በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፍቅር መተሳሰርየዓመታዊ ስብሰባ ሪፖርት

በፍቅር መተሳሰርየዓመታዊ ስብሰባ ሪፖርት

በፍቅር​—መተሳሰር የዓመታዊ ስብሰባ ሪፖርት

በዩናይትድ ስቴትስ፣ በኒው ጀርሲ ግዛት ጀርሲ ሲቲ ውስጥ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የትልልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ የተገኙ ሰዎች በሙሉ በደስታ ተሞልተዋል። ጥቅምት 3, 2009 ጠዋት ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንሲልቬንያ ለ125ኛ ጊዜ ባደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከ5,000 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ ሦስት የቤቴል ቤቶችና በካናዳ ቤቴል የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞች ደግሞ ፕሮግራሙን በኦዲዮ/ቪዲዮ አማካኝነት በቀጥታ ተከታትለዋል። ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር የተሳሰሩ በአጠቃላይ 13,235 የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች ሦስት ሰዓት የፈጀውን ይህን ስብሰባ በመከታተላቸው ተደስተዋል።

ፕሮግራሙን በሊቀ መንበርነት የመራው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን ነበር። ወንድም ጃክሰን ፕሮግራሙን የከፈተው ከቤቴላውያን የተውጣጣ አንድ የመዘምራን ቡድን ከአዲሱ የመዝሙር መጽሐፋችን ላይ መዝሙር እንደሚዘምሩ በማስተዋወቅ ነበር። ቡድኑን የመራው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን ሲሆን ሙዚቃ በንጹሕ አምልኮ ውስጥ ያለውን ትልቅ ቦታ በአጭሩ አብራርቷል። በቦታው የተገኙት ተሰብሳቢዎች ሦስት አዳዲስ መዝሙሮችን እንዲዘምሩ ተጋብዘው ነበር። በመጀመሪያ የመዘምራን ቡድኑ መዝሙሮቹን ዘመረ፤ ከዚያም ቡድኑና ተሰብሳቢዎቹ በአንድነት እንዲዘምሩ ተደረገ። የመዘምራን ቡድኑ በዚህ መንገድ እንዲዘምር የተደረገው ከዚህ ልዩ ስብሰባ ጋር በተያያዘ ብቻ ነው፤ ይህ ሁኔታ በሌሎች የጉባኤ፣ የወረዳ ወይም የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በተመሳሳይ መንገድ ለመዘመር እንደ ምሳሌ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም።

ቅርንጫፍ ቢሮዎችን የተመለከቱ ሪፖርቶች

በስብሰባው ላይ የተገኙ የአምስት አገሮች የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ሪፖርት አቅርበው ነበር። ወንድም ኬነዝ ሊተል፣ በቅርቡ ካናዳ ለዩናይትድ ስቴትስና ለካናዳ የሚያስፈልጉትን አብዛኞቹን መጽሔቶች ማተም እንደምትጀምር ይህ ደግሞ በዚያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚታተሙ ጽሑፎችን ብዛት በአሥር ዕጥፍ እንደሚያሳድገው ተናገረ። ይህን ለማከናወን ሲባል አዲስ የተገዛው የማተሚያ ማሽን በሁለት ፈረቃ ይኸውም በ24 ሰዓት ውስጥ ለ16 ሰዓት እንዲሠራ ይደረጋል።

ወንድም ሬነር ቶምፕሰን በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የመንግሥቱ ሥራ እንዴት እየተከናወነ እንዳለ የተናገረ ሲሆን ወንድም አልበርት ኦሊ ደግሞ በናይጄሪያ ስላለው እንቅስቃሴ ሪፖርት አቅርቧል። ከሞዛምቢክ የመጣው ወንድም ኤሚል ክሪትሲንገር በዚያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከብዙ አሥርተ ዓመታት ስደት በኋላ በ1992 ሕጋዊ እውቅና እንዳገኙ ገልጿል። ሦስቱም አገሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአስፋፊዎች ረገድ ከፍተኛ ጭማሪ አግኝተዋል። ከአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ የመጣው ወንድም ቪቭ ሞሪትስ ደግሞ በአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር በምትገኘው በምሥራቅ ቲሞር ስለሚታየው እድገት ተናገረ።

የበላይ አካሉ የተዋቀረባቸው ኮሚቴዎች

በ1976 የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በሙሉ የበላይ አካል አባላት በሚገኙበት ስድስት ኮሚቴዎች ሥር እንዲሆን ተደረገ። ከጊዜ በኋላ የሌሎች በጎች አባላት በእነዚህ ኮሚቴዎች ውስጥ ረዳት ሆነው እንዲያገለግሉ ተሾሙ። በአሁኑ ጊዜ በእነዚህ ኮሚቴዎች ውስጥ ገብተው የሚያገለግሉት ወንድሞች ቁጥር 23 ነው። ከእነዚህ መካከል ለስድስቱ ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸው ነበር። እነዚህ ስድስት ወንድሞች፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በአጠቃላይ 341 ዓመት አገልግለዋል፤ ይህም ሲባል እያንዳንዳቸው በአማካይ 57 ዓመታት አሳልፈዋል ማለት ነው።

በ1943 ቤቴል የገባው ወንድም ዶን አዳምስ፣ የአስተባባሪዎች ኮሚቴ ከአምስቱ ኮሚቴዎች አስተባባሪዎች የተዋቀረ እንደሆነና ይህ ኮሚቴ አምስቱም ኮሚቴዎች በተቀናጀ ሁኔታ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እንደሚረዳ ገለጸ። ይህ ኮሚቴ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ድንገተኛ ሁኔታዎች፣ ስደት፣ የፍርድ ጉዳዮች፣ አደጋዎች እንዲሁም ሌሎች አጣዳፊ ነገሮች ሲያጋጥሟቸው እርዳታ መስጠት የሚቻልባቸውን መንገዶች ያመቻቻል።

ወንድም ዳን ሞልቸን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ 19,851 የቤቴል ቤተሰብ አባላትን አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ደኅንነት ስለሚከታተለው ስለ ፐርሶኔል ኮሚቴ ማብራሪያ ሰጠ። ወንድም ዴቪድ ሲንክሌር የኅትመት ኮሚቴ ለቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ግዢ የሚከታተለው እንዴት እንደሆነ ተናገረ። ቀጥሎም ወደ 60 ለሚጠጉ ዓመታት በቤቴል ያገለገለው ወንድም ሮበርት ዎለን፣ የአገልግሎት ኮሚቴ የይሖዋ ሕዝቦች በመስኩም ሆነ በጉባኤዎች ውስጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚከታተለው እንዴት እንደሆነ አብራራ። ወንድም ዊሊያም ማለንፎንት የትምህርት ኮሚቴ የአውራጃ ስብሰባዎችን ለማዘጋጀት የሚያከናውነውን ትጋት የተሞላበት ሥራ ገለጸ። በመጨረሻ ደግሞ ወንድም ጆን ዊቸክ የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ በጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡትን ትምህርቶች እንዴት በጥንቃቄ እንደሚያዘጋጅ ተናገረ። *

የ2010 የዓመት ጥቅስ በፍቅር ላይ ያተኮረ ነው

ቀጣዮቹን ሦስት ንግግሮች የሰጡት የበላይ አካል አባላት ናቸው። ወንድም ጌሪት ሎሽ ንግግሩን የጀመረው “በሌሎች መወደድ ትፈልጋላችሁ?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ነበር። ፍቅር የሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት ሲሆን ሁላችንም ፍቅር ስናገኝ ደስተኞች እንደምንሆን ገልጿል። ወደ ሕልውና የመጣነው ይሖዋ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር ተገፋፍቶ ስለፈጠረን ነው። ለሰዎች እንድንሰብክም ሆነ እንድናስተምር በዋነኝነት የሚያነሳሳን ለይሖዋ ያለን ፍቅር ነው።

በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ፍቅር የምናሳየው ለባልንጀሮቻችን ብቻ ሳይሆን ለጠላቶቻችንም ጭምር ነው። (ማቴ. 5:43-45) ተሰብሳቢዎቹ ኢየሱስ ለእኛ ሲል ያሳለፈውን መከራ እንዲያስቡ ተናጋሪው አበረታቷቸዋል፤ በእርግጥም ኢየሱስ ለእኛ ሲል ተገርፏል፣ ተሰድቧል፣ ተተፍቶበታል እንዲሁም እንግልት ደርሶበታል። ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ለሰቀሉት ወታደሮች ጸልዮላቸዋል። ታዲያ ይህ ኢየሱስን ይበልጥ እንድንወደው አያደርገንም? ከዚያም ወንድም ሎሽ ‘ፍቅር ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል። ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም’ የሚለውን በ⁠1 ቆሮንቶስ 13:7, 8 ላይ የተመሠረተውን የ2010 የዓመት ጥቅስ ተናገረ። ወደፊት የዘላለም ሕይወት ተስፋ ብቻ ሳይሆን ለዘላለም የመውደድና የመወደድ ተስፋ ጭምር አለን።

ሊያልቅ በተቃረበ ነዳጅ እየነዳችሁ ነው?

ወንድም ሳሙኤል ኸርድ ንግግሩን የጀመረው አንድ ምሳሌ በመናገር ነው። አንድ ጓደኛችሁ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ ቦታ ይዟችሁ እየሄደ ነው እንበል። አብራችሁ እየተጓዛችሁ እያለ የነዳጁን መጠን የሚያመለክተው መሣሪያ ባዶ የሚል ምልክት እያሳየ እንደሆነ አስተዋላችሁ። ከዚያም ለጓደኛችሁ መኪናዋ ነዳጅ እየጨረሰች እንደሆነ ነገራችሁት። እሱም መኪናዋ ወደ አራት ሊትር የሚሆን ነዳጅ እንደሚኖራት ገልጾ ምንም እንዳትጨነቁ ነገራችሁ። ብዙም ሳትጓዙ ግን ነዳጅ አለቀባችሁ። አጉል ቦታ ላይ ነዳጅ እንደሚያልቅባችሁ እያወቃችሁ ሊያልቅ በተቃረበ ነዳጅ መንዳታችሁ ተገቢ ነው? ነዳጅ ሞልታችሁ መጓዛችሁ የተሻለ አልነበረም? እኛም በተመሳሳይ በደረስንበት ቦታ ሁሉ “የነዳጅ ታንከራችንን” እየሞላን መጓዛችን ተገቢ ነው፤ ምሳሌያዊው ነዳጃችን ከይሖዋ የምናገኘው እውቀት ነው።

እንግዲያው በየጊዜው በቂ ነዳጅ መሙላታችን አስፈላጊ ነው። ይህን ማድረግ የምንችልባቸው አራት መንገዶች አሉ። የመጀመሪያው የግል ጥናት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ ከመጽሐፉ ጋር በደንብ መተዋወቅ እንችላለን። ቃላትን በማንበብ ብቻ ሳንወሰን ያነበብነውን ነገር መረዳት ይኖርብናል። ሁለተኛው፣ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችንን በሚገባ መጠቀም ነው። በየሳምንቱ ቆም ብለን በቂ ነዳጅ እንሞላለን? ወይስ የምንቀዳው በጣም ትንሽ ብቻ ነው? ሦስተኛው፣ ጽሑፎች በሚጠኑባቸው የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው። አራተኛው ደግሞ ጸጥታ በሰፈነበት ሁኔታ ስለ ይሖዋ መንገዶች ማሰላሰል ነው። መዝሙር 143:5 “የቀድሞውን ዘመን አስታወስሁ፤ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ” ይላል።

‘ጻድቃን ደምቀው ያበራሉ’

ሦስተኛውንና ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ የተናገረውን ምሳሌ የሚያብራራውን የመጨረሻውን ንግግር ያቀረበው ወንድም ጆን ባር ነው። (ማቴ. 13:24-30, 38, 43) ይህ ምሳሌ “የመንግሥቱ ልጆች” ስለሚሰበሰቡበትና እንክርዳዶቹ ተለይተው ስለሚቃጠሉበት ‘የመከር’ ጊዜ የሚናገር ነው።

ወንድም ባር ይህ የመሰብሰቡ ሥራ ለዘላለም የሚቀጥል ሳይሆን የሚያበቃበት ጊዜ እንዳለ በግልጽ ተናገረ። ከዚያም “እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪከሰቱ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም” የሚለውን ማቴዎስ 24:34⁠ን ጠቀሰ። ቀጥሎም የሚከተለውን ሐሳብ ሁለት ጊዜ አነበበ፦ “ኢየሱስ በ1914 ምልክቱ መታየት ሲጀምር የተመለከቱት ቅቡዓን ሞተው ከማለቃቸው በፊት፣ እነዚህ ቅቡዓን ታላቁ መከራ ሲጀምር ከሚመለከቱት ቅቡዓን ጋር ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በተመሳሳይ ወቅት ላይ በሕይወት እንደሚኖሩ ማመልከቱ ነው።” “ይህ ትውልድ” ምን ያህል የጊዜ ርዝመት እንዳለው በትክክል ማወቅ ባንችልም በተመሳሳይ ወቅት ላይ በሕይወት የኖሩትን እነዚህን ሁለት ቡድኖች ያካትታል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ዕድሜያቸው የተለያየ ቢሆንም በዚህ ትውልድ ውስጥ የታቀፉት እነዚህ ሁለት ቡድኖች በመጨረሻ ቀኖች ውስጥ በተመሳሳይ ጊዜ በሕይወት ይኖራሉ። ምልክቱ በ1914 መታየት ሲጀምር በሕይወት ኖረው ሁኔታውን ካስተዋሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር በተመሳሳይ ወቅት ላይ የኖሩትና በዕድሜ የሚያንሱት ቅቡዓን ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ሞተው እንደማያልቁ ማወቃችን እንዴት የሚያጽናና ነው!

“የመንግሥቱ ልጆች” በሰማይ የሚያገኙትን ሽልማት በጉጉት እየተጠባበቁ ነው፤ ሆኖም ሁላችንም ታማኞች ሆነን ብርሃናችንን እስከ መጨረሻው ድረስ በድምቀት ማብራት አለብን። በዘመናችን ‘ስንዴው’ ሲሰበሰብ ለማየት መብቃታችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

የመደምደሚያ መዝሙር ከተዘመረ በኋላ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ቴዎዶር ጃራዝ የመዝጊያውን ጸሎት አቀረበ። በእርግጥም፣ ዓመታዊው ስብሰባ በጣም የሚያንጽ ነበር!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 ስድስቱም የበላይ አካል ኮሚቴዎች ስለሚያከናውኑት ሥራ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የግንቦት 15, 2008 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 29⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለሽማግሌዎች የተዘጋጀ ትምህርት ቤት

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም አንቶኒ ሞሪስ በዚህ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ለጉባኤ ሽማግሌዎች ቀጣይነት ያለው ሥልጠና እንደሚሰጥ የሚገልጽ ማስታወቂያ ተናገረ። በዩናይትድ ስቴትስ ይህ ትምህርት ቤት መሰጠት የጀመረው በ2008 መጀመሪያ አካባቢ ሲሆን ሥልጠናው የተሰጠው ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የትምህርት ማዕከል ነበር። በቅርቡ 72ኛው ክፍል የተጠናቀቀ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ በዚህ ትምህርት ቤት 6,720 ሽማግሌዎች ሠልጥነዋል። ወደፊትም ገና ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ86,000 በላይ ሽማግሌዎች አሉ። በመሆኑም የበላይ አካሉ ከታኅሣሥ 7, 2009 ጀምሮ ትምህርት ቤቱ በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክም እንዲሰጥ ወስኗል።

አራት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች አስተማሪዎች ለመሆን ለሁለት ወራት በፓተርሰን ሥልጠና ይወስዳሉ። ከዚያም እነዚህ ወንድሞች ወደ ብሩክሊን ሄደው ለሌሎች አራት ወንድሞች ሥልጠና ይሠጣሉ። እነዚህ ወንድሞች ደግሞ በብሩክሊን ትምህርት ቤቱን ይጀምራሉ፤ የመጀመሪያዎቹ አራት አስተማሪዎች በትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾችና በመንግሥት አዳራሾች በሚደረገው ትምህርት ቤት እንዲያስተምሩ ይደረጋል። እንዲህ ያለው ሥልጠና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በየሳምንቱ በስድስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት የሚሰጡ 12 አስተማሪዎች እስኪሠለጥኑ ድረስ ይቀጥላል። ከዚያ በኋላ ደግሞ በስፓንኛ የሚያስተምሩ አራት ወንድሞች ይሠለጥናሉ። ይህ ትምህርት ቤት የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤትን የሚተካ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ዓላማው ሽማግሌዎች መንፈሳዊነታቸውን እንዲያጠናክሩ መርዳት ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከ2011 የአገልግሎት ዓመት ጀምሮ ይህን ትምህርት ቤት በትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾችና በመንግሥት አዳራሾች መስጠት ይጀምራሉ።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዓመታዊው ስብሰባ የተከፈተው “ለይሖዋ ዘምሩ” ከተባለው አዲሱ የመዝሙር መጽሐፋችን ላይ በመዘመር ነው