20, 21

11. ያዕቆብ ከዔሳው ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማደስ ምን አደረገ? ውጤቱስ ምን ሆነ?

11 በጥንት ዘመን የኖረው ያዕቆብ እንዲህ ማድረግ ያለውን ጥቅም ተገንዝቦ ነበር። ያዕቆብ፣ መንትያ ወንድሙ የሆነው ዔሳው በጣም ተበሳጭቶበት ስለነበር እንዳይገድለው በመፍራት ሸሽቶ ነበር። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ያዕቆብ ከሸሸበት ተመለሰ። ዔሳውም 400 ሰዎችን አስከትሎ ወንድሙን ለመገናኘት ወጣ። በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ይሖዋ እንዲረዳው ጸለየ። ከዚያም በርካታ እንስሳትን ለዔሳው ስጦታ አድርጎ ላከ። ያዕቆብ የላከው ስጦታ የታለመለትን ግብ መቷል። ወንድማማቾቹ ሲገናኙ የዔሳው አመለካከት ተለውጦ ስለነበረ ያዕቆብን ሮጦ አቀፈው።—ዘፍ. 27:41-44፤ 32:6, 11, 13-15፤ 33:4, 10

ለዛ ባለው አነጋገር ሌሎችን አበረታቱ

12. ከወንድሞቻችን ጋር ስንነጋገር ለዛ ባላቸው ቃላት መጠቀም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ክርስቲያኖች የሚያገለግሉት አምላክን እንጂ ሰዎችን አይደለም። ያም ቢሆን በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መፈለጋችን ያለ ነገር ነው። ለዛ ባለው መንገድ መናገራችን የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ሸክም ሊያቀልላቸው ይችላል። በሌላ በኩል ግን ነቃፊ ከሆንን ወንድሞቻችን ያለባቸው ሸክም ይበልጥ እንዲከብድባቸው እንዲያውም አንዳንዶች የይሖዋን ሞገስ እንዳጡ እንዲሰማቸው ልናደርግ እንችላለን። እንግዲያው “እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል ማንኛውም መልካም ቃል” በመጠቀም ሌሎችን በሚያበረታታ መንገድ እንናገር።—ኤፌ. 4:29

13. ሽማግሌዎች (ሀ) ምክር በሚሰጡበት ጊዜ፣ (ለ) ደብዳቤ በሚጻጻፉበት ጊዜ ምን ነገር በአእምሯቸው መያዝ ይኖርባቸዋል?

13 በተለይ ሽማግሌዎች መንጋውን “በገርነት” እንዲሁም በአሳቢነት መያዝ ይኖርባቸዋል። (1 ተሰ. 2:7, 8) ሽማግሌዎች ምክር መስጠት በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ዓላማቸው ይህንን “በገርነት” ማድረግ ሊሆን ይገባል፤ ሌላው ቀርቶ “ቀና አመለካከት የሌላቸውን” እንኳ ሲያነጋግሩ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ማሳየት ይኖርባቸዋል። (2 ጢሞ. 2:24, 25) ሽማግሌዎች፣ ከሌሎች የሽማግሌዎች አካላት ወይም ከቅርንጫፍ ቢሮው ጋር ደብዳቤ መጻጻፍ በሚኖርባቸው ጊዜም ሐሳባቸውን ለዛና አክብሮት ባለው መንገድ መግለጽ ይኖርባቸዋል። ከማቴዎስ 7:12 ጋር በሚስማማ መንገድ ደጎችና ዘዴኞች መሆን ይገባቸዋል።

በቤተሰብ ውስጥ ለዛ ያለው አነጋገር መጠቀም

14. ጳውሎስ ለባሎች ምን ምክር ሰጥቷል? እንዲህ ያለውስ ለምንድን ነው?

14 ብዙውን ጊዜ የምንናገራቸው ቃላት፣ በፊታችን ላይ የሚነበበው ስሜት እንዲሁም አካላዊ መግለጫዎች በሌሎች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ አይታወቀን ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ወንዶች የሚናገሩት ነገር ሴቶችን ምን ያህል እንደሚጎዳቸው ሙሉ በሙሉ አያስተውሉ ይሆናል። አንዲት እህት “ባለቤቴ በቁጣ ሲጮኽብኝ በጣም ያስፈራኛል” ብላለች። ጠንከር ያለ አነጋገር ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ የበለጠ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሲሆን ነገሩም ለረጅም ጊዜ ከአእምሯቸው ላይወጣ ይችላል። (ሉቃስ 2:19) በተለይ ደግሞ አንዲት ሴት የምትወደውና የምታከብረው ሰው በዚህ መንገድ ከተናገራት ተጽዕኖው የባሰ ይሆናል። ጳውሎስ “ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ፤ መራራ ቁጣም አትቆጧቸው” በማለት ባሎችን መክሯቸዋል።—ቆላ. 3:19

15. አንድ ባል ሚስቱን በጥንቃቄ ሊይዛት የሚገባው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

15 በትዳር ውስጥ ረጅም ዓመታት ያሳለፈ አንድ ወንድም፣ ባል ሚስቱን በጥንቃቄ ይኸውም “ተሰባሪ ዕቃ” እንደሆነች አድርጎ ሊይዛት የሚገባው ለምን እንደሆነ በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፦ “ውድ የሆነና በቀላሉ ሊሰበር የሚችል ዕቃ ቢኖራችሁ በጣም ጠበቅ አድርጋችሁ አትይዙትም፤ አለበለዚያ ዕቃው ሊሰነጠቅ ይችላል። ዕቃው ቢጠገንም እንኳ ስንጥቁ ይታይ ይሆናል። አንድ ባል ሚስቱን ጠንከር ባለ መንገድ የሚናገራት ከሆነ ስሜቷ ይጎዳል። ይህ ደግሞ በግንኙነታቸው ላይ የማይጠፋ ስንጥቅ ሊተው ይችላል።”—1 ጴጥሮስ 3:7ን አንብብ።

16. አንዲት ሚስት ቤቷን መሥራት የምትችለው እንዴት ነው?

16 ወንዶችም ቢሆኑ ሚስቶቻቸውን ጨምሮ ሌሎች በሚናገሯቸው ነገሮች ሊበረታቱ ወይም ሊጎዱ ይችላሉ። ‘ባሏ ሙሉ በሙሉ ሊተማመንባት’ የሚችል “አስተዋይ ሚስት” እሱ ለስሜቷ እንዲጠነቀቅላት እንደምትፈልግ ሁሉ እሷም ስሜቱን ላለመጉዳት ትጠነቀቃለች። (ምሳሌ 19:14፤ 31:11) በእርግጥም አንዲት ሚስት በመልካምም ይሁን በመጥፎ በቤተሰቧ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ልታሳድር ትችላለች። “ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች፤ ተላላ ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች።”—ምሳሌ 14:1

17. (ሀ) ልጆች ወላጆቻቸውን በምን መንገድ ሊያናግሯቸው ይገባል? (ለ) አዋቂዎች ልጆችን እንዴት ሊያናግሯቸው ይገባል? ለምንስ?

17 ወላጆችና ልጆችም በተመሳሳይ እርስ በርሳቸው ለዛ ባለው መንገድ ሊነጋገሩ ይገባል። (ማቴ. 15:4) ለልጆች አሳቢነት ማሳየታችን ‘እንዲበሳጩ’ ወይም ‘እንዲመረሩ’ በሚያደርግ መንገድ ከመናገር እንድንቆጠብ ይረዳናል። (ቆላ. 3:21፤ ኤፌ. 6:4) ልጆች ተግሣጽ ቢያስፈልጋቸውም እንኳ ወላጆችም ሆኑ ሽማግሌዎች በአክብሮት ሊያነጋግሯቸው ይገባል። አዋቂዎች እንዲህ ማድረጋቸው ልጆች አካሄዳቸውን ማስተካከልና ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ጠብቀው መመላለስ ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። ልጆችን በአክብሮት ማነጋገሩ ተስፋ እንደቆረጥንባቸው በሚጠቁም መንገድ ከመናገር በጣም የተሻለ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ካደረግን እነሱም በራሳቸው ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ልጆች የተሰጣቸውን ምክር በሙሉ ላያስታውሱት ይችላሉ፤ ሌሎች ሰዎች እነሱን ያናገሩበትን መንገድ ግን አይረሱትም።

ከልብ የመነጩ መልካም ቃላት መናገር

18. መጥፎ ሐሳቦችንና ስሜቶችን ከውስጣችን ነቅለን ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው?

18 ቁጣችንን መቆጣጠር ሲባል የተረጋጉ መስሎ መታየት ማለት አይደለም። ዓላማችን ቁጣችንን አምቀን መያዝ ብቻ ሊሆን አይገባም። ውስጣችን በንዴት እየበገነ ከውጪ የተረጋጋን መስለን ለመታየት መሞከር ውጥረት ውስጥ ይጨምረናል። ሁኔታው የአንድን መኪና ነዳጅ መስጫና ፍሬን በአንድ ጊዜ እንደመርገጥ ነው። እንዲህ ማድረግ መኪናው እንዲጨናነቅ የሚያደርገው ከመሆኑም ሌላ ሊጎዳው ይችላል። ስለዚህ ንዴትህን አምቀህ ይዘህ በኋላ ላይ በቁጣ ከመገንፈል ይልቅ ውስጥህ እንዲረጋጋ ማድረጉ የተሻለ ነው። በውስጥህ የሚሰማህን መጥፎ ስሜት ለማስወገድ እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ እንድትችል መንፈስ ቅዱስ አእምሮህንና ልብህን እንዲለውጠው ፍቀድ።—ሮም 12:2ን እና ኤፌሶን 4:23, 24ን አንብብ።

19. በቁጣ እንዳንገነፍል የትኞቹን እርምጃዎች መውሰዱ ሊረዳን ይችላል?

19 ቁጣህን ለመቆጣጠር የሚያስችሉህን እርምጃዎች ውሰድ። ሁኔታው እየተጋጋለ እንደሆነና ውስጥህ በንዴት እየበገነ እንደሆነ ከተሰማህ ከአካባቢው ዘወር ማለትህ ስሜትህን ለማረጋጋት ዕድል ይሰጥሃል። (ምሳሌ 17:14) የምታነጋግረው ሰው ቆጣ ቆጣ ማለት ከጀመረ በለዘበ መንገድ ለመናገር የበለጠ ጥረት አድርግ። “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቍጣን ይጭራል” የሚለውን ጥቅስ አስታውስ። (ምሳሌ 15:1) በለሰለሰ አንደበት ቢሆንም እንኳ ደግነት የጎደለውና ጎጂ የሆነ ነገር መናገር በእሳት ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ ያህል ነው። (ምሳሌ 26:21) ስለዚህ ራስህን መግዛት ፈታኝ እንዲሆንብህ የሚያደርግ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ‘ለመናገርም ሆነ ለቁጣ የዘገየህ’ ሁን። የይሖዋ መንፈስ መልካም እንጂ ክፉ ነገር ከአፍህ እንዳይወጣ እንዲረዳህ ጸልይ።—ያዕ. 1:19

ከልብ ይቅር ማለት

20, 21. ሌሎችን ይቅር እንድንል ምን ሊረዳን ይችላል? እንዲህ ማድረግ ያለብንስ ለምንድን ነው?

20 እርግጥ ነው፣ ማንኛችንም ብንሆን አንደበታችንን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አንችልም። (ያዕ. 3:2) የቤተሰባችን አባላት እንዲሁም ውድ የሆኑት መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንኳ ምንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ አንዳንድ ጊዜ ሳያስቡት ስሜታችንን የሚጎዳ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ቶሎ ቅር ከመሰኘት ይልቅ ታጋሽ በመሆን እንደዚያ የተናገሩበትን ምክንያት ለማጤን መሞከር ይኖርብናል። (መክብብ 7:8, 9ን አንብብ።) በወቅቱ ውጥረት ውስጥ ሆነው፣ ፍርሃት አድሮባቸው፣ አሟቸው ወይም እኛ ያላወቅነው አንድ ዓይነት ችግር ገጥሟቸው ይሆን?

21 በእርግጥ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች በቁጣ ለመገንፈል ሰበብ ሊሆኑ አይችሉም። ሆኖም እነዚህን ነገሮች ማወቃችን ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ተገቢ ያልሆነ ነገር የሚናገሩት ወይም የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ እንድናስተውልና እነሱን ይቅር ለማለት እንድንነሳሳ ሊረዳን ይችላል። ማንኛችንም ብንሆን ሌሎችን የሚጎዳ ነገር እንናገራለን ወይም እናደርጋለን፤ ደግሞም በእነዚህ ጊዜያት ሰዎቹ ይቅር ቢሉን ደስ ይለናል። (መክ. 7:21, 22) ኢየሱስ፣ አምላክ ይቅር እንዲለን ከፈለግን እኛ ሌሎችን ይቅር ማለት እንዳለብን ተናግሯል። (ማቴ. 6:14, 15፤ 18:21, 22, 35) በመሆኑም ሌሎችን ይቅርታ ለመጠየቅና ይቅር ለማለት ፈጣኖች በመሆን “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” የሆነው ፍቅር በቤተሰባችንም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርብናል።—ቆላ. 3:14

22. ለዛ ያለው አነጋገር ለመጠቀም ጥረት ማድረጋችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

22 ብስጩ ሰዎች የሞሉበት ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየቀረበ ሲሄድ ደስታችንን የሚሰርቁና አንድነታችንን የሚያናጉ ፈታኝ ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መሄዳቸው አይቀርም። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን አንደበታችንን ለጥፋት ሳይሆን ለመልካም እንድንጠቀምበት ይረዳናል። እንዲህ ካደረግን ከጉባኤውም ሆነ ከቤተሰባችን አባላት ጋር ይበልጥ ሰላማዊ ግንኙነት ይኖረናል፤ እንዲሁም ምሳሌነታችን ‘ደስተኛ ስለሆነው አምላካችን’ ስለ ይሖዋ ግሩም ምሥክርነት ይሰጣል።—1 ጢሞ. 1:11

ልታብራራ ትችላለህ?

• ችግሮችን አንስቶ ለመነጋገር አመቺ ጊዜ መምረጡ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• የቤተሰብ አባላት ምንጊዜም እርስ በርሳቸው ‘ለዛ ባለው’ መንገድ መነጋገር ያለባቸው ለምንድን ነው?

• ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ላለመናገር ምን እርምጃ መውሰድ እንችላለን?

• ይቅር ባዮች እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጀመሪያ ስሜታችሁን አረጋጉ፤ ከዚያም አመቺ ጊዜ ጠብቃችሁ ግለሰቡን አነጋግሩት

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ወንድ ምንጊዜም ሚስቱን ለስለስ ባለ መንገድ ሊያነጋግራት ይገባል